ትምህርትን በዓላማ መከታተል
“ጠቢብን አስተምረው፣ በይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል።”—ምሳሌ 9:9 የ1980 ትርጉም
1. እውቀትን በተመለከተ ይሖዋ ከአገልጋዮቹ የሚጠብቀው ምንድን ነው?
ይሖዋ “የእውቀት አምላክ ነው።” (1 ሳሙኤል 2:3 አዓት) አገልጋዮቹን ያስተምራቸዋል። ሙሴ በጊዜው የሚኖሩ ሰዎች ስለ እስራኤል “ይህ ሕዝብ ታላቅ ሕዝብ ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ ነው” እንደሚሉ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ዘዳግም 4:6) እውነተኛ ክርስቲያኖችም በተመሳሳይ እውቀት ያላቸው መሆን ይገባቸዋል። እጅግ በጣም ጥሩ የአምላክ ቃል አስተማሪዎች መሆን ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ ያለውን ጥናት ዓላማ ሲያሳይ ሐዋርያው ጳውሎስ “ስለዚሁ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፣ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም [ትክክለኛ እውቀት አዓት] እውቀት እያደጋችሁ . . . በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን” ሲል ጽፏል።—ቆላስይስ 1:9, 10
2. (ሀ) የአምላክን ትክክለኛ እውቀት ለመቅሰም ምን ያስፈልጋል? (ለ) የይሖዋ ምስክሮች የአስተዳደር አካል ይህን ነገር በተመለከተ ምን ጥረት አድርጓል?
2 ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት ሲባል ጥናት ለማካሄድ ቢያንስ ቢያንስ መለስተኛ የትምህርት ደረጃ ማጠናቀቅን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ የአምላክን ቃል እውነት የተማሩ ብዙ ሰዎች ተገቢውን ዓለማዊ ትምህርት የማግኘቱ አጋጣሚ አነስተኛ በሆነባቸው ወይም ጭራሽ ማግኘት በማይቻልባቸው አገሮች የሚኖሩ ናቸው። ባጋጣሚዎች የተነሳ የመማር ዕድል አላገኙም። ይህንን ችግር ለመቋቋም የይሖዋ ምስክሮች የአስተዳደር አካል አስፈላጊ በሆነባቸው ቦታዎች በጉባኤዎች ውስጥ ለብዙ ዓመታት የጎልማሶች ትምህርት መስጫ ክፍልን ሲያቋቁምና ሲያካሂድ ቆይቷል። ከ30 ዓመታት በፊት ዲያሪዮ ደ ሞዢ የተባለ የብራዚል ጋዜጣ “የይሖዋ ምስክሮች በመሃይምነት ላይ ጦርነት አወጁ” በሚል ርዕስ ሥር አንድ ሐተታ አውጥቶ ነበር። “ችሎታ ያለው አስተማሪ በትዕግሥት ሌሎችን . . . ማንበብና መጻፍ . . . ያስተምራቸው ጀመር። . . . ተማሪዎቹም የአምላክ አገልጋዮች ለመሆን በሚያስገድዷቸው ሁኔታዎች ምክንያት ንግግሮችን ለመስጠት ይችሉ ዘንድ የቋንቋ እውቀታቸውን ማዳበር አለባቸው” በማለት አትቶ ነበር። በዚህ መንገድ በዓለም ዙሪያ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክ ቃል ጥሩ ተማሪዎች ለመሆን ችለዋል። ይህንን መሠረታዊ ትምህርት የተከታተሉት በአእምሮአቸው ከፍ ያለ ዓላማ በመያዝ ነበር።
ውጤታማ አገልጋዮች ለመሆን የሚያስፈልጉ ችሎታዎች
3, 4. (ሀ) እውነተኛ ክርስቲያኖች የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ለምንድን ነው? (ለ) በእስራኤል የነበረው ሁኔታ ምን ነበር? በዛሬው ጊዜ በየጉባኤዎቻችን ሊኖር የሚያስፈልገው ምን መሠረታዊ ትምህርት ነው?
