እርስ በርሳችሁ መተናነፃችሁን ቀጥሉ
“ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ።”—ኤፌሶን 4:29
1, 2. (ሀ) ንግግር አስደናቂ ተዓምር ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ስለ ምላሳችን አጠቃቀም ምን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ይሆናል?
“ንግግር ወዳጆችን፣ ቤተሰቦችንና ኅብረተሰቦችን አንድ ላይ የሚያስተሳስር ተአምራዊ ክር ነው። . . . ከሰብአዊ አእምሮና ከተቀናጀ የ[ምላስ] ጡንቻዎች መኮማተር ፍቅርን፣ ቅንዓትን፣ አክብሮትን፣ በእርግጥ ማንኛውንም ሰብአዊ ስሜት የሚቀሰቅሱ ድምፆችን እናወጣለን።”—መስማት፣ መቅመስና ማሽተት የተባለው መጽሓፍ
2 ምላሳችን ምግብን መቅመስና ለመዋጥ ብቻ የሚያገለግል አካል አይደለም። የምናስበውንና የሚሰማንን ስሜት ለሌሎች ለማካፈል የሚያስችለን ክፍል ነው። ያዕቆብ “አንደበት (ምላስ) ትንሽ ብልት ነው” በማለት ጽፏል። “በእርሱ ጌታን [ይሖዋን አዓት]ና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም ‘እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ’ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን።” (ያዕቆብ 3:5, 9) አዎን፣ ምላሳችንን ይሖዋን ማወደስ ለመሳሰሉት ነገሮች በመልካም መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን። ነገር ግን ፍጽምና የሌለን በመሆናችን ምላሳችንን በቀላሉ ጎጂ ወይም አፍራሽ ነገሮችን ለመናገር ልንጠቀምበት እንችላለን። ያዕቆብ “ወንድሞቼ ሆይ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም” በማለት ጽፏል።—ያዕቆብ 3:10
3. ለየትኞቹ የንግግራችን ሁለት ገጽታዎች ነው ትኩረት መስጠት የሚኖርብን?
3 ምላሱን ፍጹም በሆነ መንገድ ሊቆጣጠር የሚችል ሰው የለም፤ ሆኖም በእርግጥ ለማሻሻል መጣር ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነፅ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ” በማለት ይመክረናል። (ኤፌሶን 4:29) ይህ ትዕዛዝ ሁለት ገጽታዎች እንዳሉት አስተውሉ። እነርሱም፦ ለማስወገድ መጣር ያለብንና ለማድረግ መጣር ያለብን ነገሮች ናቸው። እስቲ ሁለቱንም ገጽታዎች እንመርምራቸው።
ብልሹ አነጋገርን አስወግዱ
4, 5. (ሀ) መጥፎ አነጋገርን በተመለከተ ክርስቲያኖች ምን ትግል አለባቸው? (ለ) “ብልሹ አነጋገር” ከሚለው ሐረግ ጋር የሚስማማው ምን ዓይነት ሥዕላዊ አገላለጽ ነው?
