ከይሖዋ ጋር ተቀራርባችሁ ኑሩ
“በጸሎት ጽኑ።”—ሮሜ 12:12
1. ጸሎትን በሚመለከት የይሖዋ ፈቃድ ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስስ ስለ መጸለይ ምን ማበረታቻ ሰጥቷል?
ይሖዋ ለታማኝ ሕዝቡ በሙሉ “ተስፋ የሚሰጥ አምላክ” ነው። “ጸሎት ሰሚ” በመሆኑ በፊታቸው ያስቀመጠላቸውን አስደሳች ተስፋ እንዲጨብጡ እንዲረዳቸው የሚያቀርቡትን ልመና ይሰማቸዋል። (ሮሜ 15:13፤ መዝሙር 65:2) አገልጋዮቹን ሁሉ በፈለጉበት በማናቸውም ሰዓት ወደሱ እንዲቀርቡ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል ያበረታታቸዋል። ከልብ የሚያሳስባቸውን ጉዳይ ለመስማት ምንጊዜም ዝግጁ ነው። እንዲያውም “በጸሎት እንዲጸኑና” “ያለማቋረጥ እንዲጸልዩ” ያበረታታቸዋል።a (ሮሜ 12:12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17) ይሖዋ ሁሉም ክርስቲያኖች ዘወትር በጸሎት እንዲያነጋግሩት፣ በተወዳጅ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ልባቸውን ለሱ እንዲያፈሱ ፈቃዱ ነው።—ዮሐንስ 14:6, 13, 14
2, 3. (ሀ) አምላክ “በጸሎት እንድንጸና” የሚያሳስበን ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ እንድንጸልይ እንደሚፈልግ ምን ማረጋገጫ አለን?
2 አምላክ ይህን ጥብቅ ማሳሰቢያ የሚሰጠን ለምንድን ነው? ምክንያቱም የኑሮ ጭነቶችና ኃላፊነቶች ከብደውብን መጸለይ ልንረሳ ስለምንችል ነው። ችግሮቻችን ውጠውን በተስፋችን እንዳንደሰትና መጸለይ እንድናቆም ሊያደርጉን ይችላሉ። ከነዚህ ነገሮች አንጻር እንድንጸልይና የእርዳታና የመጽናናት ምንጭ ወደሆነው ወደ አምላካችን ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ ማሳሰቢያዎች ያስፈልጉናል።
3 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 4:8) አምላክ ልዑል ቢሆንምና እኛም ፍጽምና የጐደለን ብንሆንም ለሱ የምንናገረውን ለመስማት እስከማይችል ድረስ በንቀት አይመለከተንም ወይም ራሱን ከእኛ አያርቅም። (ሥራ 17:27) በተጨማሪም ግዴለሽ ወይም ደንታቢስ አይደለም። መዝሙራዊው “የይሖዋ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና ጆሮቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል” ይላል።—መዝሙር 34:15፤ 1 ጴጥሮስ 3:12
4. የይሖዋን ጸሎት አድማጭነት እንዴት በምሳሌ ማስረዳት ይችላል?
