የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 8/15 ገጽ 5-7
  • ምሥራቹን ለማየት የታወሩ ዓይኖችን መግለጥ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምሥራቹን ለማየት የታወሩ ዓይኖችን መግለጥ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መንፈሳዊ መታወርን ማሸነፍ
  • ዘላቂ ፈውስ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው
  • በአምላክ አዲስ ዓለም የሚኖረው ደስታ
  • ዓይነ ስውራን ስለ ይሖዋ እንዲማሩ እርዷቸው
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2015
  • ዓይነ ስውራን ምን ተስፋ አላቸው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ዓይነ ስውርነት
    ንቁ!—2015
  • ፈሪሳውያን ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው በጥያቄ አፋጠጡት
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 8/15 ገጽ 5-7

ምሥራቹን ለማየት የታወሩ ዓይኖችን መግለጥ

አንድ የዴንማርኮች አነጋገር “ዓይነ ስውር ስላላየው ሰማይ ሰማያዊነቱ አይደበዝዝም” ይላል። እኛስ ከቀን ወደ ቀን ጥድፊያ በሞላበት ዓለም ውስጥ ስንኖር ሁኔታዎች ጥርት ብለው ይታዩናልን? የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንመለከተዋለንን? የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርብልንን ምሥራች በእርግጥ እናምናለንን?

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ አካላዊ ዓይነ ስውርነትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ተመልክተን ነበር። አሁን ደግሞ ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን የማየት ችሎታ እስቲ እንመርምር። ይህ ዓይነቱ የማየት ችሎታ ዘላቂ ደስታችንን እንዲሁም የምናፈቅራቸው ሰዎች ያላቸውን የወደፊት ተስፋ የሚነካ ይሆናል።

የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ዘመን’ ውስጥ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ሰዎች የዕለት ጉርስ ለማግኘት በሚፍጨረጨሩበት፣ ከጤናና ከቤተሰብ ችግሮች ጋር በሚታገሉበት እንዲሁም በማኅበራዊ ኑሮ የሚከሰተውን የፍትሕ መዛባትና የፍቅር እጦትን ለመወጣት በሚደክሙበት በአሁኑ ጊዜ እየታየ ያለው ነገር ምንድን ነው? አብዛኞቹ ሰዎች በጓደኞቻቸው፣ በሃይማኖትና በመንግሥት ላይ ያላቸው እምነት እየተዳከመ ሄዷል። አንዳንዶች ምንም መውጫ መንገድ እንደሌለ ተሰምቷቸው ችግሮቻቸው በቀላሉ መፍትሔ ሊያገኙ አይችሉም ወደሚል ድምዳሜ ደርሰዋል። ዣኮብ ፒኘይሩ ጎልድበርግ የተባሉ ሰው በብራዚል አገር በሚታተም ዦርናል ዳ ታርዴ በተባለ አንድ ጋዜጣ ላይ “በአሁኑ ጊዜ ያሉት ሰዎች የሚያስመርሩ እውነታዎች ከፊታቸው ድቅን ሲሉ ስሕተቱ ምን ላይ እንደሆነ ረጋ ብለው በማሰብ ፋንታ በተፈጠሩት ስሕተቶች ይበሳጫሉ፤ እንዲሁም ፋይዳ ወደሌላቸው ሃይማኖቶች ፊታቸውን በማዞር መፍትሔ ለማግኘት ይሞክራሉ” በማለት የታዘቡትን ጽፈዋል። ቢሆንም ነገሮች ቢበላሹም እንኳ ምክንያታዊ አስተሳሰብ እንዲኖረን እንፈልጋለን። አይደለም እንዴ?