4 ኤፌሶን 4:29 በመጀመሪያ “ከአፋችሁ ብልሹ አነጋገር አይውጣ አዓት።” በማለት አጥብቆ ያሳስበናል። ይህም ቀላል ላይሆን ይችላል። ቀላል ላይሆን የሚችልበት አንዱ ምክንያት በዙሪያችን ባለው ዓለም ብልሹ አነጋገር በጣም የተለመደ በመሆኑ ነው። ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ገናናነት የሚጨምርላቸው ወይም ጠንካሮች መስለው እንዲታዩ የሚያደርጋቸው እየመሰላቸው በየቀኑ ሲሰዳደቡ ይሰማሉ። አስፀያፊ አነጋገሮችን መስማትን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት አንችል ይሆናል፣ እነዚህን መጥፎ አነጋገሮች ላለመቅሰም ግን ሆነ ብለን ጥረት ልናደርግ እንችላለን፣ ይኖርብናልም። እነዚህ አስፀያፊ አነጋገሮች በአእምሮአችን ወይም በአፋችን ምንም ቦታ የላቸውም።
5 የጳውሎስ ማስጠንቀቂያ የተመሠረተው ከተበላሸ ዓሣ ወይም ከበሰበሰ ፍሬ ጋር ዝምድና ባለው የግሪክኛ ቃል ላይ ነው። እስቲ በዓይነ ሕሊናችሁ የሚከተለውን ተመልከቱ፦ አንድ ሰው ትዕግሥቱ እያለቀ ሲሄድና ወዲያው በጣም ሲናደድ ትመለከታላችሁ። በመጨረሻም ቱግ ይልና የበሰበሰ ዓሣ ከአፉ ሲወጣ ትመለከታላችሁ። ከዚያም የሸተተ፣ የበሰበሰ ፍሬ ተስፈንጥሮ ሲወጣና በዙሪያው ሁሉ ሲረጭ ታያላችሁ። እርሱ ማን ነው? ከእኛ መካከል አንዱ ቢሆን ምን ያህል የሚያሳዝን ነው! ሆኖም ‘ብልሹ አነጋገር ከአፋችን እንዲወጣ ከፈቀድን’ ይህ ምስል ሁኔታችንን ለመግለጽ ይስማማል።
6. ኤፌሶን 4:29 ለነቀፋና ለአፍራሽ ንግግር የሚሠራው እንዴት ነው?
6 የኤፌሶን 4:29 ሌላው አጠቃቀም ደግሞ ሁልጊዜ ጉድለት ፈላጊዎች ከመሆን እንድንርቅ የሚጠይቅ ነው። ስለማንወዳቸው ወይም ስለማንቀበላቸው ነገሮች የየራሳችን አስተያየትና ስሜት እንዳለን የታመነ ነው፣ ነገር ግን ስለተጠቀሰው ሰው ወይም ቦታ ወይም ነገር ሁሉ አፍራሽ አስተያየት (ወይም ብዙ አስተያየቶች) የሚሰጥ ሰው አጋጥሟችሁ ያውቃልን? (ከሮሜ 12:9ና ከዕብራውያን 1:9 ጋር አወዳድር) የእንዲህ ዓይነቱ ሰው አነጋገር ይቦጫጭቃል፣ ቅር ያሰኛል፣ ያሳዝናል፣ ወይም አቃጥሎ ያጠፋል። (መዝሙር 10:7፤ 64:2-4፤ ምሳሌ 16:27፤ ያዕቆብ 4:11, 12) ይህ ሰው ሚልክያስ የገለጻቸውን ነቃፊዎች ምን ያህል እንደሚመስል ላይገነዘበው ይችላል። (ሚልክያስ 3:13-15) ባጠገቡ ያለ ሰው የሸተተ ዓሣ ወይም የበሰበሰ ፍሬ ከአፉ ሾልኮ እንደወጣ ቢነግረው ምን ያህል ይደነግጥ ነበር!
7. እያንዳንዳችን ስለራሳችን ምን ዓይነት ምርመራ ማድረግ ይኖርብናል?
7 አንድ ሰው ሁልጊዜ አፍራሽ ወይም ስህተት ፈላጊነት የተሞላበት አስተያየት እንደሚሰጥ ማየት ቀላል ሲሆን ‘እኔስ እንዲህ ማድረግ እወዳለሁን? በእርግጥ እንዲህ ነኝን?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። አንዳንድ ጊዜ ከተናገርናቸው ቃላት በስተጀርባ ያለውን መንፈስ መለስ ብለን መመርመር ጥበብ ይሆናል። ቃላቶቻችን ይበልጡን አፍራሽና ነቀፌታ አዘል ናቸውን? የኢዮብን ሦስት የሐሰት አጽናኞች እንመስላለንን? (ኢዮብ 2:11፤ 13:4, 5፤ 16:2፤ 19:2) ለምን ብሩሕ ጎን ያላቸውን ነገሮች ፈልገን አናወራም? ጭውውቱ ይበልጥ ትችት ወይም ስህተት ፈላጊነት የተሞላበት ከሆነ ለምን ወደ ገንቢ ነገሮች እንዲያመራ አናደርግም?