4 ይሖዋ እንድንጸልይ ይጋብዘናል። ፀሎትን በርካታ ሰዎች አንድ ላይ ሆነው በሚያወሩበት ጊዜ ከሚኖረው ሁኔታ ጋር ልናወዳድር እንችላለን። አንተም ሌሎች ሲያወሩ ለመስማት እዚያ ቦታ ነህ እንበል። ያንተ ሥራ ግን መመልከት ወይም መታዘብ ብቻ ነው እንበል። ነገር ግን በዚህ ጊዜ አንዱ ወዳንተ ዞር ብሎ ስምህን ጠርቶ ቢያነጋግርህ ትኩረትህን በተለየ መንገድ ይስበዋል። በተመሳሳይም አምላክ ሕዝቡ በየትኛውም ስፍራ ያሉ ቢሆኑ ትኩረቱ ሁልጊዜ ወደነሱ ነው። (2 ዜና 16:9፤ ምሳሌ 15:3) ስለዚህ ሁልጊዜ እየተከላከለልንና እየጠበቀን ቃሎቻችንን በትኩረት ያዳምጣል። ይሁን እንጂ በጸሎት የአምላክን ስም በምንጠራበት ጊዜ ትኩረቱ ሙሉ በሙሉ ይሳብና እኛን ብቻ ልዩ በሆነ ሁኔታ ያዳምጣል። ይሖዋ ታላቅ ኃይል ስላለው ድምፅ ሳያሰማ በልቡና በአእምሮው ብቻ የሚጸልየውን ሰው ልመናዎች እንኳ ሳይቀር ማየትና መረዳት ይችላል። አምላክ በቅንነት ስሙን ወደሚጠሩና ከሱ ጋር ተቀራርበው ለመኖር ወደሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ እንደሚቀርብ አረጋግጦልናል።—መዝሙር 145:18
ከአምላክ ዓላማ ጋር የሚስማማ ምላሽ
5. (ሀ) ጸሎታችንን በሚመለከት “በጸሎት ጽኑ” የሚለው ምክር ምን ያመለክታል? (ለ) አምላክ ጸሎቶችን የሚመልሰው እንዴት ነው?
5 በጸሎት እንድንጸና የተሰጠው ምክር አንዳንዴ ይሖዋ የሚሰጠን ምላሽ ግልጽ ሆኖ እስኪታየን ድረስ ስለአንድ ጉዳይ ረዘም ላለ ጊዜ መጸለያችንን እንድንቀጥል ሊፈቅድ እንደሚችል ያመለክታል። በጣም የሚያስፈልገን ነገር ሳይፈጸምልን በመቆየቱ ምክንያት ሞገስ እንዲያሳየን ወይም ፍቅራዊ ቸርነቱን እንዲያደርግልን መለመን ሊታክተን ይችላል። ስለዚህ ይሖዋ አምላክ እንዲህ ላለው ዝንባሌ ሳንሸነፍ ዘወትር ሳናቋርጥ እንድንጸልይ ይለምነናል። ጸሎታችንን እንደሚቀበልና እኛ የመሰለንን ብቻ ሳይሆን በእርግጥ የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚያሟላልን በመተማመን ስለሚያሳስቡን ነገሮች እሱን መለመናችንን እንቀጥል። ይሖዋ አምላክ ልመናችንን ከዓላማው ጋር እንደሚያመዛዝን ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል እኛ በለመንነው ነገር ሌሎች ይነኩ ይሆናል። ጉዳዩን ብስክሌት እንዲሰጠው የሚለምን ልጅ ካለው አባት ሁኔታ ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። አባትየው ልጁ ብስክሌት ቢገዛለት ሌላው ልጁም እንዲገዛለት እንደሚፈልግ ያውቃል። አንደኛው ልጅ ብስክሌት ለመንዳት የማይችል ሕፃን ሊሆን ስለሚችል አባትየው በዚህ ወቅት ለማንኛቸውም ላለመግዛት ሊወስን ይችላል። በተመሳሳይ ሁኔታም ሰማያዊው አባታችን ከዓላማውና ነገሮችን ለመፈጸም ከሚወስነው ጊዜ አንጻር ለእኛና ለሌሎች በእርግጥ ከሁሉ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ ይወስናል።—መዝሙር 84:8, 11፤ ከዕንባቆም 2:3 ጋር አወዳድር።
6. ጸሎትን በሚመለከት ኢየሱስ ምን ምሳሌ ሰጥቷል? በጸሎት መጽናትስ ምን ያሳያል?
6 እዚህ ላይ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንደሚገባቸው የሚያሳይ ምሳሌ” የሰጣቸው መሆኑ ሊታወስ ይገባል። አንዲት ፍትሕ ያጣች መበለት በመጨረሻ ፍትሕ እስኪበየንላት ድረስ አንድን ሰብአዊ ዳኛ በመለመን መወትወቷን ቀጥላ ነበር። ኢየሱስ ጨምሮ “እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን?” ብሏል። (ሉቃስ 18:1-7) በጸሎት መጽናት እምነታችንን፣ በይሖዋ ላይ መመካታችንን፣ ከሱ ጋር ተቀራርበን ለመኖርና ውጤቱን በሱ እጅ በመተው ለመለመን ፈቃደኛ መሆናችንን ያሳያል።—ዕብራውያን 11:6
ከይሖዋ ጋር ተቀራርበው የኖሩ ሰዎች ምሳሌዎች
7. ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን በመኖር ረገድ የአቤልን እምነት ልንመስል የምንችለው እንዴት ነው?
