የስግብግብነትን ወጥመድ ሽሸው
“ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሡ ግን ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ።” — 1 ጢሞቴዎስ 6:9 አዓት
1. የወጥመዶች ጉዳይ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?
“ወጥመድ” የሚለው ቃል ያልጠረጠረን እንስሳ ሳያስበው ለመያዝ አንድ አዳኝ ያዘጋጀውን አታላይ መሣሪያ ያስታውሰናል። ይሁን እንጂ ለእኛ በጣም አደገኛ የሆኑት እንደነዚህ ዓይነቶቹ የማጥመጂያ መሣሪያዎች ሳይሆኑ በመንፈሳዊና በስነ ምግባር ረገድ ሊያጠምዱን የሚችሉት መሆናቸውን አምላክ በግልጽ ነግሮናል። ዲያብሎስ እነዚህን ወጥመዶች በማስቀመጥ ረገድ ልዩ ችሎታ አለው። — 2 ቆሮንቶስ 2:11፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:24–26
2. (ሀ) ይሖዋ አደገኛ ወጥመዶችን እንድንሸሻቸው የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) አሁን እንድናተኩርበት የተደረግነው የወጥመድ ዓይነት የትኛው ነው?
2 ይሖዋ በዓይነታቸው የተለያዩትንና በርከት ያሉትን አንዳንዶቹን የሰይጣን ወጥመዶች ለይተን እንድናውቅ በማድረግ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል አምላክ ከንፈሮቻችንን ወይም አፋችንን ጥበብ በጎደለው መንገድ ብንጠቀምበት፣ በችኮላ ወይም መናገር የማይገባንን ነገር ብንናገርበት ወጥመድ ሊሆንብን እንደሚችል ያስጠነቅቀናል። (ምሳሌ 18:7፤ 20:25) ከቁጡ ሰው ጋር ባልንጀራ መሆን ወጥመድ እንደሚሆን ሁሉ ኩራትም ወጥመድ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 22:24, 25፤ 29:25) ወደ ሌላው ወጥመድ ደግሞ መለስ እንበል። “ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሡ ግን በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞት ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:9 አዓት) ከዚህ ወጥመድ በስተጀርባ ያለው ነገር ወይም የዚህ ወጥመድ መሠረት “ስግብግብነት” በሚለው ቃል ሊጠቃለል ይችላል። ምንም እንኳ ስግብግብነት ሀብታም ለመሆን ቆርጦ በመነሣት የሚገለጽ ቢሆንም ስግብግብነት ብዙ ገጽታዎች ያሉት ወጥመድ ነው።
ይሖዋ ስለ መስገብገብ አደገኛነት ያስጠነቅቀናል
3, 4. ጥንታዊው የሰው ታሪክ ስለ ስግብግብነት ምን ትምህርት ይዟል?
3 በመሠረቱ ስግብግብነት ገንዘብን፣ ንብረትን፣ ሥልጣንን፣ ጾታን ወይም ሌሎች ነገሮችን በብዛት ለማግኘት የሚገፋፋ ቅጥ ያጣ ወይም ከልክ ያለፈ ምኞት ነው። ለስግብግብነት አደጋ የተጋለጥነው የመጀመሪያዎቹ እኛ አይደለንም። ከረጅም ጊዜ በፊት በኤደን የአትክልት ቦታ ስግብግብነት መጀመሪያ ሔዋንን ቀጥሎም አዳምን አጠመዳቸው። ከእርሷ ይበልጥ የኑሮ ተሞክሮ የነበረው የሔዋን ባል ከይሖዋ በቀጥታ መመሪያ ተቀብሎ ነበር። አምላክ ገነት የሆነ መኖሪያ አዘጋጅቶላቸው ነበር። ባልተበከለች ምድር ላይ የበቀሉ የተለያዩና ጥሩ ጥሩ ምግቦችን ይመገቡ ነበር። አብረዋቸው የሚኖሩና አምላክን ለዘላለም የሚያገለግሉ ፍጹማን ልጆች ይኖሩናል ብለው መጠበቅ ይችሉ ነበር። (ዘፍጥረት 1:27–31፤ 2:15) ማንኛውንም ሰው ለማስደሰት ይህ ዝግጅት በቂ አልነበረምን?
