የተማረ ሰው
“ወንድሞች ሆይ፣ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፣ ኃያላን የሆኑ ብዙዎች፣ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም።” (1 ቆሮንቶስ 1:26) እነዚህ ቃላት እንደሚያመለክቱት በዓለማዊ የጥበብ ባሕር ውስጥ መዘፈቅ ወይም ከፍተኛ ወደሆነ ማኅበራዊ ደረጃ ላይ መድረስ አደጋ አለው። እንዲህ ያሉት ነገሮች አንድ ሰው የምሥራቹን እንዳይቀበል ዕንቅፋት ሊሆኑበት ይችላሉ።—ምሳሌ 16:5፤ ማርቆስ 10:25
ሆኖም በጳውሎስ ዘመን በሥጋዊ መንገድ ጥበበኞች የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እውነትን ተቀብለዋል፤ ከነዚህም አንዱ ጳውሎስ ራሱ ነበር። በደንብ የተማረና ስመ ጥር ከሆነ ቤተሰብ የመጣ ቢመስልም ጳውሎስ ቀናተኛ የወንጌል ሰባኪ ነበር። ስለዚህ በዚች ዓለም ውስጥ ጥሩ ቦታ ያላቸው ሰዎችም ትክክለኛ ልብ ካላቸው ይሖዋን ሊያገለግሉ እንደሚችሉ አሳይቷል። እንዲያውም ሥጋዊ ችሎታቸውን ለይሖዋ አገልግሎት ሊጠቀሙበት ይችላሉ።—ሉቃስ 16:9
የጠርሴስ ተወላጅ
ጳውሎስ የተወለደው በኋላ “ስመ ጥር” ብሎ በገለጻት በጠርሴስ ከተማ ነበር። (ሥራ 21:39) ምናልባትም የቋንቋ እውቀቱን በተለይም በሚስዮናዊ ሥራው ወቅት በጣም የጠቀመውን በጊዜው የበላይ የነበረውን የግሪክኛ ቋንቋ እውቀት ያገኘው እዚህ ሳይሆን አይቀርም። በጠርሴስ የነበረው ኑሮ ጳውሎስን ለአይሁድ የአኗኗር መንገዶች ብቻ ሳይሆን በኋላ የአሕዛብ ሐዋርያ ሆኖ ባገለገለበት ጊዜ ጥሩ ተሞክሮ በመሆን ለጠቀመው ለአሕዛብ ባሕልም ጭምር አጋልጦት ነበር። እነሱ ሊረዱት በሚችሉት መንገድ እውነትን እንዴት አድርጎ መግለጽ እንደሚችል ያውቅ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 9:21) ለምሳሌም ያህል በሥራ ምዕራፍ 17 ላይ ያለውን ለአቴናውያን ያቀረበውን ንግግር ተመልከቱ። እዚህ ላይ ከአቴናውያን ሃይማኖት እንዲያውም ከባለቅኔዎች አንዱ የተናገረውን እንኳ ሳይቀር በመጥቀስ በዘዴ አቀነባብሮ ስለ እውነት መስክሯል።
ሮማዊ ዜግነት ያለው
ጳውሎስን የጠቀመው ሌላም ዓለማዊ ሁኔታ ነበረው። ዜግነቱ ሮማዊ ስለነበር ይህንንም የምሥራቹን ለማስፋፋት ተጠቅሞበታል። በፊልጵስዩስ እሱና ጓደኞቹ ገና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ተደብድበውና ወደ ወኅኒ ተጥለው ነበር። በአንድ የሮም ዜጋ ላይ ደግሞ ይህን መፈጸም ሕገወጥ ነበርና ጳውሎስ የደረሰበትን ነገር ለባለ ሥልጣኖቹ በገለጸ ጊዜ ወደሚቀጥለው ጉዞው ከመሄዱ በፊት እዚያ እንዲቆይና ጉባኤዎችን እንዲያገለግል ፈቀዱለት።—ሥራ 16:37-40
ቆይቶም በአገረ ገዢው በፊስጦስ ፊት ሲቀርብ ጳውሎስ ይህን የሮማዊ ዜግነቱን ጉዳይ ለቄሣር ይግባኝ ለማለት ተጠቅሞበታል። በዚህ መንገድ በሮማ ግዛት ውስጥ በመጨረሻው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ፊት ለምሥራቹ መከላከያ አቅርቧል።—ሥራ 25:11, 12፤ ፊልጵስዩስ 1:7
ጳውሎስ ተግባራዊ በሆነ መንገድ ያገኘው ሥልጠና በኋላ ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል። ድንኳን መስፋትን ተምሮ ነበር፤ ይህንንም ከአባቱ የተማረው ሳይሆን አይቀርም። ይህን ሥራ በመማሩ ምክንያት አንዳንድ ጊዜ የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥመው ራሱን ደግሞ በአገልግሎቱ እንዲቀጥል አስችሎታል። (ሥራ 18:1-3) ከዚህም ሌላ ሰፊ ሃይማኖታዊ ትምህርትንም ገብይቶ ነበር። ያደገው “ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ” ሆኖ ነበር። (ሥራ 23:6) ገናና ከሆኑት የአይሁድ መምህራን አንዱ በሆነው በገማልያል እግር አጠገብ ሆኖ ተምሯል። (ሥራ 22:3) ምናልባትም ጥሩ ከሆነው ከዛሬው የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ጋር ሊወዳደር የሚችለው እንዲህ ያለ ትምህርት ለማግኘት መቻሉ ጳውሎስ እንደ ትልቅ ተደርጎ ከሚቆጠር ቤተሰብ የመጣ መሆኑን ያሳያል።
