በአንድ ልብ መጓዝ
“አቤቱ ይሖዋ፣ . . . አስተምረኝ፣ ስምህን ለመፍራት ልቤን አንድ አድርግልኝ።”—መዝሙር 86:11
1. ይሖዋ ታማኝ ሆነው ከጎኑ ለሚቆሙለት ወሮታቸውን የከፈላቸው እንዴት ነው?
‘ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ብቻ አምላክ ነህ።’ (መዝሙር 86:8, 10) ዳዊት በአድናቆት በተሞላ ልብ አምላክን አወድሷል። ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ከመሆኑ በፊት እንኳን ይሖዋ ከሳኦልና ከፍልስጥኤማውያን እጅ አድኖታል። በዚህ ምክንያት “ይሖዋ አለቴ፣ ጠንካራ ምሽጌና ታዳጊዬ ነው፤ ታማኝ ሆነው ለሚቆሙልህ ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ” በማለት ለመዘመር ችሏል። (2 ሳሙኤል 22:2, 26 አዓት) ይሖዋ ታማኝ ሆነው ከጎኑ የሚቆሙ አገልጋዮቹን ከብዙ መከራዎች ጠብቆ አቆይቷቸዋል። ዳዊት በዚህ ታማኝ አምላኩ ላይ እምነትና ትምክህት ሊጥል ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ ቀጣይ የሆነ መመሪያ አስፈልጎት ነበር። አሁን ዳዊት “አቤቱ ይሖዋ፣ ስለ መንገድህ አስተምረኝ” ሲል ለመነ።—መዝሙር 86:11 አዓት
2. ይሖዋ ከሱ የተማርን እንድንሆን ዝግጅት ያደረገው እንዴት ነው?
2 ዳዊት ከዓለም አስተሳሰቦች ወይም ፍልስፍናዎች ሙሉ በሙሉ ለመራቅ ፈልጎ ነበር። አንዱ የአምላክ ነቢይ በኋላ እንደገለጸው “ከይሖዋ የተማረ” ለመሆን ፈልጎ ነበር። (ኢሳይያስ 54:13) ዳዊት ማሰላሰል የሚችልባቸው ግፋ ቢል እስከ ዘጠኝ የሚደርሱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ብቻ ኖረው ሊሆን ይችላል። ሆኖም በመጻሕፍቱ በኩል ከይሖዋ የሚገኘው ይህ መመሪያ ለእርሱ ውድ ነገር ነበር! እኛ በዛሬው ጊዜ ትምህርት የምናገኝባቸው 66 የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እንዲሁም “በታማኝና ልባም ባሪያ” የሚዘጋጁ የተትረፈረፉ የመንግሥት ጽሑፎች አሉን። (ማቴዎስ 24:45) ልክ እንደ ዳዊት “እግዚአብሔር ያዘጋጀውን . . . የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር” ለመመርመር መንፈሱ እንዲረዳን ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን እንለምነው።—1 ቆሮንቶስ 2:9, 10
3. መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ትምህርት እኛን ሊጠቅመን የሚችለው በምን በምን መንገዶች ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ለሚነሳው ለእያንዳንዱ ጥያቄና ችግር መልስ አለው። “በመጽናናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።” (ሮሜ 15:4) ከይሖዋ የሚመጣውን ትምህርት መቅሰማችን ችግሮችን እንድንቋቋም ያጠነክረናል፣ በምንተክዝበት ጊዜ ያጽናናናል እንዲሁም በልባችን ውስጥ የተተከለው የመንግሥቱ ተስፋ ዘወትር ደማቅ ሆኖ እንዲበራ ያደርግልናል። የአምላክን ቃል በማንበብና “ቀንና ሌሊት” እርሱን በማሰላሰል ደስታ እናግኝ። ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተች ጥበብ “ለሚይዙአት የሕይወት ዛፍ ናት፣ የተመረኰዘባትም ሁሉ ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው።”—መዝሙር 1:1-3፤ ምሳሌ 3:13-18፤ በተጨማሪም ዮሐንስ 17:3ን ተመልከት።
4. በምናደርጋቸው ነገሮች ረገድ ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቶልናል?
