ገንዘብን መውደድ ምን ስህተት አለው?
ፖል እና ሜሪ በአንድ ደሀ የአፍሪካ አገር ውስጥ ሱፐር ማርኬት ለመክፈት ቻሉ።a ሌት ከቀን ጠንክረው በመሥራት በጣም ብዙ ገንዘብ አገኙ። ከጊዜ በኋላ ምቾትና ውበት ባላቸው የቤት ዕቃዎች የተሞላ ትልቅ ቤት በማግኘታቸው ሜሪ ልትኩራራ ቻለች። ፖል ደግሞ ምቾት ያለው መኪና ለመግዛት ችሎ ነበር።
አንድ ቀን የመንግሥት ተቃዋሚ የሆነ የአንድ ቡድን አባሎች ፖልን አነጋገሩት። “የንግድ ድርጅትህ ዓላማችንን ለመደገፍ በየወሩ [100 ዶላር] እንዲያዋጣ እንፈልጋለን” ሲሉ ጠየቁት። በፖለቲካዊ ትግል ውስጥ አንድን ወገን ደግፈው ለመቆም ባለመፈለጋቸው ፖልና ሜሪ በድፍረት አናዋጣም አሉ። በገለልተኛ አቋማቸው ምክንያት ከመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ያገኛሉ ብለው ጠረጠሯቸው። በአንድ የሳምንት መጨረሻ ቀን ላይ ፖልና ሜሪ ከከተማ ወጣ ብለው ሳሉ ሱቃቸው ተዘረፈ፤ መኪናቸውና የሚያምረው ቤታቸውም በእሳት ተቃጠሉ።
በእውነቱ የሚያሳዝን ታሪክ ነው፤ ነገር ግን ከዚህ ልንማር እንችላለንን? ሀብታም ለመሆን ሲሉ ጠንክረው የሠሩ ብዙ ሰዎች ሀብታቸውን የመዘረፍ አደጋ ላይደርስባቸው ይችል ይሆናል። ሆኖም የወደፊቱ ሁኔታቸው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ” ያለው ለምንድን ነው? — 1 ጢሞቴዎስ 6:9
ገንዘብን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አንድ እውነተኛ ክርስቲያን በእርሱ ወይም በእርሷ እርዳታ ለሚኖሩ የቤተሰብ አባሎች የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ማቅረብ አለበት (አለባት)። አንዳንድ ጊዜ እንደ ሥራ ማጣት ወይም የጤና ችግሮች ያሉ ሁኔታዎች ይህንን ማድረጉን ሊያከብዱት ይችላሉ። በሌላው በኩል ግን ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ ሆን ብሎ ቸል የሚል ሰው “ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።” — 1 ጢሞቴዎስ 5:8
በአንዳንድ የገጠር መንደሮች ሰዎች ኑሮአቸው በእርሻ ሥራ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ የራሳቸውን እህል ያመርታሉ፤ እንስሳትንም ያረባሉ። አንዳንዶች በእህል ለውጥ ወይም በሚሰጡት ግልጋሎት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ስለሚያገኙ በገንዘብ እምብዛም አይጠቀሙም። ይሁን እንጂ ቤተሰባቸውን ከእነርሱ በሚገኝ ገቢ የሚያስተዳድሩ አብዛኞቹ አባወራዎች ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን የሚያቀርቡት ተቀጥረው በመሥራት በሚያገኙት ደመወዝ ነው። ያገኙትንም ገንዘብ ለምግብና ለቤተሰቡ ደኅንነት አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ነገሮችን ለመግዛት ይጠቀሙበታል። በተጨማሪም በጥበብ ተቆጥቦ የተቀመጠ ገንዘብ በችግር ወይም በአደጋ ጊዜ መጠነኛ ጥበቃ ሊሰጥ ይችላል። ለምሳሌ ያህል የሕክምና ወጪዎችን ለመሸፈን ወይም ለቤቱ አስፈላጊ የሆኑ ጥገናዎች ለማድረግ ሊጠቅም ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስም በትክክል “ገንዘብ ጥላ [ጥበቃ አዓት] ናትና፤” እንዲሁም “ሁሉ ያለ ገንዘብ አይገኝም” በማለት ያለውን እውነታ የሚገልጸው ለዚህ ነው። — መክብብ 7:12፤ 10:19 የ1980 ትርጉም
ገንዘብ ብዙ ነገር ለማከናወን ስለሚያስችል ገንዘብ ያለውን ኃይል በተመለከተ እውን ያልሆነ አመለካከት የመያዝ አደጋ አለ። አንድ ክርስቲያን ይበልጥ አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ጋር ሲወዳደር የገንዘብ ጥቅም ውስን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገዋል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብን ከአምላካዊ ጥበብ ጋር በማወዳደር እንዲህ ይላል:- “የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና፤ የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን እንድትሰጥ ነው።” (መክብብ 7:12) በዚህ ረገድ አምላካዊ ጥበብ ከገንዘብ የሚበልጠው በምን መንገድ ነው?
