የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 12/1 ገጽ 7-12
  • የይሖዋ በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋ በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከሁሉ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ብልጽግና
  • በአሁኑ ጊዜ የሚገኝ መንፈሳዊ ሀብት
  • አሥራቶችና ቁርባኖች
  • “ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ”
  • ይሖዋን መስረቅ
  • “በእውነተኛው ጌታ” መፈረድ
  • “አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • የሚልክያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • ከይሖዋ ቀን በሕይወት የሚተርፈው ማን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • ይሖዋ የክህደትን ጎዳና ይጠላል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 12/1 ገጽ 7-12

የይሖዋ በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች

“የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፣ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም።”—ምሳሌ 10:22

1-3. ብዙዎች ስለ ቁሳዊ ነገሮች የሚጨነቁ ቢሆንም ሁሉም ስለ ቁሳዊ ሀብት መገንዘብ የሚኖርባቸው ምንድን ነው?

አንዳንድ ሰዎች ስለ ገንዘብ ወይም ገንዘብ ስለማጣታቸው አውርተው አይጠግቡም። በቅርብ ዓመታት ገንዘብን በተመለከተ ብዙ መወያያ አግኝተዋል። በ1992 የበለጸገው የምዕራቡ ዓለምም እንኳን የኢኮኖሚ ድቀት አጋጥሞት ስለነበር አስተዳዳሪዎችም ሆነ ተራ ሠራተኞች ከሥራ ተባረዋል። ብዙዎቹም እንደገና አስተማማኝ የሆነ ብልጽግና ለማየት የመቻላቸው ጉዳይ አሳስቦአቸው ነበር።

2 ስለ ቁሳዊ ደኅንነታችን ማሰብ ስህተት ነው እንዴ? አይደለም፣ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ በገንዘብ ረገድ ስላለን ሁኔታ ማሰብ ያለ ነገር ነው። በዚያውም ስለ ሀብት ማወቅ ያለብን አንድ መሠረታዊ እውነት አለ። በመጨረሻው መገንዘብ ያለብን ሁሉም ቁሳዊ ሀብት የሚመጣው ከፈጣሪ መሆኑን ነው። እርሱ “ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፣ በእርሷ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፣ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት]” ነው።—ኢሳይያስ 42:5

3 ምንም እንኳን ይሖዋ ሀብታምና ድሃ መሆን ያለበትን ሰው አስቀድሞ ባይወስንም ‘በምድርና በውስጥዋ ካለው’ የምናገኘውን ድርሻ ስለምንጠቀምበት መንገድ ሁላችንም በእርሱ ተጠያቂዎች ነን። ሀብታችንን በሌሎች ላይ ፈላጭ ቆራጭ ለመሆን የምንጠቀምበት ከሆነ ይሖዋ በኃላፊነት ይጠይቀናል። ለይሖዋ አምላክ ሳይሆን ለሀብት ባሪያ የሚሆን ማንኛውም “በባለጠግነቱ የሚተማመን ሰው ይወድቃል።” (ምሳሌ 11:28፤ ማቴዎስ 6:24፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9) ለይሖዋ ተገዢ የሆነ ልብ ያልታከለበት ቁሳዊ ብልጽግና በመጨረሻው ከንቱ ሆኖ ይቀራል።—መክብብ 2:3-11, 18, 19፤ ሉቃስ 16:9

