ትዕግሥት የጠፋው ለምንድን ነው?
ኤሚልዮ በ60ዎቹ ዕድሜአቸው ውስጥ ነበሩ።a ትልቅ ወንድ ልጃቸውን ለመቅበር ወደ ሃዋይ ሄደው ነበር። ብዙም ተንቀሳቃሽ መኪናዎች በሌሉበት በአንድ ኮረብታ አጠገብ ባለ መንገድ ላይ ከአንዳንድ ወዳጆቻቸው ጋር እየተጫወቱ ሲጓዙ ከአንድ መኖሪያ ቤት ወደ ዋናው መንገድ ወደ ኋላው በፍጥነት የሚጓዝ መኪና ኤሚልዮን አስደነገጣቸው። መኪናው ለጥቂት ሊገጫቸው ነበር፤ ኤሚልዮ በጣም ከመናደዳቸውና ትዕግሥት ከማጣታቸው የተነሳ ሹፌሩ ላይ ጮኹበት፤ የመኪናውን የኋላ ኮፈን በእጃቸው መቱት። ጭቅጭቅ ተነሣ። ሹፌሩ ኤሚልዮን ሲገፈትራቸው ኤሚልዮ ድንጋያማ በሆነው የእግረኞች መሄጃ መንገድ ላይ በጭንቅላታቸው ወደቁ። ከጥቂት ቀናት በኋላም በጭንቅላታቸው ላይ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ሞቱ። እንዴት ያለ አሳዛኝ ነገር ነው!
የምንኖረው ትዕግሥት በጠፋበት ዓለም ውስጥ ነው። ከመጠን በላይ በሆነ ፍጥነት የሚነዱ ሹፌሮች ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል። ሌሎች በሕግ በተወሰነው ፍጥነት የሚጓዙ መኪናዎችን ከልክ በላይ ተጠግተው አደገኛ በሆነ መንገድ ይነዳሉ። ሌሎች ደግሞ ከሌላ መኪና ኋላ ሆኖው ለመጓዝ ትዕግሥት ስለሌላቸው የተወሰነላቸውን መስመር ጥሰው ዚግዛግ እየነዱ ይሄዳሉ። በቤት ውስጥ ደግሞ የቤተሰብ አባሎች ራሳቸውን መቆጣጠር እስኪሳናቸው ድረስ ይቆጣሉ፤ ይደባደባሉ። ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ጉድለቶች ወይም ስሕተቶች ሳቢያ በጣም ሊበሳጩ ይችላሉ።
ትዕግሥት ይህን ያህል የጠፋው ለምንድን ነው? ሁኔታው ሁልጊዜ እንደዚህ ነበርን? በዘመናችን ትዕግሥተኛ መሆን በጣም አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?
ትዕግሥት የማጣት ምሳሌዎች
መጽሐፍ ቅዱስ አንድ አንገብጋቢ የሆነ ውሳኔ ከማድረጓ በፊት ባሏን ለማማከር ትዕግሥት ስላጣች አንዲት ሴት ይነግረናል። የሴትየዋ ስም ሔዋን ነበር። ከባሏ ከአዳም ቀድማ የተከለከለውን ፍሬ በላች። ለዚህ ከፊሉ ምክንያት ትዕግሥት ማጣት ሳይሆን አይቀርም። (ዘፍጥረት 3:1–6) ባሏስ ምን አደረገ? እሱም ቢሆን እንዲረዳው ወይም መመሪያ እንዲሰጠው ወደ ሰማያዊ አባቱ ወደ ይሖዋ ባለመቅረብ ሔዋንን ተከትሎ ኃጢአት ሲሠራ ትዕግሥት አጥቶ ሊሆን ይችላል። በሁላችንም ላይ ሞት ያስከተለብን ስግብግብነታቸው ወደ ኃጢአት የመራቸው ትዕግሥት ማጣት ታክሎበት ሳይሆን አይቀርም። በተጨማሪም ትዕቢትንና ትዕግሥት ማጣትን ጨምሮ ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌን ከእነሱ ወርሰናል።—ሮሜ 5:12
የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ኃጢአት ከሠሩ ከ2,500 ዓመታት በኋላ የአምላክ ምርጥ ሕዝብ የነበሩት እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜያት ከፍተኛ የእምነትና የትዕግሥት ማጣት ድክመት አሳይተዋል። ይሖዋ ከጥቂት ጊዜ በፊት ከግብፅ ባርነት በተአምር ያወጣቸው ቢሆንም በፍጥነት “ሥራውን ረሱ፣ በምክሩም አልታገሡም።” (መዝሙር 106:7–14) በተደጋጋሚ ጊዜያት ትዕግሥት ስላጡ ብቻ ከባድ ኃጢአቶችን ሠሩ። የወርቅ ጥጃ ሠርተው አመለኩ፤ ይሖዋ በሰጣቸው የመና ዝግጅት ላይ አጉረመረሙ፤ እንዲሁም ብዙዎቹ ይሖዋ በሾመው በሙሴ ላይ እንኳ ሳይቀር ዓምፀው ነበር። በእርግጥም ትዕግሥት ማጣታቸው ሐዘንና ጥፋት አስከትሎባቸዋል።
የመጀመሪያው የእስራኤል ንገሥ ሳኦል ልጆቹ ንጉሣዊ ወራሾቹ መሆን የሚችሉበትን እድል አጣ። ለምን? ምክንያቱም ለይሖዋ መሥዋዕት ሊያቀርብ የነበረውን ነቢዩ ሳሙኤልን መጠበቅ ስላልቻለ ነው። ሳኦል ሰው ስለፈራ ከሳሙኤል ቀድሞ መሥዋዕት አቀረበ። ሳኦል ሥርዓቱን እንደጨረሰ ወዲያውኑ ሳሙኤል በመምጣቱ የተሰማውን ስሜት ገምቱ! ምነው ጥቂት ቢቆይ ኖሮ!—1 ሳሙኤል 13:6–14
ሔዋን ፍሬውን በችኮላ ከመውሰዷ በፊት ምነው አዳምን በጠበቀች ኖሮ! እስራኤላውያን የይሖዋን ምክር መጠበቅ እንዳለባቸው ምነው ቢያስተውሱ ኖሮ! አዎን፣ ትዕግሥት እነሱንም ሆነ እኛን ከብዙ ሐዘንና ሥቃይ ያድነን ነበር።
ትዕግሥት የማጣት መንስኤዎች
መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ትዕግሥት የጠፋበትን ዋነኛ ምክንያት ይነግራናል። ሁለተኛ ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 3 ትውልዳችን “የሚያስጨንቅ ዘመን” እንደሆነ ይነግረናል። ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ፣ . . . ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ . . . ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ . . . ይሆናሉ” ይላል። (ቁጥር 2 እና 3) እንዲህ ዓይነቱ የስግብግብነትና የራስ ወዳድነት ጠባይ በብዙ ሰዎች ልብና አእምሮ ውስጥ ስለተተከለ ሰዎች ሁሉ ሌላው ቀርቶ ክርስቲያኖችም ጭምር ትዕግሥት ማሳየት ከባድ ሆኖባቸዋል። ዓለማውያን ከመጠን በላይ በሆነ ፍጥነት ሲነዱ ወይም ተሰልፈው የሚጠብቁ ሰዎችን ቀድመው ሲቆሙ ስንመለከት ወይም ደግሞ የስድብ ናዳ ሲያወርዱብን ትዕግሥታችን ክፉኛ ይፈተናል። እነሱን ለመምሰል ወይም አጸፋ ለመመለስ ልንፈተንና እነሱ ወዳሉበት ዝቅተኛ ወደሆነ የራስ ወዳድነትና የኩራት ደረጃ ልናዘቅጥ እንችላለን።
አንዳንድ ጊዜ ትዕግሥት እንድናጣ የሚያደርጉን የገዛ ራሳችን የተሳሳቱ ድምዳሜዎች ናቸው። ችኮላ፣ የተሳሳተ አስተሳሰብና ትዕግሥት ማጣት እንዲሁም የቁጡነት ባሕርይ ያላቸውን ግንኙነት ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እንዴት አድርጎ እንደገለጸ ልብ በሉ። እንዲህ አለ፦ “ታጋሽም ከትዕቢተኛ ይሻላል። በነፍስህ ለቁጣ ችኩል አትሁን፣ ቁጣ በሰነፍ ብብት ውስጥ ያርፋልና።” (መክብብ 7:8, 9) አንድ እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ሁኔታውን ሙሉ በሙሉና በትክክል ለመረዳት ጊዜ ወስደን ጉዳዩን ካጤንነው በይበልጥ የሰዎችን ሁኔታ ልንረዳ፣ ልንራራላቸውና ልንታገሣቸው እንችላለን። በሌላ በኩል ግን የትዕቢትና የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ሙሴን እንዳስጨነቁት አጉረምራሚና አንገተ ደንዳና እንደነበሩት እስራኤላውያን ጠባብ አስተሳሰብ እንዲኖረን፣ ትዕግሥት እንድናጣና መራራ ጥላቻ እንዲያድርብን ሊያደርግ ይችላል።—ዘኁልቁ 20:2–5, 10
