መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ የተጻፈ የአምላክ ስጦታ የሆነው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ይላል። በተጨማሪም ጥበብና ኃይል እንዳለው ይገልጻል። (1 ዮሐንስ 4:8፤ ኢዮብ 12:13፤ ኢሳይያስ 40:26) “መንገዱ ሁሉ ፍትህ” እንደሆነም ይነግረናል። (ዘዳግም 32:4 (አዓት)) በተጨማሪም አምላክ ምህረትና ርህራሄን የመሳሰሉ ባሕርያት እንዳሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎአል።—ዘጸአት 34:6፤ ሮሜ 9:15
ይሖዋ አምላክ እንደነዚህ የመሰሉ ባህርያት እንዳሉት መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚገልጽ አምላክን የሚፈልጉ ሰዎች ወደ እርሱ እንዲጠጉ ይገፋፋቸዋል። ይህ መጽሐፍ ስለ ፍጥረት፣ ስለ ኃጢአትና ሞት አመጣጥ እንዲሁም ከአምላክ ጋር መታረቅ ስለሚቻልበት መንገድ ይናገራል። ምድር ዳግመኛ ገነት እንደምትሆን የሚያስደንቅ ተስፋ ይሰጣል። ይሁንና እነዚህ ነገሮች ሁሉ ዋጋ የሚኖራቸው በመንፈስ የተጻፈ የአምላክ ስጦታ መሆኑ ሊረጋገጥ ከተቻለ ብቻ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ እና ሳይንስ
መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዛሬ የደረሰበትን ትችት በሙሉ በድል አድራጊነት ተቋቁሞአል። ለምሳሌ ያህል ክፍት በሆነ አእምሮ ከተነበበ ከእውነተኛ ሳይንስ ጋር እንደሚስማማ ተረጋግጦአል። እርግጥ ነው መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ መመሪያዎችን ለመስጠት የተጻፈ መጽሐፍ እንጂ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ አይደለም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንሳዊ እውነታዎች ጋር ይስማማ እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
አናቶሚ (የሰውነት አሠራር ጥናት)፦ መጽሐፍ ቅዱስ የሰብዓዊ ሽል የአካል ክፍሎች በሙሉ በመጽሐፍ የተጻፉ እንደሆኑ ይናገራል። ይህም ትክክል ነው። (መዝሙር 139:13-16) አንጐል፣ ልብ፣ ሳንባ፣ ዓይን እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች በሙሉ በእናት ማህፀን ውስጥ በሚገኘው የዳበረ እንቁላል ውስጥ የዘር መለያ ኮድ (genetic code) ውስጥ የተመዘገቡ ናቸው። ይህ መለያ ኮድ እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል መቼ እንደሚሠራ የሚገልፅ የጊዜ ሠሌዳም አለው። እስቲ አስቡት! ይህ ስለ ሰው የአካል ክፍሎች አሠራር የሚገልጸው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈው ሳይንቲስቶች የዘር መለያን ኮድ (genetic code) ከማወቃቸው ከ3,000 ዓመት በፊት ነው።
