የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 8/1 ገጽ 20-24
  • ውድ የሆነው መንፈሳዊ ቅርሳችን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ውድ የሆነው መንፈሳዊ ቅርሳችን
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአባቴ የልጅነት ሕይወት
  • ወደ ምሥራቅ አፍሪካ
  • ፍቅር የተሞላበት ክርስቲያናዊ አስተዳደግ
  • እስከመጨረሻው ታማኝ መሆን
  • ወላጆቻችን አምላክን መውደድ አስተምረውናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ብርቅ የሆነ ክርስቲያናዊ ውርስ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • የወላጆቼን ፈለግ መከተል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • አባቴ ወይም እናቴ ታማሚ ቢሆኑስ?
    የወጣቶች ጥያቄ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 8/1 ገጽ 20-24

ውድ የሆነው መንፈሳዊ ቅርሳችን

ፊሊፕ ኤፍ ስሚዝ እንደተናገረው

“በጨለማዋ አፍሪካ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚቀጣጠል ችቦ ተለኩሷል” ከላይ ያሉትን ቃላት በ1992 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 75 ላይ ስናነብ እንዴት ተደስተን ነበር! እነዚህ ቃላት አያቴ ፍራንክ ደብልዩ ስሚዝ በጊዜው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚደንት ለነበረው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ በ1931 በጻፈው ደብዳቤ ላይ ያሰፈራቸው ቃላት ነበሩ። አያቴ ይህንን ደብዳቤ የጻፈው እርሱና ወንድሙ ስላደረጉት የስብከት ጉዞ ሪፖርት ሲያደርግ ነበር።

የ1992 የዓመት መጽሐፍ እንዲህ በማለት አብራርቷል፦ “ሁለት ደፋር አቅኚ አገልጋዮች ማለትም ግሬ ስሚዝና ታላቅ ወንድሙ ፍራንክ ምሥራቹን ለማሰራጨት የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ለመቃኘት ከኬፕ ታውን [ደቡብ አፍሪካ] ተነሥተው በእንግሊዝ ሥር ወደምትገኝ የምሥራቅ አፍሪካ አገር ለመሄድ ተነሱ። ዲ ሶቶ የተባለች መኪናቸውን ወደ ካራቫን (እንደ ቤት የምታገለግል መኪና) ለወጧትና መጽሐፎች ከያዙ 40 ካርቶኖች ጋር መርከብ ላይ ጭነዋት የኬንያ ወደብ ወደሆነችው ሞምባሳ ተጓዙ።”

ከሞምባሳ ተነስተው የኬንያ ዋና ከተማ ወደሆነችው ናይሮቢ ስላደረጉት ጉዞ አያቴ ለወንድም ራዘርፎርድ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እስካሁን ካደረግኋቸው ጉዞዎች ሁሉ በጣም አስፈሪ በሆነ የመኪና ጉዞ ነበር የጀመርነው። 580 ኪሎ ሜትር ለመጨረስ ሙሉ ቀን እየተጓዝን አራት ቀናት ወስዶብን ነበር። . . . ትንሽ እንደተጓዝን መንገዱን ለማስተካከልና የተቦረቦረውን ለመሙላት አካፋ ይዤ ከመኪና መውጣት ነበረብኝ። በተጨማሪም ረግረጋማ ቦታዎች ላይ ስንደርስ የመኪናችን ጎማዎች እንዲቆነጥጡ ለማድረግ ቀርከሃና እንጨት ቆርጠን እንረበርብበት ነበር።”

ፍራንክና ግሬ ናይሮቢ ከደረሱ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻቸውን ለ21 ተከታታይ ቀናት አሰራጩ። “ከሰማነው ነገር ለመደምደም እንደቻልነው ሥራው ሃይማኖታዊቷን የናይሮቢ ከተማ አምሷት ነበር” በማለት አያቴ ጽፏል። በኋላም አያቴ የሁለት ዓመት ልጁ ዶንቨን እና ባለቤቱ ፊሊስ ወደሚኖሩበት አገሩ ለመመለስ ጓጓ። በዚያን ጊዜ ፊሊስ ሁለተኛ ልጃቸውን ማለትም አባታችንን ፍራንክን አርግዛ ነበር። መጀመሪያ በተገኘው መርከብ ከሞምባሳ ተነስቶ መጓዝ ጀመረ፤ ቢሆንም አገሩ ከመድረሱ በፊት በወባ በሽታ ሞተ።

