የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 7/1 ገጽ 12-17
  • ክርስቲያኖችና ዛሬ ያለው ሰብአዊ ኅብረተሰብ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ክርስቲያኖችና ዛሬ ያለው ሰብአዊ ኅብረተሰብ
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዛሬ ያሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች
  • ከዓለም የተለዩ ናቸው፤ ጠላትነት ግን የላቸውም
  • የገዢ መደቦች በትክክል አላወቋቸውም
  • ‘በየቦታው ሰዎች ይቃወሙታል’
  • ክርስቲያኖች ናቸው፤ የሥላሴ አማኞች ግን አይደሉም
  • ሃይማኖቶችን ለማዋሃድ አይጥሩም
  • የይሖዋ ምሥክሮች
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • በእውነት ይመላለሳሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖችና ዓለም
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • በእምነታቸው የተጠሉ ሰዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 7/1 ገጽ 12-17

ክርስቲያኖችና ዛሬ ያለው ሰብአዊ ኅብረተሰብ

“ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።”—ማቴዎስ 24:9

1. የክርስትና መለያ ምልክት ምን እንደሚሆን ተገልጾ ነበር?

ከዓለም የተለዩ መሆን የጥንት ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት ነበር። ክርስቶስ ለሰማያዊ አባቱ ለይሖዋ ባቀረበው ጸሎት ላይ ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር “እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:14) ኢየሱስ በጰንጤናዊው ጲላጦስ ፊት በቀረበበት ጊዜ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:36) የጥንት ክርስቲያኖች ከዓለም የተለዩ መሆናቸው በክርስቲያን ግርክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችና በታሪክ ጸሐፊዎች ተመሥክሮላቸዋል።

2. (ሀ) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ በጥንት ክርስቲያኖችና ከዓለም መካከል ባለው ግንኙነት ላይ የታየ ለውጥ ነበርን? (ለ) የኢየሱስ መንግሥት የምትመጣው ሰዎችን ሁሉ በመለወጥ ነውን?

2 በተከታዮቹና በዓለም መካከል በሚኖረው ግንኙነት ላይ ለውጥ እንደሚኖርና መንግሥቱ የምትመጣው ዓለምን ወደ ክርስትና በመለወጥ እንደሚሆን ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ ገልጿል? አልገለጸም። ኢየሱስ ከሞተም በኋላ ተከታዮቹ እንኳን እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ለመጻፍ ሊነሳሱ ቀርቶ ስለዚህ ነገር ትንሽ ፍንጭ አልተሰጣቸውም። (ያቆብ 4:4 [ከ62 እዘአ ጥቂት ቀደም ብሎ የተጻፈ]፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17፤ 5:19 [በ98 እዘአ ገደማ የተጻፈ።]) ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን “መገኘት” እና በመንግሥታዊ ሥልጣን ‘መጥቶ’ ‘የነገሮችን ሥርዓት መደምደሚያ’ ወደ ‘መጨረሻው’ ከማምጣቱ ወይም ከማጥፋቱ ጋር ያያይዘዋል። (ማቴ 24:3, 14, 29, 30፤ ዳን 2:44፤ 7:13, 14) ኢየሱስ ስለ እሱ ፓሩሲያ ወይም መገኘት በሰጠው ምልክት እውነተኛ ተከታዮች እንዲህ ብሏቸው ነበር፡ “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፣ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።”​—ማቴዎስ 24:9

ዛሬ ያሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች

3, 4. (ሀ) አንድ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ የጥንት ክርስቲያኖችን የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮችና የጥንት ክርስቲያኖች በምን ተመሳሳይ ቃላት ተገልጸዋል?

3 አባላቶቹ እየተጠሉና እየተሰደዱ ለክርስቲያን መሠረታዊ ሥርዓት ታማኝ በመሆንና ከዓለም በመለየት ለራሱ ጥሩ ስም ያተረፈ የትኛው ሃይማኖታዊ ቡድን ነው? ለጥንት ክርስቲያኖች ከተሰጠው ታሪካዊ መግለጫ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማው የትኛው ዓለም አቀፍ ክርስቲያናዊ ድርጅት ነው? ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ ይህን በተመለከተ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “የጥንቱ ክርስቲያን ኅብረተሰብ ምንም እንኳን በመጀመሪያው ጊዜ በአይሁድ ኅብረተሰብ መካከል ያቆጠቆጠ ሌላው ኑፋቄ ተደርጎ ቢታይም በሃይማኖታዊ ትምህርቱና በተለይ ደግሞ በአባላቱ ‘በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ’ የክርስቶስ ምስክሮች በመሆን ባሳዩት ቅንዓት የክርስትና እምነት ለየት ያለ ነበር። (ሥራ 1:8) ​— ጥራዝ 3 ገጽ 694