3 እውነተኛ ክርስቲያኖች የትምህርት ፍላጎት አላቸው፤ ይህም ራሱን ትምህርትን ከመውደድ የተነሳ ሳይሆን ይበልጥ ውጤታማ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች ለመሆን ሲሉ ነው። ክርስቶስ “አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ለሁሉም ክርስቲያኖች ተልእኰ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ሌሎችን ለማስተማር በመጀመሪያ እነሱ ራሳቸው ሊማሩ ይገባቸዋል። ይህም ጥሩ የአጠናን ዘዴዎች ማወቅን ይጠይቃል። ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥንቃቄ መመርመር መቻል አለባቸው። (ሥራ 17:11) ተልዕኳቸውን ለማሟላት በደንብ ማንበብ መቻልም ያስፈልጋቸዋል።—ዕንባቆም 2:2፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:13ን ተመልከቱ።
4 ባለፈው ርዕሰ ትምህርት እንደተመለከትነው በጥንቷ እስራኤል የነበሩት ትንንሽ ልጆች ሳይቀሩ ባጠቃላይ ማንበብና መጻፍ ይችሉ ነበር ብሎ ለማመን ጥሩ ምክንያት አለን። (መሳፍንት 8:14፤ ኢሳይያስ 10:19) በዛሬው ጊዜ ወጣት አገልጋዮች ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ ንጹህ የሆኑ ማስታወሻዎችን መያዝ ያስፈልጋቸዋል። ደብዳቤዎችን ይጽፋሉ፣ በስብሰባዎች ላይ ማስታወሻዎችን ይይዛሉ እንዲሁም የሚጠኑ ጽሑፎቻቸውን አንብበው ለሌሎች ያብራራሉ። ይህ ሁሉ ሊነበብ የሚችል የእጅ ጽሑፍ ማዳበርን ይጠይቃል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መዝገቦችን መያዝም ቢያንስ ቢያንስ መሠረታዊ የሒሳብ እውቀት ያስፈልገዋል።
ተገቢ የሆነ ትምህርት የማግኘቱ ጥቅም
5. (ሀ) “ስኩል” (ትምህርት ቤት) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ምንጩ ምንድን ነው? (ለ) ወጣቶች ሊይዙት የሚገባቸው የትኛውን አጋጣሚ ነው?
5 “ስኩል” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ትርፍ ጊዜ” ወይም ትርፍን ጊዜ እንደ መማር ላለ ጠቃሚ የሆነ ነገር ማዋል የሚል መሠረታዊ ትርጉም ካለው ስኮሌ ከሚባለው የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው። ቆይቶም እንዲህ ያለው ትምህርት የሚካሄድበትን ቦታ ያመለክት ጀመር። ይህም በአንድ ወቅት ላይ በግሪክም ሆነ በአብዛኞቹ ሌሎች አገሮች ትምህርት ለማግኘት ትርፍ ጊዜ የነበራቸው ባለ ልዩ መብት የሆኑ ሰዎች ያሉበት መደብ ብቻ እንደነበር ያመለክታል። ባጠቃላይ ሠራተኛው መደብ መሃይም ሆኖ ይቀር ነበር። ዛሬ በብዙ አገሮች ትንንሽ ልጆችና ወጣቶች የመማሪያ ጊዜ ይሰጣቸዋል። ወጣት ምስክሮች ጊዜ ዋጅተው እውቀትና ችሎታ ያላቸው የይሖዋ አገልጋዮች መሆን ይገባቸዋል።—ኤፌሶን 5:15, 16
6, 7. (ሀ) ተገቢ የሆነ ትምህርት የማግኘት አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው? (ለ) የውጭ አገር ቋንቋ መማር ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው በምን በምን መንገዶች ነው? (ሐ) በአሁኑ ጊዜ ብዙ ወጣቶች ትምህርት በሚጨርሱበት ጊዜ ያላቸው ሁኔታ እንዴት ያለ ነው?