የእንስሳት ባሕርይ፦ መጽሐፍ ቅዱስ “ጥንቸልም ያመሰኳል” ይላል። (ዘሌዋውያን 11:6) ፍራንስዋ ቡርሊየር (ዘ ናቹራል ሂስትሪ ኦቭ ማማልስ 1964 በገጽ 41 ላይ) እንዲህ ብለዋል፦ “ጥንቸሎች የበሉትን ምግብ መልሰው በመዋጥ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁለት ጊዜ በአንጀታቸው እንዲያልፍ የማድረግ ልማድ አላቸው። ለማዳ ጥንቸሎች ማታ የሚጥሉትን ፍግ ሳያኝኩ መልሰው ይውጣሉ። ሲነጋም በሆዳቸው ከነበረው ምግብ ግማሽ ያህል የሆነው በጠጥ ሆኖ ይወጣል። በዱር የሚኖሩ ጥንቸሎች ይህን የሚያደርጉት በቀን ሁለት ጊዜ ነው። በአውሮፓ ጥንቸሎችም ላይ ተመሳሳይ የሆነ ባሕርይ ታይቷል።” ይህን አመለካከት አስመልክቶ ማማልስ ኦቭ ዘ ወርልድ የተባለው መጽሐፍ (በኢ. ፒ. ዎከር 1964 ቮልዩም 2 ገጽ 647) “ይህ ልማድ ጡት አጥቢ እንስሳት ከሚያደርጉት የማመንዠክ ልማድ ጋር ሳይመሳሰል አይቀርም” ብለዋል።
የመሬት ቁፋሮ ጥናት፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስማቸው የተጠቀሱት ነገሥታት፣ ከተሞች እና ሕዝቦች በሸክላ ሰሌዳዎች፣ በሸክላ ዕቃዎች፣ በተለያዩ ቅርጾችና በሌሎችም ተመሣሣይ ነገሮች ላይ ተገኝተዋል። ለምሳሌ ያህል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ኬጢያውያን ተብለው የሚጠሩት በእርግጥ ጥንት የነበሩ ሕዝቦች ናቸው። (ዘጸአት 3:8) ሰር ቻርለስ ማርስተን ዘ ባይብል ካምስ አላይቭ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እንዳያምኑ ያደረጉና የመጽሐፍ ቅዱስን አስተማማኝነት ያዋረዱ ሁሉ በተገኙት ማስረጃዎች አማካኝነት ራሳቸው ተዋርደዋል። አዋቂነታቸውም ውድቅ ሆኖአል። በአካፋ አማካኝነት የተገኙት ማስረጃዎች አጠያያቂ የነበሩትን ነገሮች ስላረጋገጡ አፍራሽ ትችቶችን በማስወገድ ላይ ናቸው።”
የመሬት ቁፋሮ ጥናት መጽሐፍ ቅዱስን በብዙ መንገዶች ደግፎአል። ለምሳሌ ያህል በዘፍጥረት ምዕራፍ 10 ላይ የተጠቀሱት ቦታዎችና ስሞች ትክክል መሆናቸውን አረጋግጦአል። የንግድና የሃይማኖት ማዕከል የነበረችውና አብርሃም የተወለደባት የከለዳውያን ከተማ የነበረችው የዑር ከተማ በመሬት ቆፋሪዎች ተገኝታለች። (ዘፍጥረት 11:27-31) በደቡባዊው ምሥራቅ የኢየሩሳሌም ክፍል ከግዮን ወንዝ ከፍ ብሎ ባለው ሥፍራ ትገኝ የነበረችውና ዳዊት ከኢያቡሳውያን የወሰዳት ከተማ በመሬት ቆፋሪዎች ተገኝታለች። (2 ሳሙኤል 5:4-10) ንጉሥ ሕዝቅያስ ባሠራው የውኃ መተላለፊያ ቦይ አንደኛ መውጫ ላይ የነበረው የሰሊሆም የድንጋይ ጽሑፍ በ1880 ላይ ተገኝቷል። (2 ነገሥት 20:20) ባቢሎን በ539 ከዘ.አ.በ በቂሮስ እጅ መውደቋ በ19ኛው መቶ ዘመን እ.ዘ.አ ተቆፍሮ በተገኘው የናቦኒደስ ዜና መዋዕል ላይ ተገልጸዋል። በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት ሁኔታዎች ከፔርስ ቦሊስ በተገኘው የድንጋይ ጽሑፍ እና በሹሻን ወይም በሱሳን በ1880 እስከ 1890 ተቆፍሮ በተገኘው በንጉሥ አርጤክስስ ቤተመንግሥት ውስጥ በተገኙት ማስረጃዎች ተረጋግጧል። 1961 በቂሳርያ ከተማ የነበረው የሮማውያን ትያትር ቤት ውስጥ የተገኙት ቅርሳ ቅርሶች ኢየሱስ እንዲሰቀል አሳልፎ የሰጠው የሮማ ገዢ የነበረው ጴንጤናዊው ጲላጦስ በእርግጥ የነበረ ሰው መሆኑን አረጋግጠዋል።—ማቴዎስ 27:11-26
