የማርያም ፍልሰታ በአምላክ የተገለጠ ቀኖና ነውን?
የኢየሱስ እናት ማርያም ከነሥጋዋ ወደ ሰማይ ዐርጋለች የሚለው በሚልዮን የሚቆጠሩ ካቶሊኮች የሚያምኑበት መሠረተ ትምህርት የማርያም ፍልሰታ ተብሎ ይጠራል። ታሪክ ጸሐፊው ጆርጅ ዊልያም ዳግላስ “የድንግል ማርያም ፍልሰታ ወይም ወደ ሰማይ ማረግ ቤተ ክርስቲያኗ በየዓመቱ ከምታከብራቸው በዓሎች ሁሉ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውና ከማርያም መታሰቢያ በዓሎች ሁሉ ታላቁ ነው” ይላል።
የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ሊቃውንት መጽሐፍ ቅዱስ ማርያም ወደ ሰማይ ስለ ማረጓ ምንም እንደማይናገር ያምናሉ። እንዲያውም ይህ ተወዳጅ መሠረተ ትምህርት ብዙ ዘመን ሲያጨቃጭቅ እና ሲያከራክር የቆየ ጉዳይ መሆኑን የሚያውቁት በጣም ጥቂት ካቶሊኮች ናቸው። ታዲያ ቤተ ክርስቲያኗ የማርያምን ፍልሰታ እንደ ቀኖና አድርጋ እንዴት ልትቀበለው ቻለች?a በአምላክ የተገለጠ ቀኖና ነው ብሎ ለማመን የሚያስችል ምክንያት አለን? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የአእምሮ እውቀት ለማግኘት ተብሎ ብቻ የሚመረመር አይደለም። እውነትን ለሚያፈቅሩ ሰዎች ትልቅ ትርጉም አለው።
የቀኖናው አመጣጥ
ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት ማርያም ወደ ሰማይ አርጋለች የሚለው አሳብ በክርስቲያኖች ዘንድ ፈጽሞ የማይታወቅ እንደነበረ ስታውቅ ትገረም ይሆናል። ዛህ ጋሎ የተባሉት ካቶሊካዊ የሃይማኖት ሊቅ ሎሳርቫቶሬ ሮማኖ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “መጀመሪያ አካባቢ የማርያም ሞት መታሰቢያ ከክርስቲያናዊው ኅብረተሰብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበረውም” በማለት ጽፈዋል።
የሥላሴ ትምህርት የቤተ ክርስቲያን ዋነኛ መሠረተ ትምህርት ከሆነ በኋላ ግን ለማርያም ከፍተኛ ቦታ መስጠት ተጀመረ። “ወላዲተ አምላክ”፣ “ያለኃጢአት የተፀነሰች”፣ “አማላጅቷ” እና “የሰማይ ንግሥት” የሚሉት አንጸባራቂ ስሞች ተሰጧት። የሃይማኖት ሊቅ የሆኑት ጋሎ “የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ስለ ማርያም አሟሟት ምንም የገለጹት ነገር አለመኖሩ የማርያምን ፍጹምነት የተገነዘቡትንና የቅድስና አክብሮት ሊሰጧት የፈለጉትን አላረካም። በዚህም ምክንያት ሕዝባዊ ግምት የወለደው የማርያም ዕርገት ወይም ፍልሰታ መግለጫ ተፈጠረ” በማለት ምክንያቱን አስረድተዋል።
በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ አካባቢ የፍልሰታ ማርያም ራእይ የሚባል አዋልድ መጽሐፍ መሰራጨት ጀመረ። ይህ መጽሐፍ ማርያም ወደ ሰማይ ስላረገችበት ሁኔታ የሚናገሩ አስገራሚ ነገሮች ይገኙበታል። ለምሳሌ ያህል “የቅድስት ወላዲተ አምላክ አሟሟት” የሚለውን የጽሑፉን ክፍል እንውሰድ። መጽሐፉ የተጻፈው ዮሐንስ ከሞተ ከ400 ዓመታት በኋላ ቢሆንም ይህንን የጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስ ነው ይባላል። በዚህ የሐሰት ታሪክ መሠረት የክርስቶስ ሐዋርያት በተአምር ወደ ማርያም ተሰብስበው ዕውር፣ ደንቆሮ እና አንካሳ ስትፈውስ ተመለከቱ። በመጨረሻም ጌታ ማርያምን “እነሆ፣ የተወደደው ሥጋሽ ወደ ገነት ይወሰዳል፣ ቅዱስ ነፍስሽም በሰማይ በአባቴ ዘንድ የቅዱሳን መላእክት ሰላምና ደስታ በሰፈነበት ደማቅ ብርሃን ውስጥ በተትረፈረፈ ብልጽግና ለዘላለም ትኖራለች” ሲል ሐዋርያቱ እንደሰሙ ተጽፏል።