ከሁሉ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ብልጽግና

4. መንፈሳዊ ብልጽግና በቁሳዊ ሀብት ከመትረፍረፍ የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ከቁሳዊ ብልጽግና በተጨማሪ ስለ መንፈሳዊ ብልጽግናም ይናገራል። ይህ መንፈሳዊ ብልጽግና የተሻለ ዓይነት ብልጽግና እንደሆነ ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 6:19-21) መንፈሳዊ ብልጽግና ከይሖዋ ጋር ለዘላለም የሚዘልቅ አርኪ ዝምድና ያመጣል። (መክብብ 7:12) ከዚህም በላይ በመንፈሳዊ ባለጠጎች የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ተገቢ ቁሳዊ በረከቶችን አያጡም። በአዲሱ ዓለም መንፈሳዊ ሀብት ከቁሳዊ ብልጽግና ጋር የተያያዘ ይሆናል። በዛሬው ጊዜ በአብዛኛው እንደሚታየው በመራራ ፉክክር ወይም ጤንነትና ደስታን መሥዋዕት አድርገው ሀብት ከሚያገኙት ሰዎች ጋር ሲወዳደር ታማኝ የሆኑ ሰዎች ተረጋግተው የሚኖሩበት ቁሳዊ ንብረት ያገኛሉ። (መዝሙር 72:16፤ ምሳሌ 10:28፤ ኢሳይያስ 25:6-8) በሁሉም መንገድ ‘የይሖዋ በረከት ባለጠጋ እንደሚያደርግና ኀዘንንም ከእርሱ ጋር እንደማይጨምር’ ይገነዘባሉ።—ምሳሌ 10:22

5. ኢየሱስ ቁሳዊ ነገሮችን በሚመለከት ምን ተስፋ ሰጥቷል?

5 በአሁኑ ጊዜም እንኳን ሳይቀር ለመንፈሳዊ ነገሮች ዋጋ የሚሰጡ ሰዎች ቁሳዊ ነገሮችን በተመለከተ እርግጠኛ መረጋጋት ይሰማቸዋል። እውነት ነው፣ ወጪያቸውን ለመሸፈንና ቤተሰባቸውን ለመመገብ ይሠራሉ። ወይም አንዳንዶቹ በኤኮኖሚ ውድቀት ጊዜ ሥራቸውን ያጡ ይሆናል። ይሁን እንጂ በጭንቀት አይዋጡም። በዚህ ፈንታ ኢየሱስ እንደሚከተለው ሲል በተናገረው ተስፋ ያምናሉ፦ “እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ . . . ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።”—ማቴዎስ 6:31-33

በአሁኑ ጊዜ የሚገኝ መንፈሳዊ ሀብት

6, 7. (ሀ) የአምላክን ሕዝቦች መንፈሳዊ ብልጽግና አንዳንድ ገጽታዎች ግለጽ። (ለ) በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ያለው ምን ትንቢት ነው? ይህስ ምን ጥያቄዎችን ያስነሳል?

6 ስለዚህ የይሖዋ ሕዝቦች መንግሥቱን ለማስቀደም ስለመረጡ ምንኛ የተባረኩ ናቸው! ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራቸው አጥጋቢ ውጤት ይደሰታሉ። (ኢሳይያስ 60:22) “በታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል ሳያቋርጡ የሚጎርፉትን ጥሩ መንፈሳዊ ምግቦች ስለሚያገኙ በይሖዋ የተማሩ ናቸው። (ማቴዎስ 24:45-47፤ ኢሳይያስ 54:13) በተጨማሪም የይሖዋ መንፈስ በእነርሱ ላይ ስለሆነ አስደሳች ወደሆነ ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት መርቷቸዋል።—መዝሙር 133:1፤ ማርቆስ 10:29, 30

7 ይህ በእርግጥም ገንዘብ ሊገዛው የማይችል መንፈሳዊ ብልጽግና ነው። እርሱም ይሖዋ እንደሚከተለው ሲል የሰጠው ተስፋ ፍጻሜ ነው፦ “በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ፤ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፣ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት]።” (ሚልክያስ 3:10) በእርግጥም እኛ በአሁኑ ጊዜ ይህ ተስፋ ሲፈጸም ተመልክተናል። ታዲያ የሀብት ሁሉ ምንጭ የሆነው ይሖዋ አገልጋዮቹ አንድ አሥረኛ ወይም አሥራት እንዲያመጡ የሚጠይቀው ለምንድን ነው? ከአሥራቱ የሚጠቀመውስ ማን ነው? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ይሖዋ በ5ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በሚልክያስ በኩል እነዚህን ቃላት ለምን እንደተናገረ እንመልከት።

አሥራቶችና ቁርባኖች

8. በሕጉ ቃል ኪዳን መሠረት የእሥራኤላውያን ቁሳዊ ብልጽግና የተመካው በምን ላይ ነበር?

