ዓለማዊ ቅዠቶችን አስወግዳችሁ የመንግሥቱን እውነቶች ተከታተሉ
“ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።”—ማቴዎስ 6:33
1. ምሳሌያዊውን ልባችንን በሚመለከት የአምላክ ቃል ምን ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጣል? ምሳሌያዊው ልባችን ሊያታልለን የሚችልበት ዋነኛው መንገድ ምንድን ነው?
“አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና።” (ምሳሌ 4:23) ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን ይህን የመሰለ ማስጠንቀቂያ መስጠት ያስፈለገው ለምንድን ነው? “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ” ስለሆነ ነው። (ኤርምያስ 17:9) ምሳሌያዊው ልባችን እኛን ለማሳት የሚጠቀምበት ዋነኛው ዘዴ ለዓለማዊ ቅዠቶች እንድንገዛ በማድረግ ነው። ይሁን እንጂ ቅዠቶች ምንድን ናቸው? ቅዠቶች እውነት ያልሆኑ ሐሳቦች፣ የቀን ሕልሞች፣ በአንድ ቦታ ያልረጉና ከሥራ ፈት አእምሮ የሚመነጩ ምኞቶች ናቸው። እነዚህ የቀን ሕልሞች ዓለማዊ ቅዠቶች በሚሆኑበት ጊዜ ደግሞ ጊዜ አባካኝ ብቻ ከመሆን አልፈው በጣም ጎጂዎች ይሆናሉ። ስለዚህ ፈጽመን ልናስወግዳቸው ይገባል። በእርግጥ ኢየሱስ እንዳደረገው አመፅን የምንጠላ ከሆነ ልባችን ለዓለማዊ ቅዠቶች እንዳይገዛ እንጠብቀዋለን።—ዕብራውያን 1:8, 9
2. ዓለማዊ ቅዠቶች ምንድን ናቸው? ልናስወግዳቸው የሚገባንስ ለምንድን ነው?
2 ይሁን እንጂ ዓለማዊ ቅዠቶች ምንድን ናቸው? እነዚህ ቅዠቶች በሰይጣን የሚገዛውን ዓለም ባህርያት የሚያንፀባርቁ ናቸው። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ዮሐንስ “በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም . . . እንጂ ከአባት” እንዳልሆነ ጽፏል። (1 ዮሐንስ 2:16፤ 5:19) ታዲያ ክርስቲያኖች ዓለማዊ ቅዠቶችን ማስወገድ ያለባቸው ለምንድን ነው? እንዲህ ያሉ ቅዠቶች በአእምሮአችንና በልባችን ውስጥ የራስ ወዳድነት ስሜት ስለሚቀሰቅሱ ነው። አንድ ሰው ስህተት ስለሆኑ ድርጊቶች የቀን ሕልም ቢያልም ወደ ፊት በእርግጥ የሚያደርጋቸውን ነገሮች በአእምሮው መለማመዱ ወይም ማውጠንጠኑ ነው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል፦ “ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።”—ያዕቆብ 1:14, 15
ለማስጠንቀቂያ የሚሆኑ ምሳሌዎች
3. የራስ ወዳድነት ቅዠቶችን ጎጂነት በሚገባ የሚያሳየን ከሁሉ የበለጠ ምሳሌ የማን ሁኔታ ነው?
3 ዓለማዊ ቅዠቶች መወገድ ያለባቸው ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት። ለራስ ወዳድነት ቅዠቶች ተገዢ መሆን ጎጂ ውጤት እንደሚያመጣ ለማሳየት በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ የሚገባው ምሳሌ የሰይጣን ዲያብሎስ ሁኔታ ነው። ስለ ራሱ የነበረው ከፍተኛ ግምት በልቡ ውስጥ እንዲያድግ መፍቀዱ ተወዳዳሪ የማይገኝለትን የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ቦታ እስከመመኘት አደረሰው። የመመለክም ፍላጎት አደረበት። (ሉቃስ 4:5-8) ይህ ምኞቱ እውን የማይሆን ቅዠት ነበርን? አዎ፣ በእርግጥ ቅዠት ነበር! እውን ሊሆን የማይችል ቅዠት መሆኑም ሰይጣን ለሺህ ዓመት በሚታሰርበትና በተለይም ሁለተኛ ሞት በሆነው “በእሳት ባህር” ውስጥ በሚጣልበት ጊዜ በማያጠያይቅ ሁኔታ ይረጋገጣል።—ራዕይ 20:1-3, 10
4. ሰይጣን ሔዋንን ያታለላት እንዴት ነው?