እህቴ፣ ወንድሜና እኔ በዚህ የዓመት መጽሐፍ ላይ ያለውን ታሪክ ስናሰላስል ወደኋላ መለስ ብለን በጣም የምንወደውን አባታችንን እናስታውሳለን። አባታችን የ1992 የዓመት መጽሐፍ ከማግኘታችን ትንሽ ወራት ቀደም ብሎ በተደረገለት የልብ ቀዶ ሕክምና ሳቢያ በተከሰተ የጤና ችግር በ1991 ሞቶ ነበር። ምንም እንኳ አባቱን አይቶት ባያውቅም አባቱ ለይሖዋ ስለነበረው ጥልቅ ፍቅር ይነግረን ነበር። ከ28 ዓመት በኋላ በ1959 ልጁ የእርሱን ኮቴ በመከተል በምሥራቅ አፍሪካ ክርስቲያናዊ አገልግሎት እየፈጸመ እንዳለ ቢያውቅ ኖሮ አያቴ እንዴት ይደሰት ነበር!

የአባቴ የልጅነት ሕይወት

አባታችን አባቱ ከሞተ ከሁለት ወራት በኋላ ኬፕ ታውን ውስጥ ሐምሌ 20, 1931 ተወለደ። አባባ ለይሖዋ ያለውን ፍቅር ያሳየው ከልጅነቱ ጀምሮ ነበር። ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለ የትምህርት ቤት ጓደኞቹ እያሾፉበት ኬፕ ታውን ውስጥ በሚገኘው በዋናው የባቡር ጣቢያ ውስጥ በመቆም ጀርባና ደረት ላይ በሚነገት ማስታወቂያ አማካኝነት የሚደረገውን ምሥክርነት ያከናውን ነበር። በ11 ዓመቱ በውኃ በመጠመቅ ራሱን ለይሖዋ መወሰኑን አሳየ። አባባ አንዳንድ ጊዜ አንዱን ጎዳና በሙሉ በአገልግሎት እንዲሸፍን ብቻውን ይመደብ ነበር። 18 ዓመት ሲሞላው በዕድሜ የገፉ እህቶች ባሉበት ኬፕ ታውን አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ቡድን ውስጥ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ይመራ ነበር።

በ1954 የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በሚቀጥለው ዓመት አውሮፓ ውስጥ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ እንደሚደረግ አስታውቆ ነበር። አባባ ለመሄድ በጣም ቢመኝም ከኬፕ ታውን ተነስቶ ስብሰባው ወደሚደረግበት ሥፍራ ለመጓዝ የሚያስችለው ገንዘብ አልነበረውም። ስለዚህ ሰሜን ሮዴዢያ (የአሁኗ ዛምቢያ) በሚገኘው የመዳብ ማዕድን ማውጫ ውስጥ ሦስት ወር በኬሚስትነት ለመሥራት ተዋዋለ። ድርጅቱ የማዕድን ክምችት እንዳለና እንደሌለ እንዲሁም ክምችቱ ምን ያህል መጠን እንዳለው የሚመረምር ሲሆን የሚገኘው በአፍሪካ ምድረ በዳ ውስጥ ነበር።

አባባ ሰሜን ሮዴዢያ ውስጥ ብዙ ቁጥር ያላቸው አፍሪካውያን የይሖዋ ምሥክሮች እንዳሉ ያውቅ ስለነበር እንደደረሰ ፈልጎ አገኛቸውና የት እንደሚሰበሰቡ አወቀ። ምንም እንኳ የአካባቢውን ቋንቋ መናገር ባይችልም ከእነርሱ ጋር ጊዜውን ያሳልፍና የማይን የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ በቋሚነት ይገኝ ነበር። በማዕድን ማውጫው የሚገኙ አውሮፓውያን የዘር ጥላቻ ስላለባቸው አብዛኛውን ጊዜ አፍሪካውያኑን በመሳደብ ይህንን ጥላቻቸውን ያሳዩ ነበር። አባባ ግን ምንጊዜም ክፉ ቃል ከአፉ አይወጣም ነበር።