በዓለም ላይ ትዕግሥት እንዲጠፋ ያደረገው ሌላው ምክንያት ከአምላክ ከመራቅ የመጣው ተስፋ መቁረጥ ነው። ዳዊት ሰዎች አምላክን ተስፋ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ሲገልጽ “ነፍሴ ሆይ፣ አንቺ በእግዚአብሔር ተገዢ፣ ተስፋዬ ከእርሱ ዘንድ ናትና” ብሏል። (መዝሙር 62:5) አብዛኞቹ ይሖዋን የማያውቁ ሰዎች ጠባብ አመለካከትና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ስላላቸው ከመሞታቸው በፊት እያንዳንዷ ጥቃቅን ደስታና ጥቅም እንዳታመልጣቸው ይጥራሉ። መንፈሳዊ አባታቸው እንደሆነው እንደ ሰይጣን ዲያብሎስ ሁሉ እነሱም ድርጊታቸው በሌሎች ላይ ስለሚያስከትለው ውጤት ብዙውን ጊዜ አይጨነቁም።—ዮሐንስ 8:44፤ 1 ዮሐንስ 5:19
በአሁኑ ወቅት ትዕግሥት እምብዛም የሚገኝ አለመሆኑ አያስደንቅም። ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት፣ የሥርዓቱ አምላክ የሆነው ሰይጣንና የውዳቂው ሥጋችን ኃጢአተኛ ዝንባሌዎች ለማንም ሰው፣ ትዕግሥትን ለማሳየት ከልብ ለሚጥሩትም እንኳ ቢሆን ትዕግሥት ማሳየትን ከባድ ያደርግባቸዋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም በአምላክ ዓላማዎች አፈጻጸም ረገድ “ታገሡ” ሲል ይመክረናል። (ያዕቆብ 5:8) ትዕግሥት ይህን ያህል ከፍተኛ ዋጋ ያለው ለምንድን ነው? ትዕግሥተኛ መሆን ምን ዋጋ እንዲከፈለን ያደርጋል?
ትዕግሥት ይህን ያህል ከፍተኛ ዋጋ ያለው ለምንድን ነው?
“በትዕግሥት ጸንተው የሚጠብቁትም ጭምር ማገልገል ይችላሉ።” እነዚህ ቃላት የተነገሩት እንግሊዛዊው ገጣሚ ጆን ሚልተን “በዓይነ ስውርነቱ” በሚል ርዕስ ከሦስት መቶ ዓመታት በፊት በጻፈው ግጥም ላይ ነበር። ሚልተን በግጥሙ የመጀመሪያ ክፍል ላይ በ40ዎቹ ዓመታት ዕድሜው ውስጥ በመታወሩ ሳቢያ አምላክን ሙሉ በሙሉ ማገልገል ባለመቻሉ የተሰማውን ብስጭትና ጭንቀት ገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ ከላይ በተጠቀሰው የግጥሙ የመጨረሻ መስመር ላይ እንደተንጸባረቀው አንድ ሰው መከራዎችን በትዕግሥት በመቻልና ለማገልገል የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በእርጋታ በመጠበቅ አምላክን ሊያገለግል እንደሚችል ተገነዝቦ ነበር። ሚልተን በትዕግሥት በአምላክ ላይ ትምክህት በመጣል የመጠበቅን አስፈላጊነት ተረድቶ ነበር።
አብዛኞቻችን ጥሩ የማየት ችሎታ ይኖረን ይሆናል፤ ሆኖም ሁላችንም እንድንናደድ ወይም እንድንጨነቅ የሚያደርጉን የአቅም ገደቦች አሉብን። ትዕግሥትን ልንኮተኩት የምንችለው እንዴት ነው? እንዴትስ በተግባር ማሳየት እንችላለን?
