በእገዳ ሥር ሆኖ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማተም
በማልኮልም ጂ ቬል እንደተነገረው
“ልጆች የተባለውን መጽሐፍ እትም” መጽሐፉ በነሐሴ 10, 1941 በሴይንት ሉዊስ ሚዙሪ ዩ ኤስ ኤ በወጣ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወቅት ከአውስትራሊያ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ይህን ያልተጠበቀ መመሪያ ተቀበልኩ። መመሪያው ያልተጠበቀ የነበረው ለምንድን ነው?
የስብከቱ ሥራችን በጥር 1941 ታግዶ ስለነበር በአነስተኛ መጠንም እንኳ የኅትመቱን ሥራ መቀጠል ቀላል አልነበረም። ከዚህም በላይ ልጆች የተባለው መጽሐፍ ባለሙሉ ቀለም ሥዕሎችም የያዘ 384 ገጾች ያሉት መጽሐፍ ነበር። የማተሚያ መሣሪያችን መሻሻል ያስፈልገዋል። ወረቀት ተወግዶ ነበር። ሠራተኞቹም ጥራዝ መጽሐፎችን ለመሥራት የሠለጠኑ አልነበሩም።
በእገዳ ሥር በነበርንበት ጊዜ በኅትመት ሥራ እንዴት ሊሳካልን እንደቻለ ከመግለጼ በፊት በአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የኅትመት ሥራዎች የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል የተሾምኩት እንዴት እንደሆነ ልንገራችሁ።
አስተዳደጌ
እኔ በ1914 በተወለድኩባት በባላራት ቪክቶሪያ የበለጸገች ከተማ ውስጥ አባቴ የማተሚያ ንግድ ድርጅት ነበረው። ስለዚህ የኅትመት ሥራ በአባቴ ማተሚያ ቤት ውስጥ ተማርኩ። በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያኑ የመዝሙር ቡድን ውስጥ በመዘመርና የቤተ ክርስቲያኑን ደውል በመደወል በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች እሳተፍ ነበር። እንዲያውም በእሁድ ትምህርት ቤት እንዳስተምር ተሹሜ ነበር። ይህ ሁኔታ ግን አእምሮዬን ይረብሸው ነበር።
ምክንያቱም አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችን በተመለከተ ከባድ ጥያቄዎች ነበሩኝ። ከጥያቄዎቹ መካከል ሥላሴ፣ እሳታማ ሲኦልና ነፍስ አትሞትም የሚሉት ይገኙበታል። ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ የሰጠኝ ሰው አልነበረም። በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያናችን ቄስ ራሳቸውን የይሖዋ ምሥክሮች ብለው ስለሚጠሩ ስለ አንድ ትንሽ የሃይማኖት ቡድን በተደጋጋሚ በቁጣ መናገሩ ይከነክነኝ ነበር። አንድ አነስተኛ የሆነ ቡድን 40,000 ሕዝብ ለሚገኝባት ከተማ ይህን ያህል አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? ብዬ አሰብኩ።
አንድ እሁድ ቀን ከምሽት ስብከት በኋላ ከቤተ ክርስቲያኑ ውጭ ቆሜ ሳለ በአቅራቢያው ከሚገኘው የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ልጃገረዶች ተሰብስበው አለፉ። ከእነሱ መካከል ከአንዷ ጋር ጓደኝነት ጀመርኩ። ስሟ ሉሲ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ከወላጆቿ ጋር ልታስተዋውቀኝ ቤቷ ወሰደችኝ። እናቷ ቬራ ክሎጋን ከይሖዋ ምሥክሮች አንዷ መሆኗን ሳውቅ ምን ያህል
