የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 7/15 ገጽ 19-22
  • በጭንቀት ጊዜ መጽናኛ ማግኘት ይቻላል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በጭንቀት ጊዜ መጽናኛ ማግኘት ይቻላል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ተጨንቆ የነበረው ሐዋርያ ተጽናና
  • አምላክ የሚሰጠንን የሥራ ምድብ እንዴት መመልከት ይገባናል?
  • ከዚህ በፊት ያደረግናቸው ነገሮች በሚያስከትሉብን የጸጸት ስሜት በምንጨነቅበት ጊዜ መጽናናት
  • ጸሎትን በፍጹም ቸል አትበሉ
  • የተጨነቃችሁት ጥርጣሬ ስላላችሁ ነውን?
  • ይሖዋ መጽናናትን እንደሚሰጥ አስታውሱ
  • ተስፋ አትቁረጡ!
  • “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” በሆነው በይሖዋ ታመኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ይሖዋ ‘በመከራ ጊዜ መጠጊያችን’ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • ‘ያዘኑትን አጽናኑ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ይሖዋ በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 7/15 ገጽ 19-22

በጭንቀት ጊዜ መጽናኛ ማግኘት ይቻላል

የጭንቀት ስሜቶችን እንዴት መመልከት ይኖርብናል? ለይሖዋ የተወሰንን ሰዎች ከሆንን ግሩም የሆነ ተስፋና መንፈሳዊ ሀብት እያለን የጭንቀት ስሜት ቢያጋጥመን እንደ እንግዳ ነገር መቁጠር ይገባናልን? እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማን ከሆነ ለይሖዋ አገልግሎት ብቁ አይደለንም ማለት ነውን?

ሐዋርያው ያዕቆብ “ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 5:17) አምላክ ልዩ በሆነ መንገድ በኤልያስ ቢጠቀምበትም እንደሱ ያለ ታማኝ ነቢይ እንኳ የጭንቀት ስሜት ተሰምቶት ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት በጭንቀት ምክንያት “ይበቃኛል” ብሎ ነበር። “አቤቱ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ ብሎ እንዲሞት ለመነ።” (1 ነገሥት 19:4) ፍጹም አቋሙን እስከ መጨረሻ የጠበቀው ኢዮብ፣ ታማኟ ሐናና ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ጭንቀት አጋጥሞአቸዋል። መዝሙራዊው ዳዊት እንኳን “የልቤ ችግር ብዙ ነው ከጭንቀቴ አውጣኝ” ሲል ጸልዮአል።—መዝሙር 25:17

ይሖዋ ሰዎችን ለአገልግሎቱ መጠቀሙ ምንም ነገር የማይሰማቸው ግድየለሽ ሰዎች አያደርጋቸውም። ሰብአዊ ድካሞችና ስሜቶች ስለሚኖሩአቸው ፈተና በሚደርስባቸው ጊዜ የጭንቀት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። (ሥራ 14:15) ይሁን እንጂ የአምላክ አገልጋዮች የስሜት መረበሽን ለማሸነፍ የሚያስችሏቸው ከሌሎች የተሻለ እርዳታ ያገኛሉ። አንዳንድ ግለሰቦች የደረሰባቸውን የአዕምሮ መረበሽና የጭንቀት ስሜት እንዲያሸንፉ የረዳቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ እስቲ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመልከት።

ተጨንቆ የነበረው ሐዋርያ ተጽናና

ሐዋሪያው ጳውሎስ መጨነቅ ምን እንደሆነ ቀምሶአል። ጳውሎስ “ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ . . . ሥጋችን ዕረፍት አልነበረውም በውጭ ጠብ ነበር፣ በውስጥ ፍርሃት ነበር። ነገር ግን ሐዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 7:5, 6) ጳውሎስ የተጨነቀው በዚያ ጊዜ በተከሰቱት የተለያዩ የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ነበር። “በውጭ” ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ከባድ ስደት ነበር። (ከ2 ቆሮንቶስ 1:8 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ የተነሳው ዓይነት ችግር በሌሎች ጉባኤዎችም ይነሳ ይሆናል ብሎ ያስብ ስለነበረ “በውስጥ ፍርሃት ነበረ።”

