የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 6/1 ገጽ 6-10
  • ብናዝንም ተስፋ የሌለን አይደለንም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ብናዝንም ተስፋ የሌለን አይደለንም
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሞት ወደ ሰብዓዊው ቤተሰብ ገባ
  • ያዘኑ ታማኝ ሰዎች
  • በኢየሱስ ዘመን የነበረው የሐዘን ሁኔታ
  • ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?
  • በሐዘን ላይ ላሉ የሚሆን ተግባራዊ እርዳታ
  • በሞት የተለዩህ የምትወዳቸው ሰዎች ያላቸው እውነተኛ ተስፋ
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ምን ይሆናሉ?
    ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
  • ሙታን ያላቸው አስተማማኝ ተስፋ
    የምትወዱት ሰው ሲሞት
  • ማዘን ስህተት ነውን?
    ንቁ!—2001
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 6/1 ገጽ 6-10

ብናዝንም ተስፋ የሌለን አይደለንም

“ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፣አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን።”—1 ተሰሎንቄ 4:13

1. የሰው ልጆች ዘወትር ምን ያጋጥማቸዋል?

አንድ የምትወደው ሰው በሞት ተለይቶሃልን? በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ብንገኝም አብዛኞቻችን አንድ ዘመዳችንን ወይም ወዳጃችንን በማጣት ሐዘን ደርሶብናል። ምናልባት ሟቹ አያታችን፣ ወላጃችን፣ የትዳር ጓደኛችን ወይም ልጃችን ሊሆን ይችላል። እርጅና፣ በሽታና ድንገተኛ አደጋዎች በየጊዜው በሰዎች ላይ ሞት ያስከትላሉ። ወንጀል፣ ዓመፅና ጦርነት የሚደርሰውን መከራና ሐዘን ያባብሱታል። በየዓመቱ በመላው ዓለም በአማካይ ከ50 ሚልዮን በላይ ሰዎች ይሞታሉ። በ1993 በአማካይ በየቀኑ ይሞቱ የነበሩት ሰዎች ቁጥር 140,250 ነበር። ሞት የወዳጆችንና የቤተሰብ አባላትን ሕይወት ይነጥቃል፤ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለው ሐዘን ደግሞ ከፍተኛ ነው።

2. የልጆችን ሞት በተመለከተ እንግዳ የሚሆነው ነገር ምንድን ነው?

2 አንዲት ነፍሰ ጡር ልጃቸውን በአሳዛኝ ሁኔታ በድንገት በመኪና አደጋ ያጡ በዩ ኤስ ኤ ካሊፎርኒያ ውስጥ የሚኖሩ ወላጆች የደረሰባቸው ሁኔታ አያሳዝነንምን? ባልታሰበ ወቅት አንዲት ብቸኛ ልጃቸውንና ወደፊት የልጅ ልጃቸው ሊሆን የሚችለውን ሕፃን አጡ። የአደጋው ሰለባ የሆነችው ሴት ባል ሚስቱንና የመጀመሪያ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን አጣ። ትንሽም ሆነ ትልቅ ልጃቸው የሞተባቸው ወላጆች ሁኔታው እንግዳ ይሆንባቸዋል። ልጆች ከወላጆቻቸው በፊት መሞታቸው የተለመደ ነገር አይደለም። ሁላችንም መኖር እንፈልጋለን። ስለዚህ ሞት እውነትም ጠላት ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:26

ሞት ወደ ሰብዓዊው ቤተሰብ ገባ

3. አዳምና ሔዋን አቤል ሲሞት ምን ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል?

