የክርስቲያን ቤተሰብ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ይሰጣል
“ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ በመስማማት ኑሩ፤ የሌላውን ሰው ችግር እንደ ራሳችሁ አድርጋችሁ አስቡ፤ በወንድማማችነት ፍቅር ተወደዱ፤ ደጎችና ትሑቶች ሁኑ።” — 1 ጴጥሮስ 3:8 የ1980 ትርጉም
1. ሁላችንም ምን ምርጫ አለን? ምርጫችንስ የወደፊት ሕይወታችንን እንዴት ይነካዋል?
ከላይ የሚገኘው ጥቅስ እጅግ ጥንታዊ ሰብዓዊ ተቋም ለሆነው ለቤተሰብ በሚገባ ይሠራል! በዚህ ረገድ ወላጆች ምሳሌ መሆናቸው ምንኛ ጠቃሚ ነው! የወላጆች ባሕርይ ገንቢም ይሁን አፍራሽ አብዛኛውን ጊዜ በልጆቻቸው ላይ ይንፀባረቃል። ሆኖም እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የራሱን ምርጫ የመከተል ነፃነት አለው። ክርስቲያኖች ብንሆንም መንፈሳዊ ሰዎች ወይም ሥጋዊ ሰዎች ለመሆን፣ አምላክን ለማስደሰት ወይም ለማስከፋት ልንመርጥ እንችላለን። የምንመርጠው ምርጫ በረከት፣ የዘላለም ሕይወትና ሰላም ሊያመጣልን አለዚያም እርግማንና ዘላለማዊ ሞት ሊያስከትልብን ይችላል። — ዘፍጥረት 4:1, 2፤ ሮሜ 8:5–8፤ ገላትያ 5:19–23
2. (ሀ) ጴጥሮስ ለቤተሰብ እንደሚያስብ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) መንፈሳዊነት ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
2 ሐዋርያው በ1 ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 8 ላይ ያሉትን ቃላት የተናገረው ለሚስቶችና ለባሎች የሚጠቅሙ ጥሩ ጥሩ ምክሮችን ከሰጠ በኋላ ነው። ጴጥሮስ ስለ ክርስቲያን ቤተሰቦች ደኅንነት ከልቡ ያስብ ነበር። አንድነት ያለውና እርስ በርሱ የሚተሳሰብ ቤተሰብ ለመመሥረት ቁልፉ ጠንካራ መንፈሳዊነት መሆኑን ያውቅ ነበር። በዚህ ምክንያት በቁጥር 7 ላይ ለባሎች የሰጠው ምክር ቸል ቢባል ባልየው ከይሖዋ ጋር ያለው ግንኙነት መንፈሳዊ እክል ይገጥመዋል።a ባልየው ሚስቱ የሚያስፈልጋትን ነገር ከማቅረብ ችላ የሚል ወይም ደግነት በጎደለው መንገድ የሚጫናት ከሆነ የሚያቀርባቸው ጸሎቶች ሊታገዱበት ይችላሉ።
የመንፈሳዊነት ፍጹም ምሳሌ የሆነው ክርስቶስ
3. ጳውሎስ የክርስቶስን ጥሩ ምሳሌነት ለባሎች ያጎላው እንዴት ነው?
3 የአንድ ቤተሰብ መንፈሳዊነት ጥሩ ምሳሌ በመሆን ላይ የተመካ ነው። ባልየው ክርስትናን በተግባር የሚያሳይ ሰው ከሆነ መንፈሳዊ ባሕርያትን በማሳየት ረገድ ግንባር ቀደም ይሆናል። የሚያምን ባል ካልኖረ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ እናት ይህንን ኃላፊነት ለመሸከም ትሞክራለች። በሁለቱም ሁኔታዎች ረገድ ልንከተለው የሚገባን ፍጹም አርአያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጠባዩ፣ አነጋገሩና አስተሳሰቡ ሁልጊዜ የሚያንጽና አእምሮን የሚያድስ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ በተደጋጋሚ አንባቢዎቹ የክርስቶስን የፍቅር አርዓያነት እንዲከተሉ አሳስቧል። ለምሳሌ እንዲህ ብሏል:- “ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ ባልም የሚስት ራስ ነው፤ ደግሞም ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን አዳኝዋ ነው። ባሎች ሆይ! ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደደና ራሱን ስለ እርስዋ አሳልፎ እንደ ሰጠ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ።” — ኤፌሶን 5:23, 25, 29 የ1980 ትርጉም፤ ማቴዎስ 11:28–30፤ ቆላስይስ 3:19
4. ኢየሱስ በመንፈሳዊነት ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል?