4 “የዳዊት ልጅ” እየተባለም ይጠራ የነበረው የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ መመሪያ ለማግኘት ዘወትር ወደ ይሖዋ ይመለከት ነበር። (ማቴዎስ 9:27)a “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና።” “አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች” አላደርግም አለ። (ዮሐንስ 5:19፤ 8:28) ኢየሱስ “ፍለጋውን እንድንከተል” ምሳሌ ትቶልናል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስ የይሖዋን ቃል በጣም አጥንቶ መሆን አለበት። እኛም ልክ እንደ እርሱ አድርገን ብናጠና በማንኛውም ሁኔታ ይሖዋ እንድናደርግ የሚፈልግብንን እናደርጋለን ማለት ነው። ምን ጊዜም ትክክለኛው መንገድ የይሖዋ መንገድ ነው!
5. “እውነት” ምንድን ነው?
5 ቀጥሎ ዳዊት “በእውነትህም እሄዳለሁ” በማለት አቋሙን አስታወቀ። (መዝሙር 86:11) ከዚያ አንድ ሺህ ዓመታት ያህል ቆይቶ ጲላጦስ የዳዊት ልጅ የሆነውን ኢየሱስን “እውነት ምንድን ነው?” ሲል ጠይቆት ነበር። ኢየሱስም ለጲላጦስ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” በማለት መልሱን ነገረው። ጨምሮም “እኔ ንጉሥ እንደሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ” አለው። (ዮሐንስ 18:33-38) በዚህ መንገድ ኢየሱስ እውነት በመሲሐዊው መንግሥት ላይ እንደሚያተኩር አሳወቀ። እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ መልዕክት በመንግሥቱ አማካኝነት የይሖዋ ስም እንደሚቀደስ የሚገልጽ ነው።—ሕዝቅኤል 38:23፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ ራእይ 11:15
6. በእውነት ውስጥ ስንጓዝ ስለምን ነገር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል?
6 በእውነት ውስጥ መጓዝ ሲባል ምን ማለት ነው? የመንግሥቱን ተስፋ ዋነኛው የሕይወታችን ዓላማ ማድረግ ማለት ነው። የመንግሥቱ እውነት በሕይወታችን ውስጥ ሕያው ሆኖ መታየት አለበት። የመንግሥቱን ጉዳዮች በአንደኛ ቦታ በማስቀመጥ ረገድ አቋማችን ያልተከፋፈለ መሆን አለበት። የኢየሱስንም ምሳሌ በመከተል ስለ መንግሥቱ እውነቶች ምስክርነት ለመስጠት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች ሁሉ በቅንዓት ልንጠቀምባቸው ይገባል። (ማቴዎስ 6:33፤ ዮሐንስ 18:37) ግማሹን ጊዜ ለስሙ ያህል ብቻ እያገለገልን ከዚያ በኋላ ግን ከመጠን በላይ በሆነ መዝናኛ እየተዝናናን ወይም ጊዜ የሚፈጅ ሥራ እየሠራን ወይም “ለገንዘብ . . . ባሪያዎች” ሆነን እየተገዛን ራሳችንን በማስደሰት በእውነት ውስጥ ለመጓዝ አንችልም። (ማቴዎስ 6:24) ከዋናው ጎዳና ወጥተን በእነዚህ መንገዶች በመሄድ ጭልጥ ብለን ልንጠፋ እንችላለን። ዳግመኛ ‘ወደ ሕይወት ወደሚወስደው ጠባብ መንገድ’ ለመመለስ ፈጽሞ አንችል ይሆናል። ከእውነት መንገድ ፈጽሞ ፈቀቅ አንበል! (ማቴዎስ 7:13, 14) ታላቁ ፈጣሪያችን ይሖዋ መንገዳችንን እያበራ ‘ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ እንዳትሉ . . . መንገዱ ይህ ነው። በእርሱ ሂዱ’ እያለ በቃሉና በድርጅቱ በኩል ይነግረናል።—ኢሳይያስ 30:21
ተገቢ የሆነ ፍርሃት
7. ልባችንን “አንድ” ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?
