“እንደ አምላካችን እንደ ይሖዋ ያለ ማን ነው?”
‘በላይ እንደሚኖረው እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ማን ነው?’—መዝሙር 113:5
1, 2. (ሀ) የይሖዋ ምስክሮች ለአምላክና ለመጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ያለ አመለካከት አላቸው? (ለ) ሊመረመሩ የሚገባቸው ምን ጥያቄዎች አሉ?
ለይሖዋ ውዳሴ የሚሰጡ በእውነትም የተባረኩ ናቸው። በእነዚህ ደስተኛ ሕዝቦች መካከል መገኘት ምንኛ የሚያስደስት መብት ነው! ምስክሮቹ እንደመሆናችን መጠን የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠንን ምክር፣ ሕጎች፣ ትምህርቶች፣ ተስፋዎችና ትንቢቶች እንቀበላለን። ከቅዱሳን ጽሑፎች በመማራችንና ‘ከይሖዋ የተማርን’ በመሆናችን ደስተኞች ነን።—ዮሐንስ 6:45
2 የይሖዋ ምስክሮች ለአምላክ ባላቸው ጥልቅ አክብሮት ምክንያት “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ማን ነው?” ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ። (መዝሙር 113:5) እነዚህ የመዝሙራዊው ቃላት እምነት ያለን መሆኑን ያመለክታሉ። ነገር ግን ምስክሮቹ እንዲህ ዓይነት እምነት ያላቸው ለምንድን ነው? ይሖዋን ለማወደስስ ምን ምክንያት አላቸው?
እምነትና ውዳሴ ተገቢ ናቸው
3. የሀሌል (የውዳሴ) መዝሙሮች ምንድን ናቸው? እንዲህ ተብለው የተጠሩትስ ለምንድን ነው?
3 በይሖዋ ማመን ተገቢ ነው፣ ምክንያቱም እርሱ ልዩ አምላክ ነው። ይህም የስድስቱ የውዳሴ መዝሙሮች ክፍል በሆኑት በመዝሙር 113, 114, እና 115 ላይ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። የሂለል ራቢናዊ [የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች] ትምህርት ቤት እንደሚለው መዝሙር 113 እና 114 ይዘመሩ የነበሩት በአይሁዳውያን የማለፍ በዓል ጊዜ ከምግብ በኋላ ሁለተኛው የወይን ጽዋ ከተቀዳና የበዓሉ ትርጉም ከተብራራ በኋላ ነበር። ከመዝሙር 115 እስከ 118 ያሉት የሚዘመሩት ከአራተኛው የወይን ጽዋ በኋላ ነበር። (ከማቴዎስ 26:30 ጋር አወዳድር።) እነዚህ መዝሙሮች ትርጉሙ “ያህን አመስግኑ” ማለት የሆነውን ሃሌ ሉያ የሚል ቃል በተደጋጋሚ ስለሚጠቀሙ “የሀሌል (የውዳሴ) መዝሙር” ተብለው ይጠራሉ።
4. “ሃሌ ሉያ” የሚለው ቃል ትርጉሙ ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥስ ምን ያህል ጊዜ ይገኛል?
4 “ሃሌ ሉያ!” የሚለው ቃል በመዝሙራት ውስጥ 24 ጊዜ ተጠቅሶ ከሚገኘው የዕብራይስጥ ቃል በቀጥታ የተወሰደ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌሎች ስፍራዎች ይህ ቃል በግሪክኛ አጻጻፉ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን ከመውደቋና ይሖዋ አምላክ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ የተገኘውን ደስታ ለመግለጽ አራት ጊዜ ተጽፎ ይገኛል። (ራእይ 19:1-6) አሁን ሦስቱን የሀሌል (የውዳሴ) መዝሙሮች ስንመረምር እነዚህን መዝሙሮች ራሳችን ለይሖዋ ምስጋና ወይም ውዳሴ እየዘመርን እንዳለን አድርገን ልናስብ እንችላለን።
ያህን አመስግኑ!
