የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 6/15 ገጽ 12-16
  • የሰዎች አጥማጅ ሆኖ ማገልገል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የሰዎች አጥማጅ ሆኖ ማገልገል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘ሰዎችን ማጥመድ’
  • የሰዎች አጥማጆች
  • በሰው ዘሮች ባሕር ውስጥ ዓሣ ማጥመድ
  • “በጌታ” ቀን የሚፈጸመው ዓሣ የማጥመድ ሥራ
  • አራት ደቀ መዛሙርት ሰው አጥማጆች ሊሆኑ ነው
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • አራት ደቀ መዛሙርት ተጠሩ
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
  • በዓለም ውኃዎች ውስጥ ሰዎችን ማጥመድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ ማስገር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 6/15 ገጽ 12-16

የሰዎች አጥማጅ ሆኖ ማገልገል

“ኢየሱስ ስምዖንን፦ ‘አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ’ አለው።”​—ሉቃስ 5:10

1, 2. (ሀ) ዓሣ ማጥመድ በሰዎች ታሪክ ውስጥ ምን ሚና ተጫውቷል? (ለ) ከ2,000 ዓመታት ያህል በፊት ምን አዲስ ዓይነት ዓሣ የማጥመድ ሥራ ተጀመረ?

የሰው ልጅ በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት ለምግብ የሚሆነው ዓሣ ለማግኘት በምድር ባሕሮች፣ ሐይቆችና ወንዞች ዓሣ ሲያጠምድ ኖሮአል። በጥንታዊቱ ግብጽ ከአባይ ወንዝ የሚጠመዱ ዓሦች የዕለታዊ ምግብ ዋነኛ ክፍል ሆነው ነበር። በሙሴ ዘመን የአባይ ወንዝ ወደ ደምነት በተለወጠ ጊዜ ግብጻውያን የተቸገሩት ውኃ በማጣታቸው ብቻ ሳይሆን ዓሦቹ በመሞታቸው ምክንያት የሚበላ ዓሣ በማጣታቸው ጭምር ነበር። ይሖዋ አምላክ በሲና ተራራ ሕጉን ለእሥራኤላውያን በሰጠበት ጊዜም ስለሚበሉ ዓሦችና ንጹሕ ባለመሆናቸው ምክንያት መበላት ስለማይገባቸው ዓሦች ነግሮአቸው ነበር። ይህም እሥራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ ዓሣ እንደሚበሉና ከመካከላቸውም አንዳንዶቹ ዓሣ አጥማጆች እንደሚሆኑ ያመለክታል።​—ዘጸአት 7:20, 21፤ ዘሌዋውያን 11:9-12

2 ይሁን እንጂ 2,000 ዓመታት ያህል ቆይቶ ሌላ ዓይነት ዓሣ የማጥመድ ሥራ ተጀምሮአል። ይህም ዓሣ አጥማጆቹን ብቻ ሳይሆን ዓሦቹንም ጭምር የሚጠቅም መንፈሣዊ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ነው። ይህ ዓይነቱ ዓሣ የማጥመድ ሥራ በአሁኑም ጊዜ በመካሄድ ላይ ሲሆን በዓለም በሙሉ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ጥቅም አስገኝቶአል።

‘ሰዎችን ማጥመድ’

3, 4. ኢየሱስ ክርስቶስን የተከተሉት ሁለት ዓሣ አጥማጆች የትኞቹ ናቸው?

3 በ29 እዘአ ይህን አዲስ ዓይነት ዓሣ የማጥመድ ሥራ የሚያስተዋውቀው ሰው፣ ኢየሱስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ተጠመቀ። ከጥቂት ሣምንታት በኋላ ዮሐንስ ለሁለት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ እያመለከተ “እነሆ፣ የእግዚአብሔር በግ” አለ። ከደቀ መዛሙርቱም አንዱ እንድርያስ የተባለው ቶሎ ብሎ ወደ ወንድሙ ወደ ስምዖን ጴጥሮስ ሄደና “መሲሑን አገኘነው” ሲል ነገረው። እንድርያስና ስምዖን ሁለቱም ዓሣ አጥማጆች ነበሩ።​—ዮሐንስ 1:35, 36, 40, 41፤ ማቴዎስ 4:18