7 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮች ስላቀረቡአቸው ፀሎቶች የሚገልፁ ብዙ ታሪኮች አሉት። እነዚህ ታሪኮች “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ ለትምህርታችን ተጽፈዋል።” (ሮሜ 15:4) ከይሖዋ ጋር ተቀራርበው የኖሩ ሰዎችን አንዳንድ ምሳሌዎች በመመልከት ተስፋችን ይጠናከራል። አቤል በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አቅርቧል። ያቀረበው ጸሎት ያልተመዘገበ ቢሆንም መሥዋዕቱን እንዲቀበልለት ወደ አምላክ በጸሎት ቀርቦ እንደነበረ አያጠራጥርም። ዕብራውያን 11:4 “አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ። በዚህም እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ተመሰከረለት” ይላል። በዘፍጥረት 3:15 ላይ ስላለው የአምላክ ተስፋ ያውቅ ነበር። ነገር ግን እርሱ ያውቅ የነበረው አሁን እኛ ከምናውቀው ጋር ሲወዳደር በጣም ጥቂት ነበር። ሆኖም አቤል በዚያው ባለው ዕውቀት ተጠቅሞበታል። ስለዚህ ዛሬም በአምላክ እውነት ላይ አዲስ ፍላጐት ያሳደሩ አንዳንድ ሰዎች ብዙም እውቀት ባይኖራቸው ይጸልያሉ፤ አቤል እንዳደረገውም ባላቸው እውቀት በተቻላቸው መጠን ያህል ይሠሩበታል። አዎ እምነታቸውን በሥራ ያሳያሉ።
8. አብርሃም ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ እንደኖረ እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው? ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?
8 ሌላው የአምላክ ታማኝ አገልጋይ “ለሚያምኑ ሁሉ አባት የሆነው” አብርሃም ነበር። (ሮሜ 4:11) ዛሬ ከምንጊዜውም የበለጠ ጠንካራ እምነት ያስፈልገናል፤ አብርሃም እንዳደረገውም በእምነት መጸለይ ያስፈልገናል። ዘፍጥረት 12:8 “ለይሖዋ መሠዊያን ሠራ፤ የይሖዋንም ስም ጠራ” ይላል። አብርሃም የአምላክን ስም ያውቅና በሚጸልይበትም ጊዜ በስሙ ይጠቀም ነበር። “የዘላለሙን አምላክ የይሖዋን ስም በመጥራት” ብዙ ጊዜ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ጸንቷል። (ዘፍጥረት 13:4፤ 21:33) አብርሃም ዝነኛ በሆነበት እምነቱ አምላክን ጠርቷል። (ዕብራውያን 11:17-19) አብርሃም በመንግሥቱ ተስፋ በጣም እንዲደሰት ጸሎት ረድቶታል። እኛስ የአብርሃምን በጸሎት የመጽናት ምሳሌ እየተከተልን ነውን?
9. (ሀ) የዳዊት ጸሎቶች በዛሬው ጊዜ ላሉት የአምላክ ሕዝቦች ብዙ ጥቅም ያላቸው ለምንድን ነው? (ለ) እንደ ዳዊት ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ስለመኖር ከመጸለይ ምን ይገኛል?
