በኢየሱስ ላይ የተነሱት ጥርጣሬዎች ምክንያታዊ ናቸውን?
የናዝሬቱ ኢየሱስ በእርግጥ ተአምራት ፈጽሟልን? የእርሱ ደቀ መዛሙርት እንዳወጁት ከሞት ተነስቷልን? ጭራሹንስ በሕይወት ኖሯልን? ባለንበት ትውልድ ብዙ ሰዎች እንደነዚህ የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በሙሉ ልብ መመለስ የተሳናቸው ይመስላል። ለምን? ምክንያቱም በኢየሱስ ላይ አንዳንድ ጥርጣሬዎች ስላደሩባቸው ነው፤ ጥርጣሬ ደግሞ እርግጠኛ ያለመሆን ስሜት፣ አንድ ነገር እውነት ወይም የሚቻል መሆኑንና አለመሆኑን አለማወቅ ነው። ነገር ግን ኢየሱስን በተመለከተ የሚነሱ የጥርጣሬ ስሜቶች ተገቢ ናቸውን? እስቲ እንመልከት።
በኢየሱስ ላይ የተነሱት ጥርጣሬዎች የተዘሩበት መንገድ
በ19ኛው መቶ ዘመን ማብቂያና በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ የጀርመን የሃይማኖት ምሁራን ኢየሱስ “የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የሐሳብ ፈጠራ ሰው” እንደሆነ አድርገው ገልጸውታል። በኢየሱስ እውነተኝነት ላይ ያስነሱት ጥያቄ በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በምሁራን መካከል ወደተነሳው ውዝግብ አምርቷል፤ ይህ ውዝግብ በዚያን ጊዜ ወደ ተራው ሕዝብ የደረሰ ሲሆን እስካሁን ድረስ ተጽእኖ አሳድሯል። ለምሳሌ በቅርቡ በጀርመን የተደረገ አንድ ጥናት ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል 3 በመቶ የሚሆኑት ኢየሱስ “ጭራሽ በሕይወት ያልኖረ” ከመሆኑም በተጨማሪ “ሐዋርያት የፈጠሩት ነው” ብለው እንደሚያምኑ አሳይቷል። አዎን፣ ኢየሱስን በተመለከተ ባለንበት መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የተዘሩት የጥርጣሬ ዘሮች አሁንም እንኳ ተቀባይ ልብ አግኝተዋል።
ኢየሱስ “ፈጠራ” ነበር የሚለው መደምደሚያ ምክንያታዊ ያልሆነው ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ቮልፍጋን ትሪሊንግ እንዲህ ብለዋል፦ “ኢየሱስ በሕይወት ኖሯል ወይስ አልኖረም በሚል የተነሳው ውዝግብ ወይም እውነተኛ ሰው ነበር ወይስ ተረት የሚለው ንትርክ ተደምድሟል። ጥያቄው ምሁራዊ መልስ አግኝቷል፤ እንዲህ ያለው መልስ ቢያንስ ለነገሩ ክብደት የሚሰጡ ሰዎች ችግሩን አወዛጋቢ እንደሆነ አድርገው እንዳይመለከቱ ያደርጋቸዋል።” ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን አንዳንዶች አሁንም ይጠራጠራሉ። ስለዚህ አንድ ሰው የኢየሱስን እውነተኝነት ማረጋገጥም ሆነ በእርሱ ላይ የተነሱትን ሌሎች ጥርጣሬዎች ማስወገድ የሚችልበትን መንገድ ቀረብ ብለን እንመርምር።
ጥርጣሬዎችን የሚያስወግዱ ማስረጃዎች
ኢየሱስ እንደ አንድ ተራ ወንጀለኛ ሆኖ በአሳፋሪ ሁኔታ መገደሉ “የኢየሱስን እውነተኝነት ለሚቃወሙ ሰዎች የሚሆን ከሁሉ የበለጠ አሳማኝ ማስረጃ” ነው በማለት ትሪልንግ ገልጸዋል። ለምን? ምክንያቱም ግድያው “አዲሱ እምነት በአይሁዳውያንና አይሁዳውያን ባልሆኑ ሰዎቸ መካከል እንዳይስፋፋ ከማገድ አልፎ እንቅፋት ሆኖ ነበር።” (ከ1 ቆሮንቶስ 1:23 ጋር አወዳድር።) የመሲሑ የኢየሱስ ሞት ለአይሁዳውያንም ሆነ ለአሕዛብ ውርደት ከሆነ የሐዋርያት ፈጠራ ሊሆን አይችልም! በተጨማሪም የኢየሱስ ሞት ታሪካዊ ክንውን እንደሆነ የተረጋገጠው በአራቱ ወንጌሎች ብቻ ሳይሆን ሮማዊው ጸሐፊ ታሲተስና የአይሁዱ ታልሙድ ይህንኑ ያረጋግጣሉ።a
በኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት ወቅት የተፈጸሙ ሌሎች ክንውኖችም ስለ እርሱ ከሚናገሩት ነገር አንፃር የወንጌሎችን ተኣማኒነት የሚያረጋግጡ የውስጥ ማስረጃዎች እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። ለምሳሌ የኢየሱስ ተከታዮች አነስተኛ ከተማ ከሆነችው ከናዝሬት እንደሚመጣ ፈጥረው ያወሩ ነበርን? ወይስ ታማኙ ጓደኛቸው አሳልፎ እንደሚሰጠው ከራሳቸው አመንጭተው ይናገራሉን? ደቀ መዛሙርቱ በፍርሃት ትተውት እንደሸሹ የሚናገር የራሳቸውን ታሪክ ፈጠሩ ብሎ ማሰቡ ትክክል ይመስላልን? ደቀ መዛሙርቱ ፈጽሞ ያልሆኑ የፈጠራ ታሪኮችን በዝርዝር ካዘጋጁ በኋላ እነዚህን ታሪኮች በመላው ዓለም አውጀዋል ማለቱ በእርግጥም ስሜት የማይሰጥ ነው! ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ የተጠቀመበት የማስተማር ጥበብ በልዩ ስልቱ ተለይቶ የሚታወቅ ነበር። የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁዳውያን ሥነ ጽሑፍ ኢየሱስ ከተጠቀመባቸው ምሳሌዎች ጋር ትንሽ እንኳን የሚቀራረቡ ምሳሌዎችን አልያዘም። እንደ ተራራው ስብከት የመሳሰሉ ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን “ፈጥሮ” ማንነቱን የሚደብቅ ሰው ማን ነው? እነዚህ ሐሳቦች በጠቅላላ ስለ ኢየሱስ ሕይወት የዘገቡት ወንጌሎች እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ናቸው።
ኢየሱስ በሕይወት የኖረ ሰው እንደነበረ የሚያረጋግጥ የውጪ ማስረጃም አለ። አራቱ ወንጌሎች ቁልጭ ያለ ማለትም በትክክል የተዘረዘረ ታሪክ እንዳለው አድርገው ገልጸውታል። እንደ ቤተ ልሔምና ገሊላ የመሳሰሉት ሥፍራዎች፣ እንደ ጴንጤናዊው ጲላጦስና ፈሪሳውያን የመሳሰሉ ታዋቂ ግለሰቦችና ቡድኖች፣ እንዲሁም የአይሁዳውያን ልማዶችና ሌሎች ልዩ የሚያደርጓቸው ነገሮች ፈጠራዎች አልነበሩም። የመጀመሪያው መቶ ዘመን የሕይወት ገጽታ አንዱ ክፍል ከመሆናቸውም በላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ምንጮችና አርኪዮሎጂያዊ ግኝቶች የተረጋገጡ ናቸው።
በዚህ መሠረት ኢየሱስ በሕይወት የኖረ ሰው ስለመሆኑ አሳማኝ የሆነ የውስጥም ሆነ የውጭ ማስረጃ አለ።
ነገር ግን ብዙ ሰዎች ኢየሱስ በሕይወት የኖረ ሰው እንደሆነ ባይጠራጠሩም እንኳ ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተዓምራት ይጠራጠራሉ። ከላይ በተጠቀሰው ጥናት መሠረት ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተአምራትና ትንሣኤው “እንደተፈጸሙ” በጽኑ የሚያምኑ አዘውትረው ቤተ ክርስቲያን የሚሳለሙ ጀርመናውያን ቁጥር ጥቂት ነው። በኢየሱስ ተአምራትና ትንሣኤ ላይ የተነሱት ጥርጣሬዎች ትክክል ናቸውን?
