ከአደገኛ ሁኔታ ሽሽ
ከመርከበኞች ይበልጥ አደገኛ ሁኔታን በንቃት የሚከታተሉ ሰዎች ብዙ አይደሉም። መርከበኞች የአየሩን፣ የማዕበሉን ወይም የሞገዱን ሁኔታና መርከቡ ከባሕሩ ዳርቻ በምን ያህል ርቀት የሚገኝ መሆኑን በጥንቃቄ መከታተል አለባቸው። ማዕበልና ነፋስ ባንድ ላይ ሆነው መርከቧን ወደ ባሕሩ ዳርቻ በሚገፏት ጊዜ መርከበኞች ከባድ ሥራና አደገኛ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል።
እንዲህ ባለው አደገኛ ሁኔታ በተለይ መርከቧ በነፋስ በሚገፋ ሸራ የምትንቀሳቀስ ከሆነች መርከበኛው በመርከቧና በባሕሩ ዳርቻ መካከል በቂ ርቀት እንዲኖር ጥረት ያደርጋል። አንድ የመርከብ አነዳድ መመሪያ መጽሔት ኃይለኛ ማዕበል በሚኖርበት ጊዜ በባሕር ዳርቻ አካባቢ መሆን ‘አንድ መርከበኛ ሊያጋጥሙት ከሚችሉት አደገኛ ሁኔታዎች ሁሉ የከፋ’ እንደሚሆን አብራርቷል። ታዲያ መፍትሔ ሆኖ የቀረበው ሐሳብ ምንድን ነው? ‘መርከብህ እንዲህ ባለው አደገኛ ሁኔታ እንዲገኝ ፈጽሞ አትፍቀድ’ የሚል ነው። በአሸዋማ ወይም በአለታማ የባሕር ዳርቻ የሚደርሰውን የመስጠም አደጋ ለማስቀረት የሚደረገው ጥንቃቄ ከአደገኛው ሁኔታ መራቅ ነው።
ክርስቲያኖች የእምነት መርከባቸውን ሊያሰጥምባቸው የሚችሉ አደጋዎችን ነቅተው መከታተል አለባቸው። (1 ጢሞቴዎስ 1:19) የምንኖርበት ሁኔታ በመረጥነው መንገድ ጸንተን እንድንኖር የሚያመች አይደለም። አንዲት ጀልባ በነፋስና በማዕበል ተገፍታ ከመንገዷ እንደምትወጣ ሁሉ እኛም ሳያቋርጥ ወደ ኋላ በሚጎትተን ፍጹም ባልሆነው ሥጋችንና የማዕበል ያህል ኃያል በሆነውና ሳያቋርጥ በሚነፍሰው የዓለም መንፈስ ተገፍተን ለአምላከ የወሰንነውን የሕይወት መስመር ልንስት እንቸላለን።
በአደገኛ አካባቢ ይኖር የነበረ አንድ ሰው
ሳይታወቀን በአደገኛ መንፈሳዊ ውኃዎች ውስጥ መግባት ምንኛ ቀላል ነው!
