የዓለምን ብርሃን እየተከተሉ ያሉት እነማን ናቸው?
“በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ [ታበራላችሁ። አዓት ]” — ፊልጵስዩስ 2:15
1. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አስመሳይ ሃይማኖታዊ መብራቶች ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ታላቅ ብርሃን” እንዲሁም “የዓለም ብርሃን” በማለት ማንነቱን በግልጽ አሳውቋል። (ኢሳይያስ 9:2፤ ዮሐንስ 8:12) ሆኖም በምድር በነበረበት ጊዜ እርሱን የተከተሉት ሰዎች ከጠቅላላው ሕዝብ ብዛት አንፃር ሲታዩ አነስተኛ ነበሩ። አብዛኞቹ አስመሳይ መብራቶችን ለመከተል መረጡ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እነዚህ አስመሳይ መብራቶች የጨለማ ነበሩ። የአምላክ ቃል ስለነዚህ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፣ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።” — 2 ቆሮንቶስ 11:13–15
2. ኢየሱስ በሰዎች ላይ ለመፍረድ መሠረት የሚሆነው ነገር ምንድን ነው አለ?
2 ስለሆነም ይህ ብርሃን አስደናቂ የመሆኑን ያህል ፈላጊዎቹ ሁሉም ሰዎች አይደሉም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፣ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም።” — ዮሐንስ 3:19, 20
ጨለማን የሚወዱ
3, 4. በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ብርሃኑን ለመከተል አለመፈለጋቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?
3 ይህ ሁኔታ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እንዴት እንደተፈጸመ ተመልከት። መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጡ አስደናቂ ተአምራት እንዲያደርግ የሚያስችል ሥልጣን አምላክ ለኢየሱስ ሰጥቶት ነበር። ለምሳሌ ያህል ዕውር ሆኖ የተወለደ የአንድ ሰው ዓይን በአንድ የሰንበት ቀን እንዲበራ አደረገ። እንዴት ያለ አስደናቂ የምሕረት ድርጊት ነበር! ሰውየው ምን ያህል አመስግኖ ይሆን! ለመጀመሪያ ጊዜ ለማየት ቻለ! ይሁን እንጂ የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስ ይህንን መልካም ድርጊት በመፈጸሙ ምን አሉ? ዮሐንስ 9:16 እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ [ስለ ኢየሱስ]:- ይህ ሰው ሰንበትን አያከብርምና ከእግዚአብሔር አይደለም አሉ።” ልባቸው ምን ያህል ጠማማ ነበር! በጣም አስደናቂ ፈውስ ተፈጽሟል። ነገር ግን ዕውር ለነበረው ሰው ደስታቸውን ከመግለጽና ፈዋሹንም ከማድነቅ ይልቅ ኢየሱስን አወገዙት! ይህንን በማድረጋቸውም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ መግለጫ በሆነው ሥራ ላይ በግልጽ ኃጢአት ሠሩ። ይህም ስርየት የሌለው ኃጢአት ነበር። — ማቴዎስ 12:31, 32
4 እነዚህ ግብዞች ዕውር የነበረውን ሰው ስለ ኢየሱስ በጠየቁት ጊዜ ሰውየው እንዲህ አላቸው:- “[ኢየሱስ] ከወዴት እንደ ሆነ እናንተ አለማወቃችሁ ይህ ድንቅ ነገር ነው፣ ዳሩ ግን ዓይኖቼን ከፈተ። እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኃጢአተኞችን እንዳይሰማ እናውቃለን። ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዓይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም፤ ይህ ሰው [ኢየሱስ] ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም ሊያደርግ ባልቻለም ነበር።” የሃይማኖት መሪዎቹ ምን አሉ? “መልሰው:- አንተ ሁለንተናህ በኃጢአት ተወለድህ፣ አንተም እኛን ታስተምረናለህን? አሉት። ወደ ውጭም አወጡት።” የቱን ያህል ርኅራኄ የጎደላቸው ሰዎች ነበሩ! ልባቸው እንደ ድንጋይ የጠነከረ ነበር። ስለሆነም ኢየሱስ በአካላዊ ዓይናቸው ማየት ቢችሉም በመንፈሳዊ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የታወሩ እንደሆኑ ነግሯቸዋል። — ዮሐንስ 9:30–41
5, 6. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሃይማኖታዊ መሪዎች ጨለማን እንደወደዱ የሚያሳይ ምን ነገር አደረጉ?
