‘ከሕፃናት አፍ’
ሳሙኤል ትንሽ ልጅ ሳለ እንደ ክፉዎቹ የሊቀ ካህኑ ኤሊ ልጆች ከመሆን ይልቅ ለጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ የቆመ ነበረ። (1 ሳሙኤል 2:22፤ 3:1) በኤልሳዕ ዘመን በሶርያ ምርኮኛ የነበረች አንዲት ትንሽ እስራኤላዊት ለእመቤቷ ድፍረት የተሞላበት ምሥክርነት ሰጠች። (2 ነገሥት 5:2–4) ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ በነበረበት ጊዜ ከእስራኤል አስተማሪዎች ጋር በልበ ሙሉነት ይናገር፣ ጥያቄዎችን ይጠይቅና ተመልካቾቹን ጉድ ያሰኘ መልስ ይሰጥ ነበር። (ሉቃስ 2:46–48) በታሪክ ዘመናት ሁሉ ወጣት አምላኪዎቹ ይሖዋን በታማኝነት አገልግለዋል።
አሁን ያሉ ወጣቶችስ ያን መሰል መንፈስ አሳይተዋልን? እንዴታ! ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የተገኙ ሪፖርቶች እጅግ ብዙ ወጣቶች ለይሖዋ አገልግሎት ‘በፈቃዳቸው ራሳቸውን እንዳቀረቡ’ ያሳያል። (መዝሙር 110:3 አዓት) የድካማቸው መልካም ውጤት ወጣትም ሆኑ በዕድሜ የገፉ፣ ሁሉም ክርስቲያኖች ‘መልካም ሥራን ከመሥራት እንዳይታክቱ’ ያበረታቸዋል።—ገላትያ 6:9
ስድስት ዓመት ሲሞላት አስፋፊ የሆነችውና በክፍሏ ለሚገኙት ሁሉ መመሥከርን ግቧ ያደረገችው አዩሚ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናት። በመማሪያ ክፍሉ መጻሕፍት ቤት ውስጥ በርከት ያሉ መጻሕፍትን እንድታስቀምጥ ሲፈቀድላት የትምህርት ቤት ባልንጀሮቿ ሊጠይቋት ለሚችሉት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ራሷን አዘጋጀች። አስተማሪዋንም ጨምሮ ሁሉም የክፍል ጓደኞቿ ከጽሑፎቹ ጋር በደንብ ተዋወቁ። አዩሚ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባሳለፈቻቸው ስድስት ዓመታት 13 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርታለች። እሷ አራተኛ ክፍል እያለች ስትጠመቅ፤ እሷ ያስጠናቻት ጓደኛዋ ደግሞ ስድስተኛ ክፍል እያለች ተጠመቀች። ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዋ እናትና ሁለት ታላቅ እህቶቿ አጥንተው ተጠመቁ።
ጥሩ ጠባይ ይመሠክራል
ሐዋርያው ጴጥሮስ “በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን” ብሏል። ወጣት ክርስቲያኖችም ይህንን ትእዛዝ በቁም ነገር ያዩታል። (1 ጴጥሮስ 2:12) በውጤቱም ጥሩ ጠባያቸው ብዙ ጊዜ መልካም ምሥክርነት ሰጥቷል። በአፍሪካዊቷ አገር ካሜሩን አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት የጉባኤ ስብሰባ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ሲገኝ ከአንዲት ልጅ ጎን ተቀመጠ። ተናጋሪው ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥተው እንዲመለከቱ ሲጋብዝ ትንሿ ልጅ በራሷ መጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅማ ጥቅሶቹን ቶሎ ታወጣና ንባቡን ልብ ብላ ትከታተል እንደነበረ ሰውየው አስተዋለ። አድራጎቷ በጣም ስለማረከው በስብሰባው መደምደሚያ ላይ ወደ ተናጋሪው ሄደና “ይህች ትንሽ ልጅ መጽሐፍ ቅዱስን ከእናንተ ጋር ማጥናት እንድፈልግ አድርጋኛለች” አለው።