9 ዳዊት በጸሎት በመጽናት ረገድ የታወቀ ሰው ነበር። መዝሙሮቹም ጸሎት ምን መሆን እንዳለበት የሚያሳዩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል የአምላክ አገልጋዮች ስለ ደህንነት ወይም መዳን ስለማግኘት (መዝሙር 3:7, 8፤ 60:5) ስለ አመራር (25:4, 5) ስለ ጥበቃ (17:8) ስለ ኃጢአት ይቅርታ (25:7, 11, 18) እና ስለመሳሰሉት ሊጸልዩ ይችላሉ። ዳዊት ጭንቀት ሲሰማው “የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት” በማለት ጸልዮአል። (86:4) እኛም በተመሳሳይ ይሖዋ በተስፋችን እንድንደሰት እንደሚፈልግ በማወቅ ስለልብ ደስታ ልንጸልይ እንችላለን። ዳዊት ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ በመኖር “ነፍሴ በኋላህ ተከታተለች፤ እኔንም ቀኝህ ተቀበለችኝ” በማለት ጸልዮአል። (63:8) እኛስ ዳዊት እንዳደረገው ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን እንኖራለንን? እንዲህ ካደረግን እኛንም ይደግፈናል።
10. መዝሙራዊው አሳፍ በአንድ ወቅት ምን የተሳሳተ አስተሳሰብ ነበረው? ምንስ ሊገነዘብ ቻለ?
10 ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ከኖርን ችግር በሌለበትና በተንደላቀቀ ኑሮ በሚኖሩ ክፉዎች ከመቅናት መቆጠብ ያስፈልገናል። ክፉዎች “ሁልጊዜ ተዝናንተው ስለሚኖሩ” መዝሙራዊው አሳፍ በአንድ ወቅት ይሖዋን ማገልገል ምንም ዋጋ እንደሌለው ተሰምቶት ነበር። ሆኖም አስተሳሰቡ ስሕተት መሆኑንና ክፉዎች “በድጥ ስፍራ” እንደተቀመጡ መሆናቸውን አስተውሎ ነበር። ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ ከመኖር የሚሻል ነገር እንደሌለ ተገነዘበ። ስለዚህ ለአምላክ “እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ። ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ። . . . እነሆ ካንተ የሚርቁ ይጠፋሉና . . . ለእኔ ግን ወደ ይሖዋ መቅረብ ይሻለኛል። ሥራዎችህን ሁሉ እናገር ዘንድ መታመኛዬን በልዑል ጌታ በይሖዋ አደረግሁ” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 73:12, 13, 18, 23, 27, 28) ተስፋ የሌላቸው ክፉዎች በሚኖሩበት ከሐሳብ ነፃ የሆነ አኗኗር በመቅናት ፈንታ ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን በመኖር አሳፍን እንምሰለው።
11. ዳንኤል ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ በመኖር ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሆነው ለምንድን ነው? እንዴትስ ልንመስለው እንችላለን?
11 ዳንኤል ስለ ጸሎት የወጣውን መንግሥታዊ እገዳ ችላ በማለቱ በአንበሶች ጉድጓድ የመጣል አደጋ ቢደቀንበትም በቆራጥነት በጸሎት ጸንቷል። ነገር ግን ይሖዋም ዳንኤልን ለማስጣል “መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘግቷል።” (ዳንኤል 6:7-10, 22, 27) ዳንኤል በጸሎት በመጽናቱ እጅግ አድርጎ ተባርኳል። እኛስ በተለይ ለመንግሥቱ ስብከታችን ተቃውሞ ሲያጋጥመን በጸሎት እንጸናለንን?
ኢየሱስ ምሳሌያችን
12. (ሀ) ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ ጸሎትን በሚመለከት ምን ምሳሌ አሳይቷል? ይህስ ክርስቲያኖችን ሊጠቅማቸው የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) የኢየሱስ የናሙና ጸሎት ስለ ጸሎት ምን ይገልጻል?