5 እነዚህ ሃይማኖታዊ ግብዞች በአምላክ መንፈስ ላይ ኃጢአት የሚሠሩ መሆናቸው ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ባስነሳበት በሌላ አጋጣሚም በግልጽ ታይቷል። በዚያ ተዓምር ምክንያት ብዙ ተራ ሰዎች በኢየሱስ አመኑ። ይሁን እንጂ የሃይማኖት መሪዎቹ ምን እንዳደረጉ ልብ በል። “እንግዲህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን [የሳንሄድሪንን አዓት] ሸንጎ ሰብስበው:- ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና። እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ አሉ።” (ዮሐንስ 11:47, 48) ይጨነቁ የነበረው ስለ ራሳቸው ማዕረግና ክብር ነበር። የተከፈለው ኪሣራ ተከፍሎ ሊያስደስቱ የሚፈልጉት ሮማውያንን እንጂ አምላክን አልነበረም። በዚህ ምክንያት ምን አደረጉ? “እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው [ኢየሱስን] ሊገድሉት ተማከሩ።” — ዮሐንስ 11:53
6 በዚሁ ብቻ ተወስነው ቀሩን? አልቀሩም። ቀጥሎ ያደረጉት ነገር ምን ያህል ጨለማን የሚወዱ ሰዎች እንደነበሩ ያመለክታል። “የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ደግሞ ሊገድሉት ተማከሩ፣ ከአይሁድ ብዙዎች ከእርሱ የተነሳ ሄደው በኢየሱስ ያምኑ ነበርና።” (ዮሐንስ 12:10, 11) እንዴት ያለ ሊታመን የማይችል ክፋት ነበር! ምንም እንኳን ማዕረጋቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ይህንን ሁሉ ቢያደርጉም በመጨረሻው ምን ሆነ? በዚያው ትውልድ ዘመን አይሁዳውያን በሮማውያን ላይ በማመፃቸው በ70 እዘአ ሮማውያን መጡባቸውና አገራቸውንና ሕዝባቸውን ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸውንም ጭምር ወሰዱባቸው! — ኢሳይያስ 5:20፤ ሉቃስ 19:41–44
ኢየሱስ ያሳየው ርኅራኄ
7. እውነትን የሚወዱ ሰዎች ወደ ኢየሱስ የጎረፉት ለምን ነበር?
7 በዘመናችንም መንፈሳዊ ብርሃንን የሚፈልጉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። እውነትን የሚያፈቅሩ ሰዎች ግን ወደ ብርሃን ለመምጣት ይፈልጋሉ። አምላክ ሉዓላዊ ገዥአቸው እንዲሆን ይፈልጋሉ። ብርሃኑ ምን እንደሆነ እንዲገልጥ አምላክ ወደ ላከው ወደ ኢየሱስ በጉጉት ይመለከታሉ፤ እርሱንም ይከተሉታል። ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ትሑት የሆኑ ሰዎች ያደረጉት ይህንን ነበር። ወደ እርሱ ጎረፉ። ፈሪሳውያን እንኳን ይህንን መካድ አልቻሉም። “ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዷል” ሲሉ አማረዋል። (ዮሐንስ 12:19) ኢየሱስ “ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ላይ ይጭናሉ፣ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም። ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ” ካላቸው ከእነዚያ ራስ ወዳድ፣ ትዕቢተኛና የሥልጣን ጥመኞች የሆኑ ሃይማኖታዊ መሪዎች ተቃራኒ ስለነበር በግ መሰል የሆኑ ሰዎች ኢየሱስን ይወዱት ነበር። — ማቴዎስ 23:4, 5
8. ኢየሱስ ከግብዞቹ ሃይማኖታውያን ተቃራኒ የሆነ ምን አመለካከት ነበረው?