4 ኢየሱስ በመንፈሳዊነት እንዲሁም በፍቅር፣ በደግነትና በርኅራኄ በሚገለጥ ራስነት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው ምሳሌ ነው። ራሱን የሚያስደስት ሳይሆን ራሱን መሥዋዕት የሚያደርግ ነበር። ሁልጊዜ ለአባቱ ክብር ይሰጥና የአባቱን የራስነት ሥልጣን ያከብር ነበር። የአባቱን መመሪያ ይከተል ስለነበር እንደሚከተለው ለማለት ችሏል:- “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፣ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።” “አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች [አላደርግም።]” — ዮሐንስ 5:30፤ 8:28፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3
5. ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በመስጠቱ ለባሎች ምሳሌ የሚሆናቸው እንዴት ነው?
5 ይህ ለባሎች ምን ትርጉም አለው? በሁሉም ነገር እንደ ምሳሌያቸው አድርገው ሊከተሉት የሚገባቸው ሁልጊዜ ራሱን ለአባቱ ያስገዛ የነበረውን ክርስቶስን ሊሆን ይገባል ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ በምድር ላይ ለሚገኙት ፍጥረታት ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ እንደሰጠ ኢየሱስም ለተከታዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ አቅርቦላቸዋል። የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች ከማቅረብ አልቦዘነም። አንድ ጊዜ 5,000 በሌላ ጊዜ ደግሞ 4,000 ሰዎችን በተዓምር መመገቡ ለአሳቢነቱና ኃላፊነት ይሰማው የነበረ ለመሆኑ ማስረጃ ነው። (ማርቆስ 6:35–44፤ 8:1–9) ዛሬም በተመሳሳይ ኃላፊነት ያለባቸው የቤተሰብ ራሶች የቤተሰባቸው አባላት ስለሚያስፈልጓቸው ሥጋዊ ነገሮች ያስባሉ። ይሁን እንጂ ኃላፊነታቸው በዚህ ብቻ የተወሰነ ነውን? — 1 ጢሞቴዎስ 5:8
6. (ሀ) ሊሟሉ የሚገባቸው የትኞቹ ለቤተሰብ የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ነገሮች ናቸው? (ለ) ባሎችና አባቶች የሰው ችግር የሚገባቸው መሆናቸውን እንዴት ሊያሳዩ ይችላሉ?
6 ኢየሱስ እንደተናገረው ቤተሰቦች ከዚህ የበለጠ አስፈላጊነት ያላቸው መንፈሳዊና ስሜታዊ ፍላጎቶች አሏቸው። (ዘዳግም 8:3፤ ማቴዎስ 4:4) በቤተሰብም ውስጥ ሆነ በጉባኤ አንዳችን በሌላችን እንነካለን። የምናንጽ እንድንሆን የሚገፋፋን ጥሩ አመራር ማግኘት ያስፈልገናል። በዚህ ረገድ ባሎችና አባቶች ሊጫወቱት የሚገባቸው ከፍተኛ ሚና አለ። ሽማግሌዎች ወይም ዲያቆናት ከሆኑ ደግሞ የበለጠ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ነጠላ ወላጆችም ልጆቻቸውን በሚረዱበት ጊዜ ይህንን የመሰሉ ባሕርያት ማንፀባረቅ ያስፈልጋቸዋል። ወላጆች የቤተሰባቸው አባላት የሚናገሩትን ብቻ ሳይሆን ያልተናገሯቸውንም ነገሮች ጭምር መረዳት አለባቸው። ይህም አስተዋይነትን፣ ጊዜንና ትዕግሥትን ይጠይቃል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ባሎች አሳቢዎች መሆንና ከሚስቶቻቸው ጋር በማስተዋል መኖር እንደሚገባቸው የተናገረበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። — 1 ጢሞቴዎስ 3:4, 5, 12፤ 1 ጴጥሮስ 3:7
ልናስወግዳቸው የሚገቡ አደጋዎች
