አንዳንዶች እንደገና የሚወለዱት ለምንድን ነው?
“ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም።” (ዮሐንስ 3:3) እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ከ1,900 ዓመታት በፊት ከተናገራቸው ጀምሮ ብዙ ሰዎችን አስደስተዋል፣ ግራም አጋብተዋል።
ኢየሱስ ስለተናገረው እንደገና የመወለድ ጉዳይ ተገቢ ግንዛቤ ለማግኘት በመጀመሪያ፦ አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምንድን ነው? ሰው ሲሞት ነፍሱ ምን ትሆናለች? የአምላክ መንግሥት እንድትፈጽመው የተፈለገው ዓላማስ ምንድን ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመርመር አለብን።
አምላክ ለሰው ልጅ ያለው ዓላማ
የመጀመሪያው ሰው አዳም ፍጹም የሆነ ሰብአዊ የአምላክ ልጅ ሆኖ ተፈጥሮ ነበር። (ሉቃስ 3:38) ይሖዋ አዳም እንዲሞት ፈጽሞ አላሰበም ነበር። አዳምና ሚስቱ ሔዋን ለዘላለም የሚኖርና ገነቲቱን ምድር የሚሞላ ኃጢአት የለሽ ሰብአዊ ቤተሰብ የማስገኘት ተስፋ ነበራቸው። (ዘፍጥረት 1:28) አምላክ ለወንድና ለሴት ባወጣው የመጀመሪያ ዓላማ ውስጥ ሞት ቦታ አልነበረውም። ሞት የሰው ልጅን መድረክ የወረረው በመለኮታዊው ሕግ ላይ ዓመፅ በመሠራቱ ምክንያት ነበር።—ዘፍጥረት 2:15-17፤ 3:17-19
የተነሣው ዓመፅ የአምላክ ሉዓላዊነት ትክክለኛ ስለመሆኑና ሰዎች ለሕጎቹ ታማኞች ሆነው ለመኖር ያላቸውን ችሎታ የሚመለከቱ ከባድ የሥነ ምግባር አከራካሪ ጥያቄዎችን አስነስቷል። ለእነዚህ አከራካሪ ጥያቄዎች እልባት ለማስገኘት ጊዜ ያስፈልግ ነበር። ይሖዋ አምላክ ለምድር የነበረው ዓላማ ግን አልተለወጠም፤ ሊያደርገው የወሰነውን ነገር ደግሞ መፈጸም ሊያቅተው አይችልም። ምድርን በገነት ውስጥ ዘላለማዊ ሕይወት አግኝተው በሚደሰቱ ፍጹም ሰብአዊ ቤተሰብ ሊሞላት አስቧል። (መዝሙር 37:29፤ 104:5፤ ኢሳይያስ 45:18፤ ሉቃስ 23:43) ኢየሱስ እንደገና ስለመወለድ የተናገራቸውን ቃላት ስንመረምር ይህን መሠረታዊ እውነት ማስታወስ አለብን።
በሞት ጊዜ ነፍስ ምን ትሆናለች?