8. ሚልክያስ 3:16 በንግግር ረገድ ምን ትምህርት ይሰጠናል? ትምህርቱን በሥራ ላይ እያዋልነው መሆናችንንስ እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
8 ሚልክያስ የሚከተለውን ማነፃፀሪያ አቅርቧል፦ “የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] የሚፈሩ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] አደመጠ፣ ሰማም፣ እግዚአብሔርንም [ይሖዋንም አዓት] ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።” (ሚልክያስ 3:16) አምላክ ለገንቢ ቃላት እንዴት ምላሽ እንደሰጠ አስተዋላችሁን? ይህ ዓይነቱ ጭውውት በሚቀራረቡ ሰዎች ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል? እኛም የየዕለቱን ንግግራችንን በተመለከተ በግላችን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን። ጭውውታችን ‘ለአምላክ የምናቀርበውን የምስጋና መስዋዕት’ የሚያንፀባርቅ ቢሆን ለራሳችንና ለሌሎችም እንዴት እጅግ መልካም ነው።—ዕብራውያን 13:15
ሌሎችን ለማነጽ ጣሩ
9. ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ሌሎችን ለማነጽ ጥሩ አጋጣሚዎች የሆኑት ለምንድን ነው?
9 የጉባኤ ስብሰባዎች ‘ለሚሰሙት ጥሩ ነገርን የሚያስተላልፍ ማናቸውም በጎ ቃል’ ለመናገር እጅግ በጣም ጥሩ አጋጣሚዎች ናቸው። (ኤፌሶን 4:29) ይህንንም በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ላይ ንግግር ስንሰጥ፣ በትዕይንት ስንካፈል፣ ወይም ጥያቄና መልስ ባለባቸው ክፍሎች ሐሳብ በምንሰጥበት ጊዜ ልናደርገው እንችላለን። እንዲህ በማድረጋችንም “እውቀት የተሞላበት ንግግር ከወርቅና ከከበረ ዕንቁ ይበልጥ የተወደደ ነው” የ1980 ትርጉም የሚለው ምሳሌ 20:15 ትክክል መሆኑን እናረጋግጣለን። ደግሞስ ምን ያህል ልብን እንደምንነካ ወይም እንደምናንጽ ማን ያውቃል?
10. አብዛኛውን ጊዜ የንግግር ጭውውት የምናደርገው ከነማን ጋር መሆኑን መለስ ብለን ካሰብንበት በኋላ ምን ማስተካከያ ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል? (2 ቆሮንቶስ 6:12, 13)
10 ከስብሰባ በፊትና በኋላ ያለው ጊዜም ለሰሚዎች በሚስማማ ጭውውት ሌሎችን ለማነጽ አመቺ ጊዜ ነው። እነዚህን ጊዜያት ተዝናንተን ከምንቀርባቸው ዘመዶቻችንና አነስተኛ ቁጥር ካላቸው ጓደኞቻችን ጋር የሚያስደስት ጭውውት በማድረግ ማሳለፍ ቀላል ነው። (ዮሐንስ 13:23፤ 19:26) ይሁን እንጂ ከኤፌሶን 4:29 ጋር በመስማማት የምታነጋግሩአቸው ሌሎች ሰዎችንም ለምን አትፈልጉም? (ከሉቃስ 14:12-14 ጋር አወዳድር።) ለአንዳንድ አዳዲስ ሰዎች፣ የሸመገሉ ሰዎች፣ ወይም ወጣቶች፣ በእነርሱ ደረጃ እንድንሆን ከሕፃናት ጋር በመቀመጥም ሳይቀር ከመደበኛው ወይም ከተራ የሰላምታ ልውውጥ ያለፈ ጭውውት ለማድረግ አስቀድመን ልንወስን እንችላለን። ሰዎችን ለመጥቀም ያለን እውነተኛ ስሜትና የሚያንጽ ጭውውት በማድረግ የምናሳልፋቸው ጊዜያት ሌሎች ሰዎች በመዝሙር 122:1 ላይ የተገለጸውን የዳዊትን ስሜት ይበልጥ እንዲያስተጋቡ ሊያደርጋቸው ይችላል።
11. (ሀ) በመቀመጫ ረገድ ብዙዎች ምን ልማድ ጀምረዋል? (ለ) አንዳንዶች የሚቀመጡበትን ቦታ ሆን ብለው የሚለዋውጡት ለምንድን ነው?