4 ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ዳርቻ ጴጥሮስና እንድርያስ ይኖሩበት ከነበረው አካባቢ ብዙም ሳይርቅ ለብዙ ሰዎች ይሰብክ ነበር። “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ ለተሰበሰቡት ሰዎች ይነግራቸው ነበር። (ማቴዎስ 4:13, 17) ጴጥሮስና እንድርያስ ኢየሱስ የሚናገረውን ለማዳመጥ በጣም ጓጉተው እንደነበረ መገመት ይቻላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በዚያ ቀን የሚናገረው ቃል መላ ሕይወታቸውን ለዘላለም እንደሚለውጠው አላሰቡም ነበር። ከዚህም በላይ ኢየሱስ በዚያ ጊዜ የተናገረውና ያደረገው ነገር በዚህ ዘመን ለምንኖረው ሁሉ ከፍተኛ ትርጉም አለው።

5. ዓሣ አጥማጁ ጴጥሮስ ኢየሱስን ሊያገለግል የቻለው እንዴት ነበር?

5 እንዲህ እናነባለን፦ “ሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃል እየሰሙ ሲያስጠብቡት ሳሉ፣ እርሱ ራሱ በጌንሳሬጥ ባሕር ዳር ቆሞ ነበር፤ በባሕር ዳርም ቆመው የነበሩትን ሁለት ታንኳዎች አየ፤ ዓሣ አጥማጆች ግን ከእነርሱ ውስጥ ወጥተው መረቦቻቸውን ያጥቡ ነበር።” (ሉቃስ 5:1, 2) በዚያ ዘመን በዓሣ አጥማጅነት የሚተዳደሩ ሰዎች ዓሣ የሚያጠምዱት በምሽት ነበር። እነዚህም ሰዎች ሌሊቱን ዓሣ ሲያጠምዱ ከቆዩ በኋላ መረባቸውን ያጥቡ ነበር። ኢየሱስ ለተሰበሰቡት ሰዎች ለመስበክ እንዲያመቸው በአንደኛው ታንኳ ለመጠቀም ወሰነ። “ከታንኳዎቹም የስምዖን ወደ ነበረች ወደ አንዲቱ ገብቶ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ በታንኳይቱም ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ነበር።”​—ሉቃስ 5:3

6, 7. ኢየሱስ ዓሣ ከማጥመድ ሥራ ጋር ግንኙነት ያለው ምን ተአምር ፈጸመ? ይህስ ዓሣ ስለማጥመድ ሥራ ምን እንዲናገር አስችሎታል?

6 ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተሰበሰቡትን ሰዎች ከማስተማር የበለጠ ሌላ ዓላማ ነበረው። “ነገሩንም ከጨረሰ በኋላ፣ ስምዖንን፦ ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ አለው።” እነዚህ ዓሣ አጥማጆች ሌሊቱን በሙሉ ሲሠሩ እንዳደሩ ልብ በሉ። ጴጥሮስ፦ “አቤቱ ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም፤ ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ” ብሎ መመለሱ ምንም አያስደንቅም። ይህንንስ ባደረጉ ጊዜ ምን ተከናወነ? “እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረቦቻቸውም ተቀደዱ። በሌላ ታንኳም የነበሩትን ጓደኞቻቸውን መጥተው እንዲያግዙአቸው ጠቀሱ፤ መጥተውም ሁለቱ ታንኳዎች እስኪሰጥሙ ድረስ ሞሉአቸው።”​—ሉቃስ 5:4-7

7 ኢየሱስ ተአምር አደረገ። በዚያ በተንጣለለ ባሕር ላይ ሌሊቱን በሙሉ ሲደክሙ አድረው ምንም አላገኙም ነበር። አሁን ግን ዓሣ የሚርመሰመስበት ባሕር ሆነ። ይህ ተአምር ለጴጥሮስ ትልቅ እምነት ጨምሮለታል። “ስምዖን ጴጥሮስ ግን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጉልበት ላይ ወድቆ፦ ጌታ ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ አለው። ስላጠመዱት ዓሣ እርሱ፣ ከእርሱ ጋርም የነበሩ ሁሉ ተደንቀዋልና፣ እንዲሁም ደግሞ የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ።” ኢየሱስም ጴጥሮስን ካረጋጋው በኋላ ሕይወቱን የለወጡትን ቃላት ተናገረው። “አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ አለው።”​—ሉቃስ 5:8-10

የሰዎች አጥማጆች

8. ዓሣ በማጥመድ ሥራ የሚተዳደሩ አራት ሰዎች ሰዎችን እንዲያጠምዱ ለቀረበላቸው ግብዣ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነበር?

