የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 5/15 ገጽ 10-15
  • ጋብቻ ደስታ የሚገኝበት ብቸኛ ቁልፍ ነውን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጋብቻ ደስታ የሚገኝበት ብቸኛ ቁልፍ ነውን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ደስተኛ እንድንሆን የሚያደርጉን ምክንያቶች
  • “በጌታ ይሁን እንጂ”
  • “በጌታ” ማግባት የማይቻል ሲሆን
  • እውነተኛ ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ
  • “ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የሚበልጥ”
  • ጋብቻ ደስታ የሚገኝበት ብቸኛ ቁልፍ አይደለም
  • ይሖዋን በማገልገል የሚገኝ እውነተኛ ደስታ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ጋብቻ​—አፍቃሪ ከሆነው አምላክ የተገኘ ስጦታ
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
  • ነጠላነትንና ትዳርን አስመልክቶ የተሰጠ ጥበብ ያዘለ ምክር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • መጽሐፍ ቅዱስ ሳያገቡ ስለመኖርና ስለ ትዳር ምን ይላል?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 5/15 ገጽ 10-15

ጋብቻ ደስታ የሚገኝበት ብቸኛ ቁልፍ ነውን?

“ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነፃነት አላት። እንደ ምክሬ ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት።”—1 ቆሮንቶስ 7:39, 40

1. ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ይሖዋ ምን ይገልጻሉ? ለፍጥረቶቹስ ምን አድርጐላቸዋል?

ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት) እርሱ የመልካም ስጦታዎች ሁሉ ለጋስ ሰጪ እንደመሆኑ መጠን የማሰብ ችሎታ ላላቸው ፍጡሮቹ በሙሉ ማለትም ለመላእክትም ሆነ ለሰው ልጆች በአገልግሎት እንዲደሰቱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ አዘጋጅቶአል። (ያዕቆብ 1:17) ከዚህም በላይ የወፎች ዝማሬ፣ የቡችሎች ቡረቃ፣ የዓሣዎች ጭፈራ እንስሳትም በተወሰነላቸው የመኖሪያ አካባቢ እንዲደሰቱ ሆነው የተፈጠሩ መሆናቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። እንዲያውም መዝሙራዊው፦ “የይሖዋ ዛፎች እርሱም የተከላቸው የሊባኖስ ዝግባዎች ረክተዋል” ብሎአል።—መዝሙር 104:16

2. (ሀ) ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ በማድረግ እንደሚደሰት የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? (ለ) የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ምን የሚደሰቱበት ምክንያት ነበራቸው?

2 ኢየሱስ የይሖዋ ትክክለኛ ነጸብራቅ ነው። (ዕብራውያን 1:3) በዚህም ምክንያት ኢየሱስ “ደስተኛና ብቻውን የሆነ ገዢ” መባሉ የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። (1 ጢሞቴዎስ 6:15) እርሱም የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ ምግብ ከመብላት የበለጠ ደስታ እንደሚያስገኝ እንዲሁም ለይሖዋ የጠለቀ አክብሮትና ጤናማ የሆነ ፍርሃት በማሳየት ደስታ ልናገኝ እንደምንችል የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። (መዝሙር 40:8፤ ኢሳይያስ 11:3፤ ዮሐንስ 4:34) ሰባዎቹ ደቀመዛሙርት ከመንግሥት ስብከት ጉዞአቸው ተመልሰው ስላጋጠማቸው ሁኔታ በደስታ በነገሩት ጊዜ ኢየሱስ “በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት” አድርጓል። የተሰማውን ደስታ ለአባቱ በጸሎት ከገለጸ በኋላ ወደ ደቀመዛሙርቱ ዘወር ብሎ፦ “የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው። እላችኋለሁና፣ እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩምም፣ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወድደው አልሰሙም” አለ።—ሉቃስ 10:17-24