5. መዝሙር 113 ለየትኛው ጥያቄ መልስ ይሰጣል? የመዝሙር 113:1, 2 ትዕዛዝ በተለይ የሚሠራው በእነማን ላይ ነው?
5 መዝሙር 113 ይሖዋን የምናመሰግነው ለምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል። መዝሙሩን የሚከፍተውም “እናንተ ሕዝቦች፣ ይሖዋን አመስግኑት! እናንተ የይሖዋ ባሪያዎች፣ ምስጋና አቅርቡ፣ የይሖዋን ስም አመስግኑ። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ የይሖዋ ስም ቡሩክ ይሁን” በሚለው ትዕዛዝ ነው። (መዝሙር 113:1, 2 አዓት) “ሃሌ ሉያ!” አዎን፣ “ያህን አመስግኑ!” ይህ ትዕዛዝ በተለይ በዚህ “የፍጻሜ ዘመን” በሚኖሩት የአምላክ ሕዝቦች ላይ ይሠራል። (ዳንኤል 12:4) ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም የይሖዋ ስም በምድር ዙሪያ ከፍ ከፍ መደረግ ይኖርበታል። በአሁኑ ጊዜ ምስክሮቹ ይሖዋ አምላክ መሆኑን፣ ክርስቶስ ንጉሥ መሆኑንና መንግሥቱም በሰማይ እንደ ተቋቋመች እያወጁ ነው። ሰይጣን ዲያብሎስና ድርጅቱ ይህንን የይሖዋን መወደስ ሊያግዱ አይችሉም።
6. ይሖዋ ‘ከፀሐይ መውጫ እስከ መግቢያው ድረስ’ የተመሰገነው እንዴት ነው?
6 የውዳሴ መዝሙሩ ይሖዋ ምድርን በምስጋና መዝሙር እንድትሞላ እስኪያደርግ ድረስ እየጨመረ ይሄዳል። “ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያው ድረስ የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] ስም ይመስገን።” (መዝሙር 113:3) ይህም አንዳንድ ምድራዊ ፍጥረታቱ በየቀኑ የሚያደርጉትን የአምልኮ ተግባር ብቻ የሚያመለክት አይደለም። ፀሐይ በምሥራቅ ወጥታ በምዕራብ ስለምትጠልቅ ምድርን በሙሉ ትሸፍናለች። ፀሐይ በምታበራበት ሥፍራ ሁሉ ከሐሰት ሃይማኖትና ከሰይጣን ድርጅት ግዞተኛነት ነፃ የወጡ ሕዝቦች በሙሉ በቅርቡ የይሖዋን ስም ያወድሳሉ። እንዲያውም ፍጻሜ የሌለው ይህ መዝሙር በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ ቅቡአን ምስክሮችና የንጉሡ የኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ ልጆች በሚሆኑት ሰዎች እየተዘመረ ነው። የይሖዋ ውዳሴ ዘማሪዎች በመሆናቸው ምንኛ ታድለዋል!
ይሖዋ ተወዳዳሪ የለውም
7. በመዝሙር 113:4 ላይ ምን ሁለት የይሖዋ የበላይነት ገጽታዎች ተገልጸዋል?
7 መዝሙራዊው “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በአሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍተኛ ነው፣ ክብሩም ከሰማያት በላይ ነው” ሲል ያክላል። (መዝሙር 113:4) ይህም የአምላክን የበላይነት ሁለት ገጽታዎች ያስታውሳል፦ (1) “ከሰማያት በላይ ከፍ ባለው” በልዑል ይሖዋ ዘንድ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታና በሚዛንም እንዳለ ትንሽ ትቢያ መሆናቸውን፣ (ኢሳይያስ 40:15፤ ዳንኤል 7:18) (2) መላእክትም እንኳን ሳይቀሩ ሉዓላዊ ፈቃዱን ስለሚፈጽሙ ክብሩ ከግዑዞቹ ሰማያት በላይ እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን።—መዝሙር 19:1, 2፤ 103:20, 21
8. ይሖዋ በሰማይና በምድር ላይ ያሉ ጉዳዮችን ለመመልከት ራሱን ዝቅ የሚያደርገው እንዴት ነው?
