የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ሐቀኝነት አገልግሎታችንን ያስመሰግናል
ሐቀኝነት ለክርስቲያኖች መሠረታዊ ግዴታ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን 13:18 ላይ “በነገር ሁሉ በመልካም እንድንኖር ወደን፣ መልካም ሕሊና እንዳለን ተረድተናልና” ሲል ጽፎአል። “በሐቀኝነት እየተመራን መመላለሳችን ‘የመድኃኒታችንን የእግዚአብሔርን ትምህርት ያስመሰግናል።’ (ቲቶ 2:10) በደቡብ ፓሲፊክ በቶንጋ መንግሥት የሚገኙ ሁለት ምስክሮች ባሳዩት ሐቀኝነትና በመንግሥቱ ስብከት ትልቅ ምስክርነት እየሰጡ ነው። በምዕራብ ሳሞአ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ እንደሚከተለው ይናገራል፦
“ምስክሮች የሆኑ ባልና ሚስት በደሴታቸው በሚገኙ አራት መንደሮች ላሉ ሕዝቦች ስለ አምላክ መንግሥት ቢነግሩአቸውም ምንም ያህል ውጤት አላገኙም ነበር። ከዚያ በኋላ ባልዋ ታሞ ሳለ ሚስቲቱ የእርሻቸውን ሥራ መከታተልና ብቸኛው የገቢ ምንጫቸው የሆነውን የኮኮናት ተክላቸውን መቁረጥና ማድረቅ አስፈለጋት። ገዢዎች ኮኮናቱን ማየት የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሲደርስ የሌላ ሰው ጆንያ ከራሷ አምስት ጆንያዎች ጋር ተደባልቆ ነበር። መንደረተኞቹ ትርፉን ጆንያ እንድታስቀምጠውና ከአምላክ እንደተሰጠ በረከት አድርጋ እንድትመለከተው መከሩአት። እህት ግን ይህን ምክር ባለመቀበል ለስድስት ጆንያዎች ቢከፈላትም እንኳን የራሷ ገንዘብ የሆነውን ብቻ ተቀበለች። ሐቀኝነቷ ሳይስተዋል አላለፈም።
“በኋላ ባልየው ወደ ሌላ ደሴት ሲሄድ አንድ ባለሱቅ ዕቃ እንዲገዛለት ጠየቀው። ምስክሩም እንደተጠየቀው ገዝቶ መጣና ለሰውየው ቀሪውን ገንዘብ መለሰለት። ሰውየው በጣም ተረገመ። የላከው ሰው ገንዘብ ሲመልስለት ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ተናገረ። አንዳንድ ነገሮችን እንዲገዙለት የነገራቸው ሌሎች ሰዎች ግን መልሱን ለራሳቸው ይወስዱት ነበር። ሌላ ጊዜ ምስክሩ ከዚህ ሰው ሱቅ አንድ ነገር በሚፈልግበት ጊዜ የሚፈልገውን ነገር ወስዶ ክፍያውን በሱቁ ውስጥ እንዲያስቀምጥ ነግሮ የሱቁን ቁልፍ ይሰጠው ነበር። ባለሱቁ ለምስክሩ ይህን ሲነግረው የሚሰሙ ሰዎች የሱቁን ቁልፍ ለእነርሱ እየከለከለ ለምስክሩ ለምን እንደሚሰጠው ይጠይቁት ነበር። ባለሱቁም በመንደሩ ውስጥ የሚያምነው ሰው እርሱ ብቻ እንደሆነ ይነግራቸው ነበር።
“የእነዚህ ባልና ሚስት ጥሩ ጠባይ በመንደረተኞቹ መካከል መነጋገሪያ እየሆነ ነው። ምስክሮቹ በሐቀኝነታቸው፣ ከፖለቲካ ገለልተኞች በመሆናቸውና ስለ አምላክ መንግሥት የሚመሰክሩ በመሆናቸው የታወቁ ናቸው። ይህ ሁኔታ በመንደረተኞቹ እምነትና በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች መካከል ልዩነት እንዳለ ያሳያል። አሁን መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ሲነሱ ሰዎቹ መልስ ለማግኘት ብዙውን ጊዜ ወደ ምስክሮቹ ይመጣሉ። እንዲያውም ባልየው በመጽሐፍ ቅዱስ ርዕስ ላይ የተነሳ ጥያቄን ለመመለስ መንደረተኞቹ ተሰብስበው ወደሚጠሩበት ቦታ ማታ ከመኝታው ተነስቶ የሚሄድበት ጊዜም አለ። በመንደሩ ውስጥ ሰው ሞቶ በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በሚገኝበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት ምን እንደሚናገር ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲያሳይ ብዙ ጊዜ ይጠየቃል፤ የሚሰጠው ሐሳብም ተቀባይነት ያገኛል።”
ስለዚህ ምስክሮች የሆኑት ባልና ሚስት ያሳዩት ሐቀኝነትና ያደረጉት የመንግሥት ስብከት በዚህ ውብ የፓሲፊክ ደሴት ላይ ጥሩ ምስክርነት እየሰጠ ነው። ሌሎችም መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚያጠኑና ለእውነት አቋም እንደሚወስዱ ተስፋ ያደርጋሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ ይሖዋ አምላክ እንደሚባርካቸው ጥርጥር የለውም።—ዮሐንስ 8:32