ወደ ጉልምስና ለማደግ ያደረግሁት ውሳኔ
ካርል ዳካው እንደተናገረው
“ወደ ጉልምስና ማደግ ወይስ ወደ ኃጢአት መመለስ? የቱን ትመርጣላችሁ?” ይህ በሰኔ 15, 1948 መጠበቂያ ግንብ እትም ውስጥ የሚገኝ የአንድ ትምህርት ርዕስ ነበር። ርዕሰ ትምህርቱ ዩናይትድ ስቴትስ ባለው የእርሻ ቦታ ካጋጠመኝ መንፈሳዊ አደጋ ከ43 ዓመት በላይ በደቡብ አሜሪካ እንዳሳልፍ ወዳደረገኝ የሚስዮናዊነት ሥራ ለውጥ እንዳደርግ በጣም ረድቶኛል።
የተወለድኩት መጋቢት 31, 1914 በሜኔሶታ ግዛት በቨርገስ ከተማ በምትገኝ በአንዲት ትንሽ የእንጨት ጎጆ ውስጥ ሲሆን በቤተሰቡም ውስጥ ካለነው አራት ልጆች እኔ ሦስተኛ ልጅ ነኝ። በልጅነቴ ያሳለፍኳቸው ዓመታት በጣም የሚያስደስቱ ነበሩ። ከአባቴ ጋር ዓሣ እናጠምድ እንደ ነበር አስታውሳለሁ። ሆኖም እናቴን ሁሌ ስለሚያማት በቤት ሥራዎች ለመርዳት ከአምስተኛ ክፍል ትምህርቴን ለማቋረጥ ተገደድኩ። የ13 ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ በሽታዋን ተመርምራ የሳንባ ካንሰር እንደሆነ ታወቀ።
እናቴ ብዙም በሕይወት እንደማትቀጥል ስላወቀች ቦታዋን እንድረከብ ታዘጋጀኝ ጀመር። ኩሽና ውስጥ ትቀመጥና ምግብ ማብሰልና መጋገር እንዴት እንደምችል መመሪያዎችን ትሰጠኛለች። በተጨማሪም ልብስ ማጠብ፣ የአትክልቱን ቦታ ጥሩ አድርጎ መያዝና አንድ መቶ ዶሮዎችን መንከባከብ አስተምራኛለች። እንዲሁም በየቀኑ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ እንዳነብ ታበረታታኝ ነበር፤ ምንም እንኳ የማንበብ ችሎታዬ ውስን ቢሆንም ምክሯን በተግባር አውየዋለሁ። ለአሥር ወራት ካሰለጠነችኝ በኋላ እናቴ ጥር 27, 1928 ሞተች።
ጦርነቱ ሕይወታችንን ለወጠው
መስከረም 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተከፈተ በኋላ ባለንበት በሉተራን ቤተ ክርስቲያን በየሳምንቱ እሁድ እሁድ ለሠራዊቱ ይጸለይ ነበር። ታላቅ ወንድሜ ፍራንክ ሰውን ላለመግደል ወስኖ ስለ ነበር ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት አሻፈረኝ በማለቱ በቁጥጥር ሥር ዋለ። ፍርዱ በሚሰማበት ጊዜ “ንጹሐን ሰዎችን ከመግደሌ በፊት እናንተ ልትገድሉኝ ትችላላችሁ!” በማለት ገለጸ። በዋሽንግተን ግዛት የባሕር ጠረፍ አቅራቢያ ባለችው ማክኔል ደሴት በሚገኘው እስር ቤት አንድ ዓመት እንዲያሳልፍ ተፈረደበት።
እዚያም በጦርነቱ ወቅት ፍጹም ገለልተኛ በመሆናቸው ምክንያት የታሰሩ ከ300 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች አገኘ። (ኢሳይያስ 2:4፤ ዮሐንስ 17:16) ወዲያው ከእነርሱ ጋር መቀራረብ ጀመረና እዚያው እስር ቤት እያለ ተጠመቀ። በጥሩ ጠባዩ የተነሳ ቅጣቱ ወደ ዘጠኝ ወራት ተቀነሰለት። ኅዳር 1942 ፍራንክ መፈታቱን ሰማን፤ ከተፈታ በኋላ ወዲያውኑ ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች ነገረን። መልእክቱን በመጽሐፍ ቅዱሶቻችን አማካኝነት በጥንቃቄ ከመረመርነው በኋላ ፍራንክ ያስተማረን ነገር እውነት መሆኑን ሁላችንም ለመገንዘብ ችለናል።