በአጭር ጊዜ ውስጥ እኔና ሉሲ ተጋባን። በ1939 በቪክቶሪያ ዋና ከተማ ሜልበርን እንኖር ነበር። ሉሲ የይሖዋ ምሥክር ሆናለች እኔ ግን እያቅማማሁ ነበር። ሆኖም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በዛው ዓመት ሲፈነዳ ከቅዱሳን ጽሑፎች ስለተማርኳቸው ነገሮች በጥሞና ማሰብ ጀመርኩ። የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በ1941 መታገዱ ቁርጥ ያለ አቋም እንዳደርግ ረዳኝ። ሕይወቴም ለይሖዋ አምልክ ወሰንኩና ወዲያውኑ ተጠመቅሁ።
በሕይወታችን ውስጥ የተደረጉ ትላልቅ ለውጦች
በአንድ ወቅት በሜልበርን ውስጥ ምቹ አፓርታማ ተከራይተን እንኖር ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ሌሎች በርከት ያሉ ምሥክሮች ወዳሉበት ቤት እንድንዛወር ተጋበዝን። ከመኝታ ቤት ዕቃዎች በስተቀር ሌሎች ሁሉንም የቤት ቁሳቁሶች ሸጥንና የአቅኚዎች ቤት ተብሎ ይጠራ ወደነበረው ቦታ ተዛወርን። አታሚ ሆኜ መሥራቴን ቀጠልኩ፤ ይህም የቤቱን ውጪ ለመሸፈን አስተዋጽኦ እንዳደርግ አስችሎኛል። ባሎች የሆኑት ሌሎቹም እንዲህ አደረጉ። በዚህም ምክንያት ሚስቶቻችን በስብከቱ ሥራ ሙሉ ጊዜያቸውን መካፈል ቻሉ። እኛ ወንዶቹ ደግሞ ማታ ማታና በሳምንቱ መጨረሻ ቀኖች በወንጌላዊነቱ ሥራና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አብረናቸው እንካፈል ነበር።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ እኔና ሚስቴ ወደ ሲድኒ እንድንመጣ እንደተጋበዝን የሚገልጽ ደብዳቤ ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ደረሰን። የመኝታ ቤት ዕቃዎቻችንን ሸጥንና የነበረብንን ጥቂት እዳ ከፈልን። ነገር ግን ወደ በባቡር ወደ ሲድኒ የምንሄድበት ገንዘብ ለማግኘት ስንል የሉሲን የጋብቻ ቀለበት መሸጥ ነበረብን!
በጦርነቱ ወቅት በነበረው ቁጥጥርና ከጥቂት ጊዜ በኋላ በተጣለው ዕገዳ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱሶችንም ሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከባሕር ማዶ ማስገባት አይቻልም ነበር። በዚህ ምክንያት የአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ የመንፈሳዊውን ምግብ አቅርቦት እንዳይቋረጥ ለማድረግ ድብቅ የኅትመት ሥራ ለማቋቋም ወሰነ። እኔም ሥራውን በበላይነት እንድቆጣጠር ግብዣ ቀረበልኝ። በአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ወደ 60 ለሚጠጉ ዓመታት ካገለገለው ስኮትላንዳዊው ጆርጅ ጊቢ ጋር ጎን ለጎን የመሥራት መብት አግኝቻለሁ።a “ልጆች የተባለውን መጽሐፍ እትም” የሚለውን መመሪያ የተቀበልኩት በዚያ ጊዜ ነበር።
የማተሚያ መሣሪያ መልሶ ማግኘት
ብዙ ድርጊት በተከናወኑባቸው በእነዚህ የጦርነት ዓመታት ያሳለፍናቸው ተሞክሮዎች ብዙዎቹ አስደሳች ሲሆኑ አንዳንዶች አስደንጋጭ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል የኅትመት ሥራችንን ለመጀመር መሣሪያ ያስፈልገን ነበር። ቀደም ሲል ከጦርነቱ በፊት በነበሩት ዓመታት የተወሰኑ የኅትመት ሥራ እናከናውንበት የነበረው መሣሪያ በመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ተይዟል። የማኅበሩ አነስተኛ ማተሚያ ቤትም ታሽጎ እየተጠበቀ ነው። መሣሪያው በድብቅ ለማተም አመቺ ወደ ሆነ ቦታ ስፍራ መውሰድ የምንችለው እንዴት ነው?
