ጥሪ ሲቀርብላችሁ መልስ ትሰጣላችሁን?
በሺኒቺ ቶሀር እንደተነገረው
በመጀመሪያው የሕይወቴ ክፍል ላይ አምላክን ጠርቼውም ሆነ በምሄድበት አቅጣጫ እንዲመራኝ ጠይቄው አላውቅም ነበር። አያቶቼ ከጃፓን ወደ ሃዋይ ፈልሰው የመጡ ሲሆኑ ወላጆቼም ቡዲሂስቶች ነበሩ። በእምነታቸው እምብዛም ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ስላልነበሩ በማድግበት ጊዜ አምላክን በሚመለከት ብዙም አስቤበት አላውቅም ነበር።
ከዚያ በኋላ ስለ ዝግመተ ለውጥ ተማርኩና በአምላክ ማመን ምን ያህል ሞኝነት እንደሆነ ማሰብ ጀመርኩ። ይሁን እንጂ በመደበኛ ትምህርቴ እየገፋሁ ስሄድ የሳይንስ ትምህርት ከከዋክብት ጥናት፣ ከፊዚክስና ከሥነ ሕይወት ጋር አስተዋወቀኝ። ማታ ማታ ወደ ሰማይ አትኩሬ እመለከትና እነዚህ ሁሉ ከዋክብት ሊመጡ የቻሉት እንዴት እንደሆነ በማሰብ እገረማለሁ። በውስጤ ‘እነዚህን ሁሉ የሚቆጣጠር አምላክ ይኖር ይሆን?’ የሚል ድምፅ በቀስታ ይሰማኛል። በማይታየው ዓለም ውስጥ አንድ አካል ሳይኖር እንደማይቀር እየተሰማኝ መጣ። ልቤ ‘ይህ አምላክ ማን ነው?’ በማለት ይጠይቅ ጀመር።
ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተመረቅሁ በኋላ ከሩዝ የሚሠራ የጃፓኖች መጠጥ መጥመቂያ ፋብሪካ ውስጥ በመካኒክነት ሥራዬ ስለተያዝኩ አምላክን በሚመለከት ጥያቄ ላይ የማሰላስልበት ጊዜ አጣሁ። ብዙም ሳይቆይ በ1937 ሚስቴ ከሆነችው ከማሳኮ ጋር ተገናኘን። በመጨረሻም ሦስት ልጆችን በመውለድ ተባረክን። ማሳኮም እንዴት ያለች እምነት የሚጣልባት ጓደኛና ጠንክራ የምትሠራ እናት መሆኗን አስመስክራለች።
አሁን ቤተሰብ ያለኝ ሆንኩ። ስለ ወደፊት ሁኔታችንም በቁምነገር አሰብኩ። እንደገና ውጪ እየወጣሁ ከዋክብትን ትክ ብዬ ማየት ጀመርኩ። አምላክ እንዳለ አመንኩ። ያ አምላክ ማን እንደሆነ ግን አላውቅም ነበር፤ ብቻ እንዲሁ እሱን እጠራ ጀመር። በተደጋጋሚ ‘አንተ ካለህ እባክህ ቤተሰቤ የደስታን መንገድ እንዲያገኝ እርዳው’ እያልኩ ለመንኩት።
በመጨረሻ ጥሪዬ ተመለሰልኝ
ከጋብቻችን ጀምሮ የምንኖረው ከወላጆቼ ጋር ነበር። በ1941 ግን ሃዋይ ውስጥ በሂሎ ከተማ ለብቻችን መኖር ጀመርን። በአዲሱ ቤታችን ተመቻችተን ከተቀመጥን በኋላ ታኅሣሥ 7 ቀን 1941 ጃፓኖች የፐርል ወደብን በጦር ኃይል ደበደቡ። የውጥረት ጊዜ ነበር። ሁሉም ሰው ስለ ወደፊቱ ጊዜ ይጨነቅ ጀመር።