8 የጎላ ልዩነት ያሳየውን የርኅሩኁን የኢየሱስን አመለካከት ልብ በል:- “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፣ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።” (ማቴዎስ 9:36) በዚህስ ምክንያት ምን አደረገ? በሰይጣን ሥርዓት ተጨቁነው ለነበሩት እንዲህ አላቸው:- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።” (ማቴዎስ 11:28–30) ኢየሱስ “ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፣ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል። የተወደደችውንም የእግዚአብሔርን [የይሖዋን አዓት] ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ፣ የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ” በሚለው በኢሳይያስ 61:1, 2 ላይ በቅድሚያ ስለ እርሱ የተነገረውን ቃል ፈጽሟል።
ብርሃን አብሪዎችን መሰብሰብ
9. በ1914 ምን ከፍተኛ ድርጊቶች ተፈጽመዋል?
9 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላም አምላክ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ለእርሱ የሚሰጥበት ጊዜ እስከሚደርስ መጠበቅ ነበረበት። መንግሥት በሚረከብበት ጊዜ “በጎቹን ከፍየሎቹ” ይለያል። (ማቴዎስ 25:31–33፤ መዝሙር 110:1, 2) “የመጨረሻዎቹ ቀናት” በ1914 ሲጀምሩ ያ ጊዜ ደረሰ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) ኢየሱስ የአምላክ ሰማያዊት መንግሥት ንጉሥ የመሆን ሥልጣን ተቀብሎ ብርሃኑን ለመከተል የሚፈልጉትን ሰዎች የእርሱን ሞገስ በሚያገኙበት በቀኙ መሰብሰብ ጀመረ። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ይህ የመሰብሰቡ ሥራ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ሄዷል።
10. ኢየሱስ በመሰብሰቡ ሥራ ላይ እየተጠቀመባቸው ስላሉት ሰዎች ምን ጥያቄ ሊጠየቅ ይችላል?
10 በክርስቶስ ኢየሱስ መሪነት የሚካሄደው የመሰብሰቡ ሥራ እጅግ የተሳካ ውጤት እያስገኘ ነው። ከሁሉም ብሔራት የተሰባሰቡ መንፈሳዊ ብርሃን ወደበራለት እውነተኛው አምልኮ የመጡ ይህን ያህል የበዙ ሰዎች በታሪክ ውስጥ በጭራሽ ኖረው አያውቁም። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ከአምላክና ከክርስቶስ የሚመጣውን ብርሃን በመከተል ላይ የሚገኙት እነማን ናቸው? ፊልጵስዩስ 2:15 እንደሚለው ‘በዓለም እንደ ብርሃን በማብራት’ ‘የሕይወትን ውኃ በነፃ እንዲወስዱ’ ሌሎችን እየጋበዙ ያሉት እነማን ናቸው? — ራእይ 22:17
11. ከመንፈሳዊ ብርሃን ጋር በተዛመደ ሁኔታ ሕዝበ ክርስትና ያላት ቦታ ምንድን ነው?
11 ታዲያ ሕዝበ ክርስትና እንደዚህ እያደረገች ነውን? በተለያዩ ሃይማኖቶች የተከፋፈለችው ሕዝበ ክርስትና በዓለም እንደ ብርሃን ሆና እያበራች እንዳልሆነች የተረጋገጠ ነው። እንዲያውም ቀሳውስቱ በኢየሱስ ዘመን እንደነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች ናቸው። ከአምላክና ከክርስቶስ የሚመጣውን እውነተኛ ብርሃን እያንጸባረቁ አይደሉም። ከሠላሳ ሦስት ዓመታት በፊት ቲኦሎጂ ቱዴይ የተባለው መጽሔት “ይህ ብርሃን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብሩህ ሆኖ የማይበራ መሆኑን ስንገልጽ በቁጭት ነው። . . . ቤተ ክርስቲያን ከተከበበችበት ማኅበረሰብ ያልተለየች ወደ መሆን አዘንብላለች። ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ብርሃን መሆኗ ቀርቶ ከዓለም የሚያበራውን ብርሃን ተቀብላ የምታንጸባርቅ ሆናለች” ብሎ ነበር። አሁን ያለው የሕዝበ ክርስትና ሁኔታ ደግሞ ከዚያም የባሰ ነው። ሕዝበ ክርስትና ከዓለም ተቀብላ እንደምታንጸባርቀው የተነገረለት ብርሃን እንደ እውነቱ ከሆነ ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም፤ ምክንያቱም ከሰይጣንና ከዓለሙ ሊገኝ የሚችለው ጨለማ ብቻ ነው። እርስ በርሳቸው ከሚጋጩትና ጨርሶ ዓለማዊ ከሆኑት የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ምንም ዓይነት የእውነት ብርሃን ሊገኝ አይችልም።
12. በዛሬው ጊዜ እውነተኛ የብርሃን አብሪዎች ድርጅት የሆኑት እነማን ናቸው?
