መታሰብ የሚገባው ቀን
“በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬያችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”—ዮሐንስ 16:33
1, 2. በታሪክ ዘመናት ሁሉ ከሁሉ የሚበልጠው አንድ ቀን የትኛው ነው? ለምንስ?
በአሁኑ ጊዜ ዓለም ስለሰላም ብዙ ያወራል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ ሰላም ተገኘ ተብሎ የተወራው ቪ.ኢ ዴይ ከተባለው የአውሮፓ ድል ቀንና ቪ.ጄ ዴይa ከተባለው በጃፓን ላይ ድል ከተገኘበት ቀን በኋላ ነበር። በያመቱ በሚከበረው የገና በዓልም ላይ ሰዎች ‘ሰላም በምድር’ ስለሚሆንበት ጊዜ ያስባሉ። (ሉቃስ 2:14) ይሁን እንጂ በሰው ልጅ ታሪክ በሙሉ ከሌሎች ቀኖች ሁሉ ልዩ ሆኖ የሚታይ አንድ ቀን አለ። ይህም ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ ከላይ የተጠቀሱትን ቃላት የተናገረበት ቀን ነው። ሰው በዚህ ምድር ላይ ከኖረባቸው ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ቀናት ውስጥ ለሰው ልጅ ዘለቄታ ያለው ጥቅም ያስገኘውና የሰው ዘርን አካሄድ ፈጽሞ የለወጠው ይህ አንድ ቀን ነው።
2 ይህ ታላቅ ቀን በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት ኒሳን 14 ቀን ላይ ይውላል። በ33 እዘአ ኒሳን 14 የዋለው ሚያዚያ 1 ቀን ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነበር። በዚህ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መክፈቻ በሆነው ዕለት የተፈጸሙትን ነገሮች እንመርምር።
ኒሳን 14!
3. ኢየሱስ እነዚያን የመጨረሻ ሰዓቶች የተጠቀመባቸው እንዴት ነው?
3 ፀሐይ መጥለቅ ስትጀምር ይሖዋ ዘመናትንና ወራትን እንደሚለውጥ የምታስታውሰው ሙሉ ጨረቃ አበራች። (ሥራ 1:7) ታዲያ ኢየሱስ ከ12 ሐዋርያቱ ጋር የአይሁድን ዓመታዊ የማለፍ በዓል ለማክበር በተሰበሰበበት ፎቅ ቤት ውስጥ ምን በመከናወን ላይ ነው? ኢየሱስ ‘ከዚህ ዓለም ወደ አብ ለመሄድ ሲዘጋጅ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከመጨረሻ ወደዳቸው።’ (ዮሐንስ 13:1) ይህንን ፍቅሩን ያሳያቸው እንዴት ነው? ኢየሱስ በአንደበቱም ሆነ በምሳሌነቱ ዓለምን ለማሸነፍ የሚረዱአቸውን ባሕርያት በደቀ መዛሙርቱ ውስጥ መቅረጹን ቀጥሏል።
ትሕትናንና ፍቅርን መልበስ
4. (ሀ) ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ አንድ አስፈላጊ የሆነ ጠባይ ያሳያቸው እንዴት ነበር? (ለ) ጴጥሮስ የትሕትናን አስፈላጊነት እንደተማረ የምናውቀው እንዴት ነው?