የመንፈሳዊ እድገት ጋሬጣዎች
በ1944 ከአጎቴ ጋር ለመኖር በሞንታና ግዛት ወደምትገኘው ሞልታ ወደምትባል ቦታ ተዛወርኩ። ከአጎቴ ጋር የምንመሳሰልበት ነገር አለ፤ ይኸውም ሁለታችንም ሚስቶቻችን ለስድስት ወራት አብረውን ከኖሩ በኋላ ጥለውን ሄደው ነበር። በእርሻና ምግብ በማብሰል ስለምረዳው ከእርሱ ጋር በመሆኔ በጣም ተደሰተ፤ የምናገኘውንም ትርፍ እኩል እንካፈል ነበር። አጎቴ አብሬው የምቆይ ከሆነ የእርሱን 260 ሄክታር የእርሻ ቦታ እንደምወርስ ተናገረ። እነዚያ ጊዜያት በእርሻ የተትረፈረፈ ምርት የተገኘባቸው ዓመታት ከመሆናቸውም በላይ የግብርናን ሥራ ወድጄው ነበር። በየዓመቱ ከወትሮው የበለጠ ሰብል ከማግኘታችንም በተጨማሪ አራት መስፈሪያ ስንዴ 3 ዶላር ከ16 ሳንቲም ያወጣ ነበር።
ነገር ግን አጎቴ ሞልተ በሚገኘው አነስተኛ የምሥክሮች ጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘቴን አልወደደውም። ሰኔ 7, 1947 አጎቴ ሳያውቅ ውልፍ ፖይንት በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ ላይ ተጠመቅሁ። እዚያም አንድ ክርስቲያን ወንድም አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ እንድሆን ግብዣ አቀረበልኝ። ሕይወቴን እንዲህ ባለ መንገድ መጠቀም የልቤ ፍላጎት ቢሆንም አጎቴ ይህንን ያህል ብዛት ያለው ሰዓት ለአገልግሎቱ እንዳውል በፍጹም እንደማይፈቅድልኝ ገለጽኩለት።
ይህ ከተፈጸመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ እንድሆን ይገፋፋኝ ከነበረ አንድ ጓደኛዬ የተላከልኝን ደብዳቤ አጎቴ ከፍቶ አነበበው። አጎቴ በጣም ተናዶ ወይ ስብከት እንዳቆም አለዚያም እርሻውን ትቼ እንድሄድ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠኝ። የእርሻ ሥራ በጣም ከመውደዴ የተነሳ በራሴ ውሳኔ የምተወው ስለማይመስለኝ የተሰጠኝ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ጥሩ ነበር። ስለዚህ ሚኔሶታ ወደሚገኙት ቤተሰቦቼ ተመለስኩ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉም ተጠምቀው በዴትሮኢት ሌክስ ጉባኤ ይሰበሰቡ ነበር።
መጀመሪያ ቤተሰቦቼ አቅኚ እንድሆን ያበረታቱኝ ነበር፤ ሆኖም በ1948 በመንፈሳዊ መቀዝቀዝ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ነበር “ወደ ጉልምስና ማደግን ወይስ ወደ ኃጢአት መመለስን? የቱን ትመርጣላችሁ?” የሚለው ርዕሰ ትምህርት የሚያስፈልገኝን መንፈሳዊ ማበረታቻ ያቀረበልኝ። “ከቀን ወደ ቀን በእውቀት ማደግን ወደን አሻፈረኝ የምንል ከሆነ በጣም አስከፊ ውጤቶች መከተላቸው የማይቀር ነው” በማለት ያስጠነቅቃል። ርዕሰ ትምህርቱ እንዲህ አለ፦ “በጽድቅ እድገት ማድረግ አለብን እንጂ ባለንበት መቆምና ወደ ኋላ መመለስ አንችልም። የማያቆም እድገት እንደገና ወደ ኋላ መመለስን የሚከላከል ታላቅ ኃይል ነው።”