8 መዝሙራዊው በአምላክ ታላቅነት ተገፋፍቶ “መኖሪያውን በላይ እንደሚያደርገው እንደ አምላካችን እንደ ይሖዋ ያለ ማን ነው? ሰማይንና ምድርን ለመመልከት ራሱን ዝቅ ያደርጋል” ብሏል። (መዝሙር 113:5, 6) አምላክ በጣም ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሳ በሰማይና በምድር ላይ ያሉ ነገሮችን ለመመልከት ራሱን ዝቅ ማድረግ አለበት። ይሖዋ የማንም የበታች ወይም ደግሞ የሌሎች ተገዥ ባይሆንም ዝቅተኛ ለሆኑ ኃጢአተኞች ምሕረትና ርህራኄ ሲያሳያቸው ራሱን ዝቅ ያደርጋል። ይሖዋ ለቅቡዓን ክርስቲያኖችና ለሰው ልጆች ዓለም ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን “የማስተስሪያ መሥዋዕት” አድርጎ መስጠቱ የትሕትናው መግለጫ ነው።—1 ዮሐንስ 2:1, 2
ይሖዋ ርህሩኅ ነው
9, 10. አምላክ ‘የተዋረደውን ከፍ በማድረግ ከአለቆች ጋር የሚያስቀምጠው’ እንዴት ነው?
9 መዝሙራዊው የአምላክን ርህራኄ ጠበቅ አድርጎ በመግለጽ “ከአለቆች ጋር ከሕዝቡም አለቆች ጋር ያኖረው ዘንድ ችግረኛን ከመሬት የሚያነሳ፣ ምስኪኑንም ከፋንድያ ከፍ ከፍ የሚያደርግ፤ መካኒቱን በቤት የሚያኖራት፣ ደስ የተሰኘችም የልጆች እናት የሚያደርጋት። ሃሌ ሉያ” ይላል። (መዝሙር 113:7-9) ይሖዋ ቅን የሆኑትን ችግረኞች ሊያድን፣ ሁኔታቸውን ሊለውጠውና፣ ተገቢ ፍላጎቶቻቸውንና ምኞቶቻቸውን በመፈጸም ሊያረካቸው እንደሚችል የይሖዋ ሕዝቦች ያምናሉ። ‘ልዑሉና ከፍ ያለው አምላክ የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስና የተደቆሱትን ሰዎች ልብ እንደገና ሕያው ያደርጋል።’—ኢሳይያስ 57:15
10 ይሖዋ ‘የተዋረደውን ከፍ በማድረግ ከአለቆች ጋር የሚያስቀምጠው’ እንዴት ነው? አምላክ በሚፈቅድበት ጊዜ አገልጋዮቹን ከአለቆች ጋር በሚተካከል ቦታ ላይ ያስቀምጣቸዋል። የግብፅ የምግብ ጉዳይ አስተባባሪ ሆኖ በነበረው በዮሴፍ ረገድ እንዲህ አድርጓል። (ዘፍጥረት 41:37-49) በእሥራኤል አገር በአምላክ ሕዝቦች ውስጥ ከነበሩ አለቆች ወይም ባለ ሥልጣኖች ጋር መቀመጥ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው መብት ነበር። በዛሬው ጊዜ እንዳሉት ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሁሉ እነዚያ የእሥራኤል ሕዝብ አለቆችም የአምላክ እርዳታና በረከት ነበራቸው።
