ተስፋ በዚህ ተስፋ አስቆራጭ ዓለም ውስጥ በጣም አስፈላጊ መከላከያ ነው
አንድ ኮሪያዊ ወጣት እናቱ ለአንድ የኮሌጅ ተማሪ የተስፋን አስፈላጊነት ለማሳመን ስትሞክር ሊረዳት ፈለገ። በአንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ የሰማውን ምሳሌ አስታውሶ ተማሪዋን አንድ እንቆቅልሽ ልትፈታለት ፈቃደኛ ትሆን እንደሆነ ጠየቃት። እርስዋም ተስማማች። እንዲህ አላት:- “ሁለት ቤተሰቦች ነበሩ። ሁለቱም በጣም ድሆች ናቸው። ኃይለኛ ዝናብ ይዘንባል ጣሪያቸውም ያፈስሳል። አንደኛው ቤተሰብ በጣም አዝኖአል፣ ቤቱ ስላፈሰሰበትም በጣም ተማርሮአል። ሁለተኛው ቤተሰብ ግን ደስ እያለው ጣሪያውን ይጠግናል። በእነዚህ ቤተሰቦች መካከል ይህን የመሰለ ትልቅ ልዩነት የኖረው ለምንድን ነው?” ወጣትዋ ሴት ግራ ተጋብታ አላውቅም አለችው። ልጁም መልሶ “ሁለተኛው ቤተሰብ ደስተኛ የሆነው ከከተማው አስተዳደር አዲስ ቤት እንደሚሰጠው የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሶት ስለነበረ ነው። በዚህም ምክንያት ተስፋ አገኙ። ልዩነቱን ያመጣው ይህ ነው” አላት።
የዚህ ልጅ እንቆቅልሽ አንድ ቀላል እውነት ያስረዳል። ምንም ዓይነት የከፋ ሁኔታ ቢያጋጥመን ተስፋ ስለ ሕይወት ያለንን ስሜት ይለውጣል። አብዛኞቻችን ልጁ እንደገለጻቸው ሁለት ቤተሰቦች በሕይወት ውስጥ ብዙ ችግር ያጋጥመናል። የጤና ችግር፣ የገንዘብ ችግር፣ የቤተሰብ ግጭት፣ ወንጀልና ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ብዙ ፈተናዎችና መከራዎች ይደርሱብናል። ኃይለኛ ዝናብን ማባረር እንደማንችል ሁሉ አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ችግሮች እንዳይደርሱብን ለማድረግ አንችልም። በዚህም ምክንያት ተስፋና ረዳት እንደሌለን ብቻችንን እንደተጣልን ይሰማን ይሆናል። ይባስ ብሎ ደግሞ አብያተ ክርስቲያናት ለአብዛኞቹ ኃጢአተኞች የወደፊቱ ተስፋ የጨለመ እንደሆነና የዘላለም ቅጣት እንደሚያጋጥማቸው አስተምረውን ይሆናል።
አንድ ሰው ምንም ማድረግ ወደማይችልበት ደረጃ እንደደረሰ ሲሰማውና ተስፋው ሲጨልምበት ለመንፈስ ጭንቀት የተጋለጠ እንደሚሆን ይነገራል። ይሁን እንጂ ሁላችንም ከእነዚህ ሁለት መንስኤዎች አንደኛውን ለማስወገድ እንችላለን። ማናችንም ብንሆን የግድ ተስፋ ቢሶች መሆን አይኖርብንም። ሁለተኛውን መንስኤ ማለትም ምንም ማድረግ የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ የሚለውን ስሜት ለመዋጋት ደግሞ ተስፋን የመሰለ ጥሩ መሣሪያ ላይገኝ ይችላል። ተስፋ ካለን የሕይወትን ውጣ ውረድ በከፍተኛ ሐዘንና ብስጭት ለመቋቋም ከመጣር ይልቅ በእርጋታና በእርካታ እንቋቋማለን። አዎ፤ ተስፋ በጣም አስፋላጊ የሆነ መከላከያ ነው።
ይህን ማመን ያስቸግርሃልን? ተስፋ ይህን የሚያህል ልዩነት ሊያመጣ የሚችል ኃይል አለውን? ሁላችንም አስተማማኝ ተስፋ ልናገኝ እንችላለንን?