አማኞች እንደዚህ ያሉትን ጽሑፎች እንዴት ተቀበሉ? ማሪዮሎጂስት ሬነ ሎረንታ “የአማኞቹ አቀባበል በጣም የተለያየ ነው። በጣም ተጠራጣሪ የሆኑት እንኳ በዚህ አምሮና ደምቆ በቀረበ ታሪክ ተመስጠው አለምንም ምርምርና ጥያቄ ተቀብለውታል። ሌሎች ደግሞ እርስ በርሱ የሚጋጭና ሊታመን የማይችል ነው በማለት አቃልለውታል። ስለዚህ የማርያም ዕርገት ንድፈ ሐሳብ ተቀባይነት የማግኘት ችግር አለበት። ይበልጥ ግራ የሚያጋባው ደግሞ በአንዳንድ ቦታዎች የማርያም ሥጋ ተገኘ እየተባለ መከበሩ ነው። ይህ ደግሞ የማርያም ሥጋ ወደ ሰማይ ዐርጓል ከሚለው እምነት ጋር ሊታረቅና ሊስማማ የማይችል አባባል ነው።
በ13ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ቶማስ አኪናስም እንደ ሌሎቹ ሃይማኖታዊ ሊቃውንት “ቅዱስ ጽሑፉ ስለማያስተምር” የማርያምን ዕርገት ቀኖና አድርጎ መደንገግ አይቻልም የሚል አቋም ነበረው። ቢሆንም እምነቱ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል። እንደ ራፋኤል፣ ኮሬጂዮ፣ ቲትያን፣ ካራቺ እና ሩቤንስ ያሉት የታወቁ ሠዓሊዎች የማርያምን ዕርገት የሚያሳዩ ሥዕሎች ሥለዋል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለዚህ ጥያቄ እልባት ሳይደረግበት ቆይቶ ነበር። ኢየሱሳዊው ጁዜፔ ፌሎግራሴ እንደሚሉት እስከዚህ መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ድረስ ካቶሊካዊ ምሁራን የማርያምን ዕርገት ንድፈ ሐሳብ “የማይደግፉ ጥናቶችና ውይይቶች” እየጻፉ ያሳትሙ ነበር። ሌላው ቀርቶ እንደ ሊዎ 13ኛ፣ ፓየስ 10ኛ እና ቤነዲክት 15ኛ የመሳሰሉት ጳጳሶች “በጉዳዩ ላይ ሐሳብ ከመስጠት ተቆጥበዋል።” ይሁን እንጂ ኅዳር 1, 1950 ቤተ ክርስቲያኗ ቁርጥ ያለ አቋም ወሰደች። ፓየስ 12ኛ የተባሉት ጳጳስ “አምላክን በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የወለደችው፣ ከዚያም ወዲህ በድንግልና የምትኖረው ማርያም ምድራዊ ሕይወቷ ሲያበቃ ሥጋና ነፍሷ በአንድነት ወደ ክብራማው ሰማይ ተወስዷል በማለት የማርያምን ፍልሰታ በአምላክ የተገለጠ ቀኖና ነው ብለን እንደነግጋለን” በማለት አስታወቁ።—ሙነፈከንቲስመስ ዲዮስ
ማርያም ከነሥጋዋ ወደ ሰማይ ሄዳለች የሚለው እምነት ካቶሊካውያን ቢፈልጉ የሚያምኑት ባይፈልጉ የሚተዉት ትምህርት መሆኑ ቀርቷል። የቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና ሆኗል። ፓየስ 12ኛ የተባሉት ጳጳስ “ማንም ሰው . . . እኛ የደነገግነውን ሊክድ ወይም በደነገግነው ላይ ጥርጣሬ ሊዘራ ቢሞክር ከመለኮታዊው ካቶሊክ እምነት ያፈነገጠና የራቀ እንደሚሆን ማወቅ ይገባዋል” በማለት ተናግረዋል።
ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ይላሉ?
ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህንን የድፍረት አቋም የወሰደችው ምንን መሠረት አድርጋ ነው? ፓየስ 12ኛ የተባሉት ጳጳስ ማርያም ዐርጋለች የሚለው ቀኖና “በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተመሠረተ ነው” ብለዋል። ማርያም ዐርጋለች የሚለውን ትምህርት ይደግፋሉ ተብለው ከሚጠቀሱት ጥቅሶች አንዱ ሉቃስ 1:28, 42 ነው። ጥቅሱ “ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ . . . የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው” በማለት ስለ ማርያም ይናገራል። የማርያም ዕርገት አማኞች ማርያም “ጸጋ የሞላባት” ስለሆነች በሞት ልትሸነፍ አትችልም ይላሉ። እንደ ‘ማሕፀኗ ፍሬ’ “የተባረከች” ስለሆነች ከኢየሱስ ጋር የሚተካከል መብት ማግኘትና ማረግ ይኖርባታል ብለው ያስባሉ። ይህ ትክክለኛ ምክንያት ነው ብለህ ታስባለህን?