11. መዝሙር 113:7-9 በተለይ የሚሠራው ለዘመናችን የይሖዋ ሕዝቦች ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
11 ‘መካኒቱን ደስተኛ እናት’ የሚያደርጋትስ እንዴት ነው? አምላክ መካን ለነበረችው ለሐና ለእርሱ አገልግሎት የሰጠችውን ልጅ ሳሙኤልን ሰጥቷታል። (1 ሳሙኤል 1:20-28) ከሁሉ የበለጠ ደግሞ በኢየሱስና በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በደቀ መዛሙርቱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ካፈሰሰ ወዲህ ጀምሮ የአምላክ ምሳሌያዊት ሴት የሆነችው ሰማያዊት ጽዮን መንፈሳዊ ልጆችን መውለድ ጀመረች። (ኢሳይያስ 54:1-10, 13፤ ሥራ 2:1-4) አይሁድ በባቢሎን በግዞት ከቆዩ በኋላ አምላክ ወደ ትውልድ አገራቸው እንደመለሳቸው ሁሉ “የአምላክ እሥራኤል” የሆኑትን ቅቡአን ቀሪዎች በ1919 ከባቢሎን ምርኮኛነት ነፃ አወጣቸውና በመዝሙር 113:7-9 ያሉት ቃላት ይፈጸሙላቸው ዘንድ በመንፈሳዊ እጅግ አብዝቶ ባረካቸው። (ገላትያ 6:16) የመንፈሳዊ እሥራኤል ቀሪዎችና ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ጓደኞቻቸው ለይሖዋ በታማኝነት የሚቆሙ ምስክሮች በመሆን “እናንተ ሕዝቦች፣ ያህን አመስግኑ!” ለሚሉት የመዝሙር 113 ቃላት ከልብ የመነጨ ምላሽ እየሰጡ ነው።
የይሖዋ ወደርየለሽነት ማስረጃ
12. መዝሙር 114 ይሖዋን ልዩ አምላክ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው?
12 መዝሙር 114 እሥራኤላውያንን የሚመለከቱ ሁኔታዎችን በመጥቀስ የይሖዋን ወደርየለሽነት ያሳያል። መዝሙራዊው “እስራኤል ከግብጽ፣ የያዕቆብም ቤት ከእንግዳ [ቋንቋቸው ከማይገባ አዓት] ሕዝብ በወጣ ጊዜ፣ ይሁዳ መቅደሱ፣ እስራኤልም ግዛቱ ሆነ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 114:1, 2) አምላክ የእስራኤልን ሕዝብ ለጆሮአቸው እንግዳ የሆነ ቋንቋ ከነበራቸው ከግብፃውያን ባርነት ነፃ አውጥቶአቸዋል። በቅኔያዊ አነጋገር ይሁዳና እስራኤል እየተባሉ የሚጠሩት የይሖዋ ሕዝቦች ከመከራ መዳናቸው ዛሬም አምላክ አገልጋዮቹን ሁሉ ከመከራ እንደሚያድናቸው ያሳያል።
13. መዝሙር 114:3-6 የይሖዋን የበላይነት የሚያሳየውና በጥንቱ የእሥራኤል ሕዝብ ተሞክሮ ላይ የሚውለው እንዴት ነው?