7 የዳዊት ጸሎት በቁጥር 11 ላይ “ስምህን ለመፍራት ልቤን አንድ አድርግልኝ” በማለት ይቀጥላል። እኛም እንደ ዳዊት የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ልባችን ያልተከፋፈለና ፍጹም እንዲሆን እንፈልጋለን። ይህም ሙሴ ለእስራኤላውያን ከሰጠው ከሚቀጥለው ምክር ጋር የሚስማማ ነው፦ “እስራኤል ሆይ፣ አሁንስ አምላክህን እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] ትፈራ ዘንድ፣ በመንገዱም ሁሉ ትሄድ ዘንድ፣ አምላክህንም እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] ትወድድ ዘንድ፣ በፍጹምም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ ታመልከው ዘንድ፣ መልካምም እንዲሆንልህ ዛሬ ለአንተ የማዝዘውን የእግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] ትእዛዝና ሥርዓት ትጠብቅ ዘንድ ነው እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ከአንተ የሚፈልገው ምንድር ነው?” (ዘዳግም 10:12, 13) በእርግጥም ለይሖዋ አገልግሎት ልባችንንና ነፍሳችንን መስጠታችን ለእኛው ጥቅም ነው። በዚህ መንገድ ገናና ለሆነው ስሙ ተገቢ ፍርሃት እንዳለን እናሳያለን። የይሖዋ ስም ቃል በቃል ሲተረጎም “እንዲሆን የሚያደርግ” ማለት ነው። ይህም በተለይ ታላላቅ ዓላማዎቹን ፍጻሜ ላይ እንደሚያደርስ ያመለክታል። በመላው ጽንፈ ዓለም ላይ ያለውን ከፍተኛ ሥልጣኑንም ይወክላል። ለይሖዋ ታላቅ ግርማ አክብሮታዊ ፍርሃት በማሳየት ስናገለግለው ሟች ሰውን በመፍራት ከመንገዳችን አንወጣም። ልባችን አይከፋፈልም። ከዚህ ይልቅ ሕይወታችንን በእጁ የያዘውን የመጨረሻውን ከፍተኛ ፈራጅና የበላይ ገዢ የሆነውን ጌታ ይሖዋን የማያስደስት ማንኛውንም ነገር ለማድረግ እንፈራለን።—ኢሳይያስ 12:2፤ 33:22
8, 9. (ሀ) ‘የዚህ ዓለም ክፍል አለመሆን’ ምን ማለት ነው? (ለ) ‘በቲያትር መድረክ ላይ እንዳለን ሆነን የምንታይ’ በመሆናችን ምክንያት ምን እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብናል?
8 ነቀፋና ስደት ቢያጋጥመንም እንኳን በዙሪያችን ያለው ክፉ ዓለም ክፍል ባለመሆን የኢየሱስን የድፍረት ምሳሌ እንከተላለን። (ዮሐንስ 15:17-21) ይህ ማለት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ባሕታዊ መሆን አለባቸው ወይም ገዳም ገብተው መደበቅ አለባቸው ማለት አይደለም። ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም። በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ ደግሞ ወደ ዓለም ላክኋቸው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:15-18) ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም የመንግሥቱን እውነት እንድናውጅ ተልከናል። ኢየሱስ ሰው በቀላሉ ሊቀርበው የሚችል ነበር። ሰዎች እንዴት እንደሚያስተምር በማየት መንፈሳቸው ይነቃቃ ነበር። (ከማቴዎስ 7:28, 29፤ ከማቴዎስ 11:28, 29 እና ከዮሐንስ 7:46 ጋር አወዳድር።) እኛም እንዲሁ መሆን ይገባናል።
9 ተግባቢ በመሆን የምናሳየው የወዳጅነት አቀራረባችን፣ ጥሩ የሆነው አበጣጠራችንና አለባበሳችን፣ ደግነት ያለበትና ንጹህ የሆነው አነጋገራችን እኛም ሆንን መልዕክታችን ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ባላቸው ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝ ያደርገናል። ከአለባበስ ዝርክርክነት፣ ቅጥ ካጣ ከአስነዋሪ ልብስ፣ ወደ ዓለማዊ ተግባሮች ሊመራን ከሚችል ጓደኝነትና በዙሪያችን ባለው ዓለም ከምናየው መረን የለቀቀና ሥርዓት የለሽ ከሆነ አኗኗር መራቅ አለብን። ‘ለዓለምና ለመላእክት በቲያትር መድረክ ላይ እንዳለን ሆነን ስለምንታይ’ ምሳሌ የምናሳይ ክርስቲያኖች ሆነን ለማገልገልና ለመኖር በየቀኑ የ24 ሰዓት ግዳጅ አለብን። (1 ቆሮንቶስ 4:9፤ ኤፌሶን 5:1-4፤ ፊልጵስዩስ 4:8, 9፤ ቆላስይስ 4:5, 6) ይህን ለመፈጸም ልባችን አንድ መሆን አለበት።
10. ይሖዋ በቅዱስ አገልግሎቱ ልባቸውን አንድ የሚያደርጉትን የሚያስታውሳቸው እንዴት ነው?