4 ይሁን እንጂ አንድ ሰው በቂ ነገር ማግኘቱ ስግብግብነት እንዳያጠምደው ይከላከልለታል ማለት አይደለም። ሔዋን የሚበልጥ ነፃነት ለማግኘትና የራሷን ደረጃዎች በማውጣት እንደ አምላክ የመሆን ምኞት አጠመዳት። አዳምም የመጣው ይምጣ ብሎ ከውቢቷ ሚስቱ ጋር ባለው ጓደኝነት ለመቀጠል የፈለገ ይመስላል። እነዚህ ፍጹማን ሰዎች በስግብግብነት ወጥመድ ስለተያዙ አንተም ስግብግብነት ለምን አደገኛ እንደሚሆንብን መረዳት አያቅትህም።
5. የስግብግብነትን ወጥመድ መሸሹ ለእኛ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
5 እኛም በስግብግብነት ወጥመድ እንዳንያዝ መጠንቀቅ አለብን፤ ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት አስጠንቅቆናል:- “ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ [ስግብግቦች አዓት] . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) በተጨማሪም ጳውሎስ “ዝሙትና ርኩሰት ሁሉ ወይም መመኘት [ስግብግብነት አዓት] በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ” በማለት ነግሮናል። (ኤፌሶን 5:3) ስለዚህ ፍጹም ያልሆነውን ሥጋችንን ለማስደሰት ስንል ስግብግብነት በጨዋታችን ውስጥ ሊጠቀስ እንኳ አይገባውም።
6, 7. (ሀ) ስግብግብነት ምን ያህል ኃይለኛ ሊሆን እንደሚችል አጉልተው የሚያሳዩት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ምንድን ናቸው? (ለ) እነዚህ ምሳሌዎች ለእኛ ማስጠንቀቂያ ሊሆኑን የሚገባቸው ለምንድን ነው?
6 ይሖዋ የስግብግብነትን አደጋ ነቅተን እንድንጠብቅ እኛን ለመርዳት ብዙ ምሳሌዎችን አስመዝግቦልናል። የአካንን መስገብገብ አስታውስ። አምላክ ኢያሪኮ ፈጽማ እንድትጠፋ ነገር ግን ወርቋ፣ ብሯ፣ ነሐሷ እና ብረቷ ለእርሱ ንብረት ሆነው ገቢ እንዲደረጉ አዘዘ። አካን መጀመሪያ ላይ ይህንን መመሪያ ለመከተል አስቦ ኖሮ ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ስግብግብነት አጠመደው። ኢያሪኮ እንደገባ ለእርሱ ልኩ የሆነ ግሩም ልብስ ጨምሮ ብዙ ነገር በርካሽ የሚገኝበት ገበያ ውስጥ የደረሰ መሰለው። በሺህ በሚቆጠር ብር የሚገመት ወርቅና ብር ሲያገኝ ‘ወይ መታደል! ይኼማ ዘረፋ አይደለም እንዴ!’ ብሎ አስቦ ይሆናል። ልክ እንዳሰበውም ዝርፊያ ወይም ስርቆት ነበር! ሊጠፋ ወይም ገቢ ሊደረግ የሚገባውን በመመኘት የአምላክን ንብረት ሰረቀ፣ አካን ይህን በማድረጉ ሕይወቱን አጣ። (ኢያሱ 6:17–19፤ 7:20–26) እንዲሁም የግያዝንና የአስቆሮቱ ይሁዳን ምሳሌም ተመልከት። — 2 ነገሥት 5:8–27፤ ዮሐንስ 6:64፤ 12:2–6
7 ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱ ሰዎች ስለ ይሖዋ ደረጃዎች ምንም ያማያውቁ አረማውያን አለመሆናቸውንም መርሳት የለብንም። ከዚህ ይልቅ ራሳቸውን ለአምላክ በመወሰን ከእርሱ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ነበራቸው። ሦስቱም የአምላክን ሞገስ እንዳገኙ የመቆየትን አስፈላጊነትና የአምላክን ኃይል የሚያስገነዝቡ ተአምራቶችን በዓይናቸው የተመለከቱ ነበሩ። ይሁን እንጂ የስግብግብነት ወጥመድ ለውድቀታቸው ምክንያት ሆነ። እኛም በማንኛውም ዓይነት መልኩ በስግብግብነት ወጥመድ እንድንጠመድ ብንፈቅድ ከአምላክ ጋር የገባነውን የተቀራረበ ዝምድና ልናጣው እንችላለን። በተለይ ለእኛ አደገኛ ሊሆኑብን የሚችሉ የስግብግብነት ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው?