የግሪክ ፈላስፎች የአምላክ መንፈስ ቅዱስ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የገለጸላቸውን ባለማወቃቸው የሕይወትን ትርጉም ለማግኘት ተፍጨርጭረው ነበር። ሰው ለጥቂት ዓመታት ብቻ፣ ብዙውን ጊዜም በአሳዛኝ ሁኔታ ከኖረ በኋላ ሕልውናው ያከትማል ብለው ማመን አቅቷቸው ነበር። በዚህ ረገድ ትክክል ነበሩ። ሰው ከሞተ በኋላ ስላለው ተስፋ በሰጡት መደምደሚያ ረገድ ግን ተሳስተዋል። በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ የማትሞት ነፍስ ስላለች ከሞት በኋላ ሕልውናው በሆነ ዓይነት መንገድ ይቀጥላል ብለው ደመደሙ።
አይሁዳውያንና ክርስቲያን ነን ባዮች በዚህ አስተሳሰብ ተነክተዋል። የሰማይ ታሪክ የተሰኘው መጽሐፍ “ስደተኛ አይሁዶች ከግሪክ ምሁራን ጋር በተገናኙባቸው ቦታዎች ሁሉ የማትሞት ነፍስ አለች የሚለው ሐሳብ ብቅ ይል ነበር” ይላል። መጽሐፉ ጨምሮም “ስለ ነፍስ የሚናገረው የግሪክ መሠረተ ትምህርት በአይሁዳውያን እምነቶች በኋላም በክርስትና እምነቶች ላይ የማይፋቅ የአስተሳሰብ አሻራ ጥሏል። . . . ፊሎ [የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአሌክሳንድሪያው አይሁዳዊ ፈላስፋ] የፕላቶ ፍልስፍናና የመጽሐፍ ቅዱስ ባሕል ልዩ ውሕደት በመፍጠር በኋላ ዘመን የሚመጡ ክርስቲያን ተፈላሳፊዎች ለሚያድርባቸው አስተሳሰብ መንገድ ጠርጓል” ይላል።
ፊሎ ምን ብሎ ያምን ነበር? ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ በመቀጠል “ለእርሱ [ለፊሎ] ሞት ነፍስን ከመወለድ በፊት ወደነበረችበት የመጀመሪያው ሁኔታ የሚመልሳት ነበር። ነፍስ የመንፈሳዊው ዓለም ክፍል በመሆኗ በአካል ውስጥ ያለው ሕይወት ብዙውን ጊዜ አሳዛኝ የሆነ አጭር ምዕራፍ ብቻ ይሆናል” ይላል። ይሁን እንጂ አዳም “ከመወለዱ በፊት የነበረበት ሁኔታ” ጭራሽ አለመኖር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መሠረት ምድር ከፍተኛ ወይም ዝቅተኛ ወደሆነ ሕልውና መሸጋገሪያ መድረክ ብቻ የሆነች ይመስል አምላክ በሞት ጊዜ ወዲያውኑ ወደ ሌላ ዓለም መሸጋገር እንዲኖር ዓላማው አልነበረም።
የሰው ነፍስ የማትሞት ናት የሚለው እምነት በአምላክ መንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰጠ ትምህርት አይደለም። አንድ ጊዜም እንኳን “የማትሞት ነፍስ” የሚል አባባል አይጠቅስም። አዳም የተፈጠረው ከነፍስ ጋር ሳይሆን ነፍስ ሆኖ እንደሆነ ይናገራል። ዘፍጥረት 2:7 “እግዚአብሔር ይሖዋ አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ሠርቶ በአፍንጫው የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበትና ሰው ሕያው ነፍስ ሆነ” [አዓት] ይላል። የሰው ልጅ በሰማይ ዘላለማዊ ሕይወት የማግኘትም ሆነ በሲኦል እሳት የዘላለም ስቃይ የመቀበል አጋጣሚ በፊቱ አይጠብቀውም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ሟቹ ነፍስ ወይም ሰው እየሰማ የሚኖርበት ሁኔታ እንደሌለው ይገልጻል። (መዝሙር 146:3, 4 የ1980 ትርጉም፤ መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4) በዚህ ምክንያት ፈላስፋዎች ስለ ነፍስ የያዙት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አመለካከት ነበር። ኢየሱስ እንደገና ስለመወለድ የተናገራቸውን ቃላት እንዳንረዳ ከሚጋርዱብን አሳሳች ሐሳቦች መጠንቀቅ ያስፈልገናል።
ነገሥታት ሆኖ ለመግዛት እንደገና መወለድ