12 ኢየሱስ ከምድራዊ አገልግሎቱ መጀመሪያ ጀምሮ ሲጸልይ ታይቷል። በተጠመቀበት ጊዜ የነበረው የጸሎት ዝንባሌ በዘመናችን የውኃ ጥምቀት ለሚያካሂዱት ምሳሌ ይሆናቸዋል። (ሉቃስ 3:21, 22) አንድ ሰው የውኃ ጥምቀቱ ምሳሌ የሆነለትን ተግባር ማከናወን ይችል ዘንድ አምላክ እንዲረዳው ሊጸልይ ይችላል። ኢየሱስ ሌሎችንም ወደ ይሖዋ በጸሎት እንዲቀርቡ ረድቷቸዋል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ አንድ ቦታ ላይ ሆኖ ሲጸልይ ከቆየ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “እንዴት እንደምንጸልይ አስተምረን” ብሎ ጠየቀው። በዚያ ጊዜ ኢየሱስ የቃሎቹ ቅደም ተከተል የአምላክ ስምና ፈቃድ ቅድሚያ ቦታ መያዝ እንዳለበት የሚያሳየውንና አብዛኛውን ጊዜ የናሙና ጸሎት የሚባለውን ጸሎት ነገራቸው። (ሉቃስ 11:1-4) በመሆኑም በጸሎታችን ላይ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር” ችላ ባለማለት ተገቢ አስተሳሰብ መያዝና ሚዛናችንን መጠበቅ ያስፈልገናል። (ፊልጵስዩስ 1:9, 10) እርግጥ አንድ ጉዳይ ይበልጥ የሚተኮርበት ወይም አንድ ለየት ያለ ችግር መፍትሔ ማግኘት የሚያስፈልግበት ጊዜ ይኖራል። ክርስቲያኖችም እንደ ኢየሱስ አንዳንድ የሥራ ምድቦችን ለማከናወን ወይም የተለዩ ፈተናዎችን ወይም አደጋዎችን ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ብርታት ለማግኘት ወደ አምላክ በጸሎት ይቀርቡ ይሆናል። (ማቴዎስ 26:36-44) እንዲያውም የግል ጸሎቶች የማይዳስሱት የኑሮ ክፍል አይኖርም።
13. ኢየሱስ ለሌሎች የመጸለይን አስፈላጊነት ያሳየው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ በመልካም አርዓያነቱ ስለሌሎች የመጸለይን አስፈላጊነት አሳይቷል። እሱ እንደተጠላና እንደተሰደደ ሁሉ ደቀ መዛሙርቱም እንደሚጠሉና እንደሚሰደዱ ያውቅ ነበር። (ዮሐንስ 15:18-20፤ 1 ጴጥሮስ 5:9) ስለዚህ “ከክፉው እንዲጠብቃቸው” አምላክን ለምኗል። (ዮሐንስ 17:9, 11, 15, 20) ጴጥሮስን የሚጠብቀውን ልዩ ፈተና አስቀድሞ ስላወቀም “እምነትህ እንዳይጠፋ ስላንተ አማለድሁ” ብሎታል። (ሉቃስ 22:32) እኛም የራሳችንን ችግርና ፍላጐት ብቻ የምንመለከት ሳንሆን ስለሌሎችም በማሰብ ለወንድሞቻችን ዘወትር ብንጸልይ እንዴት ጠቃሚ ይሆናል!—ፊልጵስዩስ 2:4፤ ቆላስይስ 1:9, 10
14. ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት በሙሉ ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ እንደኖረ እንዴት እናውቃለን? እኛስ እንዴት ልንመስለው እንችላለን?
14 ኢየሱስ በአገልግሎቱ በሙሉ ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ በመኖር በጸሎት ጸንቷል። (ዕብራውያን 5:7-10) ሐዋርያው ጴጥሮስ በሥራ 2:25-28 ላይ “ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና ‘ይሖዋን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት። እንዳልታወክ በቀኜ ነውና’ በማለት መዝሙር 16:8ን ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚናገር አመልክቶአል። እኛም እንዲህ ልናደርግ እንችላለን። አምላክ ወደ እኛ እንዲቀርብ ልንጸልይ እንችላለን። እኛም ይሖዋን ሁልጊዜ በሐሳባችን እፊታችን በማድረግ በሱ እንደምንታመን ልናሳይ እንችላለን። (ከመዝሙር 110:5፤ ኢሳይያስ 41:10, 13 ጋር አወዳድር) እንዲህ ስናደርግም ይሖዋ ስለሚደግፈንና ስለማንንገዳገድ ሁሉንም ዓይነት ችግሮች እናስወግዳለን።