ለሀብት ወይም ለንብረት በመስገብገብ መጠመድ
8. ሀብትን በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል?
8 አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ሀብታም የመሆንን ፍቅር ከማሳደግ ወይም ለብዙ ሀብት ከመጎምጀት ስለመራቅ የሚናገሩ ግልጽ ማስጠንቀቂያዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሰምተዋል። በማቴዎስ 6:24–33፣ በሉቃስ 12:13–21 እና በ1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10 ላይ የሚገኙትን አንዳንዶቹን ግልጽ ማስጠንቀቂያዎች ለምን መለስ ብለህ አታያቸውም። እነዚህን ምክሮች አምንባቸዋለሁ እሠራባቸውማለሁ የሚል ስሜት ይኖርህ ይሆናል። አካን፣ ግያዝና ይሁዳስ ቢሆኑ እነዚህን ምክሮች እንደሚያምኑባቸው አልተናገሩም ብለህ ታስባለህን? አደርገዋለሁ ብለን በነገሩ ከመስማማት አልፈን መሄድ እንዳለብን ግልጽ ነው። ለሀብት ወይም ለንብረት መስገብገብ ዕለታዊ አኗኗራችንን እንዳይነካብን መጠንቀቅ አለብን።
9. ዕቃ መግዛትን በተመለከተ ዝንባሌያችንን መመርመር የሚገባን ለምንድን ነው?
9 በዕለታዊ ኑሮአችን እንደ ምግብ፣ ልብስና ለቤት የሚያስፈልጉ ሌሎች ነገሮችን መግዛት ይኖርብናል። (ዘፍጥረት 42:1–3፤ 2 ነገሥት 12:11, 12፤ ምሳሌ 31:14, 16፤ ሉቃስ 9:13፤ 17:28፤ 22:36) ነገር ግን የንግዱ ዓለም ተጨማሪ እንዲሁም አዳዲስ ነገሮች እንዲኖሩን የሚያስችል ምኞት እንዲያድርብን ያነሳሳል። ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችንና ቴሌቪዥኖችን የሞሉት ብዙዎቹ የንግድ ማስታወቂያዎች ከሽፋኑ በስተጀርባ ስግብግብነትን የሚያበረታቱ ናቸው። ጃኬቶች፣ ኮቶች፣ ቀሚሶችና ሹራቦች፣ አዳዲስ ጫማዎች በሚያጓጓ ሁኔታ የተደረደሩባቸው ማስቀመጫዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችና ካሜራዎችን ያቀፈ እንዲህ ያለ አቀራረብ በየሱቁ ውስጥ ይገኛል። ክርስቲያኖች ራሳቸውን እንዲህ እያሉ ቢጠይቁ አስተዋይነት ይሆናል:- ‘ዕቃ መግዛት ጎላ ብሎ የሚታይ የሕይወቴ ክፍል ወይም በጣም የምደሰትበት ነገር ሆኗልን?’ ‘የማየው አዲስ ነገር ሁሉ ያስፈልገኛልን? ወይስ የንግዱ ዓለም በውስጤ ስግብግብነትን እየተከለብኝ ነው?’ — 1 ዮሐንስ 2:16
10. በተለይ ለወንዶች አደገኛ የሆነው የስግብግብነት ወጥመድ የትኛው ነው?