ለምሳሌ ያህል በየብስ በተከበበው የሙት ባሕር አካባቢ የደረሰውን ሁኔታ እንመልከት። የሎጥን ምሳሌ እንጥቀስ። በሰዶም ለመኖር ያደረገው ውሳኔ ብዙ ችግርና ኃዘን አስከትሎበታል። አብርሃምና ሎጥ መንጎቻቸውን በሚጠብቁት እረኞች መካከል ጥል በመነሣቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለመኖር ተስማሙ። ሎጥ በዮርዳኖስ አውራጃ ዙርያ ያለውን ቦታ እንደመረጠና በአውራጃው ሜዳ ባሉት ከተሞች ድንኳኑን እንደተከለ ታሪኩ ይነግረናል። ቆይቶም የሰዶማውያን አኗኗር ቢያስጨንቀውም በሰዶም ለመኖር ወሰነ።—ዘፍጥረት 13:5–13፤ 2 ጴጥሮስ 2:8
ሎጥ ከሥነ ምግባር ውጭ በሆነ አኗኗራቸው ይሖዋን በጥልቅ ባሳዘኑትና በአካባቢያቸው የነበሩት ሕዝቦች እንዲጮሁ ምክንያት በሆኑት ሰዎች ከተማ መኖሩን የቀጠለው ለምን ነበር? የሰዶም ከተማ የበለጸገች ነበረች፤ የሎጥ ሚስትም በከተማው ካለው ኑሮ ባገኘችው ቁሳዊ ጥቅም እንደ ተደሰተች አያጠራጥርም። (ሕዝቅኤል 16:49, 50) ምናልባት ሎጥም ጭምር ሞቅ ባለው የሰዶም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተማርኮ ይሆናል። የኖረበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ከከተማዋ ቀደም ብሎ መውጣት ነበረበት። በመጨረሻም ሎጥና ቤተሰቡ አደገኛውን አካባቢ ለቅቀው የወጡት የይሖዋ መላእክት እንዲወጡ በማስቸኮል ከወተወቷቸው በኋላ ነበር።
የዘፍጥረት ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን፦ ተነሣ፣ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፤ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፋ እያሉ ያስቸኩሉት ነበር።” ሎጥ እንዲህ ያለ አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠው በኋላም ‘ዘግይቷል።’ በኋላም መላእክት “የእርሱን እጅ የሚስቱንም እጅ የሁለቱን የሴቶች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት።”—ዘፍጥረት 19:15, 16
ሎጥና ቤተሰቡ በከተማይቱ ዳር እያሉ መላእክቱ “ራስህን አድን፤ ወደ ኋላህ አትይ፣ በዚህም ዙርያ ሁሉ አትቁም እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ” በማለት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጡ። (ዘፍጥረት 19:17) ያም ሆኖ ሎጥ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለቅቆ ከመውጣት ይልቅ ቅርብ ወደሆነችው ከተማ ወደ ዞዓር ለመሄድ እንዲፈቅዱለት ለመነ። (ዘፍጥረት 19:18–22) ሎጥ በተቻለው መጠን ከአደጋ ለመሸሽ ፈቃደኛ እንዳልነበረ ግልጽ ነው።
ወደ ዞዓር ሲገቡ የሎጥ ሚስት ትታቸው የወጣቻቸውን ነገሮች በመመኘት ይመስላል ወደ ኋላዋ ተመለከተች። የመላእክቱን ትእዛዝ ችላ በማለቷ ሕይወቷን አጣች። ጻድቁ ሎጥ ከሁለት ሴቶች ልጆቹ ጋር ከከተማዋ ጥፋት ዳነ። ሆኖም ከአደጋ ሳይርቅ ለመኖር በመምረጡ በጣም ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ከፈለ።—ዘፍጥረት 19:18– 26፤ 2 ጴጥሮስ 2:7
አደጋ ሊያስከትል ከሚችል ሁኔታ መራቅ
በሎጥ ላይ የደረሰው መራራ ተሞክሮ አደገኛ ወደሆነ አካባቢ ብንቀርብ ወይም ከአደገኛው አካባቢ ላለመውጣት ብናመነታ ምን ሊደርስብን እንደሚችል ያሳያል። ጎበዝ መርከበኞች እንደሚያደርጉት እንዲህ ካለው አደገኛ ሁኔታ ብንርቅ ጥበበኞች መሆናችንን እናሳያለን። ልንርቃቸው የሚገቡን አንዳንድ አደገኛ አካበቢዎች የትኞቹ ናቸው? አንዳንድ ክርስቲያኖች በሥራ ጉዳዮች ከመጠን በላይ በመጠላለፋቸው፣ ከዓለማዊ ጓደኞች ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መመሥረታቸው ወይም ለማግባት በማያስችላቸው ሁኔታ ላይ እያሉ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ስሜታዊ ቅርርብ በማድረጋቸው ከመንገዳቸው ስተዋል።
ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች ሁሉ አደጋ ሊያስከትሉ ከሚችሉት ሁኔታዎችን መራቅ ጥበብ ነው። ለምሳሌ ያህል ወርቃማ የሥራ አጋጣሚ የሚባሉት ሁኔታዎች ለሚያስከትሏቸው መንፈሳዊ አደጋዎች ንቁዎች ነንን? አንዳንድ ወንድሞች ቤተሰቦቻቸውንና ጤንነታቸውን ጎድተው፣ ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶቻቸውን ችላ ብለው በንግድ ሥራዎች ተጠላልፈዋል። አንዳንዴ የሚያታልላቸው ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለው የተሻለ የምቾት ኑሮ ይሆናል። ሌሎችን ደግሞ የሚያታልላቸው የንግድ ችሎታቸውን ለማስመስከር ያላቸው ፍላጎት ነው። አንዳንዶች እንዲህ ባለው ሥራ ለመጠላለፍ የተገፋፉት ለሌሎች ወንድሞች የሥራ መስክ ለማስገኘት ወይም በዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ ተጨማሪ መዋጮ ለማድረግ እንዲችሉ በማሰብ እንደሆነ ይናገራሉ። ምናልባትም ንግዱ በደንብ ሲካሄድ የመንግሥቱን ጉዳዮች ለማራመድ ተጨማሪ ጊዜ ይኖረናል ብለው አስበውም ይሆናል።
ካሰቡት እንዳይደርሱ የሚያግዷቸው አንዳንድ እንቅፋቶች ምንድን ናቸው? ያልተረጋጋው የኢኮኖሚ ሁኔታ ወይም ‘ጊዜና አጋጣሚ’ ጥሩ እቅድ የተደረገበትን ሥራ ሊያሰናክሉት ይችላሉ። (መክብብ 9:11) ከከባድ ዕዳ ጋር የሚደረገው ትግል ጭንቀት ከመፍጠሩም በላይ ለመንፈሳዊ ነገሮች ጊዜ ያሳጣል። አንድ ሥራ ወይም ንግድ ቢሳካም እንኳ ጊዜ የሚያሟጥጥና አእምሮን የሚያደክም እንዲሁም ከዓለማውያን ጋር መቀራረብን የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል።
በስፔይን የሚኖር አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ አንድ የመድን ኩባንያ የሚያስጎመጅ ሐሳብ ባቀረበለት ጊዜ በከባድ የገንዘብ ችግር ላይ ይገኝ ነበር። በትርፍ ጊዜው የኢንሹራስ ወኪል መሆኑ ብዙ ገንዘብ ሊያገኝ የሚያስችለው ቢሆንም የቀረበለትን ሐሳብ አልተቀበለውም። ሁኔታውን እንዲህ ሲል ያስረዳል፦ “ቀላል ውሳኔ አልነበረም፤ ቢሆንም አልፈልግም በማለቴ ተደስቻለሁ። አንደኛ ነገር ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ቢሆንም ቲኦክራሲያዊ ትውውቅ ካለኝ ሰዎች የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት ፈቃደኛ አልነበርኩም። ራሴን በራሴ የማስተዳደሩን ሐሳብ ብወደውም በሥራ ምክንያት ብዙ መጓዝና ለብዙ ሰዓት መሥራት ነበረብኝ። ይህ ደግሞ ቤተሰቤንና ጉባኤውን ችላ እንድል ማድረጉ የማይቀር ነበር። ከሁሉም በላይ ቀርቦልኝ የነበረውን ሐሳብ ተቀብዬ ቢሆን ኖሮ ሕይወቴን መቆጣጠር ይሳነኝ እንደነበር አምናለሁ።”
ማንም ክርስቲያን ሕይወቱን መቆጣጠር እንዲሳነው አይፈቅድም። ኢየሱስ በእረፍትና በምቾት ለመኖር በማሰብ ብዙ ሀብት ስላከማቸው ሰው ምሳሌ በመናገር እንዲህ ያለው አካሄድ ሊያስክትል የሚችለውን አሳዛኝ ውጤት ገልጿል። ይህ ሰው በቂ ገንዘብ አጠራቅሜአለሁ ብሎ ባሰበበት ሌሊት ሞተ። ኢየሱስ “ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፣ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው” በማለት አስጠነቀቀ።—ሉቃስ 12:16–21፤ ከያዕቆብ 4:13–17 ጋር አወዳድር።
በተጨማሪም ከዓለማዊ ሰዎች ጋር የጠበቀ ቅርርብ እንዳይኖረን መጠንቀቅ አለብን። ምናልባት ጎረቤት፣ የትምህርት ቤት ጓደኛ፣ የሥራ ባልደረባ ወይም የንግድ ሸሪካችን ሊሆን ይችላል። ‘የይሖዋ ምስክሮችን ያከብራል፣ ጥሩ ሥነ ምግባር አለው፤ አልፎ አልፎም ስለ እውነት እንነጋገራለን’ ብለን እናስብ ይሆናል። ሆኖም የሌሎች ተሞክሮ እንዳረጋገጠው ውሎ አድሮ እንዲህ ያለውን ዓለማዊ ጓደኛ ከመንፈሳዊ ወንድማችን ወይም እኅታችን አስበልጠን ልንገኝ እንችላለን። እንዲህ ያለው ቅርርብ የሚያስከትላቸው አንዳንድ አደጋዎች ምንድን ናቸው?
