የአምላክን አዲስ የነፃነት ዓለም በእልልታ መቀበል
“[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ሐዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።”—ራእይ 21:4
1, 2. እውነተኛ ነፃነት ሊያመጣ የሚችለው ማን ብቻ ነው? ስለ እርሱስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምን ልንማር እንችላለን?
ነቢዩ ኤርምያስ “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” በማለት የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸውን ታሪክ አረጋግጧል። የሰውን አካሄድ ሊያቀና የሚችለው ማን ብቻ ነው? ኤርምያስ በመቀጠል “አቤቱ [ይሖዋ (አዓት)] አርመኝ” ብሏል። (ኤርምያስ 10:23, 24) አዎ፣ ሰብዓዊውን ቤተሰብ ከሚያስጨንቁት ችግሮች ሊያወጣውና እውነተኛ ነፃነት ሊያመጣለት የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው።
2 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አገልጋዮቹን ነፃ ለማውጣት እንደሚችል የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎችን ይሰጠናል። “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል።” (ሮሜ 15:4) ይሖዋ በሐሰት አምልኮ ላይ የፈጸማቸው ፍርዶችም ተመዝግበውልናል። እነሱም “እኛን የዘመናት ፍጻሜ የደረሰብንን ሊገስጹን [ማስጠንቀቂያ እንዲሆኑን (አዓት)] ተጽፈዋል።”—1 ቆሮንቶስ 10:11
ሕዝቡን ነፃ አወጣ
3. ይሖዋ ግብፅ የነበሩትን ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት ችሎታ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነበር?
3 አምላክ በሐሰት አምልኮ ላይ ፍርዱን ለማስፈጸምና ፈቃዱን የሚያደርጉትን ሰዎች ነፃ ለማድረግ ችሎታ ያለው መሆኑን የሚያሳይ ምሳሌ የጥንት ዘመን ሕዝቦቹ በግብፅ ባርነት ሥር በነበሩ ጊዜ ተፈጽሟል። ዘጸአት 2:23-25 እንዲህ ይላል፦ “የእሥራኤል ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፣ ጮኹም ስለ ባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። እግዚአብሔርም የልቅሶአቸውን ድምጽ ሰማ።” ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከግብጽ የሐሰት አማልክት የሚበልጥ መሆኑን በአስደናቂ ሁኔታ በማሳየት በአገሩ ላይ አሥር መቅሠፍቶች አመጣ። እያንዳንዱ መቅሰፍት የግብጽ አማልክት የሐሰት አማልክት መሆናቸውንና ያመልኩአቸው የነበሩትን ግብፃውያን ለመርዳት የማይችሉ መሆናቸውን በማጋለጥ የተለያዩ የግብፅ አማልክትን እንዲያዋርዱ ታስበው የመጡ ነበሩ። እንዲህ በማድረግም አምላክ ሕዝቡን ነፃ አውጥቶ ፈርዖንንና ሠራዊቱን በቀይ ባሕር ውስጥ አስጥሞ አጠፋቸው።—ዘጸአት ምዕራፍ 7 እስከ 14
4. አምላክ በከነዓናውያን ላይ ፍርዱን ማስፈጸሙ ፍትሕ የጎደለው እርምጃ ያልነበረው ለምንድን ነው?