15. (ሀ) በጸሎት ከመጽናት ወደኋላ ማለት የማይገባን በምን ረገድ ነው? (ለ) አመስጋኝነታችንን በሚመለከት ምን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል።
15 ይሖዋ ስላደረገልን ደግነቱ ሁሉ፣ አዎ፣ ለኃጢአታችን ቤዛዊ መሥዋዕት እንዲሆን ስለሰጠን ስለ ልጁን ስጦታ ጭምር “ስለሚበልጠው የእግዚአብሔር ጸጋ” ምስጋናችንን ሳንገልጽ ፈጽሞ አንቅር። (2 ቆሮንቶስ 9:14, 15፤ ማርቆስ 10:45፤ ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 8:32፤ 1 ዮሐንስ 4:9, 10) በእርግጥም “ሁልጊዜ ስለሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለሁሉ አመስግኑ።” (ኤፌሶን 5:19, 20፤ ቆላስይስ 4:2፤ 1 ተሰሎንቄ 5:18) ሐሳባችን በጎደለን ነገር ተይዞ ወይም ሐሳባችን በግል ችግሮቻችን ተጠምዶ ላለን ነገር የሚኖረንን አመስጋኝነት እንዳይነካብን ወይም እንዳያበላሽብን መጠንቀቅ አለብን።
ሸክሞቻችንን በይሖዋ ላይ መጣል
16. አንዳንድ ጭንቀቶች ሲያስቸግሩን ምን ማድረግ አለብን?
16 በጸሎት መጽናታችን ለአምላክ ያደርን መሆናችን ምን ያህል ጥልቀት እንዳለው ያሳያል። አምላክን በምናነጋግርበት ጊዜ ከሱ መልስ ከመምጣቱ በፊትም እንኳ በእኛ ላይ ጥሩ ውጤት ይኖረዋል። አንዳንድ ዓይነት ችግር አእምሮአችንን እያስጨነቀው ከሆነ “ትካዜህን በይሖዋ ላይ ጣል። እሱም ይደግፍሃል” የሚለውን ምክር በመከተል ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ለመኖር እንችላለን። (መዝሙር 55:22) ሸክማችንን ሁሉ ማለት ጭንቀታችንን፣ ትካዜያችንን፣ ቅሬታችንን ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜታችንን፣ ፍርሃታችንንና ወዘተ በአምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ በመተማመን በሱ ላይ ስንጥል የልብ መረጋጋት “አእምሮን ሁሉ የሚያልፈውን የአምላክ ሰላም” እናገኛለን።—ፊልጵስዩስ 4:4, 7፤ መዝሙር 68:19፤ ማርቆስ 11:24፤ 1 ጴጥሮስ 5:7
17. የአምላክን ሰላም እንዴት ልናገኝ እንችላለን?
17 ይህ የአምላክ ሰላም የሚመጣው ባንዳፍታ ነውን? ወዲያውኑ አንድ ዓይነት እፎይታ ብናገኝም ኢየሱስ “ሳታቋርጡ ለምኑ ይሰጣችሁማል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ ታገኙማላችሁ፤ ሳታቋርጡ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል” በማለት መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ስለ መጸለይ የተናገረው ቃል እዚህም ላይ ይሠራል። (ሉቃስ 11:9-13) የጭንቀት ስሜታችንን አሽቀንጥረን የምንጥለው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በመሆኑ በጭንቀቶቻችን ረገድ የአምላክን ሰላምና የሱን እርዳታ ለመሻት በጸሎት መጽናት ያስፈልገናል። በጸሎት በመጽናት የተፈለገውን መፍትሔ ወይም የልብ እርጋታ እንደምናገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
18. በአንዳንድ ሁኔታዎች ስለምን እንደምንጸልይ ካላወቅን ይሖዋ ምን ያደርግልናል?