11 የሚያንጽ ጭውውት ለማድረግ የሚረዳው ሌላው ነገር በስብሰባው ጊዜ የምንቀመጥበትን ቦታ መለዋወጥ ነው። የምታጠባ እናት መጸዳጃ ክፍሉ አጠገብ ትቀመጥ ይሆናል፣ ወይም ደግሞ የአካል ድካም ያለበት ወይም በዕድሜ የሸመገለ ሰው ለመተላለፊያው በቀረበ ቦታ ላይ መቀመጥ ይመርጥ ይሆናል። ሌሎቻችንስ? አንድን ቦታ ብቻ መልመድ ወደዚያው መቀመጫ ወይም ቦታ እንድናመራ ሊያደርገን ይችላል፤ ወፍም እንኳን በደመ ነፍስ ወደ ለመደችው መሥፈሪያ ቅርንጫፍ ትመለሳለች። (ኢሳይያስ 1:3፤ ማቴዎስ 8:20) ይሁን እንጂ በግልጽ ለመናገር የትም ቦታ ልንቀመጥ ስለምንችል በስተቀኝ በኩል፣ በስተግራ በኩል፣ ወደፊት ቀረብ ብለን፣ ወዘተ የምንቀመጥበትን ቦታ በመለዋወጥ ከተለያዩ ወንድሞችና እህቶች ጋር የበለጠ ለምን አንተዋወቅም? ይህን የምናደርግበት ምንም መደበኛ የሆነ ደንብ ባይኖርም የሚቀመጡበትን ሥፍራ የሚለዋውጡ ሽማግሌዎችና ሌሎችም የጎለመሱ ክርስቲያኖች ጥሩ ነገሮችን የሚያካፍሉት ለጥቂት የቅርብ ጓደኞቻቸው ብቻ ከሚሆን ይልቅ ለብዙዎች እንዲሆን የቀለለ መንገድ ሆኖ አግኝተውታል።
በአምላካዊ መንገድ አንጹ
12. በታሪክ በሙሉ የታየው ምን የማይፈለግ ዝንባሌ ነው?
12 አንድ ክርስቲያን ሌሎችን ለማነጽ ያለው ፍላጎት በዚህ ረገድ ብዙ ሕጎችን ማውጣት በሚቀናው ሰብአዊ ዝንባሌው ከመመራት ይልቅ አምላክን እንዲመስል ሊገፋፋው ይገባል።a ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ብዙ ጊዜ አብረዋቸው ያሉትን ሰዎች ባወጡት ሕግ መሠረት መቆጣጠር ይቀናቸዋል፣ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮችም እንኳን ለዚህ ዝንባሌ ተሸንፈዋል። (ዘፍጥረት 3:16፤ መክብብ 8:9) በኢየሱስ ዘመን የአይሁድ መሪዎች እነሱ ‘በጣታቸውም እንኳን ሊነኩት የማይወዱትን ከባድ ሸክም ተብትበው በሌሎች ትከሻ ላይ ይጭኑ ነበር።’ (ማቴዎስ 23:4) ምንም ጉዳት የሌላቸውን ልማዶች ግዳጅ ወደሆኑ ወጎች ለውጠዋቸው ነበር። ለሰው ደንብና ሕግ ከልክ በላይ ቦታ በመስጠታቸው ምክንያት አምላክ የበለጠ ቁም ነገር እንዳላቸው የገለጻቸውን ነገሮች ችላ ብለው ነበር። ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ብዙ ደንቦችን በማውጣታቸው የታነጸ ማንም አልነበረም፤ የእነርሱ መንገድ የአምላክ መንገድ አልነበረም።—ማቴዎስ 23:23, 24፤ ማርቆስ 7:1-13
13. ለመሰል ክርስቲያኖች በርካታ ሕጎችን ማውጣት ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?