8 በሚልክያስ ዘመን የአምላክ ሕዝቦች የበለጸጉ አልነበሩም። ለምን? የደኸዩበት ምክንያት በከፊል ከቁርባንና ከአሥራት ጋር ግንኙነት ነበረው። በዚያን ጊዜ የእሥራኤል ሕዝብ በሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን ሥር ነበር። ይሖዋ ያንን ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ እሥራኤላውያን የበኩላቸውን ካደረጉ በመንፈሳዊም በቁሳዊም እንደሚባርካቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር። የእሥራኤል ብልጽግና በታማኝነታቸው ላይ የተመካ ነበር ለማለት ይቻላል።—ዘዳግም 28:1-19

9. በጥንቶቹ እሥራኤላውያን ዘመን ይሖዋ አሥራትን እንዲከፍሉና ቁርባንን እንዲያመጡ የፈለገባቸው ለምን ነበር?

9 እሥራኤላውያን በሕጉ ሥር ከነበራቸው ግዴታ ከፊሉ ቁርባንን ወደ ቤተ መቅደሱ ማምጣትና አሥራትን መክፈል ነበር። ከቁርባኖቹ አንዳንዶቹ በይሖዋ መሠዊያ ላይ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠሉ የነበሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ምርጡ ለይሖዋ ካቀረበ በኋላ የተረፈውን በካህናቱና በመሥዋዕቱ አቅራቢዎች መካከል የሚከፋፈሉ ነበሩ። (ዘሌዋውያን 1:3-9፤ 7:1-15) አሥራትን በተመለከተ ሙሴ ለእሥራኤላውያን “የምድርም አሥራት ወይም የምድር ዘር ወይም የዛፍ ፍሬ ቢሆን፣ የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] ነው፤ ለእግዚአብሔር [ለይሖዋ አዓት] የተቀደሰ ነው” በማለት ነግሯቸዋል። (ዘሌዋውያን 27:30) አሥራቱ በመገናኛው ድንኳን፣ በኋላም በቤተ መቅደሱ ለሚሠሩ ሌዋውያን ሠራተኞች ይሰጥ ነበር። በምላሹም ካህናት ያልሆኑ ሌዋውያን ከተቀበሉት ውስጥ አንድ አሥረኛውን ለአሮናዊ ካህናት ይሰጡ ነበር። (ዘኁልቁ 18:21-29) እሥራኤላውያን አሥራትን እንዲከፍሉ ይሖዋ የፈለገባቸው ለምን ነበር? በመጀመሪያ ለይሖዋ ጥሩነት ያላቸውን አድናቆት በተጨባጭ ማሳየት እንዲችሉ ነበር። ሁለተኛ ደግሞ ሌዋውያንን ለመደገፍ አስተዋጽኦ ያደርጉ ዘንድና ሌዋውያኑም ሕጉን ማስተማርን ጨምሮ ኃላፊነቶቻቸውን በመፈጸም ላይ ማተኮር ይችሉ ዘንድ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 17:7-9) በዚህ መንገድ ንጹሕ አምልኮም ድጋፍ ያገኝና ሁሉም ይጠቀም ነበር።

10. እሥራኤላውያን አሥራትንና ቁርባንን ማምጣት በተዉ ጊዜ ምን ሆነ?