3 የመጀመሪያዎቹ ሰብአዊ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ካመፁበት ጊዜ ጀምሮ ኃጢአትና ሞት በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ላለፉት ስድስት ሺህ ዓመታት ያህል ነገሥታት ሆነው ሲገዙ ቆይተዋል። (ሮሜ 5:14፤ 6:12, 23) እነዚህ ወላጆቻችን አቤል የተባለው ልጃቸው ቃየን በተባለው ወንድሙ ሲገደል ምን ተሰምቷቸው እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። በብዙ ምክንያቶች የተነሳ በጣም አሳዛኝ ገጠመኝ እንደሆነባቸው ጥርጥር የለውም። በራሳቸው ልጅ ላይ ከደረሰው ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው ሲሞት ተመልክትው ነበር። ዓመፃቸውና ነፃ ምርጫቸውን አላግባብ መጠቀማቸውን መቀጠላቸው ያስከተለውን ውጤት ተመልክተው ነበር። ቃየን አምላክ ቢያስጠነቅቀውም እንኳ የመጀመሪያውን የራስን ወንድም የመግደል ተግባር ለመፈጸም መረጠ። ሔዋን ሴት የተባለውን ልጅ በወለደችበት ወቅት “ቃየን በገደለው በአቤል ፋንታ እግዚአብሔር ሌላ ዘር ተክቶልኛል” ብላ ስለ ነበር በአቤል ሞት በጣም አዝና እንደነበር እናውቃለን።—ዘፍጥረት 4:3–8, 25

4. ነፍስ አትሞትም የሚለው ተረት አቤል ከሞተ በኋላ ምንም ሊያጽናና ያልቻለው ለምን ነበር?

4 በተጨማሪም የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ወላጆቻችን አምላክ በእነሱ ላይ የፈረደባቸው ፍርድ ማለትም ሳይታዘዙ ቀርተው ቢያምፁ ‘እንደሚሞቱ’ የተነገራቸው ቃል ሲፈጸም ተመልክተዋል። የሰይጣን ውሸት ቢኖርም ነፍስ አትሞትም የሚለው ተረት በወቅቱ ስላልተስፋፋ ከዚህ ትምህርት የሚያገኙት የሐሰት ማጽናኛ አልነበራቸውም። አምላክ አዳምን ‘ወደ ወጣህበት መሬት ትመለሳለህ። . . . አፈር ነህና፣ ወደ አፈር ትመለሳለህ’ ብሎት ነበር። ሰው ወደፊት የማትሞት ነፍስ ሆኖ በሰማይ፣ በሲኦል፣ ነፍሳት የክርስትና ጥምቀት ባለመቀበላቸው ምክንያት ወደ ሰማይ እንዳይገቡ የታገዱበት መኖሪያ ነው ተብሎ በሚታመነው፣ በመንጽሔ ወይም በሌላ ቦታ ይኖራል ብሎ አምላክ የጠቀሰው ነገር የለም። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:4, 5, 19) አዳምና ሔዋን ኃጢአት የሠሩ ሕያው ነፍሳት እንደመሆናቸው መጠን ውሎ አድሮ ይሞቱና ከሕልውና ውጪ ይሆናሉ። ንጉሥ ሰሎሞን በመንፈስ አነሣሽነት እንዲህ ብሎ ጽፎ ነበር፦ “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቷልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቷል፣ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም።”—መክብብ 9:5, 6

5. ሙታን ያላቸው እውነተኛ ተስፋ ምንድን ነው?

5 እነዚህ ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው! ከዛሬ ሁለት ወይም ሦስት መቶ ዓመታት በፊት የነበሩ የቀድሞ አባቶቹን ማን ያስታውሳል? ብዙውን ጊዜ መቃብራቸው እንኳ የት እንደሆነ አይታወቅም ወይም ከረጅም ጊዜ በፊት ተረስቷል። ታዲያ ይህ ማለት እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምንም ተስፋ የላቸውም ማለት ነውን? በጭራሽ አይደለም። ማርታ የሞተ ወንድሟን አልዓዛርን አስመልክታ ለኢየሱስ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” ብላው ነበር። (ዮሐንስ 11:24) ዕብራውያን፣ አምላክ ሙታንን ወደፊት እንደሚያስነሳ ያምኑ ነበር። ሆኖም ይህ እምነታቸው የሚወዱት ሰው በሞት ሲለያቸው እንዳያዝኑ አላገዳቸውም።—ኢዮብ 14:13

ያዘኑ ታማኝ ሰዎች

6, 7. አብርሃምና ያዕቆብ ሰው ሲሞትባቸው ምን ስሜት አሳይተው ነበር?