10 የይሖዋን ስም በመፍራት፣ ታላቁን ዓላማውን በማሰላሰልና ሕይወታችንን በቅዱስ አገልግሎቱ በመሙላት ልባችንን አንድ የምናደርግ ሁሉ ይሖዋ ያስታውሰናል። “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና።” (2 ዜና መዋዕል 16:9) ሚልክያስ 3:16 በትንቢታዊ ሁኔታ ስለ ዘመናችን ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] የሚፈሩ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] አደመጠ፣ ሰማም፣ እግዚአብሔርንም [ይሖዋንም አዓት] ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።” ለይሖዋ በምናሳየው ይህን በመሰለ ጤናማ ፍርሃት ልባችን አንድ ይሁንልን!
የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት
11. የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ታማኝ ሆነው በሚቆሙለት ላይ የሚገለጸው እንዴት ነው?
11 የዳዊት ጸሎት እንዴት ያለ ልብን የሚነካ ነው! “አቤቱ አምላኬ [ይሖዋ አዓት] ሆይ፣ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፣ ለዘላለምም ስምህን አከብራለሁ፤ ምሕረትህ [ፍቅራዊ ደግነትህ አዓት] በእኔ ላይ ታላቅ ናትና፣ ነፍሴንም ከታችኛይቱ ሲኦል አድነሃታልና” በማለት ይቀጥላል። (መዝሙር 86:12, 13) ዳዊት በዚህ መዝሙር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ስለ ፍቅራዊ ደግነቱ ማለትም ስለ ታማኝ ፍቅሩ ይሖዋን አመሰገነ። ይህ ፍቅሩ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ የማይቻል በሚመስል ሁኔታ ውስጥ እንኳን ማዳን ይችላል። ሳኦል በምድረ በዳ ውስጥ ያሳድደው በነበረበት ወቅት ዳዊት በሞት አፋፍ ላይ እንደሚሄድ ያህል ተሰምቶት ይሆናል። ከታችኛው ሲኦል ማለትም ጥልቅ ከሆነው መቃብር ጋር ፊት ለፊት እንደተያየ ያህል ነበር። ይሖዋ ግን ከዚያ አዳነው! ይሖዋ በዚህ ዘመን ላሉት አገልጋዮቹም በተመሳሳይ ሁኔታ አስደናቂ በሆነ መንገድ ብዙ ጊዜ አድኗቸዋል። እንዲሁም እስከ ሞት ድረስ እንኳን በታማኝነት ፍጹም አቋማቸውን የጠበቁትን ኃይል ሰጥቶ አጽንቷቸዋል። ታማኝ ሆነው የሚቆሙ ሁሉ አስፈላጊ ከሆነም በትንሣኤ አማካኝነት ተገቢ ዋጋቸውን ያገኛሉ።—ከኢዮብ 1:6-12፤ ከኢዮብ 2:1-6, 9, 10፤ ከኢዮብ 27:5፤ ከኢዮብ 42:10፤ ከምሳሌ 27:11፤ ከማቴዎስ 24:9, 13፤ ከራእይ 2:10 ጋር አወዳድር።b
12. ቀሳውስት ትዕቢተኞችና ጨካኞች የሆኑት እንዴት ነው? ዋጋቸውስ ምን ይሆናል?