ጳውሎስ ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የመጀመሪያ ደብዳቤውን ጽፎ ነበር። በደብዳቤውም ላይ በጉባኤው ውስጥ ያሉትን ብዙ መጥፎ ሁኔታዎች አውግዞአል። በዚህም ምክንያት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ ደብዳቤው የሚኖራቸው ስሜት አሳስቦታል። ይሁን እንጂ ቲቶ የቆሮንቶስ ሰዎች የጳውሎስን ደብዳቤ በጥሩ መንፈስ እንደተቀበሉት የሚገልጽ ጥሩ ዜና ይዞለት ስለ መጣ ተጽናንቷል። በተመሳሳይም ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ካሉት አገልጋዮቹ በአንዱ በመጠቀም የምስራች ይዞልን እንዲመጣና ጭንቀታችንን እንዲያቃልልልን ሊያደርግ ይችላል።

አምላክ የሚሰጠንን የሥራ ምድብ እንዴት መመልከት ይገባናል?

አንዳንድ ክርስቲያኖች ስለ አገልግሎታቸው ይጨነቃሉ። አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች አምላክ የሰጣቸውን የሥራ ምድብ መፈጸም በጣም ከባድ ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ሙሴ በግብጽ ለነበሩት እስራኤላውያን የአምላክ ወኪል ለመሆን ብቁ እንዳልሆነ ተሰምቶት ነበር። አንደበተ ርቱዕ እንዳልሆነ ተናግሮ ነበር። (ዘጸአት 3:11፤ 4:10) ይሁን እንጂ ሙሴ በአምላክ በመተማመንና አሮንን እንደ አፍ አድርጎ በመጠቀም የተሰጠውን ሥራ ተቀብሎአል።

ከጊዜ በኋላ ግን ሙሴ በአሮን በኩል መናገሩን አቆመ። በተመሳሳይም በመጀመሪያ ላይ የክርስትና አገልግሎት ከባድ ሆኖ የተሰማቸው ሰዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ስልጠና ካገኙ በኋላ ብቃት ያላቸው ሰባኪዎች ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል ብዙ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች አድገው አቅኚና ሚሲዮናዊ በመሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ችለዋል። ይሖዋ ለክርስቲያን አገልጋዮቹ የተሰጣቸውን ሥራ ለመፈጸም የሚያስችላቸውን ብቃትና ኃይል እንደሚሰጣቸው ትምክህት ሊጣልበት የሚችል መሆኑን ማወቅ ያጽናናል።—ዘካርያስ 4:6፤ 2 ቆሮንቶስ 2:14-17፤ ፊልጵስዩስ 4:13

ከዚህ በፊት ያደረግናቸው ነገሮች በሚያስከትሉብን የጸጸት ስሜት በምንጨነቅበት ጊዜ መጽናናት

በአምላክ አገልግሎት መሥራት የሚገባንን ያህል ባለመሥራታችን ምክንያት የሚሰማን ጸጸት ቅስማችንን ሊሰብርብን ይችላል። ለተወሰኑ ዓመታት ቀዝቅዞ የነበረ አንድ ወንድም በመስክ አገልግሎት መካፈል ይጀምራል። ከዚያም ጥቂት እንደቆየ በጠና ይታመምና የአልጋ ቁራኛ ይሆናል። በዚህ ሁኔታው ቅስሙ የተሰበረው ይህ ወንድም “ቀደም ብዬ ጠንካራ በሆንኩበት ጊዜ ከኃላፊነት ሸሸሁ። አሁን ለመሥራት በምፈልግበት ጊዜ ደግሞ መሥራት አቃተኝ” ብሏል።

ስላለፈው በመጸጸት የስሜት ኃይላችንን ከመጨረስ ይልቅ አሁን የተቻለንን ያህል ብንሠራ ጥበብ አይሆንምን? የኢየሱስ ግማሽ የሥጋ ወንድሞች የሆኑት ያዕቆብና ይሁዳ ሞቶ እስከተነሳበት ጊዜ ድረስ አላመኑም ነበር። በዚህ ምክንያት ቢጸጸቱም እንኳን ይህ ጸጸታቸው የአምላክ አገልጋዮች ከመሆንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ከመሆን እንኳን አላገዳቸውም።