6 ከአራት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት የአብርሃም ሚስት የነበረችው ሣራ ስትሞት “አብርሃምም ለሣራ ሊያዝንላትና ሊያለቅስላት ተነሣ።” ያ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የሚወዳትንና ታማኝ ሚስቱን በማጣቱ ተሰምቶት የነበረውን ጥልቅ ሐዘን ገለጸ። የወንድነት መንፈስ የነበረው ብርቱ ሰው የነበረ ቢሆንም ሐዘኑን በእንባ መግለጽ አላሳፈረውም ነበር።—ዘፍጥረት 14:11–16፤ 23:1, 2

7 የያዕቆብ ሁኔታም ተመሳሳይ ነበር። ልጁ ዮሴፍ በአውሬ ተበልቷል ብሎ እንዲያምን በተደረገ ጊዜ ምን ተሰምቶት ነበር? በዘፍጥረት 37:34, 35 ላይ የሚከተለውን እናነባለን፦ “ያዕቆብም ልብሱን ቀደደ፣ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፤ መጽናናትን እንቢ አለ፣ እንዲህም አለ፦ ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ። አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ።” አዎን፣ የምንወደው ሰው ሲሞትብን ሐዘናችንን መግለጻችን ሰብዓዊነትና ተፈጥሮአዊ ነገር ነው።

8. ዕብራውያን ብዙውን ጊዜ ሐዘናቸውን ይገልጹ የነበሩት እንዴት ነበር?

8 አንዳንዶች ዘመናዊ ከሆኑ ወይም በአካባቢያቸው ካለው ልማድ አንፃር ሲታይ ያዕቆብ የተሰማው ሐዘን ከልኩ ያለፈና የተጋነነ ነበር ብለው ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ያዕቆብ ያደገበት ጊዜና በወቅቱ የነበረው ባህል የተለየ ነበር። ሐዘኑን ለመግለጽ የለበሰው ማቅ ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው እዚህ ቦታ ላይ ነበር። ሆኖም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንደተገለጸው ሐዘን በለቅሶ፣ ሙሾ በማውጣትና አመድ ላይ በመቀመጥ ይገለጽ ነበር። ዕብራውያን የተሰማቸውን ሐዘን እንዳይገልጹ እንዳልተከለከሉ ከዚህ መረዳት ይቻላል።a—ሕዝቅኤል 27:30–32፤ አሞጽ 8:10

በኢየሱስ ዘመን የነበረው የሐዘን ሁኔታ

9, 10. (ሀ) ኢየሱስ አልዓዛር ሲሞት ምን ተሰምቶት ነበር? (ለ) ኢየሱስ ያሳየው ስሜት ስለ እሱ ምን ይጠቁመናል?

9 የኢየሱስን የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት በተመለከተ ምን ማለት እንችላለን? ለምሳሌ ያህል፣ አልዓዛር በሞተበት ወቅት እህቶቹ ማርታና ማርያም ሲያለቅሱ ነበር። ፍጹሙ ሰው ኢየሱስ በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ቤታቸው ሲደርስ ምን ተሰምቶት ነበር? የዮሐንስ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ፦ ጌታ ሆይ፣ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር አለችው። ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ ወዴት አኖራችሁት? አለም። ጌታ ሆይ፣ መጥተህ እይ አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።”—ዮሐንስ 11:32–35

10 “ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።” እነዚህ ጥቂት ቃላት ስለ ኢየሱስ ሰብዓዊነት፣ ርኅራኄና ስሜት ብዙ ይናገራሉ። ስለ ትንሣኤ ተስፋ ሙሉ በሙሉ የሚያውቅ ቢሆንም “ኢየሱስ አለቀሰ።” (ዮሐንስ 11:35 ኪንግ ጀምስ ቨርሽን) ዘገባው በመቀጠል ተመልካቾች “[አልዓዛርን] እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ” እንዳሉ ይናገራል። ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ወዳጁን በሞት ሲያጣ አልቅሶ ከነበረ በአሁኑ ወቅት አንድ ሰው ወይም አንዲት ሴት ቢያለቅሱ እንደማያስነውር የተረጋገጠ ነው።—ዮሐንስ 11:36

ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?

11. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጹ ለቅሶን የሚመለከቱ ምሳሌዎች ምን ልንማር እንችላለን? (ለ) ተስፋ የሌላቸው ሰዎች በሚያዝኑበት መንገድ የማናዝነው ለምንድን ነው?

11 ከእነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎች ምን ልንማር እንችላለን? ማዘን ሰብዓዊነትና ተፈጥሮአዊ ነገር እንደሆነና ሐዘናችንን ለመግለጽ ማፈር እንደሌለብን ልንማር እንችላለን። የትንሣኤ ተስፋ ሐዘናችንን ቢቀንስልንም እንኳ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ከባድ ሐዘን ያስከትላል። ለብዙ ዓመታት ምናልባትም ለብዙ አሥርተ ዓመታት የነበረ የጠበቀ ወዳጅነትና መጥፎውንም ሆነ ጥሩውን ነገር አብሮ የማሳለፉ ሁኔታ በድንገትና በአሳዛኝ ሁኔታ ያከትማል። ተስፋ እንደሌላቸው ወይም ሐሰተኛ ተስፋ እንዳላቸው ሰዎች እንደማናዝን እሙን ነው። (1 ተሰሎንቄ 4:13) በተጨማሪም ሰው የማትሞት ነፍስ አለችው በሚሉ ወይም ከሞቱ በኋላ እንደገና ተወልዶ ስለመኖር በሚናገሩ አፈ ታሪኮች አንታለልም። ይሖዋ ‘ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ ለማምጣት ቃል እንደገባ እናውቃለን። (2 ጴጥሮስ 3:13) አምላክ “እንባዎችንም ሁሉ [ከዓይኖቻችን] ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”—ራእይ 21:4

12. ጳውሎስ በትንሣኤ ላይ ያለውን እምነት የገለጸው እንዴት ነበር?

12 ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?b ክርስቲያኑ ጸሐፊ ጳውሎስ “የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው” ብሎ ሲጽፍ እንዲያጽናናንና ተስፋ እንዲለግሰን በመንፈስ ተነሣስቶ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:26) ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል “የሚጠፋው የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው” በማለት ይገልጻል። ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ይህን ያህል እርግጠኛ እምነት ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው? ወደ ክርስትና የተለወጠውና ክርስትናን የተማረው ከሞት በተነሣው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ስለ ነበር ነው። (ሥራ 9:3–19) ጳውሎስ “ሞት በሰው [በአዳም] በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው [በኢየሱስ] በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና” ብሎ ሊገልጽ የቻለውም በዚህ ምክንያት ነበር።—1 ቆሮንቶስ 15:21, 22

13. አልዓዛር ከሞት ሲነሣ በዓይን ያዩ ሰዎች ምን ተሰምቷቸው ነበር?

13 የኢየሱስ ትምህርቶች የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ታላቅ መጽናናትና ተስፋ ይሰጡናል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ የአልዓዛርን ሁኔታ በተመለከተ ምን አደረገ? የአልዓዛር አስከሬን ለአራት ቀናት ወዳረፈበት መቃብር ሄደ። ጸለየና “ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ፦ አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ። የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደተገነዙ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ። ኢየሱስም፦ ፍቱትና ይሂድ ተውት አላቸው።” በማርያምና በማርታ ፊት ላይ ይነበብ የነበረውን የመገረምና የደስታ ስሜት ልትገምት ትችላለህን? ጎረቤቶቹ ይህን ተአምር ሲመለከቱ ምንኛ ተደንቀው ይሆን! ይህን ተአምር ያዩ ብዙዎች በኢየሱስ ማመናቸው አያስደንቅም። ጠላቶቹ ግን “ሊገድሉት ተማከሩ።”—ዮሐንስ 11:41–53

14. የአልዓዛር ትንሣኤ እንደ ናሙና ሆኖ የሚያገለግለው ለምን ነገር ነው?