የታጠቁ ዘበኞች በፈረቃ እየተለዋወጡ በቀን 24 ሰዓት የማኅበሩን ንብረት ይጠብቃሉ። ሆኖም በጀርባ በኩል ካሉ ግድግዳዎች አንዱ እምብዛም ጥቅም ላይ ከማይውል የባቡር ሃዲድ ጋር ይዋሰናል። አንዳንድ ብልሃተኛ የሆኑ የቤቴል ሠራተኞች በሕዝቅኤል 12፡ 5-7 ላይ ያለውን የሚያስታውሱ ዘዴዎችን የተወሰኑ ጡቦችን አፍርሰው በግድግዳ ውስጥ ግቡ። ወደ ውስጥ መግባታቸው እንዳይታወቅ ከቦታቸው ያነሱአቸውን ጡቦች ግድግዳው ላይ መልሰው አስቀመጡአቸው። ለሁለት ሳምንት ያህል ሌሊት ሌሊት ሾልከው በመግባት ላይኖ ታይፕ የተባለ አንድ አነስተኛ የማተሚያ መሣሪያና ሌሎች ማሽኖችን በጥንቃቄ አወላለቁ። ከዚያም ተረኞች የነበሩት ዘበኞች እያዩአቸው እነዚያን የተነቃቀሉ መሣሪያዎች ይዘው አለፉ!
ውሎ አድሮ ከሌሎች ቦታዎች ተጨማሪ መሣሪያ አገኘን፤ ወዲያውኑ በሲድኒ ከተማ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የተሟሉ የኅትመት ሥራዎች በድብቅ ይካሄዱ ነበር። በዚህ መንገድ ልጆች የተባለውን መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን የአዲሲቱ ዓለም፣ “ነፃ የሚያወጣችሁ እውነት” እና መንግሥቲቱ ቀረባለች የተባሉትን መጠናቸው ትልልቅ የሆኑ መጻሕፍት እንዲሁም የ1942፤ 1943፤ 1944 እና 1945 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፎችን ማተምና መጠረዝ ችለናል። በተጨማሪም በእነዚህ የጦርነትና የእገዳ ዓመታት ወቅት በአውስትራሊያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አንድም የመጠበቂያ ግንብ እትም አላመለጣቸውም። ይህም የይሖዋ እጅ አጭር እንዳይደለ የበለጠ አረጋግጦልናል።—ኢሳይያስ 59:1
ድንገተኛ ፍተሻዎችን መቋቋም
ከባድ ጦርነቶች ይካሄዱ በነበረበት ወቅት ምርመራዎች ይካሄዱ ነበር። የንግድ ማተሚያ ቤቶች ብዙውን ጊዜ ምን እንደሚታተም በሚመረምሩ የመንግሥት ባለሥልጣኖች በድንገት ይፈተሹ ነበር። በዚህም ምክንያት በድብቅ ይሥሩ ከነበሩት ማተሚያ ቤቶች አንዱ የማስጠንቀቂያ መሣሪያ ነበረው። እንግዳ ተቀባይዋ በቀላሉ በምትደርስበት ርቀት ወለሉ ላይ መጥሪያ ነበር። የማታውቀው ወይም ተቆጣጣሪ ነው ተብሎ የሚጠረጠር ሰው ደረጃውን መውጣት ሲጀምር መጥሪያውን ትጫናለች።
መጥሪያው ድምፅ ሲሰማ በቅጽበት ሰዎች በሁሉም አቅጣጫ በየመስኮቱ ሲሾልኩ ይታያል! በቅጥር ሠራተኞች ስም የተመዘገቡ የቅጥር ሠራተኞች እየተሠሩ የነበሩትን ማንኛውንም የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች ሆነ ሌላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ለመደበቅ እዚያው ይቆያሉ። ይህን ለማድረግ ለንግድ ደንበኞቻችን ከምናዘጋጃቸው ሌሎች ጽሑፎች ጋር ተመሳሳይ መጠን ያላቸው ወረቀቶችን ይጠቀሙ ነበር።