እንደገና የሚወለዱ ሰዎች ‘ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባሉ’ ሲል ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ ነግሮታል። (ዮሐንስ 3:3-5) ይህች መንግሥት ምንድን ናት? በምሳሌያዊ አነጋገር ገና በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ ይሖዋ አምላክ የቀደመውን እባብ የሰይጣን ዲያብሎስን ራስ ለመቀጥቀጥ በአንድ ልዩ “ዘር” ማለትም ለወደፊት በሚመጣ ገዢ እንደሚጠቀም ያለውን ዓላማ አስታውቋል። (ዘፍጥረት 3:15፤ ራእይ 12:9) በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ በየጊዜው ደረጃ በደረጃ እንደተገለጸው ይህ “ዘር” የአምላክ ሉዓላዊነት ልዩ መግለጫ በሆነች መሲሐዊት መንግሥት ውስጥ ከሌሎች ጋር አብሮ የሚገዛው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ተለይቶ ተገልጿል። (መዝሙር 2:8, 9፤ ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14) እርሷም የሰማይ መንግሥት ስትሆን፣ የይሖዋን ሉዓላዊነት የምታረጋግጥና የሰው ልጆችን የኃጢአትና የሞት ግዞተኞች ከመሆን የምታድን የሰማይ መስተዳድር ናት።—ማቴዎስ 6:9, 10
ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙት ከሰው ልጆች መካከል የተዋጁ 144,000 ናቸው። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1-4) አምላክ ፍጹም ካልሆኑት የአዳም ቤተሰቦች ውስጥ ከክርስቶስ ጋር በመሢሐዊ መንግሥቱ አብረው የሚገዙ “የልዑሉ ቅዱሳን” እንዲሆኑ ጥቂት ሰዎችን መርጧል። (ዳንኤል 7:27፤ 1 ቆሮንቶስ 6:2፤ ራእይ 3:21፤ 20:6) እነዚህ ወንዶችና ሴቶች “እንደገና ይወለዳሉ” ብሎ በተናገረው በኢየሱስ ክርስቶስ አምነዋል። (ዮሐንስ 3:5-7) ይህ ልደት የሚፈጸመው እንዴትና ለምንድን ነው?
እነዚህ ግለሰቦች የክርስቶስ ተከታዮች በመሆን በውኃ ተጠምቀዋል። አምላክ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕትነት መሠረት ኃጢአታቸውን ይቅር ብሎላቸዋል፣ ጻድቃን እንደሆኑ አስታውቋል፣ እንደ መንፈሳዊ ልጆቹ አድርጎ ተቀብሏቸዋል። (ሮሜ 3:23-26፤ 5:12-21፤ ቆላስይስ 1:13, 14) እንዲህ ላሉት ግለሰቦች ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ይላቸዋል፦ “‘አባባ’ ብላችሁ የምትጠሩበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ በፍርሃት ለመኖር የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁም። የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኛ መንፈስ ጋር ሆኖ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ይመሰክራል። እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን የእርሱ ወራሾች ነን፤ ከክርስቶስም ጋር እንወርሳለን፤ አሁን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች ብንሆን በኋላ የክብሩ ተካፋዮች እንሆናለን።”—ሮሜ 8:15-17 የ1980 ትርጉም
እነዚህ ሰዎች የክርስቶስ ተከታዮች በመሆናቸው በሕይወታቸው አዲስ ልደት ወይም አዲስ ጅምር ያገኙ ናቸው። ይህም በክርስቶስ ሰማያዊ ውርሻ እንደሚካፈሉ እርግጠኛ እምነት እንዲኖራቸው አድርጓል። (ሉቃስ 12:32፤ 22:28-30፤ 1 ጴጥሮስ 1:23) ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን እንደገና መወለድ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፣ እድፈትም ለሌለበት፣ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት [ወለደን።] . . . ይህም ርስት . . . ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል” በማለት ይገልጸዋል። (1 ጴጥሮስ 1:3, 4) እነዚህ ግለሰቦች ይህን አዲስ ሕይወት በሰማይ ሊያገኙ የሚችሉት አምላክ ኢየሱስን ከሙታን እንዳስነሣው እነርሱንም ስለሚያስነሣቸው ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:42-49
ምድርስ ምን ትሆናለች?
