ተስፋ መቁረጥን የሚያሸንፈው ተስፋ!
የዌብስተር ናይንዝ ኮሌጂየት ዲክሽነሪ ተስፋ ቢስነት ተብሎ የተተረጎመውን “ዲስፔር” የተባለ የእንግሊዝኛ ቃል ሲፈታ “ፈጽሞ ተስፋ ማጣት” ብሎአል። ስለዚህ የተስፋ ቢስነትን ስሜት ለማሸነፍ ተስፋ ያስፈልጋል ማለት ነው።
መንገድ አዳሪ የሆነ ችግረኛ ሰው ተስፋ ካለው በተስፋ ቢስነት ስሜት ወይም በጭንቀት አይዋጥም። ተስፋ በከባድ ጭንቀት ለሚሰቃዩ ሰዎች እንኳን ስቃያቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸውን ኃይልና ጥንካሬ ይሠጣቸዋል። ይሁን እንጂ ተስፋው የሚያስተማምን ተስፋ መሆን ይኖርበታል። ይህ ምን ማለት ነው?
ለተስፋ የሚሆን መሠረት
የእሥራኤላውያን አባት የአብርሃም ሚስት በነበረችው በሣራ ላይ የደረሰባትን ተመልከቱ። ዕድሜዋ 90 ዓመት እስኪሞላ ድረስ መካን በመሆንዋና ልጅ ባለመውለዷ ተስፋ ቆርጣ ነበር። ሆኖም ባሏ 99 ዓመት ዕድሜ ሲሆነው ይሖዋ ከረዥም ጊዜ በፊት የገባውን ቃል እንደገና አደሰ። አብርሃም ይህ እውነተኛ ተስፋ መሆኑን ያውቅ ነበር። ሣራ በዚህ ተአምራዊ ሁኔታ ይስሐቅን ስትወልድ ምንኛ ተደስታ እንደነበር ገምቱ! (ዘፍጥረት 12:2, 3፤ 17:1-4, 19፤ 21:2) ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው የአብርሃም እምነት ከንቱ አልሆነም። “ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፣ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፣ በእምነት በረታ እንጂ ባለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል አልተጠራጠረም።”—ሮሜ 4:20
ጳውሎስ ከይሁዲነት ወደ ክርስትና ለተለወጡት በዘመኑ ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ሲጽፍ አምላክ በኢየሱስ በኩል ባዘጋጀው የመዳን ተስፋ ላይ እንዲመኩ የሚያስችሉአቸው ሁለት ጠንካራ ምክንያቶች እንዳሉ ገልጿል። አምላክ ለአብርሃም የገባውን ቃልና ከቃሉ ጋር የተናገረውን መለኮታዊ መሐላ በመጥቀስ ሐዋርያው እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጠው ይምላሉና፣ ለማስረዳትም የሆነው መሐላ የሙግት ሁሉ ፍጻሜ ይሆናል፣ ስለዚህም እግዚአብሔር፣ የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ፣ እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይችል በሁለት በማይለወጥ ነገር በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ፣ በመሐላ በመካከል ገባ።” (ዕብራውያን 6:16-18) አዎ፣ የአምላክ የተስፋ ቃሎች እውነተኛና ሊታመኑ የሚችሉ ናቸው። ይሖዋ ሁሉን ቻይና ቃሉ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ዋስትና ሊሰጥ የሚችል ብቸኛ አምላክ ነው።
“እርግጠኛና ጽኑ” የሆነ ተስፋ
ስለዚህ የክርስቲያኖች ተስፋ ‘እርግጠኛና የጸና’ እንደሆነ ጳውሎስ ጽፏል። (ዕብራውያን 6:19) ጳውሎስ ተስፋው የተመሠረተው በምን ላይ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ይህንንም ሲገልጽ “እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃ ውስጥ የገባ ነው” ብሎአል። ምን ማለቱ ነው? ጳውሎስ እንዲህ ሲል በጥንትዋ ኢየሩሳሌም ስለነበረው ቤተ መቅደስ መናገሩ እንደሆነ ግልጽ ነው። በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከሌላው የሕንፃ ክፍሎች በመጋረጃ የተለየ ቅድስተ ቅዱሳን ነበር። (ዘጸአት 26:31, 33፤ ማቴዎስ 27:51) እርግጥ፣ በኢየሩሳሌም ይገኝ የነበረው ቤተ መቅደስ ከፈራረሰ ብዙ ጊዜ ሆኖታል። ታዲያ ይህ ቅዱስ የሆነ ሥፍራ በጊዜያችን ምን ያመለክታል?