የፐርል ወደብ ከተደበደበች ከአንድ ወር በኋላ መኪናዬን እየወለወልኩ ሳለ አንድ ሰው መጣና ልጆች የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ እንድወስድ ጋበዘኝ። ስሙ ራልፍ ጋሩት እንደሆነ በመንገር ራሱን አስተዋወቀኝና የይሖዋ ምስክሮች የጉባኤ አገልጋይ እንደሆነ ገለጸልኝ። ምን እያለ እንዳለ አልገባኝም ነበር፤ ነገር ግን ስለ አምላክ ለማወቅ ፍላጎት ስለነበረኝ መጽሐፉን ተቀበልኩት። በሚቀጥለው ሳምንት ራልፍ ተመልሶ መጣና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድንጀምር ጋበዘኝ። ምንም እንኳን ከዚያ በፊት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብሰማም መጽሐፍ ቅዱስን ሳይ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ለመጀመር ተስማማሁ፤ ሚስቴና ታናሽ እህቷም አብረው ማጥናት ጀመሩ።
መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል የመሆኑ እውነት በእርግጥ ስሜቴን መሰጠው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ይሖዋ ዓላማ ያለው መሆኑ ደግሞ ከዚያ ይበልጥ አስደናቂ ነበር። ስፈልገው የነበረው ፈጣሪ እሱ ነበር። (ኢሳይያስ 45:18) የጠፋችው የመጀመሪያዋ ገነት እዚችው ምድር ላይ እንደገና እንደምትቋቋምና እኛም እዚያ ለመገኘት እንደምንችል ስንማር በጣም ተደነቅን። (ራእይ 21:1-4) ለአምላክ ያቀረብኩት ጥሪ መልሱ ይህ ነበር!
አዲስ ስላገኘነው ስለዚህ እውነት ለማንኛውምና ለእያንዳንዱ ሰው ተናገርን። ወላጆቼ ያበድን መስሏቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ተስፋ አላስቆረጠንም። በከፍተኛ ትጋት ከተደረገ የሦስት ወር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በኋላ በሚያዝያ 19 ቀን 1942 ሚስቴና እኔ ራሳችንን ለአምላካችን ለይሖዋ መወሰናችንን ለማሳየት ተጠመቅን። በዚያን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ተባብረውን የነበሩት የማሳኮ ታናሽ እህት ዮሺ ቶማ እና ባለቤቷ ጄሪ ከእኛ ጋር ተጠመቁ። የቅዱሳን ጽሑፎች ዕውቀታችን ውስን ነበር፤ ነገር ግን አምላክን ማገልገል እንድንፈልግ እኛን ለማንቀሳቀስ ይህ በቂ ነበር።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሁንም በመካሄድ ላይ ስለነበር መጨረሻው በጣም እንደቀረበ ተሰማኝ። ሚስቴና እኔም ሰዎችን ስለሁኔታው ሁኔታ የማስጠንቀቁ አስፈላጊነት ተሰማን። በዚህ ረገድ የጋሩት ቤተሰቦች ምሳሌዎቻችን ነበሩ። እሱና ሚስቱ ሁለቱም የይሖዋ ምስክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ማለትም አቅኚዎች ሆነው ያገለግሉ ነበር። የእኛን ሁኔታ ከራልፍ ሁኔታ ጋር አወዳደርኩት። ሚስትና አራት ልጆች አሉት። እኔ ሚስትና ሦስት ልጆች ብቻ አሉኝ። እሱ ሊያደርገው ከቻለ እኔም ላደርገው መቻል ይገባኛል። ስለዚህ ከተጠመቅን ከወር በኋላ ለአቅኚነት አገልግሎት አመለከትን።