ይህ ማለት ግን ሁሉም ታዛዥ ሰዎች ከምድር ወደ ሰማይ ለመሄድ በመጨረሻው እንደገና ይወለዳሉ ማለት አይደለም። እንዲህ ዓይነት የተሳሳቱ አስተሳሰቦች “በሰውነት ውስጥ ያለው ሕይወት አጭርና ብዙውን ጊዜም አሳዛኝ ምዕራፍ ብቻ [ነው]” ብሎ እንዳስተማረው እንደ ፊሎ ያሉ ፈላስፎች ከያዙት አስተሳሰብ ጋር ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን በይሖዋ አምላክ የመጀመሪያ ምድራዊ ፍጥረት ላይ ምንም ስህተት አልነበረም።—ዘፍጥረት 1:31፤ ዘዳግም 32:4
የሰው ሕይወት አጭርና አሳዛኝ እንዲሆን ፈጽሞ አልታሰበም ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስና በሰማይ ነገሥታትና ካህናት በመሆን ለማገልገል እንደገና የሚወለዱት ሰዎች የሰይጣን ዓመፅ ያስከተላቸውን ጎጂ ውጤቶች በሙሉ ያስወግዳሉ። (ኤፌሶን 1:8-10) ‘የአብርሃም የተስፋው ዘር’ ስለሆኑ በእነርሱ “የምድር ነገዶች ሁሉ ራሳቸውን ይባርካሉ።” (ገላትያ 3:29፤ ዘፍጥረት 22:18 አዓት) ይህም ለታዛዦቹ የሰው ልጆች በገነታዊ ምድር ላይ በዛሬው ጊዜ ካለው አጭርና በመከራ የተሞላ ሕይወት በጣም የተለየ ሕይወት የሚያስገኝ ነው።—መዝሙር 37:11, 29፤ ራእይ 21:1-4
እነማን ይጠቀማሉ?
አምላክ የሰው ልጆችን ለመባረክ ካለው ዝግጅት ተጠቃሚዎች ከሚሆኑት መካከል በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት የሚያሳዩ ትንሣኤ የሚያገኙ ሙታን ይገኙበታል። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15) ከእነርሱም አብዛኞቹ ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በጭራሽ ሰምተው የማያውቁ ስለሆኑ በኢየሱስ ማመናቸውን ሊያሳዩ ያልቻሉ ነበሩ። ከእነዚህ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች መካከል የኢየሱስ ሞት ለሰማያዊ ሕይወት በሩን ከመክፈቱ በፊት እንደሞተው እንደ ዮሐንስ መጥምቁ ያሉ ታማኝ ሰዎች ይገኙበታል። (ማቴዎስ 11:11) ከእነዚህም ሌላ ‘ከሁሉም አሕዛብ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ልብሳቸውን በበጉ [በኢየሱስ ክርስቶስ] ደም አጥበው አንጽተዋል።’ በአሁኑ ጊዜ እንደገና የተወለዱት የክርስቶስ “ወንድሞች” በግንባር ቀደምትነት ለሚመሩት የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ተስማሚ ምላሽ ይሰጣሉ፤ በጸዳች ምድር ላይ ለመኖር በአርማጌዶን ከሚሆነው የአምላክ ጦርነት በሕይወት ይተርፋሉ። (ራእይ 7:9-14 ፤ 16:14-16፤ ማቴዎስ 24:14፤ 25:31-46) ስለዚህ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምንም እንኳን በሰማያት ከክርስቶስ ጋር ለመግዛት እንደገና ባይወለዱም መዳን ያገኛሉ።—1 ዮሐንስ 2:1, 2
በምድራዊ ገነት ውስጥ ሕይወትን ከሚወርሱት መካከል ትገኝ ይሆን? በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት ላይ እምነት ካደረግህና ከእውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ ጋር በመተማመን የነቃ ተሳትፎ ካደረግህ ከተባበርህ ልትገኝ ትችላለህ። ጉባኤው በፈላስፎች አስተሳሰብ የተበከለ ሳይሆን “የእውነት አምድና ምሰሶ” ሆኖ ጸንቶ የቆየ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:15፤ ከዮሐንስ 4:24፤ 8:31, 32 ጋር አወዳድር።) ከዚያ በኋላ እንደገና የተወለዱ የአምላክ ልጆች በሰማይ የሚገዙበትንና የአምላክ ምድራዊ ፍጥረታት በሙሉ ባማረች ምድራዊ ገነት ላይ ወደ ፍጽምና የሚመለሱበትን አስደናቂ ጊዜ በተስፋ ልትጠባበቅ ትችላለህ። ስለዚህ ዘላለማዊ በረከት በሚኖርበት በዚያ አዲስ ዓለም የመኖር አጋጣሚ አያምልጥህ።—ሮሜ 8:19-21፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዳም በሰማይ ለዘላለም የመኖር ወይም በእሳታማ ሲኦል ለዘላለም የመሠቃየት አማራጮች ፈጽሞ አልቀረበለትም ነበር