አስትሮኖሚ፦ ሰዎች ምድር ክብ መሆኗን ከማወቃቸው ከ2,700 ዓመታት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ “እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀመጣል” ሲል ጽፏል። (ኢሳይያስ 40:22) “ክብ” ተብሎ የተተረጐመው ቹግ የተባለው የዕብራይስጥ ቃል “ጠፈር” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። (ኤ ኮንኮርዳንስ ኦቭ ሂብሩ ኤንድ ካልዲ ስክሪፕቸር በቢ.ዴቪድሰን የተፃፈ) በተጨማሪም ምድርን ከህዋ ላይ፣ አንዳንድ ጊዜም በጣም ከፍ ብሎ ከሚበርር አውሮፕላን ላይ ሆነው ሲመለከቷት የምድር አድማስ “ክብ” ሆኖ ይታያል። ኢዮብ 26:7ም አምላክ “ምድርን በባዶ ሥፍራ ላይ እንዳንጠለጠላት” ይናገራል። ይህም እውነት ነው። ምክንያቱም አስትሮነመሮች (የከዋክብት ተመራማሪዎች) እንደሚያውቁት ምድርን ደግፎ የያዛት ምንም የሚታይ ነገር የለም።
ቦታኒ (የአዝርዕትና የተክሎች ጥናት)፦ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘር ሁሉ አነስተኛ የሰናፍጭ ቅንጣት ነው ስላለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክል አይደለም በማለት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። (ማርቆስ 4:30-32) ኢየሱስ ትንሿ ብሎ የጠቀሳት 0.039-0.063 ኢንች ስፋት ያላትን (ብራሲካ ኒግራ ወይም ሲናፐስ ኒግራ የተባለችውን) ጥቁሯን የሰናፍጭ ዘር ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ኦርቺድ የተባለው ተክል ብናኝ ዱቄት የሚያክል መጠን ያለው ዘር አለው። ኢየሱስ ግን ይናገር የነበረው የኦርቺድ ዘር ለሚዘሩ ሰዎች አልነበረም። እነዚህ የገሊላ አይሁዳውያን በአገራቸው የሚኖሩ ገበሬዎች ከሚዘሩአቸው ዘሮች ሁሉ የምታንሰው የሰናፍጭ ዘር እንደሆነች ያውቃሉ። እዚህ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምር የነበረው ስለ አምላክ መንግሥት ነው እንጂ ስለ ቦታኒ ወይም ስለ ተክሎች ባሕርይ አልነበረም።
ጂኦሎጂ(የሥነ ምድር ጥናት)፦ የታወቁት የጂኦሎጂ ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ዋለስ ፕራት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምድር አፈጣጠር የሚሰጠውን መግለጫ አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፦ “ጂኦሎጂስት እንደመሆኔ መጠን ስለ ምድር አመሠራረት እና ስለ ሕይወት አመጣጥ ያለንን ዘመናዊ አስተሳሰብ ከብት አርቢ ለሆኑ ዘላኖች ማለትም የዘፍጥረት መጽሐፍ ለተጻፈላቸው ዓይነት ሰዎች አስረዳ ተብዬ ብጠየቅ በመጀመሪያ የዘፍጥረት ምዕራፍ ላይ የተጻፈውን አገላለጽ ከመጠቀም የተሻለ ነገር ላደርግ አልችልም” ብለዋል። ፕራት እንዳስተዋሉት በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ስለ ውቅያኖስ አመሠራረት፣ ስለ ምድር መገለጥ፣ ስለ ባሕር እንስሳት መገኘት፣ ስለ አዕዋፍ እና ስለ አጥቢ እንስሳት መገኘት የተገለጸው ቅደም ተከተል ከዘመናት አቆጣጠር ጋር ይስማማል ብለዋል።