ለቤተሰብህ መኖሪያ ቤት ለማግኘት አስበሃል እንበል። ቤቱ ይገኝ እንጂ በገንዘብ በኩል ምንም ችግር የለብህም። ምናልባትም በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ቤቶችን በማጠያየቅ ዞረህ ፈልገህ ይሆናል። የቤት ደላላዎች የምትፈልገውን ዓይነት ቤት ለማግኘት ቢጥሩም ያሰብከው ቤት አልተገኘም። የቤተሰብህን ደህንነትና ደስታ የሚነካ በመሆኑ ተስማሚውን ቤት እስክታገኝ ድረስ ከመፈለግ ወደኋላ አትልም። ትላለህ እንዴ? በመጨረሻው የተመኘኸውን ቤት ስታገኝ የሚሰማህን ደስታ አስብ።

አዲስ ቤት ለማግኘት ጊዜ ወስደህ እንደምታፈላልግ ሁሉ ለችግሮችህ መፍትሔ የሚሆኑ ሐሳቦችን ለማግኘት ለምን መጽሐፍ ቅዱስን አትመረምርም? አንድን ቤት ለመግዛት ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ጥቅሙንና ጉዳቱን አውጥተን አውርደን እንደምናመዛዝን ሁሉ ከአምላክ ቃል ባነበብነው ላይም በጥንቃቄ ማሰብ ያስፈልገናል። ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ እውነቱን ማወቅና ማመን አንድን ቤት ከማግኘት የበለጠ ነገር ነው። ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል።—ዮሐንስ 17:3

የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በጣም ጠቃሚ ሆኖ እያለ ብዙ ሰዎች በውስጡ ያለውን ምሥራች ለማየት ዓይናቸው የታወረው ለምንድን ነው? ከምክንያቶቹ አንዱ “ዓለምም በሞላው በክፉው” ስለተያዘ ነው። ይህም ብዙዎቹን ያስገርም ይሆናል። (1 ዮሐንስ 5:19) በዚህም ምክንያት ሰይጣን ዲያብሎስ “የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፣ . . . የማያምኑትን አሳብ አሳወረ።” (2 ቆሮንቶስ 4:4) የምናየው በዓይናችን ቢሆንም ወደ ዓይናችን የገባው ብርሃን ምን ትርጉም እንዳለው ፍቺ የሚሰጠው አንጎላችን ነው። ይህም በመሆኑ ዕውርነት “ለማስተዋል ወይም ለማመዛዘን አለመቻል ወይም አለመፈለግ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ይህም “ማየት ከማይፈልግ ሰው የበለጠ የታወረ የለም” የሚለውን የተለመደ የእንግሊዝኛ አባባል ያስታውሰናል።

ዓይነ ስውር የሆነ ሰው ከፊት ለፊቱ ምን እንዳለ ለማየት አይችልም፤ ስለዚህም ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። ዛሬ የብዙዎችን አካላዊ መታወር ሊለውጠው የሚችል ነገር የለም። ሆኖም ማንም ሰው በመንፈሳዊ ዕውር ሆኖ እንዲቀር የሚያስገድደው ምንም ነገር የለም።

መንፈሳዊ መታወርን ማሸነፍ

በቂ ንጽሕና አለመኖሩ የማየት ችሎታን እንደሚያዳክም ሁሉ በሥነ ምግባር ባዘቀጠ አካባቢ መኖርም በሥነ ምግባር ወደ መታወር ያደርሳል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ሠራሽ ወጎችና ልማዶች እንዳንጠመድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ኢየሱስ “ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ” በማለት በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች መንጎቻቸውን በተሳሳተ መንገድ እየመሯቸው መሆኑን በግልጽ ተናግሮ ነበር።—ማቴዎስ 15:14

በመንፈሳዊና በሥነ ምግባር ዕውር በሆኑ መሪዎች ከመታለል ይልቅ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማየት የቻሉት ምንኛ ደስተኞች ናቸው! ኢየሱስ “የማያዩ እንዲያዩ . . . ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 9:39) ታዲያ በመንፈሳዊ የታወሩት ማየት የሚችሉት እንዴት ነው? እስቲ አካላዊ መታወርን መመርመራችንን እንቀጥል።