13 ይሖዋ በፍጥረታቱ ሁሉ ላይ የሚኖረው ሉዓላዊነት ከሚከተሉት ቃላት በግልጽ ይታያል፦ “ባሕር አየች ሸሸችም፣ ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ። ተራሮች እንደ ኮርማዎች፣ ኮረብቶችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ። አንቺ ባሕር የሸሸሽ፣ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ፣ ምን ሆናችኋል? እናንተም ተራሮች፣ እንደ ኮርማዎች፣ ኮረብቶችስ እንደ ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ?” (መዝሙር 114:3-6) አምላክ ለሕዝቡ በቀይ ባሕር ላይ መንገድን በከፈተ ጊዜ ቀይ ባሕር “ሸሸ።” ውኃው ተከንብሎባቸው በሞቱት ግብፃውያን ላይ የእሥራኤል ሕዝብ የይሖዋን ታላቅ እጅ በተግባር አየ። (ዘጸአት 14:21-31) እሥራኤላውያን ወደ ከነዓን ምድር እንዲገቡ ለማድረግ ተመሳሳይ በሆነ የመለኮታዊ ኃይል መግለጫ የዮርዳኖስ ወንዝ “ቆመ” ወይም እንደ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም “ወደ ኋላው ተመለሰ።” (ኢያሱ 3:14-16) የሕጉ ቃል ኪዳን ሲቋቋም የሲና ተራራ በጨሰና በተናወጠ ጊዜ ‘ተራሮች እንደ ኮርማዎች ዘለሉ።’ (ዘጸአት 19:7-18) መዝሙራዊው መዝሙሩን ሊደመድም ሲል ነገሮችን በጥያቄ መልክ ያስቀመጣቸው ምናልባት ሕይወት የሌላቸው ባሕሩ፣ ወንዙ፣ ተራሮችና ኮረብቶች የይሖዋ ኃይል በተገለጠ ጊዜ በፍርሃት ተውጠውና ተደንቀው እንደነበረ ለመግለጽ ታስቦ ይሆናል።
14. በመሪባና በቃዴስ በይሖዋ ኃይል ምን ተፈጽሞአል? ይህስ ዘመናውያን አገልጋዮቹን እንዴት ሊነካቸው ይገባል?
14 መዝሙራዊው አሁንም ገና የይሖዋን ኃይል ሲጠቅስ “ምድር ሆይ፣ በጌታ ፊት፣ አለቱን ወደ ኩሬነት፣ ጭንጫውንም አለት ወደ ውኃ ምንጭ በሚለውጠው በያዕቆብ አምላክ ፊት ተናወጪ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 114:7, 8 አዓት) መዝሙራዊው በምሳሌያዊ መንገድ የሰው ልጅ የምድርን ሁሉ አጽናፈ ዓለማዊ ገዢ ማክበር እንዳለባት አመልክቷል። ይሖዋ የመንፈሳዊ እሥራኤላውያንና የምድራዊ ጓደኞቻቸው አምላክ እንደሆነ ሁሉ “የያዕቆብ [ወይም የእስራኤል አዓት] አምላክ” ነበር። እሥራኤላውያን በመሪባና በቃዴስ በረሃ ሳሉ ይሖዋ በተአምራዊ መንገድ “ድንጋዩን ወደ ኩሬነት፣ ጭንጫውንም አለት ወደ ውኃ ምንጭነት ለውጦ” ንጹሕ ውኃ በመስጠት ኃይሉን አሳይቷል። (ዘጸአት 17:1-7፤ ዘኁልቁ 20:1-11) እንዲህ ዓይነቶቹ የይሖዋን አስፈሪ ኃይልና የርህራኄ እንክብካቤ የሚያስታውሱ ታሪኮች ምስክሮቹ በእርሱ ላይ የማያጠያይቅ እምነት እንዲኖራቸው ጠንካራ ምክንያት ይሰጧቸዋል።
ከጣዖት አማልክት የተለየ ነው
15. መዝሙር 115 እንዴት ይዘመር ኖሮ ይሆናል?
15 መዝሙር 115 ይሖዋን እንድናወድስና እንድንተማመንበት አጥብቆ ይመክረናል። በረከትና እርዳታ የሚገኙት ከእርሱ መሆኑን በመግለጽ ጣዖቶች ዋጋ ቢስ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ይህ መዝሙር በመቀባበል ይዘመር ኖሮ ይሆናል፤ ማለትም አንዱ ድምፅ “ይሖዋን የምትፈሩ ሆይ፣ በይሖዋ ታመኑ” በማለት ይዘመር ይሆናል። ጉባኤው ደግሞ “ረድኤታቸውና መታመኛቸው እርሱ ነው” በማለት መልሰው ይሆናል።—መዝሙር 115:11 አዓት
16. በይሖዋና በአሕዛብ የጣዖት አማልክት መካከል ምን ልዩነት አለ?
