በስድስት ዓመት ዕድሜ የተተለመ ግብ መከታተል
በሳንድራ ካዋን እንደተነገረው
ብዙ ወላጆች እንደሙዚቃና ዳንስ የመሳሰሉትን ሞያዎች ለልጆቻቸው ይመርጡና ገና ከሕፃንነታቸው ጀምረው ያሠለጥኑአቸዋል። የኔ እናትም ያደረገችልኝ ይህንኑ ነው። ከሁለት ሳምንት ዕድሜዬ ጀምራ ወደሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ወደመስክ አገልግሎት ትወስደኝ ነበር።
የአራት ዓመት ልጅ በሆንሁ ጊዜ እናቴ ብቻዬን ለመስበክ እንደምችል ተሰማት። የመጀመሪያ ሙከራዬ ቁልጭ ብሎ ይታወሰኛል። ወደ አንድ ትልቅ የገበሬ ቤት በመኪናችን ሄድንና እናቴና ሌሎቹ መኪና ውስጥ ሲጠብቁ እኔ ከመኪናው ወረድኩና ወደ በሩ ሄድኩ። አንዲት ደግ ሴት አደመጠችኝና አሥር ትናንሽ መጻሕፍትን አበረከትኩላት። ለጽሑፎቹ የሰጠችኝ ዋጋ አንድ ትልቅ ሳሙና ነበር። ሣሙናው በጣም ትልቅ ስለነበር በሁለቱም እጆቼ መያዝ ነበረብኝ። በደስታ ፈነደቅሁ!
በዚያው ዓመት ማለትም በ1943 የሙሉ ጊዜ አቅኚዎችን ለሚስዮናዊነት ሥራ ለማሠልጠን የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተከፈተ። በሕይወቴ ውስጥ የሚስዮናዊነትን አገልግሎት ግብ እንዳደርግ እናቴ አበረታታችኝ። በዚያ ጊዜ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በመጧጧፍ ላይ ነበር። እናቴም በአውሮፓ ከወላጆቻቸው በኃይል ተነጥቀው ስለተወሰዱ የይሖዋ ምስክሮች ልጆች ትነግረኝ ነበር። ማንኛውንም ዓይነት ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንዲኖረኝ ትፈልግ ነበር።
በ1946 የበጋ ወራት በክሌቭላንድ ኦሃዮ በተደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ተጠመቅሁ። በዚያን ጊዜ ዕድሜዬ ገና ስድስት ዓመት ብቻ ቢሆንም ለይሖዋ ያደረግሁትን ውሳኔ ለመፈጸም ቆርጨ ነበር። በዚያው የበጋ ወራት ለመጀመሪያ ጊዜ አቅኚ ሆኜ አገለገልኩ። አንድ ቀን ጧት በሳን ዲያጎ ካሊፎርኒያ በሚገኝ አንድ መናፈሻ አደባባይ ለተቀመጡ ሰዎች አርባ መጽሔቶችን እንዳበረከትኩ ትዝ ይለኛል። የረዳኝ ትንሽና ተናጋሪ መሆኔ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ።
የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ፕሬዚዳንት የነበረው ወንድም ራዘርፎርድ በ1942 ከመሞቱ በፊት ታሞ ሳለ ክረምቱን ባሳለፈበት በቤትሳሪም አቅራቢያ ብዙ ጊዜ ሰብከናል። እዚያ ያሉ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን አዘውትረን እንጎበኝና ከእነሱም ጋር ራት እንበላ ነበር። እንደነዚህ ያሉት አስደሳች ጉብኝቶች የምፈልገው አኗኗር በእርግጥ የአቅኚነት ኑሮ እንደሆነ እንድወስን አድርገውኛል። በዚያን ጊዜም የጊልያድ ትምህርት ቤትንና የሚስዮናዊነት አገልግሎትን የሕይወቴ ግብ አደረግሁ።