12 አሳዳጆችን በተመለከተ ዳዊት “አቤቱ፣ ዓመፀኞች [ትዕቢተኞች የ1980 ትርጉም] በእኔ ላይ ተነሥተዋል፣ የክፉዎችም [የጨካኞችም የ1980 ትርጉም] ማኅበር ነፍሴን ፈለጉአት፣ በፊታቸውም አላደረጉህም” በማለት ጮኸ። (መዝሙር 86:14) በዛሬው ጊዜ ያሉ አሳዳጆች የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትም ጭምር ናቸው። እነሱ አምላክን እናመልካለን በማለት ያለ እፍረት ይናገራሉ፤ ነገር ግን ቅዱስ ስሙን “ጌታ” በሚል የማዕረግ ስም ተክተውታል። እንዲሁም አምላክን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየትም ቦታ ላይ ያልተጠቀሰውን ምሥጢራዊ ሥላሴ እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል። እንዴት ያለ ትዕቢተኝነት ነው! ከዚህም በተጨማሪ የፖለቲካ ኃይላት የይሖዋ ምስክሮችን በሕግ እንዲያግዱና እንዲያስሩ ለማግባባት ይሞክራሉ። አሁንም በዓለም ዙሪያ ይህ ሁኔታ ያለባቸው አገሮች ቁጥር አስገራሚ ነው። እነዚህ የአምላክን ስም የሚያጐድፉ ቀሳውስት ጋለሞታ መሰል ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን ሌሎች ክፍሎች ጋር በአንድነት ብድራታቸውን ያጭዳሉ።—ራእይ 17:1, 2, 15-18፤ 19:1-3
13. ይሖዋ ጥሩነቱን ሲያሳውቅ ምን ምን ባሕርያትን አሳይቷል?
13 የዳዊት ጸሎት አስደሳች የሆነውን ጉልህ ልዩነት በመግለጽ “አቤቱ [ይሖዋ ሆይ፣ አዓት] አንተ ግን መሓሪና ርኅሩኅ አምላክ ነህ፤ መዓትህ የራቀ [ለቁጣ የዘገየህ፣ አዓት] ምሕረትህም [ፍቅራዊ ደግነትህም አዓት] እውነትህም የበዛ” በማለት ይቀጥላል። (መዝሙር 86:15) እንደነዚህ ያሉት የአምላካችን ባሕርያት በእርግጥም ዕጹብ ድንቅ ናቸው። እነዚህ ቃላት ሙሴ የይሖዋን ክብር ለማየት ወደጠየቀበት ወደ ሲና ተራራ ይወስዱናል። ይሖዋም “እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም [የይሖዋንም አዓት] ስም በፊትህ አውጃለሁ” በማለት መለሰለት። ይሁን እንጂ “ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም” በማለት ሙሴን አስጠነቀቀው። ከዚያ በኋላ ይሖዋ በደመና ውስጥ ወርዶ “እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር [ይሖዋ፣ ይሖዋ አዓት] መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና [ፍቅራዊ ደግነትና አዓት] እውነት” ነው ሲል አወጀ። (ዘጸአት 33:18-20፤ 34:5, 6) ዳዊት እነዚህን ቃላት በጸሎቱ ውስጥ ጠቀሳቸው። እንዲህ ያሉት የይሖዋ ባሕርያት ከማንኛውም ውበት ይበልጣሉ! ከራሳችን ተሞክሮ በመነሳት በእነዚህ መልካም ባሕርያት የታየውን የይሖዋን ጥሩነት አናደንቅምን?
“የጥሩነት ምልክት”
14, 15. ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ‘የጥሩነቱን ምልክት’ የሰጣቸው እንዴት ነው?
14 ዳዊት “ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም፤ ለባሪያህ ኃይልህን ስጥ፣ የሴት ባሪያህንም ልጅ አድን። ምልክትንም ለመልካም [የጥሩነትህን ምልክት አዓት] ከእኔ ጋር አድርግ፤ የሚጠሉኝ ይዩ ይፈሩም፣ አቤቱ [ይሖዋ ሆይ፣ አዓት] አንተ ረድተኸኛልና አጽንተኸኛልምና” በማለት የይሖዋን በረከት ለማግኘት እንደገና ለመነ። (መዝሙር 86:16, 17) ዳዊት ‘የይሖዋ የሴት ባሪያ ልጅ’ እንደመሆኑ እርሱም የይሖዋ ንብረት መሆን ያለበት መሆኑን ተቀብሏል። ሕይወታችንን ለይሖዋ የወሰንንና በአገልግሎቱ እንደ ባሪያ ሆነን የምንሠራ የሁላችን ሁኔታም እንዲሁ ነው። ይሖዋ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት የሚሰጠው አዳኝ የሆነ ጥንካሬም ያስፈልገናል። በዚህ ምክንያት አምላካችን ‘የጥሩነቱን ምልክት’ እንዲያደርግልን እንጠይቀዋለን። የይሖዋ ጥሩነት እስካሁን የተወያየንባቸውን መልካም ባሕርያት ሁሉ የያዘ ነው። በዚህ መሠረት ይሖዋ ምን ዓይነት ምልክት ወይም ማስተማመኛ ይሰጠናል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን?