በአሁኑ ጊዜ ማየት የተሳናቸውን ለመርዳት የተደረጉ ብዙ ዝግጅቶች አሉ። አሁን ያሉት ዝግጅቶች ያልነበሩበት ጊዜ ነበር። በ1784 ቫለንቲን ኤዌይ የተባለ ሰው ለዓይነ ስውራን የሚሆን ልዩ ትምህርት ቤት እስካቋቋመበት ጊዜ ድረስ ዓይነ ስውራንን ለመርዳት ሆን ተብሎ የተደረገ ጥረት አልነበረም። ከዚያ በኋላ ሊዊ ብሬል የተባለ ሰው በስሙ የሚጠራ የማስተማሪያ ዘዴ ፈለሰፈ። ይህን ዘዴ የፈለሰፈው ማየት የተሳናቸው ሰዎች ማንበብ እንዲችሉ ለመርዳት ነው።

በመንፈሳዊ የታወሩ ሰዎችንስ ለመርዳት የተደረገ ነገር ይኖራልን? ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጣም ሩቅ ወደሆኑ ቦታዎች ምሥራቹን ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። (ማቴዎስ 24:14) የይሖዋ ምሥክሮች ምሳሌያዊም ሆነ አካላዊ ዕውርነት ላለባቸው ሰዎች ተስፋ አዘል መልእክት ለማድረስ ደስተኞች ናቸው።

በብራዚል የምትኖር አንዲት ባለትዳር ሴት የሚከተለውን ጽፋለች፦ “አካላዊ መታወር ያለብኝ ብሆንም በመንፈሳዊ ማየት የምችል መሆኔን መናገር እፈልጋለሁ። ምን ዓይነት አስገራሚ አምላክ አለን! ‘ይሖዋ እጁን ከፍቶ ሕይወት ላላቸው ሁሉ መልካምን እንደሚያጠግብ’ በማወቃችን ደስተኞች ነን።” (መዝሙር 145:16) ዦርዥ የተባለ አንድ በአካል የታወረ ሰው እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሕይወቴ በሁለት ሊከፈል ይችላል። ይህም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከመገናኘቴ በፊት የነበረኝ ሕይወትና አሁን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከተገናኘሁ በኋላ ያለኝ ሕይወት ነው። በይሖዋ ምሥክሮች አማካኝነት ዓለምን ጥርትና ቦግ ባለ ብርሃን መመልከት ጀምሬያለሁ። በጉባኤ ውስጥ ከሁሉም ወንድሞችና እኅቶች ጋር ግሩም የሆነ ግንኙነት አለኝ፤ በዚህም እደሰታለሁ።” መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ በምድር ላይ ቃል በቃልም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ የታወረ ሰው እንደማይኖር ያረጋግጥልናል፤ ይህም የሚያስደስት ነው። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? በምድር ዙርያ “[ይሖዋ አዓት] የዕውሮችን ዓይን ያበራል” የሚለው ተስፋ እውን የሚሆነው እንዴት ነው?—መዝሙር 146:8

ዘላቂ ፈውስ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው

ምንም እንኳ የሕክምና እውቀት እየጨመረ ቢሆንም ብዙ ዓይነት በሽታዎች ዕውርነትን፣ ሥቃይንና ሞትን ማስከተላቸውን ቀጥለዋል። ታዲያ የተመጣጣኝ ምግብ እጦትን፣ የንጽሕና ጉድለትን እንዲሁም የማየት ችሎታንም ሆነ ደስታን የሚነሱ ነገሮችን ለማስወገድ የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው? ኢየሱስ ዕውሮችንም ሆነ ሌላ ሕመም የነበረባቸውን ሰዎች ሲፈውስ ወደፊት ምን እንደሚያደርግ በትንሹ ማሳየቱ ነበር። ኢየሱስ ያከናወነው የማስተማርና የመፈወስ ተግባር በአምላክ ንጉሣዊ አገዛዝ ሥር በምትተዳደረው ምድር ላይ ለሚፈስሰው በረከት ጥላ ነበር።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈውስ የሚደረግበት ጊዜው ቅርብ ነው።a ይህን መለኮታዊ የፈውስ ፕሮግራም ሐዋርያው ዮሐንስ አስደሳች በሆነ ሥዕላዊ መግለጫ እንዲህ ሲል ገልጾታል። “በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ። በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፣ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ።”—ራእይ 22:1, 2