እንደ ራስ ቁር
የሕክምናው ዓለም ተስፋ ያለውን አስደናቂ ኃይል መገንዘብ ጀምሮአል። ከናዚ እልቂት የተረፉት የጭንቀት ስፔሺያሊስት ዶክተር ሽሎሞ ብሬዝኒትዝ በሕይወት ከሚያጋጥሙ ችግሮች በአብዛኞቹ “ጭንቀት የሚደርስብን ከችግሩ ከራሱ ሳይሆን ለችግሩ ከምንሰጠው ትርጉም ነው። ተስፋ የችግሮቹን ክብደት ይቀንሳል” ብለዋል። ዘ ጆርናል ኦቭ ዘ አሜሪካን ሜዲካል አሶሴሽን በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ ርዕሰ አንቀጽ ተስፋ “በጣም ኃይለኛ መድኃኒት ነው” በማለት አረጋግጦአል። አሜሪካን ሄልዝ የተባለው መጽሔት ደግሞ እንደሚከተለው በማለት ዘግቦአል:- “አንድ ዓይነት ተስፋ የሚያሳጣ ነገር ሲያጋጥማቸው በሽታቸው የሚባባስባቸውና አዲስ ዓይነት ተስፋ የሚሰጣቸው ነገር ሲያገኙ የሚሻላቸው በሽተኞች በተለይም የካንሰር በሽተኞች በጣም ብዙ ናቸው።” — ከምሳሌ 17:22 ጋር አወዳድር።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የተስፋን አስፈላጊነት ከጥንት ጀምሮ ያውቃሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ተሰሎንቄ 5:8 ላይ ክርስቲያኖችን “የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር” ሲል መክሮአል። “የመዳን ተስፋ እንደ ራስ ቁር” የሆነው እንዴት ነው?
የራስ ቁር ምን ዓይነት አገልግሎት እንዳለው እንመልከት። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ወታደሮች ከውስጡ የሱፍ ወይም የቆዳ ጉዝጓዝ ያለው ከብረት ወይም ከመዳብ የተሠራ የራስ ቁር ያደርጉ ነበር። ይህ የራስ ቁር የወታደሩን ጭንቅላት በውጊያ ላይ ከሚወረወር ፍላጻ፣ ከዱላና ከሠይፍ ይከላከልለት ነበር። በዚህም ምክንያት የራስ ቁር እያላቸው ለመልበስ የሚያመነቱ ወታደሮች ይኖራሉ ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ ወታደሩ የራስ ቁር ስላደረገ ምንም ዓይነት ጉዳት ሊያገኘው አይችልም ወይም ጭንቅላቱ በሚመታበት ጊዜ ምንም ነገር አይሰማውም ማለት አይደለም። የራሱ ቁር አብዛኛውን የምት ኃይል ስለሚቀንስ ለሞት የሚያደርስ ጉዳት እንዳይደርስበት ይከላከላል ማለት ነው።
የራስ ቁር የአንድን ወታደር ጭንቅላት እንደሚከላከል ሁሉ ተስፋም አእምሮን ይጠብቃል። ተስፋ ያጋጠመንን ችግርና እንቅፋት ሁሉ ምንም ነገር እንዳልደረሰ አድርገን እንድናልፍ አያስችለን ይሆናል። ከዚህ ይልቅ ተስፋ የሚያጋጥሙን ችግሮችና እንቅፋቶች ከፍተኛ የአእምሮ፣ የስሜትና የመንፈሳዊ ጤንነት ጉዳት እንዳያደርሱብን የምታቸውን ኃይል ያረግብልናል።
ታማኙ አብርሃም ይህን ምሳሌያዊ የራስ ቁር ለብሶ እንደነበረ ግልጽ ነው። ይሖዋ የሚወደውን ልጁን ይሥሐቅን እንዲሰዋለት ጠየቀው። (ዘፍጥረት 22:1, 2) ለአብርሃም ተስፋ ቆርጦና ተደናግጦ ለመውደቅ በጣም ቀላል ነበር። ይህም አምላክን እንዳይታዘዝ ሊያደርገው ይችል ነበር። አእምሮውን እንዲህ ካለው ስሜት የጠበቀው ምን ነበር? ቁልፍ ሚና የተጫወተው ተስፋ ነበር። ዕብራውያን 11:19 እንደሚለው “እግዚአብሔር ከሙታን እንኳን ሊያስነሳው እንዲቻለው አስቦአል።” በተመሳሳይም ኢዮብ በትንሣኤ ላይ የነበረው ተስፋ አእምሮውን ከምሬት ጠብቆ ነበር። ቢማረር ኖሮ አምላክን ይረግም ነበር። (ኢዮብ 2:9, 10፤ 14:13–15) ኢየሱስ ክርስቶስ የመከራ ሞት ከፊቱ በተደቀነ ጊዜ ወደፊት በሚያገኘው አስደሳች ተስፋ ተጽናንቶና ተበረታትቶ ነበር። (ዕብራውያን 12:2) ለእውነተኛ ተስፋ መሠረቱ አምላክ ምንም ዓይነት ስህተት እንደማይሰራ እንዲሁም ቃሉን ሳይፈጽም እንደማይቀር እርግጠኛ መሆን ነው። — ዕብራውያን 11:11