12 በዛሬው ጊዜ እውነተኛውን ብርሃን የሚያበራው ዓለም አቀፍ ድርጅት የይሖዋ ምስክሮች የአዲስ ዓለም ማኅበር ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። የዚህ ማኅበር አባሎች የሆኑት ወንዶች፣ ሴቶችና ወጣቶችም ጭምር ከይሖዋና ከክርስቶስ ያገኙትን ብርሃን በሰው ልጆች ሁሉ ፊት እንዲበራ በማድረግ ተባብረዋል። ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ ወደ 70,000 በሚጠጉ የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ከአራት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ብርሃን አብሪዎች ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ በትጋት ለሰዎች ሲናገሩ ነበር። መንፈሳዊ ብርሃን እንዲበራላቸው የሚፈልጉ በጣም ብዙ ሰዎች አሁንም በየዓመቱ እየተሰበሰቡ መሆናቸውን እናያለን። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው ወደ ትክክለኛው የእውነት እውቀት ከመጡ በኋላ እየተጠመቁ ናቸው። በእውነትም የአምላክ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን [ትክክለኛውን የእውነት እውቀት አዓት] ወደ ማወቅ” እንዲደርሱ ነው። — 1 ጢሞቴዎስ 2:4
13. ከይሖዋ የሚመጣውን ብርሃን ከምን ጋር ልናወዳድረው እንችላለን?
13 በዛሬው ጊዜ ከይሖዋ የሚመጣውን ብርሃን የጥንቶቹ የአምላክ ሕዝቦች ከግብፅ በወጡበት ጊዜ ከሆነው ነገር ጋር ለማመሳሰል እንችላለን፤ “በቀንና በሌሊትም ይሄዱ ዘንድ፣ መንገድ ሊያሳያቸው ቀን በደመና ዓምድ፣ ሊያበራላቸውም ሌሊት በእሳት ዓምድ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በፊታቸው ሄደ።” (ዘጸአት 13:21, 22) የቀኑ ደመናና የሌሊቱ እሳት ከይሖዋ የተገኙ አስተማማኝ መሪዎች ነበሩ። በቀን ብርሃን እንድትሰጥ አምላክ ከፈጠራት ከፀሐይ ባለነሰ ሁኔታ የሚያስተማምኑ መሪዎች ሆነውላቸው ነበር። ስለዚህ እኛም ይሖዋ ክፉ በሆኑት በእነዚህ መጨረሻ ቀናት የእውነት ፈላጊዎችን መንገድ በመንፈሳዊ ሁኔታ እንደሚያበራላቸው ልንተማመን እንችላለን። ምሳሌ 4:18 እንዲህ ሲል ያረጋግጥልናል:- “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል።”
የመንግሥቱን ብርሃን ማንጸባረቅ
14. የብርሃን አብሪዎች ዋና ዓላማ ምን መሆን አለበት?
14 የብርሃኑ ምንጭ ይሖዋ ሲሆን ዋናው የብርሃን አንጸባራቂም ኢየሱስ ነው፤ የኢየሱስ ተከታዮች የሆኑትም ያንን ብርሃን ማንጸባረቅ አለባቸው። ስለ ተከታዮቹ ሲናገር ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። . . . መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።” (ማቴዎስ 5:14, 16) የኢየሱስ ተከታዮች በሰው ልጆች ፊት የሚያበሩት ብርሃን ዋና መልእክቱ ምንድን ነው? በዚህ በዓለም ታሪክ መደምደሚያ ላይ ምን ብለው እንዲያስተምሩ ታዘዋል? ኢየሱስ ተከታዮቹ ስለ ዲሞክራሲ፣ ስለ አምባገነንነት፣ ስለ መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን ጥምረት ወይም ስለ ማንኛውም ሌላ ዓለማዊ አስተሳሰብ እንደሚሰብኩ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ ቢኖርም “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት በማቴዎስ 24:14 ላይ አስቀድሞ ተናግሯል። ስለዚህ በዛሬው ጊዜ ብርሃን አብሪዎች የሰይጣንን ዓለም በማጥፋት አዲሱን የጽድቅ ዓለም ስለሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ለሌሎች ይናገራሉ። — 1 ጴጥሮስ 2:9
15. ብርሃኑን የሚፈልጉ ሰዎች ወዴት ዘወር ይላሉ?