የሚያበረታቱ ምሳሌዎች
መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ የትዕግሥት ምሳሌዎችን ይዟል። የይሖዋ ትዕግሥት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ያስችላል። (2 ጴጥሮስ 3:9, 15) ኢየሱስ ቀንበሩን እንድንሸከምና ‘ለነፍሳችን እረፍት እንድናገኝ’ በደግነት ሲጋብዘን የአባቱን አስደናቂ የሆነ ትዕግሥት ፍጹም በሆነ ደረጃ አንጸባርቋል። (ማቴዎስ 11:28–30) ኢየሱስና ይሖዋ ስላሳዩት ትዕግሥት ማሰላሰላችን ይበልጥ ታጋሾች እንድንሆን ሊረዳን ይችላል።
ዮሴፍ ለመናደድ፣ መራራ ጥላቻ ለማሳየት ወይም የበቀል እርምጃ ለመውሰድ በቂ ምክንያት ነበረው። ወንድሞቹ እሱን ለመግደል በማሤርና በመጨረሻም ለባርነት በመሸጥ ክፉኛ በድለውት ነበር። በግብፅ ውስጥ ለጲጥፋራ በትጋትና በታማኝነት ቢያገለግልም እንኳ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ተከሶ ታስሮ ነበር። ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስበት በትዕግሥት ጸና፤ ይህን ያደረገው እንደዚህ ዓይነቶቹ ፈተናዎች የአምላክን ዓላማ ይፈጽማሉ ብሎ ይሆናል። (ዘፍጥረት 45:5) ትሕትናንና ማስተዋልን ጨምሮ ይሖዋን ማመንና ተስፋ ማድረግን አዳብሮ ስለነበር ዮሴፍ በጣም ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ጊዜ እንኳ ትዕግሥትን ለማሳየት ችሏል።
ትዕግሥት ለማሳየት የሚረዳው ሌላው ነገር የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ነው። ለምሳሌ ያህል ቁጡ ከሆንና በአሽሙር መናገር የሚቀናን ከሆነ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ አግኝተን የመንፈስ ፍሬ ማፍራት እንድንችል ልንጸልይ እንችላለን። ትዕግሥትንና ራስን መግዛት በመሳሰሉት በእያንዳንዱ የመንፈስ ፍሬ ላይ ማሰላሰል እነዚህ ባሕርያት ከትዕግሥት ጋር ምን ያህል እንደሚዛመዱ እንድናስተውል ይረዳናል።—ገላትያ 5:22, 23
ትዕግሥት የሚያስገኘው ዋጋ
ትዕግሥተኛ መሆናችን ብዙ ጥቅሞችን ሊያስገኝልን ይችላል። የባሕሪያችንን ጥንካሬ ያሻሽልልናል እንዲሁም በችኮላና በቂልነት አንዳንድ ድርጊቶችን ከመፈጸም ይጠብቀናል። አስቸጋሪ ወይም አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን በጣም በመቸኮላችን ምክንያት ጎጂ የሆኑ ስሕተቶችን ያልፈጸምን ማናችን ነን? አንድ ሸካራ ቃል ተናግረን ወይም አክብሮት የጎደለው ጠባይ አሳይተን ይሆናል። ከምናፈቅረው ሰው ጋር በማይረባ ነገር የተፈጠረው አለመግባባት እልህ ወደ ታከለበት የጦፈ ጭቅጭቅ እንዲለወጥ ፈቅደን ይሆናል። ለረጅም ጊዜያት ከተናደድን፣ ከተበሳጨንና ከተሠቃየን በኋላ ‘ምናለ ትንሽ ብታገሥ ኖሮ’ ብለን ልንጸጸት እንችላለን። ትዕግሥት ማሳየታችን ከማናቸውም ዓይነት ሐዘን ይጠብቀናል። ይህን ማወቃችን ብቻ ሕይወታችንን የበለጠ ሰላም፣ እርጋታና እርካታ የተሞላበት ያደርገዋል።—ፊልጵስዩስ 4:5–7
በተጨማሪም ታጋሾች መሆናችን የተረጋጋና ሰውን የሚያምን ልብ እንዲኖረን ይረዳናል። ይህም የአካል፣ የስሜትና የመንፈስ ጤንነት እንድናገኝ ሊረዳን ይችላል። (ምሳሌ 14:30) ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣና ግልፍተኛነት ከባድ የስሜትና የአካል ሕመም አልፎ ተርፎም ሞት ሊያስከትል ይችላል። በሌላው በኩል ግን ታጋሾች ከሆንን ሌሎችን በተለይም መንፈሳዊ ወንድሞቻንንና ቤተሰባችን ይበልጥ አዎንታዊ በሆነ መልኩ እንመለከታቸዋለን። ትዕግሥተኞች ከሆንን ቶሎ የምንበሳጭና ስሕተት ለቃሚ ከመሆን ይልቅ ይበልጥ አሳቢዎችና ሌሎችን የምንረዳ ወደ መሆን እናዘነብላለን። ሌሎች ሰዎች በበኩላቸውም ከእኛ ጋር መሆን ይበልጥ ቀላልና አስደሳች ይሆንላቸዋል።