14 ኢየሱስ ያንን የማይረሳ ትንሣኤ የፈጸመው በብዙ የዓይን ምሥክሮች ፊት ነበር። ከዚህ ትንሣኤ በፊት በአንድ ወቅት “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን [የአምላክን ልጅ ድምፅ] የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ” ሲል አስቀድሞ የተናገረው ወደፊት ለሚፈጸም ትንሣኤ እንደ ናሙና ሆኖ የሚያገለግል ነበር።—ዮሐንስ 5:28, 29

15. ጳውሎስና ሐናንያ ኢየሱስ እንደተነሣ ምን ማስረጃ ነበራቸው?

15 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሐዋርያው ጳውሎስ በትንሣኤ ያምን ነበር። በትንሣኤ ለማመን ምን ምክንያት ነበረው? ቀደም ሲል የክርስቲያኖች አሳዳጅ የሆነው ሳውል በሚል መጥፎ ዝናው ይታወቅ ነበር። ስሙና ዝናው በአማኞች ዘንድ ፍርሃት አሳድሮ ነበር። እንዲያውም ክርስቲያኑ ሰማዕት እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ ሲገደል ተስማምቶ አልነበረምን? (ሥራ 8:1፤ 9:1, 2, 26) ሆኖም ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ሲጓዝ ከሞት የተነሣው ክርስቶስ ለጊዜው እንዲታወር በማድረግ አእምሮውን እንዲገዛ አደረገው። ሳውል አንድ ድምፅ እንዲህ ብሎ ሲናገረው ሰማ፦ “ሳውል ሳውል፣ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? . . . ጌታ ሆይ፣ ማን ነህ? አለው። እርሱም፦ አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ . . . አለው።” ከዚያም ከሞት የተነሣው ክርስቶስ ራሱ በደማስቆ ውስጥ ይኖር የነበረውን ሐናንያን ጳውሎስ እየጸለየ ወዳለበት ቤት እንዲሄድና የማየት ችሎታውን እንዲመልስለት አዘዘው። ስለዚህ ጳውሎስና ሐናንያ በራሳቸው ላይ ከደረሰው ተሞክሮ አንፃር በትንሣኤ ለማመን በቂ ምክንያት ነበራቸው።—ሥራ 9:4, 5, 10–12

16, 17. (ሀ) ጳውሎስ የሰው ነፍስ አትሞትም በሚለው የግሪክ ጽንሰ ሐሳብ ያምን እንዳልነበረ እንዴት ልናውቅ እንችላለን? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ምን አስተማማኝ ተስፋ ይሰጣል? (ዕብራውያን 6:17–20)

16 ሳውል ማለትም ሐዋርያው ጳውሎስ ስደት የሚደርስበት ክርስቲያን ሆኖ ፊልክስ በተባለ ገዢ ፊት በቀረበበት ወቅት ምን መልስ እንደሰጠ ልብ በል። በሥራ 24:15 ላይ “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ” የሚል እናነባለን። ጳውሎስ የሰው ነፍስ አትሞትም፤ ከሞት በኋላ ወዳለው ሕይወት ወይም ከመሬት በታች ወዳለው ዓለም ትሻገራለች በሚለው አፈ ታሪካዊ የሆነ አረማዊ የግሪክ ጽንሰ ሐሳብ ያምን እንዳልነበረ ግልጽ ነው። በትንሣኤ ያምን ነበር፤ ሰዎች በትንሣኤ እንዲያምኑም ያስተምር ነበር። ይህም ለአንዳንዶች ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት ያላቸው መንፈሳዊ ፍጥረታት ሆነው የመኖር ለብዙዎች ደግሞ ፍጹም በሆነች ምድር ላይ እንደገና በሕይወት የመኖር ሽልማት ያስገኛል።—ሉቃስ 23:43፤ 1 ቆሮንቶስ 15:20–22, 53, 54፤ ራእይ 7:4, 9, 17፤ 14:1, 3