4 ሐዋርያቱ ከሌሎች በልጦ ለመገኘት በነበራቸው ፍላጎት ምክንያት ያደረባቸውን የመቀናናትና የኩራት መንፈስ ማስወገድ ነበረባቸው። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ማበሻ ጨርቅ ታጥቆ እግራቸውን ሊያጥብ ተነሳ። ይህ የፈጸመው ድርጊት የሕዝበ ክርስትና ሊቀ ጳጳስ በየዓመቱ በሮም እንደሚያደርጉት ያለ የይስሙላ ትህትና አልነበረም። በፍጹም አልነበረም! እውነተኛ ትህትና ‘ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ከሚቆጥር’ ልብ የሚመነጭ ራስን ለሌላው አሳልፎ የመስጠት ባሕርይ ነው። (ፊልጵስዩስ 2:2-5) ጴጥሮስ በመጀመሪያ ኢየሱስ እግራቸውን ለማጠብ የተነሳበትን ምክንያት ስላልተረዳ ኢየሱስ እግሩን እንዳያጥበው እምቢ ብሎ ነበር። እርማት በተሰጠው ጊዜ ግን እግሩን ብቻ ሳይሆን ሰውነቱን በሙሉ እንዲያጥበው ጠየቀ። (ዮሐንስ 13:1-10) ይሁን እንጂ ጴጥሮስ የተፈለገውን ትምህርት አግኝቶአል። ዓመታት ካለፉ በኋላ እሱም ለሌሎች ትክክለኛውን ምክር ሲሰጥ እናገኘዋለን። (1 ጴጥሮስ 3:8, 9፤ 5:5) በዛሬው ጊዜ ሁላችንም ለክርስቶስ እንደባሮች ሆነን ማገልገላችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!—ምሳሌ 22:4፤ ማቴዎስ 23:8-12 ተመልከቱ።
5. አንድ ሌላ አስፈላጊ ጠባይ ጠቃሚ መሆኑን ያሳየው የትኛው የኢየሱስ ትዕዛዝ ነው?
5 ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የኢየሱስ ምክር ተጠቃሚ አልሆነም። እሱም የአስቆሮቱ ይሁዳ ነው። የማለፍን ራት ሲበሉ ሳሉ ኢየሱስ በመንፈሱ ታወከ። አሳልፎ የሚሰጠውም ይሁዳ እንደሆነ አውቆ አሰናበተው። ኢየሱስ ለ11 ታማኝ ደቀመዛሙርቱ “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትዕዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” በማለት የነገራቸው ከዚህ በኋላ ነበር። (ዮሐንስ 13:34, 35) ይህ በእርግጥም እጅግ ታላቅ በሆነው በኢየሱስ ምሳሌነት የተገለጸ አዲስ ትዕዛዝ ነበር! መስዋዕታዊ ሞት የሚሞትበት ሰዓት እየተቃረበ ሲሄድም ኢየሱስ የላቀ ፍቅር አሳይቷል። እያንዳንዷን ውድ ደቂቃ ደቀመዛሙርቱን ለማስተማርና ለማበረታታት ተጠቅሞባታል። በኋላም “እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት። ነፍሱን ስለወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” በማለት የፍቅርን አስፈላጊነት አጥብቆ ገልጿል።—ዮሐንስ 15:12, 13
“መንገድ፣ እውነትና ሕይወት”
6. ኢየሱስ ወዳጆቹ በሆኑት ደቀመዛሙርት ፊት ምን ግብ አስቀመጠ?
6 ኢየሱስ ለ11ዱ ታማኝ ደቀመዛሙርት “ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ። በእኔም ደግሞ እመኑ፤ በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ሥፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 14:1, 2) ይህ ሥፍራ የሚዘጋጅላቸው “በመንግሥተ ሰማያት” ነው። (ማቴዎስ 7:21) ኢየሱስ ይህ የታማኝ ደቀመዛሙርት ቡድን እንዴት ወደ ግቡ እንደሚደርስ ተናግሯል። “እኔ መንገድም እውነትም ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” አላቸው። (ዮሐንስ 14:6) ይህ ቃል በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለሚያገኙት የሰው ዘሮችም ይሠራል።—ራዕይ 7:9, 10፣ 21:1-4
7-9. ኢየሱስ ራሱን “መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ” ያለው ለምን ነበር?