አምላክ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠበትን ሥፍራ ሰማይን ያመለክታል! ጳውሎስ ይህንን ሲገልጽ “ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ” በማለት ኢየሱስ ባረገ ጊዜ የሆነውን ነገር ተናግሮአል። (ዕብራውያን 9:24) ስለዚህ ተስፋ መቁረጥን ለማሸነፍ የሚያስችለው የክርስቲያን ተስፋ የተመካው በፖለቲካ ሰዎች ላይ ሳይሆን በሰማያዊው ዝግጅት ላይ ነው። አምላክ በሾመውና ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በሰጠው በኢየሱስ ላይ የተመካ ነው። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) በተጨማሪም ብዙውን ጊዜ በዚህ መጽሔት ዓምድ ላይ እንደሚገለፀው የአምላክን ሰማያዊ መንግሥት እንዲያስተዳድር የተሾመው ንጉሥ ኢየሱስ ነው። እርሱም በ1914 መግዛት ጀምሮአል። ይህች ሰማያዊት መንግሥት ብዙ ሰዎች ተስፋ ቢሶች እንዲሆኑ ያደረጉአቸውን ምክንያቶች ታስወግዳለች።
ተስፋ—“የነፍስ መልሕቅ ነው”
ጳውሎስ አንባቢዎቹን በኢየሱስ በኩል የሚያገኙት የመዳን ተስፋ ጠንካራ መሠረት ያለው መሆኑን ለማሳመን ሲል በምሳሌ ተጠቅሞአል። “ይህም ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ አለን” ብሎአል።—ዕብራውያን 6:19
መልሕቅ እንደ ጳውሎስ ባሉት የባሕር ተጓዦች በሚገባ የታወቀ ነገር ነው። የጥንት መልሕቆች ከዘመናዊ መልሕቆች ጋር በጣም ተመሳሳይነት አላቸው። ብዙውን ጊዜ የሚሰሩት ከብረት ሲሆን በጫፋቸው ላይ የባሕሩን ዳርቻ በሚገባ ቆንጥጠው የሚይዙ ሁለት ጥርስ መሰል ብረቶች አሏቸው። በ58 እ.ዘ.አ. ጳውሎስ ወደ ሮም በሚጓዝበት ጊዜ የተሳፈረበት መርከብ ከደረቁ መሬት ጋር የመጋጨት አደጋ ገጥሞት ነበር። ሆኖም መርከቡ ወደ መሬት ሲጠጋ መርከበኞቹ “ከመርከቡ በረንዳ ላይ አራት መልሕቆችን ወረወሩ።” በእነዚህ መልሕቆች ምክንያት መርከቡ ከአደጋ ለመዳን ችሎአል።—ሥራ 27:29, 39, 40, 44
ታዲያ ተስፋህ ልክ እንደ መልሕቁ አስተማማኝ እንዲሆንና የኢኮኖሚ ችግሮችን፣ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ በሽታዎችን ወይንም የሚያጋጥምህን ማንኛውንም ዓይነት “ሞገድ” ለመቋቋም እንዲያስችልህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በመጀመሪያ ደረጃ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች እውነተኛ እንደሆኑ እመን። “ሁሉንም ነገር ፈትን።” (1 ተሰሎንቄ 5:21) ለምሳሌ በሚቀጥለው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች አግኝተው ሲያነጋግሩህ ምን እንደሚሉ አዳምጣቸው። በአካባቢህ ብዙ ጊዜ የማይገኙ ከሆነ በአቅራቢያህ ወደሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ በመሄድ ፈልጋቸው። ከእነርሱ ጋር እንድትሰበሰብ አያስገድዱህም። በሚያመችህ ቦታና ጊዜ ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግልህ ይጋብዙሃል።
ይህ ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አምላክ ‘ለሚፈልጉት ዋጋቸውን የሚሰጥ መሆኑን’ ያረጋግጥልሃል። (ዕብራውያን 11:6) በቅርቡ በኢየሱስ ክርስቶስ የምትገዛው የአምላክ መንግሥት ማናቸውንም ዓይነት ምግባረ ብልሹነት እና ብዙዎች ተስፋ ቢስ እንዲሆኑ ያደረጉአቸውን ያልተስተካከለ ሁኔታ ታስወግዳለች። በዚህች መንግሥት አገዛዝ ምድራችን ወደ ገነትነት ትለወጣለች። አምላክም ለሚወዱት ሁሉ ዘላለማዊ ሕይወት ይሰጣቸዋል። (መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:4) ምንኛ ክብራማ ተስፋ ነው!
ይህ ተስፋ እውነተኛ መሆኑን ለማረጋገጥ መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ አንብብ። ከዚያም በኋላ ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና የግል ዝምድና እንዲኖርህ በመጣጣር ልክ እንደ አብርሃም የአምላክ ወዳጅ ሁን። (ያዕቆብ 2:23) ይሖዋ ጸሎት ሰሚ አምላክ ስለሆነ የሚያሳስቡህን ችግሮች ንገረው። አምላክን በቅንነትና ከልብህ ከቀረብከው ጸሎትህ ሸክምህን ለማቃለልና የተስፋ ቢስነት ስሜትህን ለማሸነፍ ያስችልሃል። እንዲያውም የአምላክ መንፈስ የሚያስጨንቅህ ሁኔታ የሚለወጥበትን መንገድ ሊከፍትልህ ይችላል።—መዝሙር 55:22፤ 65:2፤ 1 ዮሐንስ 5:14, 15
“መልካሙን ያዝ”!