15 ይሖዋ ‘የበጎ ስጦታ ሁሉ የፍጹምም በረከት ሁሉ’ ሰጪ እንዲሁም “ለሚለምኑት . . . መንፈስ ቅዱስን” በመስጠት በኩል ለጋስ የሆነ አምላክ ነው። (ያዕቆብ 1:17፤ ሉቃስ 11:13) መንፈስ ቅዱስ ዋጋ ሊተመንለት የማይችል እንዴት ያለ የይሖዋ ስጦታ ነው! ይሖዋ በስደት ጊዜ እንኳን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የልብ ደስታ ይሰጣል። በዚህ ምክንያት የኢየሱስ ሐዋርያት ሕይወታቸውን ለማጥፋት ሙከራ እየተደረገባቸው እያለ እንኳን አምላክን እንደ ገዢአቸው አድርገው ለሚታዘዙት መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጥ በደስታ ለማወጅ ችለዋል። (ሥራ 5:27-32) የመንፈስ ቅዱስ ደስታ “የጥሩነት ምልክት” ሆኖ ሳይለያቸው ሠርቷል።—ሮሜ 14:17, 18
16, 17. (ሀ) ይሖዋ ለጳውሎስና ለበርናባስ ምን የጥሩነቱን ምልክት ሰጣቸው? (ለ) በስደት ላይ ለነበሩት የተሰሎንቄ ሰዎች ምን ምልክት ተሰጣቸው?
16 ጳውሎስና በርናባስ በትንሹ እስያ በኩል ባደረጉት የሚስዮናዊ ጉዞ በመንገዳቸው ላይ ችግርና ከባድ ስደትም ጭምር አጋጥሟቸው ነበር። በጵስድያ አንጾኪያ በሚሰብኩበት ጊዜ አይሁዳውያን መልእክታቸውን አንቀበልም አሉ። በዚህ ምክንያት ፊታቸውን ወደ አሕዛብ አዞሩ። ታዲያ ምን ውጤት ተገኘ? “አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፣ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ።” ይሁን እንጂ አይሁዳውያን ሁከት ስላስነሱ ሚስዮናውያኑ ከአገራቸው ወጥተው ሄዱ። እነሱና አዲሶቹ አማኞች በዚህ ምክንያት ተስፋ ቆርጠው ይሆን? በጭራሽ! ከዚህ ይልቅ “ደቀ መዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።” (ሥራ 13:48, 52) ይሖዋ ይህንን የጥሩነቱን ምልክት ሰጣቸው።
17 ቆይቶም በተሰሎንቄ የነበረው አዲስ ጉባኤ ስደት ደረሰበት። ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ የማጽናኛ ደብዳቤ እንዲጽፍና በመከራ ጊዜ ላሳዩት ጽናት እንዲያመሰግናቸው አደረገው። “ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር” ተቀብለዋል። (1 ተሰሎንቄ 1:6) “የመንፈስ ቅዱስ ደስታ” መሐሪ፣ ለጋስ፣ ለቁጣ የዘገየና ፍቅራዊ ደግነቱና እውነቱ የበዛ ከሆነው አምላክ እንደተሰጠ ምልክት በመሆን እነሱን ማጠናከሩን ቀጠለ።
18. በምሥራቅ አውሮፓ ያሉት ወንድሞቻችን ለይሖዋ ጥሩነት አድናቆት ያሳዩት እንዴት ነው?