የእውነተኛ ተስፋ መሠረት
እውነተኛ ተስፋ ልክ እንደ እምነት በሐቅ፣ በእውነትና በተረጋገጠ ነገር ላይ የተመሠረተ ነው። ይህም አንዳንዶችን ሊያስደንቃቸው ይችላል። አንድ ጸሐፊ እንዳለው “ብዙ ሰዎች ተስፋ እውነተኛውን ነገር በድንቁርና አለመቀበል እንደሆነ ያስባሉ።” ይሁን እንጂ እውነተኛ ተስፋ የሕልም እንጀራ ወይም የፈለግነውን ማግኘታችን አይቀርም ወይም ማንኛውም የሚያጋጥመን ችግር መፍትሔ ይኖረዋል የሚል ጭፍን እምነት አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው የጭፍን ተስፋ በትክክል ስለማይፈጸም ተዳፍኖ ይቀራል። — መክብብ 9:11
እውነተኛ ተስፋ ግን ከዚህ የተለየ ነው። የሚመነጨው ከምኞት ሳይሆን ከእውቀት ነው። በመግቢያው ላይ በቀረበው እንቆቅልሽ የተገለጸውን ሁለተኛ ቤተሰብ እንውሰድ። የከተማው አስተዳደር ቃሉን ያለመጠበቅ ልማድ እንዳለው የታወቀ ቢሆን ይህ ቤተሰብ ምን ዓይነት ተስፋ ይኖረው ነበር? ቤተሰቡ የጠነከረ ተስፋ የሚኖረው ከተሰጠው የተስፋ ቃል በተጨማሪ ቃሉ እንደሚፈጸም የሚያረጋግጥ ማስረጃ ቢኖረው ነው።
ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋ ምሥክሮች ከአንድ መስተዳድር ማለትም ከአምላክ መንግሥት ጋር የተቆራኘ ተስፋ አላቸው። ይህ መንግሥት የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እምብርት ነው። በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት እንደ አብርሃም የመሳሰሉ ታማኝ ሴቶችና ወንዶች ተስፋቸውን የመሠረቱት በዚህ መንግሥት ላይ ነበር። (ዕብራውያን 11:10) አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ይህን የተበላሸ አሮጌ የዓለም ሥርዓት እንደሚያጠፋና አዲስ ሥርዓት እንደሚያመጣ ቃል ገብቶአል። (ሮሜ 8:20–22፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) ይህ የመንግሥት ተስፋ እርግጠኛ ነው እንጂ ቅዠት አይደለም። የዚህ ተስፋ ምንጭ የሆነው የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ይሖዋ በታማኝነቱ ላይ ምንም ዓይነት ክስ ሊቀርብበት የማይችል ነው። ይሖዋ እንዳለና የሰጣቸውን ተስፋዎች በሙሉ ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል እንዳለው ለመገንዘብ የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች ብቻ መመርመር ይበቃል። (ሮሜ 1:20) ቃሉ ሳይፈጸም የማይቀር መሆኑን ለመመልከት የሚያስፈልገው ለሰው ልጆች ስላደረጋቸው ነገሮች የሚገልጸውን የታሪክ መዝገብ መመርመር ብቻ ነው። — ኢሳይያስ 55:11