8 ኢየሱስ በዚህ መንገድ ሰዎችን ከዓሣ ጋር አመሳሰለ። በኑሮው ዝቅተኛ የሆነውን ይህን ዓሣ አጥማጅ ሥጋዊ ሥራውን ትቶ በጣም ከፍተኛ የሆነውን ሰዎችን የማጥመድ ሥራ እንዲሠራ ጋበዘው። ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ ግብዣውን ተቀብለው “ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት።” (ማቴዎስ 4:18-20) ኢየሱስ ከዚህ ቀጥሎ በታንኳቸው ውስጥ ሆነው መረባቸውን ይጠግኑ የነበሩትን ያዕቆብንና ዮሐንስን ጠራ። እነርሱንም ሰዎችን የማጥመድ ሥራ እንዲሠሩ ጋበዛቸው። እነሱስ ምን ምላሽ ሰጡ? “እነርሱም ወዲያው ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።” (ማቴዎስ 4:21, 22) ኢየሱስ ሰዎችን በማጥመድ ረገድ ከፍተኛ ችሎታ እንዳለው አሳይቶአል። በዚህ ጊዜ እንኳን አራት ሰዎችን አጥምዶአል።

9, 10. ጴጥሮስና ጓደኞቹ ምን ዓይነት እምነት አሳዩ? በመንፈሳዊ ዓሣ የማጥመድ ሥራስ የሰለጠኑት እንዴት ነው?

9 ዓሣ አጥማጅነትን ሙያው ያደረገ ሰው የሚተዳደረው የያዛቸውን ዓሦች እየሸጠ ነው። ሆኖም መንፈሣዊ ዓሣ አጥማጅ ግን እንዲህ ለማድረግ አይችልም። ስለዚህ እነዚህ ደቀ መዛሙርት ሁሉን ትተው ሲከተሉት በኢየሱስ ላይ ከፍተኛ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል። ይሁን እንጂ የመንፈሣዊ ዓሣ አጥማጅነት ሥራቸው የተሳካ ውጤት እንደሚያስገኝ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ አልነበራቸውም። ኢየሱስ ባዶ የነበረው ባሕር በጣም ብዙ በሆኑ ዓሦች እንዲሞላ አድርጎአል። በተመሳሳይም ደቀ መዛሙርቱ በእስራኤል ብሔር ውስጥ መንፈሣዊ መረባቸውን ሲጥሉ በአምላክ እርዳታ ሰዎችን ለማጥመድ እንደሚችሉ እርግጠኛ ሊሆኑ ይችሉ ነበር። በእርግጥም በዚያ ዘመን የተጀመረው መንፈሣዊ ዓሣ የማጥመድ ሥራ እስከ አሁን ድረስ ቀጥሎአል። ይሖዋም እጅግ ብዙ ምርት እንዲገኝ አድርጎአል።

10 ኢየሱስ እነዚያን ደቀ መዛሙርት ከሁለት ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ሰዎችን እንዴት እንደሚያጠምዱ አሰልጥኗቸዋል። አንድ ጊዜ አስፈላጊውን መመሪያ በጥንቃቄ ከሰጣቸው በኋላ ከእርሱ ቀድመው በመሄድ ብቻቸውን እንዲሰብኩ ልኮአቸዋል። (ማቴዎስ 10:1-7፤ ሉቃስ 10:1-11) ኢየሱስ አልፎ በተሰጠና በተገደለበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተደናግጠው ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ከሞተ ሰዎችን የማጥመዱ ሥራ ይቆማል ማለት ነው? ብዙም ሳይቆይ የተፈጸሙ ሁኔታዎች መልሱን ሰጥተውናል።

በሰው ዘሮች ባሕር ውስጥ ዓሣ ማጥመድ

11, 12. ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ከዓሣ ማጥመድ ጋር የተያያዘ ምን ተአምር ፈጸመ?