10 አሥራቶቹና ቁርባኖቹ በኋላ ሌዋውያን የሚጠቀሙባቸው ቢሆንም በእርግጥ ለይሖዋ የሚቀርቡ ስጦታዎች ስለነበሩ ጥራት ያላቸውና ለእርሱ ለመቅረብ ብቃት ያላቸው መሆን ነበረባቸው። (ዘሌዋውያን 22:21-25) እሥራኤላውያን አሥራት ማምጣትን በተዉ ጊዜ ወይም ዝቅተኛ ስጦታዎችን ባመጡ ጊዜ ምን ሆነ? በሕጉ ውስጥ የተደነገገ ቅጣት ባይኖርም መጥፎ ውጤቶች ነበሩት። ይሖዋ በረከቱን ይነፍጋቸውና ቁሳዊ ድጋፍ የተነፈጋቸው ሌዋውያን ራሳቸውን ለመርዳት የቤተ መቅደሱን ሥራቸውን ይተዉ ነበር። ስለዚህ የእሥራኤል ሕዝብ በሙሉ ጉዳት ይደርስበት ነበር።

“ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ”

11, 12. (ሀ) እሥራኤላውያን ሕጉን ከመጠበቅ ችላ ማለታቸው ምን ሁኔታ አስከትሎባቸው ነበር? (ለ) ይሖዋ እሥራኤላውያንን ከባቢሎን ባመጣቸው ጊዜ የሰጣቸው ተልእኮ ምን ነበር?

11 በእሥራኤላውያን የታሪክ ሂደት ወቅት አንዳንዶቹ እሥራኤላውያን አሥራት መክፈልን ጨምሮ ሕጉን ለመጠበቅ በመጣር በኩል ምሳሌ የሚሆኑ ነበሩ። (2 ዜና መዋዕል 31:2-16) ባጠቃላይ ሲታይ ግን ሕዝቡ ቸልተኛ ነበር። ይሖዋ በመጨረሻው በጠላቶቻቸው ድል ተነስተው በ607 ከዘአበ ወደ ባቢሎን እንዲጋዙ እስኪፈቅድ ድረስ ከእርሱ ጋር የነበራቸውን ቃል ኪዳን በተደጋጋሚ አፍርሰው ነበር።—2 ዜና መዋዕል 36:15-21

12 ይህ ከባድ ቅጣት ነበር፤ ይሁን እንጂ ከ70 ዓመታት በኋላ ይሖዋ ሕዝቦቹን ወደ ትውልድ አገራቸው መለሳቸው። በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ስለ ገነት የተነገሩ አብዛኞቹ ትንቢቶች የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት ከዚህ የአይሁዳውያን መመለስ በኋላ ነበር። (ኢሳይያስ 35:1, 2፤ 52:1-9፤ 65:17-19) ይሖዋ ሕዝቡን ወደ ትውልድ አገራቸው የመለሰበት ዋናው ምክንያት ግን ምድራዊ ገነትን ለማቋቋም ሳይሆን ቤተ መቅደሱን እንደገና ለመገንባትና ንጹሕ አምልኮን ለማቋቋም ነበር። (ዕዝራ 1:2, 3) እሥራኤላውያን ይሖዋን ታዘው ቢሆን ኖሮ ቁሳዊ ጥቅሞችም ያገኙ ነበር። የይሖዋም በረከት በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊም ባለጠጎች ያደርጋቸው ነበር። በመሆኑም በ537 ከዘአበ አይሁዶች ወደ ትውልድ አገራቸው እንደደረሱ በኢየሩሳሌም መሠዊያ ሠሩና የቤተ መቅደሱን ሥራ ጀመሩ። ይሁን እንጂ ኃይለኛ ተቃውሞ አጋጠማቸውና አቆሙ። (ዕዝራ 4:1-4, 23) በዚህም የተነሳ እሥራኤላውያን የይሖዋን አስደሳች በረከት አላገኙም።

13, 14. (ሀ) እሥራኤላውያን ቤተ መቅደሱን እንደገና መሥራትን በተዉ ጊዜ ምን ተከተለ? (ለ) ቤተ መቅደሱ በመጨረሻው እንደገና የተሠራው እንዴት ነበር? ይሁን እንጂ በእሥራኤል በኩል የተረሱ ምን ነገሮች መኖራቸው ተገልጾአል?