በአንድ ፍተሻ ወቅት ላይ ሁለት ተቆጣጣሪዎች ሰፋ ያለ መጠን ያላቸው አስቂኝ ነገሮች የተጻፉባቸው መጽሐፎች ላይ ተቀመጡ፤ ሆኖም ከዚያ ቀን በፊት የታተሙ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች ከሥር ነበሩ። በሌላው የከተማው ክፍል በሚገኘው የማተሚያ ቤት ቀን ቀን ለንግድ የሚሆን ኅትመት እናከናውን ነበር፤ ሌሊትና በሳምንቱ የመጨረሻ ቀኖች ደግሞ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎችን እናትም ነበር።
የሚያስፈልገንን ወረቀት ማግኘት
የማተሚያ ወረቀቶችን ማግኘት ትልቅ ችግር ነበር። ሆኖም እንዳንድ ትላልቅ ማተሚያ ቤቶች በጦርነቱ ወቅት የሥራቸው እንቅስቃሴ አነስተኛ በመሆኑ የሚቀርብላቸውን ኮታ ሙሉ በሙሉ ስለማይጠቀሙበት የተረፋቸውን ወረቀት ይሸጡልን ነበር። በአንድ ወቅት ላይ ግን ከሌላ ቦታ ወረቀት አገኘን።
አንድ መርከብ ቡናማ የሆኑ ብዙ ወረቀቶችን ይዞ አውስትራሊያ ደረሰ፤ ይሁን እንጂ መርከቡ በባሕር ላይ ጉዳት ደርሶበት ስለነበር ውሃ ገብቶ ብዙውን ወረቀት አራሰው። ተጭኖ የመጣው ወረቀት በሙሉ ለጨረታ ቀረበ። የሚገርመው ነገር ብቸኛ ተጫራቾች እኛ ነበርን። ይህም በጣም አነስተኛ በሆነ ዋጋ እንድገዛው አስችሎናል። ወረቀቱን ፀሐይ ላይ አደረቅነው፤ በዚህ መንገድ አብዛኛው ወረቀት ጥቅም እንዲውል አደረግን። ከዚያም ለማተሚያ መሣሪያዎች በሚስማማ መንገድ አስተካክለን ቆረጥናቸው።
እንግዲህ ቡናማውን ወረቀት እንዴት ልንጠቀምበት እንችል ይሆን? አስቂኝ ነገር የተጻፉባቸው መጽሐፎችን የሚያነቡ ሰዎች ባለቀለም በሆነ ወረቀት መጠቀም ይችላሉ ብለን አሰብን። አልተሳሳትንም ነበር። ስለዚህ አስቂኝ ነገሮች ለሚጻፍባቸው መጽሐፎች ተመድበው የነበሩትን ነጭ ወረቀቶች የመጠበቂያ ግንብ እና ሌሎች የማኅበሩ ጽሑፎች ለማተም ተጠቀምንባቸው።
ሴቶች የተጫወቱት ከፍተኛ ሚና
በጦርነቱ ዓመታት በአውስትራሊያ ብዙ ክርስቲያን ሴቶች የጥረዛ ሥራን ተምረዋል። ከእነርሱ መካከል አንዳንዶች በአንድ እጅግ ሞቃት በሆነ የበጋ ወቅት ከሰዓት በኋላ ከሲድኒ ከተማ ዳርቻ ከአንድ መንገድ ጀርባ በተከራየነው አነስተኛ ጋራዥ ውስጥ ብቻቸውን ይሠሩ ነበር። እንዳይታዩ በማለት መስኮቱንም ሆነ በሩን ይዘጉታል። ከሙጫው ማቅለጫ ልዩ የሆነ ሽታ ያለው ጭስ ይወጣ ነበር። ሙቀቱም የሚቻል አልነበረም። ስለዚህ ልብሳቸውን አውልቀው በውስጥ ልብሳቸው ይሠሩ ነበር።
ከዕለታት አንድ ቀን በሩ ተንኳኳ። ክርስቲያን እህቶቻችን ማነው ብለው ሲጠይቁ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የመጣው ባለሥልጣን እኔ ነኝ የሚል መልስ ሰጣቸው። በጦርነቱ ጊዜ ሠራተኞችን ወደ ተፈለገው ቦታ እንዲያሰማራ ሥልጣን ከተሰጠው መሥሪያ ቤት የመጣ ሰው ነበር። እኅቶች ከሙቀቱ የተነሣ በውስጥ ልብሳቸው እየሠሩ ስለነበር ሊያስገቡት እንደማይችሉ ጮክ ብለው መለሱለት።
ሹሙ ለጥቂት ጊዜ ዝም አለ። ከዚያም በዚያ አካባቢ ሌላ ቀጠሮ እንዳለውና ምርመራውን ለማካሄድ በሚቀጥለው ቀን ተመልሶ እንደሚመጣ ተናገረ። ወዲያውኑ እነዚህ ሴቶች ደወሉልንና በዚያው ሌሊት የጭነት መኪና ልከን ጥረዛ የሚከናወንበትን ማንኛውም ነገር ወደ ሌላ ቦታ ወሰድነው።