የምንኖርበት ጊዜ አጣዳፊ መሆኑን አቅልለን ማየት ወይም ከመንፈሳዊ ነገሮች ይልቅ ለቁሳዊ ነገሮች ያለንን ፍላጎት ማሳደግ ልንጀምር እንችላለን። ምናልባትም ዓለማዊ ጓደኛችንን ላለማስከፋት ስንል በዓለም ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ምኞትም ሊያድርብን ይችል ይሆናል። (ከ1 ጴጥሮስ 4:3–7 ጋር አወዳድር።) በሌላ በኩል ደግሞ መዝሙራዊው ዳዊት ይሖዋን ከሚወዱት ሰዎች ጋር ጓደኛ መሆንን መርጧል። “ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፣ በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 22:22) የዳዊትን ምሳሌ በመከተል በመንፈሳዊ ሊገነባን የሚችል ጓደኝነት መፈለጋችን ከአደጋ ይጠብቀናል።
ሌላው በጣም አደገኛ የሆነው አካሄድ ደግሞ ማግባት በማያስችል ሁኔታ ላይ እያሉ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ስሜታዊ ቅርርብ መመሥረት ነው። የተቀራረብነው ሰው አመለካከቱ ከራሳችን አመለካከት ጋር የሚስማማ፣ የሚማርክና ተጫዋች ሲሆን አደገኛ ይሆናል። አንድ ሰው ‘እስከ ምን ድረስ እንደምቀራረብ አውቃለሁ። ከጓደኝነት ያለፈ ነገር የለንም’ የሚል ምክንያት በማቅረብ መቀራረብ ሊያስደስተው ይችላል። ሆኖም ስሜት አንዴ ከተቀሰቀሰ በኋላ ለመቆጣጠር ቀላል አይሆንም።
ሜሪ የተባለች ወጣት ባለትዳር እኅት ከማይክል ጋር መሆን ደስ ይላት ነበር።a ማይክል ጥሩ ወንድም ቢሆንም ጓደኛ ለማግኘት ተቸግሮ ነበር። ማይክልና ሜሪ የሚመሳሰሉባቸው ብዙ ነገሮች ነበሯቸው። በተጨማሪም እርስ በእርሳቸው ለመቀላለድና ለመጨዋወት እንደሚችሉ ተገነዘቡ። ሜሪ አንድ ነጠላ ወንድም ምስጢሩን ሲያካፍላት ደስ አላት። ብዙም ሳይቆይ ንጹሕ ወዳጅነት ይመስል የነበረው ቅርርብ ጥልቅ ወደ ሆነ ስሜታዊ መፈቃቀር ተለወጠ። ብዙ ጊዜ አብረው ያሳልፉ ነበር። ከጊዜ በኋላም የጾታ ብልግና ፈጸሙ። “አደጋው ሊከሰት እንደሚችል ከመጀመሪያው መገንዘብ ነበረብኝ። ጓደኝነታችን ካደገ በኋላ ይበልጥ ጥልቅ ወደሆነ ጉድጓድ የሚያሰምጥ ሲረግጡት የሚከዳ አሸዋ ሆነብን” በማለት ሜሪ በትካዜ ትናገራለች።
መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?” ሲል የሰጠውን ማስጠንቀቂያ መርሳት የለብንም። (ኤርምያስ 17:9) ሞገድ በነፋስ ኃይል የምትንቀሳቀሰዋን ጀልባ ከአለት ጋር ለማጋጨት እንደሚገፋት ሁሉ እኛንም ተንኮለኛው ልባችን አጥፊ ወደሆነ ስሜታዊ ቅርርብ ሊገፋፋን ይቸላል። ታዲያ መፍትሄው ምን ይሆን? ማግባት በማያስችል ሁኔታ ላይ ከሆንክ ማራኪ ሆኖ ካገኘኸው ሰው ሆን ብለህ ለመራቅ ጥረት አድርግ።—ምሳሌ 10:23