ገና አቅኚ ከመሆኔ በፊት የብረት ጊታሬን፣ ሳክስፎኔንና ቫዮሊኔን ጨምሮ አስፈላጊ ያልሆኑ እቃዎችን መሸጥ ጀመርኩ። ለሙዚቃ ትልቅ ፍቅር የነበረኝ ብሆንም ከትንሿ ሐርሞኒካዬ በስተቀር ሁሉንም አስወገድኳቸው። ከዚህም በላይ ከሩዝ በሚሠራ የጃፓኖች መጠጥ መጥመቂያ ፋብሪካ ውስጥ የነበረኝ ሥራ ከዚያ ወዲህ አስደሳች ሆኖ አልታይ አለኝ። (ፊልጵስዩስ 3:8) ተጎታች ቤት ሠራሁና ይሖዋ እንዲጠቀምብኝ ያቀረብኩትን ልመና ይመልስልኝ እንደሆነ ለማየት መጠባበቅ ጀመርኩ። መልሱ እስኪመጣ ብዙም መጠበቅ አላስፈለገኝም። ከሰኔ 1 ቀን 1942 ጀምሮ አቅኚ ሆነን ለማገልገል ተቀባይነት አገኘን። በቀጥታ ይሖዋን ሙሉ ጊዜ ማገልገል ጀመርን። በዚህ ውሳኔያችንም ተቆጭተን አናውቅም።
በሃዋይ ውስጥ አቅኚ ሆኖ ማገልገል
ከጋሩት ቤተሰብ ጋር ሆነን ካኡንና ታዋቂ ቡና አብቃይ አካባቢ የሆነውን ኮንን ጨምሮ ሃዋይንና ትልቁን ደሴት ሸፈንን። በእነዚያ ቀናት እንሠራ የነበረው በሸክላ ማጫወቻዎች በመጠቀም ነበር። በጣም ከባድ ነበር። ይሁን እንጂ እኛም ገና ወጣቶች ስለነበርን በቂ ጉልበት ነበረን። በአንድ እጃችን የሸክላ ማጫወቻውን በሌላው ደግሞ ቦርሳ ሙሉ መጻሕፍት ይዘን በቡና ማሳዎች፣ በእርሻዎችና በየትም ቦታ ሰሚ ጆሮ ወዳላቸው ሰዎች የሚወስደንን ማንኛውንም የእግር መንገድ እንከተል ነበር። ከዚያም መላውን ደሴት ከሸፈንን በኋላ በትልቁ ደሴት ላይ ወዳለው ወደ ኮሃላ ተመደብን። ኮሃላ አነስተኛ የሸንኮራ እርሻ ስትሆን ካውካሲያኖች፣ የፊሊፒንስ ሰዎች፣ ቻይናውያን፣ የሃዋይ ሰዎች፣ ጃፓናውያንና ፖርቱጋላውያን የሚኖሩባት ነች። እያንዳንዱ ቡድን የራሱ የሆነ ባሕል፣ አስተሳሰብ፣ ምርጫና ሃይማኖት አለው።
አቅኚነት ከጀመርኩ በኋላ እንደገና ሥጋዊ ሥራ ለመሥራት በፍጹም አልተቀጠርኩም። ቆጥቤ ባጠራቀምኩት ገንዘብ ለተወሰነ ጊዜ ኖርን። አስፈላጊ በሚሆንበትም ጊዜ በጦር ዓሣ ለማጥመድ እሄዳለሁ። በሚያስገርም ሁኔታ ሁልጊዜ ዓሦች ይዤ እመለስ ነበር። የዱር አትክልቶችንና በመንገዱ ዳር ላይ የሚበቅሉትን የሚበሉ ቅጠላ ቅጠሎችን እንለቅማለን። እነዚህም በራት ሰዓት ሳህኖቻችንን ያሳምሩታል። ዚንክ ከተቀባ ቲን የተባለ ብረት ምድጃ ሠራሁ። ማሳኮም ዳቦ መጋገርን ተማረች። እስከዛሬ ከበላኋቸው ዳቦዎች ሁሉ የሚበልጥ በጣም ጥሩ ዳቦ ነበር።
በ1943 ለክርስቲያናዊ ስብሰባ ወደ ሆነሉሉ ስንሄድ የሃዋይ ቅርንጫፍ የበላይ ተመልካች የነበረው ዶናልድ ሃስሌት ወደዚያ እንድንዛወርና በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመኪና ማቆሚያ ላይ በተገነባው አነስተኛ አፓርታማ ውስጥ እንድንኖር ጋበዘን። የቅርንጫፉ ንብረቶች ጠባቂ ሆኜ ተመደብኩ። ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም እዚያ በአቅኚነት በመሥራት ተደስቻለሁ።