4 “እንደ ሌላ ኑፋቄ ተደርጎ ቢታይም” “በሃይማኖታዊ ትምህርቱ. . . ለየት” “የክርስቶስ ምስክሮች በመሆን ባሳዩት ቅንዓት” የሚሉት አነጋገሮች ልብ በል። አሁን ደግሞ ያው ኢንሳይክሎፔዲያ ይሖዋ ምሥክሮችን እንዴት አድርጎ እንደሚገልጻቸው ተመልከት፡ “ኑፋቄ ናቸው. . . ምስክሮቹ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የዓለም መጨረሻ ይመጣል ብለው አጥብቀው ያምናሉ። ያለ መታከት እንዲሠሩ የሚገፋፋቸው ኃይል ይህ ጠንካራ እምነት ነው። እየቀረበች ስላለችው የእሱ መንግሥት በማወጅ ለይሖዋ ምሥክርነት መስጠት ለእያንዳንዱ የዚህ ኑፋቄ አባል መሠረታዊ ግዴታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛው የእምነታቸውና የአኗኗራቸው መሠረት አድርገው ይመለከቱታል። አንድ ሰው እውነተኛ ምሥክር ለመሆን በዚያም ሆነ በዚህ ውጤታማ በሆነ መንገድ መስበክ አለበት።”​— ጥራዝ 7፣ ገጽ 864-5

5. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርት የተለየው በምን መንገዶች ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር የሚስማማ መሆኑን የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ስጥ።

5 የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርት የተለየ የሆነው በምን መንገዶች ነው? ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ ጥቂቶቹን ይጠቅሳል፦ “እነዚህ [የይሖዋ ምሥክሮች] ሥላሴን የአረማውያን የጣዖት አምልኮ ነው በማለት ያወግዙታል። . . . ኢየሱስ ከይሖዋ ብቻ የሚያንስ ዋነኛ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ፤ እንደ አነስተኛ አምላክ (ኤ ጎድ) አድርገው ይመለከታሉ፤ (ዮሐንስ 1:1ን በዚህ ዓይነት ተርጉመውታል) ኢየሱስ ሰው ሆኖ እንደሞተና የማይሞት መንፈሳዊ ልጅ ሆኖ እንደተነሳ፤ ለሰው ዘር በምድር ላይ ለዘላለም የምኖር መብት መልሶ ለማምጣት የከፈለው ዋጋ መከራውንና ሞቱን እንደሆነ አድርገው ያምናሉ። ‘እጅግ ብዙ ሰዎች’ (ራእይ 7፡9) የሚባሉት እውነተኛ ምስክሮች በምድራዊ ገነት ውስጥ ለመኖር ተስፋ ያደርጋሉ፤ ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ ክብር የሚያገኙት 144,000 ታማኞች ብቻ ናቸው። (ራእይ 7:4፤ 14:1, 4) ክፉዎች ሙሉ በሙሉ ይጠፋሉ። . . . . ምስክሮቹ ውሃ ውስጥ በመጥለቅ የሚያከናውኑት ጥምቀት . . . ለይሖዋ አምላክ አገልግሎት ራሳቸውን መወሰናቸውን የሚያሳዩበት ውጫዊ ምልክት [ነው]። የይሖዋ ምሥክሮች ደም አንወስድም በማለት በጣም ይታወቃሉ። የጋብቻና የጾታ ሥነ ምግባር ሕጋቸው በጣም ጥብቅ ነው።” የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ ከሌሎች ሊሆኑ ይችላሉ፤፤ ይሁን እንጂ በእነዚህ ነጥቦች ላይ ያላቸው አቋም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጽኑ ሆኖ የተመሠረተ ነው።— መዝሙር 37:29፤ ማቴዎስ 3:16፤ 6:10፤ የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29፤ ሮም 6:23፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 8:6፤ ራእይ 1:5

6. የይሖዋ ምሥክሮች እንደያዙ የቀጠሉት አቋም ምንድን ነው? ለምንስ?

