የሕይወትን ሩጫ እንዴት እየሮጣችሁ ነው?
“በሩጫ ውድድር ሁሉም እንደሚሮጡና ከእነርሱም አንዱ ብቻ ሽልማት እንደሚቀበል ታውቁ የለምን? ስለዚህ እናንተም ሽልማቱን ለመቀበል ሩጡ።”—1 ቆሮንቶስ 9:24 የ1980 ትርጉም
1. መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያናዊ አኗኗራችንን ከምን ጋር ያመሳስለዋል?
መጽሐፍ ቅዱስ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት ከሩጫ እሽቅድምድም ጋር ያመሳስለዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሕይወቱ መጨረሻ ገደማ ስለ ራሱ “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፣ ሩጫውን ጨርሻለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄያለሁ” ብሏል። ለክርስቲያን መሰሎቹም “እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን . . . በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት [በመጽናት አዓት] እንሩጥ” በማለት እንደርሱ እንዲያደርጉ አጥብቆ አሳስቧቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 4:7፤ ዕብራውያን 12:1
2. ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ላይ ምን የሚያበረታታ ጅምር እናያለን?
2 የሩጫ ውድድርም መነሻ፣ ውድድሩ የሚካሄድበት ሜዳና የመጨረሻ ግብ ወይም መድረሻ ስላለው ሕይወት ለማግኘት የምናደርገው ጥረት ከሩጫ ውድድር ጋር መመሳሰሉ ተገቢ ነው። ለሕይወት ለመብቃት በምናደርገው የመንፈሳዊ ዕድገት ሂደትም እንደዚሁ ነው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው በየዓመቱ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በሕይወት ሩጫ እሽቅድምድም ውስጥ ገብተው ጥሩ ጅምር ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል ባለፉት አምስት ዓመታት 1,336,429 ሰዎች ራሳቸውን ወስነው በውኃ በመጠመቅ ወደ ሩጫ ውድድሩ ውስጥ ገብተዋል። እንዲህ የመሰለው ብርቱ አጀማመር በጣም የሚያበረታታ ነው። ይሁን እንጂ ዋናው ቁም ነገር የመጨረሻው ግብ ላይ እስኪደርሱ ድረስ በሩጫ ውድድሩ ላይ መቆየቱ ነው። እናንተስ ይህን እያደረጋችሁ ነውን?
ለሕይወት የሚደረግ ሩጫ
3, 4. (ሀ) ጳውሎስ በሩጫው ውድድር እስከ መጨረሻ የመቆየትን አስፈላጊነት ያመለከተው እንዴት ነው? (ለ) አንዳንዶች የጳውሎስን ምክር ሳይቀበሉ የቀሩት እንዴት ነው?