6 የታሪክ፣ የጂኦግራፊ፣ የሳይንስና የመሳሰሉት ትምህርቶች መሠረታዊ እውቀት መቅሰም ወጣት ምስክሮች ስለ ብዙ ነገር የተመጣጠነ እውቀት ያላቸው አገልጋዮች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። በትምህርት ቤት የሚያሳልፉት ጊዜ የሚያስተምራቸው ብዙ የትምህርት ዓይነቶችን ብቻ ሳይሆን የመማር ሂደትንም ጭምር ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ከትምህርት ቤት ከወጡ በኋላም ቢሆን መማርና ማጥናት አይተዉም። ይሁን እንጂ ከጥናታቸው የሚያገኙት ውጤት በከፍተኛ ሁኔታ የተመካው እንዴት እንደሚያጠኑ በማወቃቸው ላይ ነው። በዓለማዊ ትምህርት ቤቶችም ሆነ በጉባኤ የሚያገኙት ትምህርት የማሰብ ችሎታዎቻቸውን ለማዳበር ይረዳቸዋል። (ምሳሌ 5:1, 2) ሲያነቡ አስፈላጊ የሆኑትን፣ ሊታወሱ የሚገባቸውንና በቃል መጠናት ያለባቸውን ነገሮች በተሻለ ሁኔታ ለማስተዋል ይችላሉ።
7 ለምሳሌ ያህል የውጭ ቋንቋ መማር የወጣቶችን የአእምሮ ችሎታ ከማዳበሩም ሌላ በይሖዋ ድርጅት ውስጥም ይበልጥ ጠቃሚ ያደርጋቸዋል። በርከት ባሉ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ያሉ ብዛት ያላቸው ወጣት ወንድሞች እንግሊዝኛ ቋንቋን በደንብ መናገር ወይም ማንበብ መቻላቸው የሚጠቅም ሆኖ አግኝተውታል። ከዚህም በላይ ሁሉም ክርስቲያን አገልጋዮች የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን በደንብ ለመናገር መጣር ይገባቸዋል። የመንግሥቱ የምሥራች ጥርት ባለና በትክክለኛው ሰዋስው ሊገለጽ ይገባዋል። እውነታዎቹ እንደሚያሳዩት በዛሬው ጊዜ ብዙዎቹ ወጣቶች ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ እንኳን በትክክል በመጻፍና በመናገር፣ እንዲሁም ቀላል የሒሳብ ስሌት በመሥራት በኩል ችግር አለባቸው። የታሪክና የጂኦግራፊ እውቀታቸውም የባሰውን የደበዘዘ ነው።
በቂ ትምህርት ማግኘት
8. ዓለማዊ ትምህርትንና አንድ ሰው ራሱን መቻሉን በተመለከተ አግባብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንድን ናቸው?
8 እንግዲያው አሁን ዓለማዊ ትምህርትን በተመለከተ ሊኖረን የሚገባውን ክርስቲያናዊ አመለካከት የምንመረምርበት ተገቢ ጊዜ የመጣ ይመስላል። በዚህ ነገር ላይ አግባብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንድን ናቸው? በመጀመሪያ በብዙ አገሮች በሚገባ ሁኔታ ለ“ቄሳር” መገዛት ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ይጠይቅባቸዋል። (ማርቆስ 12:17፤ ቲቶ 3:1) ወጣት ምስክሮችም የትምህርት ቤት ሥራቸውን በተመለከተ “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፣ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት” የሚለውን ቆላስይስ 3:23ን ማስታወስ ይኖርባቸዋል። እዚህ ላይ ሊጨመር የሚችለው ሁለተኛው መሠረታዊ ሥርዓት ክርስቲያኖች የሙሉ ጊዜ አቅኚ አገልጋዮች ቢሆኑም እንኳን ራሳቸውን ችለው ለመኖር መቻል ያለባቸው መሆኑ ነው። (2 ተሰሎንቄ 3:10-12) አንድ ሰው ያገባ ከሆነ ለሚስቱና የሚወለዱ ልጆችም ካሉ ለልጆቹ ተገቢውን ነገር ማቅረብና በችግር ላይ ላሉት በጥቂቱም ቢሆን የሚያስፈልጋቸውን መስጠት እንዲሁም ለአገሩም ሆነ ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ ድጋፍ ለማድረግ መቻል ይኖርበታል።—ኤፌሶን 4:28፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8
9, 10. (ሀ) በብዙ አገሮች ያለው አዝማሚያ ምን ይመስላል? (ለ) አቅኚ የሆነ አንድ አገልጋይ አጥጋቢ እንደሆነ አድርጎ ሊመለከተው የሚገባው ደሞዝ ምን ያህል ሊሆን ይችላል?