4 የመጀመሪያዋ ሴት የሔዋን ሁኔታም ደግሞ ሌላው የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆነናል። ሰይጣን ምኞቱን እውን ለማድረግ ባደረገው ጥረት ይህን ቅዠቱን ወደ ሔዋን አእምሮ በማምጣት ከተከለከለው ፍሬ ብትበላ እንደማትሞት እንዲያውም እንደ አምላክ በመሆን ጥሩና መጥፎውን መለየት እንደምትችል በመንገር አሳሳታት። ይህ እውን ሊሆን የማይችል የራስ ወዳድነት ቅዠት ነበርን? በእርግጥ ነበር። ይህም ይሖዋ በሔዋንና በባሏ በአዳም ላይ በተናገረው ፍርድ ላይ ታይቷል። በዚህም ምክንያት እነሱም ሆኑ ፍጽምና የሌላቸው ዝርያዎቻቸው በገነት ውስጥ ለመኖር የሚያስችላቸውን መብት አጡ።—ዘፍጥረት 3:1-19፤ ሮሜ 5:12
5. አንዳንዶቹን የአምላክ መላእክታዊ ልጆች ወደ ውድቀት ያደረሳቸው ምንድን ነው? ምንስ ውጤት አስከተለባቸው?
5 በተጨማሪም አንዳንድ የአምላክ መላእክታዊ ልጆች የደረሰባቸው ሁኔታ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆነናል። (ዘፍጥረት 6:1-4) ይሖዋ በሚገኝበት በሰማይ ያገኙአቸው በነበሩት በረከቶች ረክተው ከመኖር ይልቅ በምድር ስላሉ ሴቶችና ከነሱ ጋር የጾታ ግንኙነት ማድረግ ምን ያህል አስደሳች ሊሆን እንደሚችል መቃዠት ጀመሩ። እነዚህ ታዛዥነት የጎደላቸው መላእክት ይህን ቅዠታቸውን እውን የሚያደርግ ድርጊት በመፈጸማቸው ምክንያት በኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ድምጥማጣቸው የሚጠፋበትን ጊዜ በእንጦሮጦስ መንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ታስረው ይጠባበቃሉ።—2 ጴጥሮስ 2:4፤ ይሁዳ 6፤ ራዕይ 20:10
ዓለማዊ ቅዠቶችን አስወግዱ
6, 7. ስለ ቁሳዊ ሀብት የሚያሳስቡ ዓለማዊ ቅዠቶች ጎጂና አሳሳች የሆኑት ለምንድን ነው?
6 አሁን ደግሞ አደገኛ ከሆኑትና በጣም ከተለመዱት ሰይጣን የሚያስፋፋቸው ቅዠቶች አንዱን እንመልከት። በሁሉም ዓይነት የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎች ለዓለማዊ ቅዠቶች ተገዢ እንድንሆን በሚገፋፉ መልእክቶች እንፈተናለን። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ቅዠቶች የሚመጡት ሀብት ለማግኘት ከመጎምጀት ነው። ሀብታም መሆን በራሱ ምንም ዓይነት ስህተት የለውም። አምላካዊ ሰዎች የነበሩት አብርሃም፣ ኢዮብና ንጉሥ ዳዊት በጣም ሀብታሞች ነበሩ። ነገር ግን ቁሳዊ ሀብት ለማግኘት የሚጎመጁ ሰዎች አልነበሩም። ቁሳዊ ሃብት የማካበት ቅዠት ሰዎች ሀብት ለማግኘት ለበርካታ ዓመታት አድካሚ ሥራ እንዲሠሩ ያነሳሳቸዋል። በተጨማሪም እንዲህ ያለው ቅዠት በውድድሮች ላይ እንደ መወራረድና የሎተሪ ቲኬት እንደመግዛት በመሰሉት የቁማር ድርጊቶች ወደመካፈል ይመራቸዋል። በሀብት ረገድ የቅዠት አስተሳሰብ እንዳያድርብን እንጠንቀቅ። ቁሳዊ ሀብትን እንደ ራስ መጠበቂያና መተማመኛ የምንቆጥር ከሆነ የሚከተለውን ትክክለኛ ምሳሌ ልብ እንበል። “በቁጣ ቀን ሀብት አትረባም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች።” (ምሳሌ 11:4) በእርግጥ ቁሳዊ ሀብት “ከታላቁ መከራ” እንድንተርፍ በምንም መንገድ አይረዳንም።—ማቴዎስ 24:21፤ ራዕይ 7:9, 14