ጸሎትን በፍጹም ቸል አትበሉ

የአምላክ አገልጋዮች በሚጨነቁበት ጊዜ ከልባቸው መጸለይ ይኖርባቸዋል እንዲያውም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በጭንቀት ጊዜ የተጸለዩ ብዙ ጸሎቶች ይገኛሉ። (1 ሳሙኤል 1:4-20፤ መዝሙር 42:8) አንዳንዶች “በጣም ስለተጨነቅሁ መጸለይ አልችልም” ብለው ያስባሉ። በዚህ ጊዜ ለምን ዮናስን አታስታውስም? ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ እያለ “ነፍሴ በዛለችብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] አሰብሁት ጸሎቴም ወደ አንተ ወደ ቅዱስ መቅደስህ ገባች። . . . እኔ ግን በምስጋና ቃል እሠዋልሃለሁ የተሳልሁትንም እከፍላለሁ” ብሏል። (ዮናስ 2:4-9) አዎ፣ ዮናስ ጸለየ፣ አምላክም አጽናናው አዳነውም።

በስዊድን የምትኖር አንዲት እህት ለብዙ ዓመታት በአቅኚነት ስታገለግል የቆየችና ከአገልግሎትዋም ብዙ በረከት ያገኘች ብትሆንም በድንገት ሊሰማት በጀመረው የሐዘን ስሜት ተዳከመች። ተስፋ መቁረጧን ለይሖዋ በጸሎት ነገረችው። ከጥቂት ቀን በኋላ በመጠበቂያ ግንብ ማህበር ቅርንጫፍ ቢሮ ከሚሠራ አንድ ወንድም ስልክ ተደወለላት። በዚያ አገር ያለውን የቤቴል ቤት ለማስፋፋት በሚደረገው ሥራ በሳምንት አንድ ቀን መጥታ ልትረዳ ትችል እንደሆነ ጠየቃት። ይህች እህት “በቤቴል ያለውን መንፈስና ሕንፃውን የማስፋፋቱን ሥራ ማየቴና በዚህ ሥራ ለመካፈል መቻሌ የሚያስፈልገኝን ተጨማሪ ኃይል ሰጠኝ” ብላለች።

የጭንቀት ስሜት የሚሰማን ከሆነ ይህን ስሜት ከምንቋቋምባቸው ዘዴዎች አንዱ ጸሎት እንደሆነ ማስታወስ ጥሩ ነው። (ቆላስይስ 4:2) ይሖዋም ለጸሎታችን ምላሽ በመስጠት ወደበለጠ አገልግሎት የሚያስገባ በር ይከፍትልናል ወይም ብዙ ፍሬ እንድናገኝ በማስቻል አገልግሎታችንን ይባርክልናል። (1 ቆሮንቶስ 16:8, 9) ያም ሆነ ይህ “የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች ሐዘንንም ከእርሷ ጋር አትጨምርም።” (ምሳሌ 10:22) ይህም የተሰበረውን መንፈሳችንን እንደሚያነሳሳ የተረጋገጠ ነው።

የተጨነቃችሁት ጥርጣሬ ስላላችሁ ነውን?

አንድ የይሖዋ አገልጋይ ጥርጣሬ የሚሰማው ጊዜ ሊኖር ይችላል። እንዲህ ያለው ሁኔታ በእኛ ላይ ቢከሰት ወዲያውኑ የአምላክን ሞገስ እንዳጣን አድርገን መደምደም አይኖርብንም። የጌታውን መነሳት ከዓይን ምስክሮች ሰምቶ የተጠራጠረውን ቶማስን ኢየሱስ አልቀበልህም አላለውም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ጥርጣሬው እንዲወገድለት ቶማስን በፍቅር ረዳው። ቶማስም ኢየሱስ ሕያው ሆኖ መነሳቱን በተገነዘበ ጊዜ በጣም ተደሰተ።—ዮሐንስ 20:24-29

ወደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ ሾልከው የገቡ አንዳንድ “አምላካዊ ያልሆኑ ሰዎች” በሐሰት ትምህርቶች፣ በማጉረምረምና በመሳሰሉት ድርጊቶቻቸው አንዳንዶች የሚያስጨንቅ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው አድርገው ነበር። ስለዚህ ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ “ጥርጣሬ ላላቸው ለአንዳንዶች ምህረት ማሳየታችሁን ቀጥሉ፤ ከእሳትም ነጥቃችሁ በማውጣት አድኗቸው” ሲል ጽፏል። (ይሁዳ 3, 4, 16, 22, 23) የይሁዳ የእምነት ጓደኞች በተለይም ሽማግሌዎች አምላክ በምህረት እንዲመለከታቸው ከፈለጉ ምህረት ለሚገባቸው ተጠራጣሪዎች ምህረት ማሳየት ይፈለግባቸው ነበር። (ያዕቆብ 2:13) የዘላለም ጥፋት “እሳት” ስለሚጠብቃቸው ዘላለማዊ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋአል። (ከማቴዎስ 18:8, 9፤ 25:31-33, 41-46) ጥርጣሬ የነበራቸው የእምነት ጓደኞቻችን የደግነት እርዳታ ተደርጎላቸው በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሲሆኑ በጣም ያስደስታል።

ከባድ ፈተናዎች ስለደረሱብን አምላክ ከእኛ ጋር መሆኑን የምንጠራጠር ከሆነ ችግራችንን ግልጽ አድርገን መጸለይ ያስፈልገናል። እንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጠን ሳናቋርጥ እንጠይቀው። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ጥበብና የጸለይንለትን ነገር ሳይነቅፍ በልግስና ይሰጠናል። ‘በምንም ሳንጠራጠር በእምነት’ መለመናችንን መቀጠል አለብን። “የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባህርን ማዕበል ይመስላልና።” ተጠራጣሪ የሆኑ ሰዎች በጸሎታቸውና በመንገዳቸው ሁሉ ስለማይጸኑና ስለሚወላውሉ ከአምላክ ዘንድ አንዳች አያገኙም። (ያዕቆብ 1:5-8) ይሖዋ ስለሚደርሱብን ፈተናዎች ተገቢ አመለካከት እንድንይዝና ፈተናዎቹንም ጸንተን እንድንቋቋማቸው እንደሚረዳን እምነት ይኑረን። በእምነት ጓደኞቻችን አማካኝነት ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ወቅት አንዳንድ ጥቅሶችን ልናገኝ እንችላለን። በአምላክ ተቆጣጣሪነት የሚፈጸሙ ሁኔታዎች ምን ማድረግ እንደሚኖርብን እንድንገነዘብ ሊረዱን ይችላሉ። መላእክትም እኛን በመምራት ሥራ ይካፈላሉ። አለዚያም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት መመሪያ ልናገኝ እንችላለን። (ዕብራውያን 1:14) ዋናው ነገር በአፍቃሪው አምላካችን ላይ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ጥበብ እንዲሰጠን መለመናችን ነው።—ምሳሌ 3:5, 6

ይሖዋ መጽናናትን እንደሚሰጥ አስታውሱ

ጳውሎስ በይሖዋ ላይ መመካቱን በጸሎት አሳይቶአል። የመጽናናትም ምንጭ ይሖዋ እንደሆነ አውቋል። ሐዋሪያው “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፣ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን” ሲል ጽፎአል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

የመጽናናት ሁሉ አምላክ አገልጋዮቹ የሚያጋጥማቸውን ጭንቀት ያውቃል። ከጭንቀታቸውም ሊያሳርፋቸው ይፈልጋል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በማሰብ በተጨነቀ ጊዜ ከጭንቀት የሚያሳርፈው መልዕክት በክርስቲያን ጓደኛው በቲቶ አማካኝነት መጥቶለታል። ዛሬም መጽናኛ ከምናገኝባቸው መንገዶች አንዱ ይህ ሊሆን ይችላል። ጭንቀት በሚያጋጥመን ጊዜ ራሳችንን ከማግለል መራቅ አለብን። (ምሳሌ 18:1) አምላክ እኛን ከሚያጽናናባቸው መንገዶች አንዱ ከክርስቲያን ጓደኞቻችን ጋር የምናደርገው ስብሰባ ነው። ‘ከመጠን በላይ ስላዘንኩና ቅስሜ ስለተሰበረ ከክርስቲያን ወዳጆቼ ጋር ለመሰብሰብና አብሮ ለመዋል የሚያስችል ጥንካሬ የለኝም’ ብለን ልናስብ እንችላለን። ይሁን እንጂ ይህን ዓይነቱን ስሜት መዋጋት ይገባናል እንጂ የእምነት ጓደኞቻችን ሊሰጡን ከሚችሉት መጽናናት ራሳችንን ማግለል አይገባንም።

ተስፋ አትቁረጡ!

