የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 12/15 ገጽ 5-7
  • ወንጌል ሊጠቅምህ የሚችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወንጌል ሊጠቅምህ የሚችለው እንዴት ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከወንጌሉ እርዳታ ያገኙ ሰዎች
  • ምሥራቹ በአሁኑ ጊዜ ምን ትርጉም አለው?
  • ወንጌል በዛሬው ጊዜ ያለው ኃይል
  • ወደፊት የሚመጡ በረከቶች
  • ‘መልካም ዜና ማብሰር’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ወንጌል በእርግጥ ምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ወንጌል
    ለይሖዋ ‘በደስታ ዘምሩ’
  • ሁሉም ሰው የሚያስፈልገው ምሥራች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 12/15 ገጽ 5-7

ወንጌል ሊጠቅምህ የሚችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ከሥነ ጽሑፍ አንፃር ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለው ተቆጥሮ በአንዳንድ አምላክ የለሾችም ዘንድ እንኳን በጣም ይከበራል። ይሁን እንጂ መጽሐፉ የሚለውን ነገር በሥራ ላይ ለማዋል ብለው የሚያነቡት ጥቂቶች ናቸው። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ምሥራች ወደ ሁለት ሺህ ዓመታት ያህል የቆየ በመሆኑ ብዙ ሰዎች ተሻሽሎ ዘመናዊ መደረግ እንደሚኖርበት ያምናሉ። ወንጌሉ ዘመን ያለፈበት ወይም የቀረ ነገር ነውን? በጭራሽ አይደለም።

መጽሐፍ ቅዱስ ተወዳዳሪ የሌለው የእርዳታ ምንጭ መሆኑን የሚያውቁ በሚልዮን የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች፣ ወጣቶችና አዛውንት አሉ። የቱደይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን መጽሐፍ ቅዱስ መቅድም “መጽሐፍ ቅዱስ ሊደነቅና ሊከበር የሚገባው ታላቅ ሥነ ጽሑፍ ብቻ ሳይሆን ሊረዱትና በዕለታዊ ኑሮ ውስጥ ተግባራዊ ሊያደርጉት የሚገባ መልእክት የያዘ በየትም ቦታ ለሚኖሩ ሰዎች የሚሆን የምሥራች ነው” በማለት የገለጸው ትክክል ነው።

ወንጌል ለአንተ ምን ትርጉም አለው? የዕለታዊ ኑሮህ መመሪያ አድርገህ ትጠቀምበታለህን? በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምሥራቹ የሰሙትን አንዳንድ ሰዎች እንዴት እንደጠቀማቸውና በዘመናችንም አንዳንድ ሰዎች እንዴት እንደተጠቀሙ ተመልከት።

ከወንጌሉ እርዳታ ያገኙ ሰዎች

በኢየሱስ ዘመን እንደ ዓሣ አጥማጆች ያሉ ብርቱ ሠራተኞች እንዲሁም የቤት እመቤቶች በምሥራቹ ተስበው አምላክ ለሰዎች ስላለው ዓላማ የሚገልጸውን እውነት ተምረዋል። ወንጌሉ ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ ለውጦታል። ብዙውን ጊዜም ትልቅ እፎይታ አምጥቶላቸዋል። ለምሳሌ ያህል መግደላዊት ማርያም ከአጋንንት መዳፍ ተላቃለች። የቀራጮች አለቃ የነበረው ዘኬዎስ የስግብግብነት አኗኗሩን ተወ። (ሉቃስ 8:2፤ 19:1-10) ዓይነ ስውሮችና ለምጻሞችም ምሥራቹን ወደሚሰብከው ወደ ኢየሱስ ሲመጡ እርዳታ አግኝተዋል። (ሉቃስ 17:11-19፤ ዮሐንስ 9:1-7) ኢየሱስ “ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፣ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፣ ሙታንም ይነሣሉ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል” ብሎ በትክክል ሊናገር ችሎ ነበር።—ማቴዎስ 11:5