7 ቁሳዊ ሀብት በቀላሉ ሊያታልለን ይችላል። “ለባለጠጋ ሰው ሀብቱ እንደ ጸናች ከተማ ናት፤ በአሳቡም እንደ ረጅም ቅጥር” የተባለውም በዚህ ምክንያት ነው። (ምሳሌ 18:11) ሀብቱ እንደ ጸናች ከተማና እንደ ረዥም ቅጥር ሆኖ የሚታየው “በአሳቡ” ብቻ ነው። ምክንያቱም ቁሳዊ ሀብት የዕቃዎች ዋጋ በሚጋሽብበት፣ የኢኮኖሚ ውድቀት በሚኖርበትና የፖለቲካ ብጥብጥ በሚነሳበት ጊዜ ወይም ወደ ሞት የሚያደርስ በሽታ በሚይዝበት ጊዜ ሊሰጥ የሚችለው ጥበቃ በጣም ጥቂት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በቁሳዊ ሀብት መተማመን ከንቱ እንደሆነ አስጠንቅቆአል። (ሉቃስ 12:13-21) በተጨማሪም “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ” የሚሉትም የሐዋርያው ጳውሎስ የማስጠንቀቂያ ቃላት አሉን።—1 ጢሞቴዎስ 6:10
8. ጾታን የሚመለከቱ ዓለማዊ ቅዠቶች ምን ያህል የተስፋፉ ናቸው? ምን ዓይነት አደጋስ ይፈጥራሉ?
8 ሌሎቹ ቅዠቶች ደግሞ ሕጋዊ ካልሆነ የጾታ ግንኙነት ጋር የሚዛመዱ ናቸው። የተወሰኑ የስልክ ቁጥሮችን በመደወል ጸያፍ ንግግሮችንና የጾታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ መልዕክቶችን መስማት ተወዳጅነት ማግኘቱና በጣም እየተስፋፋ መሄዱ በኃጢአት የረከሰው የሰው ልጅ ባሕርይ ምን ያህል የጾታ ቅዠቶችን ማሰላሰል እንደሚወድ ያሳየናል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ይህ ገንዘብ እያስከፈሉ የብልግና ንግግሮችን በስልክ የማሰማቱ ሥራ ብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚያስገኝ ንግድ ሆኗል። አእምሮአችን የተከለከሉ የጾታ ጉዳዮችን እንዲያሰላስል የምንፈቅድ ከሆነ ንጹሕ ክርስቲያኖች መስለን ብቻ ለመታየት የምንፈልግ ግብዞች መሆናችን አይደለምን? እንዲህ ዓይነቶቹ ቅዠቶች የጾታ ብልግና ወደመፈጸም ሊያደርሱ አይችሉምን? እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች አጋጥመዋል። አንዳንዶችም ምንዝር ወይም ዝሙት በመፈጸማቸው ምክንያት ከክርስቲያን ጉባኤ ተወግደዋል። እንዲህ ስላለው ቅዠት አዘውትረው የሚያስቡ ሰዎች በማቴዎስ 5:27, 28 ላይ በሚገኙት የኢየሱስ ቃላት መሠረት በልባቸው ምንዝር በመፈጸማቸው በደለኞች አይሆኑምን?
9. በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከዓለማዊ ቅዠቶች እንድንጠበቅ የሚያስጠነቅቁ ምን ጥሩ ምክሮች ይገኛሉ?