ካለፈው ጊዜ የተገኘ ትምህርት
በ66 እዘአ በኢየሩሳሌም ውስጥ የተፈጸሙት ሁኔታዎች አምላካዊ ጥበብ ከገንዘብ ይልቅ ጥቅም እንዳለው የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። ወራሪውን የሮማ ሠራዊት መክተው ከመለሱ በኋላ በኢየሩሳሌም የነበሩ አይሁዶች ንግድ ለማካሄድ ጥሩ ጊዜ መጣ ብለው ያመኑ ይመስላል። አዲስ ለተገኘው ነፃነታቸው ክብር የራሳቸውን ገንዘብ ሠርተው ማውጣትም ጀመሩ። ሳንቲሞቻቸው “ለጽዮን ነፃነት” እንዲሁም “ቅድስቲቱ ኢየሩሳሌም” የሚሉ ቃላት በዕብራይስጥ ቋንቋ የታተመባቸው ነበሩ። በእያንዳንዱ አዲስ ዓመት “ሁለተኛው ዓመት”፣ “ሦስተኛው ዓመት” እና “አራተኛው ዓመት” የሚል መለያ ጽሑፍ የተቀረጸባቸው አዳዲስ ሳንቲሞችን ሠርተው አወጡ። እንዲያውም የመሬት ቁፋሮ ተመራማሪዎች 70 እዘአን የሚያመለክቱ “አምስተኛው ዓመት” የሚል ጽሑፍ የተቀረጸባቸው ብርቅ ሳንቲሞችን አግኝተዋል። አይሁዳውያን ክርስቲያኖችስ አዲሱን የአይሁዳውያን ገንዘብ የዘላቂ ነፃነት ምልክት አድርገው ተመልክተውት ነበርን?
አልተመለከቱትም፤ ምክንያቱም የጌታቸውን የጥበብ ቃላት በአእምሮአቸው ይዘው ነበረ። ኢየሱስ በ66 እዘአ ስለተፈጸመው የሮማውያን ወረራ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። ይህ ነገር በሚሆንበት ጊዜ ተከታዮቹ ‘ከኢየሩሳሌም እንዲወጡ’ መክሯቸው ነበር። (ሉቃስ 21:20–22) አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ይህን እንዳደረጉ ታሪክ ይመሰክራል። ኢየሩሳሌምን ለቅቀው በመውጣታቸው ምክንያት ዕቃ፣ ንብረት እንዲሁም የንግድ አጋጣሚዎችን በማጣት ለመጐዳት ፈቃደኞች እንደነበሩ ግልጽ ነው። ከአራት ዓመት በኋላ የሮም ወታደሮች ተመልሰው በመምጣት ከተማዋን ከበቧት።
የዓይን ምስክር የነበረው ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ በጻፈው መሠረት “በከተማዋ ውስጥ በጣም ብዙ ወርቅ ነበር።” ነገር ግን የገንዘብ ብዛት ኢየሩሳሌምን “ቤቶችንና ቤተሰቦችን በሙሉ ከጨረሰው” “እየከፋ የሚሄድ” ረሃብ አላዳናቸውም። አንዳንድ ነዋሪዎች የወርቅ ሳንቲሞችን በመዋጥ ከከተማው ለመሸሽ ሞክረው ነበር። ነገር ግን ገንዘቡን ለማውጣት ሲሉ ሆዳቸውን በሚቀድዷቸው ጠላቶቻቸው ተገድለዋል። ጆሴፈስ ሲያብራራ “ለባለጠጎች ከከተማ ውጭ መውጣታቸው በከተማው ውስጥ የመቆየታቸውን ያህል አደገኛ ሆኖባቸው ነበር። ከዳተኞች ናቸው በሚል ሰበብ ብዙዎቹ ገንዘባቸው ሊወስዱ በሚፈልጉ ሰዎች ተገድለዋል” ብሏል።