9 አንድ ወጣት ክርስቲያን እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማክበርና ክርስቲያናዊ ግዴታዎቹን ለመወጣት እስከምን ድረስ መማር ያስፈልገዋል? ይህ ከአገር ወደ አገር ይለያያል። ይሁን እንጂ በጠቅላላው ሲታይ በብዙ አገሮች ውስጥ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ በቂ ደሞዝ ለማግኘት የሚያስፈልገው የትምህርት ደረጃ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረው ይልቅ አሁን እንደጨመረ ያሳያል። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ካሉት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፎች የሚመጡት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በብዙ ቦታዎች በሕግ የሚጠየቀውን መለስተኛ የትምህርት ደረጃ አጠናቆ እንዲያውም በአንዳንድ አገሮች ሁለተኛን ወይም ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ካጠናቀቁ በኋላ እንኳን በቂ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ እንደመጣ ያሳያሉ።
10 “በቂ ደሞዝ” ሲባል ምን ማለት ነው? ከፍተኛ ደሞዝ የሚከፈላቸውን ሥራዎች አያመለክትም። የዌብስተር መዝገበ ቃላት “በቂ” የሚል ትርጉም ያለውን እዚህ ላይ የገባውን “ዲሰንት” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል “አጥጋቢ፣ ደህና” በማለት ይተረጉመዋል። ለምሳሌ ያህል የምሥራቹ አቅኚ አገልጋዮች ለመሆን ለሚፈልጉት “አጥጋቢ” የሚባለው ምን ያህል ነው? እንዲህ ያሉት ባጠቃላይ በወንድሞች ወይም በቤተሰባቸው ላይ “እንዳይከብዱባቸው” የትርፍ ሰዓት ሥራ ያስፈልጋቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 2:9) ደሞዛቸው “አጥጋቢ” ወይም “ደህና” ነው ሊባል የሚቻለው የሚያገኙት ገንዘብ ክርስቲያናዊ አገልግሎታቸውን ለመፈጸም የሚችሉበት በቂ ጊዜና ጥንካሬ ትቶላቸው በበቂ ሁኔታ ለመኖር የሚያስችላቸው ሲሆን ነው።
11. አንዳንድ ወጣቶች የአቅኚነት አገልግሎትን ያቋረጡት ለምንድን ነው? ምን ጥያቄስ ይነሳል?
11 በዛሬው ጊዜ በአብዛኛው ያለው ሁኔታ ምንድን ነው? በአንዳንድ አገሮች በቀና አስተሳሰብ የተነሳሱ ብዙ ወጣቶች መንግሥት እንዲያጠናቅቁ የሚፈልግባቸውን መለስተኛ የትምህርት ደረጃ ከጨረሱ በኋላ አቅኚዎች ለመሆን ሲሉ ትምህርታቸውን ይተዋሉ። ምንም ዓይነት የንግድ ሥራ ትምህርት ወይም ዓለማዊ የትምህርት ችሎታ የላቸውም። በወላጆቻቸው ባይረዱ ኖሮ የትርፍ ሰዓት ሥራ መፈለግ ይኖርባቸው ነበር። አንዳንዶች የዕለት ጉርስ ለማግኘት ብቻ ለረጅም ሰዓታት እንዲሠሩ የሚጠይቁባቸውን ሥራዎች ለመያዝ ተገደዋል። አካላዊ ድካም ስለሚኖራቸውም የአቅኚነት አገልግሎታቸውን አቋርጠዋል። እንዲህ ያሉት ሰዎች በገንዘብ ረገድ ራሳቸውን ችለው ወደ አቅኚነት አገልግሎት እንዲመለሱ ምን ለማድረግ ይችላሉ?
ትምህርትን በሚመለከት ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
12. (ሀ) ትምህርትን በተመለከተ አንድ ክርስቲያን ሊያስወግዳቸው የሚገቡት ሁለት የተራራቁ አመለካከቶች ምንድን ናቸው? (ለ) ራሳቸውን ለወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮችና ለልጆቻቸው ትምህርት ሊኖረው የሚገባው ዓላማ ምን መሆን ይኖርበታል?