16 ክብር መሰጠት የሚገባው ለእኛ ሳይሆን የፍቅራዊ ደግነት ወይም የታማኝ ፍቅርና የእውነተኛነት አምላክ ለሆነው ለይሖዋ ስም ነው። (መዝሙር 115:1) ጠላቶች በማሾፍ “አምላካቸው ወዴት ነው?” ብለው ይጠይቁ ይሆናል። የይሖዋ ሕዝቦች ግን “አምላካችንስ በላይ በሰማይ ነው፣ . . . የፈቀደውን ሁሉ አደረገ” ብለው ሊመልሱ ይችላሉ። (ቁጥር 2, 3) የአሕዛብ ጣዖታት ግን የብርና የወርቅ ሰው ሠራሽ ምስሎች ስለሆኑ ምንም ለመሥራት አይችሉም። አፍ፣ ዓይንና ጆሮ ቢኖራቸውም መናገር የማይችሉ፣ ዕውሮችና ደንቆሮች ናቸው። አፍንጫ አላቸው፤ ነገር ግን አያሸቱም። እግር አላቸው፣ መራመድ ግን አይችሉም። ጉሮሮም አላቸው፣ ነገር ግን አንድም ድምፅ ሊያወጡ አይችሉም። ለምንም የማይረቡ ጣዖቶችን የሚሠሩና የሚያምኑባቸው ሰዎች ልክ እንደ ጣዖቶቹ ሕይወት የለሽ ይሆናሉ።—ቁጥር 4-8
17. ሙታን ይሖዋን ሊያወድሱት ስለማይችሉ እኛ ምን ማድረግ አለብን? እንዲህ በማድረጋችንስ ምን ተስፋ ልናደርግ እንችላለን?
17 ቀጥሎ ይሖዋ ለእሥራኤል፣ ለአሮን ክህነታዊ ቤትና አምላክን ለሚፈሩ ሁሉ ረዳትና ተከላካይ ጋሻ መሆኑን በመገንዘብ በእርሱ እንዲተማመኑ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። (መዝሙር 115:9-11) ይሖዋን የምንፈራ በመሆናችን ለአምላክ ከፍተኛ አክብሮትና እርሱን ላለማስከፋት ጤናማ የሆነ ፍርሃት አለን። “የሰማይና የምድር ፈጣሪ” ታማኝ አምላኪዎቹን እንደሚባርክ እምነት አለን። (ቁጥር 12-15) ሰማያት የዙፋኑ ሥፍራዎች ናቸው፣ ምድርን የሠራት ግን የታማኝና ታዛዥ የሰው ልጆች ዘላለማዊ ቤት እንድትሆን ነው። ዝም ያሉትና ምንም ስሜት የሌላቸው ሙታን ይሖዋን ሊያወድሱት አይችሉም፤ እኛ ሕያዋን ግን ፈጽሞ ለእርሱ ያደርን በመሆንና በታማኝነት ልናወድሰው ይገባናል። (መክብብ 9:5) የዘላለም ሕይወት የሚያገኙትና “ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም” ስለ እርሱ ጥሩ በመናገር ለዘላለም “ያህን የሚባርኩት” ይሖዋን የሚያወድሱ ብቻ ናቸው። እንግዲያስ “እናንተ ሕዝቦች፣ ያህን አመስግኑ!” የሚለውን ማሳሰቢያ ከልብ ከሚቀበሉት ጋር በታማኝነት እንቁም።—መዝሙር 115:16-18
የይሖዋ ድንቅ ባሕርያት
18, 19. የይሖዋ ባሕርያት እርሱን ከሐሰት አማልክት ለይተው የሚያሳውቁት በምን በምን መንገዶች ነው?