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ወላጆቻቸው የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ 25 ልጆች ያሉበት ትምህርት ቤት አለ። ጥሩ ጠባያቸው ለይሖዋ ምሥክሮች መልካም ዝና አትርፎላቸዋል። አንዲት አስተማሪ፣ በተለይ የራሷ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶችን መርዳት ተስኖት ምሥክሮቹ ግን ልጆቻቸውን በተሻለ ሁኔታ ለማሰልጠን እንዴት እንደተሳካላቸው ግራ እንደሚገባት ምሥክር ለሆነች አንዲት ወላጅ ነገረቻት። ትምህርት ቤቱን ለማገዝ አዲስ አስተማሪ መጣች። እሷም ወዲያውኑ የምሥክሮቹን ልጆች ጥሩ ጠባይ አስተዋለች። ከይሖዋ ምሥክሮች አንዷ ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለባት ከምሥክሮቹ ልጆች አንዱን ጠየቀችው። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንዳለባት ነገራትና ወላጆቹ ይህችን ፍላጎት ያሳየች ሴት ተከታትለው እንዲረዷት አመቻቸላቸው።
በኮስታ ሪካ ሁለት የክፍል ጓደኞቹ ስለ ሥላሴ፣ ስለ ነፍስና ስለ ሲኦል እሳት ያለውን ጥያቄ ለመመለስ በመጽሐፍ ቅዱስ በተጠቀሙ ጊዜ ሪጎቤርቶ የእውነትን ድምፅ ለየ። በቅዱሳን ጽሑፎች አጠቃቀማቸው የተካኑ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ከተመለከተው ልዩ በሆነው ወርቅ ጠባያቸውም ጭምር ስለተነካ ለሚናገሩት ሁሉ ክብደት ይሰጥ ነበር። ሪጎቤርቶ የቤተሰብ ተቃውሞ ቢኖርበትም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ጥሩ እድገት እያደረገ ነው።
በስፔይን ከሁለት አንዳቸው የዘጠኝ ዓመት ልጅ የሆኑ ሁለት ምሥክሮች ኦኖፍሬ የሚባል ሰው አነጋገሩ። ትልቁ አስፋፊ ባብዛኛው ሲናገር ትንሹ አስፋፊ ጥቅሶቹን እያወጣ ያነብና በቃል የሚያስታውሳቸውን አንዳንድ ጥቅሶች ይጠቅስ ነበር። ኦኖፍሬ ተገረመ። ያ ትንሽ ልጅ ጥቅሶችን ጥሩ አድርጎ መያዝ ከተማረበት ቦታ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወሰነ። ከዚያም የሚቀጥለው እሑድ ጠዋት ወደ መንግሥት አዳራሹ ሄደ። ምሥክሮቹ ለስብሰባቸው እስከመጡበት እኩለ ቀን ድረስ እደጅ ቆይቶ ነበር። ከዚያን ወዲህ ጥሩ እድገት አደረገና በቅርቡ ራሱን መወሰኑን በውኃ ጥምቀት አሳየ።
ጥሩ ውጤት ያገኙ ወጣት ምሥክሮች
አዎን፣ ይሖዋ ልበ ቅን የሆኑትን ለመንካት በአዋቂዎችም በወጣቶችም ይጠቀማል። ይህ ከሀንጋሪ ከተገኘ ተሞክሮ በተጨማሪ ታይቷል። በዚያ አንዲት የሆስፒታል ነርስ የአሥር ዓመቷን ታማሚ ሊጠይቁ በመጡ ቁጥር እንደ ምግብ ሁሉ የሚነበቡ ነገሮችም ይዘውላት እንደሚመጡ ልብ አለች። ወጣቷ ልጅ ይህን ያህል በቁም ነገር የምታነበው ምን ይሆን እያለች ስትገረም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ደረሰችበት። ነርሷ ካነጋገረቻት በኋላ “በእውነቱ ከመጀመሪያዋ ዕለት ጀምሮ እያስተማረችኝ ነው” አለች። ወጣቷ ልጅ ሆስፒታሉን ስትለቅ በወረዳ ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ለነርሷ ግብዣ ብታቀርብላትም ግብዣውን ገሸሽ አደረገችው። ኋላ ግን በ“ንጹሕ ልሳን” የወረዳ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ተስማማች። ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀምራ ከአንድ ዓመት በኋላ ተጠመቀች፤ ይህ ሁሉ ሆስፒታል ያሳለፈችውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማንበብ የተጠቀመችበት ትንሿ ልጅ ውጤት ነው።