በተከታዩ ዓመት ወላጆቼ ተፋቱ። የቤተሰብ ሁኔታ መለወጡ ግን መንፈሳዊነታችንን አላቀዘቀዘውም። እናቴ አቅኚ ነበረች። እኔና ወንድሜ ማግኘት ስላለብን ማሠልጠኛም አጥብቃ ታስብ ነበር። ትንሿ ተጎታች ቤታችን የክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ጉብኝት ተጓድሎባት አያውቅም ነበር። እናቴ ከጊልያድ ምሩቃን ጋር እንድንገናኝ ጥረት ታደርግ ነበር። ከእነዚህም መካከል ወደተመደቡበት ወደ ጃፓን አገር ከመሄዳቸው በፊት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ያገለግሉ የነበሩት ሎይድና መልባ ባሪ የተባሉት ሁለት የጊልያድ ምሩቃን ይገኛሉ። ሚስዮናዊ ለመሆን የምመኘውን እኔን ትንሿን ልጃገረድ ጊዜ ወስደው ያበረታቱኝ ነበር። ይህም በእርግጥ ልቤን ነክቶታል።
የአሥር ዓመት ዕድሜ ሲሞላኝ እናቴ እንደ እሷ አቅኚ የሆነ አንድ ግሩም ወንድም አገባች። ወንድሜንና እኔን በአሳዳጊነት የተቀበለን በወረቀት ብቻ ሳይሆን በልቡም ጭምር ነበር። ለይሖዋ የነበረው ፍቅርና ለአገልግሎት የነበረው ቅንዓት ወደሌላ ሰው የሚተላለፍ ዓይነት ነበር።
እናቴና አባቴ እኛን ሁለት ልጆቻቸውን በአሥራዎቹ አስቸጋሪ የወጣትነት ዕድሜያችን ለመምራት የጋራ ጥረት አድርገዋል። ቤታችን ሁልጊዜ በጥሩ ትዝታ የማስታውሰው መንፈሳዊ መጠለያ ነበር። በአነስተኛ ገቢ ሁለት ልጆች እያሳደጉ አቅኚ ሆኖ ማገልገል ቀላል አልነበረም። ራሳቸውን መስዋዕት ማድረግ ነበረባቸው። ይሁንና እናቴና አባቴ በይሖዋ የሚመኩና የመንግሥቱን ፍላጎቶች የሚያስቀድሙ ነበሩ።
በ1950 በኒውዮርክ ከተማ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስብሰባ በሚገባ አስታውሳለሁ። አባቴ ከባንክ ገንዘብ ተበደረና በወጪ የሚያግዙን ሦስት መንገደኞች ጨምረን ወደ ስብሰባው ሄድን። እናቴ፣ አባቴ፣ ወንድሜና እኔ ከሳንዲያጎ እስከ ኒውዮርክ በጋቢናው ውስጥ ስንቀመጥ ሌሎቹ በኋላው መቀመጫ ተቀመጡ። የአባቴ አሠሪ የሁለት ሳምንት ፈቃድ ለመስጠት ፈቃደኛ ስላልነበረ አባቴ በስብሰባው ላይ መገኘቱ ሥራውን አሳጣቶታል። ይሁንና አባቴ ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚሰጠን አረጋገጠልን። በእርግጥም ሰጥቶናል። አባቴ የባንኩን ብድር ለመክፈል መኪናውን ሸጠና ከዚያ በኋላ የተሻለ ሥራ አገኘ። ይህና ሌሎች ተመሳሳይ ተሞክሮዎች ከዓመታት በኋላ ባሌና እኔ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በገጠሙን ጊዜ በጣም ጠቅመውኛል።
ከኒውዮርክ ስንመለስ እግረመንገዳችንን የጊልያድን ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁበትን የመንግሥት እርሻ ጎበኘን። ከመማሪያ ክፍሎቹ በአንዱ ቆሜ ለራሴ “ገና አሥራ አንድ ዓመት እንኳን አልሞላኝም። እዚህ ለመምጣት አልደርስም። አርማጌዶን ቀድሞ ይመጣል” እንዳልኩ አስታውሳለሁ። ይሁንና ይህ ጉብኝት ጊልያድን ከበፊቱ ይበልጥ ግቤ ለማድረግ እንድቆርጥ አድርጎኛል።