9 ኃጢአተኛው ልባችን ያለውን እንዲህ ያሉትን ቅዠቶች የማሰላሰል ዝንባሌ ለማሸነፍ “እኛን በሚቈጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፣ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም” የሚለውን የጳውሎስን ማስጠንቀቂያ በአእምሮአችን መያዝ ይኖርብናል። (ዕብራውያን 4:13) ሁልጊዜ “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ” እንደጸናው እንደ ሙሴ ለመሆን መፈለግ ይኖርብናል። (ዕብራውያን 11:27) ሁልጊዜ ዓለማዊ ቅዠቶች ይሖዋን እንደማያስደስቱና በውጤቱም እኛን ሊጎዱን እንደሚችሉ ራሳችንን ማሳሰብ ይኖርብናል። በሥጋ ከዘራን ከሥጋ መበስበስን እንደምናጭድ ከሚያስገድደን ሐቅ ማምለጥ ስለማንችል ሁሉንም የአምላክ መንፈስ ፍሬዎች በተለይም ራስ መግዛትን ስለ መኮትኮት አጥብቀን ማሰብ ይኖርብናል።—ገላትያ 5:22, 23፤ 6:7, 8
የመንግሥቱ እውነቶች
10, 11. (ሀ) ፈጣሪ መኖሩን የሚያረጋግጡ ምን ነገሮች አሉ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ በእውነት የአምላክ ቃል ለመሆኑ ምን ማስረጃዎች አሉ? (ሐ) ስለ አምላክ መንግሥት ንጉሥ እውንነት የሚያስረዱ ምን ማረጋገጫዎች አሉ?
10 ዓለማዊ ቅዠቶችን ለማስወገድ የሚረዳን ከሁሉ የተሻለው መንገድ የመንግሥቱን እውነቶች በትጋት መከታተል ነው። ከአምላክ የሚመነጩት የመንግሥቱ እውነቶች ከዓለማዊ ቅዠቶች ጋር በጣም የሚፃረሩ ናቸው። አምላክ እውን ነውን? አምላክ መኖሩ የሚያጠያይቅ ነገር አይደለም። ገሐዱ ፍጥረት አምላክ ስለመኖሩ ይመሰክራል። (ሮሜ 1:20) ይህም ከመቶ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በታተመው ዘ ዲቫይን ፕላን ኦቭ ዘ ኤጅስ (መለኮታዊው የዘመናት እቅድ) በተባለው መጽሐፍ ላይ የሰፈረውን ያስታውሰናል። እንዲህ በማለት ያትታል፦ “በቴሌስኮፕ (አቅርቦ በሚያሳይ መሣሪያ) ወይም በተፈጥሮ ዓይኑ ብቻ እንኳን ወደ ሰማይ መመልከት የሚችል ሰው የተፈጥሮን ግዙፍነት፣ የተስተካከለ ቅርጽ፣ ውበት፣ ቅንጅት፣ ስምምነትና ልዩነት እየተመለከተ የእነዚህ ሁሉ ፈጣሪ በጥበብም ሆነ በኃይል ከራሱ እጅግ የላቀ መሆኑን ቢጠራጠር ወይም እንዲህ ያለው ሥርዓት ያለ ፈጣሪ በአጋጣሚ የመጣ ነው ብሎ ለአንድ አፍታ እንኳን ቢያስብ የማመዛዘን ችሎታውን የሳተ ወይም አውቆ ቸል ያለ ሰው በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ሞኝ (ምክንያታዊነት የጎደለው ወይም አውቆ ችላ የሚል) ነው።”—መዝሙር 14:1
11 ስለ መንግሥቱ የምንማረው ዕውቀት በሙሉ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ በጽሑፍ የሰፈረ የአምላክ ቃል ነውን? እርስ በርሱ ካለው ስምምነት፣ ከሳይንሳዊ ትክክለኛነቱ፣ እንዲሁም የሰዎችን አኗኗር ለመለወጥ ከሚያስችለው ኃይሉና በተለይም ደግሞ ከትንቢቶቹ አፈጻጸም ለመመልከት እንደሚቻለው በእርግጥም የአምላክ ቃል ነው።a የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስስ ምን ለማለት ይቻላል? በእውነት በሕይወት የኖረ ሰው ነበርን? የወንጌል ዘገባዎችና በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያሉት ደብዳቤዎች በማያጠራጥርና ግልጽ በሆነ ሁኔታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ታሪካዊነት ይመሰክራሉ። ኢየሱስን እንደ ተራ ሰው የሚቆጥረው የአይሁዳውያን ታልሙድ እንኳን ስለ ኢየሱስ ታሪካዊነት ማስረጃ ይሰጣል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ አይሁዳውያንና ሮማውያን ታሪክ ጸሐፊዎችም ይህንን አረጋግጠዋል።
12, 13. ስለ አምላክ መንግሥት እውንነት የሚመሰክሩ ምን እውነታዎች አሉ?
