የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 11/1 ገጽ 22-25
  • “እንጣላለን እንጂ አንጠፋም”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “እንጣላለን እንጂ አንጠፋም”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ትልቅ እንቅፋት
  • ደስተኛ ቤተሰብ
  • መንፈሳዊ ሽባነትን መቋቋም
  • ሌላ እንቅፋትን መቋቋም
  • የምችለውን ማድረግ
  • ይሖዋ ላደረገልኝ ያልተቋረጠ ድጋፍ አመስጋኝ ነኝ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ‘እንደ ሚዳቋ የምዘልበት’ ጊዜ ይመጣል
    ንቁ!—2006
  • ከድክመቴ ጥንካሬ ማግኘት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
  • በጣም በሚያስፈልገኝ ወቅት ያገኘሁት ተስፋ
    ንቁ!—2014
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 11/1 ገጽ 22-25

“እንጣላለን እንጂ አንጠፋም”

ዩልፍ ሄልጌሰን እንደተናገረው

ሐምሌ 1983 አጎንብሰው ይመለከቱኝ የነበሩት ዶክተሮች “ነቅቷል!” በማለት በደስታ ጮኹ። 15 ሰዓታት የፈጀ ውስብስብ ቀዶ ሕክምና ከተደረገልኝ በኋላ ከአከርካሪዬ ውስጥ 12 ሴንቲ ሜትር ርዝማኔ ያለው እጢ ወጣልኝ። ጨርሶ ሽባ ሆንኩ።

ከጥቂት ቀናት በኋላ በደቡብ ስዊድን ከምትገኘው ሄልሲንግቦርግ ከምትባለው የትውልድ ከተማዬ 60 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ አንድ ሆስፒታል ተዛወርኩ። እዚያም አንድ የማገገሚያ ፕሮግራም ጀመርኩ። ፊዚዮቴራፒስቱ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ቢነግረኝም ይህን ፕሮግራም ለመጀመር ጓጉቼ ነበር። እንደገና በእግሬ ለመራመድ በጣም እጓጓ ነበር። በየቀኑ ለአምስት ሰዓታት የሚደረገውን የአካል እንቅስቃሴ ፕሮግራም በትጋት በመከታተሌ በፍጥነት ለውጥ ማሳየት ጀመርኩ።

ከአንድ ወር በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በጉባኤያችን ውስጥ በሚያገለግልበት ወቅት እሱና ሌሎቹ ክርስቲያን ሽማግሌዎች በተኛሁበት የሆስፒታል ክፍል ውስጥ የጉባኤ ሽማግሌዎች ስብሰባ ለማድረግ ረዥም ጉዞ አድርገው መጡ። በዚህ የወንድማማቻዊ ፍቅር መግለጫ በጣም ተደሰትኩ! ከስብሰባው በኋላ ለበሽተኞች እንክብካቤ የሚያደርጉት ነርሶች ለሁላችንም ሻይና ሳንድዊች በማቅረብ አስተናገዱን።

በመጀመሪያ ዶክተሮቹ ባሳየሁት ለውጥ ተገርመው ነበር። ከሦስት ወራት በኋላ በተሸከርካሪ ወንበሬ ላይ መቀመጥ ጀመርኩ። እንዲያውም ለጥቂት ደቂቃዎች ለመቆም ችዬ ነበር። በጣም ተደሰትኩ። እንደ ቀድሞዬ በእግሬ ለመራመድ ቆርጬ ተነሣሁ። ቤተሰቦቼና መሰል ክርስቲያኖች ሊጠይቁኝ በሚመጡበት ወቅት ብዙ ማበረታቻዎችን ይሰጡኝ ነበር። እንዲያውም ለጥቂት ጊዜያት ወደ ቤት ተመልሼ ለመሄድ ችዬ ነበር።