ደስተኛ እንድንሆን የሚያደርጉን ምክንያቶች

3. ለደስታ ምክንያት የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

3 እኛስ በዚህ በመጨረሻው ቀን በይሖዋ ቃልና ዓላማ መሠረት የሚፈጸሙትን ነገሮች የራሳችን ዓይኖች ለማየት በመቻላቸው ደስ መሰኘት አይገባንምን? እንደ ኢሳይያስ፣ ዳንኤልና ዳዊት የመሳሰሉት የጥንት ታማኝ ነቢያትና ነገሥታት ሊረዱ ያልቻሉአቸውን ትንቢቶች ለመረዳት በመቻላችን ልንደሰት አይገባንምን? ደስተኛ ገዥ በሆነው ንጉሣችን በኢየሱስ ክርስቶስ መሪነት ሥር ሆነን ደስተኛ የሆነውን አምላክ ይሖዋን ለማገልገል በመቻላችን ደስ አልተሰኘንምን? በእርግጥ ደስ ተሰኝተናል።

4, 5. (ሀ) በይሖዋ አገልግሎት ደስተኞች ሆነን ለመቀጠል ከምን መራቅ ይገባናል? (ለ) ለደስታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ይህስ ምን ጥያቄ ያስነሳል?

4 ይሁን እንጂ በይሖዋ አገልግሎት እየተደሰትን ለመኖር ከፈለግን ለደስታችን የግድ አስፈላጊ ናቸው የምንላቸውን የራሳችንን ቅድመ ሁኔታዎች በዓለማዊ አስተሳሰቦች ላይ መመሥረት የለብንም። ይህ ዓለም ለደስታ አስፈላጊ ናቸው የሚላቸው ነገሮች በቀላሉ አስተሳሰባችንን ሊያጨልሙብን ይችላሉ። ዓለም ለደስታ አስፈላጊ ናቸው ከሚላቸው ነገሮች መካከል ቁሳዊ ሀብት፣ የቅንጦት ኑሮና የመሳሰሉት ይገኙበታል። ይህ ዓለም ስለሚያልፍ በእነዚህ ነገሮች ላይ የተመሠረተ ማንኛውም “ደስታ” ዘላቂ አይሆንም።—1 ዮሐንስ 2:15-17

5 አብዛኞቹ የይሖዋ ውስን አገልጋዮች ዓለማዊ ግቦች ላይ መድረስ እውነተኛ ደስታ እንደማያመጣ ይገነዘባሉ። ለአገልጋዮቹ እውነተኛ ደስታ የሚያመጡትን መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ነገሮች የሚሰጠው ሰማያዊ አባታችን ብቻ ነው። “በታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል ለሚሰጠን መንፈሳዊ ምግብ ምን ያህል አመስጋኞች መሆን ይገባናል! (ማቴዎስ 24:45-47) ከፍቅራዊው የአምላክ እጅ ለምንቀበለው ሥጋዊ ምግብና ሌሎች ቁሳዊ ነገሮችም አመስጋኞች ነን። ከዚህም በተጨማሪ ጋብቻና ከጋብቻ ጋር የተያያዘው የቤተሰብ ኑሮ የሚያመጣው ደስታ ግሩም ስጦታ ነው። ኑአሚን ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ምራቶቿ ያላት ልባዊ ምኞት በሚከተሉት ቃላት መገለጹ ምንም አያስደንቅም፦ “[ይሖዋ (አዓት)] በየባላችሁ ቤት ዕረፍት ይስጣችሁ” አለቻቸው። (ሩት 1:9) ስለዚህ ጋብቻ ትልቅ ደስታ የሚገኝበትን በር ሊከፍት የሚችል ቁልፍ ነው። ይሁን እንጂ ለደስተኛ ሕይወት በር የሚከፍት ቁልፍ ጋብቻ ብቻ ነውን? በተለይ ወጣቶች ጋብቻ ለደስታ ብቸኛ ቁልፍ መሆኑንና አለመሆኑን በጥንቃቄ መመርመር ይኖርባቸዋል።

6. በዘፍጥረት መጽሐፍ መሠረት የመጀመሪያው የጋብቻ ዓላማ ምን ነበር?