ግቤ ላይ ለመድረስ ያደረግኩት ጥረት
በትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ ሁሉ ከአንደኛ ክፍል ጀምሬ በያንዳንዱ በጋ አቅኚ ሆኜ አገለግል ነበር። ከዚያም ሰኔ 1957 ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተመረቅሁ ከሁለት ሳምንት በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆንኩ።
በ1957 በሎስ አንጀለስ በተደረገው የወረዳ ስብሰባ ላይ ጊልያድ ለመግባት ፍላጎት ላላቸው የተደረገው ስብሰባ ለኔ ልዩ ትርጉም ነበረው። ለዚህ ስብሰባ ወደተወሰነው ድንኳን ስሄድ የስድስት ዓመት ዕድሜ ሳለሁ ጀምሮ የማውቀውን ቢል የሚባል ወጣት ወንድም አገኘሁት። ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተጨማሪ ሠራተኛ ያስፈልግበት ወደነበረው ወደ ሉዊዚያና ሄዶ ያገለግል ነበር። ሁለታችንም ለሚስዮናዊ አገልግሎት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለን ስናይ ተገረምን። ከስድስት ወር በኋላ ሚስዮናዊነትን የጋራ ፕሮጀክት ልናደርግ ወሰንን። የአገልግሎት ምድብ እንዲሰጠን ለማህበሩ ጻፍንና ከሠርጋችን ከአንድ ወር በፊት በዌስት ቨርጂኒያ ውስጥ በሮምኔይ ተመደብን።
በ1958 በኒውዮርክ በተደረገው ስብሰባ ከተገኘን በኋላ ወደ ተመደብንበት ሥፍራ ተዛወርን። በዚያ ስብሰባ ላይ ሳለን ጊልያድ ለመግባት ፍላጎት ላላቸው በተደረገው ስብሰባ ላይ ተገኝተን ነበር። ጊልያድ ለመግባት ፍላጎት ያላቸው ተሰብሳቢዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ነበሩ። ብዛታቸውን ስናይ ወደ ጊልያድ የመጠራት አጋጣሚያችን በጣም የመነመነ እንደሆነ ተሰምቶን ነበር። የሆነ ሆኖ ከተጋባን ገና አሥራ አንድ ሳምንት ብቻ ቢሆነንም የመጀመሪያ ማመልከቻችንን አቀረብን። በሚቀጥለው ዓመት በፊላደልፊያ በተደረገው የወረዳ ስብሰባ ላይ ሁለተኛ ማመልከቻችንን አቀረብን።
ቢልና እኔ በሮምኔይ ሳለን ባጋጠሙን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሁሉ በይሖዋ ላይ መመካትን ተማርን። ሮምኔይ 2,000 ያህል ነዋሪዎች የነበሩባት ከተማ ነበረች። ሥራ ማግኘት የማይቻል ነገር ነበር። የምንኖረው ለካሊፎርኒያ የአየር ጠባይ እንደሚስማማ ሆኖ በተሠራ 4.5 ሜትር ርዝመት ባለው እቤት በተሠራ ተጎታች ቤት ውስጥ ነበር። የቧንቧ ውሃ፣ ማሞቂያም ሆነ ማቀዝቀዣ አልነበረንም። ተጎታቹ ውስጥ በጣም ቀዝቃዛ ከመሆኑ የተነሣ ውሃው ወደ በረዶነት ይለወጥ ስለነበር ከባልዲው ውሃ ለመቅዳት መጀመሪያ በረዶውን ሰብረን ማንሣት ነበረብን። ወንድሞች ያደኑትን ምግብ ለኛ በማካፈል የተቻላቸውን ያህል ይረዱን ነበር። አጋዘን፣ ራኩን የሚባል ድመት መሳይ እንስሳና ሽኮኮ እንበላ ነበር። ከአገልግሎት ስንመለስ የምንበላው ነገር አይኖረንም ብለን ያሰብንበት ብዙ ጊዜ ነበር። እቤት ስንደርስ ግን በራፋችን ላይ ፍራፍሬ ወይም አይብ ተቀምጦ እናገኝ ነበር።