ቤተሰቦቼ ሌሎች ምክንያቶችን ቢያቀርቡም እውነተኛው ችግር ሀብታም ለመሆን ያላቸው ምኞት እንደነበረ አምናለሁ። ይበልጡን ጊዜ ለግብርና ማዋልና ለስብከቱ ትንሽ ሰዓት መስጠት የሚያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅማ ጥቅም ለማየት ችለዋል። ሀብታም የመሆን ምኞት በሚያስከትለው ወጥመድ ከመያዜ በፊት አቅኚ ለመሆን እቅድ አወጣሁ። ቀላል እንደማይሆን አውቃለሁ፤ እንዲያውም ላደርገው አልችልም ብዬ አስቤ ነበር። ስለዚህ በ1948 ሆን ብዬ ከዓመቱ አስቸጋሪ በሆነው የታኅሣሥ ወር አቅኚነትን ለመጀመር በማመልከት ራሴን ፈተንኩ።
በአቅኚነት አገልግሎት መቀጠል
ይሖዋ ጥረቴን ባርኮልኛል። ለምሳሌ አንድ ቀን ውርጩ ሳይጨመር የቅዝቃዜው መጠን ከዜሮ በታች 27 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ደርሶ ነበር። በተደጋጋሚ እጆቼን እያፈራረቅሁ መደበኛውን የመንገድ ላይ ምሥክርነቴን ሳከናውን በጣም የቀዘቀዘውን እጄን ኪሴ ውስጥ እከትና ሌላኛው እጄ ደግሞ እስኪቀዘቅዝና ወደ ኪሴ መግባት እስከሚያስፈልገው ድረስ መጽሔቶችን ይዤ እቆም ነበር። አንድ ሰው ወደ እኔ መጣ። የምሠራውን ለጥቂት ጊዜ እንደተመለከተ ከነገረኝ በኋላ “መጽሔቶቹ ውስጥ ያለው ይህን ያህል አንገብጋቢ ጉዳይ ምንድን ነው? እስቲ እነዚያ ሁለቱን ስጠኝና ላንብባቸው” ብሎ ጠየቀኝ።
በዚህ ጊዜ ከቤተሰቦቼ ጋር የቅርብ ግንኙነት ማድረግ መንፈሳዊነቴን አደጋ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ስለደረስኩበት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርን ጠየቅሁና ሞንታና በምትገኘው ሚልዝ ሲቲ አዲስ የአገልግሎት ምድብ ተሰጠኝ። እዚያም የቡድን አገልጋይ (በአሁን ጊዜ መሪ የበላይ ተመልካች እንደሚባለው ማለት ነው) ሆኜ አገለግል ነበር። ሁለት በሦስት ሜትር በሆነ ተጎታች ቤት እየኖርኩ ግማሽ ቀን በደረቅ የልብስ ንጽህና መስጫ ውስጥ በመሥራት ራሴን እረዳ ነበር። አልፎ አልፎም በጣም በምወደው የአጨዳ ሥራ ተቀጥሬ እሠራ ነበር።
በዚህ ወቅት ቤተሰቦቼ በአስከፊ መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ሰማሁ። በመጨረሻም እነርሱና ሌሎቹ የዲትሮኢት ሌክስ ጉባኤ አባላት የይሖዋን ድርጅት መቃወም ጀመሩ። ከጉበኤው 17 የመንግሥቱ አስፋፊዎች 7 ብቻ በታማኝነት ጸኑ። ቤተሰቤ እኔንም ከይሖዋ ድርጅት ለማውጣት ቆርጦ ስለነበር ለዚህ አንድ መፍትሄ ብቻ እንዳለ ተገነዘብኩ፤ ይኸውም ይበልጥ በመንፈሳዊ ማደግ ነበር። ግን እንዴት?