ሕክምና፦ ሲ ሬይመር ስሚዝ ዘ ፊዚሽያን ኤግዛሚንስ ዘ ባይብል (ሐኪም መጽሐፍ ቅዱስን ሲመረምር) በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ “መጽሐፍ ቅዱስ ሕክምናን አስመልክቶ የሚናገረው ነገር ሁሉ ትክክለኛ መሆኑ በጣም ያስደንቀኛል . . . እንደ እባጭ፣ ቁስል፣ ስለመሳሰሉት በሽታዎች የተገለጹት የአስተካከም ዘዴዎች በዘመናዊው የሕክምና ዘዴም ቢሆን የሚሠራባቸው ናቸው። እስከ አሁን ድረስ በብዙ ሰዎች የሚታመኑ አጉል እምነቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ዓይነት ቅጠል በኪስ ውስጥ መያዝ ቁርጥማት እንዳይዝ ይከላከላል፣ እንቁራሪት በእጅ መያዝ ኪንታሮት ያመጣል፣ ከሱፍ የተሠራ ቀይ ጨርቅ አንገት ላይ መጠቅለል የጉሮሮ ቁስል ይፈውሳል፣ አንድ ሕፃን የሚታመመው ትላትሎች ስላሉበት ነው እንደሚሉት አጉል እምነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኙም። ይህ ራሱ የሚያስደንቀኝና መጽሐፉ መለኮታዊ ምንጭ እንዳለው የሚያረጋግጥ ሆኖልኛል” ብለዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ታሪክ የሚናገራቸው ነገሮች አስተማማኝነታቸው
ጠበቃ የሆኑት ኤርዊን ኤች ሊንተን ኤ ሎየር ኤግዛምንስ ዘ ባይብል (ጠበቃው መጽሐፍ ቅዱስን ሲመረምር) በሚለው መጽሐፋቸው “ስለ ፍቅር የተጻፉ ልብ ወለድ መጽሐፎች፣ አፈ ታሪኮች እና ሐሰተኛ የምሥክርነት ቃሎች የሚተርኩአቸው ነገሮች የት ቦታ እንደተፈጸሙና መቼ እንደተፈጸሙ አይገልጹም። ስለ ሆነም እኛ ጠበቆች አንድ ቃል እውነተኛ መሆኑን የሚያረጋግጠው የመጀመሪያ ሕግ ነገሩ የተፈጸመበት ቦታና ጊዜ መገለጹ ነው የምንለውን ደንብ እንደጣሱ እናውቃለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ግን የተፈጸሙበት ጊዜና ቦታ መጠቀሱ በከፍተኛ ደረጃ ትክክል መሆናቸውን ያሳያል” ብለዋል።
የዚህን ነጥብ እውነተኛነት ለማሳየት ሊንተን የጠቀሱት ሉቃስ 3:1, 2ን ነው። እዚህ ላይ የዚህ ወንጌል ጸሐፊ ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን የጀመረበትን ወቅት ለማሳወቅ የሰባት ባለሥልጣኖችን ስም ጠቅሷል። ሉቃስ የገለጻቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ልብ በሉ። “ጢባርዮስ ቄሣርም በነገሠ በአሥራ አምስተኛይቱ ዓመት፣ ጴንጤናዊው ጲላጦስም በይሁዳ ሲገዛ፣ ሄሮድስም በገሊላ የአራተኛው ክፍል ገዥ፣ ወንድሙ ፊልጶስም በኢጡርያስ በጥራኮኒዶስም አገር የአራተኛው ክፍል ገዥ፣ ሊሳኒዮስም በሳቢላኒስ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሆነው ሳሉ፣ ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ።”
መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በመሳሰሉ ዝርዝር መረጃዎች የተሞላ ነው። በተጨማሪም እነዚህ የወንጌል ክፍሎች የተጻፉት የአይሁድ፣ የግሪክ እና የሮማውያን ባሕሎች እጅግ በዳበሩበት ጊዜ ላይ ነበር። የጠበቆች፣ የጸሐፊዎችና የመሳሰሉት ባለሙያዎች ዘመን ነበር። ስለዚህ በወንጌሎችም ውስጥ ሆነ በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ያሉት ዝርዝር ጉዳዮች ትክክለኛ ባይሆኑ ኖሮ ሐሰትነታቸው ይጋለጥ ነበር። ይሁን እንጂ የዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለ ሰው ይኖር እንደነበረ አረጋግጠዋል። የሮማ ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ታሲተስ ስለ ኢየሱስና ስለ ተከታዮቹ ሲጽፍ “ክርስቲያን የሚለው ስያሜ መገኛ የሆነው ክርስቶስ በጴንጤናዊው ጲላጦስ እጅ የመጨረሻውን አሰቃቂ ቅጣት ተቀብሎአል” ብሏል። (አናልስ 15ኛ መጽሐፍ፣ 44) መጽሐፍ ቅዱስ የሚተርካቸው ታሪኰች እውነተኛ መሆናቸው መጽሐፉ አምላክ ለሰው ዘሮች የሰጠው ስጦታ መሆኑን ያረጋግጥልናል።