ያልተጠበቀ ጥሪ
በ1943 ማኅበሩ ለውጭ አገር አገልግሎት ሚስዮናውያንን ለማሰልጠን ትምህርት ቤት እንደከፈተ ሰማን። በዚያ ብንካፈል ምን ያህል እንወድ ነበር! ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች አይጋበዙም ነበርና በነገሩ ላይ ገፋ አድርገን አላሰብንበትም። ይሁን እንጂ በ1947 ወንድም ሃስሌት ማኅበሩ በጃፓን ውስጥ የውጭ አገር አገልግሎት መሥራት የሚፈልጉ የሃዋይ ተወላጆች ይኖሩ እንደሆነ ለማወቅ እንደሚፈልግ ነገረን። ስለዚህ ነገር ምን እንደምናስብ ጠየቀንና ልክ እንደ ኢሳይያስ “እኔን ላከኝ” አልኩት። (ኢሳይያስ 6:8) ሚስቴም የተሰማት ልክ እንዲሁ ነበር። የይሖዋን ጥሪ ለመቀበል ምንም አላንገራገርንም።
ስለዚህ ሚስዮናዊ ሆነን ለመሰልጠን የመጠበቂያ ግንብ የጊሊያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንድንካፈል ተጋበዝን። ጥሪው ሦስቱን ሕፃናት ልጆቻችንንም ይጨምር ነበር። ሌሎች አምስት ይኸውም ዶናልድና ማብል ሃስሌት፣ ጄሪና ዮሺ ቶማ እንዲሁም ኤልሲ ታነጋው ተጋብዘው ነበርና በ1948 የክረምት ወራት አብረን ወደ ኒው ዮርክ ሄድን።
አህጉሩን በአውቶቡስ አቋረጥነው። ከሦስት ቀን የአውቶቡስ ጉዞ በኋላ ሁላችንም ስለደከምን ወንድም ሃስሌት ዕረፍት እንድንወስድና ሌሊቱን ሆቴል ውስጥ እንድናሳልፈው ሀሳብ አቀረበ። ከአውቶቡሱ ስንወርድ አንድ ሰው ወደኛ ቀረበና “ጃፓናውያን! እነሱን ለመግደል ወደ ቤቴ ሄጄ ጠመንጃ አመጣለሁ!” እያለ ጮኸ።
“ጃፓናውያን እኮ አይደሉም” አለ ወንድም ሃስሌት። “የሃዋይ ሰዎች ናቸው። አትለያቸውም እንዴ?” እንዲህ ባለው በፍጥነት በተሰጠ አስተያየት ዳንን።
በእውነት እኛ የ11ኛው የጊልያድ ተማሪዎች ክፍል ነን? ልክ እንደ አስደሳች ሕልም መሰለን። የነገሩ እውንነት ወዲያው ተረጋገጠ። በክፍላችን ውስጥ በዚያ ጊዜ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት በነበረው በናታን ኤች ኖር የተመረጥን 25 ተማሪዎች ነበርን። የምንሠለጥነውም በጃፓን ለሚኖረው የሚስዮናዊነት አገልግሎት ነበር። የጃፓን ዝርያ ስላለብኝና ጃፓንኛ በጥቂቱ መናገር እችል ስለነበር ለእነዚህ የተማሪዎች ቡድን ቋንቋውን እንዳስተምር ተመደብኩ። የቋንቋው በቂ ችሎታ ስላልነበረኝ ይህን ማድረግ ቀላል ባይሆንም ሁላችንም እንደምንም ሞከርን።