የሚስዮናዊነትን አገልግሎት ማከናወን
በ1950 በኒው ዮርክ ሲቲ በተደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ወቅት ሚስዮናውያን ተማሪዎች ከመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት 15ኛ ኮርስ ሲመረቁ ተመለከትኩ። ‘አቤት፣ ምናለ እኔም ከአገራቸው ውጪ ተመድበው ይሖዋን ለማገልገል ከሚሄዱት መካከል መሆን በቻልኩ’ ብዬ አሰብኩ።
ማመልከቻ አስገባሁና በየካቲት 1951 የሚጀምረው 17ኛው የጊልያድ ኮርስ አባል እንድሆን ተቀባይነት አገኘሁ። ትምህርት ቤቱ ያለበት በሰሜናዊ ኒው ዮርክ የሚገኝ አንድ የእርሻ ቦታ በጣም ውብ ነበር። ከትምህርት ሰዓታት በኋላ በረት ውስጥ ከብቶች ጋር ወይም ውጪ እርሻ ቦታ መሥራት በጣም እፈልግ ነበር። ነገር ግን በጊዜው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመንግሥት እርሻ የበላይ ተመልካች የሆነው ጆን ቡዝ በደረቅ የልብስ ንጽህና መስጫ ውስጥ የመሥራት ልምድ ያለኝ እኔ ብቻ እንደሆንኩ ነገረኝ። ስለዚህ ይህንን እንድሠራ ተመደብኩ።
ጊልያድ እንደኔ ላለ እስከ አምስተኛ ክፍል ብቻ ለተማረ ሰው ቀላል አልነበረም። በየመኝታ ቤቶቹ ያሉት መብራቶች ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ሲሆን መጥፋት ያለባቸው ቢሆንም እኔ ግን ብዙውን ጊዜ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አጠና ነበር። አንድ ቀን ከአስተማሪዎቹ አንዱ ቢሮው እንድመጣ ጠራኝ። “ካርል፤ ማርክህ በጣም ጥሩ እንዳልሆነ ለመመልከት ችያለሁ” አለ።
‘ወይኔ፤ ለቅቄ እንድሄድ ሊጠይቁኝ እኮ ነው’ ብዬ በልቤ አሰብኩ።
ነገር ግን አስተማሪው እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ከማጥናት ይልቅ ጊዜዬን እንዴት በተሻለ መንገድ መጠቀም እንደምችል ፍቅር በተሞላበት ሁኔታ አንዳንድ ምክሮች ለገሰኝ። ፈራ ተባ እያልኩ “እዚህ ጊልያድ ለመቆየት ብቁ ነኝ?” ብዬ ጠየቅሁ።
“አዎን፣ ትቆያለህ፤ ለዲፕሎማው ብቁ ትሆን እንደሆነና እንዳልሆነ ግን እንጃ” ሲል መለሰ።
የትምህርት ቤቱ ፕሬዘዳንት ናታን ኤች ኖር ከተናገራቸው ቃላት ማጽናኛ አገኘሁ። የሚያደንቀው ከፍተኛ ማርክ ማግኘትን ሳይሆን በአገልግሎት ምድባቸው ጸንተው በመቆየት “ሥራቸውን የሙጥኝ” የሚሉ ሚስዮናውያንን እንደሆነ መጀመሪያ ላይ ለተማሪዎቹ ነግሯቸው ነበር።
በጣም የሚከብደኝ ትምህርት ስፓንኛ ቋንቋ ማጥናት ነበር፤ ቢሆንም ከለመድኩት የአገሬ ቅዝቃዜ ጋር አንድ ዓይነት በሆነው በአላስካ እመደባለሁ ብዬ ተስፋ አደርግ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በእንግሊዝኛ መስበክ እንደምችል አስቤ ነበር። ስለዚህ በኮርሱ አጋማሽ ላይ ደቡብ አሜሪካ በምትገኘው ኢኳዶር እንዳገለግል ምድብ ስቀበል እንዴት ክው እንዳልኩ ልትገምቱ ትችላላችሁ። አዎን፣ የግድ ስፓንኛ መናገር ሊኖርብኝ ከመሆኑም በላይ ቦታው የሚገኘው በጣም ሞቃት በሆነው የምድር ወገብ ነው!