15 ብርሃንን የሚወዱ ሁሉ በዚህ ዓለም ጉራና ግቦች አይዘናጉም። ይህ ዓለም ወደ ፍጻሜው እየተጠጋ ስለሆነ ይህ ጉራና ግብ ሁሉ በቅርቡ በንኖ ይጠፋል። ከዚህ ይልቅ ጽድቅ ወዳድ የሆኑ ሰዎች የአምላክን መንግሥት ብርሃን በአራቱም የምድር ማዕዘናት በሚያበሩት ሰዎች ወደሚታወጀው የምሥራች ዘወር ለማለት ይፈልጋሉ። እነዚህ ሰዎች በራእይ 7:9, 10 ላይ “ከዚህም በኋላ አየሁ፣ እነሆም፣ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ . . . በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮኹ:- በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ” በመባል አስቀድሞ የተነገረላቸው ናቸው። ቁጥር 14 “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው” ይላል። አዎን፤ በዚህ ዓለም ላይ ከሚመጣው ጥፋት ተርፈው በአምላክ መንግሥት ወደሚተዳደረው ፍጻሜ የሌለው አዲስ ዓለም ይገባሉ።
መንፈሳዊ ብርሃን የበራለት አዲስ ዓለም
16. በታላቁ መከራ ወቅት የሰይጣን ዓለም ምን ይደርስበታል?
16 ይህ ወደፊት የሚመጣ አዲስ ዓለም ብሩህ በሆነው የእውነት ብርሃን ይጥለቀለቃል። አምላክ ይህንን የነገሮች ሥርዓት ባጠፋው ማግስት ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር አስቡት። ሰይጣንና አጋንንቱ እንዲሁም የፖለቲካ፣ የንግድና የሃይማኖት ሥርዓቶቹ በሙሉ ይወድማሉ! መላው የሰይጣን የፕሮፓጋንዳ አውታርም ፈጽሞ ይበጣጠሳል። ስለዚህ ከታላቁ መከራ በኋላ የዚህን ክፉ ዓለም ዓላማ የሚያራምድ አንድም ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ መጽሐፍ ወይም በራሪ ጽሑፍ አይኖርም። ከዓለማዊ የቴሌቪዥን ወይም የራዲዮ ጣቢያዎች የሚተላለፍ የሰዎችን ምግባር የሚያበላሽ ምንም ፕሮግራም አይኖርም። መላው የሰይጣን ዓለም መርዛማ አካባቢ በአንድ ኃይለኛ ምት ከሥፍራው ይጠረጋል! — ማቴዎስ 24:21፤ ራእይ 7:14፤ 16:14–16፤ 19:11–21
17, 18. የሰይጣን ዓለም ከጠፋ በኋላ የሚኖረውን መንፈሳዊ ሁኔታ እንዴት አድርገህ ትገልጸዋለህ?
