ክርስቲያኖች የዕረፍትን ቀን ማክበር አለባቸውን?
ሰኔ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ዝናባማ ወር ሆኖ ነበር። በዚህ ምክንያት በ1991ዱ የዊምብሌደን የቴኒስ ሻምፒዮና ውድድር ወቅት ለዘመናት የቆየ አንድ ዓለማዊ ባሕል ተጣሰ። የባከነውን ጊዜ ለማካካስ ሲባል በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የቴኒስ ግጥሚያዎች እሁድ ቀን ተከናወኑ። እንዲህ ካሉ ሕጉን ከሚጥሱ አጋጣሚዎች በስተቀር በእንግሊዝና በሌሎችም አገሮች እሁድ የተቀደሰ የዕረፍት ቀን ሆኖ ቆይቷል።
አንዳንድ ሰዎች የተለየ የዕረፍት ቀን ያከብራሉ። በዓለም ዙሪያ ያሉ አይሁዳውያን ዓርብ ፀሐይ ከጠለቀችበት ጊዜ አንስቶ ቅዳሜ ዕለት ጀንበር እስከምትጠልቅበት ጊዜ ያለውን ወቅት አጥብቀው ያከብራሉ። በሰንበት ቀን የእስራኤል አየር መንገድ በረራ አያደርግም፤ እንዲሁም በአንዳንድ ከተሞች የሕዝብ ትራንስፖርት የለም። በኢየሩሳሌም አንዳንድ ወግ አጥባቂዎች ሕጋዊ አይደለም ብለው የሚያስቡትን የትራፊክ እንቅስቃሴ ለማገድ ሲሉ የተወሰኑ መንገዶች ያስዘጋሉ።
በርካታ ሃይማኖቶች ሳምንታዊውን የዕረፍት ቀን ወይም ሰንበትን እስካሁን በማክበር መቀጠላቸው አንዳንድ ጥያቄዎችን ያስነሳል። ሰንበትን ማክበር ያለባቸው አይሁዶች ብቻ ናቸውን? አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች የተለየ ሳምንታዊ የዕረፍት ቀን ሊያደርጉ የቻሉት ለምንድን ነው? ሳምንታዊውን የዕረፍት ቀን ማክበር ዛሬም ከእኛ የሚፈለግ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግዴታ ነውን?
ሰንበት ሁልጊዜ የነበረ ነገር ነውን?
በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ ሰንበት ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የምናገኘው በዘጸአት መጽሐፍ ውስጥ ነው። እስራኤላውያን በበረሃ ሳሉ መና የተባለ ተዓምራዊ ምግብ ከይሖዋ ዘንድ ያገኙ ነበር። ሰባተኛው ቀን ማንኛውንም ሥራ መሥራት ክልክል የነበረበት “የይሖዋ ሰንበት” ስለነበረ በየሳምንቱ በስድስተኛው ቀን የድርሻቸውን ሁለት እጥፍ ይሰበስቡ ነበር። — ዘጸአት 16:4, 5, 22–25
ከዚህ በተጨማሪ እስራኤላውያን የሰንበት ቀን የተሰጣቸው በግብጽ ምድር ባሮች እንደነበሩ እንዲያስታውሳቸው ነበር። እንዲህ ዓይነቱን ሕግ በፊትም የሚያከብሩት የነበረ ነገር ቢሆን ኖሮ ይህ ማስታወሻ ባላስፈለጋቸውም ነበር። ስለዚህ ሰንበትን የሚመለከቱ ሕግጋት የተሰጡት ለእስራኤላውያን ብቻ ነበር። — ዘዳግም 5:2, 3, 12–15
ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸውና ከባድ ልማዶች