10 ዕቃ መግዛት የሴቶች ወጥመድ ሲሆን ብዙ ገንዘብ ለማግኘት መሯሯጥ ደግሞ የብዙ ወንዶች ወጥመድ ነው። ኢየሱስ ይህን ወጥመድ በቂ ገቢ የነበረው ነገር ግን ‘ጎተራውን አፍርሶ ሌላ የሚበልጥ ጎተራ ሠርቶ እህሉንና ያለውን ንብረት በሙሉ ለማከማቸት’ ስላሰበ አንድ ሀብታም ሰው በተናገረው ምሳሌው ላይ ጠቅሶታል። ኢየሱስ “ተጠንቀቁ፣ ከመጐምጀትም ሁሉ [ወይም ከስግብግብነት] ተጠበቁ” በማለት ስግብግብነት አደገኛ መሆኑን በግልጽ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:15–21) ሀብታም ሆንን አልሆንን ይህንን ምክር በሥራ ላይ ማዋል አለብን።
11. አንድ ክርስቲያን ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት በመስገብገብ ወጥመድ ሊያዝ የሚችለው እንዴት ነው?
11 ብዙ ገንዘብ ወይም በገንዘብ የሚገዙ ነገሮችን በብዛት የማግኘቱ ስግብግብነት አብዛኛውን ጊዜ በሌላ ነገር ሽፋን ይመጣል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀብታም ለመሆን የሚያስችል እቅድ ለምሳሌ አክሳሪ ሊሆን ቢችልም አንዴ እንደምንም ተብሎ የሚሞከርበት አስተማማኝ የገንዘብ ማግኛ ዕድል ብቅ ይል ይሆናል። ወይም አንድ ሰው አጠያያቂ በሆነ ወይም በሕገ ወጥ የንግድ ልማዶች ውስጥ ገብቶ ገንዘብ ለማግኘት ይፈተን ይሆናል። ይህ የመጐምጀት ምኞት በጣም ሊያይልና ወጥመድ ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 62:10፤ ምሳሌ 11:1፤ 20:10) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አንዳንዶች እምነት የሚጣልባቸው ወንድሞቻቸው ዋነኛ ደንበኞቻችን ይሆኑልናል በሚል ተስፋ ንግድ ጀምረዋል። ይህን ያደረጉት ተፈላጊ ምርቶችን ወይም አገልግሎቶችን በመስጠት ‘በገዛ እጆቻቸው መልካምን እየሠሩ ለመድከም’ ካልሆነና በክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ነግደው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀብታም ለመሆን በማሰብ ከሆነ ስግብግቦች ናቸው ማለት ነው። (ኤፌሶን 4:28፤ ምሳሌ 20:21፤ 31:17–19, 24፤ 2 ተሰሎንቄ 3:8–12) ለገንዘብ መስገብገብ አንዳንዶቹን በሎተሪ፣ በዕጣዎችና በውርርዶች አማካኝነት ቁማር እንዲጫወቱ አድርጓቸዋል። ሌሎችም አዘኔታንና ምክንያታዊነትን ቸል ብለው ብዙ ገንዘብ ወይም ውርስ ሊያስገኝላቸው የሚችል የፍርድ ቤት ሙግት በችኰላ ጀምረዋል።
12. ለሀብት መስገብግብ ሊወገድ እንደሚችል የምናውቀው ለምንድን ነው?