በተለይ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች ትዕግሥት ማሳየት ያስፈልጋቸዋል። አንዳንድ ጊዜ መሰል ክርስቲያኖች ከባድ ችግሮች ይዘው ይመጡና ያነጋግሯቸዋል። በአንድ በኩል ሽማግሌዎቹ ራሳቸው በግል ወይም በቤተሰብ ችግሮቻቸው ተዳክመው ወይም ሐሳባቸው ተከፈፍሎ ሊሆን ይችላል፤ በሌላ በኩል ግን እነዚህ ቅን ሰዎች ግራ ተጋብተው፣ አዝነው ወይም ተጨንቀው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ሽማግሌዎች እንደነዚህ ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ትዕግሥት ማሳየታቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው! በዚህ መንገድ “በየዋህነት” ሊያስተምሩና ‘መንጋውን በርኅራኄ’ ሊይዙ ይችላሉ። (2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25፤ ሥራ 20:28, 29) ውድ የሆነው የሰዎች ሕይወት በአደጋ ላይ ነው። ደግ፣ አፍቃሪና ታጋሽ ሽማግሌዎች ለጉባኤው እንዴት ያሉ በረከት ናቸው!
የቤተሰብ ራሶች ቤተሰባቸውን በትዕግሥት፣ ችግራቸውን በመረዳትና በደግነት መያዝ አለባቸው። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባልም ተመሳሳይ ባሕርያትን እንዲያሳይ ሊጠብቁበትና ሊያበረታቱት ይገባል። (ማቴዎስ 7:12) ይህም በቤተሰብ ውስጥ ፍቅርና ሰላም እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ክርስቲያን አገልጋዮች በመስክ አገልግሎት ላይ ሳሉ ትዕግሥት ማሳየታቸው ከዚህ አገልግሎት ሙሉ ደስታ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ማናቸውንም የሚያጋጥማቸውን የግዴለሽነት ስሜትና ተቃውሞ በተሻለ ሁኔታ ጸንተው ለመቋቋም ይችላሉ። ታጋሽ አገልጋዮች የሚያነጋግሯቸው ሰዎች ሲቆጡ ከእነሱ ጋር ከመከራከር ይልቅ ሰላማቸውንና ደስታቸውን ሳያጠፉ በለዘበ ምላስ መልስ ለመስጠት ወይም ዝም ብለው ለመሄድ ይችላሉ። (ማቴዎስ 10:12, 13) ከዚህም በላይ ክርስቲያኖች ሰውን ሁሉ በትዕግሥትና በደግነት ሲይዙ የመንግሥቱ መልእክት በግ መሰል የሆኑ ሰዎችን ይማርካቸዋል። ይሖዋ በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ፍቅር ወደ ተሞላበት የይሖዋ ጉባኤ እንዲጎርፉ በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ በትዕግሥት የተደረገውን ጥረት ባርኮታል።
በእርግጥም ትዕግሥት ማሳየት ዋጋ ያስገኛል። ቸኩለን እርምጃ በመውሰዳችንና አንደበታችን ከመጠን በላይ ከመፍጠኑ የተነሳ ከሚመጡ ከበርካታ ችግሮችና አደጋዎች እንጠበቃለን። ይበልጥ ደስተኞች፣ የተረጋጋንና ጤነኞች ልንሆን እንችላለን። በአገልግሎታችን፣ በጉባኤና በቤታችን ውስጥ የበለጠ ደስታና ሰላም እናገኛለን። ከሁሉ በላይ ግን ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ይኖረናል። ስለዚህ ይሖዋን በትዕግሥት ጠብቁ። ትዕግሥት አሳዩ!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስማቸው ተለውጧል።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በዕለታዊ ኑሮህ ምን ያህል ታጋሽ ነህ?