12 ለትምህርት ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት መያዝ ሊረዳ ይችላል። በብዙዎቹ ዓለማዊ ወጣቶች ዘንድ ትምህርት የክብር ምልክት፣ ወደ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ለመድረስ የሚረዳቸው መሰላል፣ በሀብት ተንደላቆ ለመኖር የሚያስችል ቁልፍ ተደርጎ ይታያል። ለሌሎች ደግሞ ትምህርት ቶሎ ጨርሰው ለመገላገል የሚጣደፉበት አሰልቺ ሥራ ነው። ከእነዚህ አመለካከቶች የትኛውም ቢሆን ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ተገቢ አይደለም። ታዲያ “ሚዛናዊ አመለካከት” ሊባል የሚችለው ምንድን ነው? ክርስቲያኖች ትምህርትን የሚመለከቱት የሆነ ግብ ለማሳካት እንደሚረዳ አድርገው መሆን ይኖርበታል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ዓላማቸው የሚቻለውን ያህል ውጤታማ በሆነ መንገድ ይሖዋን ማገልገል ነው። በሚኖሩበት አገር ያለው ዝቅተኛው ወይም ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሰጠው ትምህርት አቅኚዎች ሆነው ለማገልገል ራሳቸውን የሚደግፉበት በቂ ገቢ የሚያስገኝላቸው ሥራ ለመያዝ የማይፈቅድላቸው ከሆነ ተጨማሪ ትምህርት ወይም ሥልጠና ስለ መውሰድ ማሰብ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ይህም የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ግብ በማድረግ የሚከናወን ሊሆን ይገባዋል።
13. (ሀ) በፊሊፒንስ ያለች አንዲት እህት ያሉባትን የቤተሰብ ግዴታዎች እየተወጣች በአቅኚነት ልትቀጥል የቻለችው እንዴት ነበር? (ለ) ለጊዜው ተስማሚ የሆነው ምን ማስጠንቀቂያ ነው?
13 አንዳንዶች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲጀምሩ ወይም አቋርጠው ከነበረ እንደገና እንዲቀጥሉበት ያስቻላቸውን የሥራ ዕድል የከፈቱላቸውን የሥልጠና ኮርሶች ወስደዋል። አንዲት በፊሊፒንስ ያለች እህት ቤተሰቧ የሚተዳደረው ከእርሷ በሚገኝ ገቢ ነበር፤ ነገር ግን አቅኚ ለመሆን ፈለገች። ቅርንጫፍ ቢሮው “አቅኚ ለመሆን የቻለችው ሰርቲፋይድ አካውንታንት (በሒሳብ አያያዝ ከዲግሪ በላይ) እንድትሆን ያስቻላትን ተጨማሪ ትምህርት በመውሰዷ ነው” በማለት ሪፖርት አድርጓል። ይኸው የቅርንጫፍ ቢሮ ሪፖርት “በቅርንጫፋችን ሥር ትምህርታቸውን እየተማሩ አቅኚ ለመሆን ፕሮግራማቸውን ያስተካከሉ ብዙዎች አሉ። ባጠቃላይ ማጥናትን የሚወዱ ሁሉ የተሻሉ አስፋፊዎች ናቸው። እርግጥ ይህ የሚሆነው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ የጦፈ ስሜት እስካላደረባቸው ድረስ ነው” በማለት ያብራራል። የመጨረሻው አገላለጽ ልናስብበት የሚገባንን ምክንያት ይሰጠናል። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የሚወሰደው ተጨማሪ ትምህርት ዓላማው ሊዘነጋ ወይም ወደ ቁሳዊ ግብ ሊለወጥ አይገባውም።
14, 15. (ሀ) ትምህርትን በሚመለከት ጥብቅ ደንቦችን ማውጣት የማይቻለው ለምንድን ነው? (ለ) ኃላፊነት ያላቸው አንዳንድ ወንድሞች ምን ዓለማዊ ትምህርት አግኝተዋል? ይሁን እንጂ ለዚህ ምን ማካካሻ አግኝተዋል?