3 ጳውሎስ በሩጫው የመቆየትን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽ “በሩጫ ውድድር ሁሉም እንደሚሮጡና ከእነርሱም አንዱ ብቻ ሽልማት እንደሚቀበል ታውቁ የለምን? ስለዚህ ሽልማቱን ለመቀበል ሩጡ” በማለት መክሯል።—1 ቆሮንቶስ 9:24
4 እርግጥ ነው፣ በጥንት ዘመን በሚደረጉት ጨዋታዎች ሽልማቱን የሚቀበለው አንዱ ብቻ ነበር። በሕይወት ሩጫ ግን እያንዳንዱ ሰው ለሽልማቱ ብቁ ሊሆን ይችላል። እሽቅድምድሙን እስከ መጨረሻው ድረስ ለመፈጸም በውድድሩ ቦታ መቆየት የግድ አስፈላጊ ነው! ደስ የሚለው ነገር ብዙዎች ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳደረገው በእሽቅድምድሙ ስፍራ እስከ ሕይወታቸው መጨረሻ በታማኝነት ሮጠዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎችም መሮጣቸውን ቀጥለዋል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ወደ ፊት ሳይገፉ ወይም እስከ መጨረሻው ለመድረስ ጥረት ሳያደርጉ ቀርተዋል። ሌሎች ነገሮች እንዲያደናቅፉአቸው ስለፈቀዱ ከእሽቅድምድሙ እስከ መውጣት ወይም በአንድ ዓይነት መንገድ ከእሽቅድምድሙ ሥፍራ እስከ መባረር ደርሰዋል። (ገላትያ 5:7) ይህም ሁላችንም ለሕይወት በሚደረገው እሽቅድምድም እየሮጥን ያለነው እንዴት እንደሆነ ራሳችንን እንድንመረምር ምክንያት ሊሆነን ይገባል።
5. ጳውሎስ የሕይወትን ሩጫ ከግጥሚያ ውድድር ጋር ማመሳሰሉ ተገቢ ነበርን? አብራራ።
5 ጳውሎስ “አንዱ ብቻ ዋጋውን ይቀበላል” ሲል በአእምሮው ይዞት የነበረው ምንን ነበር? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በሕይወት ሩጫ እሽቅድምድም ውስጥ ከገቡት ውስጥ አንዱ ብቻ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ይቀበላል ማለቱ አልነበረም። ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ የአምላክ ፈቃድ መሆኑን ደጋግሞ ስለተናገረ አንድ ሰው ብቻ የዘላለም ሕይወት ይቀበላል ማለቱ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። (ሮሜ 5:18፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4፤ 4:10፤ ቲቶ 2:11) ጳውሎስ የሕይወት ሩጫ እሽቅድምድም እያንዳንዱ ተወዳዳሪ ሌሎቹን ሁሉ ለማሸነፍ የሚሞክርበት ውድድር ነው ማለቱ አልነበረም። ይህ ዓይነቱ የውድድር መንፈስ የነበረው በዚያ ዘመን ከኦሎምፒክ ጨዋታዎችም እንኳን ይበልጥ ክብር እንዳለው ይታሰብ በነበረው በኢስትሚያን ጨዋታ ተወዳዳሪዎች መካከል ብቻ እንደነበረ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አሳምረው ያውቁ ነበር። ታዲያ ጳውሎስ በአእምሮው ይዞት የነበረው ነገር ምን ነበር?
6. ጳውሎስ ስለ ሯጩና ስለ ሩጫ ውድድሩ በተናገረበት ጥቅስ ዙሪያ ያሉት ሐሳቦች የሚገልጹት ምንድን ነው?
6 በመሠረቱ ጳውሎስ የሯጩን ምሳሌ ሲጠቅስ ይናገር የነበረው ስለ ራሱ የመዳን ተስፋ ነበር። ቀደም ባሉት ቁጥሮች [በቁጥር 19-22] ላይ እንዴት ጠንክሮ እንደሠራና በብዙ መንገድም ጥረት እንዳደረገ ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 9:19-22) ከዚያም በቁጥር 23 ላይ “በወንጌልም ማኅበርተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ” በማለት ተናግሯል። ሐዋርያ እንዲሆን መመረጡ ወይም ለሌሎች በመስበክ ብዙ ዓመታት ማሳለፉ ብቻ ለመዳኑ ዋስትና እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። በምሥራቹ በረከቶች ለመካፈል ለምሥራቹ ሲል አቅሙ የፈቀደለትን ማንኛውንም ነገር ማድረጉን መቀጠል ነበረበት። “አንዱ ብቻ ሽልማት በሚቀበልበት” በኢስትሚያን ውድድር የእግር ሩጫ እሽቅድምድም እንደሚሮጥ ያህል ራሱን በማትጋት ሙሉ በሙሉ ለማሸነፍ በማሰብ መሮጥ ነበረበት።—1 ቆሮንቶስ 9:24ሀ
7. “ሽልማቱን ለመቀበል ሲባል ለመሮጥ” ምን ያስፈልጋል?