6 መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻ የጀመረበትን ሁኔታ ሲተርክ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረው በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው። ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም።” (ዘፍጥረት 1:27, 28) ይሖዋ የጋብቻን ሥርዓት በማቋቋሙ ምክንያት አዳም ተጨማሪ ሰብአዊ ፍጥረታትን ለማስገኘት እንዲሁም የሰውን ዘር ለማብዛት አገልግሏል። ይሁን እንጂ ጋብቻ ከዚህ የበለጠ ነገርንም ይጨምራል።

“በጌታ ይሁን እንጂ”

7. አንድ አበው ብርቱ ጥንቃቄ ያደረገው የትኛውን መሠረታዊ የጋብቻ ሕግ ለመፈጸም ነበር?

7 ጋብቻን ያቋቋመው ይሖዋ ስለሆነ ለአገልጋዮቹ ደስታ የሚያመጣላቸው ጋብቻ ማሟላት የሚኖርበትን ሕግና ሥርዓት ያወጣል ብለን እንጠብቅበታለን። ሕጉ ከመሰጠቱ በፊት የአበው ዘመን ይሖዋን ከማያመልኩ ሰዎች ጋር በጋብቻ መተሳሰር የተከለከለ ነገር ነበር። አብርሃም ለልጁ ለይስሐቅ ከከነዓናውያን ሴቶች ሚስት እንዳያመጣለት አገልጋዩን ኤሊዔዘርን በይሖዋ አምሎታል። ኤሊዔዘርም ይሖዋ ለጌታው ልጅ የመረጣትን ሴት ለማግኘት አብርሃም ያዘዘውን በሙሉ ፈጽሞአል፣ ሩቅ መንገድም ተጉዞአል። (ዘፍጥረት 24:3, 44) ስለዚህ ይስሐቅ ርብቃን አገባ። ልጃቸው ዔሳው ግን አረማውያን ከነበሩት ኬጢያውያን መካከል መርጦ ሚስቶችን ባገባ ጊዜ እነዚህ ሚስቶቹ “የይስሐቅንና የርብቃን ልብ ያሳዝኑ ነበር።”—ዘፍጥረት 26:34, 35፤ 27:46፤ 28:1, 8

8. በሕጉ ቃል ኪዳን መሠረት በጋብቻ ላይ ምን እገዳ ተጥሎ ነበር? ለምንስ?

8 የሕጉ ቃል ኪዳን ይሠራ በነበረበት ዘመን ከተጠቀሱት የከነዓናውያን ነገዶች ወንዶችን ወይም ሴቶችን ማግባት የተከለከለ ነበር። ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚከተለው በማለት አዝዞ ነበር፦ “ከእነርሱም ጋር አትጋባ፤ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፣ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ። እንዳይከተለኝ ሌሎችንም አማልክት እንዲያመልክ ልጅህን ያስታልና፤ [የይሖዋ (አዓት)] ቁጣ ይነድባችኋል፣ ፈጥኖም ያጠፋችኋል።”—ዘዳግም 7:3, 4

9. መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻን በሚመለከት ለክርስቲያኖች ምን ምክር ይሰጣል?

9 ስለዚህ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎችን ስለማግባት ተመሳሳይ ዕገዳ መደረጉ ሊያስደንቀን አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን እንዲህ በማለት መክሮአል፦ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፣ ጽድቅ ከአመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?” (2 ቆሮንቶስ 6:14, 15) ይህ ምክር በብዙ የኑሮ ዘርፎች የሚሠራ ሲሆን በተለይ በጋብቻ ላይ በትክክል የሚሠራ ነው። ጳውሎስ በሰጠው ግልጽ መመሪያ መሠረት የይሖዋ ውስን አገልጋዮች በሙሉ አንድን ሰው ለማግባት ከማሰባቸው በፊት ‘ከጌታ ጋር ኅብረት ያለው መሆኑን’ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 7:39 አዓት

“በጌታ” ማግባት የማይቻል ሲሆን

10. ብዙዎቹ ያላገቡ ክርስቲያኖች ምን በማድረግ ላይ ናቸው? ምን ጥያቄስ ይነሳል?