7 ኢየሱስ “መንገድ” ነው። ወደአምላክ በጸሎት ለመቅረብ የሚቻልበት አንዱና ብቸኛው መንገድ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው። ኢየሱስ ራሱ አብ በኢየሱስ ስም የሚለምኑትን ማንኛውንም ነገር እንደሚሰጣቸው አረጋግጦላቸዋል። (ዮሐንስ 15:16) በሃይማኖታዊ ምስሎች አማካኝነት ወይም በ“ቅዱሳን” በኩል የሚቀርቡ ጸሎቶች ወይም “ሰላም ለኪ” እንደሚሉት ያሉ ድግምቶችና ተደጋጋሚ ጸሎቶች በአብ ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት የላቸውም። (ማቴዎስ 6:5-8) በተጨማሪም ኢየሱስን በሚመለከት በሥራ 4:12 ላይ “እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” የሚል እናነባለን።
8 ኢየሱስ “እውነት” ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ሲጽፍ “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ፀጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፣ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን” በማለት ጽፏል። (ዮሐንስ 1:14) ኢየሱስ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተነገሩትን በመቶ የሚቆጠሩ ትንቢቶቸ ስለፈጸመ እርሱ ራሱ ለእነዚህ ትንቢቶች እውነት ሆኖላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:20፤ ራዕይ 19:10) ለደቀ መዛሙርቱና ሊያዳምጡት ለመጡ ብዙ ሕዝብ በመናገር፣ ከግብዞቹ ካህናት ጋር በመከራከርና በሕያው ምሳሌነቱ እውነትን አሳውቋል።
9 ኢየሱስ “ሕይወት” ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም” ብሏል። (ዮሐንስ 3:36) በኢየሱስ መሥዋዕት ማመን ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራል። ይህም ሕይወት “ታናሽ መንጋ” ለሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ የማያልፍ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘት ሲሆን እጅግ ብዙ ሰዎች ለሆኑት “ሌሎች በጎች” ደግሞ ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ይሆናል።—ሉቃስ 12:32፤ 23:43፤ ዮሐንስ 10:16
በስደት መጽናት
10. ‘ዓለምን ለማሸነፍ’ የሚያስፈልገን ምንድነው? ኢየሱስ በዚህ ረገድ ምን ማበረታቻ ሰጥቷል?
10 በይሖዋ አዲስ ሥርዓት ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ ‘በክፉው [በሰይጣን ዲያብሎስ] የተያዘውን’ ዓለም መቋቋም አለባቸው። (1 ዮሐንስ 5:19) እንግዲያውስ በዮሐንስ 15:17-19 ላይ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት እንዴት የሚያበረታቱ ናቸው! እንዲህ አለ፦ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዛችኋለሁ። ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደጠላኝ እወቁ። ከዓለም ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለአይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል።” እውነተኛ ክርስቲያኖች እስከዚህ እስከ 1992 ዓመት ድረስ የተጠሉ ሆነዋል። ታዲያ ከኃያሉ የአምላክ እጅ ሥር ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ባገኙት ብርታት አማካኝነት ጸንተው የቆሙ ክርስቲያኖች ባሳዩት መልካም አርአያ ምንኛ እንደሰታለን! (1 ጴጥሮስ 5:6-10) ሁላችንም በሚከተሉት ልብን የሚያስደስቱ ቃላት ውይይቱን በደመደመው በኢየሱስ በማመን በፈተናዎች ልንጸና እንችላለን፦ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”—ዮሐንስ 16:33
አዲስ ቃል ኪዳን ማስተዋወቅ
11. ኤርምያስ አዲስ ቃል ኪዳንን በሚመለከት ምን ተንብዮአል?
11 በዚሁ ምሽት የማለፍ በዓል ሥርዓት እንዳበቃ ኢየሱስ ስለአዲስ ቃል ኪዳን ተናገረ። ነቢዩ ኤርምያስ በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ስለዚህ ቃልኪዳን እንደሚከተለው በማለት በትንቢት ተናግሮ ነበር፦ “እነሆ ከእሥራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፣ ይላል [ይሖዋ (አዓት)] . . . ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። . . . በደላቸውን እምራቸዋለሁና፣ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።” (ኤርምያስ 31:31-34) ይህን አዲስ ቃል ኪዳን የሚያጸናው መሥዋዕት ኒሳን 14 ቀን በ33 እዘአ መቅረብ ነበረበት!
12. ኢየሱስ አዲስ ቃል ኪዳን ያቋቋመው እንዴት ነበር? ቃል ኪዳኑስ ምን ነገር ያከናውናል?