13 ክርስቲያኖች የአምላክን ሕጎች አጥብቀው ለመከተል ከልብ ይፈልጋሉ። ያም ሆኖ ብዙ ከባድ ሕጎችን የማውጣቱ ዝንባሌ ሊያሸንፈን ይችላል። ለምን? አንዱ ምክንያት ስሜታችን ወይም ምርጫችን ስለሚለያይ ሌሎች የሚጠሉትንና መደረግ የለበትም ብለው የሚያስቡትን ነገር አንዳንድ ሰዎች ግን ተስማሚ ሆኖ ሊያገኙት ስለሚችሉ ሊሆን ይችላል። ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ጉልምስና ረገድ ባላቸው ዕድገትም ይለያያሉ። ታዲያ ሌላው ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና እንዲያድግ ለመርዳት አምላካዊው መንገድ ብዙ ሕጎችን ማውጣት ነውን? (ፊልጵስዩስ 3:15፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:19፤ ዕብራውያን 5:14) አንድ ሰው በእርግጥ ከልክ ያለፈ መስሎ የሚታይ ወይም አደገኛ የሆነ አካሄድ በሚከተልበት ጊዜም እንኳን የሚከለክለውን ሕግ ማውጣት የተሻለ መፍትሔ ነውን? ብቃት ላላቸው ክርስቲያኖች የአምላክ መንገድ የሚሆነው ከተሳሳተው ሰው ጋር በየዋህነት ምክንያትን እያቀረቡ በመነጋገር ለመመለስ መሞከር ነው።—ገላትያ 6:1
14. አምላክ ለእሥራኤላውያን የሰጣቸው ሕጎች ለምን ዓላማዎች አገልግለዋል?
14 እውነት ነው፣ አምላክ እሥራኤልን እንደ ሕዝቡ አድርጎ ይጠቀምባቸው በነበረበት ጊዜ ስለ ቤተ መቅደስ አምልኮ፣ ስለ መስዋዕቶች፣ ስለ ንጽሕናም እንኳን ሳይቀር በመቶ የሚቆጠሩ ሕጎችን አውጥቶላቸው ነበር። ይህም ልዩ መሆን ለነበረበት ሕዝብ ተገቢ ነበር፣ አብዛኞቹ ሕጎችም ትንቢታዊ ቁም ነገርነት ስለነበራቸው አይሁዳውያንን ወደ መሲሕ ለመምራት ረድተዋል። ጳውሎስ “እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኗል፤ እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም” በማለት ጽፏል። (ገላትያ 3:19, 23-25) ሕጉ በመከራው እንጨት ላይ ተጠርቆ ከጠፋ በኋላ ክርስቲያኖች በእምነት የታነጹ ሆነው እንዲኖሩ ማድረጊያው መንገድ በብዙ የሕይወት ዘርፎች ላይ ሠፊ የሕጎች ዝርዝር መስጠት አላስፈለገውም ነበር።
15. አምላክ ለክርስቲያን አምላኪዎቹ ምን አመራር ሰጥቷቸዋል?
15 እርግጥ ሕግ የለንም ማለት አይደለም። አምላክ ከጣኦት፣ ከዝሙትና ምንዝር እንዲሁም በደም ያለአገባብ ከመጠቀም እንድንርቅ ያዘናል። ነፍስ ግድያን፣ መዋሸትን፣ መናፍስትነትንና ልዩ ልዩ ዓይነት ኃጢአቶችን ለይቶ በመጥቀስ ያወግዛል። (ሥራ 15:28, 29፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ራዕይ 21:8) በቃሉ ውስጥ በብዙ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ምክር ይሰጠናል። ሆኖም እኛ ከእሥራኤላውያን ይልቅ በከፍተኛ ደረጃ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የመማርና በሥራ ላይ የማዋል ኃላፊነት አለብን። ወንድሞች ሕግን ከመፈላለግ ወይም ከማውጣት ይልቅ እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲገነዘቡአቸውና እንዲያስቡባቸው በመርዳት ሽማግሌዎች ሊያንጹአቸው ይችላሉ።
የሚያንጹ ሽማግሌዎች
16, 17. ለክርስቲያን ወንድሞች ሕግን በማውጣት ረገድ ሐዋርያት ምን መልካም ምሳሌ ትተዋል?