6 ይኸውም የሮማ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ በ1965 (ይህ ሐሳብ በተጻፈበት ዓመት ይመስላል) “ምስክሮቹ አሁንም ራሳቸውን የሚኖሩበት ክፍል አድርገው አይቆጥሩም” በማለት ጨምሮ ይናገራል። ደራሲው ጊዜ እያለፈ ሲሄድና የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ እንዲሁም “ኑፋቄያዊ ባሕርያትን እየተዉና የቤተ ክርስቲያን መልክ እየያዙ ሲመጡ” የዚህ ዓለም ክፍል ይሆናሉ ብሎ አስቦ የነበረ ይመስላል። ይሁን እንጂ ይህን ሳይሆን ቀረ። ዛሬ በ1965 ከነበሩት ከአራት እጥፍ የሚበልጡ ምስክሮች አሉ። የይሖዋ ምስክሮች ለዚህ ዓለም ያላቸው አቋም እንደያዙ ቀጥለዋል። ኢየሱስ ‘የዓለም ክፍል’ እንዳልነበረ ሁሉ ‘እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም።’—ዮሐንስ 17:16

ከዓለም የተለዩ ናቸው፤ ጠላትነት ግን የላቸውም

7, 8. የጥንት ክርስቲያኖችና ዛሬ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች የሚያመሳስላቸው አንዱ ሁኔታ ምንድን ነው?

7 ሮበርት ኤም ግራንት ኧርሊ ክርስቲያኒቲ ኤንድ ሶሳይቲ በተባለው መጻፋቸው ላይ ሰማዕቱ ጀስቲን በሁለተኛው መቶ ዘመን የጥንት ክርስቲያኖች ለማስረዳት የጻፈውን በመጥቀስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ክርስቲያኖች አብዮተኞች ቢሆኑ ኖሮ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ተደብቀው ይቀሩ ነበር . . . ሰላምና ሥርዓታማነትን በማስፈን በኩል ክርስቲያኖች የንጉሡ የቅርብ ረዳቶች ናቸው።” በተመሳሳይም ዛሬ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች በሰላም ወዳድነታቸውና ሥርዓታማ ክርስቲያኖች በመሆናቸው በዓለም ዙሪያ የታወቁ ናቸው። የትኛው ዓይነት መንግሥትም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮችን የሚፈራበት ምንም ነገር እንደሌለ ያውቃል።

8 አንድ የሰሜን አሜሪካ የጋዜጣ ዓምድ አዘጋጅ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች በማንኛውም የፖለቲካ መንግሥት ላይ ምንም ዓይነት ስጋት ይፈጥራሉ ብሎ ማመን ምክንያተቢስነትና አጉል ጥርጣሬ ነው። የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት መሆን እንዳለበት ሁሉ እነሱ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገልበጥ የማይሞክሩ ሰላም ወዳዶች ናቸው።” ዣን ፒየር ካተሌን (በኅሊና ምክንያት በጦርነት አንሳተፍም ባዮች) በተባለው መጻፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች በሚገባ ለባለሥልጣናት የሚገዙና ሕግን ሁሉ የሚያከብሩ ናቸው። የሚፈለግባቸውን ግብር ይከፍላሉ፤ በዚህ ዓለም ጉዳይ ውስጥ ራሳቸውን ስለማያጠላልፉ መንግሥታት ትክክል ስለ መሥራታቸው ለመጠያየቅ፣ መንግሥትን ለመለወጥ ወይም ለማጥፋት አይፈልጉም።” የይሖዋ ምሥክሮች ለመታዘዝ እምቢ የሚሉት መንግሥት ሙሉ በሙሉ ለአምላክ የወሰኑትን ሕይወታቸውን እንዲሰጡት የጠየቃቸው እንደሆነ ብቻ ነው በማለት ካተሊን አክለው ይገልጻሉ። በዚህም ከጥንት ክርስቲያኖች ጋር በጣም ይመሳሰላሉ።—ማርቆስ 12:17፤ የሐዋርያት ሥራ 5:29

የገዢ መደቦች በትክክል አላወቋቸውም

9. ከዓለም መለየትን በተመለከተ በጥንት ክርስቲያኖችና በዘመናችን ባሉት ካቶሊኮች መካከል ያለው ጉልህ ልዩነት ምንድን ነው?