18 ይሖዋ ሕይወት ከሌላቸው ጣዖታት በተለየ ሁኔታ ሕያው የሆነና አስደናቂ ባሕርያትን የሚያሳይ አምላክ ነው። የፍቅር አብነት የሆነና “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ለቁጣ የዘገየና ባለ ብዙ ፍቅራዊ ደግነት” ነው። (ዘጸአት 34:6 አዓት፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ይሖዋ የሕፃናት መሥዋዕት ከሚቀርብለት ከከነዓናውያን ጨካኝ አምላክ ከሞሎክ ምንኛ የተለየ ነው! የዚህ አምላክ [የሞሎክ] ምስል የሰው ቅርጽና የበሬ ጭንቅላት እንደነበረው ተገልጿል። ጣዖቱ በጣም እስኪግል ድረስ ከሥሩ እሳት ይነድና በተዘረጉት ክንዶቹ ላይ ሕፃናት እንዲያርፉ ሲደረጉ ከሥሩ ወዳለው የሚንበለበል ምድጃ ይወድቁ እንደነበር ተነግሯል። ይሖዋ ግን በጣም አፍቃሪና መሐሪ ከመሆኑ የተነሣ እንዲህ ዓይነቱ ሰውን መሥዋዕት አድርጎ የመቀበል ሐሳብ ‘ወደ ልቡም አልገባም።’—ኤርምያስ 7:31
19 የይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት ፍጹም ፍትሕን፣ ወሰን የሌለው ጥበብንና ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ኃይሉንም ይጨምራሉ። (ዘዳግም 32:4፤ ኢዮብ 12:13፤ ኢሳይያስ 40:26) በአፈ ታሪክ የሚነገርላቸው አማልክትስ? ፍትሕ በማድረግ ፈንታ የባቢሎናውያን ተባእትና እንስት አማልክት ቂመኞች ነበሩ። የግብፅ አማልክት የጥበብ አብነቶች ሳይሆኑ ሰብአዊ ድክመቶች ያሏቸው ሆነው ይገለጹ ነበር። ይህም የሚያስደንቅ አይደለም፤ ምክንያቱም ተባዕትና እንስት እንደሆኑ ይታመንባቸው የነበሩ የሐሰት አማልክት ጥበበኞች ነን ይሉ የነበሩ “ደንቆሮ” ሰዎች የሥራ ውጤት ናቸው። (ሮሜ 1:21-23) የግሪካውያን አማልክት እርስ በርሳቸው የሚመቀኛኙ እንደነበሩ ይታመን ነበር። ለምሳሌ ያህል በተረቶቻቸው ውስጥ ዚየስ ክሮኖስ የተባለውን አባቱን ከዙፋን በማውረድ ሥልጣኑን ያለ አግባብ ተጠቅሞበታል፤ ክሮኖስም ኡራነስ የተባለ አባቱን ከዙፋን አውርዷል ተብሎ ይታመን ነበር። ታዲያ ፍጹም ፍቅር፣ ፍትሕ፣ ጥበብና ኃይል ያለውን ሕያውና እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ማገልገልና ማወደስ ምንኛ በረከት ነው!
ይሖዋ ዘላለማዊ ውዳሴ ይገባዋል
20. ንጉሥ ዳዊት የይሖዋን ስም እንዲያወድስ ያደረጉት ምን ምክንያቶች ናቸው?
20 የሀሌል መዝሙሮች እንደሚገልጹት ይሖዋ ዘላለማዊ ውዳሴ ይገባዋል። በተመሳሳይም ዳዊትና እንደ እርሱ እሥራኤላውያን የሆኑ ሰዎች ለቤተ መቅደሱ ግንባታ መዋጮ ባደረጉ ጊዜ ዳዊት በጉባኤው ፊት እንደሚከተለው ብሏል፦ “አቤቱ፣ የአባታችን የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ተባረክ። አቤቱ፣ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፣ ክብርም፣ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፣ መንግሥት የአንተ ነው፣ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ። ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፣ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፣ ታላቅ ለማድረግ፣ ለሁሉም ኃይልን ለመስጠት በእጅህ ነው። አሁንም እንግዲህ አምላካችን ሆይ፣ እንገዛልሃለን፣ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን።”—1 ዜና መዋዕል 29:10-13
21. ይሖዋ በሰማያዊ ጭፍራዎች እየተመሰገነ ያለ ለመሆኑ ራእይ 19:1-6 ምን ማስረጃ ይሰጣል?