4 አምላክ እሥራኤልን ወደ ከነዓን ሲያመጣቸው እነዚያ አጋንንት አምላኪ የከነዓን ነዋሪዎች ጠፍተው ምድሪቱ ለአምላክ ሕዝቦች ተሰጠች። ይሖዋ የጽንፈ-ዓለሙ ልዑል ገዢ በመሆኑ በወራዳ ሃይማኖቶች ላይ ፍርዱን የማስፈጸም መብት አለው። (ዘፍጥረት 15:16) የሀሊ ባይብል ሀንድቡክ ስለ ከነዓናውያን ሃይማኖት እንዲህ ይላል፦ “በከነዓናውያን አማልክት የአምልኮ ሥርዓት ላይ በጣም ልቅ የሆነ ጭፈራ፣ ስካርና ብልግና ይፈጸም ነበር። ቤተ መቅደሳቸው የብልግና ድርጊት የሚፈጸምባቸው ማዕከላት ነበሩ። . . . ከነዓናውያን የአምልኮ ሥርዓት የሚፈጽሙት በአማልክቶቻቸው ፊት ዝሙት በመፈጸም ነበር። ዝሙት ከፈጸሙ በኋላ የበኩር ልጆቻቸውን አርደው ለእነዚህ አማልክቶቻቸው ይሠዋሉ። በአብዛኛው የከነዓን ምድር በሙሉ ሰዶምንና ገሞራን ይመስል ነበር።” ደራሲው በመቀጠል “እንዲህ ያለ ጸያፍ ነውርና የጭካኔ ድርጊት ይፈጽም የነበረ ሥልጣኔ የመኖር መብት ሊኖረው ይችላልን? . . . የከነዓንን ፍርስራሾች ቆፍረው ጥናት ያደረጉ ምሁራን አምላክ ለምን ከዚያ ቀደም ብሎ እንዳላጠፋቸውና ለምን እስከዚያ ጊዜ ድረስ እንደታገሣቸው ይደንቃቸዋል” ብለዋል።
5. አምላክ የጥንት ሕዝቦቹን ነፃ ማውጣቱ እኛ ለምንኖርበት ዘመን በምሳሌነት የሚያገለግለው እንዴት ነው?
5 አምላክ በሀሰት አምልኮ ላይ እርምጃ በመውሰድ የቃል ኪዳን ሕዝቡን ነፃ አውጥቶ ተስፋ የገባላቸውን ምድር ለእነሱ መስጠቱ ወደፊት ለሚሆኑት ነገሮች ጥላ ወይም ምሳሌ በመሆን ያገለግላል። አምላክ በቅርቡ የዚህን ዓለም የሐሰት ሃይማኖቶችና ደጋፊዎቻቸውን አውድሞ ዘመናዊ አገልጋዮቹን ወደ አዲስ የጽድቅ ዓለም የሚያስገባበትን ጊዜ ይጠቁማል።—ራእይ 7:9, 10, 13, 14፤ 2 ጴጥሮስ 3:10-13
በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ እውነተኛ ነፃነት
6. አምላክ በአዲሱ ዓለም ከሚያስገኛቸው አስደናቂ ነፃነቶች ውስጥ አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
6 በአዲሱ ዓለም ውስጥ አምላክ የሰው ልጆች እንዲያገኙ ያሰበላቸውን የተለያዩ የነጻነት ገጽታዎች ሁሉ ለሕዝቦቹ በመስጠት ይባርካቸዋል። የሰው ልጅ ከፖለቲካ፣ ከኤኮኖሚና ከሐሰት ሃይማኖት ጭቆና ነፃ ይወጣል። ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ስለሚኖራቸው ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ይወጣሉ። “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29፤ ማቴዎስ 5:5
7, 8. በአዲሱ ዓለም ውስጥ ፍጹም ጤንነትን መልሶ በማግኘት ረገድ ምን ተሞክሮ ይኖራል?