የሙሴ ሕግ ሰንበትን በተመለከተ ዝርዝር መመሪያ ስለማይሰጥ ራቢዎች [የአይሁድ መምህራን] ለብዙ መቶ ዘመናት በተለይ በሰንበት ቀን ማንኛውንም ሥራ መሥራትን የሚከለክሉ በጣም ብዙ ሕግጋት አውጥተዋል። በሚሽና መሠረት የተከለከሉ ሥራዎች እንደ መስፋት፣ መጻፍና የእርሻ ሥራ ባሉ በ39 ዋና ዋና ክፍሎች ተመድበዋል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ አይደሉም። ኢንሳይክሎፒድያ ጁዳይካ ከሚሽና በመጥቀስ “ቅዱስ ጽሑፉ ስለጉዳዩ የሚገልጸው ጥቂት ሆኖ ሳለ የወጡት ሕጎች ግን ብዙ ናቸው፤ ነገሩ ተራራን በአንዲት ጸጉር እንደማንጠልጠል ያህል ነው” ሲል አስታውቋል።
“በሰባተኛው ቀን ማንም ከስፍራው አይሂድ” የሚለውን ትዕዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ ሲባል መጓዝ የሚፈቀድበት የመጨረሻው ርቀት ተወስኖ ነበር። ይህም “የሰንበት የጉዞ ወሰን” ተብሎ ይጠራ ነበር። በአንዳንድ ምንጮች መሠረት ይህ ወሰን እስከ ሁለት ሺህ ክንድ ወይም 900 ሜትር ይደርስ ነበር። (ዘጸአት 16:29) ይሁን እንጂ ይህን ደንብ ለማለፍ የሚያስችል ረቂቅ ዘዴ ነበረ። ይኸውም:- ከሰንበት በፊት ባለው ምሽት ምግቦችን ከቤቱ ሁለት ሺህ ክንድ አርቆ በማስቀመጥ ነው። ይህ ቦታ የቤተሰቡ መኖሪያ ቤት ቅጥያ ተደርጎ ይወሰድና ከዚያ ቦታ አንስቶ ሌላ ሁለት ሺህ ክንድ በመቁጠር እስከዚያ ድረስ መሄድ ይቻል ነበር።
ከእነዚህ ሰው ሠራሽ እገዳዎች ብዙዎቹ በኢየሱስ ዘመን ይሠራባቸው ነበር። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ በእርሻ መካከል ሲያልፉ እሸት እየቀጠፉ በመብላታቸው የሃይማኖት መሪዎች ደቀ መዛሙርቱን ነቅፈዋቸው ነበር። እሸት መቅጠፍ እንደ ማጨድ፣ እሸቱን ማሸት ደግሞ እንደ መከካት ወይም መፍጨት አድርገው በመቁጠር የሰንበትን ሕግ ጥሰዋል በማለት ከሰሷቸው። የይሖዋን ሕግ መንፈስ በማይገባ ሁኔታ በማቅረባቸውና የራሳቸውን ከመጠን ያለፈ ጥብቅ አመለካከት በመያዛቸው ምክንያት ኢየሱስ በብዙ አጋጣሚዎች አውግዟቸዋል። — ማቴዎስ 12:1–8፤ ሉቃስ 13:10–17፤ 14:1–6፤ ዮሐንስ 5:1–16፤ 9:1–16
ከቅዳሜ ወደ እሁድ የተቀየረው ሰንበት
“እሁድ አምላክን በሙሉ ልብ ለማገልገል የተወሰነ ዕለት ይሆናል።” ይህ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያወጣችው ሰንበትን የሚመለከት አራተኛ ትዕዛዝ ነው። በቅርቡ የታተመው ለጎልማሶች የሚሆን መንፈሳዊ ትምህርት የተባለው የፈረንሣይኛ መጽሐፍ ሲያብራራ እንዲህ ይላል:- “የክርስቲያኖች እሁድ የሚከበረው ከሰንበት በኋላ ማለትም በስምንተኛው ቀን ላይ ነው። በሌላ አነጋገር የፍጥረት መጀመሪያ በሆነው ቀን ላይ ነው። የሰንበትን እገዳዎች የያዘ ቢሆንም በክርስቶስ የማለፍ በዓል ላይ ያተኮረ ነው።” ከቅዳሜ ወደ እሁድ የተደረገው የሰንበት ዝውውር እንዴት ሊከሰት ቻለ?