7 ከዚህ ልንማረው የምንችል ብዙ ነገር አለ። በእሽቅድምድም ሥፍራ የሚገባ ሁሉ ለማሸነፍ የሚፈልግ ቢሆንም ሊያሸንፉ የሚችሉት ሙሉ በሙሉ ለማሸነፍ ቆርጠው የገቡ ብቻ ናቸው። በዚህም ምክንያት በእሽቅድምድሙ ስለገባን ብቻ ረክተን መዘናጋት አይኖርብንም። ‘በእውነት ውስጥ’ ስለሆንን ብቻ ማንኛውም ነገር ቀላል ይሆናል ብለን ማሰብ የለብንም። ክርስቲያን የሚለውን ስም ተሸክመን ይሆናል፣ ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች መሆናችንን የምናረጋግጥበት ማስረጃ አለንን? ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን ማድረግ እንዳለበት የምናውቃቸውን ነገሮች ይኸውም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መገኘት፣ በመስክ አገልግሎት መሳተፍና የመሳሰሉትን እናደርጋለንን? እንዲህ እያደረግን ከሆነ ይህ የሚያስመሰግን ነገር ነው፣ በዚህ እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ልማድም ለመጽናት መጣር ይኖርብናል። ይሁንና ከምናደርገው ነገር ይበልጥ ተጠቃሚዎች ልንሆን እንችላለንን? ለምሳሌ ያህል በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ለመስጠት እንድንችል ሁልጊዜ እንዘጋጃለንን? የምንማረውን ነገር በግል ሕይወታችን በሥራ ላይ ለማዋል እንጥራለንን? በመስክ አገልግሎታችን ላይ የሚያጋጥመን ችግር ምንም ይሁን ምን የተሟላ ምሥክርነት ለመስጠት እንድንችል ችሎታችንን ለማሻሻል ትኩረት እንሰጣለንን? ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ መጠይቅ ማድረግና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራትን የሚያስከትለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቀበል ፈቃደኞች ነንን? ጳውሎስ “ስለዚህ እናንተም ሽልማቱን ለመቀበል ሩጡ” በማለት አጥብቆ አሳስቧል።—1 ቆሮንቶስ 9:24ለ
በሁሉም ነገር ራስን መግዛት አሳዩ
8. ጳውሎስ “በነገር ሁሉ ራስን መግዛት” እንዲያሳዩ መሰል ክርስቲያኖችን ለመምከር ያነሳሳው ምን ሊሆን ይችላል?
8 ጳውሎስ በሕይወቱ ዘመን ብዙ ሰዎች ለሕይወት በሚደረገው እሽቅድምድም ፍጥነታቸውን ሲቀንሱ፣ አቅጣጫቸውን ሲቀይሩ፣ ወይም እስከነጭራሹ መሮጣቸውን ሲተዉ ተመልክቷል። (1 ጢሞቴዎስ 1:19, 20፤ ዕብራውያን 2:1) ክርስቲያን ባልደረቦቹ በአድካሚና በማያቋርጥ ውድድር ውስጥ እንዳሉ በተደጋጋሚ ያሳስባቸው የነበረው በዚህ ምክንያት ነበር። (ኤፌሶን 6:12፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:12) የሯጩን ምሳሌ አንስቶ ሰፋ አድርጎ ሲያብራራ “የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 9:25ሀ) ጳውሎስ ይህን ሲናገር የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አሳምረው የሚያውቁትን አንድ ነገር ይኸውም በኢስትሚያን ጨዋታ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች የሚሰጣቸውን ጥብቅ ማሠልጠኛ መጥቀሱ ነበር።
9, 10. (ሀ) አንድ ጸሐፊ የኢስትሚያን ግጥሚያ ተወዳዳሪዎችን የገለጿቸው እንዴት ነው? (ለ) ስለገለጻው በተለይ ልናስተውለው የሚገባን ምንድን ነው?