14 በጥቂት አገሮች ውስጥ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሙያ ሥልጠናዎችን ይሰጣሉ። ይህም አንድን ወጣት ክርስቲያን ለአንድ ዓይነት የንግድ ሥራ ሊያዘጋጀው ወይም ከተመረቀ በኋላ ሥራ ሊያስይዘው ይችላል። ሁኔታው እንደዚህ ባይሆንም እንኳን በአንዳንድ አገሮች ታታሪ ወጣቶች መሠረታዊውን ትምህርት ብቻ ተምረው አቅኚ ለመሆን የሚያስችላቸው በቂ ገቢ የሚያገኙበትን የትርፍ ሰዓት ሥራ አግኝተዋል። ስለዚህ ተጨማሪ ትምህርት መማርን የሚደግፉ ወይም የሚከለክሉ ጥብቅ ደንቦችን ማውጣት አይቻልም።
15 በአሁኑ ጊዜ እንደ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በመሆን ወይም በማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት ወይም ከቅርንጫፎቹ በአንዱ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚያገለግሉ ብዙዎች ያጠናቀቁት መሠረታዊ ትምህርትን ብቻ ነው። መማራቸውን በፍጹም ያላቆሙ፣ ሥልጠና የተቀበሉና የትልልቅ ኃላፊነቶች አደራ የተሰጣቸው ታማኝ አቅኚዎች ናቸው። ባደረጉት ምርጫ ምንም አይቆጩም። በሌላው በኩል ግን ተመሳሳይ ዕድሜ ያላቸው ሌሎች ወጣቶች የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለማግኘት በመምረጣቸው ምክንያት እምነት በሚያጠፉ ፍልስፍናዎችና “በዚህ ዓለም ጥበብ” ተሸንፈው ወድቀዋል።—1 ቆሮንቶስ 1:19-21፤ 3:19, 20፤ ቆላስይስ 2:8
ወጪውን ማስላት
16. (ሀ) ተጨማሪ ትምህርት አስፈላጊ መሆን አለመሆኑን የሚወስነው ማን ነው? በአእምሮ ውስጥ ከፍ ተደርጎ ሊያዝ የሚገባው ነገር ምን መሆን ይኖርበታል? (ለ) ሊታሰብበት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
16 አንድ ወጣት ክርስቲያን ተጨማሪ ትምህርት ወይም ሥልጠና መውሰድ አለበት ወይም የለበትም ብሎ የሚወስነው ማን ነው? እዚህ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ የራስነት መሠረታዊ ሥርዓት ይገባል። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 6:1) በዚህ ሁኔታ ወላጆች ልጆቻቸውን በሚመርጡት የንግድ ሥራ ወይም ሞያና ለዚያም የሚያስፈልገው የትምህርት መጠን በኩል ሊመሯቸው ይፈልጋሉ። በብዙ አገሮች የትምህርትና የሥራ ምርጫዎች የሚደረጉት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መጀመሪያ ላይ ነው። ክርስቲያን ወላጆችና ወጣቶች የመንግሥቱን ፍላጎቶች በአእምሮ ከፍ አድርጎ በመያዝ ጥበብ ያለበት ምርጫ ለማድረግ እንዲችሉ ይሖዋ እንዲመራቸው መጠየቅ የሚያስፈልጋቸው ያን ጊዜ ነው። ወጣቶች የተለያዩ ዝንባሌዎችና ተሠጥኦዎች አሏቸው። ጥበበኛ ወላጆች እነዚህንም ግምት ውስጥ ያስገቧቸዋል። የጉልበት ሥራም ይሁን የቢሮ ሐቀኛ ሠራተኛ መሆን የሚያኮራ ነው። ምንም እንኳን ዓለም የቢሮ ሥራን ከፍ አድርጎ አንድ ሰው በእጆቹ በርትቶ የሚሠራውን ሥራ ቢያንኳስስም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ አያደርግም። (ሥራ 18:3) ስለዚህ በዛሬው ጊዜ ወላጆችና ወጣት ክርስቲያኖች ጥቅሙንና ጉዳቱን በጥንቃቄና በጸሎት ካሰቡበት በኋላ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚቀጥል ትምህርት ለመውሰድ ወይም ላለመውሰድ ቢወስኑ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ሊተቿቸው አይገባም።
17. ምስክር የሆኑ አንዳንድ ወላጆች ለልጆቻቸው ምን መርጠውላቸዋል?