7, 8. (ሀ) ቤተሰቡ መንፈሳዊ ስብራት እንዳያጋጥመው ምን ማድረግ ያስፈልጋል? (ለ) ክርስቲያናዊውን ጉዞ በጥሩ ሁኔታ ከመጀመር በተጨማሪ ምን ያስፈልጋል? (ማቴዎስ 24:13)
7 ለቤተሰብ መንፈሳዊነት ትኩረት መስጠት ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል አንድ የመርከብ ካፒቴን አደገኛ በሆነና ጥልቀት በሌለው ውኃ ላይ በሚጓዝበት ጊዜ ካርታውን በጥንቃቄ መከታተሉ በጣም አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። በነሐሴ ወር 1992 ኩዊን ኤልዛቤት 2 የተባለች ለሽርሽር የምታገለግል አንዲት መርከብ አደገኛ የሆነ የአሸዋ ደለልና አለት ባለበት አካባቢ ታልፍ ነበር። እዚህ ቦታ ላይ ደግሞ መርከበኞች ስህተት መፈጸማቸው የተለመደ እንደሆነ ይነገራል። አንድ የአካባቢው ነዋሪ “ከዚህ አካባቢ የተነሳ ብዙ መርከበኞች ሥራቸውን አጥተዋል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። ኩዊን ኤልዛቤት 2 ከውኃ በታች ካለ አለት ጋር ተጋጨች። ይህ ስህተት መፈጸሙ ከፍተኛ ወጪ አስወጣ። ከመርከቧ አካል አንድ ሦስተኛው በመጎዳቱ መርከቧ እስክትጠገን ድረስ ለበርካታ ወራት አገልግሎት መስጠት አቆመች።
8 በተመሳሳይም የቤተሰቡ “ካፒቴን” የአምላክ ቃል የሆነውን ካርታ በጥንቃቄ ካልተከታተለ ቤተሰቡ መንፈሳዊ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። ሽማግሌ ወይም ዲያቆን ከሆነ ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን መብቶች ሊያጣ፤ ምናልባትም በሌሎቹ የቤተሰቡ አባሎች ላይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። እንግዲያው እያንዳንዱ ክርስቲያን በፊት በነበረው የጥናት ልማድና ቅንዓት በመተማመን በመንፈሳዊ ረገድ ሁሉን ነገር ያሟላ መስሎት ግድየለሽ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርበታል። ክርስቲያናዊ ጉዞአችንን በጥሩ ሁኔታ መጀመር ብቻ አይበቃም፤ ጉዞአችን በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅ አለበት። — 1 ቆሮንቶስ 9:24–27፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:19
9. (ሀ) የግል ጥናት አስፈላጊነት ምን ያህል ነው? (ለ) ራሳችንን ምን ተገቢ የሆኑ ጥያቄዎች ልንጠይቅ እንችላለን?
9 ጥልቀት እንደሌለው ውኃ፣ እንደ አለትና እንደ አሸዋ ደለል ካሉ መንፈሳዊ አደጋዎች ለመጠበቅ የአምላክን ቃል አዘውትረን በማጥናት “ካርታችንን” በጥንቃቄ መከታተል ያስፈልገናል። ወደ እውነት እንድንመጣ ባስቻለን መሠረታዊ ጥናት ብቻ ተማምነን መኖር አንችልም። መንፈሳዊ ጥንካሬያችን የሚመካው ቋሚና ሚዛናዊ የሆነ ፕሮግራም አውጥተን በምናደርገው ጥናትና አገልግሎት ላይ ነው። ለምሳሌ ይህንን እትም ይዘን በጉባኤ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ስንካፈል ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን:- ‘እኔ ወይም ቤተሰቤ በዚህ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ ያሉትን ጥቅሶች አውጥተን እያነበብንና ከትምህርቱ ጋር እንዴት እንደሚያያዙ እያሰላሰልን ርዕሰ ትምህርቱን ከልብ አጥንተነዋል ወይስ እንዲሁ መልሶቹን ብቻ ነው ያሰመርነው? ወደ ስብሰባ ከመምጣታችን በፊት ይህንን ርዕሰ ትምህርት በቅድሚያ ማንበቡን እንኳን ችላ ብለነው ይሆን?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው እውነተኛ መልስ ስለ ጥናት ልምዳችን አጥብቀን እንድናስብና ልምዳችንን ለማሻሻል ፍላጎት እንዲያድርብን ሊያደርገን ይችላል። — ዕብራውያን 5:12–14