7 ያ አዲስ ዓለም ከመጣ በኋላ ወዲያው ነዋሪዎቹ በተአምራዊ መንገድ ፍጹም ጤንነት ይመለስላቸዋል። ኢዮብ 33:25 “ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል፤ ወደ ጉብዝናውም ዘመን ይመለሳል” ይላል። ኢሳይያስ 35:5, 6 ደግሞ የሚከተለውን ተስፋ ይሰጠናል፦ “በዚያን ጊዜ የዕውሮች ዓይን ይገለጣል፣ የደንቆሮዎችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደሚዳቋ ይዘላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል።”
8 በእርጅናም ሆነ በበሽታ ምክንያት አካለ ስንኩላን የሆናችሁ ሁሉ በአዲስ ዓለም ውስጥ በየቀኑ ጧት ስትነሱ ካለፈው ቀን የበለጠ ጤናና ብርታት ሲሰማችሁ እንዴት ደስ እንደሚላችሁ ገምቱ። የተጨማተረው ቆዳችሁ ለስላሳና ጤናማ በሆነ ቆዳ ስለሚተካ ከዚያ በኋላ የቆዳ ቅባት አያስፈልጋችሁም። የፈዘዙ ወይም የታወሩ ዓይኖቻችሁ ፍጹም የሆነ የማየት ችሎታ ይኖራቸዋል። መነፅር አያስፈልጋችሁም። ፍጹም የመስማት ችሎታ ስለሚመለስላችሁ የመስሚያ መሣሪያዎቻችሁን ትጥላላችሁ። ሽባ የሆኑባችሁ ክንዶቻችሁና እግሮቻችሁ አዲስ ብርታት ስለሚያገኙ ከምርኩዞቻችሁ፣ ከብርኩማዎቻችሁና ከጋሪዎቻችሁ ትገላገላላችሁ። ምንም ዓይነት በሽታ ስለማይኖር አሁን የምትውጡአቸውን መድሃኒቶች በሙሉ ለመጣል ትችላላችሁ። በመሆኑም ኢሳይያስ 33:24 “በዚያም የሚቀመጥ ታምሜያለሁ አይልም” በማለት ተንብዮአል። በተጨማሪም “ሐሴትንና ደስታን ያገኛሉ፣ ሐዘንና ትካዜም ይሸሻሉ” ይላል።—ኢሳይያስ 35:10
9. ጦርነት ለዘላለም ወደ ፍጻሜው የሚመጣው እንዴት ነው?
9 ከዚያ ወዲያ በጦርነት የሚሠዋ ሰው አይኖርም። “[አምላክ] እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፣ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርነትንም ይቆርጣል። በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።” (መዝሙር 46:9) ኢሳይያስ 9:6 “የሰላም መስፍን” ብሎ የሚጠራው የአምላክ መንግሥት መሪ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የጦር መሣሪያዎች እንዲኖሩ አይፈቅድም። ኢሳ 9 ቁጥር 7ም በመጨመር “አለቅነቱም ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም” ይላል።
10, 11. በምድር ላይ ፍጹም ሰላም መኖሩ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
10 የሰው ልጅም ሆነ ይህች ምድር ከጦር መሣሪያዎች ነፃ መሆናቸው ምንኛ ታላቅ በረከት ይሆናል! ሰዎች ባለፉት ጦርነቶች የተገለገሉባቸው መሣሪያዎች እንኳን እስከአሁን ድረስ የሰው ልጆችን በማጥፋት ላይ ናቸው። በፈረንሳይ አገር ብቻ ከ1945 ወዲህ ከ600 በላይ የቦምብ አስወጋጅ ጠበብት በቀድሞ ጊዜያት በተደረጉ ጦርነቶች የተጣሉ ቦምቦችን ለማክሸፍና ለማስወገድ ሲሞክሩ ሞተዋል። የፈረንሳይ አገር የቦምብ አስወጋጅ መሥሪያ ቤት ሐላፊ እንዲህ ብለዋል፦ “እስከ አሁን ድረስ በ1870 በፈረንሳይና በፕራሽያ መካከል ተደርጎ በነበረው ጦርነት የተጣሉ ፈንጅዎችን እንኳን እያገኘን ነው። በመጀመሪያው ዓለም ጦርነት ጊዜ በተጣሉ ፈንጂዎች የተሞሉ ሐይቆች አሁንም አሉ። በእርሻ ሥራ የተሰማሩ ገበሬዎች ትራክተራቸው በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጊዜ በተጠመደ ፀረ-ታንክ ፈንጂ ላይ ይወጣና ከመቅጽበት ይሞታሉ። እነዚህን ነገሮች በሁሉም ቦታዎች እናገኛለን።” ከሁለት ዓመት በፊት ዘ ነው ዮርክ ታይምስ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቶ ነበር፦ “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ባሉት 45 ዓመታት [ቦምብ አስወጋጅ ጓዶች] ከፈረንሳይ አገር 16 ሚልዮን የመድፍ ጥይቶችን፣ 490,000 ቦምቦችን፣ 600,000 ከባህር በታች የተቀበሩ ፈንጂዎችን አስወግደዋል። . . . እስካሁን ድረስ ፈንጂዎችና የጦር መሣሪያዎች የታጨቁባቸው በመሆናቸው ምክንያት ‘አትንኩ፣ ትሞታላችሁ’ የሚል ምልክት የተሰቀለባቸውና ሰው እንዳይደርስባችው የታጠሩ በሚልዮን ሄክታር የሚቆጠር መጠን ያላቸው መሬቶች አሉ!”