አንደኛ ነገር የቋንቋ ምሁራን “ጸጋ የሞላብሽ” የሚለው ሐረግ ትክክለኛ ያልሆነ ትርጉም ከመሆኑም በላይ ሉቃስ የተጠቀመበት የግሪክኛው ሐረግ “የአምላክን ሞገስ ያገኘሽ” ተብሎ መተርጎም ይኖርበታል ይላሉ። በዚህ ምክንያት የካቶሊክ ጀሩሳሌም ባይብል ሉቃስ 1:28ን “ከፍተኛ ሞገስ ስላገኘሽ ደስ ይበልሽ” በማለት ተርጉሞታል። ማርያም የአምላክን “ከፍተኛ ሞገስ ስላገኘች” ብቻ በሥጋ ወደ ሰማይ ተወስዳለች ብሎ ለመደምደም የሚያስችል ምንም ምክንያት የለም። የመጀመሪያው ክርስቲያን ሰማዕት እስጢፋኖስ በካቶሊክ ዱዌይ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ጸጋ የሞላበት” ወይም ከፍተኛ ሞገስ ያገኘ እንደሆነ ተገልጿል። ይሁን እንጂ ሥጋዊ ትንሣኤ እንዳገኘ አልተገለጸም። — ሥራ 6:8
ይሁን እንጂ ማርያም የተባረከች ወይም ሞገስ ያገኘች አልነበረችምን? አዎን ነበረች፤ ነገር ግን በእስራኤላውያን የመሳፍንት ዘመን የነበረችው ኢያኤል የተባለችው ሴትም “ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን” ተብላለች። (መሳፍንት 5:24) ኢያኤል ከነሥጋዋ ወደ ሰማይ ተወስዳለች ብሎ የሚከራከር ሰው እንደማይኖር የታወቀ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ማርያም ዐርጋለች የሚለው ሐሳብ ኢየሱስ ራሱ በሥጋ ወደ ሰማይ ዐርጓል በሚለው ላይ የተመሠረተ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ኢየሱስ “በመንፈስ ሕያው ሆነ” ወይም ተነሣ ይላል። (1 ጴጥሮስ 3:18፤ ከ1 ቆሮንቶስ 15:45 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ “ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 15:42 – 50
በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ሰማያዊ ትንሣኤ እንደሚያገኙ መጽሐፍ ቅዱስ መናገሩ እውነት ነው። ይሁን እንጂ 1 ተሰሎንቄ 4:13–17 ይህ ትንሣኤ እስከዚህ ክፉ ዘመን የመጨረሻ ቀኖች ማለትም “ጌታ እስከሚገኝበት” ጊዜ እንደማይጀምር በግልጽ ይናገራል። ማርያም ከሌሎች በሺህ ከሚቆጠሩ ታማኝ ክርስቲያኖች ጋር እስከዚህ ዘመን ድረስ በሞት እንዳንቀላፋች መቆየት ነበረባት።—1 ቆሮንቶስ 15:51, 52
የእምነት ሰው የነበረችው ማርያም
ከላይ ያለውን በምንናገርበት ጊዜ ማርያምን ማዋረዳችን እንዳልሆነ እርግጠኛ ሁን። ማርያም በእምነቷ ልንመስላት የሚገባ ጥሩ ምሳሌ የምትሆን ሴት ለመሆኗ ምንም ጥርጥር የለውም። ብዙ መከራና መሥዋዕትነት የሚያስከትልባት ቢሆንም የተሰጣትን የኢየሱስ እናት የመሆን መብት ያለምንም ማንገራገር ተቀብላለች። (ሉቃስ 1:38፤ 2:34, 35) ከዮሴፍ ጋር በመሆን ኢየሱስን በአምላካዊ ጥበብ አሳድጋለች። (ሉቃስ 2:51, 52) ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ በሚሠቃይበት ጊዜ ሁሉ ከአጠገቡ ሳትለይ ቆይታለች። (ዮሐንስ 19:25–27) እንዲሁም ታማኝ ደቀ መዝሙር እንደ መሆኗ በታዛዥነት በኢየሩሳሌም ቆይታ በጰንጠቆስጤ ዕለት የአምላክ መንፈስ ፈስሶባታል።—ሥራ 1:13, 14፤ 2:1–4
ስለ ማርያም የተዛባ አመለካከት መያዝ ፈጣሪንም ሆነ ማርያምን አያስከብርም። ማርያም ዐርጋለች የሚለው ቀኖና ማርያም አምላክን ታማልዳለች የሚለውን መሠረተ ቢስ የሆነ አባባል ያጠነክራል። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የመሰለ ትምህርት አስተምሯልን? ከዚህ ይልቅ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 14:6, 14፤ ከሥራ 4:12 ጋር አወዳድር።) አዎን፣ ከፈጣሪ ጋር የሚያማልደን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ እንጂ ማርያም አይደለችም። ወደ ሕይወት ሰጪያችን “በሚያስፈልገን ጊዜ” ልንቀርብ የሚገባን በኢየሱስ በኩል እንጂ በማርያም በኩል መሆን አይገባውም።—ዕብራውያን 4:16 ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርሽን፣ ካቶሊክ ኤዲሽን