ምንም እንኳን እሁድ ኢየሱስ ከሞት የተነሳበት ዕለት ቢሆንም ይህ ቀን ለጥንት ክርስቲያኖች ልክ እንደ ሌላው ቀን የሥራ ቀን ነበር። ነገር ግን በሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ምክር ቤት (ከአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ አጋማሽ እስከ ማለቂያው) የተደረገው ውሳኔ የአይሁዳውያን የቅዳሜ ሰንበት ከጊዜ በኋላ በእሁድ “ክርስቲያናዊ” ሰንበት እንደተተካ ገልጿል። ይህ ሕግ “ክርስቲያኖች አይሁዶችን እንዳይመስሉና [በአይሁዳውያን] ሰንበት ሥራ እንዳይፈቱ የሚከለክልና የጌታ ቀን [እርሱ ትንሣኤ ያገኘበት የሳምንቱ ቀን] በክርስቲያናዊ መንገድ እንዲከበር የሚያዝዝ ነበር።” ከዚያ ጊዜ አንስቶ የሕዝበ ክርስትና ደጋፊዎች ቅዳሜ ዕለት ሲሠሩ እሁድ ዕለት ግን ከመሥራት ተቆጥበዋል። በኋላ እሁድ ዕለት ቅዳሴ በሚደረግበት ሰዓት በቤተ ክርስቲያን እንዲገኙ ይፈለግባቸው ጀመር።
ወዲያው በመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ድጋፍ ሕዝበ ክርስትና ባለችባቸው አገሮች በሙሉ እሁድ ዕለት መሥራት ተከለከለ። ከስድስተኛው መቶ ዘመን በኋላ ይህንን ሕግ የተላለፉ ሰዎች በገንዘብ ይቀጡ ነበር ወይም ይገረፉ ነበር። በሬዎቻቸውም ይወረሱ ነበር። ንሥሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች አልፎ አልፎ ወደ ባርነት ደረጃ ዝቅ ሊደረጉ ይችሉ ነበር።
በእሁድ ቀኖች ቢሠሩ ተቀባይነት ከሚኖራቸው ሥራዎች ጋር የተያያዙ ሕግጋት የአይሁዳውያንን ሰንበት የሚቆጣጠረውን ባሕል ያህል የተወሳሰቡ ናቸው። የካቶሊክ መንፈሳዊ ትምህርት መዝገበ ቃላት የተባለው መዝገበ ቃላት የቤተ ክርስቲያንን ድንጋጌዎች መጎልበት በተመለከተ እንዲሁም ክልክል ከሆኑት ሥራዎች መካከል አገልግሎት ሰጪ ሥራዎች፣ የእርሻ ሥራን፣ ሕጋዊ ጉዳዮችን፣ ገበያዎችንና አደንን በመጥቀስ ረዘም ያለ ማብራሪያ ይሰጣል።
የሚያስገርመው ግን ለእነዚህ እገዳዎች መሠረት የተደረገው የአይሁዳውያን ሰንበት መሆኑ ነው። አዲሱ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ ንጉሠ ነገሥት ሻርላማኝ የእሁድ ቀኖችን በተመለከተ ያወጣቸውን ሕጎች እንዲህ ሲል ይጠቅሳል:- “ሰንበትን የማክበሩ ሐሳብ በቅዱስ ጀሮም በጥብቅ የተወገዘ መሆኑና በ538 [እዘአ] በተደረገው የኦርልየንስ ስብሰባ የይሁዲነት ትምህርት እንደሆነና ክርስቲያናዊ እንዳልሆነ ተደርጎ የተከለከለ መሆኑ ማንኛውም የጉልበት ሥራ በእሁድ ቀን እንዳይሠራ በሚያግደው በ789ኙ [እዘአ] የሻላማኝ ድንጋጌ ውስጥ ሁኔታው [አሥርቱን ትዕዛዛት] የሚጥስ ነው ተብሎ በግልጽ ተጠቅሷል።” ስለዚህ ምንም እንኳን ዓለማዊው መንግሥት እሁድን የዕረፍት ቀን አድርጎ መወሰኑ ቤተ ክርስቲያኒቱን ቢያስደስታትም ቤተ ክርስቲያኒቱ መንግሥት የዕረፍት ቀኑን ድንጋጌ እሷ አልቀበልም ያለችውን ሰንበትን የሚመለከተውን የሙሴ ሕግ መሠረት እንዲያደርግ ፈቅዳለች።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አቋም
ከአያሌ መቶ ዘመናት በፊት በርካታ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና በተለይም አውግስቲን ሰንበት ለአይሁዳውያን የተጠበቀ ጊዜያዊ ዝግጅት መሆኑን ገልጸው ነበር። እነዚያ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይህን ሲሉ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ሰንበት በኢየሱስ መሥዋዕት የተደመሰሰው የሕጉ ቃል ኪዳን ክፍል ነበር በማለት የሚናገሩትን ሐሳብ በቀላሉ መቀበላቸው ነበር። — ሮሜ 6:14፤ 7:6፤ 10:4፤ ገላትያ 3:10–14, 24, 25
የፈረንሳይኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በነዚህ አባቶች ዘመን የነበሩት ኦስካር ኩልማን የተባሉ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ምሑር “ኢየሱስ ስለመጣ፣ ስለሞተና ትንሣኤ ስላገኘ የብሉይ ኪዳን በዓላት አብቅተዋል። እነዚህን በዓላት መጠበቅ ‘ማለት ኢየሱስ በጭራሽ እንዳልመጣ አድርጎ ወደ ብሉይ ኪዳን ቃል ኪዳን መመለስ ማለት ይሆናል’ ” ሲሉ ማመናቸውን ጠቅሷል። ይህንን ተገቢ ነጥብ ስንመለከት ሰንበትን የማክበር ግዴታ ትክክል ነው ብሎ መናገር ይቻላልን?