የሚያሳዝነው ግን ክርስቲያኖች ነን ከሚሉት ሕዝቦች መካከል አብዛኞቹ እውነተኛ ተስፋ ያጡና የጨለመባቸው ናቸው። የሃይማኖት ሊቅ የሆኑት ፖል ቲሊች በቅርቡ ታትሞ በወጣው ስብከታቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “[የጥንቶቹ] ክርስቲያኖች ፍጻሜውን መጠበቅን ተምረው ነበር። ቀስ በቀስ ግን መጠበቃቸውን አቆሙ። . . . በእያንዳንዱ የጌታ ጸሎት ላይ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁ በምድር ይሁን ብለው ቢጸልዩም በምድር ላይ አዲስ ሥርዓት እንደሚመጣ ያላቸው ተስፋ እየተዳከመ መጣ።”
ምንኛ የሚያሳዝን ነገር ነው! የተስፋ ችግር ያለባቸው በሚልዮን እንዲያውም በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ ተስፋ ሊያገኙ ሲችሉ አለአንዳች ተስፋ ቀርተዋል። በዚህም ምክንያት የመጣውን ተስፋ አስቆራች ፍሬ ተመልከት። አእምሮአቸውን የሚጠብቅላቸው ጠንካራ ተስፋ ስለሌላቸው ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ‘በማይረባ አእምሮ’ ተነሳስተው ዓለምን በረከሰ ሥነ ምግባርና በዓመፅ መበከላቸው ያስደንቃልን? (ሮሜ 1:28) በዚህ ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ መጠንቀቅ በጣም አስፈላጊ ነው። የተስፋን ራስ ቁር አውልቀን ከመጣል ይልቅ ሁልጊዜ ማጠናከር ይገባናል።
ተስፋህን እንዴት ልትገነባ ትችላለህ?
ተስፋ የሚገነባበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ የተስፋው ምንጭ ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክ ማሰብ ነው። ቃሉ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት አጥና። ሮሜ 15:4 እንዲህ ይላል:- “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።”
ከዚህም በላይ ስለወደፊቱ ጊዜ ያለን ተስፋ ግልጽ ያልሆነና የደበዘዘ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባናል። በአእምሮአችን ውስጥ ግልጽ የሆነና የተረጋገጠ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልገናል። ገነት በምትሆነዋ ምድር ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ታደርጋለህን? በሞት የተለዩህ የምትወዳቸው ሰዎች ከሙታን ሲነሱ ለመቀበል ትፈልጋለህን? ከሆነስ ራስህን በዚያ ጊዜ እንዳለህ አድርገህ ትመለከታለህን? ለምሳሌ ያህል ኢሳይያስ 65:21, 22 እያንዳንዱ ሰው የራሱን ቤት እንደሚሠራና እንደሚኖርበት ይናገራል። ዓይንህን ጨፍነህ የራስህን ቤት በመሥራት ላይ እንዳለህና የመጨረሻውን የጣሪያ ሚስማር ስትመታ ሊታይህ ይችላልን? የራስህ ድካምና እቅድ አካባቢህን ምን እንዳስመሰለው ስትመለከት ምን እንደሚሰማህ አስብ! በቤቱ ሥራ ምክንያት ይሰማ የነበረው ኳኳታ ጸጥ ይላል። ጀምበርዋ ልትጠልቅ እያቆለቆለች ስትሄድ የአካባቢህን ውበት ትመለከታለህ። ዝግ ያለው ነፋስ ዛፎችን በቀስታ እያወዛወዘ በቀኑ ሥራ ምክንያት የተሰማህን ሙቀት ቀዝቀዝ ያደርግልሃል። የሕጻናት ሳቅ ከወፎች ዝማሬ ጋር ተደባልቆ ይሰማሃል። የምትወዳቸው ቤተሰቦችህ ጭውውት ከጣሪያው ሥር ይሰማሃል።