10 ብዙ ነጠላ ክርስቲያኖች የነጠላነትን ስጦታ በመኰትኰት የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ለመከተል መርጠዋል። እንዲሁም ብዙ ታማኝ ክርስቲያኖች ለጊዜው አምላካዊ የትዳር ጓደኛ ባለማግኘታቸውና “በጌታ” ሊያገቡ ባለመቻላቸው ምክንያት ትምክህታቸውን በይሖዋ ላይ በመጣል የማያምን ሰው ከማግባት ይልቅ በነጠላነታቸው ጸንተዋል። የአምላክ መንፈስ ነጠላነታቸውን በንጽሕና ለመጠበቅ የሚያስችሏቸውን እንደ ደስታ፣ ሰላም፣ እምነትና ራስን መግዛት የመሳሰሉትን ፍሬዎች በውስጣቸው እንዲያፈሩ ያደርጋል። (ገላትያ 5:22, 23) ይህን ለአምላክ የማደር ፈተና በተሳካ ሁኔታ በመወጣት ላይ ከሚገኙት መካከል በርከት የሚሉት ክርስቲያን እህቶቻችን ናቸው። እነዚህንም እህቶች በጥልቅ እናከብራቸዋለን። በብዙ አገሮች የእህቶች ቁጥር ከወንድሞች ይበልጣል። ስለዚህም በስብከቱ ሥራ እህቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው። በእርግጥም “ይሖዋ ራሱ ቃሉን ሰጠ፣ ምሥራቹን የሚናገር የሴቶች ሠራዊት በጣም ታላቅ ነው።” (መዝሙር 68:11) እርግጥ ካላገቡት ወንድና ሴት የአምላክ አገልጋዮች መካከል ብዙዎቹ ‘በፍጹም ልባቸው በይሖዋ ስለሚተማመኑና እርሱም ጐዳናቸውን ስለሚያቃናላቸው’ ታማኝነታቸውን በመጠበቅ ላይ ናቸው። (ምሳሌ 3:5, 6) ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ “በጌታ” ሊያገቡ ያልቻሉ ሁሉ ፈጽሞ ደስተኛ ሊሆኑ አይችሉም ማለት ነውን?

11. ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ካላቸው አክብሮት የተነሳ ነጠላ ሆነው የሚኖሩ ክርስቲያኖች ስለምን ነገር እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ?

11 ደስተኛ አምላክ የሆነው የይሖዋ አገልጋዮች መሆናችንንና በደስተኛው ገዥ በክርስቶስ ኢየሱስ ሥር ሆነን የምናገለግል መሆናችንን ፈጽሞ አንዘንጋ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተነገረውን እገዳ በማክበራችንና “በጌታ” የትዳር ጓደኛ ለማግኘት ባለመቻላችን ምክንያት ነጠላ ሆነን ለመኖር ብንገደድ ይሖዋና ኢየሱስ ደስታ ሳናገኝ እንድንኖር ይፈቅዳሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነውን? በፍጹም ምክንያታዊ አይደለም። ስለዚህ ሳናገባ ለመኖር ብንገደድም ደስተኛ መሆን ይቻላል ወደሚለው መደምደሚያ መድረስ አለብን። ያገባንም ሆንን ያላገባን ይሖዋ ደስተኛ ሊያደርገን ይችላል።

እውነተኛ ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ

12. ጋብቻን በሚመለከት ታዛዥ ያልነበሩት መላእክት ሁኔታ ምን ያመለክታል?

12 ለሁሉም የአምላክ አገልጋዮች የደስታ ቁልፍ ጋብቻ ብቻ አይደለም። መላእክትን እንደምሳሌ ውሰዱ። ከጥፋት ውሃ በፊት አንዳንድ መላዕክት በነጠላነታቸው ስላልረኩ ለመንፈሳዊ ፍጥረታት የማይገባ ፍላጎት በውስጣቸው ኰተኰቱ። ከዚያም ሴቶችን ለማግባት ሲሉ ሥጋዊ አካል ለበሱ። አምላክ እነዚህን ተገቢ “የመኖሪያ ቦታቸውን የተዉትን . . . መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል።” (ይሁዳ 6፤ ዘፍጥረት 6:1, 2) አምላክ መላእክት እንዲያገቡ ፈጽሞ እቅድ እንዳልነበረው ግልጽ ነው። ስለዚህ ጋብቻ ደስታ የሚያገኙበት ቁልፍ ሊሆን አይችልም ነበር።

13. ቅዱሳን መላእክት ደስተኛ የሆኑት ለምንድን ነው? ይህስ ለሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ምን ያመለክታል?