12 ስለ መንግሥቱ እውንነትስ ምን ለማለት ይቻላል? አንድ የታወቁ የፕሪስባይተርያን ቤተ ክርስቲያን አባል “አንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ስለ መንግሥቲቱ እውንነት ለሰዎች ለማስረዳት ሲሞክር ከሰማሁ ከሠላሳ ዓመታት በላይ ሆኖኛል” በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ሕዝበ ክርስትና የመንግሥቲቱን እውንነት በጣም ችላ ብላለች። ይሁን እንጂ የይሖዋ ስም በመንግሥቱ አማካኝነት መቀደስ የአምላክ ቃል አጠቃላይ መልእክት ነው። “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ” በማለት የመጀመሪያውን የመንግሥቱን ተስፋ የሰጠው አምላክ ራሱ ነው። (ዘፍጥረት 3:15) የእስራኤል ብሔር፣ በተለይም በንጉሥ ሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ለአምላክ መንግሥት ጥላ ሆኖ አገልግሎአል። (መዝሙር 72) ከዚህም በላይ የኢየሱስ ስብከት ዋነኛ መልዕክት የአምላክ መንግሥት ነበር። (ማቴዎስ 4:17) በማቴዎስ ምዕራፍ 13 ላይ እንደሚገኙት ባሉት በብዙዎቹ ምሳሌዎቹም ስለዚህች መንግሥት ገልጾአል። ኢየሱስ ስለ መንግሥቲቱ እንድንጸልይ እንዲሁም ሳናቋርጥ መንግሥቲቱን እንድንፈልግና እንድናስቀድም ነግሮናል። (ማቴዎስ 6:9, 10, 33) በእርግጥ የአምላክ መንግሥት በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ወደ 150 ለሚጠጉ ጊዜያት ተጠቅሷል።
13 መንግሥቲቱ ኃይልና ሥልጣን ያላት፣ ትክክለኛ የሆኑ ተስፋዎችን የምታሟላና እውን የሆነች መስተዳድር ናት። የራሷ የሆነ ሕግ አላት። ይህም ሕግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። መንግሥቲቱ በአሁኑ ጊዜ እንኳን ብዙ ነገሮችን እውን አድርጋለች። ታማኝ ተገዥዎችዋ የሆኑ ከ4,000,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። እነዚህም ሰዎች በ211 አገሮች ውስጥ የማቴዎስ 24:14 ፍጻሜ የሆነውን የአምላክን መንግሥት የምሥራች በመስበክ ላይ ይገኛሉ። በ1991 የአገልግሎት ዓመታቸው 951,870,021 የሚያክል ሰዓት የመንግሥቱን መልእክት በመስበክ አሳልፈዋል። ይህም ሥራ እጅግ ብዙ ሰዎች “ንጹሕ ልሳን” የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲማሩ ስላስቻለ ተጨባጭና ዘላቂ የሆነ ውጤት አስገኝቶአል።—ሶፎንያስ 3:9
የመንግሥቱን እውነቶች መከታተል
14. ለመንግሥቱ እውንነት ያለንን አድናቆት እንዴት ልናጠነክር እንችላለን?