አንዳንዶች የኢየሱስን ተአምራት የሚጠራጠሩበት ምክንያት
ማቴዎስ 9:18–36 ኢየሱስ በተአምር በሽተኞችን እንደፈወሰ፣ ሙታንን እንዳስነሳና አጋንንትን እንዳወጣ ይተርካል። ታሪክ ጸሐፊው ፕሮፌሰር ሁጎ ስታውዲንገር “እነዚህ አስደናቂ ዘገባዎች የሐሳብ ፈጠራ መሆናቸው ግልጽ ነው የሚለው ነገር በአጭር አገላለጽ የማይታመንና ከታሪክ አንጻር ሲታይ ደግሞ የማያስኬድ ነው” በማለት ተናግረዋል። ለምን? ምክንያቱም የጥንቶቹ ወንጌሎች የተጻፉት አብዛኞቹ የእነዚህ ተአምራት የዓይን ምሥክሮች ገና በሕይወት ሳሉ ነው! አይሁዳዊ ተቃዋሚዎች “ኢየሱስ አስደናቂ ተአምራት እንዳከናወነ ፈጽሞ አላስተባበሉም” በማለት ስታውዲንገር የተናገሩት ነገር ሌላው ማረጋገጫ ነው። ሌሎቹን ማረጋገጫዎች በጠቅላላ ትተን በዚህ የውጪ ማስረጃ ላይ ብቻ ተመሥርተን ብንወስን እንኳ የኢየሱስ ተአምራት ያለምንም ጥርጥር እምነት ልንጥልባቸው እንደሚገባ እናውቃለን።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
ምንም እንኳ “አብዛኞቹ ጀርመናውያን ኢየሱስ በሽተኞችን እንደፈወሰ ቢያምኑም” ብዙዎቹ ከእነዚህ ፈውሶች ጀርባ ስላለው ኃይል ይጠራጠራሉ። ለምሳሌ የኢየሱስ ተአምራት የተፈጸሙት የመንፈስ ጭንቀት ተጠናውቷቸው በነበሩ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድር አፍዝ አደንግዝ አማካኝነት እንደሆነ አንድ ታዋቂ የጀርመን የሃይማኖት ምሁር በአደባባይ ተናግረዋል። ይህ ምክንያታዊ መግለጫ ነውን?
እስቲ የሚከተሉትን ምሳሌዎች ተመልከት። ማርቆስ 3:3–5 ኢየሱስ የአንድን ሰውዬ የሰለለ እጅ እንደፈወሰ ይተርካል። ነገር ግን የሰለለ እጅ የመንፈስ ጭንቀት ውጤት ነውን? በፍጹም አይደለም። በዚህ ምክንያት ይህ ፈውስ የአፍዝ አደንግዝ ውጤት ነው ሊባል አይቻልም። ታዲያ ኢየሱስ ተአምራት ለመፈጸም ያስቻለው ምን ነበር? ፕሮፌሰር ስታውዲንገር እንዲህ በማለት አስታውቀዋል፦ “ኢየሱስ ይህንን ያደረገው በአፍዝ አደንግዝ ኃይል ነው የሚለውን አባባል የሚደግፉ ሕጎች እስከሌሉና አንድ ሰው አምላክን እስካልካደ ድረስ ከሰዎች የላቀ ኃይል ያለው አምላክ አስገራሚ ተአምራትን አይፈጽምም ብሎ ሊናገር አይችልም።” አዎን፣ ኢየሱስ ‘በአምላክ ኃይል’ በመታገዝ በሽተኛ የነበሩ ሰዎችን ቃል በቃል ፈውሷል። ስለዚህ የእርሱን ተአምራት የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለም።—ሉቃስ 9:43 አዓት፤ ማቴዎስ 12:28
ከተአምራት ሁሉ የሚልቀው ተአምር ማለትም የኢየሱስ ትንሣኤ ተፈጽሞ ከሆነ በወንጌል ውስጥ የተዘገቡት ሌሎች ተአምራቶችም በሙሉ “ተፈጽመው ሊሆን ይችላል” በማለት ዘ አሜሪካን ፒፕልስ ኢንሳይክሎፔድያ ተናግሯል። ኢየሱስ በእርግጥ ከሞት ተነስቶ ነበርን?