አንዳንዶቻችን ይህን ያህል ከባድ ጭንቀት እንዲሰማን የሚያደርግ ከባድ ፈተና አጋጥሞን ላያውቅ ይችላል። ይሁን እንጂ ሰውነት የሚያደቅቅ በሽታ፣ የትዳር ጓደኛ ሞት፣ ወይም ሌላ ዓይነት በጣም ፈታኝ የሆነ ሁኔታ የጭንቀት ስሜት ሊያመጣብን ይችላል። ይህን የመሰለ ሁኔታ ቢያጋጥመን በመንፈሳዊ ታመናል ብለን መደምደም የለብንም። አንድ የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሰው ለአምላክ አገልግሎት ሙሉ ብቃት ያለውና እንዲያውም ሌሎችን እንኳን በመንፈሳዊ ለመርዳት የሚችል ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ወንድሞቹ የመንፈስ ጭንቀት ያደረባቸው ሰዎች አንድ ስህተት እንደፈጸሙ ወይም በመንፈሳዊ እንደታመሙ እንዲያስቡ ሳይሆን ‘በሚያጽናና ቃል እንዲናገሩአቸው’ አበረታትቷል። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ጭንቀት ከመጥፎ ድርጊትና ከጥፋተኝነት ጋር የሚዛመድበት ጊዜ ቢኖርም አምላክን በንጹህ ልብ የሚያገለግሉ ግን የመንፈስ ጭንቀት የሚያጋጥማቸው በዚህ ምክንያት አይደለም። አምልኮታቸው፣ በከባድ ችግር የሚያቀርቡትም ቢሆን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አለው። ይሖዋም ይወዳቸዋል፣ አስፈላጊውንም እርዳታና ማጽናኛ ይሰጣቸዋል።—መዝሙር 121:1-3

የመንፈሳዊ እስራኤል ክፍል የሆኑት ቀሪዎች በ1918 በደረሰባቸው ፈተና በጣም ተጨንቀው ነበር። (ከገላትያ 6:16 ጋር አወዳድር።) የስብከት ድርጅታቸው ወደ መጥፋት ተቃርቦ ነበር። አንዳንዶቹም አለአግባብ ታስረዋል። ከቀድሞ ባልደረቦቻቸው ብዙዎቹ ከሃዲዎችና ተቃዋሚዎች ሆነዋል። ከዚህም በላይ ታማኞቹ ቅቡአን አምላክ ይህ ሁሉ እንዲከሰት የፈቀደበትን ምክንያት አልተረዱም ነበር። ለጥቂት ጊዜ ‘በለቅሶ ዘርተው ነበር።’ ይሁን እንጂ ተስፋ አልቆረጡም። ይሖዋን ማገልገላቸውን ቀጠሉ፣ ራሳቸውንም መረመሩ። ውጤቱስ ምን ሆነ? ‘ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው መጡ።’ (መዝሙር 126:5, 6) ቅቡአኑ አምላክ እንደነዚህ ያሉ ፈተናዎች እንዲደርስባቸው የፈቀደው እየቀረበ ላለው ዓለም አቀፍ የመከር ሥራ ሊያጠራቸው እንደሆነ በአሁኑ ጊዜ ተገንዝበዋል።

የተለያዩ ፈተናዎች ስለደረሱብን ተጨንቀን ከሆነ ከቅቡአን ቀሪዎች ተሞክሮ ልንጠቀም እንችላለን። ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ እያለቀስንም ቢሆን ትክክል የሆነውን ማድረጋችንን እንቀጥል። ከጊዜ በኋላ ከፈተናዎቻችን የምንወጣበት መንገድ ይከፈትና ‘በደስታ እየጮህን እንመጣለን።’ አዎ፣ ፈተናዎቻችንን ጸንተን ከተቋቋምን የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ የሆነውን ደስታ እናገኛለን። ይሖዋ ‘የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ መሆኑን ያረጋግጥልናል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