በዚያ ጊዜ ወንዱ ልጃችን ሎይ አሥር ዓመቱ ነበር። ሁለቱ ሴቶች ልጆቻችን ቴልማና ሳሊ ደግሞ ስምንትና ስድስት ዓመታቸው ነበር። እኛ ትምህርት ቤት በነበርንበት ጊዜ እነሱ ምን ይሠራሉ? እነሱም ትምህርት ቤት ይሄዱ ነበር! ጠዋት ጠዋት አውቶቡስ መጥቶ ወደ ትምህርት ቤት ይወስዳቸዋል፤ ከሰዓት ደግሞ ወደ ቤት ያመጣቸዋል። ልጆቹ ከትምህርት ቤት መጥተው እቤት ሲደርሱ ሎይ በማኅበሩ የእርሻ ቦታ ከወንድሞች ጋር ሲሠራ ቴልማና ሳሊ ደግሞ በላውንደሪ ውስጥ መሐረቦችን ያጣጥፉ ነበር።።
ከማናውቀው ሁኔታ ጋር ለማለማመድ አእምሮአችንን ማዘጋጀት
በነሐሴ 1 ቀን 1948 ከጊልያድ ስንመረቅ ወደ ምድብ ቦታችን ለመሄድ ጓጉተን ነበር። ወንድም ሃስሌት ሚስዮናዊያኖቹ የሚኖሩበትን ቦታ ለመፈለግ ከኛ ቀድሞ ሄደ። በመጨረሻም በቶኪዮ ውስጥ ባለ ሁለት ፎቅ ቤት አገኘና በነሐሴ 20 ቀን 1949 ቤተሰባችን ወደፊት ወደምንኖርበት ቤታችን ሄደ።
ጃፓን ከመድረሳችን በፊት ስለዚህ ምሥራቃዊ ምድር ብዙ ጊዜ አስብ ነበር። የጃፓን ሰዎች ለሰብዓዊ ጌቶቻቸውና ለንጉሠ ነገሥቱ ስላላቸው ታማኝነት አሰላሰልኩ። ብዙ ጃፓናውያን ለእነዚህ ለሰብዓዊ ገዢዎች ሲሉ ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የካሚካዝ አውሮፕላን አብራሪዎች ለንጉሠ ነገሥቱ ሲሉ አውሮፕላኖቻቸውን በጠላት የጦር መርከቦች ጭስ ማውጫ ላይ አነጣጥረው በማጋጨት ራሳቸውን ገድለዋል። የጃፓን ሕዝቦች ለሰብዓዊ ጌቶቻቸው በጣም ታማኞች ከሆኑ እውነተኛውን ጌታ ይሖዋን ቢያገኙማ ምን ያደርጉ ይሆን? ብዬ ማሰቤም ትዝ ይለኛል።
ጃፓን ስንደርስ በመላው አገሪቷ ላይ የነበሩት ሰባት ሚስዮናዊያንና እፍኝ የማይሞሉ አስፋፊዎች ብቻ ነበሩ። ሁላችንም ሥራችንን ጀመርን። እኔም የቋንቋ እውቀቴን ለማሻሻል ጣርኩና አምላክን በልባቸው ይጠሩ ለነበሩ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ቻልኩ። ከነዚያ የመጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ውስጥ በርከት ያሉት እስከዚች ቀን ድረስ በታማኝነታቸው ቀጥለዋል።
ልጆቻችንን ይዘን በሚስዮናዊነት ማገልገል
የምናሳድጋቸውን ሦስት ትንንሽ ልጆች ይዘን የሚስዮናዊነት አገልግሎትን እንዴት ልናከናውን ቻልን? ከዚህ ሁሉ በስተኋላ የነበረው ኃይል ይሖዋ ነበር። ለወጪአችን መተኪያ የሚሆን አነስተኛ ገንዘብ ከማኅበሩ እናገኝ ነበር። ማሳኮ ደግሞ ለልጆቹ ልብስ ትሠራላቸው ነበር። በተጨማሪም ከወላጆቼ ጥቂት እርዳታ እናገኝ ነበር።