በዛሬው ጊዜ የካቶሊክ ጸሐፊዎች ባጠቃላይ “ከሳምንቱ በመጀመሪያ ቀን” (እሁድ) ጳውሎስ ከባልንጀሮቹ ጋር ተገናኝቶ አብረው እንደበሉ የሚናገረውን ሥራ 20:7ን ድጋፍ አድርገው ለመጥቀስ ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ይህ በቀላሉ ነገሩን በዝርዝር ለመግለጽ የቀረበ ነጥብ ብቻ ነው። በዚህ ጥቅስም ሆነ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ይህ ዘገባ ክርስቲያኖች ሊከተሉት እንደሚገባ የሚያሳይ ምሳሌ መሆኑን የሚያመለክት ምንም ሀሳብ የለም። ነገሩ በጭራሽ ግዴታ አልነበረም። አዎን፣ እሁድን እንደ ሰንበት አድርጎ ማክበሩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የለውም።
ታዲያ ክርስቲያኖች ያላቸው ዕረፍት ምንድን ነው?
ምንም እንኳን ክርስቲያኖች ሳምንታዊውን የዕረፍት ቀን የማክበር ግዴታ ባይኖርባቸውም ሌላ ዓይነት ዕረፍት እንዲያከብሩ ግን ተጋብዘዋል። ጳውሎስ ክርስቲያን ለሆኑ አይሁዳዊ ባልንጀሮቹ ይህንን ሲያብራራላቸው እንዲህ ብሏል:- “እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል። . . . እንግዲህ . . . ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ።” (ዕብራውያን 4:4–11) እነዚህ አይሁዶች ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት የሙሴን ሕግ የሚችሉትን ያህል በጥንቃቄ ይጠብቁ ነበር። አሁን ጳውሎስ ከሞተ ሥራቸው “ዕረፍት” እንዲያደርጉ እንጂ በሥራ መዳንን ለማግኘት እንዲጣጣሩ አላበረታታቸውም። ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጆች በአምላክ ዓይኖች ጻድቃን ሊሆኑ የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ በሆነው በኢየሱስ መሥዋዕት ማመን አለባቸው።
እኛስ በዛሬው ጊዜ አምላክ ላለው አመለካከት ተመሳሳይ አክብሮት ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? የይሖዋ ምስክሮች እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ ምክንያታውያን በመሆን በብዙ አገሮች የሚሠራበትን ከሰብዓዊ ሥራዎች የሚታረፍበት ሳምንታዊ የዕረፍት ቀን በመኖሩ ይደሰታሉ። ይህም ከቤተሰብ ጋር ሆነው ለመጫወትና ለመዝናናት ጊዜ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ጊዜ በተለይ ሌሎች ክርስቲናዊ ሥራዎችን ይበልጥ ለመከታተል የሚያስችል ጊዜ ሆኖ ተገኝቷል። (ኤፌሶን 5:15, 16) እነዚህም ስብሰባዎችንና ጎረቤቶቻቸውን በመጎብኘት አማኝ የሆኑ የሰው ዘሮች በሙሉ ስለሚያገኙት እየቀረበ ስላለው ዓለም አቀፍ የሰላም ጊዜ የሚናገረውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልዕክት ለማካፈል ሲሉ በሕዝባዊ አገልግሎት መካፈልን ይጨምራሉ። ስለዚህ ጉዳይ ለማወቅ የሚፈልጉ ከሆነ የይሖዋ ምስክሮች ቅዳሜ፣ እሁድ ወይም በሌላ የሳምንቱ ቀን ላይ ሊረዱዎት ፈቃደኞች ናቸው።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የአይሁዳውያንን ወጎች ሳይሆን የሰንበትን ሕግ ሙሉ በሙሉ ጠብቆታል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች ከሰብዓዊ ሥራቸው በሚያርፉበት ጊዜ ክርስቲያናዊ ሥራዎችን መሥራታቸው የመንፈስ እርካታን አምጥቶላቸዋል