ለዘጠኝ ወር ያህል ከጊዜ ወደጊዜ እየመነመነ በሚሄድ አነስተኛ ገንዘብ እየታገልን ቆየን። በመጨረሻ ቢል ሥራ ሊያገኝ ወደሚችልበት ሜሪላንድ ውስጥ ወደሚገኘው ወደ ባልቲሞር መዛወር ጥበብ ይሆናል ብለን ወሰንን። ስለ ውሳኔያችን ለወንድሞች ስንነግራቸው አለቀሱ፤ እኛም አለቀስን። ስለዚህ ጥቂት ጊዜ ለመቆየት ወሰንን።
ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ 64 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በዌስተርንፖርት ሜሪላንድ የሚገኝ አንድ የሱፐር ማርኬት ሥራ አስኪያጅ የሆነ ምሥክር ለቢል የትርፍ ሰዓት ሥራ ሰጠው። በዚያው ወር ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን አንዱ ትልቅ የከሰል ምድጃ ያላት የምታምር ትንሽ ቤት ከነሙሉ ዕቃዋ ሰጠን። ሚልክያስ 3:10 በጣም የምወደው ጥቅስ የሆነልኝ በዚህ ጊዜ ነበር። ይሖዋ ከጠበቅነው በላይ በረከቱን አፈሰሰልን።
በመጨረሻ ጊልያድ ገባን!
በሕይወታችን አስደሳች ከነበሩት ቀናት መሃል አንዷ ጊልያድ ለመግባት የተጋበዝንባት ህዳር 1959 ነበረች። በመንግሥት እርሻው ከተሰጡት ኮርሶች የመጨረሻ በሆነው በ35ኛው ኮርስ እንድንካፈል ተጋበዝን። ሕፃን ሆኜ በጎበኘሁት በዚያው የመማሪያ ክፍል ደጅ ላይ ስቆም በቃላት ሊገለጽ የማይችል ልብን በደስታ የሚያሞቅ አስደሳች ስሜት ተሰማኝ።
ጊልያድ በበረሃ መሃል እንደሚገኝ መንፈሣዊ ገነት ነበረ። ለአምስት ወራት ያህል በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ እንደምንኖር ያህል ተሰምቶን ነበር። በሕይወታችን ውስጥ ለብዙ ዓመታት ስንጠብቀው ቆይተን ያገኘነው አንድ ነገር ከጠበቅነው የበለጠ ሆኖ የምናገኘው አልፎ አልፎ ብቻ ነው። ጊልያድ ግን እንደዚያ ነበር።
ሕንድ እንድንሄድ ተመደብን። ነገር ግን ቪዛ ተከለከልን። ስለዚህ ለዓመት ያህል ኒው ዮርክ ከተማ ሆነን ስንጠባበቅ ከቆየን በኋላ የመጠበቂያ ግንብ ማህበር በሰሜን አፍሪካ ወደምትገኘው ወደ ሞሮኮ መደበን።
የሞሮኮ ሚስዮናውያን
ሞሮኮ እንደደረስን ሕዝቡን በጣም ወደድነው። በዚያም 24 አስደሳች ዓመታት አሳለፍን። እዚያ ከሚኖሩት ብዙ ብሔረሰቦች ጋር ለመግባባት የረዱንን የፈረንሳይኛና የእስፓንኛ ቋንቋዎች ተማርን። አብዛኛውን ጊዜ የመንግሥቱን መልእክት የሚቀበሉት ከሌሎች አገሮች የመጡ ሰዎች ነበሩ።
መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናት የነበረች አንዲት ሴት የእስፓኒሽ ፍላሜንኮ ዳንኪረተኛ ነበረችና በካሳብላንካ በአንድ ዳንስ ቤት ውስጥ ተቀጥራ ትሠራ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን ሥነ ሥርዓት ከተማረች በኋላ አብራው ትኖር የነበረውን የዳንስ ቤት ባለቤት ትታ ወደ እስፓኝ ተመለሰች። እዚያም ለቤተሰቧ በሙሉ መሠከረችላቸውና ከእነሱም አንዳንዶቹ ያካፈለቻቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተቀበሉ። ከዚያ በኋላ ወደ ካሳብላንካ ተመልሳ በ1990 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ለአምላክ ታማኝ ሆና ኖረች።
በሞሮኮ ባሳለፍናቸው የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት በመንግሥት አስፋፊዎች ቁጥር ላይ ጭማሪ ሲገኝ ተመልክተናል። ይሁን እንጂ ለውጭ ሰዎች ሥራና የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ምሥክሮቹ ከሞሮኮ ወጥተው ወደ አውሮፓ መሄድ ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ካስጠናናቸው ሰዎች አንዳንዶቹ አሁን የሚኖሩት በኒውዚላንድ፣ በካናዳ፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በቡልጋሪያ፣ በሩሲያና በፈረንሳይ ሲሆን ከእነሱም አንዳንዶቹ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ይካፈላሉ።
በሚያዚያ ወር 1973 በሞሮኮ የነበረው ሥራችን በድንገት ታገደ። ይህም ለሥራችን ትልቅ ጉዳት ነበር። አንድ ሐሙስ ቀን በመንግሥት አዳራሻችን ከተሰበሰብን በኋላ ወደየቤታችን የምንሄድበት ሰዓት መድረሱን ለማሳወቅ መብራቱ እስኪጠፋብን ድረስ በደስታ እንጫወት ነበር። ያ መብራት በእንዲህ ዓይነት ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ የሚያበራበት የመጨረሻ ቀን እንደሚሆን አልጠረጠርንም ነበር። በዕገዳ ሥር ስንሆን ሳምንታዊ ስብሰባዎቻችንና የክልል ስብሰባዎችን በግል ቤቶች ውስጥ በሚደረጉ አነስተኛ ስብሰባዎች ተወሰኑ። ምሥክሮቹ በወረዳ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ወደ ፈረንሳይ ወይም ወደ እስፓኝ መሄድ ነበረባቸው።
ቁጥራችን እየቀነሰ ሲሄድ በሞሮኮ የቀረነው ጥቂት ምሥክሮች እርስ በርሳችን በጣም የተቀራረብን ሆንን። ስለዚህ በመጨረሻ የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ቅርንጫፍ እንዲዘጋና እኛም ሌላ ቦታ እንድንመደብ በተወሰነ ጊዜ ሁላችንም ብዙ አለቀስን።
ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ሄድን
አዲሱ ምድባችን የማዕከላዊው አፍሪካ ሪፑብሊክ ነበር። ከሰሜን አፍሪካ ከፍተኛ ልዩነት ነበረው! ሞሮኮ ከካሊፎርኒያ የአየር ጠባይ ጋር በጣም የሚመሳሰል ሲሆን አሁን የመጣንበት አገር ግን ሞቃትና በላብ የሚያሰጥም በረሃ ነው።