11 ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም ውጭ ከተገደለና ከሙታን ከተነሣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ገሊላ ተመለሱ። በአንድ ወቅት ሰባት ሆነው በገሊላ ባሕር አጠገብ ተቀምጠው ነበር። ጴጥሮስ ዓሣ ሊያጠምድ መሄዱ እንደሆነ ሲነግራቸው ሌሎቹም ተከተሉት። እንደተለመደው ዓሣ የሚያጠምዱት በምሽት ነበር። ሌሊቱን በሙሉ መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አድረው ምንም ዓሣ ሳያገኙ ቀሩ። ሊነጋጋ ሲል ግን በባሕሩ ዳርቻ አንድ ምስል ቆሞ ተመለከቱ። ምስሉ ከባሕሩ ጠራቸውና “ልጆች ሆይ፣ አንዳች የሚበላ አላችሁን?” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም መልሰው “የለንም” አሉት። ከባሕሩ ዳር የቆመውም ሰው መለሰና “መረቡን በታንኳይቱ በስተ ቀኝ ጣሉት፤ ታገኙማላችሁ አላቸው። ስለዚህ ጣሉት፣ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ ሊጎትቱት አቃታቸው።”​—ዮሐንስ 21:5, 6

12 በጣም የሚያስደንቅ ተሞክሮ ነበር! ደቀ መዛሙርቱ ከዚህ በፊት ዓሣ ሲያጠምዱ ያደረገው ተአምር ትዝ እንዳላቸው አያጠራጥርም። ቢያንስ ከእነርሱ ውስጥ አንዱ ከባሕሩ ዳርቻ የቆመው ምስል ማን እንደሆነ ሳያስተውል አልቀረም። “ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን፦ ጌታ እኮ ነው አለው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ራሱን ጣለ። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር ሁለት መቶ ክንድ ያህል እንጂ እጅግ አልራቁም ነበርና ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ።”​—ዮሐንስ 21:7, 8

13. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ምን ዓለም አቀፍ የማጥመድ ሥራ ተጀመረ?

13 ይህ ሁለተኛ ተአምር ምን የሚያመለክት ነበር? ሰዎችን የማጥመዱ ሥራ ገና ያላለቀ መሆኑን ነው። ይህም ቁም ነገር ኢየሱስ ሦስት ጊዜ ለጴጥሮስ፣ በጴጥሮስም በኩል ለደቀ መዛሙርቱ በሙሉ በጎቹን እንዲመግቡ በነገራቸው ቃል ጉልህ ሆኖ ተገልጾአል። (ዮሐንስ 21:15-17) ኢየሱስ በዚህ አነጋገሩ መንፈሣዊ የመመገብ ሥራ ከፊታቸው ተደቅኖ እንደሚጠብቃቸው ገልጾአል። ከመሞቱም በፊት “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” ሲል ትንቢት ተናግሮአል። (ማቴዎስ 24:14) የዚህ ትንቢት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክፍል መፈጸም የሚጀምርበት ጊዜ ደርሶአል። ደቀ መዛሙርቱ መረባቸውን በሰው ልጆች ባሕር ውስጥ የሚጥሉበት ጊዜ ቀርቦአል። መረባቸውም ባዶውን አይመለስም።​—ማቴዎስ 28:19, 20

14. ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት በነበሩት ዓመታት የኢየሱስ ተከታዮች ያከናወኑት ዓሣ የማጥመድ ሥራ የተባረከው እንዴት ነበር?

14 ኢየሱስ ወደ አባቱ ዙፋን ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለተከታዮቹ “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።” (ሥራ 1:8) መንፈስ ቅዱስ በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት በደቀ መዛሙርቱ ላይ በፈሰሰ ጊዜ ታላቁ ዓለም አቀፍ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ተጀመረ። በጰንጠቆስጤ ዕለት ብቻ ሦስት ሺህ ሰዎች ተጠመዱ። ከዚያ በኋላ ብዙ ሳይቆይ “የወንዶችም ቁጥር አምስት ሺህ ሆነ።” (ሥራ 2:41፤ 4:4) ታሪኩ እንደሚነግረን “የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ።” (ሥራ 5:14) ወዲያውኑ ሣምራውያን ምሥራቹን ተቀበሉ። ያልተገረዙ አሕዛብም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ምሥራቹን መቀበል ጀመሩ። (ሥራ 8:4-8፤ 10:24, 44-48) ከጰንጠቆስጤ ዕለት ሃያ ሰባት ዓመት ከሚያክል ጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት በሙሉ” እንደተሰበከ ተናግሮአል። (ቆላስይስ 1:23) አዎ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከገሊላ ባሕር ብዙ ርቀው በመሄድ ዓሣ አጥምደዋል። በሮማ ግዛት ተበትነው በሚኖሩት አይሁዳውያን መካከልም ሆነ ምንም ዓሣ የማይገኝበት ባሕር መስሎ በሚታየው አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች መካከል ብዙ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ፈጽመዋል። መረባቸውም ባዶውን አልተመለሰም። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሁኔታ በሚጠይቀው መሠረት በማቴዎስ 24:14 ላይ የሚገኘው የኢየሱስ ትንቢት ኢየሩሳሌም በ70 እዘአ ከመጥፋትዋ በፊት ተፈጽሞአል።