14 ታዲያ የመንግሥቱን እውነቶች መከታተል የምንችለው እንዴት ነው? ተስፋችን በጠንካራ እምነት ላይ ጽኑ ሆኖ መመሥረት ይኖርበታል። አምላክ የሰጠን የአዲሱ ዓለም ተስፋ እውን ሆኖ ሊታየን ይገባል። (2 ጴጥሮስ 3:13) እንዲሁም አምላክ ‘እንባዎቻችንን ሁሉ ከዓይኖቻችን እንደሚያብስልን፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ እንደማይሆን፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ እንደማይሆን’ በሰጠን ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል። (ራዕይ 21:4) ይህ ተስፋ ቅዠት እንዳልሆነ እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን? አምላክ ሊዋሽ ስለማይችል እርሱ በወሰነው ጊዜ እውን መሆኑ ፈጽሞ የማይቀር ነው። (ቲቶ 1:1, 2፤ ዕብራውያን 6:18) እነዚህን የተስፋ ቃሎች ዘወትር ማሰላሰል ይኖርብናል። ራሳችንን በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ እንደምንኖርና በበረከቶቹም እንደምንደሰት አድርገን መመልከታችን እምነት እንዳለን ያሳያል እንጂ እውን የማይሆን ቅዠት መቃዠት አይሆንብንም። እምነት ጳውሎስ በሰጠው ትርጉም መሠረት “በተስፋ የምንጠባበቃቸውን ነገሮች እንደምናገኝ የሚያረጋግጥ፣ የማናያቸውንም ነገሮች ስለመኖራቸው (እውን ስለመሆናቸው) የሚያስረዳ ነው።” (ዕብራውያን 11:1 የ1980 ትርጉም) የአምላክን ቃልና ቃሉን እንድንረዳና በሥራ ላይ እንድናውል የሚረዱንን ክርስቲያናዊ ጽሑፎች በየጊዜው በመመገብ እምነታችንን እናጠንክር። እንዲሁም መደበኛ በሆነ እና ባልሆነ መንገድ ለሌሎች ስለ መንግሥቱ በመናገር የምናሳልፈውን ሰዓት በጨመርን መጠን እምነታችን የበለጠ እየጠነከረና ተስፋችንም የበለጠ ብሩሕ እየሆነ ይሄዳል።
15. በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ረገድ ምን ግዴታ አለብን?
15 በተጨማሪም የአገልግሎታችንን ጥራት በማሻሻል ከመንግሥቱ እውነቶች ጋር ተስማምተን መሥራት ያስፈልገናል። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ሥራ እያለብን እንዴት የአገልግሎታችንን ጥራት ልናሻሽል እንችላለን? (ማቴዎስ 9:37, 38) ትምህርት የዕድሜ ገደብ የለውም የሚባለው አባባል እውነት ነው። ለምንም ያህል ብዙ ዓመት በምስክርነቱ ሥራ ስንካፈል የቆየን ብንሆን አቀራረባችንን ለማሻሻል እንችላለን። የአምላክን ቃል ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም ሰዎች የንጉሡን የኢየሱስ ክርስቶስን ድምፅ እንዲሰሙ በተሻለ ሁኔታ ልንረዳቸው እንችላለን። (ከዮሐንስ 10:16 ጋር አወዳድር።) የሰዎችን ዘላለማዊ ዕጣ በሚወስን ተግባር በመካፈል ላይ መሆናችንን ስንገነዘብ የአገልግሎት ቀበሌያችንን ደጋግመን በመሸፈን ሰዎች ራሳቸውን ከ“በጎች” ወይም ከ“ፍየሎች” ክፍል አድርገው ለመለየት እንዲችሉ ተደጋጋሚ የሆነ አጋጣሚ እንድንሰጣቸው መፈለግ ይገባናል። (ማቴዎስ 25:31-46) በእርግጥ ይህ ደግሞ እቤታቸው ያልተገኙትን ሰዎች በተለይም ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች በጥንቃቄ መመዝገብን ይጠይቃል።
መንግሥቱን መከታተላችሁን ቀጥሉ
16. የመንግሥቱን እውነቶች በመከታተል ረገድ ጥሩ ምሳሌ የተዉልን እነማን ናቸው? መንግሥቲቱንስ “የሚያገኟት” (የ1980 ትርጉም) (የሚይዟት አዓት) እንዴት ነው?