12 ከላይ የተመለከትናቸው በሙሉ ስግብግብነት በውስጣችን ሰርጎ ገብቶ እንደሆነና እንዳልሆነ በሐቀኝነት ራሳችንን መርምረን ለማወቅ እንድንችል የሚረዱን አቅጣጫዎች ናቸው። ስግብግብነት ካለብንም መለወጥ እንችላለን። ዘኬዎስ እንደተለወጠ አስታውስ። (ሉቃስ 19:1–10) ለሀብት ወይም ለንብረት የመስገብገብ ችግር እንዳለበት የተረዳ ማንም ሰው ከወጥመዱ ለማምለጥ የዘኬዎስን ያህል ቆራጥ እርምጃ መውሰድ አለበት። — ኤርምያስ 17:9
በሌሎች የኑሮ ገጽታዎች የሚገለጽ ስግብግብነት
13. መዝሙር 10:18 የትኛውን ሌላ የስግብግብነት ወጥመድ ይጠቅስልናል?
13 አንዳንዶች በገንዘብ ወይም በንብረት ረገድ የሚገለጸው ስግብግብነት በሌላ መልኩ ከሚገለጸው ይበልጥ አደገኛነቱ ያለምንም ችግር ይታያቸዋል። አንድ የግሪክኛ መዝገበ ቃላት “ስግብግብነት” ወይም “መጐምጀት” ተብለው የተተረጎሙት የቃላት ስብስቦች “ከሥልጣንና ከመሳሰሉት እንዲሁም ከንብረት ጋር በተያያዘ መንገድ ‘ተጨማሪ መፈለግ’ የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ በማለት ተናግሯል። አዎ፣ ተስገብግበን በሌሎች ላይ ያለንን ሥልጣን ለማሳየት፣ ምናልባትም ባለን ሥልጣን የተነሣ እንዲንቀጠቀጡልን እንፈልግ ይሆናል። — መዝሙር 10:18
14. ለሥልጣን ጥመኛ መሆን በየትኞቹ አቅጣጫዎች ጉዳት ያስከትላል?
14 ከጥንት ጀምሮ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በሌሎች ላይ ሥልጣን ነበራቸው። የሰው ኃጢአት ብዙ ባሎች የሚስቶቻቸው ‘ገዢዎች’ እንዲሆኑ ማድረጉ አሳዛኝ ውጤት እንደሚኖረው አምላክ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ዘፍጥረት 3:16) ሆኖም ይህ ድክመት በትዳር አካባቢ ብቻ ሳይወሰን ተስፋፍቷል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ሰው ሰውን ለመጉዳት ገዢ የሚሆንበት ጊዜ አለ” በማለት በሺ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ተናግሯል። (መክብብ 8:9) ይህም በፖለቲካዊ ወይም በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ እውነት መሆኑን ሳትመለከት አትቀርም። ነገር ግን በበኩላችን እንደ አቅማችን የበለጠ ሥልጣን ወይም ተደማጭነትን ለማግኘት እንጥራለንን?
15, 16. አንድ ክርስቲያን ተጨማሪ ሥልጣን በመመኘት ወጥመድ ውስጥ ሊወድቅ የሚችለው በየትኞቹ አቅጣጫዎች ነው? (ፊልጵስዩስ 2:3)