10. ራስን መመርመር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
10 ራሳችንን እንዲህ ባለ መንገድ መመርመር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የምንኖረው የሰይጣን መንፈስ በሚቆጣጠረውና በተለያዩ ረቂቅ መንገዶች በአምላክና አምላክ በሰጠን ተስፋዎች ላይ ያለንን እምነት ለማዛባት በሚጥር ዓለም ውስጥ ነው። ይህ ዓለም ስለሚያስፈልጉን መንፈሳዊ ነገሮች የምናስብበት ጊዜ እስክናጣ ድረስ በሥራ እንድንወጠር ሊያደርገን ይፈልጋል። ስለዚህ እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን:- ‘ቤተሰቤ በመንፈሳዊ ጠንካራ ነውን? ወላጅ እንደመሆኔ መጠን የሚገባኝን ያህል በመንፈሳዊ ጠንካራ ነኝን? በጽድቅና በታማኝነት ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚረዳንን አእምሮአችንን የሚያንቀሳቅሰውን መንፈሳዊ ኃይል በቤተሰብ ደረጃ እያዳበርን ነንን?’ — ኤፌሶን 4:23, 24 አዓት
11. ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በመንፈሳዊ ረገድ ጠቃሚዎች የሆኑት ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።
11 በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ በምንገኝበት ጊዜ መንፈሳዊነታችን ይጠናከራል። ኑሯችንን ለማሸነፍ ጥላቻ በሞላበት የሰይጣን ዓለም ውስጥ ለረጅም ሰዓታት ስንደክም ከቆየን በኋላ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ወይም በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ላይ የምንገኝባቸው ውድ ሰዓታት አእምሮአችንን ያድሱልናል። ለምሳሌ ያህል እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ማጥናታችን ምን ያህል አእምሮአችንን አድሶልናል! መጽሐፉ ስለ ኢየሱስ፣ ስለ ሕይወቱና ስለ አገልግሎቱ የተሻለ ግንዛቤ እንድናገኝ ረድቶናል። አውጥተን እንድናነባቸው የቀረቡትን ጥቅሶች በጥንቃቄ አንብበናል፤ በግላችንም ምርምር አድርገንባቸዋል፤ በዚህም ምክንያት ከኢየሱስ ምሳሌ ብዙ ተምረናል። — ዕብራውያን 12:1–3፤ 1 ጴጥሮስ 2:21
12. የመስክ አገልግሎት መንፈሳዊነታችንን የሚፈትነው እንዴት ነው?
12 መንፈሳዊነታችን የሚፈተንበት አንዱ ጥሩ መንገድ ክርስቲያናዊ አገልግሎት ነው። ግድ የለሽ ወይም ተቃዋሚ በሆነ ሕዝብ መካከል በምናደርገው መደበኛም ሆነ መደበኛ ያልሆነ ምስክርነት ወደ ኋላ ሳንል በጽናት እንድንቀጥል ትክክለኛ የሚገፋፋ ኃይል እንዲኖረን ያስፈልጋል። ይህም የሚገፋፋን ኃይል ለአምላክና ለጎረቤቶቻችን ያለን ፍቅር ነው። እርግጥ ነው፤ ማንኛውም ሰው ተቀባይነት ሲያጣ ደስ አይለውም። በመስክ ስናገለግል ተቀባይነት ልናጣ እንችላለን። ይሁን እንጂ አንቀበልም ያሉት ምሥራቹን እንጂ እኛን አለመሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። . . . ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ ስለ ስሜ ያደርጉባችኋል።” — ዮሐንስ 15:18–21
ከቃላት ይልቅ ተግባር የጎላ ድምፅ አለው
13. አንድ ሰው የራሱን ቤተሰብ መንፈሳዊነት ሊሸረሽር የሚችለው እንዴት ነው?