ይሁን እንጂ በሕይወታቸው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ፈውስ ከማግኘታቸው የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ምሥራቹ በእነርሱ ላይ ያመጣው ለውጥ ነበር። ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በሚመለከት በተስፋ ተሞልተዋል። እምነታቸውን ከየትኛውም የማኅበራዊ ኑሮ ወንጌል የተሻለ በሆነው በአምላክ መንግሥት ላይ ይጥላሉ። (ማቴዎስ 4:23) ኢየሱስ በመሞቱ ምክንያት ተስፋቸው ከንቱ አልሆነም። ደቀ መዛሙርቱ ከዚያ በኋላ እንኳን የነበራቸውን ሁኔታ ሲገልጽ ሥራ 5:42 እንዲህ ይላል፦ “ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።” በመጀመሪያው መቶ ዘመን በብዙ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች እንዲህ ላለው ስብከት አዎንታዊ ምላሽ በመስጠታቸው ምክንያት መንፈሳዊ እርዳታ አግኝተዋል።

በዚያን ጊዜ ከሁሉ የተሻለው ዜና የመንግሥቱ ዜና ነበር። የመንግሥቱ መልእክት አሁንም የምሥራች ነውን?

ምሥራቹ በአሁኑ ጊዜ ምን ትርጉም አለው?

ሰላምና ደኅንነት ያለበት ዓለም እንዲመጣ የምትጓጓ ከሆነ የመንግሥቱ ዜና በእርግጥ መልካም ዜና ነው። እንዲያውም በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውና የተራቡ ሰዎች፣ ማንኛውንም ሰው የሚያሰጉ አስፈሪ በሽታዎች፣ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ የሚሄድ ወንጀልና በየቦታው ተዛምቶ የሚገኝ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ባለበት ዓለም ውስጥ ስለምንኖር ብቸኛና ዘላቂ የሆነው እውነተኛ የምሥራች መንግሥቲቱ ነች። እውነተኛ መሻሻል የሚገኝበት ብቸኛ ተስፋ እርሷ ናት።

ኢየሱስ ስለ ዘመናችን “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ሲል የተነበየው በዚህ ምክንያት ነው። (ማቴዎስ 24:14) የይሖዋ ምስክሮች ከ200 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የምሥራቹን በመስበክ ላይ ስለሆኑ እነዚህ ቃላት በሚያስደንቅ መንገድ በመፈጸም ላይ ናቸው። “ኖቫ ኢቫንጄሊዛሳኦ 2000” የተባለ አንድ የካቶሊክ ጽሑፍ የይሖዋ ምስክሮችን በማመስገን እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምስክሮችን የምናገኛቸው የት ነው? በቤቶች በራፍ ላይ ነው። አንድ ሰው የይሖዋ ምስክር ለመሆን የይሖዋ ንብረት ከመሆኑ በተጨማሪ ምስክር ጭምር መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ ያዩትን ነገር ለሌሎች በመንገር ሲሠሩ፣ ሲያውጁና ሲያስተዋውቁ እናገኛቸዋለን።”

ይሁን እንጂ ማንኛውም ሰው ከምሥራቹ እንዲሁ ጥቅም አያገኝም። ምሥራቹ የሚረዳው የሚሰሙትንና የሚታዘዙትን ብቻ ነው። ኢየሱስ ይህንን ነጥብ በምሳሌ ለማስረዳት ሲል ዘር ሊዘራ ስለወጣ ገበሬ የሚናገረውን አንድ ምሳሌ ሰጠ። ዘሩ የወደቀባቸው የተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ምሥራቹን የሚቀበሉ ሰዎች የሚያሳዩአቸውን የተለያዩ ዓይነት የልብ ሁኔታዎችን ያመለክታሉ። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፣ ክፉው ይመጣል፣ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ . . . በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል።”—ማቴዎስ 13:18-23

እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ በዛሬውም ጊዜ ብዙ ሰዎች ምሥራቹን ለመረዳት የሚያደርጉት ጥረት አነስተኛ ነው። ምሥራቹን አያስተውሉትም፤ ስለሆነም ጥቅሞቹን ሳያገኙ ይቀራሉ። ሌሎች ደግሞ ለምሥራቹ አድናቆት ያሳያሉ፤ ሕይወታቸውን ከአምላክ ፈቃድ ጋር እንዴት ለማስማማት እንደሚችሉም ይማራሉ። እነሱም በዚህ መንገድ ተባርከዋል። የምትመደበው ከየትኛው ቡድን ነው?