በኢየሱስ ትንሣኤ ላይ የተነሱት ጥርጣሬዎች ትክክል ናቸውን?
በመጀመሪያ የኢየሱስን ትንሣኤ እውነተኝነት ከሚደግፉ ጠንካራ የሆኑ ዝርዝር ማስረጃዎች መካከል አንዱን ተመልከት። ይህም መቃብሩ ባዶውን መገኘቱ ነው። የኢየሱስ መቃብር ባዶውን ተገኝቷል የሚለውን ሐቅ በጊዜው የነበሩ ሰዎች እንዲያውም የእርሱ ተቃዋሚች እንኳ አልተጠራጠሩትም ነበር። (ማቴዎስ 28:11–15) ማጭበርበሪያ ቢሆን ኖሮ በቀላሉ ይጋለጥ ነበር! “‘ተነሥቶአልና በዚህ የለም’ ከሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መግለጫ በስተቀር ባዶ ስለተገኘው መቃብር ይህ ነው የሚባል ማብራሪያ አልተሰጠም (ማቴ. 28:6)” በማለት ከላይ የተጠቀሰው ጽሑፍ ትክክለኛ መደምደሚያ ሰጥቷል።
ኢየሱስ ከሞት የተነሣው መሲሕ እንደሆነ በየቦታው ያወጁት የራሱ ደቀ መዛሙርት ብቻ ናቸው በማለት አንዳንዶች ተቃውሞ ያሰማሉ። ይህ እውነት ነው። ቢሆንም የመልእክታቸው ተኣማኒነት በጽኑ የተመሠረተው በተለይ ስለ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በሚናገረው ታሪካዊ ሐቅ ላይ አልነበረምን? በእርግጥ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ ደግሞም፦ ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለመሰከርን፣ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል” ብሎ መጻፉ የሁለቱን ግንኙነት ተገንዝቦ እንደነበረ ያሳያል።—1 ቆሮንቶስ 15:14, 15፤ ከዮሐንስ 19:35፤ 21:24 እና ከዕብራውያን 2:3 ጋር አወዳድር።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማንነታቸው በሰፊው የታወቀና ኢየሱስ ከሞቱ በኋላ እንደገና እንደታየ ሊመሠክሩ የሚችሉ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ከእነዚህም መካከል 12ቱ ሐዋርያትና ጳውሎስ እንዲሁም 500 ሌሎች የዓይን ምሥክሮች ይገኙበታል።b (1 ቆሮንቶስ 15:6) በተጨማሪም ታማኝ ባልሆነው ሐዋርያ በይሁዳ ፋንታ ማትያስ የተሾመው የትኛውን ብቃት አሟልቶ እንደሆነ አስታውስ። ሥራ 1:21–23 ማትያስ የኢየሱስ ትንሣኤና ከእርሱ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የተፈጸሙ ጥንታዊ ክንውኖች የዓይን ምሥክር እንደሆነ ይናገራል። የኢየሱስ ሕይወትና ትንሣኤ እውነት ሳይሆን ልብ ወለድ ቢሆን ኖሮ ለሹመቱ የቀረበው እንዲህ ዓይነቱ መስፈርት ሙሉ በሙሉ ትርጉም የለሽ ይሆን ነበር።
አያሌ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የዓይን ምሥክሮች የኢየሱስ ሕይወት፣ ተአምራት፣ ሞትና ትንሣኤ እውነት እንደሆነ ማረጋገጥ ስለሚችሉ ከላይ የተጠቀሱት መሰናክሎች ቢኖሩም እንኳ ከሌሎች አንጻር ሲታይ ክርስትና በመላው የሮማ ግዛት በፍጥነት ተሰራጭቶ ነበር። ተከታዮቹ ትንሣኤውንና ትንሣኤው ያስገኘውን መሠረታዊ እውነት በሁሉም ስፍራ ለማወጅ የሚደርስባቸውን መከራ፣ ስደትና ሌላው ቀርቶ ሞት እንኳ በጸጋ ለመቀበል ፈቃደኞች ነበሩ። የትኛውን እውነት? ኢየሱስ ከሞት ሊነሳ የቻለው በአምላክ ኃይል ብቻ እንደሆነ የሚናገረው እውነት ነው። ይሖዋ አምላክ ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው ለምን ነበር? ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ በምድር ላይ በሕይወት የኖረው ኢየሱስ ማን እንደሆነ ያሳያል።
ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ ዕለት በጣም ተገርመው ለነበሩት በኢየሩሳሌም የሚኖሩ አይሁዶች እንዲህ በማለት በግልጽ ተናግሯል፦ “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፣ ነገር ግን እርሱ፦ ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግር መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ። እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።” (ሥራ 2:32–36) አዎን፣ ይሖዋ አምላክ የናዝሬቱ ኢየሱስን “ጌታም ክርስቶስም” አድርጎታል። ኢየሱስ በዚህ የአምላክ ዓላማ ውስጥ ያለውን ሚና በተመለከተ የተነሱት ጥርጣሬዎች ትክክል ናቸውን?
ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ የሚጫወተውን ሚና መጠራጠር የሌለብን ለምንድን ነው?
የኢየሱስን ማንነትና ሚና በተመለከተ የተነሱ ጥርጣሬዎች እንዴት ሙሉ በሙሉ ሊወገዱ ይችላሉ? እውነተኛ ነቢይ እንደነበረ በሚናገረው እውነት አማካኝነት ነው። በዛሬው ጊዜ የምንመለከታቸው ጦርነቶች፣ ረሀብ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ወንጀልና የፍቅር መቀዝቀዝ እንደሚከሰቱ አስቀድሞ ተናግሯል። በተጨማሪም “ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ተንብዮአል። (ማቴዎስ 24:3–14) እነዚህ ትንቢቶች መፈጸማቸው ኢየሱስ ከሞት የተነሳው ክርስቶስ እንደሆነ፣ በማይታይ ሁኔታ ‘በጠላቶቹ መካከል’ እየገዛ እንዳለና በቅርቡ የአምላክን አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ያረጋግጣሉ።—መዝሙር 110:1, 2፤ ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 21:1–5
የሰው ዘር ከመቼውም ጊዜ ይልቅ መለኮታዊ ጥበብ ያለው አዳኝ ባስቸኳይ ያስፈልገዋል። ኢየሱስ የሰውን ዘር ለማዳን የተመረጠ መሆኑን መጠራጠር የሌለብን ለምንድን ነው? አስደናቂዎቹን ተአምራትና የኢየሱስን ትንሣኤ በዓይኑ የተመለከተው ዮሐንስ እንዲህ ብሎአል፦ “እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን።” (1 ዮሐንስ 4:14፤ ከዮሐንስ 4:42 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ በሕይወት መኖሩን፣ ተአምራት ማድረጉን፣ መሞቱንና መነሣቱን የምንጠራጠርበት ተጨባጭ ምክንያት እንደሌለን ሁሉ ይሖዋ አምላክ ሕጋዊ ንጉሥ አድርጎ በቀኙ በማስቀመጥ እንዳነገሠውም የምንጠራጠርበት ምክንያት የለም። ያለ ምንም ጥርጥር የናዝሬቱ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥና “የዓለም መድኃኒት” ነው።—ማቴዎስ 6:10
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በታልሙድ ውስጥ ስለ ኢየሱስ የተሰጡትን ተቃራኒ መግለጫዎች እውነተኛ እንደሆኑ አድርገው የተቀበሏቸው አንዳንድ ምሁራን ብቻ ናቸው። በሌላ በኩል ታሲተስ ሱቶኒዩስ፣ ወጣቱ ፕሊኒ ያቀረቡትና ሌላው ቀርቶ ፍላቪየስ ጆሴፈስ የሰጠው አንድ መግለጫ ኢየሱስ በታሪክ የኖረ ሰው መሆኑን እንደሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ተደርገው በጥቅሉ ተቀባይነት አግኝተዋል።
b ከሞት የተነሳው ኢየሱስ አንድ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ዓሣ በልቷል፤ ይህም በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች እንደሚሉት በራእይ እንዳልተገለጠላቸው ያረጋግጣል።—ሉቃስ 24:36–43