ከበባው ከተጀመረ ከስድስት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ኢየሩሳሌም ተደመሰሰች፤ ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚሆኑት ነዋሪዎቿም በረሃብ፣ በቸነፈርና በሰይፍ ሞቱ። የገንዘብ ፍቅር የብዙዎችን ዓይን አሳውሮ ወደ ጥፋትና ጉዳት ሲከታቸው የጥበብን ቃል መከተሉ ግን አይሁዳዊ ክርስቲያኖችን ከዚያ መዓት እንዲያመልጡ አስችሏቸዋል።
በታሪክ ውስጥ ገንዘብ በችግር ጊዜ ሰዎችን ለውድቀት የዳረገበት ወቅት ይህ ብቻ አይደለም። ገንዘብን መውደድ እንዴት ያለ ጨካኝ ጌታ ሊሆን ይችላል! (ማቴዎስ 6:24) ከዚህም በላይ በአሁኑ ጊዜ ያለህን ደስታ ሊወስድብህ ይችላል።
ገንዘብ ሊገዛው የማይችል ደስታ
ሀብታም የመሆን ምኞት ያፈዘዘው ሰው ብዙ ገንዘብ የማይጠይቁ ደስታዎችን እንዳይመለከት ዓይኖቹን ሊያሳውር ይችላል። ለምሳሌ ያህል በቤተሰብ መሃል የሚኖረውን ደስተኛ ግንኙነት፣ እውነተኛ ወዳጆችን፣ የተፈጥሮ ድንቆችን፣ ፀሐይ ስትጠልቅ የሚኖረውን አንፀባራቂ እይታ፣ አእምሮን የሚመስጠውን ነጐድጓድና መብረቅ፣ በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ፣ የእንስሳትን ቡረቃ ወይም ባልተበላሸ ደን ውስጥ የሚገኙትን አበቦችና ዛፎች ተመልከት።
እውነት ነው፤ ሀብታም የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ከላይ በተዘረዘሩት ደስ በሚያሰኙ ነገሮች ለመደሰት የበለጠ ጊዜ አላቸው። ነገር ግን አብዛኞቹ ሀብታቸው እንዳይጠፋ ለመጠበቅ ወይም በሀብታቸው ላይ ለመጨመር ስለሚሯሯጡ ጊዜ አይኖራቸውም። ነገሩ እንግዳ ቢመስልም የተዝናና ኑሮ ያላቸው ሰዎችም እንኳን አብዛኛውን ጊዜ ደስታ አይጨበጥላቸውም። ይህ ሁኔታ ዘመናዊ ተመራማሪዎችን ያስደንቃቸዋል። የገንዘብ ኃይል፣ ስለ አንድ አዚም የተደረገ ጥናት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ቶማስ ዋይዝማን እንዲህ ሲሉ ጠይቀዋል:- “ብዙ ሰዎች በከፍተኛ ጉጉት የሚፈልጉትና ለሁሉም ነገር መፍትሔ ይሆናል ብለው የሚያምኑበት ነገር ከተገኘ በኋላ ግን ያልጠበቁት ሁኔታ እንዲያውም የሚያሳዝን እስከመሆን የሚደርስበትን ምክንያት ማስረዳት የምንችለው እንዴት ይሆን?”