አንድ ቀን አንድ የኤፍ ቢ አይ ወኪል ጊልያድ ትምህርት ቤት መጥቶ ጠየቀኝ። በዲትሮኢት ሌክ ድርጅታችንን ትቶ ስለወጣው የቡድን አገልጋይ ልጅ ሁኔታ ጠየቀኝ። በዚያ ወቅት ኮሪያ ጦርነት እየተካሄደ ነበር፤ ይህ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች አገልጋይ ነኝ ስላለ ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ ተደረገ። አሁን የይሖዋ ምሥክር እንዳልሆነ ነገርኩት። ወኪሉ ሲሰናበተኝ “አምላክህ በሥራህ ይባርክህ” አለኝ።
ይህ ወጣት ኮሪያ ላይ በተደረገው እሱ መጀመሪያ በተካፈለበት አንድ ውጊያ ላይ እንደ ተገደለ ከጊዜ በኋላ አወቅሁ። በአምላክ ድርጅት ውስጥ ወደ ጉልምስና ማደግ ይችል ለነበረ አንድ ሰው ይህ እንዴት ያለ አሳዛኝ ውጤት ነው።
በመጨረሻም አስደሳቹ የምረቃችን ቀን ሐምሌ 22, 1951 ደረሰ። በእርግጥ ከቤተሰቦቼ መካከል የተገኘ ባይኖርም ባደረግሁት እድገት ምክንያት ዲፕሎማ ስቀበል ፍጹም ደስታ ተሰምቶኝ ነበር።
ከውጭ አገር መስክ ጋር መለማመድ
በአገልግሎት ምድቤ ላይ በነበርኩበት ጊዜ የእናቴ ማሠልጠኛ በእርግጥ ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። አዲስ የሆነብኝ በስፓንኛ ቋንቋ መስበክ እንጂ ምግብ ማብሰል፣ ልብሶችን በእጅ ማጠብና የቧንቧ ውኃ አለመኖር አልነበረም! ወረቀት ላይ በተጻፈ የስፓንኛ ስብከት አልፎ አልፎ እጠቀም ነበር። በስፓንኛ ቋንቋ የሕዝብ ንግግር ከመስጠቴ በፊት ሦስት ዓመት የፈጀብኝ ሲሆን ይህንንም ያቀረብኩት ረዣዥም ማስታወሻዎችን በመጠቀም ነው።
በ1951 ኢኳዶር ስደርስ ያሉት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ከ200 ያነሱ ነበሩ። ለመጀመሪያዎቹ 25 ዓመታት ወይም ከዚያ በላይ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ የተጓተተ ይመስል ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶቻችን ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ከሌላቸው የካቶሊክ ወጎች ፈጽሞ የተለዩ ሲሆን ለአንድ የትዳር ጓደኛ ታማኝ ስለመሆን ከሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር መጣበቃችን በተለይ በሕዝቡ ዘንድ ያልተለመደ ነበር።—ዕብራውያን 13:4