በሦስቱ ወራት ማብቂያ ላይ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ አንድ አፍሪካዊ ሠራተኛ ወደ አባባ መጣና “ምን ብለን እንደምንጠራህ ታውቃለህ?” ብሎ ጠየቀው። ሰውዬው ፈገግ አለና “ብዋን [አቶ] መጠበቂያ ግንብ ብለን ነው የምንጠራህ” አለ።

አባባ በ1955 አውሮፓ ውስጥ በተደረገው “ድል አድራጊ መንግሥት” በተባለው ስብሰባ ላይ ለመገኘት ችሎ ነበር። እዚያም በቀጣዩ ዓመት ካገባት ከማሪ ዛሃሪኡ ጋር ተገናኘ። ከተጋቡ በኋላ ዩ ኤስ ኤ ኦሃዮ ውስጥ በምትገኘው ፓርማ ከተማ መኖር ጀመሩ።

ወደ ምሥራቅ አፍሪካ

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የምሥራቹ አገልጋይ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደው እንዲያገለግሉ ለስብሰባው ተካፋዮች ጥሪ ቀረበላቸው። ወላጆቻችን ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ለመሄድ ወሰኑ። ሁሉንም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ባቀረበላቸው ሐሳብ መሠረት አደረጉ። በዚያ ክልል ሥራ ማግኘት የሚችሉት የሥራ ፈቃድ ያላቸው ብቻ ስለሆኑ ምናልባት አባባ ሥራ ላያገኝ ስለሚችል የደርሶ መልስ ትኬት ለመቁረጥ የሚያስችላቸውን ገንዘብ አጠራቀሙ።

አባባና እማማ ፓስፖርትና ቪዛ ካገኙና ከተከተቡ በኋላ ሐምሌ 1959 በመንግሥት የንግድ መርከብ ተሳፍረው ከኒው ዮርክ ተነሱና በኬፕ ታውን በኩል አድርገው ወደ ሞምባሳ ተጓዙ። ጉዞው አራት ሳምንታት ወሰደባቸው። ሞምባሳ ሲደርሱ የምሥራቹ አገልጋይ ይበልጥ በሚያስፈልግበት ቦታ ለማገልገል ከእነርሱ ቀድመው የመጡ ክርስቲያን ወንድሞች ወደ መርከብ ማቆሚያው ድረስ መጥተው ሞቅ ባለ የወዳጅነት ስሜት ተቀበሏቸው። ናይሮቢ ሲደርሱ አባባ እርሱን ሲጠብቅ የነበረ ደብዳቤ አገኘ። ደብዳቤው ኡጋንዳ ውስጥ ኢንቴቤ ከተማ በሚገኘው ጂኦሎጂያዊ ምርምር ክፍል ውስጥ በኬሚስትነት ለመሥራት ላቀረበው ጥያቄ መልስ ነበር። አባባና እማማ ወደ ኡጋንዳ ካምፓላ በሚሄድ ባቡር ተሳፍረው ወደዚያው ሄዱ፤ እዚያም አባባ ቃለ መጠይቅ ተደረገለትና ተቀጠረ። በዚያን ጊዜ ከኢንቴቤ እስከ ካምፓላ ባለው አካባቢ የነበረው ሌላ የይሖዋ ምሥክር ወንድም ጆርጅ ካዱ ብቻ ነበር።