አንድን ሀብታም ደስታ ከሚያሳጡት ነገሮች አንዱ እውነተኛ ወዳጆቹን ለይቶ ለማወቅ አለመቻሉ ነው። ባለጠጋ የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን “ሀብት ሲበዛ የሚበሉት ይበዛሉ” ብሏል። (መክብብ 5:11) ብዙ ሀብታሞች ሀብታቸውን ለመጠበቅ ወይም የሀብታቸውን ብዛት ለመጨመር ሲታገሉ በሐሳብ ይሰቃያሉ። ይህም አብዛኛውን ጊዜ የደስታ እንቅልፍ ያሳጣቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ የባለጠጋ ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል” ሲል ይገልጻል። — መክብብ 5:12
የገንዘብ ፍቅር በቤተሰብና በወዳጆች መካከል ያለውን ግንኙነትም ሊጐዳ ይችላል፤ ምክንያቱም አንድን ሰው እንዲሰርቅ ወይም የወንጀል ድርጊት እንዲፈጽም ሊፈትነው ይችላል። ገንዘብን የሚወዱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ቁማር ይጫወታሉ። የሚያሳዝነው ለአንድ ተጨማሪ ጊዜ ቁማር ለመጫወት ያላቸው ከፍ ያለ ጉጉት ብዙዎችን ዕዳ ውስጥ ከቷቸዋል። አንድ ደቡብ አፍሪካዊ የሥነ አእምሮ ሐኪም “በአብዛኛው ሱሰኛ ቁማርተኞች እኔ ዘንድ በሚመጡበት ጊዜ ሥራቸውን፣ ንግዳቸውን፣ ቤታቸውን ያጡና አብዛኞቹ ቤተሰቦቻቸው ትተዋቸው የሄዱ ስለሆኑ እርዳታ ሊደረግላቸው ከሚችልበት ነጥብ ያለፉ ናቸው።” “የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኩል ግን ሳይቀጣ አይቀርም” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ማስጠንቀቂያ ምንኛ እውነት ነው። — ምሳሌ 28:20
“ወደ ሰማይ እንደሚበርር . . . ለራሱ ክንፍ ያበጃልና”
ገንዘብን መውደድ አደገኛ የሆነበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ሰብዓዊ መንግሥታት ገንዘብ በዓለም ዙሪያ የተረጋጋ ዋጋ እንደያዘ እንዲቀጥል ለማድረግ ወይም ለመተባበር አለመቻላቸው ነው። የሥራ እጦትን፣ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆልንና የአክሲዮን ገበያ ውድቀትን ለመከላከል አልቻሉም። ማጭበርበር፣ ስርቆትና የገንዘብ ዋጋ ማጣት “ባለጠጋ ለመሆን አትድከም፤ የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው። በእርሱ ላይ ዓይንህ ብታዘወትርበት ይጠፋል፤ ባለጠግነት ወደ ሰማይ እንሚበርር እንደ ንስር ለራሱ ክንፍ ያበጃልና” የሚሉትን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቃላት እውነተኝነት ያጎላሉ። — ምሳሌ 23:4, 5
የገንዘብ ዋጋ ማሽቆልቆል። በእርግጥ ይህ ድሀ በሆኑ አገሮች ብቻ የተወሰነ ችግር አይደለም። በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የገንዘብ ዋጋ በታላቅ ፍጥነት ማሽቆልቆሉ በኢንዱስትሪ የበለጸጉትን የመካከለኛውን አውሮፓ አገሮች አጥቅቶ ነበር። ለምሳሌ ያህል ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት አንድ የጀርመን ማርክ ከአንድ የብሪታንያ ሽልንግ፣ ከአንድ የፈረንሳይ ፍራንክ ወይም ከአንድ የጣልያን ሊሬ ጋር እኩል ነበር። ከአሥር ዓመታት በኋላ ሽልንጉ፣ ፍራንኩና ሊሬው ከ1,000,000,000,000 ማርክ ጋር ከሞላ ጎደል እኩል ሆኑ። እየጨመረ የሚሄድ የገንዘብ ዋጋ ማሽቆልቆል በበለጸገው ኅብረተሰብ ላይ ምን ውጤት አለው? “በ1920ዎቹ መጀመሪያ በጦርነቱ በተሸነፉት ማዕከላዊ ኃይላት ላይ የደረሰውን ነገር እንደ መለኪያ አድርግን ብንወስድ የገንዘብ ሥርዓት መውደቅ በአብዛኛው በፍርሃት ምክንያት የሚመጡትን እንደ ስግብግብነት፣ ሕገ ወጥነት፣ ደስታ ማጣትና ጥላቻ ያሉ ሁኔታዎችን ያስከትላል። የትኛውም ኅብረተሰብ ቢሆን በዚህ ሁኔታ ሳይሽመደመድና ሳይለወጥ ሊያመልጥ አይችልም” ሲሉ አዳም ፈርገሰን ገንዘብ ሲሞት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ አትተዋል።