9 በሥልጠና ላይ ያለ ተወዳዳሪን የሚገልጽ ሕያው መግለጫ እነሆ፦ “ሠልጣኙ የአሥር ወር ሥልጠና ሳይሰጠው መወዳደር ስለማይችል ወደ ማሠልጠኛው ገብቶ ለሥልጠናው ደንቦችና ሕጎች ራሱን በደስታና ያለማንገራገር ያስገዛል። . . . በሚያጋጥሙት ጥቃቅን ችግሮች፣ በድካሞቹና ከምግብና ከመጠጥ በመታገዱ ሁሉ ኩራት ይሰማዋል። የአሸናፊነት እድሉን በትንሹም እንኳን ዝቅ ሊያደርግበት ከሚችል ከማንኛውም ነገር በከፍተኛ ሁኔታ መራቅን እንደ ክብር ይቆጥረዋል። እሱ በከባድ ጥረት ሲደክም ሌሎች ሰዎች ግን አርፈው ምግባቸውን ሲመገቡ፣ ገላቸውን እየታጠቡ ሲዝናኑና ደስታ በሞላበት ሕይወት ሲንደላቀቁ ያያል፤ ሆኖም ልቡ ያረፈው በሽልማቱ ላይ ስለሆነና ይህንንም ሽልማት ለማግኘት ጽኑ ሥልጠና አስፈላጊ እንደሆነ ስለሚገነዘብ ሥልጠናው የማይመለከታቸው ሰዎች በሚያሳልፉት ሕይወት ቅንጣት ያህል እንኳን የመቅናት ሐሳብ አይመጣበትም። በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ተዘናግቶ የሥልጠናውን ሥርዓት ቢያጓድል የማሸነፍ ዕድሉ እንደሚያመልጠው ያውቃል።”—ዘ ኤክስፖዚተርስ ባይብል ጥራዝ 5 ገጽ 674
10 ይበልጥ ሊተኮርበት የሚገባው በሥልጠና ላይ ያለው ግለሰብ እንዲህ ዓይነቱን ጽኑ ራስን የመካድ ሥራ ያለማቋረጥ መከታተሉን “እንደ ክብር የሚቆጥረው” መሆኑ ነው። እንዲያውም ሌሎች ያላቸውን መዝናናትና ምቾት ሲያይ “ቅንጣት ያህል እንኳን የመቅናት ሐሳብ አይመጣበትም።” ከዚህ ልንማር የምንችለው ነገር አለን? አዎ፣ በእርግጥ አለ።
11. በሕይወት ሩጫ እየሮጥን እያለን መጠንቀቅ ያለብን ከምን ተገቢ ያልሆነ አመለካከት ነው?
11 ኢየሱስ “ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ መንገዱም የቀጠነ ነውና የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” በማለት የተናገረውን አስታውሱ። (ማቴዎስ 7:13, 14) ‘በጠባቡ ደጅ’ ለመጓዝ በምትጥሩበት ጊዜ በሠፊው መንገድ ላይ ያሉት ሰዎች ያገኙት መስሎ በሚሰማችሁ ነፃነትና መዝናናት ትቀናላችሁን? ሌሎች የሚያደርጓቸው በራሳቸው መጥፎ መስለው ላይታዩ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች እያመለጧችሁ ያሉ ሆኖ ይሰማችኋልን? በዚህ መንገድ ለመጓዝ ቆርጠን የተነሳንበትን ምክንያት ካላስታወስን በቀላሉ እንዲህ ሊሰማን ይችላል። ጳውሎስ “እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፣ እኛ ግን የማይጠፋውን” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 9:25ለ