11 አዲሱ ዓለም ግን ምንኛ የተለየ ይሆናል! በዚያ የሚኖር ማንኛውም ሰው ጥሩ የሆነ ቤት፣ የተትረፈረፈ ምግብና መላውን ምድር ወደ ገነትነት የመለወጥ አርኪ ሥራ ያገኛል። (መዝሙር 72:16፤ ኢሳይያስ 25:6፤ 65:17-25) ከዚያ በኋላ ሰዎችም ሆኑ ምድር ራስዋ በሚልዮን በሚቆጠሩ ፈንጂዎች አይደበደቡም። ኢየሱስ በእርሱ ላይ እምነት ላሳየ አንድ ሰው “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ባለ ጊዜ በአእምሮው ይዞ የነበረው እንዲህ ያለውን አዲስ ዓለም ነበር።—ሉቃስ 23:43
ለሕይወት የሚያበቃ ምድር አቀፍ ትምህርት
12, 13. ኢየሱስና ኢሳይያስ በዘመናችን ስለሚፈጸም ምን ዓለም አቀፍ የትምህርት ሥራ ትንቢት ተናግረዋል?
12 አንድ ሰው ስለ አምላክ አዲስ ዓለም በሚማርበት ጊዜ ይሖዋ በዘመናችን ለእውነተኛ አምልኮ የተደራጀ ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንዳዘጋጀም ይማራል። ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ የአዲሱ ዓለም እምብርት ይሆናል። አሁንም ቢሆን አምላክ ይህን ጉባኤ ስለ ዓላማዎቹ ለሌሎች ለማስተማር እየተጠቀመበት ነው። ይህ ክርስቲያናዊ ድርጅት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ባህርይና መጠን ያለው ዓለም አቀፍ የትምህርት ሥራ በማከናወን ላይ ነው። ኢየሱስም ይህ እንደሚሆን ተንብዮአል። “ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ብሎአል።—ማቴዎስ 24:14
13 ኢሳይያስ “በዘመኑ ፍጻሜ [በዚህ በምንኖርበት ዘመን] የ[ይሖዋ (አዓት)]ቤት ተራራ [ከፍ ያለው ንጹሕ አምልኮ] በተራሮች ላይ ጸንቶ ይቆማል። ብዙዎች አሕዛብ ሄደው ኑ ወደ [ይሖዋ (አዓት)] ተራራ እንውጣ፣ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ” በማለት ስለዚህ ምድር አቀፍ የማስተማር ሥራ ተናግሯል።—ኢሳይያስ 2:2, 3
14. በዛሬ ጊዜ የአምላክን ሕዝቦች ለይተን ልናውቃቸው የምንችለው እንዴት ነው?
14 ስለዚህ ስለአምላክ መንግሥት የሚደረገው ዓለም አቀፍ የምሥክርነት ሥራ ወደዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች እንደቀረብንና እውነተኛ ነጻነት የሚመጣበት ጊዜም በጣም ቅርብ መሆኑን የሚያሳይ ኃይለኛ ማስረጃ ነው። ስለአምላክ አዲስ ዓለም የሚናገረውን ተስፋ ያዘለ መልእክት ይዘው ለሰዎች ለማድረስ የሚሄዱት ሰዎች በሥራ 15:14 ላይ “ለእግዚአብሔር ስም የሚሆን ሕዝብ” በመባል ተገልጸዋል። የይሖዋን ስም ተሸክመው ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ የሚገልጽ ዓለም አቀፍ ምሥክርነት የሚሰጡት እነማን ናቸው? የ20ኛው መቶ ዘመን የታሪክ መዝገብ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው በማለት መልሱን ይሰጠናል። የይሖዋ ምሥክሮች ባሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ66,000 በላይ በሆኑ ጉባኤዎች የሚሰበሰቡ ከአራት ሚልዮን በላይ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች ናቸው።—ኢሳይያስ 43:10-12፤ ሥራ 2:21
15. በፖለቲካ ጉዳዮች ረገድ የአምላክን እውነተኛ አገልጋዮች ለይተን ልናውቃቸው የምንችለው እንዴት ነው?