ድብቅ በሆነው የኅትመት ሥራችን ይሳተፉ ከነበሩት አብዛኛዎቹ ቀደም ሲል የኅትመት ሞያ ልምድ ስላልነበራቸው ለተከናወነው ነገር የይሖዋ መንፈስ አስፈላጊውን እርዳታና መመሪያ እንደሰጠ ምንም አልተጠራጠርኩም። በዚህ ሥራ መሳተፍ መቻላችን በእኔና በጥረዛ ክፍል ትሰራ ለነበረችው ለሉሲ ትልቅ መብት ነበር።
በእነዚህ አስቸጋሪ ዓመታት ሥራችን ይካሄድ የነበረው እንዴት ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ጊዜያዊ የበላይ ተመልካች የነበረው ወንድም ከሲድኒ ውጭ 96 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ ከተማ እንዲቀመጥና ከዚያ እንዳይወጣ ትእዛዝ ደረሰው። ትእዛዙ ከመሃል ከተማ ስምንት ኪሎ ሜትር ርቆ እንዳይወጣ የሚያግድ ነው። በወር ለእያንዳንዱ መኪና የሚፈቀደው የቤንዚን ራሽን አራት ተኩል ሊትር ነበር። ይሁን እንጂ ወንድሞች የሲሊንደር ቅርጽ ያለው ከብረት የተሠራ ግማሽ ቶን የሚመዝን በመኪናው ጀርባ በኩል የሚቀመጥ ጋዝ የሚያመነጭ አስደናቂ መሣሪያ ሠሩ። በዚህ ውስጥ ከሰል እየተቃጠለ እንደ ነዳጅ የሚያገለግለውን ካርቦን ሞኖክሳይድ ያመነጫል። እኔና ሌሎች ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የበላይ ተመልካቹን በግዞት ባለበት ከተማ አቅራቢያ ደረቅ ጅረት ለመገናኘት በዚህ መንገድ ተጠቅመን ለበርካታ ሌሊቶች ተጉዘናል። እንዲህ በማድረግ ጋዝ የሚያመነጨውን መሣሪያ አስነስተን ወደ ሲድኒ ከመመለሳችን በፊት ብዙ ጉዳዮች መወያየት ችለን ነበር።
በመጨረሻ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለው እገዳ ለአውስትራሊያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረበ። ዳኛው በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለው እገዳ “ፍርደ ገምደልነት፣ ግብታዊነትና ጭቆና” ነው በማለት በየኑ። የይሖዋ ምሥክሮች ውስጣዊ ሤራ ያካሄዳሉ የሚለውን ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አደረጉት። የከፍተኛው ፍርድ ቤት አባላት በሙሉ ውሳኔውን ደገፉት፤ ስለዚህ ሕጋዊ የሆኑትን የመንግሥቱን የሥራ እንቅስቃሴዎች በገሃድ መቀጠል ቻልን።
ተጨማሪ የሥራ ምደባዎችና በረከቶች
በድብቅ ይከናወን በነበረው የኅትመት ሥራችን ይሠሩ የነበሩ ብዙዎች ከጦርነቱ በኋላ ወደ አቅኚነት አገልግሎት ገቡ። ውሎ አድሮ ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ በኒው ዮርክ በሚገኘው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ሄደዋል። ሉሲና እኔም ይህ ግብ ነበረን፤ ሆኖም በመሃሉ ሴት ልጃችን በመወለዷ ወደ ኅትመት ንግድ ሥራ ለመመለስ ወሰንኩ። ዘወትር የመንግሥቱን ፍላጎቶችን እንድናስቀድም ይሖዋ እንዲረዳን ጸልየናል፤ እርሱም ረድቶናል። በሌላ የአገልጋይነት ሥራ በሚከተለው መንገድ ተሳትፌአለሁ።