12 ኢየሱስ ለ11ዱ ታማኞች ይህን ፋሲካ ከነርሱ ጋር ለመብላት በጣም ይመኝ እንደነበረ ነገራቸው። ከዚያም እንጀራ አንስቶ አመሰገነና ቆርሶ ከሰጣቸው በኋላ “ስለ እናንተ የሚሰጠው [ሥጋዬ ማለት ነው፤ (አዓት)] ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አላቸው። በዚሁ ዓይነት የቀዩን ወይን ጽዋ አንስቶ “ይህ ጽዋ ስለ እናነተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው” በማለት ሰጣቸው። (ሉቃስ 22:15, 19, 20) አዲሱ ቃል ኪዳን በሥራ ላይ የዋለው የእሥራኤልን የሕግ ቃል ኪዳን ለማጽናት ከተረጨው የእንስሳት ደም እጅግ የላቀ ዋጋ ባለው በኢየሱስ “ውድ ደም” አማካኝነት ነው! (1 ጴጥሮስ 1:19፤ ዕብራውያን 9:13, 14) ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን የገቡት ፍጹም የኃጢአት ይቅርታ አግኝተዋል። ስለዚህ መንፈሳውያን እሥራኤላውያን በመሆን ዘላለማዊ ውርሻ ከሚቀበሉት 144,000 መሃል ለመሆን የሚያስችላቸውን ብቃት ሊያገኙ ይችላሉ።—ገላትያ 6:16፤ ዕብራውያን 9:15-18፤ 13:20፤ ራዕይ 14:1
“ለመታሰቢያዬ”
13. (ሀ) መታሰቢያው በሚከበርበት ሰሞን ስለምን ነገር ማሰላሰል ይገባናል? (ለ) ከቂጣውና ከወይኑ መካፈል ያለባቸው እነማን ብቻ ናቸው? ለምንስ?
13 1,960ኛው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ሚያዝያ 17, 1992 ይውላል። ይህ ቀን እየቀረበ በመጣ መጠን የኢየሱስ ፍጹም መሥዋዕት የሚያከናውናቸውን ነገሮች ብናሰላስል መልካም ይሆናል። ይህ የመሥዋዕት ዝግጅት የይሖዋን ጥበብና ለሰው ልጅ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያጎላል። ኢየሱስ በሥቃይ እስከመሞት ድረስ እንኳን ፍጹም አቋሙን እንከን በሌለበት ሁኔታ ጠብቆ መገኘቱ ሰይጣን የሰው ልጅ አፈጣጠር ጉድለት እንዳለበትና ሰው ፈተና ቢደርስበት እንደሚሸነፍ በመግለጽ በይሖዋ ላይ ያስነሳው ግድድር ሐሰት መሆኑን አረጋግጦአል። (ኢዮብ 1:8-11፤ ምሳሌ 27:11) ኢየሱስ በዚህ መሥዋዕታዊ ደሙ አማካኝነት ይሖዋ “የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን” ለመምረጥ እንደመሣሪያ አድርጎ ለሚጠቀምበት አዲስ ቃል ኪዳን መካከለኛ ሆኗል። እነሱም በምድር ላይ እስካሉ ድረስ ‘ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን የጠራቸውን’ የአምላካቸውን የይሖዋን “በጎነት ይነግራሉ።” (1 ጴጥሮስ 2:9፤ ከዘጸአት 19:5, 6 ጋር አወዳድሩ) በመታሰቢያው ላይ ከሚቀርበው ቂጣና ወይን የሚካፈሉት እነርሱ ብቻ መሆናቸው ተገቢ ነው።
14. በሚልዮን የሚቆጠሩት ተመልካቾች መንፈሣዊ ብልጽግና የሚያገኙት እንዴት ነው?
14 ባለፈው ዓመት በምድር ዙሪያ በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት 10,650,158 ሰዎች ሲሆኑ ከነሱ መሃል ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን የተካፈሉት ከአንድ አሥረኛ በመቶ የሚያንሱ 8,850 ሰዎች ብቻ ነበሩ። ታዲያ ይህ በዓል በሚልዮን ለሚቆጠሩት ተመልካቾች ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል? ትልቅ ጥቅም አለው! ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን ባይካፈሉም እንኳን ይሖዋ በልጁ መሥዋዕት በኩል የሚያከናውናቸውን ታላላቅ ነገሮች ሲሰሙና ከመላው ምድር አቀፍ ወንድማማችነት ጋር ሲተባበሩ በመንፈሳዊ ይበለጽጋሉ።
15. ከኢየሱስ መሥዋዕት የሚጠቀሙት ቅቡዓን ብቻ የማይሆኑት ለምንድነው?