በኤል ሳልቫዶር የምትኖረው አና ሩት በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነበረች። ካሻቸው እንዲያነቡት በማሰብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በጠረጴዛዋ ላይ ትታ የመሄድ ልማድ ነበራት። ጽሑፉ ለትንሽ ጊዜ ከቦታው እንደሚጠፋና ቆይቶ እንደሚመለስ ስትመለከት የትምህርት ቤት ባልንጀራዋ ኤቭሊን እያነበበችው እንደነበር ደረሰችበት። ከጊዜ በኋላ ኤቭሊን ለማጥናት ተስማማች እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች መገኘት ጀመረች። በመጨረሻ ተጠመቀችና አሁን ቋሚ ረዳት አቅኚ በመሆን ታገለግላለች። አና ሩት ደግሞ የዘወትር አቅኚ ነች።
በፓናማ አንዲት እህት አንዲት ሴት ማስጠናት ጀመረች፤ ይሁን እንጂ በባሏ ተቃውሞ የተነሳ ጥናቱ ሊቆም ትንሽ ቀረው። ነገር ግን ከቀን ወደ ቀን ባልዬው እየለሰለሰ መጣ። ከዕለታት አንድ ቀን ምሥክር የሆነ ሥጋዊ ወንድሙ እቤቱ የሌባ ማስጠንቀቂያ ደውል እንዲያስገባለት ጠየቀው። ደውሉን እየገጠመ ሳለ የዘጠኝ ዓመቷ የወንድሙ ልጅ አዝና ወደ ቤት መጣች። ምን እንደሆነች ሲጠይቃት እሷና ታላቅ እህቷ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊመሩ ሲሄዱ ሰውየውን እቤት እንዳጡት ስለዚህም በዚያ ቀን ለይሖዋ ምንም ሊሠሩ እንዳልቻሉ ነገረችው። አጎቷም “ለእኔ ለምን አትሰብኪልኝም? ለይሖዋ አንድ ነገር አደረግሽለት ማለት ነው” አላት። የወንድሙ ልጅ በደስታ መጽሐፍ ቅዱሷን ለማምጣት ሮጠች፤ ሰውየው ማጥናት ጀመረ።
እናቷ ታዳምጥ ነበር። እየተደረገ ያለው ሁሉ ቀልድ ነው ብላ ብታስብም ዘወትር ሰውዬው ወደ ቤቷ እየመጣ የወንድሙን ልጅ መጽሐፍ ቅዱስ እንድታስጠናው ሲጠይቃት ትመለከታለች። እናትየው አማቿ የምሩን እንደሆነና አንዳንድ ከባድ ጥያቄዎች እንዳሉት ስትመለከት እሷ እየመራች ከሴት ልጅዋ ጋር ሆና ልታስጠናው ወሰነች። በሳምንት ሁለቴ ማጥናት ጀመረና ፈጣን እድገት አደረገ። በወንድሙ ልጅ መልካም ዝንባሌ ምክንያት በመጨረሻ ራሱን እስከ መወሰን ደረሰና ከሚስቱ ጋር በአንድ ትልቅ ስብሰባ ተጠመቁ።
የልጆች ድፍረት መልካም ምሥክርነት ይሰጣል
መጽሐፍ ቅዱስ “በርታ፣ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ” ይላል። (መዝሙር 27:14) እነዚህ ቃላት ለሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ይሠራሉ። ባለፈው ዓመት አዋቂዎችም ሆኑ ልጆች ሠርተውባቸዋል። በአውስትራሊያ አንዲት የአምስት ዓመት ልጅ አዲስ ትምህርት ቤት ገባችና እናትየው የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ምን እንደሆነ ልታብራራ ወደ አስተማሪው ሄደች። አስተማሪው “የምታምኑትን ሁሉ አውቄዋለሁ። ልጅሽ እያንዳንዱን ነግራኛለች” አለ። ይህች ታዳጊ ወጣት ስለ እምነቷ ያለ ማንም ርዳታ ለመናገር ወደኋላ አላለችም።