13 በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ከአንዱ የቤተሰብ አባል በስተቀር ሁሉም የቤቱን ጽዳትና ንጽሕና ለመጠበቅ ቢሞክሩ ምን ሊፈጠር ይችላል? በአንድ ዝናባማ ቀን ሁሉም ጭቃ ይዘው ላለመግባት ሲጠነቀቁ ያ ዝንጉ ሰው ግን በጭቃ እግሩ ወደ ቤት ገባ እንበል። እዚህም እዚያም የሚታዩት የጭቃ ምልክቶች የዚያን ሰው ደንታ ቢስነት ያሳያሉ፤ ይህም በሌሎቹ ላይ ሥራ ይጨምርባቸዋል። በመንፈሳዊነት በኩልም ቢሆን እንዲሁ ነው። ከቤተሰቡ ውስጥ አንዱ ራስ ወዳድ ወይም ቸልተኛ ከሆነ የቤተሰቡን ስም ሊያጎድፍ ይችላል። ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰቡ በሙሉ የክርስቶስን አስተሳሰብ ለማንጸባረቅ መጣር ይኖርበታል። ሁሉም የዘላለም ሕይወት ተስፋ እየታያቸው በአንድነት ሲሠሩ እንዴት ያስደስታል! በቤተሰቡ ውስጥ (ራስን ማመጻደቅ ሳይሆን) መንፈሳዊነት ይሰፍናል። እንዲህ ባለ ቤተሰብ ውስጥ በመንፈሳዊ ጉዳዮች እምብዛም ቸልተኝነት አይታይም። — መክብብ 7:16፤ 1 ጴጥሮስ 4:1, 2
14. ሰይጣን ከቁሳዊ ነገሮች ጋር የተያያዙ ምን ፈተናዎችን ይደነቅርብናል?
14 ሁላችንም በሕይወት ለመቆየት የሚረዱ፣ ለሰውነታችን የሚያስፈልጉና በየዕለቱ መሟላት ያለባቸው መሠረታዊ ፍላጎቶች አሉን። (ማቴዎስ 6:11, 30–32) ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ለኑሮ የሚያስፈልጉን ነገሮች እንዲኖሩን በምንመኛቸው በጣም አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮች ይሸፈናሉ። ለምሳሌ የሰይጣን ሥርዓት የተለያዩ መሣሪያዎችና ዕቃዎች ያቀርብልናል። ሁልጊዜ አዳዲስና ዘመናዊ የሆኑ ነገሮች እንዲኖሩን የምንፈልግ ከሆነ ምንጊዜም አንረካም፤ ምክንያቱም የመጨረሻ ነው የተባለው ሞዴል በሌላ አዲስና የተሻሻለ ሞዴል ተተክቶ የበፊቱ ሞዴል ዘመኑ ያለፈበት ይሆናል። የንግዱ ዓለም ማቆሚያ የሌለው እሽክርክሪት አዘጋጅቷል። እየጨመረ የሚሄደውን ፍላጎታችንን ለማርካት እንድንችል ሁልጊዜ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት እንድንጥር ያባብለናል። ይህም ‘ወደ ማይረባና ወደሚጎዳ ብዙ ምኞት’ ወይም ‘ከንቱና አደገኛ ወደሆነ ምኞት’ ሊመራን ይችላል፤ በዚህም ምክንያት ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምንመድበው ሰዓት እየቀነሰ ሄዶ ሚዛናዊነት የጎደለው ሕይወት ሊኖረን ይችላል። — 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10 የ1980 ትርጉም
15. የቤተሰቡ ራስ ጥሩ ምሳሌ መሆኑ አስፈላጊ የሚሆነው በምን መንገድ ነው?
15 በዚህም በኩል ቢሆን የክርስቲያኑ ቤተሰብ ራስ ምሳሌ ሆኖ መገኘቱ በጣም አስፈላጊ ነው። ለሥጋዊም ሆነ ለመንፈሳዊ ኃላፊነቶቹ ያለው ሚዛናዊ አመለካከት የቤተሰቡን ሌሎች አባላት ለመልካም ሥራ የሚያነሳሳቸው መሆን ይገባዋል። አባትየው ጥሩ ጥሩ የቃል መመሪያዎችን እየሰጠ የተናገራቸውን ነገሮች ግን በተግባር የማያውላቸው ከሆነ ጉዳት ማስከተሉ የተረጋገጠ ነው። እኔ እንደምላችሁ እንጂ እንደምሠራው አታድርጉ የሚል ዝንባሌ እንዳለው ልጆቹ ወዲያው ያውቁበታል። በተመሳሳይም አንድ ሽማግሌ ወይም ዲያቆን ሌሎች ከቤት ወደ ቤት እንዲሄዱ እያበረታታ እርሱ ግን ከቤተሰቦቹ ጋር ሆኖ በዚህ ሥራ የማይካፈል ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በቤተሰቡም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ያለው ተሰሚነት እየቀነሰ ይሄዳል። — 1 ቆሮንቶስ 15:58፤ ከማቴዎስ 23:3 ጋር አወዳድር።
16. ራሳችንን ምን ጥያቄዎች መጠየቅ እንችላለን?