21 ይሖዋ በሰማይም ለዘላለም የተባረከና የተመሰገነ ይሆናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ብዙ ሕዝብ” እንደሚከተለው ብለው ይሖዋን ሲያወድሱት ሰምቷል፦ “ሃሌ ሉያ [እናንተ ሕዝቦች፣ ያህን አመስግኑት!] በዝሙትዋ ምድርን ያጠፋችይቱን ታላቂቱን ጋለሞታ [ታላቂቱን ባቢሎን] ስለ ፈረደባት፣ የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለ ተበቀለ፣ ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና ማዳንና ክብር ኃይልም የአምላካችን ነው።” ደግመውም፦ “ሃሌ ሉያ! አሉ።” “ሃያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶችም” እንዲሁ አድርገዋል። ከዙፋኑም “ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆች ሆይ፣ አምላካችንን አመስግኑ” የሚል ድምፅ ተሰምቷል። ከዚያም ዮሐንስ በመጨመር “እንደ ብዙ ሕዝብም ድምፅ ያለ ድምፅ፣ እንደ ብዙ ውኃዎችም ድምፅ እንደ ብርቱም ነጎድጓድም ድምፅ ያለ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ ሃሌ ሉያ! ሁሉን የሚገዛ [ሁሉን ቻይ አዓት] ጌታ አምላካችን [ይሖዋ አዓት] ነግሦአልና” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 19:1-6
22. ይሖዋ በአዲስ ሥርዓቱ የሚወደሰው እንዴት ይሆናል?
22 ሰማያዊ ጭፍራዎች ይሖዋን ማወደሳቸው ምንኛ የተገባ ነው! በቅርብ በሚመጣው የይሖዋ አዲስ ሥርዓት ትንሣኤ የሚያገኙ ታማኝ ሰዎች ያህን በማወደስ ከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት ከሚተርፉት ጋር ይተባበራሉ። ረዣዥም ተራራዎች የውዳሴ መዝሙሮችን ለአምላክ ለማሰማት ራሳቸውን ቀና ያደርጋሉ። የለመለሙ ኮረብታዎችና ፍሬያማ ዛፎች ምስጋናውን ይዘምራሉ። አዎን፣ ሕይወት ያለውና የሚተነፍስ ማንኛውም ፍጥረት ወደ ፊት ታላቅ የሃሌ ሉያ መዝሙር በኅብረት ሲዘመር አብሮ የይሖዋን ስም ያወድሳል። (መዝሙር 148) በዚያ ደስተኛ ሠራዊት መካከል ድምፅህ ይሰማ ይሆን? ከሕዝቡ ጋር ሆነህ ለያህ በታማኝነት እየቆምክ ካገለገልከው ያንተም ድምፅ በእነዚያ ደስተኛ ሠራዊት መካከል ይሰማል። በሕይወትህ ውስጥ ዓላማህ ይህ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም እንደ አምላካችን እንደ ይሖዋ ያለ ማን ነው?
እንዴት ብላችሁ ትመልሳላችሁ?
◻ ይሖዋ አምላክን ማወደስ ያለብን ለምንድን ነው?
◻ ይሖዋ ተወዳዳሪ የሌለው በምን መንገዶች ነው?
◻ ይሖዋ ርህሩኅ ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለ?
◻ ይሖዋ ሕይወት ከሌላቸው ጣዖታትና የሐሰት አማልክት የሚለየው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ በሰማይና በምድር ውዳሴ ይሰጠዋል ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሀሌል መዝሙሮች በማለፍ በዓል ላይ ይዘመሩ ነበር