16 የመንግሥቱን እውነቶች በመከታተል ለመቀጠል ልባዊ የሆነ ጥረት ያስፈልጋል። የቀሪዎቹን ቅቡአን ክርስቲያኖች የቅንአት ምሳሌ ስንመለከት አንበረታታም? ለበርካታ ዓመታት የመንግሥቱን እውነቶች ሲከታተሉ ቆይተዋል። ይህ ጥረታቸው “ከአጥማቂው ዮሐንስ ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ የሰማይ መንግሥት ሰዎች ለመግባት የሚጋደሉባት ግብ ሆናለች። እየተጋደሉ ወደፊት የሚገፉ ሁሉም ያገኙአታል” በሚሉት የኢየሱስ ቃላት ተገልጿል። (ማቴዎስ 11:12 አዓት) እዚህ ላይ የተገለጸው ሐሳብ መንግሥቲቱ በጠላቶች እንደምትያዝ የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ መንግሥቲቱን የሚያገኙት ሰዎች ስለሚያደርጉት ጥረት የሚገልጽ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር “መጪውን መሲሐዊ መንግሥት ለማግኘት የሚደረገው ጉጉት የተሞላበትና ጠንካራ የሆነ ትግል በዚህ መንገድ ተገልጾአል” ብለዋል። ቅቡአኖች መንግሥቲቱን ለማግኘት ማንኛውንም ዓይነት ጥረት ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። “ሌሎች በጎችም” የአምላክ ሰማያዊት መንግሥት ምድራዊ ተገዢዎች የመሆንን ብቃት ለማግኘት ተመሳሳይ የሆነ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይፈለግባቸዋል።—ዮሐንስ 10:16
17. ዓለማዊ ቅዠቶችን የሚከታተሉ ሁሉ ዕጣቸው ምን ይሆናል?
17 የምንኖርበት ዘመን ልዩ አጋጣሚ የሚገኝበት ዘመን ነው። ዓለማዊ ቅዠቶችን ይከታተሉ የነበሩ ሁሉ የድካማቸውን ከንቱነት የሚገነዘቡበት ጊዜ ይመጣል። የሚገጥማቸው ዕጣ በሚከተሉት ቃላት በሚገባ ተገልጿል፦ “ተርቦም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፤ በሕልሙም፣ እነሆ፣ ይበላል፣ ነገር ግን ይነቃል ሰውነቱም ባዶ ነው፤ ተጠምቶም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፤ በሕልሙም፣ እነሆ፣ ይጠጣል፣ ነገር ግን ይነቃል፣ እነሆም ይዝላል ሰውነቱም አምሮት አለው” (ኢሳይያስ 29:8) የዚህ ዓለም ቅዠቶች ለማንም ሰው እርካታ ወይም ደስታ ለማስገኘት አይችሉም።
18. መንግሥቲቱ ይህን ያህል እውን ከሆነች ምን ዓይነት አካሄድ ልንከተል ይገባናል? ምን ዓይነት ተስፋስ እናገኛለን?
18 የይሖዋ መንግሥት እውን ናት። ክፉው ዓለማዊ የነገሮች ሥርዓት ለማይቀረው ዘላለማዊ ጥፋት የተጋፈጠ ሲሆን መንግሥቲቱ ግን የገዥነት ሥራዋን በማከናወን ላይ ነች። ስለዚህ “እንግዲህ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር ልብ ልንል ይገባናል። (1 ተሰሎንቄ 5:6) ልባችንንና አሳባችንን በመንግሥቱ እውነት ላይ እንዲያተኩር እናድርግና በዘላለማዊ በረከቶች እንደሰት። እንዲሁም ዕጣችን የዚህች መንግሥት ንጉሥ “እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” ሲል መስማት ይሁን።—ማቴዎስ 25:34
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትንንሽ ጽሑፎች ማኅበር የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የሚለውን መጽሐፍ ተመልከት።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ዓለማዊ ቅዠቶች ምንድን ናቸው? ልናስወግዳቸው የሚገባንስ ለምንድን ነው?
◻ ለዓለማዊ ቅዠቶች ተገዢ የመሆንን ከንቱነት የሚያሳዩን ምን ምሳሌዎች ናቸው?
◻ የፈጣሪን፣ በጽሑፍ የሰፈረውን ቃሉን፣ የኢየሱስ ክርስቶስንና የመንግሥቱን እውንነት የሚያረጋግጡ ምን ማስረጃዎች አሉ?
◻ በመንግሥቱ እውነታዎች ላይ ያለንን እምነት እንዴት ልናጠነክር እንችላለን?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብዛኛውን ጊዜ ዓለማዊ ቅዠቶች የሚመጡት ለቁሳዊ ሀብት ከፍ ያለ ጉጉት ከማሳደር ነው
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመንግሥቱን እውነቶች ከምንከታተልባቸው መንገዶች አንዱ ምሥራቹን መስበክ ነው
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናት የመንግሥቱን እውነቶች መከታተልህን ትቀጥላለህን?