የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 9/15 ገጽ 5-6
  • ቅናት ሕይወቴን ሊያሳጣኝ ነበር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ቅናት ሕይወቴን ሊያሳጣኝ ነበር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ፍቅር ተገቢ ያልሆነ ቅናትን ድል ያደርጋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መቅናት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ቅናትን በተመለከተ ማወቅ ያለብህ ነገር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ቅናት ትዳራችሁን እንዳይበጠብጠው ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
    ለቤተሰብ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 9/15 ገጽ 5-6

ቅናት ሕይወቴን ሊያሳጣኝ ነበር

ቅናት ክፉኛ ሊያጠቃኝ የጀመረው ሁለተኛውን ባሌን ማርክን ባገባሁበት ወቅት ነበር።a በጋራ ሆነን በርከት ያሉ የእንጀራ ልጆችን መርዳት የነበረብን ሲሆን ከቀድሞዎቹ የትዳር ጓደኞቻችን ጋር በአንዳንድ ሁኔታዎች እንገናኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታው ከአቅም በላይ ይሆናል። የቤተሰብ ግጭት ሲፈጠር ማርክ ከእኔ ጎን የሚቆም አይመስልም። አሁንም ቢሆን የቀድሞ ሚስቱን እንደሚወዳት ይሰማኝ ጀመር። ቅናቴን ከመቆጣጠር ይልቅ መላ ሕይወቴን እንዲቆጣጠረው ፈቀድኩለት። የማርክ የቀድሞ ሚስት አጠገቤ ስትሆን እረበሽ ነበር።

ማርክን ያለማቋረጥ እመለከተው ነበር፤ ሌላው ቀርቶ ዓይኑ የት እንዳረፈ እንኳ ሳይቀር እከታተል ነበር። የሚያየውን ነገር በመመልከት እርሱ በአእምሮው ውስጥ ፈጽሞ ያላሰበውን ነገር እያሰበ እንዳለ ይሰማኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የቀድሞዋን ሚስትህን ትወዳታለህ ብዬ በግልጽ እወቅሰው ነበር። በአንድ ወቅት በዚህ ድርጊት በጣም ከመረበሹ የተነሣ አንድ ትልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ጥሎ ወጣ። ይሖዋን እንዳሳዘንኩት ተሰማኝ። የኋላ ኋላ ልጆቹም እየተጎዱ ስለመጡ ቤተሰቤን ሰላም ነሣሁ። በምሠራው መጥፎ ነገር ምክንያት ራሴን ጠላሁ፤ ይሁን እንጂ ችግሩን ለማስወገድ የቱንም ያህል ብጥር ያደረብኝን የቅናት ስሜት መቆጣጠር የምችል አልመስልም ነበር።

ማርክ እኔን ከመርዳት ይልቅ ዐጸፋውን መመለስ ጀመረ። ስወቅሰው “ቀናተኛ፣ በጣም ትቀኛለሽ” ብሎ ይጮኽብኝ ነበር። እንዲያውም ሆነ ብሎ ሊያስቀናኝ የሚሞክር ይመስል ነበር። ምናልባት ይህ ነገር ለቅናቴ መፍትሔ ይሆናል ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ሁኔታው ነገሮች ይበልጥ እንዲባባሱ አደረገ። ሌሎች ሴቶችን መመልከትና ምን ያህል የተዋቡ እንደሆኑ አስተያየት መሰንዘር ጀመረ። ይህም በይበልጥ ራሴን ዝቅ እንዳደርግና የማልፈለግ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አደረገ። በውስጤ ሌላ መጥፎ ስሜት ተፈጠረብኝ፤ ጥላቻ አደረብኝ። በዚህ ደረጃ ላይ ሳለሁ ሁሉ ነገር ምስቅልቅል ስላለብኝ ከእርሱም ሆነ ከቤተሰቡ ለመለየት ፈለግሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ “ቅንዓት ግን አጥንትን ያነቅዛቀል” የሚለው ነገር በእርግጥ እውነት ነው። (ምሳሌ 14:30) አሁን ጤንነቴ መቃወስ ጀመረ። የጨጓራ አልሰር የያዘኝ ሲሆን ከዚህ በሽታ ለመላቀቅ ደግሞ ረጅም ጊዜ ወስዶብኛል። ማርክ የሚያደርገውን ነገር ሁሉ በጥርጣሬ በመመልከት ራሴን ከልክ በላይ ማስጨነቄን ቀጠልኩ። ኪሶቹን እፈትሽና የስልክ ቁጥሮችን ካገኘሁ ስልክ የሚደውልላቸውን ሰዎች ለማወቅ ብዬ እደውል ነበር። በይሖዋ ፊት እንዲህ ያለ የሚያሳፍር ነገር በመሥራቴ በውስጤ ራሴን ከመጸየፌም በተጨማሪ አለቅስ ነበር። ሆኖም ራሴን መቆጣጠር ተሳነኝ። የራሴ ዋነኛ ጠላቴ እኔው ራሴ ነበርኩ።

መንፈሳዊነቴ በጣም ስለተጎዳ መጸለይ እስከማልችልበት ደረጃ ላይ ደረስኩ። ይሖዋን እወደዋለሁ፤ ትክክል የሆነውን ነገር ለመሥራትም ከልቤ እፈልጋለሁ። ስለ ባሎችና ስለ ሚስቶች የሚናገሩትን ጥቅሶች በሙሉ አውቃቸዋለሁ፤ ይሁን እንጂ በሥራ ላይ ላውላቸው አልቻልኩም። ጥሩ ልጆች ቢኖሩኝም እንኳ በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መኖር አስጠላኝ።