17 ክርስቲያን ወላጆች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሲሉ ልጆቻቸው ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኋላ በትምህርታቸው እንዲቀጥሉ ከወሰኑ መብታቸው ነው። ይህ ትምህርት የሚወስደው ጊዜ እንደተመረጠው የንግድ ሥራ ወይም የሞያ ሁኔታ ይለያያል። ገንዘብ ነክ በሆኑ ምክንያቶችና ልጆቻቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በተቻለው ፍጥነት እንዲገቡ የሚፈልጉ ብዙ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው በሞያ ወይም የቴክኒክ ትምህርት ቤቶች የሚሰጡትን የአጭር ጊዜ የትምህርት ፕሮግራሞች እንዲከታተሉ መርጠዋል። በአንዳንድ ጊዜያት ወጣቶች ይሖዋን በሙሉ ጊዜ ማገልገልን እንደ ግብ አድርገው በመያዝ አንድ ዓይነት ሞያ ለማወቅ ሲሉ በነፃ እየሠሩ ትምህርት ቀስመዋል።
18. ተጨማሪ ኮርሶች ከተወሰዱ በአእምሮ ውስጥ መቀመጥ የሚኖርበት ነገር ምንድን ነው?
18 ተጨማሪ ኮርሶች ከሚወሰዱ ዓላማቸው በትምህርት በኩል ልቆ ለመታየት ወይም ስመ ጥር የሆኑ ዓለማዊ ሥራዎችን ለመያዝ መሆን የለበትም። ኮርሶች በጥንቃቄ መመረጥ ይኖርባቸዋል። ይህ መጽሔት ከፍተኛ ትምህርት የመማርን አደጋዎች አጥብቆ ገልጿል። ይህም ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ከፍተኛ ትምህርቶች “ሕይወት የሚገኝበትን [ጤናማውን አዓት]” የመጽሐፍ ቅዱስ “ትምህርት” ይቃወማሉ። (ቲቶ 2:1፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21) በተጨማሪም ከ1960ዎቹ ጀምሮ ከፍተኛ ትምህርት የሚሰጡ ብዙ ትምህርት ቤቶች የዓመፅና የሥነ ምግባር ውድቀት ምቹ መስፋፊያ ቦታዎች ሆነዋል። “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንዲህ ወዳለው አካባቢ መግባት ስለሚያስከትለው አደጋ በጥብቅ ሲያሳስብ ቆይቷል። (ማቴዎስ 24:12, 45) ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ወጣቶች በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በሙያ ኮሌጆች ውስጥ፣ በሥራ ቦታም እንኳን እንዲህ ያሉት አደጋዎች እንደሚያጋጥሙአቸው ሊታመን ይገባል።—1 ዮሐንስ 5:19a
19. (ሀ) ተጨማሪ ኮርሶችን ለመውሰድ የወሰኑ ምን ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይገባቸዋል? (ለ) አንዳንዶች ትምህርታቸውን ለጥሩ ነገር የተጠቀሙበት እንዴት ነው?
19 አንድ ወጣት ምስክር ተጨማሪ ትምህርት እንዲማር ከተወሰነ የዘወትሩን ክርስቲያናዊ የጥናት ልማዱን፣ በስብሰባዎች መካፈልና የስብከት ሥራውን ለማከናወን ይችል ዘንድ ከቤተሰቦቹ ሳይለይ ቢከታተለው የተሻለ ይሆናል። ገና ኮርሱ ከመጀመሩ በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተገቢ አቋም መውሰድ ይኖርበታል። ዳንኤልና ሦስቱ ዕብራውያን ባልንጀሮቹ በግዞት ምርኮኞች በነበሩበት ጊዜ በባቢሎን ውስጥ ተጨማሪ ትምህርቶች እንዲወስዱ ቢገደዱም ንጹሕ አቋማቸውን እንደጠበቁ ሊታወስ ይገባል። (ዳንኤል ምዕራፍ 1) በብዙ አገሮች ውስጥ ያሉ ወጣት ምስክሮች መንፈሳዊ ፍላጎቶችን በመጀመሪያ ደረጃ በማስቀመጥ እንደ ሒሳብ ያዦች፣ ዕቃ ሻጮች፣ አስተማሪዎች፣ አስተርጓሚዎች ወይም የጽሑፍ ተርጓሚዎች በመሆን የትርፍ ሰዓት ሥራ ለመሥራት የሚያዘጋጁአቸውን ወይም በዋናው የአቅኚነት ቋሚ ሥራቸው በበቂ ሁኔታ ሊደግፏቸው የሚችሉ ሌሎች ሥራዎች የሚያስይዟቸውን ኮርሶች ወስደዋል። (ማቴዎስ 6:33) እንዲህ ካሉት ወጣቶች ውስጥ ብዙዎቹ በኋላ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ወይም የቤቴል ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነዋል።
የተማረና ኅብረት ያለው ሕዝብ
20. በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ቦታ የሌለው ምን ዓይነት ዓለማዊ ማበላለጥ ነው?