ወንጌል በዛሬው ጊዜ ያለው ኃይል

ምሥራቹን መረዳታቸው ‘ተስፋን አጥተው ከይሖዋም ተለይተው’ የነበሩትን እንደረዳቸው ብዙ ተሞክሮዎች ይመሰክራሉ። (ኤፌሶን 2:12፤ 4:22-24) የሪዮ ዲ ጃኔሮ ነዋሪ የሆነው ሮቤርቶ እርዳታ አስፈለገው። ከወጣትነት ዕድሜው አንስቶ እንደ አደንዛዥ መድኃኒቶች፣ የጾታ ብልግናና ስርቆት በመሳሰሉ ነገሮች የረከሰ ሕይወት ይኖር ነበር። በመጨረሻም እስር ቤት ገባ። እዚያ እያለ ሮቤርቶን እየመጣ ይጠይቀው ከነበረ አንድ የይሖዋ ምስክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጠና። በመንፈሳዊ በኩል ትልቅ መሻሻል ከማሳየቱ የተነሳ በእስር ቤት የሚቆይበት ጊዜ እንኳን በከፍተኛ ሁኔታ ተቀንሶለት ነበር።

ሮቤርቶ ገንዘቧን ለመስረቅ በሽጉጥ አስፈራርቷት የነበረች አንዲት ወጣት ልጃገረድ ከእስር ቤት ከተፈታ በኋላ አገኛት። እሷም ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ታጠና ነበር። ምን ሁኔታ ተፈጸመ? ስለ ሁኔታው የሚገልጸው ቀጥሎ ያለው ደብዳቤ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ ሁለቱም በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ። በድንገት መገናኘታቸው ስሜት የሚነካ ነበር። ሁለቱም የስሜት እንባ አፍስሰው እንደ ወንድምና እህት በመሆን ተቃቀፉ። ሁለቱም ማለትም ከዚህ ቀደም ሌባ የነበረው ሰውና ጉዳት አድርሶባት የነበረችው ሴት አሁን ይሖዋን ያወድሳሉ።”

ኢዛቤል የተባለችው ሌላ ግለሰብ ቁጡ ስለነበረች እርዳታ አስፈለጋት። በመናፍስትነትና በጥንቆላ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠላልፋ ነበር። በአጋንንትም ትሠቃይ ነበር። ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር ምሥራቹ በእርግጥም የሚረዳ ሆኖ አገኘችው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከአጋንንት ቁጥጥር ተላቀቀች፤ በመጨረሻም ግልፍተኝነቷን መቆጣጠር ተምራ ባሕሪዋን ቀየረች። አሁን ሌሎችን በደግነት የምትይዝ በመሆኗ የታወቀች ታማኝ ክርስቲያን ናት።

አዎን፣ ምሥራቹ ፅንሰ ሐሳብ ብቻ የያዘ አይደለም። ሕይወት ለመለወጥ የሚያስችል እውነተኛ ኃይል አለው። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ይሁን እንጂ ከዚህ የበለጠም ነገር ያደርጋል። ወደፊት በረከቶች እንደሚመጡም ይጠቁማል።

ወደፊት የሚመጡ በረከቶች

በአምላክ ቃል መሠረት የወደፊቱ ጊዜ ግሩም ተስፋዎችን የያዘ ነው። የአምላክ መንግሥት እንድትመጣና ፈቃዱ በሰማይ እንደሆነች ሁሉ እንዲሁም በምድር እንድትሆን የሚጠይቀው የኢየሱስ ጸሎት ሲፈጸም እናያለን። (ማቴዎስ 6:10) ከአጭር ጊዜ በኋላ አሁን ያለው የነገሮች ሥርዓት አስከፊ ከሆነው ብልሹ ምግባሩና ሁከተኛነቱ ጋር ይወገዳል፤ የአምላክ ሰማያዊት መስተዳድር የሆነችው መንግሥቱ ምሥራቹን ለመስማትና ለመታዘዝ ፈቃደኞች የነበሩ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ግለሰቦች ትገዛለች።—ዳንኤል 2:44