ጀርመን በ1923 የገንዘቧን ዋጋ በድንገት በመለወጥ 12ቱን ዜሮዎች አጥፍታ የበፊቱ 1,000,000,000,000 ማርክ ከአንድ አዲስ ማርክ ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን አደረገች። ይህ እርምጃ የገንዘቡን ዋጋ ማሽቆልቆል አቆመው ነገር ግን ሌላ ከባድ ጣጣ አመጣ። ፈርገሰን ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ:- “የገንዘብ መረጋጋትን በአዲስ መልክ ማዋቀሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲከስሩ፣ በሚልዮን የሚቆጠሩት መተዳደሪያቸውን እንዲዘረፉና በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎችን ደግሞ ተስፋቸው እንዲጠፋ በማድረጉ በተዘዋዋሪ መንገድ ሙሉው ዓለም የከፋ ዋጋ እንዲከፍል አስገድዷል።” ጸሐፊው በአእምሯቸው የያዙት “አስከፊ ዋጋ” የናዚስም እንቅስቃሴ መነሳትና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንደሆነ ለመረዳት አያስቸግርም።
ባለፉት ጊዜያት ባንክ ውስጥ የተቀመጠ በጣም ብዙ ገንዘብ ብዙ ሰዎችን ለችግር ጊዜ ሊደርስላቸው አለመቻሉ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ባለበት በዚህ ጊዜ መንፈስን የሚሰብር ማስጠንቀቂያ ነው። የአምላክ ልጅ ራሱ ገንዘብ ዋጋ እንደሚያጣ አስጠንቅቆ ነበር፤ በእርግጥም ይህ ብዙ ጊዜ ተፈጽሟል። (ሉቃስ 16:9) ነገር ግን ተወዳዳሪ የማይገኝለትና ከምን ጊዜውም ይበልጥ ሰፊ የሆነው የገንዘብ ውድቀት የሚመጣው ይሖዋ አምላክ በዚህ ክፉ ዓለም ላይ ፍርድ በሚያስፈጽምበት ጊዜ ይሆናል። “በቁጣ ቀን ሀብት አትረባም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች።” — ምሳሌ 11:4
እንግዲያውስ እያንዳንዳችን በእውነተኛ ወዳጆቻችን በይሖዋ አምላክና በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የጽድቅ አቋም ጠብቀን ለመኖር መጣራችን በጣም አስፈላጊ አይደለምን?
የዘላቂ ደስታ ምንጭ
በመግቢያው ላይ የተጠቀሱት ፖልና ሜሪ የይሖዋ ምስክሮች ነበሩ። ለብዙ ዓመታት በሙሉ ጊዜ የወንጌላዊነት ሥራ ይካፈሉ ነበር። ይሁን እንጂ ሀብታም ለመሆን ያላቸው ፍላጎት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘትን እንዲያቆሙ አደረጋቸው። ለሕዝብ በሚደረገው አገልግሎት እምነታቸውን ማካፈልንም አቆሙ። ነገር ግን ከጊዜ በኋላ ነቁ። ንብረታቸውን ከተዘረፉና ቤታቸውም ከወደመ በኋላ “በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ እንደ ጢስ በኖ ለሚጠፋ ነገር ጊዜዬንና ኃይሌን ሁሉ ማጥፋቴ ምን ያህል ሞኝነት እንደነበረ አሁን ለማየት ችያለሁ” በማለት ሜሪ ተናግራለች። እነዚህ ባልና ሚስት መመለስ ወደማይችሉበት ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት አንድ ትምህርት ለመማር መቻላቸው ያስደስታል። አዎን፣ ገንዘብን መውደድ ሊያስከትል የሚችለው ትልቁ ጉዳት አንድን ሰው ከይሖዋ አምላክና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለውን ተቀባይነት ያለው ዝምድና ማሳጣቱ ነው። ያለነዚህ ወዳጆች እርዳታ በዚህ ክፉ ዓለም ላይ ከሚመጣው ጥፋት ተርፈን አምላክ ቃል ወደገባልን አዲስ የጽድቅ ዓለም ለመግባት ምን ዓይነት ተስፋ ሊኖረን ይችላል? — ማቴዎስ 6:19–21, 31–34፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
ስለዚህ ራስህን የምትመለከተው ሀብታም አድርገህም ሆነ ድሀ ገንዘብን የመውደድ ዝንባሌ እንዳያድርብህ ራስህን ጠብቅ። ከሁሉ የሚበልጠውን ሀብት ማለትም በይሖዋ አምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አቋም ላይ ለመድረስና አቋምህን አጥብቀህ ለመያዝ ትጋ። ይህንንም ልታደርግ የምትችለው “መንፈሱና ሙሽራይቱም:- ና ይላሉ። የሚሰማም:- ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” ለሚለው አስቸኳይ ጥሪ ያልተቆጠበ ትኩረት በመስጠት ነው። — ራእይ 22:17
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የተጠቀምነው እውነተኛ ስማቸውን አይደለም።
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአይሁዳውያን ዓመፅ ወቅት የተሠሩት “ ሁለተኛው ዓመት” የሚል የተቀረጸ ጽሑፍ የነበራቸው ሳንቲሞች ሁለት ገጽታዎች
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.