ተገቢ አመለካከት መያዝ
የጳውሎስ አስተዳደግና ያገኘው ሥልጠና በአይሁድ ሃይማኖት ብሩህ አጋጣሚዎችን ከፍተውለት ነበር። በዚሁ መግፋትና ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስን እንደ መሲህ አድርጎ ከተቀበለ በኋላ የጳውሎስ ግቦች ተቀየሩ። ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ሲጽፍላቸው በፊት የነበሩትን አንዳንድ ዓለማዊ አጋጣሚዎች ዘረዘረላቸውና “እንግዲህ ከዚህ በፊት ጠቃሚዎች ናቸው ብዬ አምንባቸው የነበሩትን ነገሮች ሁሉ ስለ ክርስቶስ ብዬ ዋጋ እንደሌላቸው ከንቱ ነገሮች አድርጌ እቆጥራቸዋለሁ። ከዚህም በቀር ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን ከማወቅ የበለጠ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ ስለማምን ሁሉን እንደ ኪሣራ እቆጥረዋለሁ” አላቸው።—ፊልጵስዩስ 3:7, 8 የ1980 ትርጉም
ይህ የተማረ ሰው መለስ ብሎ ወደኋላ እየተመለከተ በዓለማዊ ትምህርቱ ምን ሊሠራበት ይችል እንደነበር በማሰብ አልተቆጨም፤ ወይም “ከፍተኛ ትምህርቱን’ ከሌሎች በልጦ ለመታየት አልተጠቀመበትም። (ሥራ 26:24፤ 1 ቆሮንቶስ 2:1-4) ከዚህ ይልቅ በይሖዋ አምላክ ላይ ሙሉ እምነት በመጣል በፊት ስለነበሩት አጋጣሚዎቹ ሲናገር “በስተኋላዬ የነበረውን እየረሳሁ፣ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እተጋለሁ። ሽልማቴን ለማግኘት በፊቴ ወዳለው ግብ እሮጣለሁ፤ ይህም ሽልማት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ወደ ላይ ጠርቶ የሚሰጠኝ ሕይወት ነው።” (ፊልጵስዩስ 3:13, 14 የ1980 ትርጉም) ጳውሎስ ከፍ አድርጎ የተመለከተው መንፈሳዊ ነገሮችን ነበር።
ሆኖም ጳውሎስ ያንን በፊት ያገኘውን ሥልጠና በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ተጠቅሞበታል። ስለ አይሁዳውያን ሲናገር “ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁ” ብሎ ሲናገር በግል ካገኘው ተሞክሮ አንፃር ነበር። (ሮሜ 10:2) ፈሪሳዊ ስለነበር ለአምላክና ለቅዱሳን ጽሑፎች ቅንዓት ነበረው። ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ቅንዓቱ በትክክለኛ እውቀት የተደገፈ ሆነ፤ የቀድሞ ትምህርቱንም ለጽድቅ ዓላማ ተጠቀመበት። ለምሳሌ ያህል የእስራኤላውያንን ታሪክና የቤተ መቅደሱን አምልኮ በተመለከተ በፊት የነበረውን ጥልቅ እውቀት የክርስትና ሥርዓት ከዚያ ይልቅ ብልጫ እንዳለው በዕብራውያን መጽሐፍ ውስጥ ለማብራራት ተጠቅሞበታል።
ዛሬም በሥጋዊ መንገድ ጥበበኞች የሆኑ አንዳንዶች ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ነው። ሁሉም ዓይነት ትምህርታዊ ችሎታዎች ያላቸው ሰዎች እንዲሁም በሁሉም ዓይነት ሙያዎችና የንግድ ዘርፎች የተሠማሩ ሰዎች እውነትን ተቀብለው በፊት ያገኙትን ሥልጠና በይሖዋ አገልግሎት እየተጠቀሙበት ነው። ሆኖም ዓለማዊ ትምህርታቸው ምንም ይሁን ምን ክርስቲያኖች በጣም አስፈላጊ የሆኑት ችሎታዎች መንፈሳዊ ችሎታዎች የመሆናቸውን እውነት በፍጹም አይስቱም። ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች’ እነዚህ ናቸው፤ ምክንያቱም ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ሊመሩን ይችላሉ።—ፊልጵስዩስ 1:10