የሆኖ ሆኖ ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማበርከት ችለን ነበር። የሙዝ አምራች እርሻ ቦታዎች ማዕከል በሆነው መቻላ ከተማ ያከናወንነው አገልግሎት ለዚህ ምሳሌ ይሆናል። እኔና ኒኮላስ ዌስሊ በ1956 እዚያ ስንደርስ ብቸኛ ምሥክሮች ነበርን። ጠዋት በማለዳ ተነስተን በዚያን ጊዜ እየተገነባ ባለው አውራ ጎዳና ላይ ይሠሩ በነበሩ ገልባጭ መኪናዎች ተሳፍረን እንሄዳለን። ረዥም ርቀት ከተጓዝን በኋላ እንወርድና ወደ መኖሪያችን ስንመለስ መንገድ ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ እንመሠክርላቸዋለን።
አንድ ቀን እኔና ኒክ ከሁለታችን ማን ብዙ መጽሔቶች እንደሚያበረክት ለማየት የምናበረክተውን መመዝገብ ጀመርን። እኩለ ቀን ላይ እኔ እየመራሁ እንደነበር አስታውሳለሁ ምሽት ሲደርስ ግን እኩል 114 መጽሔቶችን አበርክተን ነበር። የመጽሔት ደንበኞቻችን ለሆኑ ሰዎች በየወሩ በመቶ የሚቆጠሩ ወቅታዊ የሆኑ ጽሑፎቻችንን እንተውላቸው ነበር። በወር ውስጥ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ መጽሔቶችን ስድስት ጊዜ አበርክቼአለሁ። ከእነዚያ መጽሔቶች ምን ያህል ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለመማር እንደቻሉ አስቡ!
በተጨማሪም በመቻላ ከተማ በኢኳዶር የመጀመሪያውን የጉባኤ ንብረት የሆነ የመንግሥት አዳራሽ የመገንባት መብት አግኝተናል። ይህ የሆነው ከ35 ዓመት በፊት በ1960 ነበር። በእነዚያ ቀደም ባሉት ጊዜያት በስብሰባችን ላይ የምንገኘው 15 የምናክል ተሰብሳቢዎች ብቻ ነበርን። ዛሬ መቻላ እድገት የሚያደርጉ 11 ጉባኤዎች አሉት።
ዩናይትድ ስቴትስን መጎብኘት
በ1970ዎቹ ማብቂያ ላይ ለዕረፍት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመልሼ በነበረበት ወቅት ከወንድሜ ከፍራንክ ጋር ጥቂት ሰዓታት አሳልፌ ነበር። ሬድ የተባለው ወንዝ አቋርጦ የሚያልፍበትን ሸለቆ ከርቀት ማየት ወደሚያስችለን አንድ ኮረብታ በመኪናው ወሰደኝ። እንደ ባሕር የተንጣለለው የተዘናፈለ የደረሰ ስንዴ ንፋሱ ሲያወዛውዘው ያምር ነበር። በዛፍ የተከበበውን የሼይኒ ወንዝ ከርቀት ማየት ይቻላል። ወንድሜ መናገር ሲጀምር በዚህ ሰላማዊ ውበት መደሰቴ ተቋረጠ።
“ሞኝ ባትሆንና እዚያ ደቡብ አሜሪካ ሄደህ ባትቀመጥ ኖሮ ይሄ የአንተም ይሆን ነበር!”