ቅኝ ገዥው መንግሥት አባባ ሉጋንዳ የተባለውን የአካባቢውን ቋንቋ እንዲማር ከፈለለት። በአገልግሎቱ ይበልጥ ውጤታማ መሆን ይችል ዘንድ ቋንቋውን እንደምንም ብሎ የመማር እቅድ ስለነበረው በጣም ተደሰተ። እንዲያውም አባባ ከጊዜ በኋላ “የመንግሥት ምሥራች” የተባለውን ቡክሌት ወደ ሉጋንዳ ቋንቋ በመተርጎም እርዳታ አበርክቷል።

አባባ ለሌሎች በመመሥከር በኩል ደፋር ነበር። በሚሠራበት ክፍል ውስጥ ለሚገኙ አውሮፓውያን በጠቅላላ ምሥክርነቱን ይነግራቸው የነበረ ሲሆን ለኡጋንዳውያንም ያለማሰለስ ይሰብክላቸው ነበር። እንዲያውም ለአፍሪካዊው የኡጋንዳ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሥክሮላቸዋል። ሰውዬው የመንግሥቱን መልእክት በማዳመጥ ብቻ ሳይወሰኑ አባባንና እማማን እራት ጋበዟቸው።

እህቴ አንቴ በ1960 ስትወለድ እኔ ደግሞ በ1965 ተወለድኩ። ቤተሰባችን በዋና ከተማው ካምፓላ ውስጥ ባለው አነስተኛ፣ ነገር ግን ታዳጊ በሆነው ጉባኤ ውስጥ ከሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ጋር በጣም ተቀራርቦ ነበር። በኢንቴቤ አቅራቢያ የምንኖር ነጭ የይሖዋ ምሥክሮች እኛ ብቻ ስለሆንን የሚያስደስቱ ገጠመኞች ነበሩን። አንድ ጊዜ የአባባ ጓደኛ ባጋጣሚ ወደ ኢንቴቤ ጎራ ብሎ ስለነበር አባባን ለማግኘት ሞከረ። “እዚህ አካባቢ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ አውሮፓውያን ባልና ሚስት ታውቃላችሁ?” ብሎ እስከጠየቀበት ጊዜ ድረስ ፍለጋው አልተሳካለትም ነበር። እንዲህ ብሎ ሲጠይቅ ሰውዬው በቀጥታ ወደ እማማና አባባ ቤት ወሰደው።

ሁለት የታጠቁ ዓማፂያን ባሉበት ቦታ ጸንቶ መኖርን ጨምሮ ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችንም ቀምሰናል። አንድ ሰሞን የመንግሥት ወታደሮች የአንድ የተወሰነ ጎሣ አባል የሆነ ማንኛውንም ሰው ይገድሉ ነበር። ቀንና ሌሊት የማያቋርጥ የተኩስ እሩምታ ነበር። ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት ድረስ ሰዓት እላፊ ስለነበር ስብሰባዎቹ የሚደረጉት ከሰዓት በኋላ ባለው ጊዜ ኢንቴቤ በነበረው የወላጆቼ ቤት ውስጥ ነበር።

የሰዓት እላፊው ገደብ ከተነሳ በኋላ አባባ ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወደ ካምፓላ በመኪና ሲወስደን አንድ ወታደር ጠመንጃ ደግኖብን መኪናችንን ካስቆመ በኋላ ወዴት እንደምንሄድ ጠየቀን። በዚያን ጊዜ እኔ ገና ሕፃን የነበርኩ ሲሆን አንቴ ደግሞ አምስት ዓመቷ ነበር። አባባ መጽሐፍ ቅዱሳችንንና ጽሑፎቻችንን በማሳየት በእርጋታ ሲያስረዳው ለቀቀን።

በኡጋንዳ ስምንት የሚያክሉ ዓመታት ካሳለፍን በኋላ በ1967 ወላጆቻችን በጤና ችግሮችና በቤተሰብ ኃላፊነቶች የተነሳ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመመለስ ወሰኑ። አባባ በሽማግሌነት ባገለገለበት ኦሃዮ የሚገኘው የካንፊልድ ጉባኤ አባል ሆንን። ወላጆቼ በካንፊልድ ላሉ ወንድሞች ካምፓላ ውስጥ በምትገኘው ትንሿ ጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ ወንድሞች የነበራቸው ዓይነት ከፍተኛ ፍቅር እያደረባቸው መጣ።