15 ከዚህም በላይ ሐዋርያው በ1 ዮሐንስ 2:1, 2 ላይ “ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን። እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፣ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ” በማለት ይነግረናል። አዎን የኢየሱስ መሥዋዕት በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠቅመው ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን የገቡትን የዮሐንስ ቡድን አባላት ቢሆንም “ለዓለሙ ሁሉ” ኃጢአትም ጭምር ምህረት ያስገኛል። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘትን አስደሳች ተስፋ በከፈተላቸው በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ለሚያምኑ የሰው ዘር ዓለም ክፍል ለሆኑት ሌሎች ሰዎች ሁሉ የቀረበ የኃጢአት ማስተስሪያ ነው።—ማቴዎስ 20:28
“በአባቴ መንግሥት”
16. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስና ተባባሪ ወራሾች ከምን ነገር የተካፈሉ ይመስላል? (ለ) በዛሬው ጊዜ ከቅቡዓን ቀሪዎችም ሆነ ከእጅግ ብዙ ሰዎች የሚፈለገው ምንድነው?
16 ኢየሱስ ሐዋርያቱን ማበረታታቱን በመቀጠል በአባቱ መንግሥት ከደቀመዛሙርቱ ጋር በምሳሌያዊ ሁኔታ ከወይን ፍሬ አዲሱን ስለሚጠጣበት ቀን አመልክቷል። (ማቴዎስ 26:29) “እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፣ በአሥራ ሁለቱም በእሥራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 22:28-30) ኢየሱስ በ1914 በሰማይ መንግሥታዊ ሥልጣን ስለያዘ ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ከተሰበሰቡት ተባባሪ ወራሾች አብዛኞቹ ከእሱ ጋር “በዙፋኖች ለመቀመጥ” ትንሣኤ አግኝተዋል ብለን ልንደመድም እንችላለን። (1 ተሰሎንቄ 4:15, 16) መላእክቱ የ‘ታላቁን መከራ ነፋሳት’ የሚለቁበት ቀን በፍጥነት እየቀረበ ነው! ይህ ቀ ሲደርስ 144,000ዎቹን መንፈሳዊ እሥራኤላውያን የማተምን በሚሊዮን የሚቆጠሩትን እጅግ ብዙ ሰዎች የመሰብሰብ ሥራ ይጠናቀቃል። እነዚህ ሁሉ የዘላለም ሕይወትን ሽልማት ለመቀበል ከፈለጉ ኢየሱስ እንዳደረገው ፍጹም አቋማቸውን ጠብቀው መገኘት አለባቸው።—ራዕይ 2:10፤ 7:1-4, 9
17 እና ከላይ የሚገኘው ሣጥን (ሀ) አንድ ቅቡዕ ታማኝነቱን ሳይጠብቅ ቢቀር እንዴት ያለ ክርስቲያን ቢተካ ተገቢ ይሆናል? (ለ) በ1938 የወጣ መጠበቂያ ግንብ ርዕሰ ትምህርት በምድር ላይ ስላለው ቲኦክራቲካዊው ድርጅት ግንባታና መስፋፋት ምን ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር?
