ዝግመተ ለውጥ በችሎት ፊት
የዝግመተ ለውጥ አቀንቃኞች ለሕያው አካሎች መገኛ ናቸው የተባለላቸው ንጥረ ነገሮች እንደገና አንድ በአንድ ይጠኑ ብለው እየተንጫጩ ነው
አንድን ወንጀል በሚመለከት ችሎት ላይ ብያኔ የምትሰጥ ዳኛ ነህ እንበል። ተከሳሹ ወንጀሉን በጭራሽ አልፈጸምኩም ይላል፤ እማኞቹም ለእሱ የምሥክርነት ቃላቸውን ሊሰጡ ቀርበዋል። የምሥክርነት ቃላቸውን ስትሰማ ግን አንደኛው የሚናገረው ሐሳብ ሌላው ከሚናገረው ጋር የሚጋጭ ሆኖ ታገኘዋለህ። የመከላከያ ምሥክሮች ናቸው ተብለው የቀረቡት እነዚህ ሰዎች እንደገና የምሥክርነት ቃላቸውን ወደሚሰጡበት ቦታ ሲጠሩ ደግሞ ሌላ ታሪክ ማውራት ይጀምራሉ። እንደ አንድ ዳኛ ሆነህ ነገሩን ስትመለከተው የምሥክርነት ቃላቸውን ክብደት ትሰጠው ነበርን? ተከሳሹን በነፃ ለማሰናበት ትገፋፋለህን? ተከሳሹን በመደገፍ የቀረቡት ሐሳቦች እርስ በእርሳቸው የማይጣጣሙ መሆናቸው የተከሳሹን ተአማኒነት አጠያያቂ ሁኔታ ውስጥ ስለሚከተው እንዲህ ታደርጋለህ ተብሎ አይጠበቅም።
የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ያለበት ሁኔታ ልክ እንደዚህ ነው። ለዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ በመሟገት ስለ ሕይወት መገኛ የተለያዩ ትንታኔዎችን ለመስጠት ብዙ ምሥክሮች ቀርበዋል። የምሥክርነት ቃላቸው በችሎት ፊት ሲሰማ ግን ሊታመንበት የሚችል ሆኖ ይገኛልን? ንድፈ ሐሳቡን በመደገፍ የሚሟገቱ ሰዎች አንድ ዓይነት ቃል ይናገራሉን?
እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ የምሥክርነት ቃሎች
ሕይወት እንዴት ተገኘ? ምናልባት የዚህን ጥያቄ ያህል ብዙ ግምታዊ ሐሳቦችን የወለደና በጣም ያወዛገበ ጥያቄ ላይኖር ይችላል። ሆኖም ትንቅንቁ በዝግመተ ለውጥና በሥነ ፍጥረት መካከል ብቻ አይደለም። በአብዛኛው ንትርኩ የሚካሄደው በራሳቸው በዝግመተ ለውጥ አማኞቹ መካከል ነው። እያንዳንዱ የዝግመተ ለውጥ ዝርዝር ጉዳይ ማለትም ሂደቱ እንዴት ሊከሰት ቻለ? የተከሰተው የት ነው? እንዲከሰት ያደረገው ማነው ወይም ምንድን ነው? ሂደቱ ምን ያህል ጊዜ ፈጅቷል? የሚሉት ዝርዝር ጉዳዮች በእጅጉ የሚያወዛግቡ ሆነዋል።
ለብዙ ዓመታት የዝግመተ ለውጥ አማኞች ሕይወት ወደ መኖር የመጣው ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑትን ንጥረ ነገሮች ከያዘ “እንደ ሾርባ ያለ” ውቅያኖስ ውስጥ ነው ሲሉ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ አንዳንዶች ሕይወትን ያስገኘው በውቅያኖስ ውስጥ ያለ በኬሚካል ውህደት የሚፈጠር አረፋ መሰል ነገር ነው ብለው ያምናሉ። ሌሎቹ ደግሞ ሕይወት የተገኘው በባሕር ወለል ላይ ከሚገኙ ፍል ውሃ የሚንዶለዶልባቸው ቦታዎች ነው የሚል ሐሳብ ይሰጣሉ። ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከጠፈር ወደ ምድር በሚወድቁ የአለት ስባሪዎች ላይ ሆነው ምድር ላይ አርፈዋል የሚል ሐሳብ የሚሰነዝሩም አሉ። ወይም ደግሞ ምናልባት አስተሮይድ የሚባሉት በማርስና በጁፒተር መካከል ካሉት በጣም ትንንሽ ፕላኔቶች ወደ ምድር ወድቀው ከባቢውን አየር በመለወጥ ሕይወት እንዲያቆጠቁጥ አድርገው ሊሆን ይችላል የሚሉም አሉ። “ከእነዚህ መካከል አንዱ ተለቅ ያለውና የብረት አካል ያለው አስተሮይድ ወድቆ ከምድር ጋር ቢላተም” ይላሉ አንድ ተመራማሪ “ትኩረትን የሚስብ አስደናቂ ነገር መከሰቱ አይቀርም።”
ሕይወት ወደ መኖር የመጣበት ሁኔታም እንደገና እየተጤነ ነው። “ሕይወት የተከሰተው በአንድ ወቅት ይታመንበት እንደነበረው ጸጥና ዝግ ባሉና ተስማሚ በሆኑ ሁኔታዎች አይደለም” በማለት ታይም መጽሔት ይገልጻል፤ “ከዚህ ይልቅ ሕይወት የተከሰተው ሰማያት በቃጠሎ ድብልቅልቃቸው ወጥቶ፣ ፕላኔቷ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች ገጽታዎቿ ተለዋውጠውና በጅራታም ኮከቦችና በአስተሮይዶች ድብደባ ደርሶባት ነው።” በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ሳይንቲስቶች በዚህ ትርምስምሱ በወጣ ሁኔታ መካከል ሕይወት እየተሻሻለ እንዲመጣ ሂደቱ በሙሉ ቀደም ሲል ይታመንበት ከነበረው ጊዜ ባነሰ ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ አለበት ይላሉ።
አምላክ ለዛውም “ካለ” በዚህ ሂደት ውስጥ የሚጫወተው ሚና ምንድን ነው? በሚለው ሐሳብም ላይ ሳይንቲስቶች የተለያየ አመለካከት አላቸው። አንዳንዶች ሕይወት እየተሻሻለ የመጣው ፈጣሪ ጣልቃ ሳይገባበት ነው ይላሉ፤ ሌሎቹ ግን አምላክ ሂደቱን አስጀመረውና ሕይወት እየተሻሻለ እንዲሄድ የማድረጉን ጉዳይ ለዝግመተ ለውጥ ተወው የሚል ሐሳብ ይሰጣሉ።
ሕይወት ወደ መኖር ከመጣ በኋላ ዝግመተ ለውጥ የተከሰተው እንዴት ነው? በዚህም ጉዳይ ላይ እንኳ የሚቀርቡት ማብራሪያዎች እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ ናቸው። ዘ ኦሪጅን ኦቭ ስፒሽስ የተባለው መጽሐፍ ከታተመ ከአንድ መቶ ዘመን በኋላ ማለትም በ1958 የዝግመተ ለውጥ አማኙ ሰር ጁሊያን ሃክስሌይ እንዲህ አሉ፦ “ተፈጥሮ የተሻሉትን ሕያዋን ነገሮች እየመረጠ ደካማዎቹን ግን አያከሰመ አሁን ወዳለው ደረጃ ሊደርስ ችሏል የሚለው የዳርዊን ታላቅ ግኝት (ናቹራል ሰሌክሽን) ለአንጋፋዎቹ የዝግመተ ለውጥ ሂደቶች ብቸኛው መገኛ መሆኑ አሁን በመጨረሻ በሚገባ ተረጋግጧል።” ሃያ አራት ዓመታት ካለፉ በኋላ ግን የዝግመተ ለውጥ አማኝ የሆኑት ሚካኤል ሩዝ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እያደገ የመጣ ብዙ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች . . . በዳርዊን መሠረታዊ ሐሳቦች ላይ የተመሠረተ ማንኛውም የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ በተለይም ተፈጥሮ የተሻሉ ሕያዋን ነገሮችን እየመረጠ ደካማዎቹ እንዲከስሙ አድርጓል የሚለውን መሠረታዊ ሐሳብ ለዝግመተ ለውጥ ሂደት ቁልፍ እንደሆነ አድርጎ የሚመለከት ማንኛውም ንድፈ ሐሳብ አሳሳችና ያልተሟላ ንድፈ ሐሳብ ነው በማለት ይከራከራሉ።”
ታይም መጽሔት የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ በሁለት እግሩ የሚያቆሙ “ብዙ ጠንካራ እውነታዎች” አሉ ቢልም ዝግመተ ለውጥ “ብዙ ቀዳዳዎች ያሉትና ቀዳዳዎቹን እንዴት መድፈን እንደሚቻል የሚገልጹ እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ ንድፈ ሐሳቦች እጥረት የሌለበት” የተወሳሰበ ተረት መሆኑን አልካደም። ችሎቱ ለጉዳዩ እልባት ሰጥቶ ዘግቶታል ከማለት ይልቅ በከፍተኛ ደረጃ የዝግመተ ለውጥ አቀንቃኞች ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹ በአሁኑ ጊዜ የሕይወት መገኛ ናቸው የሚባሉት ነገሮች እንደገና አንድ በአንድ ምርመራ እንዲካሄድባቸው እየተንጫጩ ነው።
ስለዚህ ለዝግመተ ለውጥ በተለይም በዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ላይ በመንተራስ ሕይወት ወደ መኖር ስለመጣበት ሁኔታ ለሚሰጠው ትንተና ወግኖ የሚደረገው ሙግት አንድ ወጥ በሆነ የምሥክርነት ቃል ላይ የተመሠረተ አይደለም። ቲ ኤች ጃናቢ የተባሉት ሳይንቲስት የዝግመተ ለውጥ ተሟጋቾች “ለበርካታ ዓመታት ብዙ የተሳሳቱ ንድፈ ሐሳቦችን አቅርበዋል፤ በኋላም እርግፍ አድርገው ትተዋቸዋል። ሳይንቲስቶችም እስከ አሁን ድረስ በአንድም ንድፈ ሐሳብ ላይ መስማማት ተስኗቸዋል” በማለት የታዘቡትን ተናግረዋል።
የሚገርመው ነገር ቻርልስ ዳርዊንም እንዲህ ዓይነቱ የሐሳብ አለመጣጣም እንደሚኖር አስቀድሞ በማየት አስተያየት ሰጥቶበት ነበር። ዘ ኦሪጅን ኦቭ ስፒሽስ በተባለው መጽሐፍ መግቢያ ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በዚህ ጥራዝ ውስጥ የተገለጸ የእውነታዎች ድጋፍ ያልቀረበበት አንድ ነጥብ ብዙውን ጊዜ እኔ ከደረስኩባቸው መደምደሚያዎች ፍጹም ተቃራኒ ወደሆኑ መደምደሚያዎች እንደሚመራ አውቃለሁ።”
በእርግጥም እንዲህ ያሉ እርስ በእርሳቸው የማይጣጣሙ የምሥክርነት ቃሎች በዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ተአማኒነት ላይ ጥያቄዎችን ያስነሣሉ።
ዝግመተ ለውጥ ምሁራዊ ምርጫ ነውን?
የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ይላል ማይልስቶንስ ኦቭ ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ፣ ገና ከጅምሩ “የብዙ ሰዎችን ስሜት ማርኳል፤ ምክንያቱም ሕያዋን ነገሮች ወደ መኖር የመጡት እንደየወገናቸውና ቅጽበታዊ በሆነ መንገድ ነው ከሚለው የፍጥረት ዘገባ ይበልጥ ሳይንሳዊ ስለሚመስል ነው።”
ከዚህም በላይ አንዳንድ የዝግመተ ለውጥ አቀንቃኞች የሚሰነዝሩአቸው ቀኖናዊ አነጋገሮች የሚያስፈራሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ኤች ኤስ ሼልተን የተባሉት ሳይንቲስት ሕያዋን ነገሮች ወደ መኖር የመጡት እንደየወገናቸውና ቅጽበታዊ በሆነ መንገድ ተፈጥረው ነው የሚለውን ሐሳብ “ግምት ሰጥቶ መወያየት በጣም መጃጃል ነው” በማለት በትምክህተኝነት ተናግረዋል። ሪቻርድ ዳውኪንስ የተባሉ የሥነ ሕይወት ተመራማሪ “በዝግመተ ለውጥ አላምንም የሚል ሰው ካጋጠማችሁ ያ ሰው ደንቆሮ፣ ደደብ ወይም ቀውስ ነው” ሲሉ በንቀት ተናግረዋል። ፕሮፌሰር ሬኒ ዱቦም እንደዚሁ “ምሁራን በአሁኑ ጊዜ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለ ማንኛውም ነገር ከሰማያዊ አካላት አንሥቶ እስከ ሰው ልጆች ድረስ ሁሉም በዝግመተ ለውጥ ሂደቶች አማካኝነት እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱና ወደፊትም በዚሁ መልኩ እየተሻሻሉ የሚሄዱ መሆናቸውን እንደ ሐቅ አድርገው ይቀበሉታል” ብለዋል።
ከእነዚህ አባባሎች አንጻር ማንኛውም ተመራማሪ አእምሮ ያለው ሰው የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ ምንም ሳያቅማማ መቀበል ያለበት ሊመስል ይችላል። እንዲያውም እንዲህ ማድረግ ማለት “ደደብ” ከመሆን ይልቅ “ምሁር” መሆን ማለት ነው። ሆኖም ከፍተኛ ትምህርት የተማሩ የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ ግን የማይደግፉ ብዙ ወንዶችና ሴቶች አሉ። “በውስጣቸው ጥርጣሬ ያላቸው ብዙ ሳይንቲስቶች አጋጥመውኛል” ሲሉ ፍራንሲስ ሃይቺንግ ዘ ኔክ ኦቭ ዘ ጂራፍ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ጽፈዋል። “አልፎ ተርፎም የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ፈጽሞ ሳይንሳዊ ንድፈ ሐሳብ እንዳልሆነ ተረጋግጧል ያሉ ሳይንቲስቶችም አጋጥመውኛል።”
ቻንድራ ዊክራማሲንጌ የተባሉ አንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው የብሪታንያ ሳይንቲስትም ተመሳሳይ የሆነ አቋም ወስደዋል። “የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ መሠረታዊ ንድፈ ሐሳቦች አንዳቸውም ቢሆኑ ምንም ማስረጃ የላቸውም” ብለዋል። “በ1860 ዓለምን በቁጥጥሩ ሥር ያደረገ ማኅበራዊ ኃይል ነበር። በሳይንስም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ከፍተኛ ሽንፈት አስከትሎበታል ብዬ እገምታለሁ።”
ቲ ኤች ጃናቢ የዝግመተ ለውጥ አማኞች የሚያቀርቧቸውን የመከራከሪያ ሐሳቦች በደንብ መርምረዋል። “ሁኔታው ቀደም ሲል እኛን ለማሳመን ነገሩ ከቀረበበት ሁኔታ ለየት ያለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ” ብለዋል። “ስለ ሕይወት አመጣጥ የሚናገረውን ይህን የተወሳሰበ ንድፈ ሐሳብ ለመደገፍ የቀረቡት ማስረጃዎች በጣም ጥቂትና ያልተሰባሰቡ ናቸው።”