13 ወደ ቤተ መቅደሱ ሥራ እንዲመለሱ ማሳሰቢያ ይሰጡአቸው ዘንድ ይሖዋ በ520 ከዘአበ ሐጌና ዘካርያስ የተባሉትን ነቢያት አስነሳ። ሕዝቡ ቁሳዊ ችግር እየደረሰባቸው እንዳለና ይህም ለይሖዋ ቤት ቅንዓት ስለጎደላቸው መሆኑን ሐጌ አመለከተ። እንዲህ አለ፦ “አሁንም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። ብዙ ዘራችሁ፣ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፣ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፣ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ፣ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። ወደ ተራራው ውጡ፣ እንጨትንም አምጡ፣ ቤቱንም ሥሩ፤ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፣ እኔም እመሰገናለሁ ይላል፣ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት]።”—ሐጌ 1:5-8

14 እሥራኤላውያን በሐጌና በዘካርያስ ተበረታተው ልባቸውን በመንገዳቸው ላይ አደረጉና ቤተ መቅደሱ ተሠራ። ይሁንና 60 ዓመታት ያህል ቆይቶ ነህምያ ኢየሩሳሌምን ሲጎበኝ እሥራኤል እንደገና የይሖዋን ሕግ ችላ እንዳሉ ተገነዘበ። ይህንንም አስተካከለ። በሁለተኛ ጉብኝቱ ጊዜ ግን ነገሮች እንደገና ተበላሽተው አገኛቸው። እንዲህ ሲል ገለጸ፦ “ለሌዋውያንም ዕድል ፈንታቸው እንዳልተሰጠ፣ የሚያገለግሉትም ሌዋውያንና መዘምራን እያንዳንዱ ወደ እርሻው እንደሄዱ ተመለከትሁ።” (ነህምያ 13:10) ይህ ችግርም ተስተካከለና “ይሁዳም ሁሉ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም አሥራት ወደ ዕቃ ቤቶች አመጡ።”—ነህምያ 13:12

ይሖዋን መስረቅ

15, 16. ይሖዋ በሚልክያስ በኩል እሥራኤልን የገሰጸው ምን ሳያደርጉ በመቅረታቸው ነበር?

15 ሚልክያስም ትንቢት የተናገረበት አጠቃላይ ጊዜ ይኸው ሳይሆን አይቀርም፣ እርሱም ስለ እሥራኤል እምነተቢስነት ተጨማሪ ነገር ይነግረናል። ይሖዋ ለእሥራኤል የተናገራቸውን ቃላት እንደሚከተለው በማለት መዝግቧል፦ “እናንተ ስሜን የምታቃልሉ ካህናት ሆይ፣ . . . እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት]።” ችግሩ ምን ነበር? ይሖዋ “ዕውር መሥዋዕትንም ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? አንካሳውንና የታመመውን ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን?” በማለት አብራራ።—ሚልክያስ 1:6-8

16 በዚህ ጉልህ የሆነ መንገድ እሥራኤላውያን ቁርባን ቢያቀርቡም ጥራት የሌለውና የማይረባ በመሆኑ ለይሖዋ የነበራቸውን ከፍተኛ ንቀት እንደሚያጋልጥ ሚልክያስ ገለጸ። ሚልክያስ “ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፣ እርስዋንም አልጠበቃችሁም። ወደ እኔ ተመለሱ፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት]” በማለትም ጽፏል። እሥራኤላውያን ይሖዋ ከእነርሱ የሚፈልገው ምን እንደሆነ ለይተው ለማወቅ ፈለጉና “የምንመለሰው በምንድር ነው?” ብለው ጠየቁ። ይሖዋም “ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል” ብሎ መለሰላቸው። እሥራኤላውያን የሀብት ሁሉ ምንጭ የሆነውን ይሖዋን እንዴት ሊሰርቁት ይችሉ ነበር? ይሖዋ መልስ ሲሰጥ “በአሥራትና በበኩራት ነው” አለ። (ሚልክያስ 3:7, 8) አዎን፣ እሥራኤላውያን አሥራቶቻቸውንና ቁርባኖቻቸውን ሳያመጡ በመቅረታቸው ይሖዋን እየሰረቁት ነበር።

17. አሥራቶችና ቁርባኖች በእሥራኤል ለምን ዓላማ ይውሉ ነበር? ይሖዋስ አሥራትን በተመለከተ ምን ተስፋ ሰጥቷል?