17 አንዳንድ ቅቡዓን ፍጹም አቋማቸውን ጠብቀው ባይገኙስ? በዚህ የመጨረሻ ሰዓት በዚህ ዓይነት እምነት አጉዳዮች የሚሆኑ ቅቡዓን ቁጥር አነስተኛ እንደሚሆን አያጠራጥርም። በእነዚህ ሰዎች ምትክ የሚመረጡት አዲስ የተጠመቁ ክርስቲያኖች ሳይሆኑ ለብዙ ዓመታት በታማኝነት በማገልገል ከኢየሱስ ጋር በፈተና የጸኑ ክርስቲያኖች መሆን አለባቸው ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው። በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ ዓመታት በወጡት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች አማካኝነት የተገኘው ደማቅ መንፈሳዊ ብርሃን በእነዚህ ዓመታት ቅቡዓን ቀሪዎችን የማሰባሰቡ ሥራ ተጠናቋል ሊባል እንደሚችል አመልክቶ ነበር። ከዚያ ጊዜ ወዲህ “ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው የሚያነጹ” ሰዎች የሚያገኙት አስደሳች ተስፋ ከዚህ የተለየ ነው። የይሖዋ መንፈስ በክርስቶስ በኩል ገነት በምትሆነዋ ምድር ወደሚገኘው “ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭ ይመራቸዋል።”—ራዕይ 7:10, 14, 17
ሞቅ ያለ ታላቅ ጸሎት
18. በዮሐንስ ምዕራፍ 17 ላይ ካለው የኢየሱስ ጸሎት ምን ጉልህ ትምህርት እናገኛለን?
18 ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ያደረገውን ስብሰባ በዮሐንስ 17:1-26 ላይ የተመዘገበውን ልብ የሚነካ ጸሎት በማቅረብ ደምድሞአል። በመጀመሪያ የጸለየው ፍጹም አቋሙን እስከ መጨረሻው ሲጠብቅ አባቱ እንዲያከብረው ነው። በዚህ መንገድ ይሖዋም ስሙ ከማንኛውም ወቀሳ ወይም ነቀፌታ ነጽቶ ስለሚቀደስ ይከበራል። ምክንያቱም ፍጹሙ ሰው ኢየሱስ የአምላክ ሰብአዊ ፍጥረት በጣም አሰቃቂ ፈተና ቢደርስበትም እንኳን እንከን የለሽ ሊሆን እንደሚችል አሳምሮ ስላረጋገጠ ነው። (ዘዳግም 32:4, 5፤ ዕብራውያን 4:15) በተጨማሪም የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ለአዳም ዘሮች ታላቅ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሎአል። ስለ ይሖዋ አምላክና ለይሖዋ አምላክ ስም መቀደስና ለሰው ልጆች ደህንነት ሲል ሕይወቱን ስለሰጠውና የእግዚአብሔር በግ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ምንኛ አስፈላጊ ነው! (ዮሐንስ 1:29፤ 1 ጴጥሮስ 2:22-25) ይህን ከሁሉ የላቀ ፍቅራዊ መሥዋዕት ሁለንተናህን ለይሖዋና ውድ ለሆነው አገልግሎቱ እስከመወሰን ድረስ ታደንቃለህን?
19. ቀሪዎቹና እጅግ ብዙ ሰዎች ክቡር አንድነት ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው?
19 በተጨማሪም ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ የዓለም ክፍል አለመሆናቸውን በሚያረጋግጡበት፣ እውነት የሆነውን ቃሉን አጥብቀው በሚከተሉበትና ከአብና ከልጁ ጋር ያላቸውን ክቡር አንድነት በሚጠብቁበት ጊዜ ሁሉ ቅዱስ አባቱ እንዲጠብቃቸው ጸልዮአል። ታዲያ ይህ ጸሎት ቅቡአን ቀሪዎችና እጅግ ብዙ ሰዎች በፍቅር ማሰሪያ አንድ ሆነው እስከሚያገለግሉበትና ከዚህ ዓለም ጉዳዮች፣ ከአመፁና ከክፋቱ ገለልተኛ ሆነው እስከሚኖሩበት እስከዚህ ዘመን ድረስ በአስደናቂ ሁኔታ አልተፈጸመምን? ኢየሱስ ለአባቱ ለይሖዋ የተናገራቸው የመደምደሚያ ቃላት ምንኛ ውድ ናቸው? ኢየሱስ “እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፣ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ” ብሏል።—ዮሐንስ 17:14, 16, 26
20. ኒሳን 14, 33 እዘአ በእርግጥ መታወስ ያለበት ቀን የሆነው ለምንድነው?