17 ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙዎች አሁን ካለችበት ሁኔታ በጣም የተለየ ገጽታ በሚኖራት በዚህችው ምድር ላይ የሚወዷቸውን ሰዎች በትንሣኤ አማካኝነት እንደገና እንደሚያዩ እርግጠኛ ተስፋ ይሰጠናል።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1–4

በሐዘን ላይ ላሉ የሚሆን ተግባራዊ እርዳታ

18. (ሀ) “አምላካዊ ፍርሃት” በተባሉት ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ምን ጠቃሚ መሣሪያ ወጥቶ ነበር? (ሣጥኑን ተመልከት።) (ለ) አሁን መልስ የሚያስፈልጋቸው የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው?

18 አሁን በሞት የተለዩን ፊታችን ድቅን ሲሉ ሐዘን ይሰማናል። ይህን አስቸጋሪ የሐዘን ወቅት ለመቋቋም ምን ማድረግ እንችላለን? ሌሎች ሰዎች በሐዘን ላይ ያሉትን ለመርዳት ምን ማድረግ ይችላሉ? ከዚህም በላይ በመስክ አገልግሎት ላይ የምናገኛቸውን እውነተኛ ተስፋ የሌላቸውንና በሐዘን ላይ ያሉ ቅን ሰዎችን ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን? በተጨማሪም በሞት ያንቀላፉብንን የምንወዳቸውን ሰዎች በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምን ተጨማሪ መጽናኛ ልናገኝ እንችላለን? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይደረግ ስለ ነበረው ለቅሶ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው መጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ጥራዝ 2 ከገጽ 446–7 ተመልከት።

b በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው የትንሣኤ ተስፋ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 783–93 ተመልከት።

ልትመልስ ትችላለህን?

◻ ሞት ጠላት ነው ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?

◻ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች ሐዘናቸውን የገለጹት እንዴት ነበር?

◻ እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?

◻ ጳውሎስ በትንሣኤ ለማመን የሚያስችል ምን ምክንያት ነበረው?

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በሐዘን ላይ ላሉ የሚሆን ተግባራዊ እርዳታ

ከ1994–95 በተደረጉት “አምላካዊ ፍርሃት” የተባሉት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የምትወዱት ሰው ሲሞት የተባለ አዲስ ብሮሹር መውጣቱን አሳውቆ ነበር። ይህ የሚያበረታታ ጽሑፍ የተዘጋጀው በሁሉም ብሔራት ያሉ ሰዎችን ለማጽናናት ነው። የሞትን ምንነትና ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ቀላል የሆነ ማብራሪያ እንደያዘ ተረድተህ ይሆናል። ከዚህም ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በጸዳች ምድራዊት ገነት ላይ ሙታንን ለማስነሳት የሰጠውን ተስፋ ያጎላል። በእርግጥም በሐዘን ላይ ያሉትን ያጽናናል። ስለዚህ ለክርስቲያናዊ አገልግሎት የሚጠቅም መሣሪያ ሊሆነንና የሰዎችን ፍላጎት ቀስቅሰን ብዙ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማግኘት ልንገለገልበት ይገባል። ከማንኛውም በሐዘን ላይ ካለ ቅን ግለሰብ ጋር የተወያየናቸውን ነጥቦች በቀላሉ ለመከለስ እንድንችል ለጥናት የሚረዱ ጥያቄዎች በእያንዳንዱ ክፍል መጨረሻ አካባቢ በጥሩ ሁኔታ በሣጥን ውስጥ ሰፍረዋል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አልዓዛር ሲሞት ኢየሱስ አልቅሶ ነበር

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት አስነሥቶት ነበር

[ምንጭ]

የመጀመሪያው ለቅሶ፣ በደብልዩ ቡጌሮ፤ በ1914 ከፍጥረት ፎቶ ድራማ የመጀመሪያ ቅጂዎች የተወሰደ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