18 ነገር ግን ስለ ምን ነገር እንደምንጸልይ በትክክል ባናውቅስ? ሁኔታችንን ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ባለመቻላችን ወይም ለይሖዋ ምን ልመና እንደምናቀርብ ግራ በመጋባታችን ምክንያት ውስጣዊ መቃተታችን ሳይገለጽ ይቀራል። መንፈስ ቅዱስ ስለ እኛ የሚማልድልን እንደዚህ ባለው ጊዜ ነው። ጳውሎስ “እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፤ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 8:26) እንዴት? በአምላክ ቃል ውስጥ የእኛን ሁኔታ የሚመለከቱ በመንፈስ የተጻፉ ትንቢቶችና ጸሎቶች ይገኛሉ። መንፈስ ቅዱስ እነዚህ ትንቢቶችና ጸሎቶች እንደኛ ጸሎት ሆነው እንዲቀርቡ ያደርጋል። በእኛ ሁኔታ የሚኖራቸውን ትርጉም ብናውቅ ኖሮ እነዚህን በመንፈስ የተመዘገቡ ጸሎቶች እንደምንጸልይ በመረዳት ይቀበላቸዋል። በዚሁ መሠረትም ይፈጽምልናል።
ጸሎትና ተስፋ ወደፊትም ይኖራሉ
19. ጸሎትና ተስፋ ለዘላለም የሚኖሩት እንዴት ነው?
19 ለሰማያዊው አባታችን የሚቀርቡ ጸሎቶች ለዘላለም አያቋርጡም። በተለይም ደግሞ ለአዲሲቱ ዓለምና ለበረከቶቿ የምናሰማው ምስጋና ለዘላለም አያቋርጥም። (ኢሳይያስ 65:24፤ ራእይ 21:5) ተስፋም በአንድ ዓይነት መልክ ለዘላለም መኖሩ ስለማይቀር በተስፋ መደሰታችንን እንቀጥላለን። (ከ1 ቆሮንቶስ 13:13 ጋር አወዳድር) ይሖዋ በምድር ረገድ በራሱ ላይ የወሰነው የሰንበት ዕረፍት ሲያበቃ ምን እንደሚሠራ ወይም እንደሚፈጥር ልንገምት እንኳ አንችልም። (ዘፍጥረት 2:2, 3) በማያልቀው የዘላለም ጊዜ ውስጥ ሕዝቦቹ ፈጽሞ ያልገመቱአቸውን ፍቅራዊና አስደናቂ ነገሮች ያደርግላቸዋል። መጪው ጊዜም የሱን ፈቃድ በማድረግ ረገድ አስደናቂ ነገሮችን ያመጣላቸዋል።
20. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል? ለምንስ?
20 በፊታችን እንዲህ ዓይነት የሚያስፈነድቅ ተስፋ ስላለን ሁላችንም በጸሎት በመጽናት ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን የምንኖር እንሁን። ለበረከቶቹ ሁሉ ሰማያዊ አባታችንን ማመስገናችንን ፈጽሞ አናቋርጥ። ይሖዋ “ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ የሚችል” ስለሆነ ጊዜው ሲደርስ ተስፋችን ከምንገምተው ወይም ከምንጠብቀውም እንኳ በላይ በሚያስደስት ሁኔታ ይፈጸማል። (ኤፌሶን 3:20) ስለዚህ “ጸሎት ሰሚ” ለሆነው ለይሖዋ አምላካችን ማንኛውንም ውዳሴ፣ ክብርና ምስጋና ለዘላለም የምንሰጥ እንሁን!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዌብስተር ኒው ዲክሽነሪ ኦቭ ሲኖኒምስ መሠረት “መጽናት አብዛኛውን ጊዜ ተደናቂ የሆነን ባሕርይ ያመለክታል። የጠበቁት ነገር ሳይሆን በመቅረቱ፣ በጥርጣሬና በችግሮች ተስፋ ለመቁረጥ እምቢ ማለትንና ዓላማን ወይም ውጥንን ጸንቶና ጠንክሮ መከታተልን ያመለክታል።”
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በጸሎት መጽናት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
◻ ከክርስትና ዘመን በፊት ከነበሩት የጸሎት ምሳሌዎች ምን እንማራለን?
◻ የኢየሱስ ምሳሌ ስለ ጸሎት ምን ያስተምረናል?
◻ ሸክማችንን ወይም ትካዜያችንን በይሖዋ ላይ ልንጥል የምንችለው እንዴት ነው? ከምንስ ውጤት ጋር?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወደ አንበሳ ጉድጓድ የመጣል አስፈሪ ሁኔታ ቢገጥመውም ዳንኤል በጸሎት ጸንቷል