እንዲህ ያለውን አስደሳች ሁኔታ በዓይነ ህሊና መመልከት ሥራ ከመፍታት የሚመጣ ግምታዊ ሐሳብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መፈጸሙ የማይቀረውን ትንቢት ማሰላሰል ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:18) ይህ ተስፋ ይበልጥ እርግጠኛ በሆነልህ መጠን በዚያ ቦታ እንደምትኖር ያለህ ተስፋም ይጠናከርልሃል። እንዲህ ያለው የጸናና ገሃድ የሆነ ተስፋ ‘በምሥራቹ ከማፈር’ ይጠብቅሃል። በምሥራቹ ማፈር ምሥራቹን ለሌሎች እንድታካፍል ከተሰጠህ ሥራ እንድታፈገፍግ ሊያደርግህ ይችላል። (ሮሜ 1:16) ከዚህ ይልቅ ልክ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳደረገው ለሌሎች ሰዎች በማካፈል ‘በተስፋህ ትመካለህ።’ — ዕብራውያን 3:6
ተስፋ የሚሰጠን የወደፊቱ ዘላለማዊ ዘመን ብቻ አይደለም። በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ለተስፋ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች አሉ። እንዴት? በአምስተኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ ካሲየዶሮስ የተባለ ሮማዊ ርዕሰ መንግሥት “አሁን ያገኘውን ጥቅም የተገነዘበ ሰው ወደፊት ስለሚያገኛቸው ጥቅሞች ተስፋ ያገኛል” ብሎአል። ጥበብ የተሞሉ ቃላት ናቸው። አሁን የምናገኛቸውን በረከቶች ለማድነቅ የማንችል ከሆንን ወደፊት ስለምናገኛቸው በረከቶች ከተሰጠ የተስፋ ቃል ምን ዓይነት ማጽናኛ ልናገኝ እንችላለን?
በተጨማሪም ጸሎት አሁን ያለንን ተስፋ ያጠነክርልናል። ስለወደፊቱ ተስፋችን ብቻ ሳይሆን ስለ አሁኖቹ ችግሮቻችንም መጸለይ ይኖርብናል። ከቤተሰቦቻችንም ሆነ ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር ያለን ዝምድና እንዲሻሻል፣ ስለሚቀጥለው መንፈሳዊ ምግባችን፣ የሚያስፈልጉን መንፈሣዊ ነገሮችም እንኳን እንዲሟሉልን ልንጸልይና ተስፋ ልናደርግ እንችላለን። (መዝሙር 25:4፤ ማቴዎስ 6:11) እንዲህ ያለውን ተስፋ በይሖዋ እጅ መጣል በእያንዳንዱ ቀን እንድንጸና ይረዳናል። (መዝሙር 55:22) በምንጸናበት ጊዜ ደግሞ ጽናታችን ራሱ የተስፋችንን ራስ ቁር ያጠነክርልናል። — ሮሜ 5:3–5
ስለ ሰዎች ተስፋ ማድረግ
አፍራሽ ወይም አሉታዊ አስተሳሰብ በተስፋ ራስ ቁር ላይ እንዳለ ዝገት ነው። የራስ ቁሩን የሚቦረቡር በመሆኑ ከጊዜ በኋላ ከጥቅም ውጭ ያደርገዋል። አፍራሽ ወይም አሉታዊ አስተሳሰቦችን ለይተህ ማወቅና መዋጋት ችለሃልን? ጠርጣሪ፣ ስህተት ፈላጊ፣ ተቺ መሆንና አይሆንም የሚል ዝንባሌ የብልህ አእምሮ ውጤት ነው ብለህ በማሰብ አትሞኝ። እንዲያውም አሉታዊ አስተሳሰብ የአእምሮ ችሎታን የሚጠይቅ ነገር አይደለም።