20 ኢየሱስ ወደ ጌቴሰማኒ የአትክልት ሥፍራ ሄዶ ከደቀመዛሙርቱ ጋር አጭርና የሚያንጽ ተጨማሪ ጊዜ አሳለፈ። ከዚያም ጠላቶቹ መጡበት! በኢየሱስ ላይ የደረሰው አካላዊ ስቃይ፣ በይሖዋ ላይ በተከመረበት ነቀፋ ምክንያት የተሰማው ቅስም ሰባሪ ኀዘንና በዚህ ሁሉ ያሳየው አርአያነት ያለው ፍጹም አቋም ጠባቂነት በቃላት ሊገለጽ አይችልም። ኢየሱስ በዚያ ዕለት ማታና በተከታዩ ቀን ባለፉት ብዙ ሰዓቶች እስከመጨረሻው ጸንቷል። የእሱ መንግሥት የዚህ ዓለም ክፍል አለመሆኗን በግልጽ አስረድቷል። በመጨረሻዋ ትንፋሹም “ተፈጸመ” የሚል ድምፅ አሰምቷል። (ዮሐንስ 18:36, 37፤ 19:30) በዓለም ላይ የተቀዳጀው ድል ፍጹምና የተሟላ ነበር። በእርግጥም ኒሳን 14, 33 እዘአ መታሰብ ያለበት ቀን ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቪክትሪ ኢን ዩሮፕ እና ቪክትሪ ኦቨር ጃፓን
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ኢየሱስ ስለትሕትናና ስለፍቅር ምን አስተምሮአል?
◻ ኢየሱስ “መንገድ፣ እውነትና ሕይወት” የሆነው እንዴት ነው?
◻ የአዲሱ ቃል ኪዳን ዓላማ ምንድነው?
◻ ቅቡዓን ቀሪዎችና እጅግ ብዙ ሰዎች እንዴት ባለ አንድነትና ፍቅር ይካፈላሉ?
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሳጥን]
የታላቁ ሰሎሞን ጥበብ
ሰኔ 1 እና 15, 1938 በወጡት የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ “ድርጅት” በሚል ርዕስ የወጡት ርዕሰ ትምህርቶች የይሖዋ ምስክሮች እስካሁን ድረስ የሚከተሉትን መሠረታዊ ቲኦክራቲካዊ አደረጃጀት አስተዋውቀዋል። በ1919 የተጀመረው መሠረተ ትምህርታዊና ድርጅታዊ መስተካከል ሲደረግ የቆየበት አስደናቂ ጊዜ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። (ኢሳይያስ 60:17) መጠበቂያ ግንቡ እነዚያን 20 ዓመታት ሰሎሞን በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደሱንና የንጉሡን ቤት ከገነባበት 20 ዓመታት ጋር በማወዳደር “ቅዱሳን ጽሑፎች ሰሎሞን ከ20 ዓመት የግንባታ ፕሮግራም በኋላ . . . ብሔር አቀፍ የግንባታ ሥራ እንደያዘ ያሳያሉ። (1 ነገሥት 9:10, 17-23፤ 2 ዜና 8:1-10) ከዚያም ንግሥተ አዜብ ‘የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጣች።’ (ማቴዎስ 12:42፤ 1 ነገሥት 10:1-10፤ 2 ዜና 9:1-9, 12) ይህም በምድር ላይ ላሉት የይሖዋ ሕዝቦች መጪው ቅርብ ጊዜ ምን ይዞላቸዋል? የሚል ጥያቄ ያስነሣል። በሙሉ ትምክህት በመጠባበቅ የሚሆነውን እናያለን ብሏል።” ይህ ትምክህት ያለቦታው የተጣለ አልነበረም። በቲኦክራሲያዊው ድርጅት ሥር የተደረገ ሠፊ ምድር አቀፍ የመንፈሣዊ ግንባታ ፕሮግራም ከአራት ሚሊዮን በላይ የሆኑ የታላቅ መንጋ አባሎችን አሰባስቧል። እንደ ንግሥተ ሳባ ሁሉ እነዚህ የታላቅ መንጋ አባሎችም “በታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል የሚተላለፍላቸውን የታላቁ ሰሎሞንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጥበብ ለመስማት የመጡት ከምድር ዳር ነው።—ማቴዎስ 24:45-47