እዚህም ልንጋፈጣቸው የሚገቡን አዳዲስ ችግሮች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል እኔ በደረታቸው ለሚሳቡ ፍጥረቶች ያለኝን ፍርሃት መቆጣጠር ነበረብኝ። በሦስት ወቅቶች በበር ስገባ እንሽላሊቶች ራሴ ላይ ወድቀውብኛል። አንዳንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስመራ አይጧ እኛ ጋር ለማጥናት የወሰነች ይመስል ትመጣብን ነበር! ዘልየ ለመውጣትና ለመሮጥ ብፈልግም እሜቴ አይጥ ለመሄድ እስክትወስን ድረስ ዓይኔን ከሷ ላይ ሳላነሳ ቦርሳዬንና ጫማዬን ከወለሉ ላይ አርቄ ማቆየት ተማርኩ። ከጸኑ ከምንም ነገር ጋር መላመድ እንደሚቻል ተማርኩ።
እዚህ ለስድስት ወራት ያህል ከቆየን በኋላ ሥራችን መታገዱን የሚገልጽ ማስታወቂያ በሬድዮ ተላለፈ። ስለዚህ የመንግሥት አዳራሾቻችን ተዘጉ። ሚስዮናውያንም ለቀን እንድንወጣ ተጠየቅን። በቅርንጫፍ ቢሮው ለሌላ ሦስት ዓመት ለመቆየት የቻልነው ሚስዮናውያን እኛና ሌላ ባልና ሚስት ብቻ ነበርን። ከዚያም አንድ እሁድ ጧት የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ስናደርግ የታጠቁ ፖሊሶች መጡና ወደ ፖሊስ ዋና መምሪያ ተወሰድን። ሴቶቹንና ልጆቹን ለቀቁና ባለቤቴን ቢልን ጨምሮ 23 ወንድሞችን አሠሩአቸው። ከስድስት ቀን በኋላ ባለቤቴን ለቀውት መጣ። ከሦስት ቀን በኋላ ግንቦት 1989 በመንግሥት ትዕዛዝ አገሩን ለቀን ወጣን። ሊሰናበቱን እስከ አውሮፕላን ጣቢያው ድረስ ከመጡት ብዙ አፍቃሪ ወንድሞቻችን ጋር በእንባ ተለያየን።
በመጨረሻ ወደ ሴራሊዮን
ያሁኑ ምድባችን ውብና ነጫጭ አሸዋማ የወንዝ ዳርቻዎች ያሉባት የምዕራብ አፍሪካ አገር ሴራሊዮን ነች። ሕዝቦቿ ሰው ወዳድ ናቸው። የመስክ አገልግሎትም አስደሳች ነው። በያንዳንዱ ቤት አብዛኛውን ጊዜ በማንጎ ወይም ዘንባባ ዛፍ ጥላ ሥር አረፍ እንድንል እንጋበዝ ነበር። ሕዝቦቹ ስለአምላክ መነጋገር ይወዳሉ። የምንነግራቸውንም ለመከታተል ይችሉ ዘንድ የራሳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ይይዙ ነበር።
ቢልና እኔ ሁለታችንም በፍሪታውን ቤቴል እንሠራለን። እኔ በእንግዳ ተቀባይነትና የቅርንጫፍ ቢሮውን ኮንትራቶችና ሂሣብ በመያዝ ሥራ አገለግላለሁ። የስብከት ሥራችን በታገደባቸው አገሮች ለ16 ዓመታት ካገለገልን በኋላ ሥራው ነፃ በሆነበትና በሚያብብበት አገር መሆናችን አስደስቶናል።
በሰኔ ወር 1991 የ30 ዓመት የሚስዮናዊነት አገልግሎቴን ጨረስኩ። በእርግጥ እናቴ በፊቴ ያኖረችልኝ ትልቅ ዋጋ ያለው ግብ ነበር! በሕይወት ብትኖር ኖሮ ደጋግሜ “አመሰግንሻለሁ እማማ!” ብላት ደስ ይለኝ ነበር። አባቴ እስካሁንም በሕይወት ስላለ “አመሰግናለሁ አባባ” ለማለት የምችል መሆኔ ደስ ይለኛል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኒው ዮርክ ስብሰባ 1958
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድ 35ኛ ክፍል ተመራቂዎች—ሐምሌ፣ 1960
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቢልና ሳንድራ ካዎን 1991