ስለ ማርያም እውነቱን መቀበሉ ለአንዳንዶች ይከብድ ይሆናል። ቢያንስ ቢያንስ ለረጅም ጊዜ የተያዘ እምነትና ተወዳጅ የሆነ አስተሳሰብ መተው ይሆናል። እውነት መራራ የሚሆንበት ጊዜ ቢኖርም በመጨረሻ ‘አርነት የሚያወጣው’ እውነት ነው። (ዮሐንስ 8:32) ኢየሱስ አባቱ የሚፈልገው “በመንፈስና በእውነት” የሚያመልኩትን እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:24) እነዚህ ቃሎች ቅን የሆኑ ካቶሊኮችን የሚፈታተኑ ናቸው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በካቶሊክ እምነት ሃይማኖታዊ ቀኖና በቀላሉ የሚታይ እምነት ሳይሆን በአብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ወይም “የማይሳሳት አስተማሪ” ነው በሚባለው በጳጳሱ የሚደነገግ እውነት ነው ተብሎ ይታመናል። በቅርቡ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንደ ቀኖና ሆነው ከተደነገጉት መሠረተ ትምህርቶች አንዱ የማርያም ፍልሰታ ወይም ዕርገት ነው።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ማርያም ሞታለችን?
እንደሚባለው ማርያም ወደ ሰማይ ከማረጓ በፊት ሞታለችን? የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ሊቃውንት በዚህ ረገድ በሁለት የማይወዱት ቲዎሎጂያዊ አማራጭ ውስጥ ወድቀዋል። ኖቮ ዲዝዮናሪዮ ዲ ተኦሎጊያ “ማርያም በሞት የማይደፈር ሕይወት አላት ማለት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ እንኳ እንዲህ ዓይነቱ ባሕርይ አልነበረውም” በማለት አመልክቷል። በሌላው በኩል ደግሞ ማርያም ሞታለች ብሎ መናገሩ በዚያው ልክ ከባድ ጭቅጭቅ ያስነሣል። ካር በርሰን የተባሉት ሃይማኖታዊ ሊቅ “ሞት ለመጀመሪያው ኃጢአት የሚሰጥ ቅጣት ነው። ማርያም ደግሞ [“ያለ ኃጢአት የተፀነሰች ናት” በሚለው መሠረተ ትምህርት] መሠረት ይህ ቅጣት አይመለከታትም” ብለዋል። ታዲያ የምትሞተው በምን ምክንያት ነው? ፓየስ 12ኛ የተባሉት ጳጳስ የማርያምን ዕርገት ቀኖና በሚደነግጉበት ጊዜ ስለ ማርያም አሟሟት የተነሣውን አጨቃጫቂ ነጥብ ሳይጠቅሱ ማለፋቸው አያስደንቅም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደዚህ ከመሰለው ዝብርቅ ነፃ መሆኑ ደስ ያሰኛል። ማርያም “ከኃጢአት ነፃ ሆና ተጸንሳለች” የሚለው ትምህርትም ሆነ ሐሳብ በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አይገኝም። በተቃራኒው ግን ማርያም ከኃጢያት መንጻት የሚያስፈልጋት ፍጹም ያልሆነች ሴት እንደነበረች ያመለክታል። በዚህ ምክንያት ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዳ ለአምላክ የኃጢያት መሥዋዕት አቅርባለች። (ዘሌዋውያን 12:1–8፤ ሉቃስ 2:22–24) ማርያምም እንደ ሌሎቹ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ሞታለች።—ሮሜ 3:23፤ 6:23
ይህ ቀላል እውነት ስለ ማርያም ፍልሰታ የተደነገገው ቀኖና ካስነሣው መልስ የማይገኝለት ጥያቄ ፍጹም ተቃራኒ ነው።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ የድንግል ዕርገት’ በቲቲያን የተሣለ (1488–1576 ገደማ)
[ምንጭ]
Giraudon/Art Resource, N.Y.
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማርያም ከኢየሱስ መወለድ በኋላ ወደ ቤተ መቅደሱ የኃጢአት መሥዋዕት በመውሰድ እራሷ ከኃጢአት መንጻት የሚያስፈልጋት ኃጢአተኛ መሆኗን አስታውቃለች