ጳውሎስ “ሁሉን ፈትኑ” በማለት ደቀ መዛሙርቱን ከመከረ በኋላ “መልካሙንም ያዙ” ብሎአቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:21) ይህን ከምናደርግባቸው መንገዶች አንዱ ይህ ዓይነቱ ክርስቲያናዊ ተስፋ ካላቸው ሰዎች ጋር መገናኘትና መሰብሰብ ነው። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፣ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” በማለት አስጠንቅቆአል። (ምሳሌ 13:20) ምክንያት የሌለው ጥላቻ ወይም የዓይን አፋርነት ስሜት ከእነዚህ ጥሩ ባልንጀሮች እንድትርቅ ሊያደርግህ አይገባም። ለምሳሌ ያህል በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ከዚህ በፊት ተስፋ አጥተው የነበሩ ሰዎች ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ከእምነት ባልደረቦች ጋር በሚያደርጉአቸው ስብሰባዎች አማካኝነት ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ለማጠናከርና እንደ መልሕቅ የጸናና የሚያስተማምን ተስፋ ለማግኘት ችለዋል። ታዲያ ይህ ዓይነቱ ተስፋ የተስፋ ቢስነትን ስሜት ያሸንፋልን? እንደሚያሸንፍ ምንም ጥርጥር የለውም።
ከባሏ ይደርስባት በነበረው ሥቃይ ምክንያት ተስፋ ቆርጣ የነበረችውን የአንማሪን ምሳሌ እንውሰድ። “ሕይወቴን ለማጥፋት ወስኜ ነበር” በማለት ትገልፃለች። “ሆኖም በግልጽ ባላወኩት ምክንያት ወደ አምላክ ለመጸለይ ፈለግሁ። ‘ለምን አትረዳኝም? ለረዥም ጊዜ አንተን ተስፋ አድርጌ ምንም ዓይነት መፍትሄ አላገኘሁም’ ብዬ መጸለዬ ትዝ ይለኛል። ሕይወት ምንም ትርጉም ስለሌለው ብሞት ይሻለኛል ብዬ እያሰብኩ ጸሎቴን ጨረስኩ። በዚህ ጊዜ የቤቴ በር መንኳኳት ጀመረ። ሆኖም የሚያንኳኳው ሰው ሲሰለቸው ይሄዳል በሚል ሃሳብ በሩን ሳልከፍት ዝም ለማለት ወሰንኩ።
“ይሁን እንጂ ማንኳኳቱ ቀጠለ እኔም ተርበተበትኩ። በሩን የሚያንኳኳው ማን መሆኑን ለማወቅና ቶሎ ብዬ ካሰናበትኩት በኋላ ያሰብኩትን ለመፈፀም በማሰብ እንባዬን ጠራርጌ በሩን ከፈትኩ” ትላለች አንማሪ። “ይሖዋ የተመሠገነ ይሁንና እኔ እንዳሰብኩት ሳይሆን በሩን ስከፍት ሁለት ሴቶች በር ላይ ቆመው አገኘሁ። አዎ፣ በጣም ተደናገርኩ ምን እንደሚሉም አልገባኝም። ሕይወት አላማ እንዳለው የሚገልጽ መጽሐፍ ሰጡኝ። ለመኖር ያለኝ ፍላጎት እንዲቀጣጠል ለማድረግ የሚያስፈልገኝ መጽሐፍ ነበር። የጎበኙኝ ሴቶች ቋሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲያደርጉልኝ ፕሮግራም ያዝን።” አንማሪ እንዴት የአምላክ ወዳጅ ልትሆን እንደምትችል ተማረች። ይህ ደግሞ በበኩሉ ሕይወት ትርጉም እንዳለው አስተማራት። በአሁኑ ጊዜ ሌሎች ሰዎች በአምላክ ላይ እምነት እንዲያሳድሩ በመርዳት ላይ ትገኛለች።
ተስፋ መቁረጥን ድል ለማድረግ ስለሚያስፈልጉ ነገሮች በምታሰላስልበት ጊዜ ተስፋ ቢስነት እንዲጠፋ ተመኝተህ ሊሆን ይችላል። ይሁንና “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለህ ጸልየህ የምታውቅ ከሆነ የአምላክ መንግሥት እንድትመጣና ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮችን እንድታጠፋ ጸልየሃል ማለት ነው። (ማቴዎስ 6:10) የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህና ይህን ተስፋ ከሚጠባበቁ ጋር የምታደርገው መቀራረብ ምድርን ገነት በምታደርገው በይሖዋ መንግሥት ላይ ጠንካራ ተስፋ እንዲኖርህ ይረዳሃል። (1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19) ይህ መጽሔት በየጊዜው በሚወጡት እትሞቹ ላይ የሚያስታውቀው ይህን ክብራማ ተስፋ ነው። ተስፋ መቁረጥን ለመዋጋት ይህን ተስፋ ከልብህ አጥብቀህ ያዝ። አዎ፣ በእርግጥም “ተስፋ አያሳዝንም።”—ሮሜ 5:5
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ‘ለነፍሳችን እንደ መልህቅ የሚሆንልን’ ተስፋ ይሰጠናል