በሩማኒያም የአምስት ዓመቷ አንድሬአ ድፍረት አሳይታለች። እናቷ ምሥክር ለመሆን የኦርቶዶክስ እምነቷን ስትተው ጎረቤቶቿ እሷን ለመስማት አሻፈረኝ አሉ። አንድ ቀን በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ፕሮግራም ላይ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ለጎረቤቶች የመመሥከርን አስፈላጊነት አጥብቆ ሲናገር አንድሬአ ሰማች። በነገሩም ላይ አጥብቃ አሰበችና ወደ ቤት ስትመለስ ለእናቷ “እማዬ፣ ወደ ሥራ ከሄድሽ በኋላ ተነሥቼ ልክ አንቺ እንደምታደርጊው ቦርሳዬን በጽሑፎች እሞላና ከጎረቤቶቼ ጋር ስለ እውነት ለመነጋገር እሄዳለሁ። ይሖዋም እንዲረዳኝ እጸልያለሁ” አለቻት።
በማግስቱ አንድሬአ ቀደም ሲል ተናግራ የነበረውን አደረገች። ራሷን አደፋፈረችና የአንዱን ጎረቤት መጥሪያ ደወለች። ጎረቤትየው በሩን ሲከፍት ይህች ትንሽ ልጅ እንዲህ አለች፦ “እናቴ ምሥክር ከሆነች ጀምሮ እንደማትወዷት አውቃለሁ። ብዙ ጊዜ ከእናንተ ጋር ልትነጋገር ፈልጋ ነበር ቢሆንም እናንተ ልታዳምጧት አልፈለጋችሁም። ይህ ቅር ያሰኛታል፤ ቢሆንም እንደምንወዳችሁ ልታውቁልኝ እፈልጋለሁ።” ከዚያም አንድሬአ መልካም ምሥክርነት መስጠቷን ቀጠለች። በአንድ ቀን ስድስት መጻሕፍት፣ ስድስት መጽሔቶች፣ አራት ቡክሌቶችና አራት ትራክቶች አሰራጨች። ከዚያን ጀምሮ በመስክ አገልግሎት አዘውትራ ትካፈላለች።
በሩዋንዳ ብጥብጥ ስላለ ወንድሞቻችን ታላቅ ድፍረት ማሳየት አስፈልጓቸዋል። በአንድ ወቅት አንድን የምሥክሮች ቤተሰብ ወታደሮች ሊገድሏቸው በመዘጋጀት አንድ ክፍል ውስጥ አስቀመጧቸው። ቤተሰቡ መጀመሪያ እንዲጸልዩ ፈቃድ ጠየቁ። እሺ አሏቸውና ከሴት ልጃቸው ዲቦራ በስተቀር ሁሉም ድምፅ ሳያሰሙ ጸለዩ። ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ዲቦራ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ይሖዋ፣ በዚህ ሳምንት አባባና እኔ አምስት መጽሔት አበርክተናል። ታዲያ እነዚህን ሰዎች እንዴት ተመልሰን እውነትን ልናስተምራቸውና ሕይወት እንዲያገኙ ልንረዳቸው እንችላለን? ደግሞስ እንዴት አስፋፊ መሆን እችላለሁ? አንተን ለማገልገል መጠመቅ እፈልጋለሁ” ብላ ጸለየች። ይህን ከሰማ በኋላ አንዱ ወታደር “በዚች ትንሽ ልጅ ምክንያት ልንገድላችሁ አንፈልግም” አለ። ዲቦራም “አመሰግናለሁ” ስትል መለሰች። ቤተሰቡ ተረፈ።
ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ማክተሚያ አቅራቢያ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ብዙ ሕዝብ በሆታ አቀባበል አድርጎለት ነበር። በሕዝቡ ውስጥ አዋቂዎችም ትንንሽ ልጆችም ነበሩበት። በዘገባው መሠረት ‘በመቅደስም ልጆች ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ ይጮሁ ነበር’ የካህናት አለቆች ይህንን በተቃወሙ ጊዜ፣ ኢየሱስ “ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን?” በማለት መለሰላቸው።—ማቴዎስ 21:15, 16
ሌላው ቀርቶ በዛሬው ጊዜ እንኳ የኢየሱስ ቃላት በትክክል ሲፈጸም እውነት መሆኑን መመልከታችን የሚያስደስት አይደለምን? ‘ከሕፃናትና ከሚጠቡ አፍ’፣ በአሥራዎቹ ዓመታት ከሚገኙ እንዲሁም ከወጣት ወንዶችና ሴቶች ይሖዋ ምስጋና አግኝቷል። በእርግጥም ይሖዋን ለማወደስ አነስተኛ የዕድሜ ገደብ አልተበጀለትም።—ኢዩኤል 2:28, 29