“በጌታ” ቀን የሚፈጸመው ዓሣ የማጥመድ ሥራ

15. በራእይ መጽሐፍ ላይ ምን ተጨማሪ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ተተንብዮአል? ይህስ ዓሣ የማጥመድ ሥራ የሚከናወነው መቼ ነው?

15 ይሁን እንጂ ሥራው በዚህ ብቻ የሚያበቃ አልነበረም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜ አካባቢ ይሖዋ ከሐዋርያት መካከል በሕይወት ለቀረው ለዮሐንስ “በጌታ ቀን” ስለሚፈጸሙ ነገሮች ራእይ አሳይቶት ነበር። (ራእይ 1:1, 10) በዚህ ራእይ መሠረት ይፈጸማሉ ከተባሉት አስደናቂ ክንውኖች መካከል አንዱ ምሥራቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ መሰበኩ ነው። እንዲህ እናነባለን፦ “በምድርም ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ።” (ራእይ 14:6) አዎ፣ የአምላክ አገልጋዮች በመላእክት እየተመሩ በሮማ ግዛት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ሰው በሚኖርበት የምድር ክፍል በሙሉ ምሥራቹን ይሰብካሉ። ምድር አቀፍ የሆነ የነፍሳት ዓሣ የማጥመድ ሥራ መከናወን አለበት። የዚህ ራእይ ፍጻሜ በዘመናችን እየታየ ነው።

16, 17. የኋለኛው ዘመን መንፈሳዊ ዓሣ የማጥመድ ሥራ የተጀመረው መቼ ነው? ይሖዋስ ሥራውን የባረከው እንዴት ነው?

16 ታዲያ ይህ በ20ኛው መቶ ዘመን የተከናወነው ዓሣ የማጥመድ ሥራ እንዴት ነበር? በመጀመሪያ ላይ ዓሣ አጥማጆቹ በጣም ጥቂት ነበሩ። የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት ካለቀ በኋላ በነበሩት ዓመታት በአብዛኛው ቅቡዓን የነበሩት አራት ሺህ የሚያክሉ ቀናተኛ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ብቻ ነበሩ። እነዚህም ሰዎች ይሖዋ መንገዱን በከፈተላቸው ቦታ ሁሉ መረባቸውን ጣሉ። ብዙ ነፍሳትም ሊያዙ ችለዋል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ይሖዋ ዓሣ የሚጠመድባቸውን አዳዲስ ባሕሮች ከፈተ። የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የጊልያድ ምሩቃን የሆኑ ሚሲዮናውያን በብዙ አገሮች የሚከናወነውን ሥራ በግንባር ቀደምትነት ማከናወን ጀመሩ። ምንም ፍሬ የማይገኝባቸው በሚመስሉ እንደ ጃፓን፣ ኢጣልያና እስፔይን በመሳሰሉት አገሮች ብዙ የነፍሳት መከር ሊሰበሰብ ቻለ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምሥራቅ አውሮፓ ሲከናወን የቆየው ነፍሳትን የማጥመድ ሥራ ምን ያህል ውጤት እንዳስገኘ ለማወቅ ችለናል።