“የሕይወት ውኃ” እና “የሕይወት ዛፍ” የሚሉት አባባሎች ይህ ክፉ ሥርዓት ከተደመደመ በኋላ በአምላክ አገዛዝ ሥር በሚዘረጉት የፈውስ ፕሮግራሞች የሰው ዘር ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና የሚደርስ መሆኑን ያሳያሉ። የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያስገኛቸው ጥቅሞችና (ሙሉ በሙሉ የኃጢአት ይቅርታን ማስገኘት የሚችል መሆኑን ጨምሮ) ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና ስለ አባቱ የምንቀስመው እውቀት ፍጹም ጤንነትና የዘላለም ሕይወት ያስገኙልናል።—ዮሐንስ 3:16

በአምላክ አዲስ ዓለም የሚኖረው ደስታ

ወንጀል፣ የአካባቢ ብክለትም ይሁን ድህነት ከምድር ላይ ተወግደው መኖር ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ ይታይህ። ተመልሳ በምትመጣዋ ገነት ቤተሰቦችህ ሰላም አግኝተው ሲኖሩ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። (ኢሳይያስ 32:17, 18) ፍጹም በሆነ አእምሮና ፍጹም በሆኑ የስሜት ሕዋሳት አማካኝነት ልዩ ልዩ ቀለማትን ማየት እንዴት ያስደስታል!

ስለ ቀለማት ጥልቅ ምርምር ያደረጉት ፋበር ቢረን የተባሉ ሰው እንዲህ ይላሉ፦ “ሰው ሳያቋርጥ የብርሃን፣ የቀለም ወይም የቅርጽ ለውጥ በሚያደረግ አካባቢ እንዲኖር ሆኖ የተፈጠረ ነው። በተፈጥሮ ውስጥ ምንም ለውጥ የማያደርግ አካባቢ የለም። ይህ ዓለም ደስ እንዲል ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የኅብረ ቀለማት መኖር ነው። ኅብረ ቀለማት የጠቅላላው ተፈጥሮ ክፍል ናቸው እንጂ በተወሰኑ ቦታዎች የሚገኙ አይደሉም።”

የማየት ችሎታ እንዴት ያለ ውድ ስጦታ ነው! ቃል በቃልም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ታውረው የነበሩ ዓይኖች ሲገለጡ ማየት እንዴት ደስ ይል ይሆን!

አዎን፣ ተመልሳ በምትመጣው ገነት ውስጥ በዓይነ ስውርነትም ይሁን በሌሎች የአካል ጉዳቶች የተነሣ ደስታን የሚያሳጣ ነገር አይኖርም! ከዚያ በኋላ በሌሎች የሚሳሳት ሰው አይኖርም። በዚያን ጊዜ እውነተኛ ፍቅር ስለሚኖር ሁሉም ሰዎች መንፈሳዊ ብርሃን የበራላቸው ይሆናሉ። በቅርቡ እነዚህና ሌሎች በረከቶች ይመጡልናል። ከዚያ በፊት ግን ዛሬውኑ “በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል” ሲል የሰጠውን ትንቢታዊ ተስፋ በሚፈጸምው በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መጣር ይኖርብናል።—ኢሳይያስ 35:5

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በታተመው በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በምዕራፍ 18 ላይ የቀረበውን ማብራሪያ ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል!

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