በሰዎች ላይ ያለንን ተስፋ ለማጣት በጣም ቀላል ነው። አንዳንዶች ከዚህ በፊት መጥፎ አጋጣሚ ይደርስባቸውና ዳግመኛ የሌሎችን እርዳታ ወይም ማጽናኛ አገኛለሁ የሚል ተስፋ የላቸውም። “አንዴ የተቃጠለ ዳግመኛ በእሳት አይጫወትም” ብለው ያስባሉ። እንዲያውም ሽማግሌዎችን በችግራቸው እንዲረዱአቸው ለመጠየቅ ሊያመነቱ ይችላሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰዎች ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ይመክረናል። ተስፋችንን በሙሉ ሰዎች ላይ መጣል ጥበብ አለመሆኑ አይካድም። (መዝሙር 146:3, 4) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎች ግን ከይሖዋ የተሰጡ ‘የሰዎች ሥጦታ’ ሆነው ያገለግላሉ። (ኤፌሶን 4:8, 11) “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ፣ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ” ለመሆን ከልብ የሚፈልጉ ትጋትና ተሞክሮ ያላቸው ክርስቲያኖች ናቸው። — ኢሳይያስ 32:2
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ብዙ ሰዎችም የተስፋ ምንጭ ስለመሆን ከልብ ያስባሉ። በአሁኑ ጊዜ እንኳን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት የራሳቸውን ቤተሰቦች ላጡ ሁሉ እንደ እናት፣ እንደ አባት፣ እንደ እህት፣ እንደ ወንድምና እንደ ልጅ እንዴት እንደሆኑ ተመልከት። ጭንቀት ላጋጠማቸው ሁሉ ‘ከወንድም ይበልጥ የሚጠጋ ወዳጅ’ የሆኑት ስንቶቹ እንደሆኑ አስብ። — ምሳሌ 18:24፤ ማርቆስ 10:30
ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልየህ እንደሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ጸሎትህን መልሶልህ ይሆናል። ምክንያቱም ችግርህን ብትነግረው ሊረዳህ ዝግጁ የሆነ ሽማግሌ ወይም የጎለመሰ ክርስቲያን አዘጋጅቶልህ ይሆናል። ስለ ሰዎች ሚዛናዊ የሆነ ተስፋ ከኖረን ራሳችንን ከማግለልና ከሁሉ ሰው ከመራቅ እንጠበቃለን። ራስን ማግለል ከራስ ወዳድነት የሚመነጭ ከመሆኑም በላይ ጠቀሜታ የሌለው ጠባይ ነው። — ምሳሌ 18:1
በተጨማሪም ከአንድ ክርስቲያን ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ከነበረ ጉዳዩን ተስፋ በመቁረጥና በአሉታዊ ዝንባሌ መመልከት አይገባንም። “ፍቅር ሁሉን ተስፋ ያደርጋል።” (1 ቆሮንቶስ 13:4–7) ክርስቲያን ወንድሞችንና እህቶችን ልክ ይሖዋ እንደሚመለከታቸው በተስፋ ዓይን ተመልከቱአቸው። በመልካሞቹ ባሕርዮቻቸው ላይ አተኩሩ፣ እመኑአቸው። ሁልጊዜ ለችግሮች መፍትሔ የመፈለግ ዝንባሌ ይኑራችሁ። እንዲህ ያለው ተስፋ ማንንም ከማይጠቅመው ግጭትና ጥል ይጠብ ቀናል።
በመሞት ላይ በሚገኘው በዚህ አሮጌ ዓለም የተስፋ ቢስነት ዝንባሌ አትሸነፍ። ስለዘላለሙ ሕይወታችንም ሆነ በርካታ የሆኑት የጊዜው ችግሮቻችን መፍትሔ ስለማግኘታቸው ተስፋ አለን። ይህን ተስፋ አጠንክረህ ትይዛለህን? የመዳን ተስፋ የሆነውን የራስ ቁር የለበሰ የይሖዋ አገልጋይ ሁሉ ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥመው ማንም የሚደርስለት እንደሌለ ሆኖ አይሰማውም። እኛ ራሳችን ካልጣልነው በስተቀር በሰማይም ሆነ በምድር ያለ ማንኛውም ኃይል ይሖዋ የሰጠንን ተስፋ ሊቀማን አይችልም። — ከሮሜ 8:38, 39 ጋር አወዳድር።