15 ኢየሱስ ስለ መንግስቱ ስብከት ሥራ የተናገረውን ትንቢት በመፈጸም ላይ ያሉት ሕዝቦች የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሌላ የሚታይ ማስረጃ በኢሳይያስ 2:4 ላይ ተገልጿል፦ “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ። ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም። ሠልፍም [ጦርነትም] ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” ስለዚህ ስለ እግዚአብሔር የመንግሥት አስተዳደር የሚገልጸውን ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ የሚያከናውኑት ሰዎች “ጦርነትን ከእንግዲህ ወዲህ መማር” አይገባቸውም። ኢየሱስ “የዓለም ክፍል መሆን” እንደሌለባቸው ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:16) ይህም ማለት ብሔራት በሚያደርጉአቸው ግጭቶችና ጦርነቶች የአንዱም ወገን ደጋፊዎች ባለመሆን በፖለቲካ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኞች መሆን አለባቸው ማለት ነው። ታዲያ የዓለም ክፍል ያልሆኑትና ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነትን የማይማሩት እነማን ናቸው? አሁንም የሃያኛው መቶ ዘመን የታሪክ መዝገብ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው በማለት ይመሠክራል።
16. የአምላክ ዓለም አቀፍ የትምህርት ሥራ የቱን ያህል ስፋት ይኖረዋል?
16 የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት ዓለም አቀፍ የትምህርት ሥራ አምላክ ያሁኑን ክፉ ዓለም ካጠፋ በኋላም እንኳን የሚቀጥል ነው። ኢሳይያስ 54:13 “ልጆችሽም ሁሉ [ከይሖዋ (አዓት)] የተማሩ ይሆናሉ” ይላል። ይህ የማስተማር ሥራ በሠፊው የሚካሄድ በመሆኑ ኢሳይያስ 11:9 “ውኃ ባህርን እንደሚከድን ምድር ይሖዋን በማወቅ ትሞላለች (አዓት)” በማለት ይተነብያል። ይህ በተከታታይ የሚሰጥ ትምህርት የሚያስፈልጋቸው ከዚህ አሮጌ ዓለም በሕይወት ያለፉ ሰዎችና በአዲሱ ዓለም የሚወልዷቸው ልጆቻቸው ብቻ ሳይሆኑ በትንሣኤ አማካኝነት ወደ ሕይወት የሚመለሱት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጭምር ናቸው። በመጨረሻ ላይ በምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው ነፃ ምርጫ የማድረግ መብቱን እንዴት በትክክለኛ ሁኔታ በአምላክ ሕግጋት ገደብ ውስጥ ተወስኖ እንደሚጠቀምበት ይማራል። ውጤቱስ ምን ይሆናል? “ገሮች ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:11
አሁንም እንኳን ታላቅ ነፃነት አግኝተናል
17. ሙሴ የአምላክን ጥንታዊ ሕዝቦች ምን እንዲያደርጉ ነገራቸው?
17 የጥንቶቹ እሥራኤላውያን በተስፋይቱ ምድር ደጃፍ ላይ ሳሉ ሙሴ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ እናንተ ገብታችሁ በምትወርሱአት ምድር ውስጥ እንዲህ ታደርጉ ዘንድ አምላኬ [ይሖዋ (አዓት)] እንዳዘዘኝ ሥርዓትንና ፍርድን አስተማርኋችሁ ጠብቁአት አድርጓትም። ይህችን ሥርዓት ሁሉ ሰምተው በእውነት ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ ነው በሚሉ በአሕዛብ ፊት ጥበባችሁና ማስተዋላችሁ ይህ ነውና አምላካችን [ይሖዋ (አዓት)] በምንጠራው ጊዜ ሁሉ እንደሚቀርበን፣ አምላኩ ወደ እርሱ የቀረበው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው?”—ዘዳግም 4:5-7
18. አሁንም እንኳን አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎች ምን አይነት ነፃነቶች በማግኘት ላይ ናቸው?