16 ጳውሎስ “ዕድገት ባደረግንበት ልክ በዚያው መሥመር በሥርዓት እንመላለስ ” በማለት ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 3:16 አዓት) ከዚህ አምላካዊ አመለካከት ጋር በመስማማት ሐዋርያው ጳውሎስ ከሌሎች ጋር በነበረው ግንኙነት የሚያንጽ ነበር። ለምሳሌ ያህል ከጣዖት ቤተ መቅደስ የመጣ ሥጋን ስለ መብላት ጥያቄ ተነስቶ ነበር። ወጥ የሆነ አቋም እንዲኖር ወይም ነገሩን ለማቅለል በሚል ሰበብ ይህ ሽማግሌ ለነዚያ የቀድሞ ጉባኤዎች በሙሉ አንዳንድ ሕጎችን አወጣላቸውን? አላወጣላቸውም። በእውቀትና በብስለት ወይም በጉልምስና ደረጃ መለያየት እነዚያን ክርስቲያኖች ለተለያዩ ምርጫዎች አብቅተዋቸው ሊሆን እንደሚችል አምኖ ተቀብሏል። ለራሱ ግን መልካም ምሳሌ ለመሆን ቆርጦ ነበር።—ሮሜ 14:1-4፤ 1 ቆሮንቶስ 8:4-13
17 ሐዋርያት አለባበስንና የፀጉር አበጣጠርን በመሳሰሉ አንዳንድ የግል ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ምክር እንደሰጡ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ያሳያሉ፤ ይሁን እንጂ አጠቃላይ የሆኑ ደንቦችን ለማውጣት አልቃጡም። ይህን በአሁኑ ጊዜ ላሉት መንጋውን ለማነጽ ለሚፈልጉ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችም ጥሩ ምሳሌ ነው። ይህ ደግሞ በእርግጥ አምላክ በጥንቱ እሥራኤል ረገድ የወሰደው መሠረታዊ አቋም እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው።
18. አለባበስን በተመለከተ ይሖዋ ለእሥራኤል የሰጠው ምን ሕጎችን ነበር?
18 አምላክ ለእሥራኤላውያን ስለ አለባበስ የተንዛዙ ሕጎችን አልሰጣቸውም። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ወንዶችና ሴቶች በተመሳሳይ መጎናጸፊያዎች ወይም ከላይ የሚደረቡ ልብሶች ይጠቀሙ ነበር፤ እርግጥ የሴቶች መጎናጸፊያ የተጠለፈ ወይም በቀለማት ያሸበረቀ ሊሆን ይችል ነበር። ሁለቱም ጾታዎች በዕብራይስጥ ሳድሂን የሚባለውን የበፍታ ቀሚስ ወይም የውስጥ ልብስ ይለብሱ ነበር። (መሳፍንት 14:12፤ ምሳሌ 31:24፤ ኢሳይያስ 3:23) አምላክ ስለ ልብስ የሰጣቸው ሕጎች ምን ነበሩ? ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ሁለቱንም ፆታዎች አንድ አድርገው የሚያሳውቁ ልብሶችን እንዳይለብሱ ነበር፤ ይህም ለግብረ ሰዶማዊነት ዓላማ እንዳይጠቀሙበት መከልከሉ እንደነበረ ግልጽ ነው። (ዘዳግም 22:5) እሥራኤላውያን በዙሪያቸው ከነበሩ ሌሎች አሕዛብ የተለዩ መሆናቸውን ለማሳየት በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ እንዲያደርጉና በዘርፉም ሁሉ ላይ ሰማያዊ ፈትል እንዲያደርጉ ታዘው ነበር። (ዘኁልቁ 15:38-41) ስለ አለባበስ ጉዳይ ሕጉ የሰጠው አመራር በመሠረቱ ይህ ብቻ ነው።
19, 20. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አለባበስና ስለ ፀጉር አበጣጠር ለክርስቲያኖች ምን መመሪያ ይሰጣቸዋል? (ለ) ሽማግሌዎች ስለ አለባበስና ስለ ፀጉር አበጣጠር ሕጎችን ስለማውጣት ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