17 ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ግልግል ይሆናል! ከዚያ ቀን ጀምሮ መላውን የሰው ልጅ የሚመራው ከይሖዋና ከመንግሥቱ የሚመጣው ጤናማና የሚያንጽ መንፈሳዊ ብርሃን ብቻ ይሆናል። ኢሳይያስ 54:13 “ልጆችሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር [ከይሖዋ አዓት] የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል” በማለት አሁን ያለውን ሁኔታ አስቀድሞ ገልጿል። የአምላክ መንግሥት መላዋን ምድር ስለሚቆጣጠር ኢሳይያስ 26:9 ላይ “በዓለም የሚኖሩ ጽድቅን ይማራሉ” በማለት የሰጠው ተስፋ ይፈጸማል።
18 የሁሉም ሰው አእምሮአዊና መንፈሳዊ ሁኔታ ፈጣን ለውጥ በማድረግ እየተሻሻለ ይሄዳል። በአሁኑ ጊዜ ተስፋፍተው በሚገኙት ጭንቀትን የሚፈጥሩና ሥነ ምግባር የጎደላቸው ነገሮች ፈንታ የሚያንጹ ነገሮች የዕለት ተዕለት ኑሮአችን ገጽታዎች ይሆናሉ። በዚያ ጊዜ የሚኖር ሰው ሁሉ ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጸውን እውነት ይማራል። “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] በማወቅ ትሞላለች” የሚለው የኢሳይያስ 11:9 ትንቢት ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል።
ብርሃኑን መከተል በጣም አጣዳፊ ነው
19, 20. ብርሃኑን ለመከተል የሚፈልጉ ነቅተው መጠበቅ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
19 በዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ዓመታት ውስጥ የዓለምን ብርሃን መከተል በጣም አጣዳፊ ነው። በብርሃን መመላለሳችንን ለማገድ የተከፈተብን የተጠናከረ ጦርነት ስላለ ነቅተን መጠበቅ ይገባናል። ይህ ተቃውሞ የሚመጣው የጨለማው ኃይላት ከሆኑት ከሰይጣን፣ ከአጋንንቱና ከምድራዊ ድርጅቱ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “በመጠን ኑሩ ንቁም፣ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና” ሲል ያስጠነቀቀው በዚህ ምክንያት ነው። — 1 ጴጥሮስ 5:8
20 ሰይጣን ከብርሃኑ ጋር ግንኙነት የሚያደርጉ ሁሉ በፊት በነበሩበት የጨለማ መንገድ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ ሲል ማንኛውንም እንቅፋት በመንገዳቸው ላይ ይጋርጥባቸዋል። ከዘመዶች ወይም እውነትን ከሚቃወሙ የቀድሞ ወዳጆች የሚመጣ ተፅዕኖ ሊሆን ይችላል። በሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ወይም አምላክ የለም የሚሉ እና ስለ እርሱ ምንም ነገር ማወቅ አይቻልም ብለው የሚከራከሩ ሰዎች በሚያስፋፉት ፕሮፓጋንዳ ምክንያት በመታወር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚፈጠር ጥርጣሬ ሊኖርባቸው ይችላል። መለኮታዊ ብቃቶችን አሟልቶ መኖርን አስቸጋሪ የሚያደርግባቸው የገዛ ራሳቸው የኃጢአት ዝንባሌዎችም ሊሆኑ ይችላሉ።
21. በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚፈልጉ ሁሉ ምን እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል?
21 ምንም ዓይነት ዕንቅፋቶች ቢጋረጡብህም ድህነት፣ ወንጀል፣ አድልዎና ጦርነት በሌለበት ዓለም ውስጥ ለመኖርና ለመደሰት ትፈልጋለህን? ፍጹም ጤናና የዘላለም ሕይወት አግኝተህ ገነት በሆነች ምድር ላይ በደስታ ለመኖር ትፈልጋለህን? የምትፈልግ ከሆነ ኢየሱስ ክርስቶስን የዓለም ብርሃን አድርገህ በመቀበል ተከተለው። እንዲሁም “የሕይወትን ቃል” አጥብቀው በመያዝ ‘በዓለም እንደ ብርሃን የሚያበሩት’ ሰዎች የሚያሰሙትን መልዕክት አድምጥ። — ፊልጵስዩስ 2:15, 16
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የሃይማኖት መሪዎች ጨለማን የሚወዱ መሆናቸውን የሚያሳዩት እንዴት ነው?
◻ ኢየሱስ ለሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?
◻ ብርሃን አብሪዎችን የመሰብሰቡ ሥራ እንዴት እየተካሄደ ነው?
◻ በቅርቡ ምን ከፍተኛ ለውጦች ይፈጸማሉ?
◻ በዛሬው ጊዜ የዓለምን ብርሃን መከተል አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 14, 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ዓይኖቹን የከፈተለትን ሰው ልበ ደንዳኖቹ ፈሪሳውያን ወደ ውጭ አስወጡት