የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ወንድሞችና እህቶች በሕንድ አገር ብርሃናቸውን አበሩ
በሕንድ አገር የመንግሥቱ ምሥራች በ11,524 ደስተኛ ምሥክሮች እየተሰበከ ነው። (ማቴዎስ 24:14) በ1991 የአገልግሎት ዓመት የተጠመቁት 1,066 ወንድሞችና እህቶችም ብርሃናቸውን ለሌሎች የሚያበሩ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው። በክርስቶስ የሞት መታሰቢያ በዓል ላይ 28,866 ተሰብሳቢዎች መገኘታቸውን በማየታቸው ሁሉም ተደስተው ነበር!
◻ አብዛኛዎቹ የመንግሥቱን ተስፋ የሰሙት መደበኛ ባልሆነ ምሥክርነት ነው። ለምሳሌ አንድ ምሥክር አናጢ ለሆኑት የሥራ ጓደኞቹ ስለ አምላክ መንግሥት ነገራቸው። አንዱ የሥራ ጓደኛው መልእክቱን ተቀበለና እሱም ለቤተሰቡና ለጓደኞቹ ብርሃኑን ማብራት ጀመረ። እነዚህም ግሩም የሆነውን የመንግሥቱን መልእክት በደስታ ለሌሎች መናገር ጀመሩ። በሪፖርቱ መሠረት በጥቂት ዓመታት ውስጥ 30 ሰዎች እውነትን ተቀበሉ። ብርሃናቸው ለሌሎች እንዲበራ በማድረጋቸው ይሖዋ እሱንና አዲስ የሆኑትን መንፈሳዊ ወንድሞቹን ባረካቸው።
◻ በአንድ ሌላ ጉባኤ ያለ ወጣት ወንድም በትምህርት ቤት ውስጥ ላሉት ተማሪ ጓደኞቹ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በመመስከር ብርሃኑ እንዲበራ አድርጓል። አንዳንዶች ለመንግሥቱ ተስፋ ፍላጎት ስለነበራቸው ብዙ ጊዜ እኩለ ሌሊት እስኪያልፍ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ያብራራላቸው ነበር። አንድ ካቶሊክ የነበረ ተማሪ ምንም እንኳን ከምሥክሩ ጋር ጓደኛ መሆኑን ከቀጠለ የከፋ ውጤት እንደሚከተልበት ቄሱ ቢያስጠነቅቀውም ከእውነት ጽኑ አቋም ወስዷል። እንዲያውም ተማሪው ከምሥክሮቹ እውነትን እየተማረ እንዳለ አምኖ ስለነበረ እውቀት መሰብሰቡን ቀጠለ። ከዚያም ተጠምቆ አሁን በጉባኤው ውስጥ ዲያቆን ሆኖ ያገለግላል። ግሩም በሆነው የእውነት ብርሃን አማካኝነት በሚገኘው ተስፋ ይደሰታል!—ሮሜ 12:12
◻ ሌላው ይህን ወጣት ምሥክር ያዳመጠው አምላክ የለም የሚልና በአምላክ እናምናለን በሚሉት በማፌዝ የታወቀ አንድ ተማሪ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ቀን በውይይቱ ላይ ተገኘና ብዙ ጥያቄዎች ጠየቀ። ለጥያቄዎቹ ሁሉ ምክንያታዊ የሆነ መልስ ሲያገኝ በጣም ተደነቀ። በመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወደሚለው መደምደሚያ ደረሰ። በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱ እድገት አደረገ በመጨረሻም ተጠመቀ። የሂንዱ እምነት ተከታይ የሆነው አባቱ ከቤት እስከ ማባረር ድረስ ተቃወመው። ይሁን እንጂ ይህ ወጣት ለእውነት ያለው የጸና አቋም ሁለት ሥጋዊ ወንድሞቹና ሁለት ጓደኞቹ እውነትን እንዲቀበሉና እንዲጠመቁ በማድረጉ ዋጋ አስገኝቶለታል። አሁን አንዱ ወንድሙ በሕንድ ውስጥ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ያገለግላል።
◻ በተጨማሪም አንድ የተማሪዎች አስተባባሪ ተማሪ በወጣቱ ምሥክር ውይይት ላይ ተገኝቶ ነበር። የታወቀ አጫሽና ጠጪ ነበር። አንድ ቀን ከምሥክሩ ጋር እውነትን ያጠኑትን ሁለት ተማሪዎች ለመደብደብ ፈልጎ ነበር። ምክንያቱም እነዚህ ተማሪዎች እውነትን ስለተቀበሉ ተማሪዎች ባደረጉት አድማ ላይ ለመካፈል እምቢ አሉ። በተጨማሪም በተማሪዎቹ አስተባባሪ መሪነት ለሚካሄደው ደም የመሰብሰብ ዘመቻ ደም አልለገሱም ነበር። ይህ ወጣት አሁን የይሖዋን ብርሃን የሚያበራ ምሥክር በመሆኑ እየተደሰተ ነው።
◻ አሥር ጓደኞቹ ራሳቸውን እንዲወስኑና እንዲጠመቁ ያስቻላቸው ብርሃን እንዲበራ ያደረገው ተማሪ የመሠከረላቸው መደበኛ ባልሆነ መንገድ ነበር።
በዚህ ሰፊ አገር ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ የሆነውን የአምላክ አዲስ ዓለም ሲቀበሉና ይሖዋ አምላክ በመንግሥቱ ሥር ለዘላለም እንዲኖሩ እየሰበሰባቸው ካለው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ጋር ሲተባበሩ ማየት ያስደስታል።