19 ክርስቲያኖች ከሕጉ ሥር ባለመሆናቸው ስለ አለባበስ ወይም ስለ ጌጣጌጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈረልን ዝርዝር ሕግ አለን? በእርግጥ የለም። አምላክ የሰጠን በሥራ ላይ ልናውላቸው የምንችል ሚዛናዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ነው። ጳውሎስ “ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ . . . በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ” በማለት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9) ጴጥሮስ ክርስቲያን ሴቶች ከላይ በሚታይ ጌጥ ላይ ከማተኮር ይልቅ “የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው” በመልበስ ላይ እንዲያተኩሩ አጥብቆ አሳስቧል። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4) እንዲህ ዓይነቱ ምክር ተመዝግቦ መገኘቱ አንዳንድ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በአለባበሳቸውና በፀጉር አበጣጠራቸው ይበልጥ ልከኛና ራሳቸውን የሚገዙ መሆን በይበልጥ አስፈልጓቸው እንደነበረ ያመለክታል። ሆኖም አንድ ዓይነት አለባበስን ወይም የፀጉር አበጣጠርን እንዲከተሉ በማዘዝ ወይም እንዲተዉ በመከልከል ፈንታ ሐዋርያት የሚያንጽ ምክር ብቻ ሰጡ።
20 የይሖዋ ምሥክሮች ባጠቃላይ በአለባበስና በፀጉር አበጣጠራቸው ልከኞች በመሆናቸው አድናቆት ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው። ይህንንም አድናቆት አግኝተዋልም። ይሁን እንጂ የአለባበስና የፀጉር አበጣጠር ፋሽኖች ከአገር ወደ አገርና እንዲያውም በአንድ አካባቢ ወይም ጉባኤ ውስጥም እንኳን ሳይቀር ሊለያዩ ይችላሉ። በእርግጥ በአለባበስ ወይም በፀጉር አበጣጠር ላይ አንድ ዓይነት ጠንካራ አስተያየት ወይም ስሜት ያለው አንድ ሽማግሌ ለራሱና ለቤተሰቡ ከስሜቱ ጋር እንደሚስማማ ሊወስን ይችላል። መንጋውን በሚመለከት ግን ጳውሎስ “ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም። በእምነታችሁ ቆማችኋልና” በማለት የተናገረውን ፍሬ ነገር ማስታወስ ያስፈልገዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:24) አዎን፣ ሽማግሌዎች ለጉባኤው ሕግ የማውጣትን ውስጣዊ ዝንባሌ በመግታት የሌሎችን እምነት ለመገንባት ይጥራሉ።
21. አንድ ሰው በአለባበስ ከልክ ካለፈ ሽማግሌዎች የሚያንጽ እርዳታ ሊሰጡ የሚችሉት እንዴት ነው?
21 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ አንዳንድ ጊዜ አዲስ ወይም በመንፈሳዊ ደካማ የሆነች ወይም የሆነ ሰው በአለባበስ ወይም በቅባቶችና በጌጣጌጥ አጠቃቀም አጠያያቂ ወይም ጥበብ የጎደለው አካሄድ ትከተል ወይም ይከተል ይሆናል። ታዲያ ምን መደረግ አለበት? አሁንም ገላትያ 6:1 ልባዊ እርዳታ ለማቅረብ የሚፈልጉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሊከተሉት የሚገባ አመራር ይሰጣል። አንድ ሽማግሌ ምክር ለመስጠት ከመወሰኑ በፊት ከመሰል ሽማግሌ ጋር ቢመካከርበት ጥበብ ይሆናል፤ ይህን ሲያደርግም የእርሱ ዓይነት ስሜት ወይም አስተሳሰብ ወዳለው ሽማግሌ ዘንድ ሄዶ ባይመካከር ይመረጣል። በአለባበስ ወይም በፀጉር አበጣጠር ረገድ ዓለማዊ አዝማሚያ በጉባኤው ውስጥ ያሉትን ብዙዎችን የሚነካ መስሎ ከታየ የሽማግሌዎች አካል በስብሰባው ላይ በደግነት የቀረበ የሚያንጽ ክፍል ለመስጠት ወይም በግለሰብ ደረጃ እርዳታ እንዴት ቢሰጡ እንደሚሻል ሊወያዩበት ይችላሉ። (ምሳሌ 24:6፤ 27:17) የሽማግሌዎቹ ግብ “አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም” የሚለው በ2 ቆሮንቶስ 6:3 ላይ ያለው አመለካከት እንዲንፀባረቅ ማበረታታት ነው።
22. (ሀ) ጥቃቅን የአመለካከት ልዩነቶች ቢኖሩ የሚረብሽ ሊሆን የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ ምን ጥሩ ምሳሌ ሰጥቷል?