12. ሰዎች ለማግኘት የሚፈልጉት ክብርና ዝና በኢስትሚያን ግጥሚያዎች ላይ እንደሚሰጠው አክሊል ጠፊ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
12 በኢስትሚያን ግጥሚያ የሚያሸንፈው ሰው የሚቀበለው ሽልማት በጥቂት ቀናት ወይም ሳምንታት መጠውለጉና መድረቁ የማይቀር የኢስትሚያን የጥድ አበባ ጉንጉን ወይም ይህን የሚመስል ሌላ ተክል ነበር። በእርግጥም ሯጮቹ የሚወዳደሩት ጠፊውን የአበባ ጉንጉን ለማግኘት ሳይሆን ከእርሱ ጋር ተያይዞ ለሚመጣው ክብርና ዝና ነበር። አንድ ጸሐፊ እንደገለጹት አሸናፊው ወደ ቤቱ ሲመለስ የአንድ ድል አድራጊ ጀግና አቀባበል ይደረግለት ነበር። አብዛኛውን ጊዜ እርሱን ያጀበው ሠልፍ እንዲያልፍለት የከተማዋ ቅጥር ግድግዳዎች ፈርሰው በዚያ እንዲያልፍ ይደረግለትና ለክብሩም ሐውልቶች ይቆሙለት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ቢደረግለትም ክብሩ ያው ጠፊና አላፊ ነበር። ዛሬ ካሉት ሰዎች ውስጥ እነዚያ አሸናፊዎች እነማን እንደነበሩ የሚያውቁት በጣም ጥቂቶች ሲሆኑ እነርሱም ቢሆኑ አብዛኞቹ ስለ አሸናፊዎቹ ምንም ደንታ የሌላቸው ናቸው። በዓለም ላይ ሥልጣን፣ ዝናና ሀብት ለማትረፍ ብለው ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጤንነታቸውንና የቤተሰባቸውን ደስታም ሳይቀር የሚሠውና በአምላክ ዘንድ ግን ባለጠጎች ያልሆኑ ሰዎች ዓለማዊ “አክሊላቸው” እንደ ሕይወታቸው ሁሉ አላፊ ነው።—ማቴዎስ 6:19, 20፤ ሉቃስ 12:16-21
13. በሕይወት ሩጫ ላይ ያለ ሰው አኗኗር ከአንድ ስፖርታዊ ሯጭ የሚለየው እንዴት ነው?
13 የሩጫ ተወዳዳሪዎች የሆኑ ሰዎች ከላይ እንደተገለጹት የመሳሰሉ ጥብቅ የሥልጠና መሥፈርቶችን ለማሟላት ፈቃደኞች ይሆኑ ይሆናል፤ ሆኖም ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ስለሆነ ግጥሚያው ካለፈ በኋላ ግን ወደተለመደው አኗኗራቸው ይመለሳሉ። ችሎታቸውን ላለማጥፋት ሲሉ አልፎ አልፎ ሥልጠናቸውን ይቀጥሉበት ይሆናል። ይሁን እንጂ ግፋ ቢል ለሚቀጥለው ውድድር ለመቅረብ ሲዘጋጁ ካልሆነ በቀር ያንኑ ዓይነት ከባድ ራስን የመካድ መንገድ አይከተሉም። በሕይወት እሽቅድምድም ላይ ላሉት ግን እንዲህ አይደለም። ለእነርሱ ሥልጠናና ራስን መካድ የሕይወታቸው መንገድ መሆን አለበት።—1 ጢሞቴዎስ 6:6-8
14, 15. በሕይወት ሩጫ የሚወዳደር ሰው ያለማቋረጥ ራሱን መግዛት ማሳየት ያለበት ለምንድን ነው?