13 ይሁን እንጂ ታማኞቹ መላእክት ደስተኞች ናቸው። ይሖዋ የምድርን መሠረት ሲመሠርት “የማለዳ ከዋክብት የደስታ ዝማሬ፣ የአምላክ [መላእክታዊ] ልጆች የኅብረት ውዳሴ” አሰምተዋል። (ኢዮብ 38:7 ዘ ኒው ጀሩሳሌም ባይብል) ቅዱሳን መላእክት የሚደሰቱት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ የሚያዛቸውን ለመፈጸም የይሖዋ አምላክን ‘የቃሉን ድምፅ ለመስማት’ ዘወትር ነቅተው ስለሚጠባበቁ ነው። (መዝሙር 103:20, 21 አዓት የግርጌ ማስታወሻ) አዎ፣ ቅዱሳን መላእክት ደስታ የሚያገኙት ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ነው። ሰዎችም እውነተኛ ደስታ የሚያገኙበት ቁልፍ ይህ ነው። እንዲያውም አሁን አምላክን በደስታ በማገልገል ላይ የሚገኙ ያገቡ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለሰማያዊ ሕይወት በሚነሱበት ጊዜ አያገቡም። ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ፍጥረታት ሆነው የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ በመቻላቸው ይደሰታሉ። ስለዚህ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ ያገቡም ሆኑ ያላገቡ ደስተኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ምክንያቱም የእውነተኛ ደስታ መሠረቱ ፈጣሪን በታማኝነት ማገልገል ነው።

“ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የሚበልጥ”

14. በጥንትዋ የእሥራኤል ምድር ይኖሩ ለነበሩ አምላካዊ ባሕርይ የነበራቸው ጃንደረቦች ምን ትንቢታዊ ተስፋ ተሰጥቶ ነበር? ይህስ እንግዳ ነገር የሚሆነው ለምንድን ነው?

14 አንድ ታማኝ ክርስቲያን እስከ መጨረሻው ባያገባም እንኳን አምላክ ደስታ እንደሚሰጠው እርግጠኛ ሊሆን ይችላል። በጥንቷ እስራኤል ይኖሩ ለነበሩት ጃንደረቦች ከተነገሩት ከሚከተሉት ትንቢታዊ ቃሎች ማበረታቻ ማግኘት ይቻላል፦ “[ይሖዋ (አዓት)] ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና፦ በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ።” (ኢሳይያስ 56:4, 5) እነዚህ ጃንደረቦች ስማቸውን ለዘላለም የሚያስጠሩላቸው ሚስቶችና ልጆች እንደሚሰጣቸው ቃል ይገባላቸዋል ብለው የሚያስቡ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን “ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የሚበልጥ” ነገር ማለትም በይሖዋ ቤት ውስጥ ዘላለማዊ ስም እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸዋል።

15. ስለ ኢሳይያስ 56:4, 5 ትንቢት ፍጻሜ ምን ሊባል ይችላል?