15 ሁላችንም ከሌሎች ሰዎች ጋር ለምሳሌ ከቅርብ የቤተሰብ አባሎቻችን ጋር፣ በመሥሪያ ቤታችን ወይም በትምህርት ቤታችን፣ ከጓደኞቻችን ጋር ስንሆንና በጉባኤ ውስጥ መገናኘታችን አይቀርም። አልፎ አልፎ ወይም አብዛኛውን ጊዜ ምን ቢሠራ ጥሩ እንደሚሆን ወይም እንዴት ወይም መቼ ቢሠራ ጥሩ እንደሆነ በመናገር የውሳኔ ሐሳብ የመስጠት ድርሻ ይኖረን ይሆናል። ይህ በራሱ ምንም መጥፎነት ወይም ስሕተት የሆነ ነገር የለበትም። ይሁን እንጂ ሊኖረን በቻለው በማንኛውም ሥልጣን ከልክ በላይ እንጠቀምበታለንን? ሁልጊዜ የመጨረሻው ውሳኔ የእኛ ብቻ እንዲሆን እንፈልጋለንን? ዓለማዊ ሥራ አስኪያጆች ወይም አለቆች ብዙ ጊዜ እንዲህ ያለውን ዝንባሌ በማሳየት ያላቸውን የሥልጣን ጥማት (ስግብግብነት) በማይጋፉና ሁልጊዜ አዎን አዎን በማለት ከእነሱ አመለካከት ተቃራኒ የሆነ ሐሳብ ፈጽሞ በማይሰነዝሩ አጫፋሪዎች መታጀብ ይፈልጋሉ።
16 ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር በምናደርገው ግንኙነት እንዲህ ያለውን ወጥመድ ልንሸሸው ይገባል። ኢየሱስ “የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ከእናንተ ማንም ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን” ብሏል። (ማቴዎስ 20:25, 26) እንደዚህ ያለው ትሕትና ክርስቲያን ሽማግሌዎች እርስ በርሳቸው፣ ከዲያቆናትና ከመንጋው ጋር ባላቸው ግንኙነት በግልጽ መታየት አለበት። ለምሳሌ የሥልጣን ጥማት አንድ መሪ የበላይ ተመልካች ጥቃቅን በሆኑ ነገሮች ብቻ ከሌሎች ሽማግሌዎች ጋር እየተማከረ ቁልፍ የሆኑ ውሳኔዎችን ግን እርሱ ብቻ በማድረጉ ሊንጸባረቅበት ይችል ይሆንን? የሥራ ክፍፍሎችን ለማድረግስ ፈቃደኛ ነውን? አንድ ዲያቆን የመስክ አግልግሎት ስምሪት ስብሰባን በሚመራበት ጊዜ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ የእሱን ሐሳብ እንዲቀበሉ ለማስገደድ ቢሞክር እንዲያውም ሕግ እስከማውጣት ቢደርስ ችግር ሊፈጠር ይችላል። — 1 ቆሮንቶስ 4:21፤ 9:18፤ 2 ቆሮንቶስ 10:8፤ 13:10፤ 1 ተሰሎንቄ 2:6, 7
17. ስለ ስግብግብነት ወጥመድ ስንወያይ የምግብንም ጉዳይ መጥቀስ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
17 ብዙዎች በስግብግብነት ወጥመድ የሚያዙበት ሌላው ነገር ምግብ ነው። በመብላትና በመጠጣት መደሰት በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም ይህንኑ በመደገፍ የሚናገርባቸው ቦታዎች አሉ። (መክብብ 5:18) ሆኖም ከዚህ ጋር በተያያዘ መንገድ ለረጅም ጊዜ ምኞትን ማሳደርና ከልክና ከጥጋብ በላይ ወደ መብላት መድረስ ያልተለመደ ነገር አይደለም። ይህ በአምላክ አገልጋዮች ሊታሰብበት የሚገባው ተገቢ ጉዳይ ባይሆን ኖሮ የይሖዋ ቃል በምሳሌ 23:20 ላይ “የወይን ጠጅ ከሚጠጡ ጋር አትቀመጥ ለሥጋም ከሚሣሡ ጋር [ሆዳም ሥጋ በላተኞች አዓት]” በማለት ለምን ይናገራል? ታዲያ ይህን ወጥመድ እንዴት ልንሸሸው እንችላለን?
18. ምግብና መጠጥን በሚመለከት ራሳችንን ምን ብለን ልንመረምር እንችላለን?