9 አብዛኞቹ የሮማ ንጉሠ ነገሥታት የጥንት ክርስቲያኖችን ማንነት በትክክል አሳድደዋቸዋል። ከሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ ጀምሮ ዕድሜ አለው ተብሎ በአንዳንዶች የሚገመተው ዘ ኤፒስትል ቱ ዲዮ ግነተስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ክርስቲያኖች የሚኖሩት በዓለም ውስጥ ነው፤ ይሁን እንጂ ከዓለም ጋር እጅና ጓንት አይደሉም።” በሌላ በኩል የቫቲካን ሁለተኛ ካውንስል ባወጣው የቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ካቶሊኮች “ በዓለማዊ ጉዳዮች ውስጥ በመግባት የአምላክን መንግሥት ጥቅም እንዲያስፈጽሙ” እንዲሁም “የሚኖሩበትን ዓለም ለማሻሻል መሥራት” እንደሚኖርባቸው ገልጿል።

10. (ሀ)የጥንት ክርስቲያኖች በገዢ መደቦች ዘንድ ይታዩ የነበሩት እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ የሚታዩት እንዴት ነው? ምንስ ይሰማቸዋል?

10 የሮማ ነገሥታት የጥንት ክርስቲያኖች “የታወቁ ወግ አጥባቂዎች” እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸው እንደነበር የታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ኢ ጂ ሐርዲ ይገልጻሉ። “የተማሩት ግሪኮችና የሮማ ባለሥልጣኖች [ክርስቲያኖችን] መጤ የሆኑ የምሥራቃውያን ኑፋቄ እንደሆኑ አድርገው ይንቋቸው ነበር” በማለት ፈረሳዊው ታሪክ ጸሐፊ ኤቴን ትሮክም ይናገራሉ። በቢታኒያ የሮማ ገዢ የነበረው በወጣቱ ፕሊኒ እና በንጉሥ ነገሥቱ ትራጃን መካከል የደብዳቤ ልውውጥ የገዢ መደቦች ስለ ክርስትና እውነተኛ ማንነት ምንም የማታውቁ እንደነበሩ ያሳያል። ዛሬም በተመሳሳይ የዓለም የገዢ መደቦች የይሖዋ ምሥክሮችን ማንነት በትክክል አይረዱም፤ እንዲያውም ይንቋቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ነገር የይሖዋ ምሥክሮችን አያስደንቃቸውም ወይም ተስፋ አያስቆርጣቸውም።—ሥራ 4:13፤ 1 ጴጥሮስ 4:12, 13

‘በየቦታው ሰዎች ይቃወሙታል’

11. (ሀ)ስለ ጥንት ክርስቲያኖች ምን እየተባለ ይነገር ነበር? ስለ ይሖዋ ምሥክሮችስ ምን ይባላል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካ የማይሳተፉት ለምንድን ነው?

11 ስለ ጥንት ክርስቲያኖች እንዲህ ተብሎ ነበር፦ ይህን አንተ የምትከተለውን የሃይማኖት ክፍል በየቦታው ሰዎች እንደሚቃወሙት እናውቃለን።” (ሥራ 28:22 የ1980 ትርጉም) በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ የአረመኔ እምነት ተከታይ የሆነው ሴልሰስ የክርስትና እምነት የሚስበው የማይረባውን የሰብአዊ ኅብረተሰብ ክፍል ነው ሲል ተናግሮ ነበር። በተመሳሳይም ስለ የይሖዋ ምሥክሮች “በአብዛኛው ችግረኛ ከሆነው ኅብረተሰባችን የተውጣጡ ናቸው” እየተባለ ሲነገር ቆይቷል። “ክርስቲያኖች የሚታዩት በዓለም ውስጥ በድን እንደሆኑና ለሁሉም የሕይወት ጉዳዮች ምንም የማይጠቅሙ ሰዎች ተደርገው ነበር፤. . . እንዲሁም ሁሉም እንደነሱ ቢሆን ኖሮ የሕይወት እንቅስቃሴ ምን ይመስል ነበር? ተብሎ ተጠይቆ ነበር” በማለት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት አውግስተስ ኒአደር አትተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካ ውስጥ ስለማይሳተፉ ብዙ ጊዜ በሰብአዊው ኅብረተሰብ ውስጥ ያሉ ሕይወት የሌላቸው እንጨቶች ናቸው ተብለው ተከሰዋል። ይሁን እንጂ በአንድ በኩል የፖለቲካ እንቅስቃሴ እያካሄዱ በሌላ በኩል የሰው ዘር ብቸኛ የተስፋ የአምላክ መንግሥት ናት እያሉ እንዴት ሊናገሩ ይችላሉ? የይሖዋ ምሥክሮች ቀጥለው ያሉትን የሐዋርያ ጳውሎስ ቃላት ከልብ ይቀበላሉ፦ “እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ፣ አብረኸኝ መከራ ተቀበል። የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም።”___2 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

12. በጣም አስፈላጊ በሆነ ነገር ከዓለም መለየት ነው የይሖዋ ምሥክሮች ከጥንት ክርስቲያኖች ጋር የሚመሳሰሉት?