15 እነዚህ ጃንደረቦች “ለአምላክ እስራኤል” ትንቢታዊ ጥላዎች እንደሆኑ ተደርገው የሚወሰዱ ከሆነ በይሖዋ መንፈሳዊ ቤት ወይም ቤተ መቅደስ ውስጥ ዘላለማዊ መኖሪያ የሚቀበሉትን ቅቡዓን ያመለክታሉ። (ገላትያ 6:16) በተጨማሪም ይህ ትንቢት በጥንትዋ እስራኤል ለነበሩና ከሙታን ለሚነሱ አምላካዊ አክብሮት የነበራቸው ጃንደረቦች ቃል በቃል ተፈጻሚነት እንደሚኖረው አያጠራጥርም። እነዚህ ሰዎች የክርስቶስን ቤዛዊ መስዋዕት ከተቀበሉና ይሖዋ የሚደሰትበትን ነገር መምረጣቸውን ከቀጠሉ በይሖዋ አዲስ ዓለም ውስጥ “የዘላለም ስም” ይቀበላሉ። በተጨማሪም ይህ ትንቢት በዚህ በመጨረሻው ጊዜ በይሖዋ አገልግሎት ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሲሉ የማግባትና ልጅ የመውለድ መብታቸውን ለሰዉት የ“ሌሎች በጐች” አባላት ተፈጻሚነት ይኖረዋል። (ዮሐንስ 10:16) ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ ሳያገቡና ልጅ ሳይወልዱ ሊሞቱ ይችላሉ። ታማኞች ከሆኑ ግን በትንሣኤ ሙታን “ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የሚበልጥ” “የማይጠፋ የዘላለም ስም” በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ያገኛሉ።

ጋብቻ ደስታ የሚገኝበት ብቸኛ ቁልፍ አይደለም

16. ጋብቻ ሁልጊዜ ደስታ አያመጣም ሊባል የሚችለው ለምንድነው?

16 አንዳንዶች ደስታና ጋብቻ ሊነጣጠሉ የማይችሉ ነገሮች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ በይሖዋ አገልጋዮች መካከል እንኳን ጋብቻ ሁልጊዜ ደስታ የሚያስገኝ አለመሆኑ የማይካድ ነው። ጋብቻ ለአንዳንድ ችግሮች መፍትሄ ይሆናል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ነጠላ ሰዎች ከሚያጋጥሙአቸው የበለጡ ችግሮችን ያስከትላል። ጳውሎስ ጋብቻ ‘የሥጋ መከራ’ ያመጣል ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ያገባ ሰው የሚጨነቅባቸውና ልቡ የሚከፈልባቸው ጊዜያት አሉ። ያገቡ ወንዶች ወይም ሴቶች አብዛኛውን ጊዜ ‘ሳይባክኑ ይሖዋን ማገልገል’ ያስቸግራቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 7:33-35

17, 18. (ሀ) አንዳንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ምን ሪፖርት አድርገዋል? (ለ) ጳውሎስ ምን ምክር ሰጥቶአል? ይህንንስ ምክር ሥራ ላይ ማዋል ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?

17 ነጠላነትም ሆነ ጋብቻ የአምላክ ስጦታዎች ናቸው። (ሩት 1:9፤ ማቴዎስ 19:10-12) ይሁን እንጂ ከሁለቱም የተሳካ ውጤት ለማግኘት በጥንቃቄ በጸሎት ማሰብ በጣም አስፈላጊ ነው። ብዙ ወጣት ምሥክሮች ገና በልጅነታቸው ስለሚያገቡ ወላጅነት የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመሸከም ከመድረሳቸው በፊት ልጅ እንደሚወልዱ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሪፖርት አድርገዋል። በዚህ ዓይነት በልጅነት ከተጀመሩት ትዳሮች አንዳንዶቹ ፈርሰዋል። ሌሎችም የጋብቻ ችግራቸውን ለመቋቋም ቢችሉም ከትዳራቸው ደስታ አላገኙበትም። ዊልያም ኮንግሬቭ የተባለው እንግሊዛዊ ትያትረኛ እንደጻፈው ቸኩለው ያገቡ “የብዙ ዘመን ጸጸት ያተርፋሉ። ”

18 አንዳንድ ወጣት ወንድሞች ቢያንስ ለጥቂት ዓመታት ያህል ነጠላ ሆነው እንዲኖሩ ስለሚፈለግባቸው በቤቴል አገልግሎት ወይም በጉባኤ አገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለመካፈል ፈቃደኛ እንደማይሆኑ አንዳንድ የክልል የበላይ ተመልካቾች ሪፖርት አድርገዋል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ አፍላ የጉልምስና ዕድሜ ከማለፉ በፊት ማግባት ጥሩ እንዳልሆነ አስጠንቅቋል። አፍላ ፍትወተ ሥጋ እስኪበርድ ድረስ ሳያገቡ መቆየት ተገቢ እንደሆነ ምክር ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 7:36-38) አንድ ሰው በነጠላነት የሚያሳልፈው ጊዜ ብዙ ተሞክሮና ማስተዋል እንዲያገኝና ጥሩ የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ ወይም በነጠላነት ለመኖር ጥንቃቄ የተሞላበት ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችል ብስለት ያስገኝለታል።