በፍጥነት አቋረጥኩትና “ፍራንክ እዚህ ላይ አቁም” አልኩት።
ሌላ ቃል አልተናገረም። ከጥቂት ዓመታት በኋላ በደቡብ ዳኮታ የሚገኘውን ከ400 ሄክታር በላይ የሚያክል ያማረ ሰፊ የእርሻ ቦታውንና ከአጎቴ የወረሰውን 260 ሄክታር ጭምር ትቶ በአንጎሉ ውስጥ ደም ፈሶ ሳይታሰብ ሞተ።
አሁን ቤተሰቦቼ ሁሉ በሕይወት የሉም። ነገር ግን ከዓመታት በፊት ሁላችንም የይሖዋ ምሥክሮች ሆነን አዲስ ምዕራፍ በከፈትንበት በዲትሮኢት ሌክስ ከ90 የሚበልጡ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ያሉበት መንፈሳዊ ቤተሰብ ስላለኝ እደሰታለሁ።
መንፈሳዊ እድገት ማድረግን መቀጠል
ባለፉት 15 ዓመታት እዚህ ኢኳዶር በሚገኘው መንፈሳዊ መከር የተትረፈረፈ ሰብል ተመርቷል። በ1980 የመንግሥቱ አስፋፊዎች 5,000 ያህሉ ነበር፤ አሁን ግን ከ26,000 የምንበልጥ ሆነናል። ከእነዚህም መካከል ከአንድ መቶ የሚበልጡ ሰዎች እንዲጠመቁ በመርዳት ይህን በረከት አጭጃለሁ።
አሁን በ80 ዓመት ዕድሜዬ በወር ውስጥ በአገልግሎቱ 30 ሰዓት ለማሳለፍ በ1951 የ150 ሰዓት ግቤን ለማሟላት ከምደክመው የበለጠ ጠንክሬ እሠራለሁ። ፕሮስቴት ካንሰር እንዳለብኝ ካወቅሁበት ከ1989 ጀምሮ የማገገሚያ ጊዜዬን ለንባብ ተጠቅሜበታለሁ። ከዚያ ዓመት ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር 19 ጊዜ ከማንበቤም በላይ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን መጽሐፍ 6 ጊዜ አንብቤዋለሁ። በዚህ መንገድ በመንፈሳዊ ማደጌን ቀጥያለሁ።
አዎን፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው እርሻ ቦታ ቁሳዊ ጥቅሞችን ለማግኘት አጋጣሚዎች ነበሩኝ። ነገር ግን ቁሳዊ ሀብት የሚከፍለው ወሮታ በመንፈሳዊው መከር ካገኘሁት ደስታ ጋር ሲወዳደር ከንቱ ነው። እዚህ ኢኳዶር የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በሚስዮናዊነት ሥራዬ ወቅት ከ147,000 መጽሔቶችና ከ18,000 መጽሐፎች በላይ እንዳበረከትኩ ነግሮኛል። እነዚህንም አብዛኞቹ እንደበቀሉ መንፈሳዊ ዘሮች አድርጌ እመለከታቸዋለሁ። ሌሎቹ ደግሞ ሰዎች ስለነዚህ የመንግሥት እውነቶች በሚያነቡበት ጊዜ ወደፊት በልባቸው ውስጥ ሊበቅሉ ይችላሉ።
ከሁሉም መንፈሳዊ ልጆቼና አምላካችን ይሖዋን ለማገልገል ከመረጡ ከሌሎች በሚልዮን ከሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ወደ አምላክ አዲስ ዓለም እያደጉ ከመሄድ የሚበልጥ አንዳች ነገር ይኖራል ብዬ ማሰብ አልችልም። ገንዘብ አንድን ሰው ከዚህ ክፉ ዓለም መጨረሻ አያድነውም። (ምሳሌ 11:4፤ ሕዝቅኤል 7:19) ነገር ግን እያንዳንዳችን ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና ማደጋችንን የምንቀጥል ከሆነ መንፈሳዊ ሥራችን ማፍራቱን ይቀጥላል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1949 ሞንታና በምትገኘው ሚልዝ ሲቲ ለአቅኚነት ዝግጅት ማድረግ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1952 ለሚስዮናውያን ቤታችን ውኃ ስንገዛ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1957 መቻላ ከተማ ስንሰብክ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1989 ከታመምኩ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስን 19 ጊዜ ከዳር እስከ ዳር አንብቤዋለሁ