18 ዛሬም ይሖዋን የሚያመልኩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሌላይቱ የተስፋ ምድር ማለትም በአዲሲቱ ዓለም ደጃፍ ላይ ተዳርሰዋል። እነርሱም ለሕጉ ስለሚታዘዙ ይሖዋን በአጠገባቸው አድርገዋል፣ በዚህም ምክንያት ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ልዩ ሆነው ይታያሉ። አሁንም እንኳን አምላክ ሕዝቦቹን ከሐሰት ሃይማኖት አስተሳሰቦች፣ ከዘረኛነት፣ በዕፅ ያለአግባብ ከመጠቀም፣ ከብሔርተኛነት፣ ከጦርነትና ተስፋፍቶ ካለው የአባላዘር ወረርሽኝ ነፃ አውጥቷቸዋል። በተጨማሪም ሊበጠስ በማይችል ዓለም አቀፋዊ የወንድማማችነት ፍቅር አስተሳስሮአቸዋል። (ዮሐንስ 13:35) ስለወደፊቱ ጊዜ ከመሸበር ፈንታ “ከልባቸው ደስታ የተነሳ ይዘምራሉ።” (ኢሳይያስ 65:14) አምላክን እንደ ገዢአቸው አድርገው በማገልገላቸው አሁንም እንኳን ምንኛ ታላቅ ነፃነት አግኝተዋል!—ሥራ 5:29, 32፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7፤ 1 ዮሐንስ 5:3
ሌሎች ሰዎችን ከሐሰት እምነቶች ነፃ ማውጣት
19, 20. ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሙታን ሁኔታ በሚያስተምረው ነገር ነፃ የወጡት እንዴት ነው?
19 የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩላቸው ብዙ ሰዎችም እነዚህን ነፃነቶች እያገኙ ነው። ለምሳሌ ያህል የሞቱ የቀድሞ አባቶች አምልኮ በሚፈጸምባቸው አገሮች የሞቱ ሰዎች በየትኛውም ቦታ በሕይወት የማይኖሩ በመሆናቸው በሕይወት የሚኖሩትን ሰዎች ሊጎዱ እንደማይችሉ የይሖዋ ምሥክሮች ለሌሎች በማሳወቅ ላይ ናቸው። ምሥክሮቹ “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” የሚለውን መክብብ 9:5ን ያመለክቱአቸዋል። በተጨማሪም አንድ ሰው ሲሞት “ወደ መሬቱም ይመለሳል፣ ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል” የሚለውን መዝሙር 146:4ን ይጠቅሳሉ። ስለዚህ በሕይወት የሚኖሩትን ሰዎች የሚያድኑ ወይም የሚያሸብሩ ምትሐታዊ መናፍስት ወይም የማይሞቱ ነፍሳት እንደሌሉ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። ስለሆነም በብዙ ድካም የተገኘውን ገንዘብ የፍትሐ ወይም የአማላጅነት አገልግሎት ለማግኘት ለቀሳውስት ወይም ለጠንቋዮች መክፈል አስፈላጊ አይደለም።
20 እንዲህ ዓይነቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ሰዎችን ስለ ሲኦል እሳትና የተኮነኑ ነፍሳት ይኖሩበታል ስለሚባለው መንጽሔ የሚባል የንስሐ ቦታ ከሚነገሩት የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ነፃ ያወጣል። ሰዎች ሙታን ከባድ እንቅልፍ ላይ እንደሚገኝ ሰው ምንም ነገር የማይሰማቸው መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲማሩ የሚወዱት የሞተ ዘመዳቸው እንዴት ያለ ሁኔታ አጋጥሞት እንደሆነ መጨነቃቸውን ያቆማሉ። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ “ጻድቃንም አመጸኞችም ከሙታን ይነሱ ዘንድ ተስፋ አላቸው” ሲል የተናገረው ቃል የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ።—ሥራ 24:15
21. ትንሣኤ ከሚያገኙት መሃል እነማን እንደሚያገኙ አያጠራጥርም? እንዴትስ ሊሰማቸው ይችላል?