ከሁሉም የሚበልጠው ማረጋገጫ
የመሬት ቁፋሮ፣ አስትሮኖሚ፣ ታሪክ እና ሌሎችም የእውቀት መስኮች መጽሐፍ ቅዱስን የሚደግፉ ቢሆኑም እምነታችን የተመሠረተው በእነዚህ ማረጋገጫዎች ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ የተጻፈ የአምላክ ስጦታ መሆኑን ከሚያረጋግጡት ብዙ ማስረጃዎች መካከል በውስጡ የተገለጹት ትንቢቶች በትክክል ከመፈጸማቸው የበለጠ ማረጋገጫ አይገኝም።
ይሖዋ አምላክ የእውነተኛ ትንቢት ምንጭ ነው። በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏል፦ “እነሆ፣ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፣ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ።” (ኢሳይያስ 42:9) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ጸሐፊዎቹ በአምላክ መንፈስ ቅዱስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል ተመርተው እንደጻፉት ይናገራል። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲጽፍ “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ ተጽፈዋል” ብሎአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16 አዓት) ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ “ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ”ሲል ጽፎአል። (2 ጴጥሮስ 1:20, 21) እስቲ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን እንመልከት።
በብዙ መቶ ከሚቆጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መካከል በጥንቱ መካከለኛው ምስራቅ ከ1500 ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ አስፈሪ መንግሥት የነበረው የአሦር ዋና ከተማ የነበረችውንና “የደም ከተማ” የተባለችውን ነነዌን አስመልክቶ የተነገረው ትንቢት ይገኝበታል። (ናሆም 3:1) ነነዌ የነበራትን ከፍተኛ ኃይል አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እርሱም [አምላክ] በሰሜን ላይ እጁን ይዘረጋል፣ አሦርንም ያጠፋል ነነዌንም ባድማ፣ እንደ በረሃም ደረቅ ያደርጋታል። መንጎችም የምድርም አራዊት ሁሉ በውስጥዋ ይመሰጋሉ ይብራና ጃርት በዓምዶችዋ መካከል ያድራሉ ድምፃቸው በመስኮቶችዋ ይጮኻል፤ የዝግባም እንጨት ሥራ ይገለጣልና በመድረኮችዋ ላይ ጥፋት ይሆናል።” (ሶፎንያስ 2:13, 14) በዛሬው ጊዜ አገር ጐብኚዎች የጥንቷ የነነዌ ከተማ በነበረችበት ቦታ ሊያዩ የሚችሉት ጉብታዎችን ብቻ ነው። በተጨማሪም በትንቢት እንደተነገረው የበጐች መንጋ ሣር ሲግጡባት ይታያሉ።