16 ስለዚህ ራሳችንን ብንመረምር ብዙ እንጠቀማለን። በዓለማዊ ሥራችን ዕድገት ለማግኘት በምናደርገው ጥረት ተጠምደን መንፈሳዊ ዕድገት ለማግኘት መጣራችንን ችላ ብለናልን? በሥጋዊ ኑሮአችን ስንመጥቅ በጉባኤ ውስጥ ባለን አቋም ግን እያሽቆለቆልን በመሄድ ላይ እንገኛለንን? “ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው” የሚለውን የጳውሎስን ምክር አስታውስ። (1 ጢሞቴዎስ 3:1) በሥራችን ከምናገኘው ዕድገት ይልቅ በጉባኤ ውስጥ የሚታይብን የኃላፊነት ስሜት ስለ መንፈሳዊነታችን ብዙ ይናገራል። ራሳችንን ለይሖዋ ሳይሆን ለመሥሪያ ቤት አለቆቻችን የወሰንን ይመስል እነርሱ እንደፈለጉ እንዲቆጣጠሩን እንዳንፈቅድላቸው ሚዛናዊነታችንን በጥንቃቄ መጠበቅ አለብን። — ማቴዎስ 6:24
ትርጉም ያለው የሐሳብ ግንኙነት መንፈሳዊነትን ያዳብራል
17. በቤተሰብ ውስጥ እውነተኛ ፍቅር እንዲኖር አስተዋፅኦ የሚያደርገው ምንድን ነው?
17 በዛሬው ጊዜ ብዙ ቤቶች ልክ እንደ ሆስቴሎች እየሆኑ መጥተዋል። እንዴት? የቤተሰቡ አባሎች ለመተኛትና ለመብላት ሲሉ ብቻ እቤት ይመጡና ከዚያ በኋላ በቶሎ ወደየጉዳያቸው ይሄዳሉ። ብዙውን ጊዜ በአንድ ገበታ ላይ አብረው አይበሉም። የቤተሰብ ትርጉም እየጠፋ ነው። ይህስ ምን ውጤት አስከተለ? የሐሳብ ግንኙነት የለም፤ ቁም ነገር አይጨዋወቱም። ይህ ደግሞ ለቤተሰብ አባላት ግድየለሽ ወደመሆን ምናልባትም አንዱ ለሌላው ደንታ የሌለው እስከመሆን ሊያደርሳቸው ይችላል። እርስ በእርሳችን ስንዋደድ ለመወያየትና አንዳችን ሌላውን ለማዳመጥ ጊዜ ይኖረናል። አንዳችን ሌላችንን እናበረታታለን፤ እንዲሁም እንረዳዳለን። እንዲህ ያለው መንፈሳዊነት በባልና በሚስት እንዲሁም በወላጆችና በልጆች መካከል ትርጉም ያለው የሐሳብ ግንኙነት ማድረግን ይጨምራል።b ያስደሰቱንንና ያጋጠሙንን ነገሮች እንዲሁም ችግሮቻችንን ለመካፈል እርስ በእርሳችን እንድንነጋገር ጊዜና ዘዴ ያስፈልገናል። — 1 ቆሮንቶስ 13:4–8፤ ያዕቆብ 1:19
18. (ሀ) ብዙውን ጊዜ የሐሳብ ግንኙነት እንዳናደርግ መሰናክል ከሚሆኑብን ነገሮች ዋነኛው ምንድን ነው? (ለ) ትርጉም ያላቸው ግንኙነቶች የሚገነቡት በምን ላይ ነው?