ትልቅ እንቅፋት

ሆኖም ከሦስት ወራት በኋላ ምንም ለውጥ ሳላሳይ ቀረሁ። ብዙም ሳይቆይ ፊዝዮቴራፒስቱ አንድ በጣም አሳዛዥ ነገር ነገረኝ። “ሁኔታህ ከዚህ በላይ ሊሻሻል አይችልም!” አለኝ። በዚህ ወቅት ብቻዬን በተሽከርካሪ ወንበር እንድሄድ ለማስቻል ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ምን እሆን ይሆን በማለት ግራ ተጋባሁ። ባለቤቴ ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዴት ትወጣዋለች? እሷ ራሷ ከባድ የቀዶ ሕክምና ስለ ተደረገላት የእኔ እርዳታ ያስፈልጋታል። ለዘለቄታው የሚንከባከበኝ የአንድ ድርጅት እርዳታ ያስፈልገኝ ይሆን?

በጣም ተጨነቅሁ። ቀስ በቀስ ጥንካሬዬ፣ ድፍረቴና ኃይሌ እየጠፋ ሄደ። ብዙ ጊዜያት ቢያልፉም መንቀሳቀስ አልቻልኩም። በአካል ሽባ ከመሆኔም በላይ በስሜትና በመንፈሳዊ ጭምር ደነዘዝኩ። ‘የተጣልኩ’ ሆንሁ። ሁልጊዜ በመንፈሳዊ ጠንካራ እንደ ሆንኩ አስብ ነበር። በአምላክ መንግሥት ላይ የጠበቀ እምነት ነበረኝ። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:10) መጽሐፍ ቅዱስ ጽድቅ በሚሰፍነበት የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ሁሉም በሽታዎችና የአካል ጉድለቶች እንደሚፈወሱና መላው የሰው ልጅ ፍጹም ሕይወት እንደሚያገኝ በሚናገራቸው ተስፋዎች ላይ አምን ነበር። (ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) አሁን ግን በሥጋዊ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊም ረገድ ሽባ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ‘የጠፋሁ’ መሰለኝ።—2 ቆሮንቶስ 4:9 አዓት

ወደ ሌላ ጉዳይ ከመሄዴ በፊት ስላስተዳደጌ ጥቂት ልንገራችሁ።

ደስተኛ ቤተሰብ

የተወለድኩት በ1934 ሲሆን በሽታ የሚባል አያውቀኝም ነበር። በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከኢንግሪድ ጋር ተዋወቅንና በ1958 ተጋባን፤ ከዚያም በማዕከላዊ ስዊድን በምትገኝ ኦስተርሰንድ በምትባል ከተማ ውስጥ እንኖር ጀመር። በ1963 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስንጀምር በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ለውጥ ተከሰተ። በዚያን ወቅት አቫ፣ ቦዮርን እና ሌና የተባሉ ሦስት ትናንሽ ልጆች ነበሩን። ወዲያው ጠቅላላው ቤተሰባችን ማጥናት ጀመረና በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች እውቀት ጥሩ እድገት አሳየ።

ጥናት ከጀመርን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሄልሲንበርግ ተዛወርን። እዚያም እኔና ባለቤቴ ራሳችንን ለይሖዋ ከወሰንን በኋላ በ1964 ተጠመቅን። በ1968 ትልቋ ልጃችን አቫ ስትጠመቅ ደስታችን የላቀ ሆነ። ከሰባት ዓመታት በኋላ ቦዮርን እና ሌና በ1975 ሲጠመቁ እኔ ደግሞ በቀጣዩ ዓመት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ ተሾምኩ።

የምሠራው ሰብዓዊ ሥራ የቤተሰቤን ቁሳዊ ፍላጎቶች በሚገባ እንዳሟላ ያስችለኝ ነበር። ከዚህም በላይ ቦዮርን እና ሌና ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሲገቡ ደስታችን እየጨመረ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ ቦዮርን በአርቡጃ ከተማ በሚገኘው የቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንዲያገለግል ተጋበዘ። ሕይወት አስደሳች ሆነልን። ከዚያም በ1980 መጀመሪያ ላይ እጢው በአካሌ ላይ የሚያስከትለው ሕመም ይሰማኝ ጀመር። በመጨረሻ በ1983 በተደረገልኝ ከባድ ቀዶ ሕክምና ይህ እጢ ወጣልኝ።