17 ይህ ታሪካዊ ጉዳይ አሥራትና ቁርባን በእሥራኤል ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበረ ይገልጻል። በሰጪው በኩል የሚገለጸውን አድናቆት ማሳያ ነበሩ። እውነተኛ አምልኮን በቁሳዊ መንገድ ለመደገፍም ይረዱ ነበር። ስለዚህ ይሖዋ እሥራኤላውያንን “አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ” በማለት አበረታታቸው። እንዲህ ካደረጉ ምን እንደሚከተል ይሖዋ ሲገልጽ ‘ምንም እስከማይጎድላችሁ ድረስ በረከትን አፈስስላችኋለሁ’ በማለት ቃል ገባላቸው። (ሚልክያስ 3:10) ይሖዋ በሀብት ባለጠጋ ያደርጋቸው ነበር።

“በእውነተኛው ጌታ” መፈረድ

18. (ሀ) ይሖዋ ያስጠነቀቀው ስለ ማን መምጣት ነበር? (ለ) ወደ መቅደሱ የመጣው መቼ ነበር? አብሮ የመጣው ማን ነበር? በእሥራኤል ላይ ምን ውጤት አስከተለ?

18 ይሖዋ በሚልክያስ በኩል ሕዝቡን ለመፍረድ እንደሚመጣም አስጠንቅቆ ነበር። “እነሆ፣ መልእክተኛዬን እልካለሁ፣ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት [እውነተኛው አዓት] ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፤ የምትወድዱትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፣ እነሆ፣ ይመጣል፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት]።” (ሚልክያስ 3:1) ወደ መቅደሱ እንደሚመጣ የተሰጠው ተስፋ የሚፈጸመው መቼ ነው? በማቴዎስ 11:10 ላይ ኢየሱስ መንገድን ስለሚያስተካክል መልእክተኛ የሚናገረውን የሚልክያስን ትንቢት ጠቅሶ በዮሐንስ መጥምቁ ላይ የተፈጸመ መሆኑን ተናግሮአል። (ሚልክያስ 4:5፤ ማቴዎስ 11:14) ስለዚህ በ29 እዘአ የፍርዱ ጊዜ ደርሶ ነበር! ከ“እውነተኛው ጌታ” [አዓት] ከይሖዋ ጋር አብሮ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚመጣው ሁለተኛው የቃል ኪዳን መልእክተኛ ማን ነው? ኢየሱስ ራሱ ነው። እርሱም በሁለት ወቅቶች በኢየሩሳሌም ወደነበረው ቤተ መቅደስ መጥቶ አጭበርባሪ የገንዘብ ለዋጮችን በማስወጣት ቤተ መቅደሱን በአስገራሚ ሁኔታ አጽድቶታል። (ማርቆስ 11:15-17፤ ዮሐንስ 2:14-17) የመጀመሪያውን መቶ ዘመን ፍርድ በሚመለከት ይሖዋ በትንቢት “የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም ማን ነው?” ብሎ ጠይቋል። (ሚልክያስ 3:2) በእርግጥም እሥራኤላውያን በፊቱ ሊቆሙ አልቻሉም። ተመርምረው ጎደሎ ሆነው በመገኘታቸው በ33 እዘአ የይሖዋ ምርጥ ሕዝቦች ከመሆን ተጣሉ።—ማቴዎስ 23:37-39

19. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ቀሪዎቹ ወደ ይሖዋ የተመለሱት በምን መንገድ ነበር? እነርሱስ ምን በረከቶችን አገኙ?