18 ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ጊዜና ጥረት ያስፈልጋል። የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ እርስ በእርስ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መመደብ ማለት ነው። የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ መሰናክል ከሚሆኑት ትልልቅ ነገሮች አንዱ በብዙ ቤቶች ውስጥ ትልቅ ከበሬታ ያገኘውና ጊዜ ገዳይ መሣሪያ የሆነው ቴሌቪዥን ነው። ይህም ቴሌቪዥኑን የምትቆጣጠረው አንተ ነህ ወይስ ቴሌቪዥኑ አንተን ይቆጣጠርሃል? የሚል ፈታኝ ጥያቄ ያስነሳል። ቴሌቪዥን የማየትን ልማድ መቆጣጠር ቴሌቪዥኑን እስከ ማጥፋት የሚያደርስ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግን ይጠይቃል። ይህም እርስ በርሳችን እንደ አንድ ቤተሰብ አባላት እንዲሁም እንደ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች እየተያየን በስምምነትና በመረዳዳት እንድንኖር መንገድ ይከፍትልናል። ትርጉም ያለው ዝምድና እንዲኖረን ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንን ማድረጋችን አንዳችን የሌላው ችግር የሚገባን እንድንሆን፣ ሌላው የሚያስፈልጉትን ነገሮች እንድንረዳ እንዲሁም ደስታችንን እንድንጋራና ለተደረጉልን መልካም ነገሮች ያለንን አመስጋኝነት ለመግለጽ እንድንችል ይረዳናል። በሌላ አነጋገር ትርጉም ያለው ጭውውት ማድረጋችን አንዳችን ሌላችንን እንደ ተራ ነገር አድርገን እንደማንቆጥር ያሳያል። — ምሳሌ 31:28, 29
19, 20. ለመላው ቤተሰብ የምናስብ ከሆነ ምን እናደርጋለን?
19 ስለዚህ በቤተሰባችን ውስጥ አንዳችን ለሌላችን ለማያምኑ የቤተሰቡ አባሎችም ጭምር የምናስብ ከሆንን እርስ በርስ ለመተናነጽና መንፈሳዊነታችንን ለመጠበቅ እንጥራለን ማለት ነው። “በቀረውስ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ በመስማማት ኑሩ፤ የሌላውን ሰው ችግር እንደ ራሳችሁ አድርጋችሁ አስቡ፤ በወንድማማችነት ፍቅር ተዋደዱ፤ ደጎችና ትሑቶች ሁኑ። መርቁ እንጂ ክፉውን በክፉ ፈንታ ስድብንም በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት ይህን በማድረግ በረከትን ለመውረስ ነው።” የሚለውንም የጴጥሮስን ምክር በቤተሰብ ክልል ውስጥ በሥራ ላይ እናውላለን። — 1 ጴጥሮስ 3:8, 9 የ1980 ትርጉም
20 መንፈሳዊነታችንን ለመጠበቅ የምንጣጣር ከሆነ በአሁኑ ጊዜ የይሖዋን በረከት ልናገኝ እንችላለን። ወደፊት ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ሽልማት እንድንቀበል ሊያደርገን ይችላል። እርስ በርስ በመንፈሳዊ ለመረዳዳት በቤተሰብ ደረጃ ልናደርጋቸው የምንችላቸው ሌሎች ነገሮችም አሉ። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ አብሮ ሲሠራ የሚገኙትን ጥቅሞች ይገልጻል። — ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 21:1–4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መንፈሳዊነት “ለሃይማኖታዊ ሥነ ምግባሮች መቆርቆር ወይም ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባሮችን መውደድ፤ መንፈሳዊ የመሆን ባሕርይ ወይም ሁኔታ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። (ዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮሊጄት ዲክሽነሪ) መንፈሳዊ ሰው እንስሳዊ ባሕርያት ካሉት ሥጋዊ ሰው የተለየ ነው። — 1 ቆሮንቶስ 2:13–16፤ ገላትያ 5:16, 25፤ ያዕቆብ 3:14, 15፤ ይሁዳ 19
b በቤተሰብ መካከል ሊኖር ስለሚገባው የሐሳብ ግንኙነት ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የመስከረም 1, 1991 የመጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 20–22ን ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ መንፈሳዊነት ምንድን ነው?
◻ አንድ የቤተሰብ ራስ ክርስቶስን ሊመስል የሚችለው እንዴት ነው?
◻ መንፈሳዊነታችንን ስጋት ላይ የሚጥሉ ነገሮችን ለማስወገድ ምን ልናደርግ እንችላለን?
◻ የአንድን ቤተሰብ መንፈሳዊነት ምን ሊሸረሽረው ይችላል?
◻ ትርጉም ያለው የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ላይ መገኘት የቤተሰቡን መንፈሳዊነት ያጠነክራል