ፍቅር የተሞላበት ክርስቲያናዊ አስተዳደግ

በ1971 ወንድሜ ዴቪድ ተወለደ። ያደግነው በፍቅርና በወዳጃዊነት ስሜት በተሞላ ቤት ውስጥ ነበር። ይህ የመነጨው ወላጆቻችን እርስ በርሳቸው ከነበራቸው ፍቅር የተሞላበት ግንኙነት እንደሆነ አያጠራጥርም።

ልጆች ሳለን አባባ ሁልጊዜ ልንተኛ ስንል የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ያነብልንና ከጸለየ በኋላ እማማ ሳታውቅ በሚያብለጨልጭ ወርቃማ ወረቀት የተጠቀለለ ቸኮላታ ይሰጠን ነበር። የትም ቦታ ብንሆን ሁልጊዜ አንድ ላይ ሆነን መጠበቂያ ግንብ መጽሔታችንን እናጠና ነበር። ቤተሰባችን ሽርሽር ላይ ሳለ አንድ ጊዜ በአንድ ተራራ ጥግ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ባሕሩን ፊት ለፊታችን እየተመለከትን መጠበቂያ ግንብ አጥንተናል። እነዚህ ጊዜያት ከሚያስታውሳቸው አስደሳች ነገሮች መካከል አንዱ መሆናቸውን አባባ ደጋግሞ ይናገር ነበር። አባባ የቤተሰብ ጥናት የሚያመጣውን ታላቅ ደስታ ላልቀመሱ ሰዎች እንደሚያዝን ይናገራል።

ለይሖዋ ፍቅር በማሳየት በኩል አባባ ምሳሌ በመሆን ያስተምረን ነበር። አዲስ መጠበቂያ ግንብ ወይም ንቁ! መጽሔት በመጣ ቁጥር ወይም በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተዘጋጀ አዲስ ጽሑፍ ስናገኝ አባባ ሙሉ በሙሉ በጉጉት አንብቦ ይጨርሰዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አቅልለን ከመመልከት ይልቅ እንደ ውድ ሀብት አድርገን ማክበር እንዳለብን ከእርሱ ተምረናል። ካሉን ውድ ንብረቶች መካከል አንዱ የአባባ ባለ ማጣቀሻ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እያንዳንዱ ገጽ ማለት ይቻላል ሲያጠና በቃረማቸው ማስታወሻዎች ሙሉ ለሙሉ የተሸፈነ ነው። በሕዳጉ ላይ የጻፋቸውን ማብራሪያዎች ስናነብ ዛሬም ቢሆን ትምህርቱንና ምክሩን እንደምንሰማ ያህል ነው።

እስከመጨረሻው ታማኝ መሆን

ግንቦት 16, 1991 አገልግሎት ላይ ሳለ አባባ የልብ ድካም ተነሳበት። ከሳምንታት በኋላ የተሳካ የመሰለ የልብ ቀዶ ሕክምና ተደረገለት። ቢሆንም ቀዶ ሕክምና በተደረገለት ማግሥት ማታ ላይ ከሆስፒታል ስልክ ተደወለልን። አባባ ደም ይፈሰው ነበር፤ ዶክተሮቹም በጣም ተጨንቀዋል። ደሙን ለማቆም የዚያን ዕለት ማታ በድጋሚ ቀዶ ሕክምና ቢደረግለትም ሙከራው ከንቱ ነበር። የአባባ ደም መፍሰሱን አላቆመም ነበር።

በሚቀጥለው ቀን የአባባ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ እየሆነ ስለመጣ አባባ ደም መውሰድ እንዳለበት ለማሳመን መጀመሪያ እናቴን ከዚያም ታናሽ ወንድሜን ዶክተሮች በግል አነጋገሯቸው። ቢሆንም የፈለገው ነገር ቢመጣ ደም እንደማይወስድ አባባ ቀድሞውኑ ለዶክተሮቹ ነግሯቸው ነበር። ደም የማይወስድበትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች አስረድቷቸውና ያለደም የሚሰጡ አማራጭ ሕክምናዎችን ግን እንደሚቀበል ነግሯቸው ነበር።—ዘሌዋውያን 17:13, 14፤ ሥራ 15:28, 29

