የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
የመመሥከሩ ሥራ በቤትም ሆነ በትምህርት ቤት ፍሬ ያፈራል
የአንድ ክርስቲያን ሕይወት ለሌሎች መልካም ማድረግን ያካትታል፤ በተለይ ይህንን ማድረግ የሚቻለው የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማካፈል ነው። ምሳሌ 3:27 “ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፣ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን” በማለት ይናገራል። የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሦስተኛ ዓመት ተማሪ የሆነ በአርጀንቲና የሚኖር አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር ለትምህርት ቤት ጓደኞቹ የመንግሥቱን ምሥራች የመናገር ፍላጎት አደረበት። እንዲህ ማድረጉ ከፍተኛ ውጤት አስገኝቶለታል።
ወጣቱ ምሥክር አንድ ቀን ሁሉም ሃይማኖቶች ጥሩ እንዳልሆኑ ለጓደኛው ነገረው። ወጣቱ መልሶ ምንም ዓይነት መጥፎ ነገር እንደማይሠራ ሲነግረው ምሥክሩ፦ “ለአምላክም ቢሆን ምንም አላደረግህለትም” አለው። ይህ ነገር ወጣቱን እንዲያስብ አደረገው። ከዚያም የምንኖረው በመጨረሻ ቀናት እንደሆነና አንድ ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ከፈለገ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘትና በሥራ ላይ ማዋል እንዳለበት ለጓደኛው ነገረው። የትምህርት ቤት ጓደኛው በዚህ ተስማማ። ነገር ግን ቤተሰቡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና ይፈቅድለት ይሆን? ጓደኛው በጉዳዩ እንዲያስብበት ለማድረግ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ እንዲያነብ ሰጠው።
ከጊዜ በኋላ ጓደኛው ትምህርት አቆመ። ስለ እርሱ ምንም ሳይሰማ አንድ ዓመት አለፈ። አንድ ቀን ጓደኛው ደውሎ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ለማስተዋል እንደቻለ ሲነግረው ወጣቱ ምሥክር በጣም ተደሰተ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ወዲያውኑ አመቻቸ።
ወደ ቀድሞው የትምህርት ቤት ጓደኛው ሲሄድ የጓደኛው ወላጆች ልጃቸው ምን እያደረገ እንዳለ በጣም እንዳሳሰባቸው አስተዋለ። እንዲያውም የጓደኛው ታናሽ ወንድም እያጠና ያለው ወንድሙ ያበደ መስሎት ነበር። ስለዚህ ወላጆቹ በሚቀጥለው ጥናት ላይ ታናሽ ወንድሙ እንዲገኝ አደረጉ። ጥናቱ እንዳበቃ ታላቅ ወንድሙ እንዳላበደ እንባ እየተናነቀው ለወላጆቹ ነገራቸው። እናትየው ይህንን ስትሰማ በድንጋጤ ጮክ ብላ “አንተም ተደገምክ!” አለች።
በሚቀጥለው ጥናት ላይ ራሷ ተገኘችና ልጆቹ እንዳላበዱ አረጋገጠች። ከጊዜ በኋላ እርሷና ባለቤቷ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ መላው ቤተሰብ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ በሚደረጉ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። በመጨረሻ አያቶቹም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። አሁን የመጀመሪያው ወጣት ተጠምቋል። ትዳር የመሠረተ ሲሆን እርሱና ባለቤቱ ቀናተኛ አስፋፊዎች ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ ወጣቱ ምሥክር በትምህርት ቤት በሚያከናውነው መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ሌሎች ሁለት የትምህርት ቤት ጓደኞቹን እየረዳ ነው። ከሁለቱ ጓደኞቹ የአንዱ እናትና እህትም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምረዋል። ወጣቱ ምሥክር ለትምህርት ቤት ጓደኞቹ መልካም ከማድረግ ወደ ኋላ ባለማለቱ በአጠቃላይ 11 ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አውቀዋል። እንዴት ያለ አስደሳች ውጤት ነው! በእርግጥም “ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!”—መዝሙር 144:15 አዓት