18 አምላክ ሕዝቦቹ በቁጠባ ተመጥኖ የሚሰጥ ምግብ እየበሉ ይኑሩ የሚል ሐሳብ አልሰጠም። (መክብብ 2:24, 25) እንደዚህም ሲባል መብልንና መጠጥን የጨዋታችንና የእቅዳችን ዋነኛ ክፍል ማድረጋችንን ይደግፈዋል ማለትም አይደለም። ራሳችንን እንዲህ እያልን ልንጠይቅ እንችላለን ‘ስለ በላሁት ምግብ ወይም ልበላው ስላሰበኩት የምግብ ዓይነት በምናገርበት ጊዜ ከመጠን በላይ በአድናቆት ስሜት እዋጣለሁን?’ ‘ስለ መብልና ስለ መጠጥ ሁልጊዜ አወራለሁን?’ ሌላው ምልክት ደግሞ ያላዘጋጀነውን ወይም ያልከፈልንበትን ምግብ ምናልባት እንግድነት ተጋብዘን ወይም በክርስቲያናዊ ትልልቅ ስብሳበዎች ላይ ሲቀርብ የምናሳየው ሁኔታ ነው። በእንደዚህ ዓይነቱ ወቅት ከተለመደው የአመጋገብ ልማዳችን በላይ የመብላት ዝንባሌ ይታይብናልን? ዔሳው በሕይወቱ ውስጥ ምግብ ከልክ በላይ ትልቁን ቦታ እንዲይዝ በመፍቀዱ ለዘለቄታው መጎዳቱን እናስታውሳለን። — ዕብራውያን 12:16
19. ከጾታ ግንኙነት በሚገኘው ደስታ ረገድ ስግብግብነት ችግር ሊፈጥር የሚችለው እንዴት ነው?
19 ጳውሎስ ሌላውን ወጥመድ “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኩሰት ሁሉ ወይም መመኘት [ስግብግብነት አዓት] በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ” በማለት አስታውቆናል። (ኤፌሶን 4:17–19፤ 5:3) ከጾታ ግንኙነት ለሚገኘው ደስታ መስገብገብ በአንድ ሰው ውስጥ ሊያድግ ይችላል። እንደዚህ የመሰለው ደስታ በጋብቻ ማሰሪያ ውስጥ በተገቢ ሁኔታ የሚገለጽበት መንገድ አለው። ከዚህ ደስታ ጋር ተያይዞ የሚገለጸው የሚያቀራርብ የመውደድ ስሜት ባልና ሚስትን ለረጅም ዓመታት ተጣብቀው እንዲኖሩ በመርዳት በኩል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ጳውሎስ ለጠቀሰው ስግብግብነት ነጸብራቅ የሆነውን የዛሬው ዓለም ከልክ በላይ አጋንኖ ለጾታ የሰጠውን ቦታ ብዙ ሰዎች እንደ ቀላል ነገር በመቁጠር ምንም አይደለም ሲሉ ይታያል። በብዙዎቹ ፊልሞች፣ ቪዲዮዎች እና መጽሔቶች እንዲሁም በመዝናኛ ስፍራዎች በጣም ለተስፋፋው ብልግናና እራቁትነት ራሳቸውን አጋልጠው የሰጡ ሰዎች በተለይ ከጾታ ግንኙነት ስለሚገኘው ደስታ የተሳሳተ አመለካከት ይዘዋል።
20. ከጾታ ጋር ለተያያዙት የስግብግብነት አደጋዎች በበኩላቸው ንቁዎች መሆናቸውን ክርስቲያኖች እንዴት ሊያሳዩ ይችላሉ?