በአሁኑ በብሩክሊን ኒው ዮርክ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል በማገልገል ላይ የሚገኘው በወቅቱ ግን በሲድኒ ከተማ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ይሠራ የነበረው ወንድም ሎይድ ባሪ ደወለልኝ። የሚቀጥለው ትልቅ ስብሰባችንን የሚደረግበትን ቀን አውቀው እንደሆነ ጠየቀኝ። እንደማውቀው ስገልጽለት፦ “የምግብ ዝግጅቱ ኃላፊነት ወስደህ እንድትሠራ እፈልጋለሁ” ሲል ተናገረ።
በመደንገጥ ለጥቂት ጊዜ ዝም ካልኩ በኋላ፦ “ግን በሕይወቴ እንዲህ ያለ ሥራ ሠርቼ አላውቅም” በማለት ድክም ባለ መንፈስ መለስኩለት።
“ምንም አይደለም ወንድም” ሲል በማበረታታት መለሰልኝ። “የምትማርበት ጊዜ አሁን ነው!” አዎን ተምሬያለሁ፤ ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ እንኳ የምግብ ዝግጅት የበላይ ተመልካች ሆኜ በማገልገል የመቀጠል መብት አግኝቼአለሁ።
ከዓመታት በኋላ የንግድ ማተሚያ ድርጅታችን ተስፋፋ፤ ይህም ለሥራ ጉዳይ ወደ ሌሎች እንድመላለስ አድርጎኛል። ሁልጊዜ እነዚህ ጉዞዎች በኒው ዮርክ ሲቲና በሌሎች የዩናይትድ ስቴትስ ቦታዎች ከሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ጋር እንዲገጣጠሙ አድርጌያለሁ። ይህም በትላልቅ ስብሰባዎች የተለያዩ ዲፓርትመንቶች በተለይም የምግብ ዝግጅት ክፍል ኃላፊዎች ሆነው ከሚሠሩ ወንድሞች ጋር ተገናኝቶ ለመወያየት አጋጣሚ ሰጥቶኛል። በዚህ መንገድ ወደ አውስትራሊያ ስመለስ የትልልቅ ስብሰባዎቻችንን ፍላጎቶች ለማሟላት በተሻለ ሁኔታ ማገልገል ችያለሁ።
በዕድሜ በገፋንባቸው ዓመታት ሉሲና እኔ ትንሽ ዘግየት ብለን ተወልደን ቢሆን ኖሮ የበለጠ መሥራት እንችል ነበር በማለት እናስባለን። በሌላ በኩል ሉሲ በ1916 እኔ ደግሞ በ1914 በመወለዳችን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በፊታችን ሲፈጸሙ ማየቱ አስደሳች መብት መሆኑን እንረዳለን። በተጨማሪም ብዙ ሰዎችን በማስጠናትና እውነትን እንዲያውቁ በመርዳት እንዲሁም የተጠመቁ አገልጋዮች ሆነው እርሱን ሲያገለግሉ በማየት ላገኘነው በረከት ይሖዋን እናመሰግነዋለን። ምንጊዜም ታላቁ የጽንፈ ዓለም ገዢ እርሱ መሆኑን በመቀበል ለዘላለም እርሱን በማገልገል መቀጠል እንድንችል ጸሎታችን ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የመስከረም 15, 1978 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 24-27 ተመልከት።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኘው ሥዕል]
በስትራትፊልድ ቤቴል የተቋቋመው ማተሚያ፤ 1929-73
ጆርጅ ጊብ ከማተሚያ ቤቱ ውስጥ በስተጀርባ በኩል ባለው ግድግዳ ከተወሰዱት የማተሚያ መሣሪያዎች መካከል ከአንዱ ጎን ቆሞ