22 ‘በእነርሱ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ የሚጠብቁ’ ሽማግሌዎች ጴጥሮስ እንደገለጸው ለማድረግ ማለትም መንጋውን ‘እንደ ጌቶቻቸው ሆነው እንዳይገዙ’ ይፈልጋሉ። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) ሥራቸውን በፍቅራዊ መንገድ በሚያከናውኑበት ወቅት የተለያየ ምርጫ ሊኖርባቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። ምናልባት በአንድ አካባቢ በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ጊዜ የሚያነበው ወንድም አንቀጾቹን ለማንበብ መቆም የተለመደ ይሆናል። በመስክ አገልግሎትና በሌሎች ብዙ አገልግሎት ነክ ዝርዝሮች ላይ የሚደረጉ የቡድን ዝግጅቶች የሚካሄዱት በአንድ የተለመደ መንገድ ይሆናል። ታዲያ አንድ ሰው ትንሽ ለየት ያለ አሠራር ቢኖረው አደጋ ይኖረዋልን? አፍቃሪ የበላይ ተመልካቾች ጳውሎስ ተአምራዊ ስጦታዎችን አስመልክቶ እንደገለጸው “ሁሉም ነገር በአገባብና በሥርዓት እንዲሆን” ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ይህን አገላለጽ በተጠቀመበት ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብ የጳውሎስ ዋና ትኩረት “ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ” እንደነበረ ያሳያል። (1 ቆሮንቶስ 14:12, 40) ጳውሎስ ፍጹም የሆነ አንድ ዓይነት ደንብን ወይም የተሟላ የአሠራር ቅልጥፍናን ግቡ ያደረገ ይመስል ፍጻሜ የሌለው የሕጎች ዝርዝር ለማውጣት አልጣረም። “ጌታ ሥልጣን የሰጠን እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለም” በማለት ጽፏል።—2 ቆሮንቶስ 10:8 አዓት
23. ሌሎችን በማነጽ ረገድ ጳውሎስን ልንመስል የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
23 ጳውሎስ ያለጥርጥር ገንቢ በሆነና በሚያበረታታ ንግግር ሌሎችን ለማነጽ ጥሯል። ቀረቤታውን ከጥቂት ጓደኞቹ ጋር ብቻ በመወሰን ፈንታ በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆኑትንና እንዲሁም በተለይ መታነጽ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ወንድሞችንና እህቶችን ለመጎብኘት በጣም ለፍቷል። እሱ አጥብቆ የገለጸው ሕግን ሳይሆን ፍቅርን ነው፤ “ፍቅር ያንጻልና።”—1 ቆሮንቶስ 8:1
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በቤተሰብ ውስጥ እንደሁኔታው የተለያዩ ሕጎች ቢወጡ የሚሻል ሊመስል ይችላል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች ለትናንሽ ልጆቻቸው ነገሮችን እንዲወስኑላቸው ሥልጣን ይሰጣቸዋል።—ዘፀአት 20:12፤ ምሳሌ 6:20፤ ኤፌሶን 6:1-3
የክለሳ ነጥቦች
◻ አፍራሽ ወይም የነቀፋ ንግግር የሚቀናን ከሆነ ለውጥ ማድረግ የሚገባን ለምንድን ነው?
◻ በጉባኤ ውስጥ ይበልጥ የምናንጽ እንድንሆን ምን ልናደርግ እንችላለን?
◻ ለሌሎች ብዙ ሕጎችን ስለማውጣት አምላካዊው ምሳሌ ምንድን ነው?
◻ ሽማግሌዎች ለመንጋው ሰብአዊ ደንቦችን ከማውጣት እንዲቆጠቡ የሚረዳቸው ምንድን ነው?