18 በቅርብ ጊዜያት ይሖዋ ታማኝ በሆኑ የምሥራቅ አውሮፓ ወንድሞቻችን ላይ ጥሩነቱን አሳይቷል። በዚህም ይጠሏቸው የነበሩ የቀድሞ አሳዳጆቻቸውን አሳፍሯል። ምንም እንኳን እነዚህ ውድ ወንድሞች በአሥርተ ዓመታት ከሚቆጠር ጭቆናቸው እፎይታ ያገኙት በቅርቡ ቢሆንም አብዛኞቹ ከባድ የኢኮኖሚ ችግር ስላለባቸው አሁንም ቢሆን መጽናት አስፈልጓቸዋል። ይሁን እንጂ ‘የመንፈስ ቅዱስ ደስታቸው’ ያጽናናቸዋል። አዲስ በተገኘው ነፃነታቸው ምስክርነቱን ለማስፋት ከመጠቀም ሌላ ምን የበለጠ ደስታ ሊኖራቸው ይችላል? ስለ ወረዳ ስብሰባና ስለተከናወኑት ጥምቀቶች በተደረገው ሪፖርት መሠረት ብዙ ሰዎች እያዳመጧቸው ነው።—ከሥራ 9:31 ጋር አወዳድር።
19. የመዝሙር 86:11ን ቃላት የራሳችን ልናደርጋቸው የምንችለው እንዴት ነው?
19 በዚህና ባለፈው ርዕሰ ትምህርት የተብራራው ሁሉ “አቤቱ ይሖዋ፣ አስተምረኝ . . . ስምህን ለመፍራት ልቤን አንድ አድርግልኝ” የሚለውን ልብ የሚነካውን የዳዊት ጸሎት ያስተጋባል። (መዝሙር 86:11 አዓት) የ1993 የዓመት ጥቅሳችን የሆኑትን እነዚህን ቃላት የራሳችን በማድረግ የመንግሥቱን ሥራዎች በፍጹም ልባችን ለመደገፍና ሉዓላዊ የበላይ ገዥ የሆነው የአንዱ አምላካችን የጌታ ይሖዋን የማያልቅ ጥሩነት በፍጹም ልባችን ለማድነቅ እንጣር።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረለት “ዘር” እንደመሆኑ መጠን የዳዊት መንግሥት ወራሽ ነው። ስለዚህ ቃል በቃልም ሆነ በመንፈሳዊ መንገድ “የዳዊት ልጅ” ነበር።—ዘፍጥረት 3:15፤ መዝሙር 89:29, 34-37
b ዘመናዊ ምሳሌዎችን ለማግኘት የይሖዋ ምስክሮችን የዓመት መጽሐፍ የ1974 እትም ገጽ 113-212፤ የ1985 እትም ገጽ 194-197፤ የ1986 እትም ገጽ 237-238፤ የ1988 እትም ገጽ 182-185፤ የ1990 እትም ገጽ 171-172፤ የ1992 እትም ገጽ 174-181 ያለውን ተመልከት።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ “አቤቱ ይሖዋ፣ አስተምረኝ” ብለን መጸለያችን ምን ያመለክታል?
◻ የይሖዋን ስም ለመፍራት ልባችንን አንድ ማድረግ ሲባል ምን ማለት ነው?
◻ ይሖዋ ታማኝ ሆነው ለሚቆሙለት ሁሉ ፍቅራዊ ደግነቱን የሚያሳያቸው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ “የጥሩነቱን ምልክት” የሚሰጠን እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የ1993 የዓመት ጥቅስ፦ “አቤቱ ይሖዋ፣ . . . አስተምረኝ፣ ስምህን ለመፍራት ልቤን አንድ አድርግልኝ።”—መዝሙር 86:11 አዓት
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በእውነት ውስጥ ቀጥ ብለው ለሚጓዙት አለትና ጠንካራ ምሽግ ነው
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሴንት ፒትስበርግ ሩስያ ውስጥ ሰኔ ላይ በተደረገው “ብርሃን አብሪዎች” የይሖዋ ምስክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ 46,214 ተሰብሳቢዎች ሲገኙ 3,256 ተጠምቀዋል። ‘የይሖዋን ጥሩነት’ ‘ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር’ እንዴት ግሩም በሆነ መንገድ እየተጠቀሙበት ነው!