21 ይህ ትንሣኤ ሙታን በሚፈጸምበት ጊዜ ሙታን ከአዳም የተወረሰው ሞት ለዘላለም በማይኖርበት ምድር ላይ ለመኖር ወደ ሕይወት ይመለሳሉ። ወደ ሕይወት ከሚመለሱት ሰዎች መሃል ለሞሎክ የተሠዉ ሕፃናት፣ ለአዝቴክ አማልክት የተሠዉ ወጣት ሰዎችና ለጦርነት አምላክ የተሠዉ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሰዎች እንደሚኖሩበት አያጠራጥርም። እነዚህ የሐሰት እምነት ሰለባዎች የሆኑ ሰዎች ምንኛ ይገረሙና ይደሰቱ ይሆን! እነሱም በዚያን ጊዜ “ሞት ሆይ ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ፣ ማጥፋትህ ወዴት አለ?” በማለት በደስታ ሊናገሩ ይችላሉ።—ሆሴዕ 13:14
ይሖዋን ፈልጉ
22. በአምላክ አዲስ ዓለም ለመኖር የምንፈልግ ከሆነ ምን መዘንጋት የለብንም?
22 እውነተኛ ነፃነት በሚኖርበት በአምላክ አዲስ የጽድቅ ዓለም ውስጥ ለመኖር ትፈልጋለህን? የምትፈልግ ከሆነ በ2 ዜና መዋዕል 15:2 ላይ የሚገኘውን ቃል ልብ በል፦ “እናንተ [ከይሖዋ (አዓት)] ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው። ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፣ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል።” ስለ አምላክ ለማወቅና እርሱንም ለማስደሰት የምታደርጉትን ልባዊ ጥረት አምላክ ሳይመለከተው እንደማይቀር አትርሱ። ዕብራውያን 11:6 አምላክ “ለሚፈልጉትም ዋጋቸውን” እንደሚሰጥ ይናገራል። ሮሜ 10:11 ደግሞ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም” ይላል።
23. የአምላክን አዲስ የነፃነት ዓለም በእልልታ መቀበል የሚኖርብን ለምንድን ነው?
23 እውነተኛ ነፃነት ያለበት የአምላክ አዲስ ዓለም ከአድማስ ባሻገር ቀርቧል። በዚህ አዲስ ዓለም “ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት” ይደርሳል። “[አምላክም] እንባዎችን ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ሐዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።” (ሮሜ 8:21፤ ራእይ 21:4) በዚያን ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ ራሳቸውን ቀና አድርገው “ይሖዋ ሆይ፣ በመጨረሻ እውነተኛ ነፃነት ስላጎናጸፍከን እናመሰግንሃለን!” በማለት የአምላክን አዲስ የነፃነት ዓለም በእልልታ ሊቀበሉት ይችላሉ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ይሖዋ ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት ያለውን ችሎታ ያሳየው እንዴት ነው?
◻ በአምላክ አዲስ ዓለም ምን አስደናቂ ነፃነቶች ይኖራሉ?
◻ ይሖዋ ሕዝቦቹን ለሕይወት የሚያበቃ ትምህርት የሚሰጣቸው እንዴት ነው?
◻ የአምላክ ሕዝቦች አሁንም እንኳን ይሖዋን በማገልገል ያገኙአቸው አንዳንድ ነፃነቶች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ አምላኪዎቹን ነፃ በማውጣት ከግብፅ የሐሰት አማልክት እንደሚበልጥ አሳይቷል።
[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በዛሬው ጊዜ የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች ተለይተው የሚታወቁት የአምላክን ዓለም አቀፍ የትምህርት ሥራ በመፈጸምና ስሙን በመሸከም ነው።