19 ይሁን እንጂ ሚልክያስ “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፣ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፣ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም [ለይሖዋ አዓት] በጽድቅ ቁርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ” በማለትም ጽፏል። (ሚልክያስ 3:3) ከዚህ ጋር በመስማማት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሖዋን እናገለግላለን ይሉ ከነበሩት መካከል አብዛኞቹን አምላክ ተዋቸው። አንዳንዶቹ ግን ነጽተው ተቀባይነት ያለው መሥዋዕትን በማቅረብ ወደ ይሖዋ መጥተው ነበር። እነርሱ እነማን ነበሩ? የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ ለሆነው ለኢየሱስ የእሽታ ምላሽ የሰጡት ነበሩ። ምላሽ ከሰጡት መካከል 120ዎቹ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም በአንድ ሰገነት ላይ ተሰብስበው ነበር። በመንፈስ ቅዱስ ተበረታትው በጽድቅ ቁርባንን ማቅረብ ጀመሩና በፍጥነትም ቁጥራቸው አደገ። ወዲያውም በሮማ ግዛት በሙሉ ተሠራጩ። (ሥራ 2:41፤ 4:4፤ 5:14) በዚህ መንገድ ከእሥራኤላውያን መካከል የቀሩት ወደ ይሖዋ ተመልሰው ነበር።—ሚልክያስ 3:7

20. ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ በተደመሰሱ ጊዜ የአምላክ እሥራኤል ምን ሆኑ?

20 ከእሥራኤል ግንድ ጋር የተጣበቁትን አሕዛብ የጨመረው ይህ የእሥራኤል ቀሪዎች ቡድን በመንፈስ በተቀቡ ክርስቲያኖች የተገነባው አዲሱ “የእግዚአብሔር እሥራኤል” ነው። (ገላትያ 6:16፤ ሮሜ 11:17) በ70 እዘአ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ በሮማ ሠራዊት በተደመሰሱ ጊዜ በሥጋዊ እሥራኤል ላይ “እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን” መጥቶባቸው ነበር። (ሚልክያስ 4:1፤ ሉቃስ 19:41-44) የአምላክ መንፈሳዊ እሥራኤልስ ምን ሆነ? “ሰው ለሚያገለግለው ልጁ እንደሚራራ [ይሖዋ አዓት] እንዲሁ ርኅራኄ” አሳየ። [ሚልክያስ 3:17 አዓት] የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ የኢየሱስን ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ተቀብሎ ነበር። (ማቴዎስ 24:15, 16) ከጥፋቱ ተረፉና ይሖዋ በመንፈሳዊ ባለጠጎች እያደረጋቸው መባረኩን ቀጠለ።

21. ስለ ሚልክያስ 3:1 እና 10 ገና ያልተብራሩ ምን ጥያቄዎች ይቀራሉ?

21 ይህስ ይሖዋን ምንኛ የሚያስከብር ነበር! ይሁንና ሚልክያስ 3:1 በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው? አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራው እንዲያመጡ በሚልክያስ 3:10 ላይ ለተሰጠው ማበረታቻ አንድ ክርስቲያን ምላሽ መስጠት የሚገባው እንዴት ነው? ይህ በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ ይብራራል።

ልታብራራ ትችላለህን?

◻ የመጨረሻው የሀብት ሁሉ ምንጭ ማን ነው?

◻ መንፈሳዊ ብልጽግና ከሥጋዊ ሀብት የሚሻለው ለምንድን ነው?

◻ አሥራቶችና ቁርባኖች በእሥራኤል ለምን ዓላማ ያገለግሉ ነበር?

◻ “እውነተኛው ጌታ” [አዓት] ይሖዋ እሥራኤልን ለመፍረድ ወደ ቤተ መቅደሱ የመጣው መቼ ነበር? ከምንስ ውጤት ጋር?

◻ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይሖዋ ወደ ቤተ መቅደሱ ከመጣ በኋላ ወደ እርሱ የተመለሱት እነማን ናቸው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ ኢየሱስ ይሖዋን ወክሎ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ለፍርድ ወደ ቤተ መቅደሱ መጣ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