20 በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለ አንድ ሰው ሥራው የጉልበት ሥራም ይሁን የቢሮ ሥራ፣ ግልጋሎት ሰጪነት ወይም ግብርና ሁሉም ምስክሮች ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችና ችሎታ ያላቸው አስተማሪዎች መሆን ያስፈልጋቸዋል። ሁሉም በማንበብ፣ በማጥናትና በማስተማር በኩል የሚያዳብሯቸው ችሎታዎች ዓለም በእጅ ሥራና በቢሮ ሠራተኞች መካከል በሚያደርገው ማበላለጥ ምክንያት ሊመጣባቸው ይችል የነበረውን ጉዳት አስቀርተዋል። ይህም መንፈሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ በሚሰጥባቸውና ከሁሉም በሚፈለጉባቸው በቤቴል ቤቶችና በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የግንባታ ቦታዎች የሚሠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች መካከል በተለየ ሁኔታ በግልጽ የሚታየውን ኅብረትና እርስ በርስ መከባበርን ያስገኛል። በእነዚህ ቦታዎች ብዙ ልምድ ያላቸው የቢሮ ሠራተኞች ችሎታ ካላቸው የእጅ ሙያተኞች ጋር በደስታ ይሠራሉ። ሁሉም እርስ በርሳቸው አድናቆት ያለው ፍቅር ያሳያሉ።—ዮሐንስ 13:34, 35፤ ፊልጵስዩስ 2:1-4
21. የወጣት ክርስቲያኖች ዓላማ ምን መሆን ይኖርበታል?
21 ወላጆች ሆይ፣ ልጆቻችሁ የአዲሲቱ ዓለም ኅብረተሰብ ጠቃሚ አባላት ሊሆኑ ወደሚችሉበት ግብ ምሯቸው! እናንተም ወጣት ክርስቲያኖች፣ ለመማር ያሏችሁን አጋጣሚዎች ሙሉ በሙሉ ይሖዋን ለማገልገል ለሚኖሯችሁ መብቶች የሚያዘጋጁአችሁ መንገዶች አድርጋችሁ ተጠቀሙባቸው! ሁላችሁም የተማራችሁ በመሆን አሁንም ሆነ አምላክ በሚያመጣው “አዲስ ምድር” ውስጥ ለዘላለም በደንብ የታጠቃችሁ የቲኦክራቲካዊው ኅብረተሰብ አባላት ሆናችሁ የምትገኙ ያድርጋችሁ።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ኢሳይያስ 50:4፤ 54:13፤ 1 ቆሮንቶስ 2:13
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በተጨማሪም የመስከረም 1, 1975ን የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 542-4 ተመልከት።
የማስታወስ ችሎታህን ፈትን
◻ እውነተኛ ክርስቲያኖች የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ለምንድን ነው?
◻ ትምህርትን በተመለከተ አንድ ክርስቲያን ሊያስወግዳቸው የሚገቡት የተራራቁ አመለካከቶች ምንድን ናቸው?
◻ ተጨማሪ ትምህርት የሚያስከትላቸው ሊታሰብባቸው የሚገቡ አደጋዎች ምንድን ናቸው? ምን ጥንቃቄዎችስ ሊወሰዱ ይገባል?
◻ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ቦታ የሌለው ምን ዓይነት ዓለማዊ ማበላለጥ ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣት ክርስቲያኖች በትጋት በመማር የአዲሲቱ ዓለም ኅብረተሰብ በይበልጥ ጠቃሚ አባላት ሊሆኑ ይችላሉ
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተጨማሪ ትምህርት ሊወሰድ ከተመረጠ ይሖዋን በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል ባለን ፍላጎት ተገፋፍተን የምንከታተለው መሆን ይኖርበታል