19. እንድናገባ የሚያስገድደን ምክንያት ከሌለን እንዴት ያለ አመለካከት ሊኖረን ይችላል?

19 አንዳንዶቻችን ጠንካራ የፍትወተ ሥጋ ፍላጎት ይሰማን የነበረበትን አፍላ የወጣትነት ዘመናችንን አልፈናል። አንዳንድ ጊዜ ከማግባት የሚገኙትን በረከቶች መለስ እያልን እናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ለእኛ የተሰጠን ስጦታ የነጠላነት ስጦታ ይሆናል። ይሖዋ በነጠላነታችን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንደምናገለግለውና ጋብቻ እንደማያስፈልገን ሊመለከት ይችላል። በተጨማሪም ማግባታችን አንዳንድ የአገልግሎት መብቶችን እንድንተው ሊያስገድደን ይችላል። ጋብቻ የሚያስፈልገን ነገር ካልሆነና በትዳር ጓደኛ ያልተባረክን ከሆንን አምላክ ለእኛ ያስቀመጠልን ሌላ ነገር ሊኖር ይችላል። ስለዚህ የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚሰጠን እምነት ይኑረን። ታላቅ ደስታ ሊገኝ የሚችለው አምላክ ለእኛ ያለውን ፈቃድ በትህትና ከመቀበል ነው። ለአሕዛብ ለሕይወት የሚሆን ንስሐ እንደሰጣቸው በማስተዋል “እግዚአብሔርን እንዳከበሩት” አይሁድ ወንድሞች መሆን ይገባናል።—ሥራ 11:1-18

20. (ሀ) እዚህ ላይ ለወጣት ክርስቲያኖች ነጠላነትን የሚመለከት ምን ምክር ተሰጥቶአል? (ለ) በደስታ ረገድ እውነት ሆኖ የኖረው የትኛው መሠረታዊ ነጥብ ነው?

20 ስለዚህ ጋብቻ ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ ሊሆን ቢችልም ወደ ችግር የሚያስገባም በር ሊሆን ይችላል። አንድ የተረጋገጠ ነገር አለ። ጋብቻ ደስታ የሚገኝበት ብቸኛው መንገድ አይደለም። ሁሉንም ነገር ስናገናዝብ በተለይ ወጣት ክርስቲያኖች በዛ ላሉ ዓመታት ነጠላ ሆነው ቢኖሩና ይህን የነጠላነታቸውን ዘመን ይሖዋን ለማገልገልና በመንፈሳዊ ለማደግ ቢጠቀሙበት የጥበብ መንገድ ይሆናል። ይሁን እንጂ በምንም ያህል ዕድሜና መንፈሳዊ ዕድገት ላይ የሚገኙ ቢሆኑም ራሳቸውን ያለአንዳች ገደብ ለአምላክ ለወሰኑ ሁሉ ምን ጊዜም እውነት ሆኖ የሚኖረው መሠረታዊ ነጥብ-እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ነው።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ የይሖዋ አገልጋዮች ደስተኛ የሆኑት ለምንድን ነው?

◻ ጋብቻ ወደ ትልቅ ደስታ የሚያስገባ ብቸኛ ቁልፍ ያልሆነው ለምንድን ነው?

◻ የትዳር ጓደኛን በመምረጥ ረገድ የይሖዋ ሕዝቦች ምን ይፈለግባቸው ነበር?

◻ ነጠላ ሆነው የሚኖሩ ክርስቲያኖች ደስተኛ መሆን ይችላሉ ብሎ ማመን ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ ስለ ጋብቻና ስለ ደስታ ምን የማይካድ ነገር አለ?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