ሎይ ከመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተመረቀ በኋላ በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የጃፓን ቅርንጫፍ ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ሠራ። ይሁን እንጂ በጤንነቱ ምክንያት ሕክምና ለማግኘት ወደ ሃዋይ ለመሄድ ወሰነ። አሁን እሱና ሚስቱ ካሊፎርኒያ ውስጥ ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉት ይገኛሉ። የሎይ ጋብቻ አራት ታማኝ የልጅ ልጆች በማግኘት የመባረክን ውጤት አስገኝቶልናል። ሁሉም የተጠመቁ ናቸው። አንዱ ደግሞ ከሚስቱ ጋር በይሖዋ ምስክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በብሩክሊን ቤቴል እያገለገለ ይገኛል።
ሴቶች ልጆቼ ቴልማና ሳሊ ሲያድጉ እንደ ሚስዮናዊ ለመቆጠር ቻሉ። በአሁኑ ጊዜ ቴልማ በቶያማ ከተማ ሚስዮናዊ ሆና እያገለገለች ነው። ሳሊ ደግሞ ሮን ትሮስት የሚባል ሚስዮናዊ ወንድም አገባችና በጃፓን ውስጥ ሚስዮናዊ ሆነው በተጓዥነት ሥራ ለ25 ዓመታት አገልግለዋል።
ከሰሜን ወደ ደቡብ
በቶኪዮ ሁለት ዓመት ካሳለፍን በኋላ ለሁለት ዓመት ወደ ኦሳካ ተላክን። የሚቀጥለው ምድባችን ለስድስት ዓመታት ያህል ወዳገለገልንበት ወደ ሴንዳይ ወሰደን። እነዚያ በሴንዳይ የቆየንባቸው ዓመታት በጃፓን ሰሜናዊ ጫፍ ላይ በምትገኘው ሆካይዶ በምትባለው ደሴት ላይ ለተሰጠን ምድባችን አእምሮአችንን አዘጋጅተውልናል። ሴት ልጆቻችን የሚስዮናዊነት ደረጃ የተሰጣቸው በሆካይዶ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ከዜሮ በታች ይሆን ከነበረው የበረዶ ወራት የአየር ሁኔታ ጋር የተለማመድነውም እዚሁ ነበር። በሐሩር ክልል ውስጥ በምትገኘው ሃዋይ ውስጥ ከኖሩ በኋላ እዚህ መምጣት ትልቅ ለውጥ ነበር!
ከዚያ በኋላ አንድ ቀን በደብዳቤ መልክ ከማኅበር የመጣ አዲስ ጥሪ በጆሮዬ ውስጥ አቃጨለ። ይህም በዩናይትድ ስቴትስ ቁጥጥር ሥር በምትገኘው በኦኪናዋ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ እንድንከፍት የሚጠይቅ ነበር። ቀዝቃዛ ከሆነው የጃፓን ሰሜናዊ ጫፍ አሁን በተወካይ ወደምትተዳደረው የጃፓን ደቡባዊ ጫፍ ወደሆነችው ቦታ መዛወር በጣም ፈታኝ ሁኔታ ነበር። ምን ላድርግ? ምንም እንኳን ብቃት እንደሌለኝ ቢሰማኝም እንደ ወትሮው ከታማኟ ሚስቴ ጋር በመሆን ኅዳር 1965 ኦኪናዋ ደረስኩ። በኦኪናዋ ያለው ኑሮ በጃፓን ካለው ኑሮ ጋር ተመሳሳይ ይሆን? ባሕሉስ? ሕዝቡስ ለይሖዋ የመዳን መልእክት አዎንታዊ ምላሽ ይሰጥ ይሆንን?
በደረስን ጊዜ በኦኪናዋ ከ200 ያነሱ አስፋፊዎች ነበሩ። አሁን ከ2,000 በላይ የሚሆኑ ይገኛሉ። ቀደም ባሉት ጊዜያት የግማሽ ጊዜ የክልል የበላይ ተመልካችና የቅርንጫፍ የበላይ ተመልካች ነበርኩ። በደሴቲቱ ሁሉ በመጓዜ እዚያ ካሉት ወንድሞች ጋር የቅርብ ወዳጅነት እንድመሠርት ረድቶኛል። እነሱን ማገልገሌንም እንደ መብት አድርጌ እቆጥረዋለሁ።
ከችግር ነፃ ነበርን?