20 ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ስለ ሠራው ኃጢአት የሚናገረው ታሪክ አንድ የአምላክ አገልጋይ በጾታ ስግብግብነት ወጥመድ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ያሳያል። በራሱ ጋብቻ በጾታ ለመደሰት ነፃነት ቢኖረውም ዳዊት ሕገወጥ የሆነ የጾታ ምኞት በውስጡ እንዲያድግ ፈቀደ። የኦርዮን ሚስት ምን ያህል ውብ እንደሆነች ተመለከተና ከእርሷ ጋር ሕገወጥ በሆነ መንገድ የመደሰቱን ሐሳብና ድርጊት አልገታውም። (2 ሳሙኤል 11:2–4፤ ያዕቆብ 1:14, 15) እንዲህ የመሰለውን ስግብግብነት ልንሸሸው ይገባል። በጋብቻ ውስጥም እንኳ ስግብግብነትን መሸሽ ያስፈልጋል። ይህም ከልክ ያለፉ የጾታ ግንኙነት ልማዶችን አለመቀበልን ይጨምራል። ስግብግብነትን ለመሸሽ የቆረጠ ባል በዚህ ረገድ ለሚስቱ ከልቡ ሊያስብላት ይችላል። ስለቤተሰባቸው ሁኔታ ሁለቱም ተስማምተው የመረጡት እቅድ ካለ የሚያገኘውን ደስታ ከአሁኑም ሆነ ከወደፊቱ የሚስቱ ጤንነት ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር አድርጎ አይመለከተውም። — ፊልጵስዩስ 2:4
ስግብግብነትን ለመሸሽ ባደረግከው ቁርጥ ውሳኔ ግፋበት
21. ስለ ስግብግብነት ያደረግነው ውይይት ተስፋ ሊያስቆርጠን የማይገባው ለምንድን ነው?
21 ይሖዋ ጥንቃቄ እንድናደርግ የሚመክረን ወይም የሚያስጠነቅቀን ስለማያምነን አይደለም። ለእሱ ያደሩ አገልጋዮቹ በታማኝነት ከጎኑ በመቆም ሊያገለግሉት እንደሚፈልጉ ያውቃል፤ በልበ ሙሉነትም ብዙዎቹ በዚሁ አቋማቸው ይቀጥላሉ ብሎ ተስፋ ያደርጋል። ይሖዋ ስለ ሕዝቦቹ በአጠቃላይ “በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም” በማለት ስለ ኢዮብ ለሰይጣን የተናገረውን ቃል በሚመስል መንገድ ሊናገርላቸው ይችላል። (ኢዮብ 1:8) የሚያፈቅረንና የሚያምነን ሰማያዊው አባታችን ከስግብግብነት ጋር ተያይዘው እንደተገለጹት ላሉት አደገኛ ወጥመዶች የሚያነቃን፣ ሳንበከል እንድንቀጥልና ለእርሱ የታመንን ሆነን እንድንገኝ ስለሚፈልግ ነው።
22. ያደረግነው ጥናት በግላችን አደገኛ የሚሆንብንን ወይም ደካማ የሆንንበትን አቅጣጫ ካሳየን ምን ልናደርግ ይገባናል?
22 ሁላችንም ወደ ስግብግብነት የሚያደላ ዝንባሌ ከመውረሳችንም ሌላ በዚህ ክፉ ዓለም ተጽዕኖ ጨማምረንበት ሊሆን ይችላል። ታዲያ ስለ ስግብግብነት ባደረግነው ጥናት በሀብት፣ በንብረት፣ በኃይልና በሥልጣን፣ በምግብ ወይም ከጾታ ግንኙነት በሚገኘው ተድላ ረገድ አንድ ዓይነት ድክመት እንዳለብህ ተገንዝበህ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? እንግዲያው “እጅህ ብታሰናክልህ ቁረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመሄድ ጉንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻላል” የሚለውን የኢየሱስን ምክር ሥራበት። (ማርቆስ 9:43) በዝንባሌህ ወይም በምትወዳቸው ነገሮች አንጻር አስፈላጊ ሆነው የተገኙትን ለውጦች አድርግ። የሚገድለውን የስግብግብነት ወጥመድ ሽሸው። እንዲህ ካደረግህ በአምላክ እርዳታ “ወደ ሕይወት መግባት” ትችላለህ።
ምን ተማርኩ?
◻ የስግብግብነት ወጥመድ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?
◻ ለሀብት ወይም ለንብረት መስገብገብ ወጥመድ ሊሆንብን የሚችለው በምን መንገዶች ነው?
◻ በሌሎች የኑሮ ዘርፎች ላይ የሚታየው ስግብግብነት አደገኛ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ስግብግብነትን በተመለከተ ላለብን ለማንኛውም ድክመት የሚኖረን አመለካከት ምን ሊሆን ይገባል?