14 ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰብስበው ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱና ሌሎች ሰዎች “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም [የመከራውን እንጨት አዓት] ተሸክሞ [ያለማቋረጥ አዓት] ይከተለኝ” ብሏቸዋል። (ማርቆስ 8:34) ይህን ጥሪ ስንቀበል ባለማቋረጥ የመከራውን እንጨት ለመሸከም መዘጋጀት ያለብን ራስን መካድ ብቻ በራሱ ልዩ ሽልማት ስላለው ሳይሆን የአንዳፍታ ጥንቃቄ ጉድለት፣ የአንድ ጥሩ ማስተዋል መዛባት ቀደም ብሎ የተገነባውን ሁሉ ሊያበላሸው፣ አልፎ ተርፎም የዘላለም ደህንነታችንንም ሳይቀር አደጋ ላይ ሊጥለው ስለሚችል ነው። አብዛኛውን ጊዜ መንፈሳዊ ዕድገት የሚመጣው ቀስ በቀስ ሲሆን ዘወትር ካልተጠነቀቅን ግን በአንድ ጊዜ ባዶ ሊሆን ይችላል።
15 በተጨማሪም ጳውሎስ “በነገር ሁሉ” ማለትም በሁሉም የኑሮ ዘርፍ ራስን መግዛት እንድናሳይ አጥብቆ አሳስቦናል። ይህም አስተዋይነት ነው፤ ምክንያቱም አንድ ሠልጣኝ ለፍላጎቱ ተገዥ ከሆነ ወይም የብልግና ኑሮ የሚኖር ከሆነ የሚደርስበትን አካላዊ ሥቃይና ድካም ቢታገሥ ምን ጥቅም አለው? በተመሳሳይም በሕይወት ሩጫችን በነገር ሁሉ ራስን መግዛት ማሳየት አለብን። አንድ ሰው ስካርና ምንዝርን በመሳሰሉት ነገሮች ረገድ ራሱን ሊገዛ ይችል ይሆናል፣ ሆኖም ትዕቢተኛና ጠበኛ ከሆነ የዚህን ሁሉ ዋጋ ይቀንስበታል። ወይም ደግሞ ለሌሎች ታጋሽና ደግ ሆኖ በግል ሕይወቱ ግን በስውር አንድ ዓይነት ኃጢአት የሚፈጽም ከሆነስ? ራስን መግዛት ሙሉ በሙሉ ጠቃሚ እንዲሆን ከተፈለገ “በነገር ሁሉ” መገለጥ አለበት።—ከያዕቆብ 2:10, 11 ጋር አወዳድር።
“ግብ እንደሌለው ሰው በከንቱ” አትሩጡ
16. “ያለግብ” አለመሮጥ ምን ማለት ነው?
16 በሕይወት ሩጫ ካሰብነው ለመድረስ የሚያስፈልገውን ብርቱ ጥረት በማየት ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሮአል፦ “ስለዚህ እኔ ግብ እንደሌለው ሰው በከንቱ አልሮጥም፤ ከነፋስ ጋር እንደሚታገል በከንቱ የምታገል ሰው አይደለሁም” (1 ቆሮንቶስ 9:26 አዓት) “ግብ እንደሌለው ሰው” ወይም “ያለግብ” የሚለው ቃል ቃል በቃል ሲተረጎም “ያለማስረጃ” (እንደ ኪንግደም ኢንተርሊኒየር ትርጉም)፣ “ያለተመልካች፣ ያለምልክት” (የላንጅ ኮሜንታሪ) ማለት ነው። ስለዚህ “ያለግብ” አለመሮጥ ሯጩ ወዴት እየሮጠ እንዳለ ለማንኛውም ተመልካች ግልጽ መሆን አለበት ማለት ነው። ይህን ቃል ዘ አንከር ባይብል “በጠመዝማዛ አካሄድ” ብሎ ተርጉሞታል። በባሕር ዳር ላይ ወዲያና ወዲህ የተዘበራረቀ፣ እዚህም እዚያም ዙሪያ መሥመር የሠራና አንዳንዴም ወደ ኋላ የሚመለስ ዱካ ብትመለከቱ በዚያ መንገድ ያለፈው ሰው እየሮጠ ነበር ብላችሁ በጭራሽ አታስቡም። ነገር ግን በቀጥተኛ መሥመር ላይ የሄዱ ረዣዥምና እያንዳንዱ ከሌላው ራቅ ራቅ ያሉ ዱካዎች ብትመለከቱ የሚሄድበትን አቅጣጫ በትክክል የሚያውቅ ሰው ዱካዎች እንደሆኑ ትደመድማላችሁ።
17. (ሀ) ጳውሎስ “ያለግብ” የማይሮጥ እንደነበረ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በዚህ ረገድ ጳውሎስን ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው?