የሚስዮናዊነት ሥራችን በምንም መንገድ ከችግሮች ነፃ የሆነ አልነበረም። በ1968 የእረፍት ጊዜያችንን በዩናይትድ ስቴትስ እያሳለፍን እንዳለን ማሳኮ ታመመችና ቀዶ ጥገና መደረግ አስፈለጋት። በአንጀቷ ውስጥ የነበረው እባጭ ወጣላትና አስደናቂ መሻሻል አደረገች። የሕክምና መድኅን አልነበረንምና ምናልባት ወደ ምድብ ቦታችን አንመለስ ይሆናል ብለን ሠጋን። ይሁን እንጂ በሚያስገርም ሁኔታ የእምነት ወዳጆቻችን ሁሉንም ነገር ጨረሱልን።
በእኔ በኩል ደግሞ የስኳር በሽተኞች የሚደርሱባቸውን የተለመዱ ችግሮች ይዤ እኖራለሁ። እውር ባልሆንም እንኳን የማየት ችሎታዬ በኃይል ቀንሷል። ይሁን እንጂ በይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት የመጠበቂያ ግንብና ንቁ! መጽሔቶችን የቴፕ ቅጂ በማዳመጥ መንፈሳዊ ምግብ አዘውትሬ ለመመገብ ችያለሁ። የእምነት ወንድሞቼና እህቶቼም የተለያዩ ጽሑፎችን በማንበብ ይረዱኛል።
የማየት ችሎታዬ ቀንሶ እያለ የሕዝብ ንግግር መስጠቴን ልቀጥል የምችለው እንዴት ይሆን? በመጀመሪያ ላይ ንግግሮቼን በቴፕ ቀድቼ በድምፅ ማጉያ መሣሪያ በኩል እየተሰሙ እኔ እንቅስቃሴ ብቻ አደርግ ነበር። ይሁን እንጂ ሴት ልጄ ባቀረበችው ሀሳብ መሠረት በዚህ ላይ መሻሻል አደረግሁ። አሁን ንግግሮቼን በትንሽ ቴፕ እቀዳቸውና አስቀድሜ የቀዳኋቸውን ንግግሮች በጆሮ ማዳመጫ እየሰማሁኝ ንግግሮቼን አቀርባለሁ።
ከባድ ችግሮች በሚገጥሙን በማንኛውም ጊዜ ይሖዋን መጥራታችንን በፍጹም ትተን አናውቅም። በመጨረሻም ይሖዋ ችግሮቹን ሲፈታቸው የሚመጡልን በረከቶች ሁልጊዜ ከራሳቸው ከችግሮቹ የሚበልጡ መስለው ይታዩን ጀመር። ምስጋናችንን የምናሳይበት ብቸኛው መንገድ በአገልግሎቱ መቀጠል ነው።
በኦኪናዋ 23 ዓመታት ከቆየን በኋላ በመጀመሪያ ወደ ጃፓን መጥተን ስናገለግል ከነበረበት ቦታ ጋር ተመሳሳይ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ወዳለው ቦታ ተመደብን። የማኅበሩ ዋና ቢሮና ትልቁ የሚስዮናዊያን ቤት በቶኪዮ ውስጥ ከብዙ ዓመታት በፊት ወንድም ሃስሌት በመጀመሪያ በገዛው ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ ባለበት ቦታ ላይ ይገኛሉ።
ከማሳኮና ከእኔ ሌላ 11 ዘመዶቻችን በጃፓን ውስጥ ሚስዮናውያን ሆነው እያገለገሉ ናቸው። ሁሉም ሚስዮናውያን በአብዛኛው የቡዲሂስትና የሺንቶ ባሕል ባለባት በዚህች አገር ውስጥ ይሖዋ ያመጣውን ዕድገት ማየቱን እንደ ትልቅ መብት ይቆጥሩታል። በጃፓን ውስጥ የነበረው ሥራ አነስተኛ አጀማመር ነበረው፤ የይሖዋ ኃይል ግን ከ167,000 በላይ የሆኑ የምሥራቹ አስፋፊዎች ያሉት “ሕዝብ” አድርጎ አሳድጐታል።—ኢሳይያስ 60:22
አምላክን ስጠራው መለሰልኝ። እሱ ሲጋብዘኝ ደግሞ እኔ በእሽታ መለስኩለት። ሚስቴና እኔ የሚሰማን ልናደርገው የሚገባንን እንዳደረግን ብቻ ነው። እናንተስ? ፈጣሪያችሁ ሲጣራ ትመልሳላችሁን?
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1942 የቶሀር ቤተሰብ በሃዋይ ውስጥ ከነበረው የአቅኚ ቡድናቸው አንዳንድ አባላት ጋር
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1948 የቶሀር ልጆች በጊልያድ
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሺኒቺና ማሳኮ ቶሀር ለጥሪው ምላሽ ሰጥተው የሚስዮናዊ ሥራቸውን 43ኛ ዓመት ስላጠናቀቁ ደስተኞች ናቸው