12 ፕሮፌሰር ኬ ኤስ ላቱሬት ሂስትሪ ኦፍ ክርስቲያኒት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የጥንት ክርስቲያኖች ከግሪክና ከሮም ዓለም ጋር የማይስማሙበት አንዱ አከራካሪ ጉዳይ በጦርነት መሳተፍ ነበር። ክርስቲያኖች በጦርነት መሳተፋቸውን የሚቀበል በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት የነበረና እስከ ዘመናችን የዘለቀ ምንም የክርስቲያን ጽሑፍ የለም።” ዘ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዲክሊያን ኤንድ ፎል ኦቭ ዘ ሮማን ኢምፓየር የተባለው በኤድዋርድ ጊበን የተዘጋጀው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “ክርስቲያኖች በጣም ቅዱስ የሆነው ሥራቸውን ካልተዉ በስተቀር ወታደር፣ የሕዝብ ባለሥልጣኖች ወይም መሳፍንት ሊሆኑ አይችሉም ነበር።” በተመሳሳይም የይሖዋ ምሥክሮች ጥብቅ የገለልተኝነት አቋም አላቸው፤ እንዲሁም በኢሳይያስ 2፡2-4 እና በማቴዎስ 26፡52 ላይ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዐት ይከተላሉ።

13. በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚሰነዘረው ክስ ምንድን ነው? ሐቁ ግን ምን ያሳያል?

13 የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብን ያፈርሳሉ የሚል ክስ በጠላቶቻቸው ይሰነዘርባቸዋል። እውነት ነው፣ አንድ ወይም ከዚያ በላይ የይሖዋ ምሥክር በሚሆኑበት ጊዜ ቤተሰብ የሚከፋፈልባቸው ሁኔታዎች አሉ። (ሉቃስ 12:51-53) ይሁን እንጂ በዚህ ምክንያት የፈረስ ትዳር በጣም ጥቂት እንደሆነ የስታቲስካዊ መረጃዎች ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል በፈረንሳይ ከሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ከ3 ባልና ሚስት ውስጥ 1 የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ የትዳር ጓደኛ ያለበት ነው። ይሁን እንጂ በእነዚህ የይሖዋ ምሥክር በሆኑትና ባልሆኑት መካከል ጋብቻ ላይ የሚያጋጥመው ፍቺ በአገሪቱ ውስጥ ካለው አማካኝ ፍቺ አይበልጥም። ለምን? ሐዋርያው ጳውሎስና ጴጥሮስ የማያምን ሰው ላገቡ ክርስቲያኖች በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የጥበብ ምክር ሰጥተዋል፤ የይሖዋ ምሥክሮችም የእነሱን ቃል ለመከተል ይጥራሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:12-16፤ 1 ጴጥሮስ 3:1-4) በእምነት ከተለያዩት ሰዎች ጋብቻ ከፈረሰ ብዙውን ጊዜ የመፋታቱን ሃሳብ የሚያመጣው ምስክር ካልሆነው ወገን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የማያምኑት የነበሩት የትዳር ጓደኞች የይሖዋ ምሥክር በመሆናቸውና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በአኗኗራቸው ላይ ማዋል በመጀመራቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ትዳር ከመፍረስ ድኗል።

ክርስቲያኖች ናቸው፤ የሥላሴ አማኞች ግን አይደሉም

14. በጥንት ክርስቲያኖች ላይ ምን ክስ ይሰነዘር ነበር? ይህስ የሚያስገርመው ለምንድን ነው?