ከአደጋ መላቀቅና ዳግመኛ ላለመያዝ መጠንቀቅ
በመንፈሳዊ አደጋ ውስጥ የምንገኝ ብንሆንስ? መርከበኞች መርከባቸው በነፋስና በማዕበል ምክንያት ወደ አለታማ የባሕር ዳርቻ ሲወሰድባቸው ባላቸው ኃይል ሁሉ ማዕበል ወደሌለበት ውኃ እስኪደርሱ ድረስ ከዳርቻው ለመራቅ ወደ ባሕሩ ለመቅዘፍ ይጥራሉ። እኛም በተመሳሳይ ከአደጋ ለመላቀቅ መታገል አለብን። የሚሰጠንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተቀብለን በሥራ በማዋል፣ ይሖዋ እንዲረዳን ከልብ በመጸለይና ከጎለመሱ ክርስቲያን ወንድሞች እርዳታ በመጠየቅ አደጋ ወደማያስከትለው አቅጣጫ ልናቀና እንችላለን። የአእምሮና የልብ ሰላምም መልሰን በማግኘት እንባረካለን።—1 ተሰሎንቄ 5:17
በምንም ሁኔታዎች ሥር ብንገኝ ‘ከዚህ ዓለም ነገሮች’ በመራቅ ጥበበኛ እንሁን። (ገላትያ 4:3) አብርሃም ለብዙ ዓመታት በድንኳን ቢኖርም ከሎጥ በተለየ መንገድ ዓለማዊ ከሆኑት ከነዓናውያን ርቆ ለመኖር መርጧል። ምናልባት በቁሳዊ ነገሮች ረገድ አንዳንድ ምቾቶችን አጥቶ ሊሆን ይችላል፤ ቢሆንም ቀላል የነበረው አኗኗሩ በመንፈሳዊ ጠብቆታል። አብርሃም የእምነት መርከቡን ከማጥፋት ይልቅ “ለሚያምኑ ሁሉ አባት” ለመሆን በቅቷል።—ሮሜ 4:11
የስሜት ደስታ ለማግኘት በሚጥረውና ‘መንፈሱ’ እያየለ በሚሄደው በዚህ ዓለም ተከብበን ስንኖር የአብርሃምን ምሳሌ መከተል አለብን። (ኤፌሶን 2:2) በሁሉም ጉዳዮች የይሖዋን መመሪያ ከተቀበልን ፍቅራዊ ጥበቃውን በማግኘት እንባረካለን። እኛም ዳዊት የተሰማው ዓይነት ስሜት ይሰማናል፦ “ሕይወቴን ያድሳል፤ ስለ ስሙም በትክክለኛ መንገድ ይመራኛል። ደግነትህና ፍቅርህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ እንደማይለዩኝ እርግጠኛ ነኝ፤ አምላኬ ሆይ! ለዘላለም በቤትህ እኖራለሁ።”—መዝሙር 23:3, 6 የ1980 ትርጉም
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሞቻቸው ተለውጠዋል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማግባት በማያስችል ሁኔታ ላይ ከሆንክ ማራኪ ሆኖ ካገኘኸው ሰው ጋር ስሜታዊ ቅርርብ ከመመሥረት ራቅ