የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው እውነት በቦሊቪያ ለአንዲት መነኩሲት ነፃነት አስገኘላት
ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን እውነት በመረዳታቸው ሐሰተኛ ሃይማኖትን በመሸሽ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ለማምለክ በመምጣት ላይ ይገኛሉ። በቦሊቪያ ውስጥ ቀድሞ መነኩሲት የነበረች አንዲት ሴትን ጨምሮ ከ7,600 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ይሖዋን በማምለክ ላይ ናቸው።
ኤም—— ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስትገናኝ ዕድሜዋ ገና ዘጠኝ ዓመት ብቻ ነበር። ምሥክሮቹ ወደ ቤቷ መጥተው ሲያንኳኩ በሯን ከፍታ አነጋገረቻቸው፤ በዚህ ወቅት ይሖዋ የሚለውን የአምላክን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ሰማች፤ ስሙ ከአእምሮዋ ውስጥ ሳይጠፋ ለብዙ ዓመታት ያህል ቆየ።
በቤተሰቧ ውስጥ ያለችው ሴት ልጅ እሷ ብቻ ስለነበረች መነኩሲት እንድትሆን ቤተሰቡ ይወስናል። “የአምላክ አገልጋይ በመሆን በመታጨቴ በጣም ደስታ ተሰማኝ፤ ሳስበው የነበረ ነገር ነው” በማለት ኤም—— ትናገራለች። ይሁን እንጂ በሴቶች ገዳም ውስጥ የተመለከተችው የፍትሕ መጓደልና አድልዎ ተስፋ እያስቆረጣት ደስታዋን ያሳጣት ጀመር። “እነዚያን ለረጅም ጊዜ ሲያስጨንቁኝ የነበሩትንና በአካልም ሆነ በመንፈሳዊ ስደበደብባቸው የነበሩትን ቀናት አልረሳቸውም። አምላክ የፍቅር አምላክ ሳይሆን ያለ ርህራሄ ሰዎችን የሚቀጣ አድርጌ እንድመለከተው አድርጐኝ ነበር” ትላለች።
ቀጥላም “መነኩሲት ከሆንኩ በኋላ ይሖዋ የሚለውን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማግኘት ብፈልግ ላገኘው አልቻልኩም። ያገኘሁት ‘ያህዌህ’ የሚለውን ስም ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ግራ አጋባኝ። እንዲያውም አንድ ቀን ስለ ይሖዋ የሚናገሩ ሰዎችን ለማግኘት ከቤት ወጣሁ። ይሁን እንጂ ላገኛቸው አልቻልኩም።”
“ብዙ ጊዜያቶች ካለፉ በኋላ አንድ ቀን ወደ ቤተሰቦቼ ቤት ሳመራ ‘የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ’ የሚል ጽሑፍ በአዳራሹ ላይ ተመለከትኩ። ሐሰተኛ ነቢያት መሆናቸውን ልነግራቸው ፈለግሁ፤ ነገር ግን በአዳራሹ ውስጥ ማንም አልነበረም። እሁድ ዕለት እንደገና ተመልሼ መጣሁ፣ ስብሰባው በመካሄድ ላይ ነበር። የመነኩሲት ልብስ እንደለበስኩ በመካከላቸው ሲያዩኝ ብዙዎቹ ደነቃቸው። ስብሰባው እንዳለቀ ፈጥኜ ወጥቼ ለመሄድ ሞከርኩ። ይሁን እንጂ ከምሥክሮቹ አንዷ መጣችና ሰላምታ ተለዋወጥን። በዚህ ምክንያት ‘የአምላክን ስም በከንቱ ለምን ትጠሩታላችሁ?’ ብዬ ጥያቄ አቀረብኩላት። የአቀረብኩት ጥያቄ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ውይይት መራንና በቤተሰቦቼ ቤት ውስጥ ተገናኝተን እንድንወያይ ቀጠሮ ይዘን በቀጠሮው ተገናኘን። ይሁን እንጂ ወላጆቼ አባረሯት፤ ከሁለት ወር በኋላ እንደገና ተገናኘንና በእርሷ ቤት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድናደርግ ጋበዘችኝ። ክርስቲያኖች በአምላክ ስም መጠቀም እንዳለባቸው የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ስታሳየኝ በጣም ተደነቅሁ። ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁት ዕውቀት መነኩሲት ሆኜ የተማርኳቸውን ከንቱ ነገሮች ሁሉ እንድተዋቸው አስፈላጊውን ኃይል ሰጠኝ።
“በሴቶች ገዳም ውስጥ በነበርኩባቸው ጊዜያት ያሳለፍኳቸውን በርካታ ነገሮች አስታውሳቸዋለሁ። ለምሳሌ ያህል አንድ ጊዜ ምግብ ቸገረኝና ቤተሰቦቼ እንዲልኩልኝ ደብዳቤ ጻፍኩላቸው። ነገር ግን ደብዳቤዎቹ በገዳሙ ውስጥ ከተፈተሹ በኋላ እንደሚያልፉ አላውቅም ነበር። በተከታዩ የመመገቢያ ሰዓት ላይ ብዙ ዳቦና ጄሊ በፊቴ ተቀመጠልኝና ሁሉንም በልቼ እንድጨርሰው ተገደድሁ። በዚህ ጊዜ የቀረበልኝ ምግብ ከመጠን ያለፈ ሆነብኝና ይህንኑ ለጓደኞቼ ነገርኳቸው፣ ከመካከላቸው አንዷ ልበላው ያልቻልኩትን ዳቦ እንድፈረፍረውና በወለሉ ላይ እንድበትነው ሐሳቧን አቀረበችልኝና እኔም ጓደኛዬ እንዳለችኝ አደረግሁ። ወዲያውኑ አንዲት መነኩሲት ጨመደደችኝና ወለሉ ላይ ከወረወረችኝ በኋላ የዚያን ክፍል ወለል በጠቅላላ በምላሴ እንዳጸዳው ጥብቅ ትእዛዝ ሰጠችኝ፣ ክፍሉ በጣም ትልቅ ነበር። ትእዛዟን አክብሬ እያጸዳሁ ሳለሁ ብዙ ሳቅና ካካታ እሰማ ነበር። አንዳቸውም ርህራሄ አላሳዩኝም።
“አሁን ወደ ኋላ ተመልሼ ነገሩን ስመለከተው ከዚያ ሁሉ ጣጣ መገላገሉ ትልቅ ነፃነት እንደሆነ እገነዘባለሁ። ማናችንም ልንጠብቀው እንደምንችለው ሁሉ ወደዚህ ነፃነት ለመድረስ ብዙ መስዋዕትነት ይጠይቃል፣ በዚህም ምክንያት አባቴ ከቤት አባረረኝ። ሆኖም ገዳሙን ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት ሌሎች ወጣት መነኮሳት እውነትን እንዲያውቁ የመርዳት መብት አግኝቻለሁ። ከመነኮሳቱ መካከል አንዳንዶቻችን ራሳችንን ለይሖዋ አምላክ የወሰንን ሆነናል ብዬ ስናገር በጣም ደስ እያለኝ ነው።”
“ገዳሙን ለቅቄ ከሄድኩ በኋላ ጊዜዬን የሚያባክን ነገር ግን ጥሩ ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራ ለምን መቀጠር እንዳልፈለግሁ አባቴ ሊገባው አልቻለም። የእኔ ዓላማ ግን ለአምላክ አገልግሎት ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት ነበር። አሁን የዘወትር አቅኚ ሆኜ ውጣ ውረድ የሌለበትና አስደሳች ሕይወት እየመራሁ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ያስደሰተኝ ይሖዋን በማገልገሉ ሥራ ላይ እናቴና ወንድሞቼ መካፈላቸው ነው።”
በእውነትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን እውነት ማወቅ አንድን ሰው ከዚህ ዓለም የሐሰተኛ ሃይማኖት ሥርዓት ነፃ አውጥቶ ዘላቂ ሰላምና ደስታ ያመጣለታል።—ዮሐንስ 8:32