17 መረቡ በአሁኑ ጊዜ በብዙ አገሮች እስኪቀደድ ድረስ ብዙ ዓሦችን እያጠመደ ነው። በጣም ብዙ የሆነ የነፍሳት ምርት በመሰብሰቡ አዳዲስ ጉባኤዎችንና ክልሎችን ማቋቋም ግድ ሆኖአል። ለእነዚህም የሚያገለግሉ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾችና የስብሰባ አዳራሾች በመሠራት ላይ ናቸው። ለእነዚህ ቁጥራቸው እየጨመረ ለሄደው ነፍሳት እንክብካቤ የሚያደርጉ ተጨማሪ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት አስፈልገዋል። በ1919 የነበሩት አራት ሺህ የሚያክሉ ታማኝ ሰዎች የጀመሩት ሥራ በጣም ታላቅ ሥራ ነበር። የኢሳይያስ 60:22 ትንቢት ቃል በቃል ተፈጽሞአል። አራት ሺዎቹ ዓሣ አጥማጆች ከአራት ሚልዮን በላይ ስለደረሱ በእርግጥም ‘ታናሹ ለሺህ ሆኖአል።’ ይሁን እንጂ መጨረሻው ገና አልመጣም።

18. የመጀመሪያው መቶ ዘመን መንፈሳዊ ሰው አጥማጆች የተዉልንን ግሩም ምሳሌ ልንከተል የምንችለው እንዴት ነው?

18 ይህ ሁሉ ሁኔታ ለየግላችን ምን ትርጉም ይኖረዋል? ቅዱስ ጽሑፉ ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ የሰዎች አጥማጆች እንዲሆኑ በተጋበዙ ጊዜ “ሁሉን ትተው [ኢየሱስን] ተከተሉት” ይላል። (ሉቃስ 5:11) በጣም ግሩም የሆነ የእምነትና ራስን ለአምላክ የመወሰን ምሳሌ ትተውልናል! የእነርሱን የመሰለ ራስን መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ፣ የእነርሱን የመሰለ ምንም ዓይነት ኪሣራ ቢያስከትል ይሖዋን ለማገልገል ዝግጁ የመሆን መንፈስ ልንኮተኩት እንችላለንን? በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንችላለን የሚል መልስ ሰጥተዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓሣ አጥማጆቹ ይሖዋ በፈቀደላቸው ቦታ ሁሉ መረባቸውን ይጥሉ ነበር። በአይሁዳውያንም ሆነ በአሕዛብ መካከል በራሳቸው ላይ ምንም ዓይነት ገደብ ሳያደርጉ ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን አከናውነዋል። በራሳችን ላይ ምንም ዓይነት ገደብ ሳናደርግና ሳናዳላ ላገኘነው ሰው ሁሉ እንስበክ።

19. የምናጠምድባቸው ባሕሮች ዓሣ የማይገኝባቸው መስለው ቢታዩ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

19 ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ የምትሠሩበት የአገልግሎት ቀበሌ ዓሣ የማይገኝበት ቢሆንስ? ተስፋ አትቁረጡ። ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱ መረብ እንዲሞላ ያደረገው ሌሊቱን በሙሉ ምንም ዓሣ ሳይዙ ሲለፉ ከቆዩ በኋላ እንደሆነ አስታውሱ። በመንፈሣዊ ሁኔታም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። ለምሳሌ ያህል በአየርላንድ የሚኖሩ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ለብዙ ዓመታት ደክመው እምብዛም ውጤት አላገኙም ነበር። በቅርቡ ግን ይህ ሁኔታ ተለወጠ። በ1991 የይሖዋ ምሥክሮች ዓመት የመጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው በ1990 የአገልግሎት ዓመት ፍጻሜ ላይ 29 ተከታታይ ከፍተኛ የአስፋፊ ቁጥር አግኝተዋል። የእናንተም ክልል በተመሳሳይ አንድ ቀን ይህን የመሰለ ፍሬ ያስገኝ ይሆናል። ይሖዋ እስከ ፈቀደ ድረስ ዓሣ የማጥመድ ሥራችሁን አታቋርጡ!

20. ሰዎችን በማጥመዱ ሥራ መሠማራት የሚኖርብን መቼ ነው?

