ታላቁ ፈጣሪያችንና ሥራዎቹ
ምንኛ ታላቅ ነው! የነጎድጓድ ድምፅ ያላቸው የኢጉዋኩ ወይም የኒያጋራ ፏፏቴዎች፣ የአሪዞና ወይም የሀዋይ ታላላቅ ገደላማ ሸለቆዎችና እጹብ ድንቅ የሆኑት የኖርዌይ ወይም የኒውዚላንድ ውቅያኖስ መልካዎች፤ እነዚህ የተፈጥሮ ድንቆች በሙሉ ከፍተኛ የአድናቆት ድምፅ ያሰማሉ! ይህን እንጂ እነዚህ አስደናቂ ነገሮች እናት ተፈጥሮ በመባል የሚጠራው የአጋጣሚ ውጤቶች ብቻ ናቸውን? አይደሉም፣ ከዚህ እጅግ በጣም የላቁ ናቸው! ንጉሥ ሰሎሞን “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው” በማለት የጻፈለት አፍቃሪ ሰማያዊ አባት የሆነው ታላቅ ፈጣሪ አስደናቂ ሥራዎች ናቸው። (መክብብ 3:11) በእርግጥም ሰዎች ፈጣሪያችን አጽናፈ ዓለሙን የሞላባቸውን ታላላቅ ሥራዎች እስከዘላለም መርምረው ሊጨርሱ አይችሉም።
እንዴት ያለ ታላቅ ፈጣሪ ነው ያለን! ይህ ማንኛውንም ነገር ማድረግ የማይሳነው ኃያል አምላክ “ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ [በመናገሩ]“ ምንኛ ደስተኞች ልንሆን ይገባናል!(ዕብራውያን 1:2) ይህ ልጁ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ የአባቱን ፍጥረቶች ያደንቃቸውና ይወዳቸው ነበር። የአባቱን ዓላማዎች ለመግለጽና ለአድማጮቹ የማጽናኛ ቃላትን ለመናገር እነዚህን አስደሳች ፍጥረቶች አዘውትሮ ይጠቅስ ነበር። (ማቴዎስ 6:28-30፤ ዮሐንስ 4:35, 36) ብዙዎቹ አድማጮቹም አስደናቂ የሆኑት የፍጥረት ሥራዎች “በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ“ “በእምነት“ ለማስተዋል ችለዋል። (ዕብራውያን 11:3) ዕለታዊ ኑሮአችን እንዲህ ዓይነቱን እምነት ማንፀባረቅ ይኖርበታል።—ያዕቆብ 2:14, 26
የአምላካችን ፍጥረቶች በእርግጥም ታላላቅ ናቸው። የእርሱን ጥበብ፣ ኃይል፣ ጽድቁንና ፍቅሩን አስደናቂ በሆነ መንገድ ያንፀባርቃሉ። ለምሳሌ ያህል ቆየት ብሎ የተፈጠረው የሰው ልጅ አስደሳች በሆኑት የወቅቶች መፈራረቅ እንዲደሰት ምድራችንን ዘንበል አድርጎ በማስቀመጥ በፀሐይ ዙሪያ እንድትሽከረከር አድርጓታል። አምላክ “በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፣ ብርድና ሙቀት፣ በጋና ክረምት፣ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም” በማለት ተናግሯል። (ዘፍጥረት 8:22) በተጨማሪም አምላክ ምድራችንን ጠቃሚ በሆኑ ማዕድኖች ሞልቷታል። በተለይም በኋላ ለምድራዊ ሕይወት ሁሉ አስፈላጊ ክፍልና የሕይወት ደጋፊ የሆነውን ውኃ በብዛት አዘጋጅቶአል።
“የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል“ እያንዳንዳቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ርዝማኔ ባላቸው ስድስት ተከታታይ ’የፍጥረት ቀናት’ ውስጥ ምድርን ለሰው መኖሪያነት አዘጋጅቷታል። ለማየት ያስቻለን ብርሃን፣ የምንተነፍሰው አየር፣ የምንኖርበት ደረቅ ምድር (የብስ)፣ ለምለሙ ሣርና ቅጠል፣ የቀንና የሌሊት መፈራረቅ፣ ዓሦች፣ አዕዋፍ፣ እንስሳት ሁሉም በቅደም ተከተል በታላቁ ፈጣሪያችን የተፈጠሩት ለሰው አገልግሎትና ደስታ ተብሎ ነው። (ዘፍጥረት 1:2-25) በእርግጥም “አቤቱ፣ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፣ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች” በማለት በአድናቆት ከተናገረው መዝሙራዊ ጋር ድምፃችንን ልናስተባብር እንችላለን።—መዝሙር 104:24
የአምላክ ፍጥረት ታላቅ መደምደሚያ
ስድስተኛው የፍጥረት “ቀን“ ሊያበቃ ሲቃረብ አምላክ ሰውን ቀጥሎ ደግሞ ረዳቱ የሆነችውን ሴት ፈጠረ። ይህም አስቀድሞ ከተፈጠሩት ግዑዝ ፍጥረታት ሁሉ የሚበልጥ አስደናቂ የሆነ የምድራዊ ፍጥረታት ቁንጮና መደምደሚያ ነበር። መዝሙር 115:16 “የሰማያት ሰማይ ለእግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት“ በማለት ይነግረናል። በዚህም መሠረት ይሖዋ እኛን ሰብአዊ ነፍስ አድርጎ የሠራን በምድር ላይ ቀደም ብለው በተፈጠሩት ነገሮች ለመደሰትና ለመጠቀም እንድንችል ነው። በጣም ጥሩ ከሚባለው ካሜራ ይበልጥ የተወሳሰበና በዙሪያችን ያለውን በቀለማት የደመቀ ዓለም ሊመለከት ስለሚችለው ዓይናችን ምን ያህል አመስጋኞች መሆን ይኖርብናል! በንግግር፣ በሙዚቃና ባማረ የአዕዋፍ ዝማሬ ለመደሰት የሚረዳን ከማንኛውም ሰው ሠራሽ የድምፅ መስሚያ መሣሪያ የሚበልጥ ጆሮ አለን። ሁለገብ የሆነውን ምላሳችንን ጨምሮ አስደናቂ የሆነ የመነጋገሪያ መሣሪያ ተሠርቶልናል። የምላሳችን የመቅመሻ ሕዋሳት ከማሽተት ስሜታችን ጋር ተዋሕደው ተቆጥረው የማያልቁትን የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ቀምሰን በማጣጣም እንድንደሰት ያስችሉናል። በሚያፈቅረን ሰው እጅ መዳበስ ምንኛ አስደሳች ነው! በእርግጥ ፈጣሪያችንን መዝሙራዊው እንዳደረገው “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፣ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች“ በማለት ልናመሰግነው እንችላለን።—መዝሙር 139:14
የፈጣሪያችን ፍቅራዊ ደግነት
መዝሙራዊው “እናንት ሕዝቦች ለይሖዋ ምስጋና አቅርቡ፣ እርሱ ጥሩ ነውና . . . እርሱ ብቻውን ድንቅና ታላላቅ ነገሮችን ለሚያደርገው፤ ፍቅራዊ ደግነቱ ለዘላለም ነውና“ በማለት ጽፎአል። (መዝሙር 136:1-4 አዓት) ዛሬም ይህ ፍቅራዊ ደግነቱ አሁን ስንገልጻቸው ከቆየናቸው ፍጥረቶች ሁሉ ይበልጥ አስደናቂ የሆኑ ድንቅ ነገሮችን እንዲሠራ እየገፋፋው ነው። አዎን፣ ግዑዝ ፍጥረቶችን ከመሥራት ቢያርፍም እንኳን መንፈሳዊ ፍጥረታትን ከመፍጠር አላረፈም። ይህንንም የሚያደርገው በራሱ ላይ ለተሰነዘረው ስድብና የድፍረት ግድድር መልስ ለመስጠት ነው። እንዴት?
የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት አሸብራቂ በሆነው የኤደን ገነት ተቀምጠው ነበር። ይሁን እንጂ ሰይጣን የተባለው ከዳተኛ መልአክ ራሱን አምላክ አደረገና እነዚህን ሰብአውያን ባልና ሚስት በይሖዋ ላይ ወደ ተደረገው ዓመፅ መራቸው። አምላክም ፍትሕ በተሞላበት መንገድ ሞት ስለፈረደባቸው የሚወልዱአቸው ልጆች በሙሉ፣ ማለትም መላው የሰው ዘር ኃጢአተኛና ሟች ሆኖ መወለድ ጀመረ። (መዝሙር 51:5) ስለ ኢዮብ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ማንም ሰው ፈተና ቢደርስበት ለይሖዋ ታማኝ ሊሆን አይችልም ብሎ ሰይጣን ከአምላክ ጋር እንደ ተከራከረ ያመለክታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንና እስከ ዘመናችንም ድረስ ብዙ ታማኝ ሰዎች እንዳደረጉት ሰይጣን ፍጹም ውሸታም መሆኑን ኢዮብ አረጋግጧል። (ኢዮብ 1:7-12፤ 2:2-5, 9, 10፤ 27:5) ኢየሱስ ፍጹም ሰው በመሆን ተወዳዳሪ ለሌለው ፍጹም አቋም ጠባቂነት ምሳሌ ሆኖአል።—1 ጴጥሮስ 2:21-23
ስለሆነም ኢየሱስ “የዚህ ዓለም ገዢ [ሰይጣን]በእኔ ላይ አንዳች የለውም“ ሊል ችሎአል። (ዮሐንስ 14:30) ሆኖም እስከዚህ ጊዜ ድረስ “ዓለም በሞላው በክፉው ተይዟል።“ (1 ዮሐንስ 5:19) ሰይጣን የይሖዋን ሉዓላዊነት ትክክለኛነት ከተገዳደረ በኋላ እርሱ ራሱ በሰው ልጆች ላይ ያቋቋመው ግዛት ይሳካ እንደሆነ እንዲያሳይ 6,000 የሚያህሉ ዓመታት ተሰጥቶታል። እየተበላሹ የሚሄዱት የዓለም ሁኔታዎች እንደሚመሰክሩት የሰይጣን አገዛዝ በሚያሳዝን ሁኔታ ውድቅ ሆኖአል። አፍቃሪ አምላካችን ይሖዋ በቅርቡ ይህን ብልሹ የዓለም ኅብረተሰብ በማስወገድ ሕጋዊ መብቱ የሆነውን ሉዓላዊነቱን በምድር ላይ ያረጋግጣል። ይህም ሰላማዊና የጽድቅ አገዛዝን ለሚናፍቁ ሰዎች እንዴት ያለ አስደሳች እፎይታ ያመጣል!—መዝሙር 37:9-11፤ 83:17, 18
ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ አያበቃም። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን [የሰውን ዘር]እንዲሁ ወዶአልና“ በማለት ኢየሱስ በዮሐንስ 3:16 ላይ በተናገራቸው ቃላት መሠረትም የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት በተጨማሪ ይገለጻል። ይህ በምድር ላይ ለሰው ልጆች የሚመለስላቸው የዘላለም ሕይወት ተስፋ አዲስ ነገሮችን መፍጠርንም ያጠቃልላል። እነዚህ አዲስ ነገሮች ምንድን ናቸው? በመቃተት ላይ ያለውን የሰው ዘር ሊጠቅሙት የሚችሉትስ እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርታችን ይህን ያብራራል።