ታማኝ የሆኑ ሰዎች ምድርን ቅኖች የሚኖሩባት ገነት አድርገው እንዲለውጡ ስለሚደረጉ በያቅጣጫው መሠረታዊ የሆነ መሻሻል ይከተላል። (መዝሙር 37:11, 29) ወንጀል፣ በሽታ፣ ረሐብ፣ የአካባቢ ብክለትና ጦርነቶች ለዘላለም የሚወገዱ መሆናቸው በእርግጥም የምሥራች ነው! አንተና ቤተሰብህ በሽታን ወይም ሞትን ሳትፈሩ በዚያ ዓለም ውስጥ በሰላምና በፍጹም ጤንነት ስትኖሩ በዓይነ ሕሊናህ ልትመለከተው ትችላለህን?—ራእይ 21:4

እውነት ነው፤ ብዙዎች እንዲህ ያለውን ምሥራች ያቃልሉታል፤ ወይም ሐሳባዊ ብቻ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። ነገር ግን ተሳስተዋል። ምሥራቹ ከሁሉ ይበልጥ ሊታመን በሚችል ጠንካራ ማስረጃ ላይ የተመሠረተና በአሁኑ ጊዜ እንኳን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የለወጠ ነው። ስለዚህ ሌሎች ሰዎች ባያምኑ አንተ በፍጹም አትሸበር።

ገንዘቡን ሥራ ላይ በማዋሉ ምክንያት ትርፍ እንደሚያገኝ በማሰብ በአንድ እየለማ በሚሄድ አካባቢ መሬት የገዛ አንድን አርቆ አሳቢ የሆነ ግለሰብ አስብ። ገንዘቡን በዚህ መንገድ ሥራ ላይ በማዋሉ ምክንያት የሚወቅሰው ሰው ይኖራልን? አይኖርም። እንዲያውም ሰዎች በጥበብ እየሠራ ነው ይሉታል። ታዲያ መንግሥቱን በሚመለከት ወደፊት እንደምትጠቀምበት አርቀህ በማሰብ ጉልበትህን ለምን በምሥራቹ ላይ አታውልም? ምሥራቹን መቀበል ማለት መዳንን ማግኘት ማለት ስለሆነ ገንዘብ የወጣበት ምንም ዓይነት ሥራ ከዚህ የበለጠ ትርፍ አያስገኝም።—ሮሜ 1:16

ወደፊት እንደምትጠቀምበት በማወቅ ለምሥራቹ ኃይልህንና ጉልበትህን ልታጠፋ የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ አምላክ እንዲያስተምርህ ፍቃደኛ ሁን። ከዚያም ከተማርከው ጋር የሚስማማ ነገር አድርግ። አንድ ጥንታዊ ዕብራዊ ነቢይ፦ “እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን [ፍትህን አዓት] ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም [ፍቅራዊ ደግነትንም አዓት] ትወድድ ዘንድ፣ ከአምላክህም ጋር በትሕትና [ቦታህን በማወቅ አዓት] ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” በማለት የዘረዘራቸውን ከአንተ የሚፈለጉብህን መሠረታዊ ነገሮች ተከተል። (ሚክያስ 6:8) ከአምላክ ጋር መሄድን መማሩ ጊዜንና ጥረትን ይጠይቃል። ሆኖም ሮቤርቶንና ኢዛቤልን የረዷቸው የይሖዋ ምስክሮች ባለፉት ዓመታት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችን እንደረዱ ሁሉ በዚህ በኩል አንተንም ለመርዳት ደስተኞች ናቸው።

የአምላክን ተስፋዎች መፈጸም እየተጠባበቅህ ከምሥራቹ ጋር በሚስማማ ሁኔታ በመኖር የአእምሮ ሰላም በማግኘትና ከአምላክ ጋር የቅርብ ዝምድና በመመሥረት ጉልበትህንና ጊዜህን ለምሥራቹ መስጠትህን የበለጠ አጠናክር። ጉልበትና ጊዜህን ያጠፋህለት ነገር ምንም ዓይነት የኢኮኖሚ ድቀት ወይም የፖለቲካ ቀውስ የማያናጋውና ዋስትና ያለው ይሆናል። በመጨረሻም ግሩም የሆነ ውጤት ያመጣልሃል። ያ ውጤት ምንድን ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ሲል ጽፏል።—1 ዮሐንስ 2:17

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምሥራቹ ዘሮች በተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ላይ ይወድቃሉ

[የሥዕል ምንጭ]

Garo Nalbandian

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