የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“ለትብብር መንፈስ መታሰቢያ የሚሆን ሕንፃ”
በደቡባዊ ስፔይን ጫፍ ላይ ከአንድ ድንጋይ የተፈለፈለ የጂብራልተር ቋጥኝ በመባል የሚታወቅ ግዙፍ የሆነ አንድ የበሃ ድንጋይ አለ። ይህ ድንጋይ ለብዙ መቶ ዓመታት ፖለቲካዊና ብሔራዊ ግጭቶችን በዝምታ ሲመለከት ኖሯል። በቅርቡ ግን የጂብራልተር ቋጥኝ የሚገኝበት አካባቢ ከዚህ ቀደም ታይቶ ከነበረው በተቃራኒ በዛሬው ዓለም እምብዛም የማይታይ ትብብርና አንድነት ታይቶበታል።
ከቋጥኙ 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ላ ሊኒያ የተባለች የስፔይን ከተማ ትገኛለች። በዚህ ቦታ በሚካሄደው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በነፃ ለመለገስ ዝግጁ የሆኑ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች በአንድ ላይ መጥተዋል። እነዚህ ሰዎች ለፈጣሪያቸው ለይሖዋ አምላክ አምልኮ ተስማሚ የሆነ ሕንፃ ለማቆም ጠንክረው በሚሠሩበት ወቅት የጂብራልተር ቋጥኝ በመሠራት ላይ ካለው ሕንፃ ጋር ሲወዳደር ቀድሞ ያገኝ የነበረውን ትኩረት አጣ።
በዚያ አገር ያሉ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቀጥሎ ያለውን ሪፖርት ልከዋል፦
“ዓርብ፣ መስከረም 24, 1993 ከሰዓት በኋላ ጀምረው ዘጠኝ መቶ የሚሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሌት ተቀን በጋለ ስሜት ሠርተዋል። እሁድ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ሕንፃው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ መሆኑን የሚያስታውቅ ጽሑፍ መንገዱ ዳር ላይ ተተከለ። ይህ የሚያምር አዲስ ሕንፃ በዚያው ቀን የመጀመሪያው ሕዝባዊ ስብሰባ ተካሄደበት።
“በአቅራቢያው ከምትገኘው ጂብራልተር ብዙ ምሥክሮች የስፔይን ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ድንበር ተሻግረው መጡ። የጂብራልተር ተወላጅ የሆነ አንድ ፈቃደኛ ሠራተኛ ‘ፖለቲካዊ ድንበር ዓለም አቀፋዊ የወንድማማችነት መንፈሳችንን አላቀዘቀዘብንም’ ሲል ተናግሯል። አክሎም ‘ከአንድ አራት ዓመት በፊት ወንድሞቻችን በጂብራልተር ያለውን የመንግሥት አዳራሻችንን ስንሠራ እኛን ለማገዝ ከላ ሊኒያ ድረስ መጥተው ነበር። ስለዚህ ውለታቸውን ለመመለስ በመምጣታችን ደስተኞች ነን።’
“ሁለቱ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ካደረጉት ልግስናና ከአንደሉዢያን አካባቢ ከመጡት ችሎታ ያላቸው ረዳት ሠራተኞች በተጨማሪ የላ ሊኒያ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የመንግሥት አዳራሹን ለመሥራት የሚያስፈልገውን ቦታ በነፃ ለመስጠት ወሰነ። የላ ሊኒያ ከንቲባ የመንግሥት አዳራሹ ሲሠራ ባደረጉት ጉብኝት ላይ እንዲህ አሉ፦ ‘በአካባቢው ለሚሠሩት የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት መሥሪያ የሚሆን ቦታ መስጠት በስፔይን ባለ ሥልጣኖች ዘንድ የተለመደ ነው። ለሌሎቹ ሃይማኖቶችስ ለምን እንደዚያ አይደረግም? ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ባሳዩት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ልገሳ በጣም ተነክቻለሁ፤ ልንደግፋቸው እንደሚገባ ተሰምቶኛል። ዛሬ ባለው የተከፋፈለ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለው መንፈስ ያስፈልገናል።’
“ከንቲባው ስለ መንግሥት አዳራሹ ሲናገሩ ‘ለትብብር መንፈስ መታሰቢያ የሚሆን ሕንፃ ነው’ ብለዋል። በእርግጥ ተመልካችን በጣም ያስደነቀው ነገር የሕንፃው ዲዛይን ወይም መጠን አልነበረም። የመንደሩን ሰዎች በጣም ያስደነቃቸው በሕንፃው ሥራ ላይ ተሠማርተው የነበሩት ሁሉም ፈቃደኛ ሠራተኞች መሆናቸውና በ48 ሰዓት ብቻ ተሠርቶ ማለቁ ነው!”
በላ ሊኒያና በዙሪያዋ ባሉት አካባቢዎች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በገላትያ 6:10 ላይ የሚገኙትን ቃላት በታማኝነት በሥራ ላይ አውለዋቸዋል። እዚያ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ መሰል አማኞችን “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ” በማለት መክሯቸው ነበር።