20 በእስራኤል አገር ዓሣ አጥማጆች ሥራቸውን የሚሠሩት ሌላው ሰው ሁሉ የሞቀ አልጋው ውስጥ ተመቻችቶ በሚተኛበት የሌሊት ጊዜ ነበር። ለሥራ የሚሠማሩት በሚመቻቸው ጊዜ ሳይሆን ብዙ ዓሣ ሊያገኙ በሚችሉበት ጊዜ ነበር። እኛም የክልላችንን ሁኔታ ማጥናትና አብዛኞቹ ሰዎች እቤታቸው በሚገኙበትና ምሥራቹን ለመስማት በሚችሉበት ጊዜ ዓሣ የማጥመድ ሥራችንን ማከናወን ይኖርብናል። ይህም በምሽቶች፣ በሣምንቱ የመጨረሻ ቀኖች ወይም በሌላ ጊዜ ሊሆን ይችላል። አመቺ የሚሆነው ጊዜ መቼም ይሁን መቼ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።

21. የአገልግሎት ቀበሌአችን በተደጋጋሚ የሚሸፈን ከሆነ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

21 የአገልግሎት ቀበሌአችን ተደጋግሞ የሚሸፈን ከሆነስ? ዓሣ በማጥመድ የሚተዳደሩ የዓለም ሰዎች በሚያጠምዱበት ባሕር ውስጥ የሚኖረው ዓሣ ተጠምዶ እንዳለቀ ይናገራሉ። በእኛስ መንፈሣዊ ባሕር ውስጥ የሚኖሩት ዓሦች ተጠምደው ሊያልቁ ይችላሉን? በፍጹም አይችሉም! ብዙ ክልሎች ተደጋግመው ቢሸፈኑም ፍሬ ይገኝባቸዋል። እንዲያውም በአንዳንዶቹ ክልሎች ጥሩ ፍሬ ማግኘት የተቻለው ተደጋግሞ የተሠራባቸው በመሆናቸው ነው። ቢሆንም ቤቶችን አዘውትራችሁ በተደጋጋሚ በምታዳርሱበት ጊዜ በቤት ያልተገኙ ሰዎችን በሙሉ አግኝታችሁ ለማነጋገር ጥረት አድርጉ። የተለያዩ የመነጋገሪያ ርዕሶችን ተለማመዱ። ሌላ ጊዜ ሌላ ሰው መጥቶ ማነጋገሩ የማይቀር መሆኑን በመገንዘብ በሰዎች ቤት ውስጥ ለረዥም ጊዜ አትቆዩ ወይም የቤቱን ባለቤት አታስቆጡ። በተጨማሪም በመንገድ ላይ ስብከትና መደበኛ ባልሆነ ስብከት ረገድ ያላችሁን ችሎታ አዳብሩ። በማንኛውም ሁኔታና በሚቻልበት ቦታ ሁሉ መረባችሁን ጣሉ።

22. በዚህ ዘመን የምንደሰትበት ትልቅ መብት ምንድን ነው?

22 በዚህ የማጥመድ ሥራ ዓሣ አጥማጆችም ሆኑ የሚጠመዱት ዓሦች እኩል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታውሱ። የምናጠምዳቸው ሰዎች ጸንተው ከተገኙ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ሲያጽናናው “በእነዚህም ጽና፣ ይህን ብታደርግ ራስህንም፣ የሚሰሙህንም ታድናለህ” ብሎታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) ለመጀመሪያ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ለመንፈሳዊ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ያሠለጠነው ኢየሱስ ነበር። ዛሬም ቢሆን ይህ ሥራ የሚከናወነው በኢየሱስ መሪነት ነው። (ከራእይ 14:14-16 ጋር አወዳድር።) ይህን ሥራ ወደ ፍጻሜው ለማድረስ ከኢየሱስ ሥር ሆነን ለመሥራት መቻላችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ይሖዋ እስከ ፈቀደ ድረስ መረቡን መጣላችንን አናቋርጥ። ነፍሳትን ከማጥመድ የበለጠ ምን ትልቅ ሥራ ሊኖር ይችላል?

ታስታውሳለህን?

◻ ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲሠሩት ያሰለጠናቸው ሥራ ምን ነበር?

◻ ኢየሱስ መንፈሳዊው ዓሣ የማጥመድ ሥራ በእሱ ሞት ምክንያት እንደማያቆም ያመለከተው እንዴት ነው?

◻ ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተከናወነውን መንፈሳዊ ዓሣ የማጥመድ ሥራ የባረከው በምን መንገድ ነበር?

◻ “በጌታ ቀን” ምን ዓይነት ከፍተኛ የዓሣ ምርት ለማግኘት ተችሎአል?

◻ በግለሰብ ደረጃ በምናከናውነው ዓሣ የማጥመድ ሥራ የበለጠ ውጤት ለማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ሐዋርያት መለኮታዊውን ሰዎች የማጥመድ ሥራ አስፋፉት

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