አብዛኞቹ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ያላቸው የከረረ ጥላቻ በአይ ሲ ዩ (በጠና ለታመሙ ሰዎች ልዩ እንክብካቤ የሚሰጥበት ክፍል) ውስጥ ኃይለኛ ውጥረት ፈጠረ። ይህም ከአባባ አሳሳቢ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ በጊዜው ከአቅማችን በላይ ይመስል ነበር። ይሖዋ እንዲረዳን ወደ እርሱ እንጸልይ የነበረ ሲሆን ያገኘናቸውንም ሊሠሩ የሚችሉ ምክሮች በተግባር ለማዋል ጥረት እናደርግ ነበር። ስለዚህ ወደ አይ ሲ ዩ ስንሄድ ሁልጊዜ በጥሩ ሁኔታ እንለብስና ለሕክምና ክፍሉ አባላት አክብሮት እናሳይ ነበር። አግባብ ያላቸው ጥያቄዎች በማቅረብ የአባባን ሁኔታ በቅርብ ከመከታተላችንም በተጨማሪ አባባን በመንከባከብ ረገድ እጃቸው ላለበት ለእያንዳንዱ ሠራተኞች ምስጋናችንን እንገልጽ ነበር።

የሆስፒታሉ ሠራተኞች የምናደርጋቸውን ጥረቶች ልብ ሳይሉ አላለፉም። በጥቂት ቀናት ውስጥ ውጥረቱ ወደ ደግነት ተለወጠ። አባባን ይንከባከቡት የነበሩ ነርሶች ምንም እንኳ እርዳታ እንዲሰጡት ባይመደቡም የሚያደርገውን ለውጥ መከታተላቸውን ቀጥለው ነበር። አንድ ዶክተር መጀመሪያ ላይ ለእኛ ምንም አክብሮት ያልነበረው ቢሆንም በኋላ ለስልሶ ነበር፤ እንዲያውም እናቴ እንዴት እንደምትተዳደር ይጠይቃት ነበር። ጉባኤያችንና ዘመዶቻችንም ፍቅራዊ ድጋፍ አድርገውልናል። ምግብና አጽናኝ የሆኑ አያሌ የመልካም ምኞት መግለጫ ካርዶችን ከመላካቸውም በተጨማሪ ይጸልዩልን ነበር።

የሚያሳዝነው ግን ሕክምናው በፍጹም አባባን አላሻለውም። መጀመሪያ ከተደረገለት ቀዶ ሕክምና በኋላ አሥር ቀናት ያህል ቆይቶ ሞተ። በአባባ ሞት በጥልቅ አዘንን። አንዳንድ ጊዜ መሪር ሐዘን ይሰማን ነበር። ደግነቱ አምላካችን ‘ሸክማችንን በየቀኑ እንደሚሸከምልን’ ቃል ስለገባልን ከዚህ በፊት ባላደረግነው መጠን በእርሱ ላይ መደገፍን ለምደን ነበር።—መዝሙር 68:19 አዓት

ወደፊት በአዲሱ ዓለም ውስጥ አባባን አግኝተን ለመደሰት ሁላችንም ይሖዋን በታማኝነት እያገለገልን ለመቀጠል ወስነናል።—ማርቆስ 5:41, 42፤ ዮሐንስ 5:28፤ ሥራ 24:15

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍራንክ ስሚዝ ኬፕ ታውን ውስጥ ከእናቱ ፊሊስ ጋር ሆኖ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አባባና እማማ ሲጋቡ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢንቴቤ ውስጥ የመጀመሪያውን የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ለማከናወን ወንድሞች የአንድ አፍሪካዊ ባለሥልጣን መዋኛ ተከራይተው ነበር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባሕላዊ ሰላምታ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አባባና እማማ እርሱ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