ስለዚህ የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ የማይቀበሉ ሰዎች እንደ “ደንቆሮ፣ ደደብ ወይም ቀውስ” ተቆጥረው ገሸሽ ሊደረጉ አይገባም። የዝግመተ ለውጥን እውነተኝነት አጠያያቂ የሚያደርጉ ሐሳቦችን በተመለከተ ሌላው ቀርቶ በዝግመተ ለውጥ ላይ የጸና እምነት ያላቸው ጆርጅ ጌይሎርድ ሲምፕሰን እንኳ እንደሚከተለው በማለት ሳይሸሽጉ ተናግረዋል፦ “እነዚህን አመለካከቶች እንዲሁ ስቆ ማለፍ ወይም ማናናቅ ስህተት ነው። እነዚህን አመለካከቶች የሚደግፉ ሰዎች ጥልቅ ማስተዋልና ሁኔታዎችን በደንብ የማገናዘብ ችሎታ የነበራቸውና (ያላቸው) ምሁራን ናቸው።”
ነገሩ የእምነት ጉዳይ ነው
አንዳንዶች ዝግመተ ለውጥ የተመሠረተው በእውነታ ላይ ነው፤ የፍጥረት ዘገባ ግን የተመሠረተው በእምነት ላይ ብቻ ነው ብለው ያስባሉ። እውነት ነው፣ አምላክን ያየው ሰው የለም። (ዮሐንስ 1:18ን ከ2 ቆሮንቶስ 5:7 ጋር አወዳድር።) ሆኖም የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ በዚህ ረገድ ምንም ብልጫ የለውም፤ ምክንያቱም በዓይን ባልተረጋገጡና የሰው ልጆች መልሰው ሊፈጽሟቸው ባልቻሉአቸው ክስተቶች ላይ የተመሠረተ ንድፈ ሐሳብ ነው።
ለምሳሌ ያህል ሳይንቲስቶች አዳዲስ ሕያዋን ነገሮች ያስገኛል የሚባለው “ሚውቴሽን (በነባሩ አካል ላይ የተከሰተ ባሕሪያዊ ለውጥ)” ሲከሰት ሌላው ቀርቶ “ቤኔፊሻል ሚውቴሽን” (ጠቃሚ የሚባለው ለውጥ) እንኳ ሲከናወን አልተመለከቱም። ያም ሆኖ ግን ያላንዳች ጥርጥር የተለያዩ ዝርያዎች ወደ መኖር የመጡት በዚህ መንገድ ነው ይላሉ። ሕይወት የመጣው ሕይወት ከሌለው ነገር ቅጽበታዊ በሆነ መንገድ ነው ቢሉም ይህን በዓይናቸው አላዩም፤ ሆኖም ሕይወት ወደ መኖር የመጣው በዚህ መንገድ ነው በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ።
እንዲህ ዓይነቱ ማስረጃ የሌለው በመሆኑ ቲ ኤች ጃናቢ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብን “ነገሩ ‘የእምነት’ ጉዳይ ነው” ለማለት ተገደዋል። የፊዚክስ ምሁር የሆኑት ፍሬድ ሆይል ደግሞ “የዳርዊን ወንጌል” ብለው ጠርተውታል። ዶክተር ኢቫን ሹት ደግሞ ከዚህም ጠጠር ያለ አነጋገር ተጠቅመዋል፦ “የፍጥረት አማኙ ማብራሪያ የማይሰጥባቸው ድፍን ያሉ ጉዳዮች እንዳሉ ሁሉ፣ በሙሉ ልቡ ዝግመተ ለውጥን የሚደግፈው ሰውም መልስ መስጠት የማይችልባቸው የበለጡ ነገሮች አሉ ብዬ እገምታለሁ” ብለዋል።
ሌሎች ጠበብቶችም በዚህ ይስማማሉ። “የሰውን ልጅ ተፈጥሮ በጥልቀት ስመረምረው ይህ አካል ወደ መኖር የመጣው በአንድ ቦታ ረግቶ በሚገኝ የፈላ ውኃ ውስጥ ከሟሙ ኬሚካሎች ነው የሚለው ነገር የሰው ልጅ ወደ መኖር የመጣበትን መንገድ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ያህል ተአምር ይሆንብኛል” በማለት የከዋክብት ተመራማሪ የሆኑት ሮበርት ጃስትሮው ተናግረዋል።
ታዲያ ብዙዎች ሕይወት ወደ መኖር የመጣው በፍጥረት ነው የሚለውን ሐሳብ እስከ አሁንም የማይቀበሉት ለምንድን ነው?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንዶች የሚሰነዝሩአቸው ቀኖናዊ አነጋገሮች ሰውን ሊያሳምኑ ይችላሉ