17 የጳውሎስ ሕይወት “ያለግብ” የሚሮጥ እንደነበረና እንዳልነበረ በግልጽ አሳይቷል። ክርስቲያን አገልጋይና ሐዋርያ እንደነበረ የሚያረጋግጥበት በቂ ማስረጃ ነበረው። እርሱን ለማግኘት ብሎ ሕይወቱን ሙሉ ብርቱ ጥረት ያደረገለት አንድ ግብ ነበረው። ዝና፣ ሥልጣን፣ ሀብት ወይም ምቾት ሊያገኝ ይችል የነበረ ሰው ቢሆንም በእነዚህ ነገሮች ተታልሎ ዋና ግቡን ከመከታተል ወደ ኋላ አላለም። (ሥራ 20:24፤ 1 ቆሮንቶስ 9:2፤ 2 ቆሮንቶስ 3:2, 3፤ ፊልጵስዩስ 3:8, 13, 14) የሕይወት ጎዳናችሁን መለስ ብላችሁ ስትቃኙ የምትመለከቱት ምን ዓይነት ዱካ ወይም መሥመር ነው? ግልጽ አቅጣጫን የሚያሳይ ቀጥተኛ መሥመር ነው ወይስ ያለአንዳች ግብ ወዲያና ወዲህ የተጠማዘዘ? በሕይወት ሩጫ ላይ እየተወዳደራችሁ እንዳላችሁ የሚያሳይ ማስረጃ አለን? ወደዚህ እሽቅድምድም የገባነው ለይምሰል ወዲያ ወዲህ ለማለት ሳይሆን እስከመጨረሻው ለመሮጥ መሆኑን አስታውሱ።
18. (ሀ) በእኛ በኩል “ንፋስን ከመጎሰም” ጋር ሊመሳሰል የሚችለው ምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ይህስ አደገኛ አካሄድ የሆነው ለምንድን ነው?
18 ጳውሎስ በተጨማሪ ራሱን ከአንድ ሌላ ስፖርታዊ ጨዋታ ጋር በማነፃፀር “ከነፋስ ጋር እንደሚታገል በከንቱ የምታገል ሰው አይደለሁም” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 9:26ለ) በሕይወት ሩጫ እሽቅድምድማችን ውስጥ ሰይጣንን፣ ዓለምንና የራሳችንን አለፍጽምና ጨምሮ ብዙ ጠላቶች አሉን። እነዚህን ጠላቶቻችንን እንደ ጥንታዊ የቡጢ ታጋይ በደንብ በተነጣጠረ የቡጢ ምት መትተን ልንጥላቸው መቻል አለብን። የሚያስደስተው ነገር ይሖዋ አምላክ የሚያሠለጥነንና በትግሉም የሚረዳን መሆኑ ነው። በቃሉ፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መመሪያዎችን ሰጥቶናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እያነበብንና ወደ ስብሰባዎች እየሄድን የምንማረውን በሥራ ላይ የማናውል ከሆነ ግን “ነፋስን በመጎሰም” ጥረታችንን ሁሉ ማባከናችን አይደለምን? እንዲህ ማድረጋችን በአደገኛ ሁኔታ ላይ ይጥለናል። ውጊያው ያለቀ መስሎን በሐሰተኛ የመረጋጋት ስሜት ውስጥ እንወድቃለን፣ ጠላቶቻችንን ግን ገና አላሸነፍንም። ለዚህም ነው ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ” በማለት የመከረው። “ነፋስን መጎሰም” ጠላቶቻችንን አካለ ስንኩል አድርጎ ጉዳት እንደማያደርስባቸው ሁሉ “ሰሚዎች ብቻ” መሆንም የአምላክን ፈቃድ እያደረግን መሆኑን አያረጋግጥም።—ያዕቆብ 1:22፤ 1 ሳሙኤል 15:22፤ ማቴዎስ 7:24, 25
19. የተጣልን እንዳንሆን ወይም የማንበቃ ሆነን እንዳንገኝ ልናረጋግጥ የምንችለው እንዴት ነው?