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች ከፍተኛ ማበረታቻ ሰጥተውኛል፤ እኔን ለመርዳትም የሚችሉትን ያህል ጥረዋል። ይሁን እንጂ ስለ ቅናቴ ሲያነሡ ከእፍረት የተነሣ እንዲህ ዓይነቱ ችግር እንዳለብኝ ለማመን ስለማልፈልግ እክድ ነበር።

ከጊዜ በኋላ ጤንነቴ በጣም ስለተቃወሰ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ወደ ሆስፒታል ለመሄድ ተገደድኩ። እዚያ ሳለሁ ሕይወት በዚህ መልኩ ሊቀጥል እንደማይችል ተገነዘብኩ። እኔና ማርክ ለሦስት ወራት ተለያይተን ረጋ ብለን ሁኔታችንን እንድንመረምር ወሰንን። በዚህ ወቅት አንድ የሚያስገርም ነገር ተከሰተ። በንቁ! መጽሔት ላይ “የአልኮል ሱሰኛ የሆኑ ወላጆች ላሳደጓቸው ልጆች የሚሆን እርዳታ” የሚል ርዕስ ወጣ።b

ይገርማችኋል፣ እናቴ የአልኮል ሱሰኛ ነበረች። አንድ ዓይነት አካላዊ ግፍ ባይፈጸምብኝም እንኳ ወላጆቼ እርስ በርሳቸውም ሆነ ከእኔ ጋር በጭራሽ አካላዊ ቅርርብ አያደርጉም ነበር። እናቴ እኔን ያቀፈችበትን ወይም እንደምትወደኝ የነገረችኝን ወቅት አላስታውስም። ስለዚህ እንዴት ማፍቀር እንደምችል ወይም ከዚህ የበለጠ ደግሞ እንዴት መፈቀር እንደምችል ሳላውቅ አደግሁ።

አባቴ ውሽሞች እንዳሉትና እንደማታምነው እናቴ ብዙውን ጊዜ ትነግረኝ ነበር። ስለዚህ ባጠቃላይ ለወንዶች እምነት ሳይኖረኝ ያደግሁ ይመስለኛል። በአስተዳደጌ ምክንያት ሁልጊዜ ከሌሎች ሰዎች በተለይም ከሴቶች እንደማንስ ይሰማኝ ነበር። በዚያ ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን ርዕስ ማንበቤ እነዚህ ነገሮች በእኔ ላይ ያሳደሩትን ተጽዕኖ ለመገንዘብ አስችሎኛል። ላለብኝ የቅናት ችግር ዋነኛ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ለመጀመሪያ ጊዜ አስተዋልኩ።

ይህን የንቁ! መጽሔት ርዕስ ለባሌ ለማርክ አሳየሁት፤ ርዕሱ እሱም ጭምር ስለ እኔ ሁኔታ በይበልጥ እንዲገነዘብ ረዳው። ወዲያው እኔም ሆንኩ እሱ መጽሐፍ ቅዱስ መለያየት ለሚያስቡ ባልና ሚስት የሚሰጠውን ምክር በሚገባ አጤንነው። ከዚያም ታረቅን። (1 ቆሮንቶስ 7:10, 11) በአሁኑ ወቅት ጋብቻችን ከበፊቱ የተሻለ ሆኗል። አብዛኞቹን ነገሮች በተለይ ደግሞ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎችን የሚመለከቱትን ነገሮች አንድ ላይ ሆነን እንሠራለን። ማርክ ይበልጥ ርኅራኄ ያሳየኛል። ምን ያህል እንደሚወደኝ የሚነግረኝ በየቀኑ ነው ማለት ይቻላል፤ አሁን በእርግጥ አምነዋለሁ።

ከማርክ የቀድሞ ባለቤት ጋር እንደምንገናኝ ሳውቅ አንድ የበሰለ ክርስቲያን የሚያሳየውን ዓይነት ባሕርይ እንዳሳይ እንዲረዳኝና ብርታት እንዲሰጠኝ በመለመን ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። ይህም የሚጠቅም ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ለእሷ ያለኝ ጥላቻ እንኳ እየቀነሰ መጥቷል። አፍራሽ ሐሳቦችን ማሰቤን ወይም ባዶ ግምት መላ ሕይወቴን እንዲቆጣጠር መፍቀዴን አቆምኩ።

አሁንም አንዳንድ ተገቢ ያልሆኑ የቅናት ስሜቶች ይመጡብኛል። ቅናቴ ሙሉ በሙሉ የሚወገደው በአምላክ አዲስ ዓለም ፍጹም ሕይወት ሳገኝ ብቻ ነው። እስከዚያው ድረስ ግን ቅናት እኔን እንዲቆጣጠረኝ ከመፍቀድ ይልቅ ቅናትን መቆጣጠርን ተምሬአለሁ። አዎን፣ ቅናት ሕይወቴን ሊያሳጣኝ ነበር፤ ሆኖም ለይሖዋና ለድርጅቱ ምስጋና ይግባቸውና በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ደስታ አግኝቻለሁ፤ ጤንነቴም ተመልሶልኛል። እንደገና ከይሖዋ አምላክ ጋር ጠንካራ ዝምድና መሥርቻለሁ።—አንዲት ሴት የጻፈችው

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሙ ተለውጧል።

b ግንቦት 22, 1992 ንቁ! ከገጽ 8–12 ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