የአምላክ ነቢይ የነበረው ዳንኤል ሁለት ቀንዶች የነበሩት አንድ አውራ በግና በዓይኖቹ መካከል አንድ ታላቅ ቀንድ የነበረው አንድ አውራ ፍየል በራእይ ተመልክቶ ነበር። አውራው ፍየል በጉን መትቶ ሁለቱን ቀንዶቹን ሰበረበት። በምትካቸውም ሌላ አራት ቀንዶች በቀሉለት። (ዳንኤል 8:1-8) መልአኩ ገብርኤል ይህንን ሲገልጽ እንዲህ ብሎአል፦ “ባየኸው በአውራው በግ ላይ የነበሩ ሁለቱ ቀንዶች እነርሱ የሜዶንና የፋርስ ነገሥታት ናቸው። አውራውም ፍየል የግሪክ ንጉሥ ነው በዓይኖቹም መካከል ያለው ታላቁ ቀንድ መጀመሪያው ንጉሥ ነው። እርሱም በተሰበረ ጊዜ በእርሱ ፋንታ አራቱ እንደተነሡ፣ እንዲሁ ከወገኑ አራት መንግሥታት ይነሣሉ፣ ነገር ግን በኃይል አይተካከሉትም።” (ዳንኤል 8:20-22) ከታሪክ መረዳት እንደሚቻለው በባለ ሁለት ቀንድ አውራ በግ የተመሰለው የሜዶ ፋርስ መንግሥታት በግሪክ ንጉሥ ተገልብጧል። የአውራው ፍየል “ታላቅ ቀንድ” የሚያመለክተው ታላቁ እስክንድርን ነው። እርሱ ከሞተ በኋላ አራቱ ጄነራሎች ይህን “ታላቅ ቀንድ” ተክተው አራት መንግሥታት አቋቋሙ።
በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች (“በብሉይ ኪዳን”) ውስጥ የሚገኙ በርካታ ትንቢቶች ከኢየሱስ ሕይወት ጋር ግንኙነት ባላቸው ነገሮች ተፈጽመዋል። በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች (“አዲስ ኪዳን”) ጸሐፊዎች ከእነዚህ ትንቢቶች አንዳንዶቹ እንዴት በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸሙ ገልጸዋል። ለምሳሌ ያህል የወንጌል ጸሐፊው ማቴዎስ ኢየሱስ ከድንግል እንደሚወለድ፣ መንገድ ጠራጊ እንደሚኖረው፣ በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚገባ የሚናገረው ትንቢት መፈጸሙን ጠቁሟል። (ከማቴዎስ 1:18-23፤ 3:1-3፤ 21:1-9 ከኢሳይያስ 7:14፤ 40:3፤ ዘካርያስ 9:9 ጋር አወዳድር) የእነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜ በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ የተጻፈ የአምላክ ስጦታ መሆኑን ያረጋግጡልናል።
በዘመናችን በመፈጸም ላይ የሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደምንኖር ያረጋግጡልናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ጦርነት፣ የምግብ እጥረት፣ ቸነፈርና ከመቼውም ጊዜ የበለጠ መጠንና ስፋት ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ኢየሱስ በመንግሥቱ መገኘቱን የሚያሳዩ ምልክቶች ክፍል ናቸው። (ማቴዎስ 24:3-14፤ ሉቃስ 21:10,11) በመፈጸም ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የምትገዛዋ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ቅንና ታዛዥ ለሆኑ የሰው ዘሮች ዘለቄታ ያለው ደስታ የሚያመጣው አዲስ ዓለም በቅርቡ እንደሚመጣ ያረጋግጣል።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1-5