19 በመጨረሻም ጳውሎስ ግቡን ለማግኘት የሚያስችለውን ምሥጢር ነግሮናል፦ “ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልኩ እንዳልሆን [የማልበቃ ሆኜ እንዳልገኝ አዓት] ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 9:27) እኛም እንደ ጳውሎስ ፍጹም ያልሆነው ሥጋችን ተቆጣጣሪያችን እንዲሆን ከመፍቀድ ይልቅ እኛ በእርሱ ላይ ጌታ ልንሆንበት ይገባናል። ሥጋዊ ዝንባሌዎችን፣ ናፍቆቶችንና ምኞቶችን ነቅለን መጣል ያስፈልገናል። (ሮሜ 8:5-8፤ ያዕቆብ 1:14, 15) ይህን ማድረግ ሥቃይ ያለበት ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም “መጎሰም” ተብሎ የተተረጎመው ቃል፣ ቃል በቃል ‘ከዓይን ሥር መምታት’ (ኪንግደም ኢንተርሊኒየር ትርጉም) ማለት ነው። ለውዳቂው ሥጋችን ፍላጎት ተሸንፈን ከመሞት ይልቅ በመጐሰም የጠቆረ ዓይን ይዘን መኖር አይሻለንምን?—ከማቴዎስ 5:28, 29፤ 18:9ና ከ1 ዮሐንስ 2:15-17 ጋር አወዳድር።
20. በተለይ አሁን በሕይወት ሩጫ እንዴት በመሮጥ ላይ እንዳለን መመርመር አጣዳፊ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?
20 ዛሬ ወደ ሕይወት ሩጫው መጨረሻ እየተቃረብን ነው። ሽልማቶች የሚሰጡበት ጊዜም ቀርቧል። ሽልማቱ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች “እግዚአብሔር በኢየሱስ አማካኝነት ወደ ላይ ጠርቶ የሚሰጠው የሕይወት ሽልማት ነው።” (ፊልጵስዩስ 3:14) ለእጅግ ብዙ ሰዎች ደግሞ ሽልማቱ በምድራዊ ገነት የዘላለም ሕይወት ነው። ጉዳዩ ይህን ያህል አሳሳቢ በመሆኑ እኛም እንደ ጳውሎስ “የተጣልን እንዳንሆን (የማንበቃ ሆነን እንዳንገኝ)” ቆርጠን እንነሳ። እያንዳንዳችን “ሽልማቱን ለመቀበል ሩጡ” የሚለውን ትዕዛዝ ልብ እንበል።—1 ቆሮንቶስ 9:24, 27
ታስታውሳላችሁን?
◻ የክርስቲያንን ሕይወት ከሩጫ ጋር ማመሳሰል ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ የሕይወት ሩጫ ከእግር ሩጫ የሚለየው እንዴት ነው?
◻ ራስን የመግዛት ባሕርይ ያለማቋረጥና “በነገር ሁሉ” ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
◻ አንድ ሰው “ያለግብ” የማይሮጠው እንዴት ነው?
◻ እንዲሁ “ነፋስን መጎሰም” አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ድል አድራጊው የሚያገኘው የአበባ ጉንጉንም ሆነ ክብሩና ዝናው አላፊ ብቻ ናቸው