14 በሮም ግዛት ውስጥ በጥንት ክርስቲያኖች ላይ ከሚሰነዘሩ ክሶች አንዱ በአምላክ አያምኑም የሚል መሆኑ የሚያስገርም ነው። ዶክተር አውግስተስ ኒኦንደር እንዲህ ሲል ጽፈዋል፦ “ብዙውን ጊዜ ሕዝቡ ክርስቲያኖችን የሚጠራው አማልክትን የካዱ፣ አምላክ የለም የሚሉ. . . እያለ ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። ብዙሐን አማልክትን ሳይሆን ሕያው የሆነውን አንድ አምላክ የሚያመልኩት ክርስቲያኖች ‘አምላክ ያልሆኑትን የሰው እጅ ሥራዎች ማለትም የእንጨትና የድንጋይ አማልክትን’ በሚያመልኩት አረማውያን ዘንድ አምላክ የለም ባዮች ተብለው መጠራታቸው በጣም የሚያስገርም ነገር ነው።—ኢሳይያስ 37:19

15, 16. (ሀ) አንድ ሃይማኖተኛ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምን ይላሉ? ነገር ግን ምን ጥያቄ ያስነሳል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮችም በእውነትም ክርስቲያኖች መሆናቸውን የሚያሳየው ምንድን ነው?

15 በጣም የሚያስገርመው ዛሬም አንዳንድ የሕዝበ ክርስትና የሃይማኖት መሪዎች የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያኖች አይደሉም ማለታቸው ነው። ምክንያቱም የይሖዋ ምሥክሮች ሥላሴን አይቀበሉም። በሕዝበ ክርስትና የተዛባ አባባል መሠረት “ክርስቲያኖች የሚባሉት ክርስቶስን እንደ አምላክ አድርገው የሚቀበሉ ናቸው።” ከዚህ በተቃራኒ አንድ ዘመናዊ መዝገበ ቃላት “ክርስቲያን” የሚለውን ስም “በክርስቶስ የሚያምንና የእሱን ትምህርቶች የሚከተል ሰው” የሚል ፍቺ ሲሰጠው “ክርስትና” ማለት ደግሞ “በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች ላይ የተመሠረተና እሱ የአምላክ ልጅ እንደሆነ የሚያምን ሃይማኖት ነው” የሚል ትርጉም ይሰጠዋል። ታዲያ ይህ አተረጓጎም ይበልጥ የሚስማማው ለየትኛው ቡድን ነው?

16 የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ማን ስለመሆኑ እሱ ራሱ የሰጠውን ማረጋገጫ ይቀበላሉ። እሱም “እኔ እግዚአብሔር ወልድ ነኝ” ሳይሆን “የእግዚአብሔር ልጅ” በማለት ገልጿል። (ዮሐንስ 10፡36ን ከዮሐንስ 20:31 ጋር አወዳድር።) የይሖዋ ምሥክሮች ሐዋርያ ጳውሎስ በመንፈስ ተነሳስቶ ስለ ክርስቶስ የጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ ይቀበላሉ፦ “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረው።”a (ፊልጵስዩስ 2:6) ዘ ፓጋኒዝም ኢን አወር ክርስቲያኒቲ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ [ሥላሴ] በፍጹም አልጠቀሰም፤ እንዲሁም ሥላሴ የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በየትም ቦታ ላይ አይገኝም። ሐሳቡ ቤተ ክርስቲያን ቦታ ያገኘው ጌታችን ከሞተ ከሦስት መቶ ዓመት በኋላ ነው፤ ባጠቃላይ ሐሳቡ ከአረማውያን የመነጨ ነው።” የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ክርስቶስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነውን ትምህርት ይቀበላሉ። ክርስቲያኖች ናቸው፤ የሥላሴ አማኞች ግን አይደሉም።

ሃይማኖቶችን ለማዋሃድ አይጥሩም

17. የይሖዋ ምሥክሮች የክርስትና እምነቶችን ለማዋሃድ ወይም ለመቀላቀል በሚደረገው እንቅስቃሴ የማይተባበሩት ለምንድን ነው?

17 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከሚሰነዘሩ ሌሎች ሁለት ክሶች ደግሞ የተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖችን ለማዋሃድ በሚደረገው እንቅስቃሴ ለማካፈል እንቢ ይላሉ፤ እንዲያውም “በሌሎች ሃይማኖቶች ላይ ዘመቻ ያካሂዳሉ” የሚሉት ናቸው። እነዚህ ስድቦች በጥንት ክርስቲያኖች ላይም ይሰነዘሩ ነበር። ካቶሊክን፣ ኦርቶዶክስንና ፕሮቴስታንትን ያቀፈችው ሕዝበ ክርስትና የዚህ ዓለም ክፍል እንደሆነች የማይካድ ነው። እንደ ኢየሱስም ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች “ከዓለም አይደሉም።” (ዮሐንስ 17:14) ሃይማኖቶችን ለመቀላቀል በሚደረገው እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ተግባራትና እምነቶችን ከሚያስፋፉ የሃይማኖት ድርጅቶች ጋር እንዴት ሊተባበሩ ይችላሉ?

18. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ሃይማኖት እየተከተሉ ያሉት እነሱ ብቻ መሆናቸውን ቢናገሩ ሊነቀፉ የማይችለው ለምንድን ነው? (ለ) የሮማ ካቶሊኮች እውነተኛውን ሃይማኖት እንደያዙ ቢያምኑም ምን የላቸውም?

18 የጥንት ክርስቲያኖች ይሉ እንደነበረው ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም እነሱ ብቻ እውነተኛውን ሃይማኖት እየተከተሉ እንዳሉ ቢያምኑ በትክክል ሊነቅፋቸው የሚችል ማነው? የክርስትና እምነትን ለመቀላቀል በሚደረገው እንቅስቃሴ እንደምትተባበር በግብዝነት የምትናገረው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንኳን እንደሚከተለው ብላለች፦ “ጌታ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ‘እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን. . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ ብሎ በተናገረ ጊዜ ይህንን በሰዎች ሁሉ ዘንድ የማሰራጨቱን በአደራ የተሰጣት የካቶሊክና የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን የሆነችው ይህች አንድ እውነተኛ ሃይማኖት ጸንታ ትኖራለች ብለን እናምናለን።” (ሁለተኛው የቫቲካን ካውንስል “ደክላሬሽን ኦን ሪሊጀስ ሊበሪቲ”) በግልጽ እንደሚታየው ግን እንዲህ ዓይነቱ እምነት ካቶሊኮችን ያለመታከት በቅንዓት ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ሊያነሳሳቸው አልቻለም።

19. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ምን ለማድረግ ቆርጠዋል? ለምንስ? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚመራው ምንድን ነው?

19 የይሖዋ ምሥክሮች ግን እንዲህ ዓይነቱ ቅንዓት አላቸው። አምላክ እንዲህ እንዲያደርጉ እስከፈለገበት ጊዜ ድረስ መመስከራቸውን ለመቀጠል ቆርጠዋል። (ማቴዎስ 24:14) በቅንዓት ይመሰክራሉ፤ በማንም ላይ ግን ዘመቻ አያካሂዱም። የሚመሰክሩት ለሰው ዘር ባላቸው ጥላቻ ሳይሆን ለጎረቤት ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው ነው። በተቻለ መጠን ብዙ ሰው ዘሮች ለጥፋት እንዲድኑ ተስፋ ያደርጋሉ። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) ልክ እንደ ጥንት ክርስቲያኖች “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም” ለመኖር ይጥራሉ። (ሮም 12:18) ይህን የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ርዕስ ትምህርት ላይ ይብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከሥላሴ ቀኖና ጋር በተያያዘ ይህን ሐሳብ ለመወያየት የሰኔ 15, 1971 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 355-6 ተመልከት።

ለክለሳ ያህል

□ የጥንት ክርስቲያኖች ምን በማድረግ ተለይተው ይታወቁ ነበር? የይሖዋ ምሥክሮች እነሱን የሚመስሉት እንዴት ነው?

□ የይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ ዜጎች እንደሆኑ የሚያሳዩት በምን መንገዶች ነው?

□ የገዢ መደቦች የጥንት ክርስቲያኖችን እንዴት ይመለከቱ ነበር? ዛሬስ የተለየ ነውን?

□ የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን እንደያዙ ያላቸው ጽኑ እምነት ምን እንዲያደርጉ ይገፋፋቸዋል?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኘው ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ እንደዚያ እንዲያደርጉ እስከፈለገ ድረስ መመስከራቸውን ለመቀጠል ቆርጠዋል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኘው ሥዕል]

ጲላጦስ የዓለም ክፍል ያልነበረውን ሰው ወደ ሕዝቡ በማውጣት “እነሆ ሰውዬው” አለ—ዮሐንስ 19:5

[ምንጭ]

“Ecce Homo” by A. Ciseri: Florence, Galleria d’Arte Moderna / Alinari/​Art Resource, N.Y.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