ፍጻሜያቸውን ያገኙ “የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች” በሚለው ሠንጠረዥ ሥር በመቶ ከሚቆጠሩት ትንቢቶች መካከል ልንዘረዝራቸው የቻልናቸውን ጥቂቶቹን ብቻ አቅርበናል። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተገለጹት አንዳንድ ትንቢቶች የተፈጸሙበት ሁኔታ በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጾአል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በመፈጸም ላይ ለሚገኙት ትንቢቶች የተለየ ትኩረት መስጠት ይገባናል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተተነበዩ አንዳንድ የዓለም ሁኔታዎችን ራስህ ልትገነዘብ ትችል ይሆናል። ታዲያ ለምን ሌሎች ትንቢቶችንም አትመረምርም? የይሖዋ ምሥክሮች የምትጠይቃቸውን ተጨማሪ መረጃዎች ሊያካፍሉህ ፈቃደኞች ናቸው። ልዑሉን አምላክና ዓላማውን ለማወቅ የምታደርገው ጥረት መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ የተጻፈ የአምላክ ስጦታ መሆኑን እንድታምን ይርዳህ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
ፍጻሜያቸውን ያገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች
ትንቢቶች ፍጻሜው
ዘፍጥረት 49:10 ይሁዳ የእሥራኤልን ነገሥታት የዘር ግንድ መሥርቶአል
ሶፎንያስ 2:13, 14 ነነዌ በ632 ከዘ.አ.በ. አካባቢ ጠፋች
ኤርምያስ 25:1-11፤ ኢየሩሳሌም ከተወረረች በኋላ የ70 ዓመት ባድማነት ዘመን ተጀመረ
ኢሳይያስ 13:1, 17-22፤ ቂሮስ ባቢሎንን ድል አደረገ፣ አይሁዶች ወደ አገራቸው ተመለሱ
ዳንኤል 8:3-8, 20-22 ሜዶ ፋርስ በታላቁ እስክንድር ተገለበጠች፣
የግሪክ መንግሥት ተከፋፈለ
ኢሳይያስ 7:14፤ ኢየሱስ በቤቴል ከድንግል ተወለደ
ዳንኤል 9:24-26 የኢየሱስ መሲሕ ሆኖ መቀባት (በ29 እ.ዘ.አ)
ኢሳይያስ 9:1, 2 የኢየሱስ የማስተማር አገልግሎት በገሊላ ጀመረ
ኢሳይያስ 53:4, 5, 12 ኢየሱስ ቤዛዊ መስዋዕት ሆኖ መሞቱ
መዝሙር 22:18 በኢየሱስ ልብሶች ላይ እጣ ተጣጣሉ
መዝሙር 16:10 ኢየሱስ በሦስተኛው ቀን ከሙታን መነሳቱ
ሉቃስ 19:41-44፤ 21:20-24 የኢየሩሳሌም በሮማውያን መጥፋት
(70 እ.ዘ.አ)
ሉቃስ 21:10, 11፤ ጦርነቶች፣ ራብ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣
ማቴዎስ 24:3-13 ቸነፈር፣ ዓመፅ፣ እና የመሳሰሉት
2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 “በመጨረሻው ቀን” የምንኖር መሆናችንን ይጠቁማሉ
ማቴዎስ 24:14፤ የአምላክ መንግሥት እንደተመሠረተችና
ኢሳይያስ 43:10፤ በቅርቡ ተቃዋሚዎቿን ሁሉ እንደምትደመስስ የሚገልጸውና
መዝሙር 2:1-9 በዓለም በሞላ በይሖዋ ምስክሮች
የሚደረገው ስብከት
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ ጦርነት፣ ራብ፣ ቸነፈርና የመሬት መንቀጥቀጥ በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ቢሆንም አዲስ የሰላምና የደስታ ዓለም እየቀረበ እንዳለ ከአድማስ እየታየ ነው።