መንፈሳዊ ሽባነትን መቋቋም

እንደገና መራመድ እንደማልችል ሲነገረኝ ሕይወት ጨለመብኝ። መንፈሳዊ ጥንካሬ መልሼ ላገኝ የቻልኩት እንዴት ነበር? ይህ ካሰብኩት በላይ ቀላል ነበር። ያደረግሁት ነገር ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስን አንሥቶ ማንበብ መጀመር ብቻ ነበር። ብዙ ባነበብኩ መጠን ብዙ መንፈሳዊ ጥንካሬ አገኘሁ። ከሁሉም በላይ ለኢየሱስ የተራራ ስብከት ከፍተኛ አድናቆት አደረብኝ። ደግሜ ደጋግሜ አነበብኩት፤ አሰላሰልኩበት።

እንደ ቀድሞው ሕይወትን በደስታ መመልከት ጀመርኩ። ማንበቤና ማሰላሰሌ ከእንቅፋቶች ይልቅ ሊኖሩኝ የሚችሉትን አጋጣሚዎች እንድገነዘብ አስቻለኝ። እንደገና የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለሌሎች ሰዎች የማካፈል ፍላጎት አደረብኝ። ለሆስፒታሉ ሠራተኞችና ለማገኛቸው ሰዎች በመመሥከር ይህን ፍላጎቴን አሟላ ነበር። ቤተሰቦቼ የተሟላ እርዳታ ያደረጉልኝ ሲሆን እኔን እንዴት መንከባከብ እንደሚችሉም ሥልጠና አግኝተዋል። ከዚያም ከሆስፒታል ለመውጣት ቻልኩ።

በመጨረሻ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ይህ ለሁላችንም እንዴት ያለ አስደሳች ቀን ነበር! ቤተሰቤ እኔን መንከባከብን የሚጨምር ፕሮግራም አወጣ። ቦዮርን የተባለው ልጄ በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚሠራውን ሥራ ትቶ እኔን ለመርዳት ወደ ቤት መጣ። ቤተሰቤ ይህን ያህል እንደሚወደኝና እንደሚያስብልኝ ማወቄ በጣም አጽናን ቶኛል።

ሌላ እንቅፋትን መቋቋም

ሆኖም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጤንነቴ በጣም እየተቃወሰ መጣ። መንቀሳቀስ ተሳነኝ። በመጨረሻም ቤተሰቦቼ ብዙ ቢጥሩም በቤት ውስጥ ለእኔ እንክብካቤ ማድረግ አልቻሉም። ስለዚህ የጤንነት ችግር ላለባቸው ሰዎች እንክብካቤ በሚደረግበት ድርጅት ውስጥ መግባት ይሻለኛል ብዬ አሰብኩ። ይህም ለውጥ ማድረግንና ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ራስን ማለማመድን የሚጠይቅ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ መንፈሳዊ እንቅፋት እንዲፈጥርብኝ አልፈቀድኩለትም።

መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቤንና ምርምር ማድረጌን አላቋረጥኩም። ማድረግ የምችለውን እንጂ ማድረግ የማልችለውን ማሰቤን አቆምኩ። ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ባሏቸው መንፈሳዊ በረከቶች ላይ አሰላሰልኩ። በጸሎት ከይሖዋ ጋር በይበልጥ መቀራረቤን ቀጠልኩ። በተጨማሪም ማንኛውንም አጋጣሚ ለሌሎች ለመስበክ እጠቀምበት ነበር።

አሁን ሌሊትና ከፊሉን የቀን ጊዜዬን የጤንነት ችግር ያለባቸው ሰዎች እንክብካቤ በሚደረግላቸው ድርጅት ውስጥ አሳልፋለሁ። ከሰዓት በኋላና ማታ ማታ ወደ ቤት ወይም ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን እሄዳለሁ። አንድ ማኅበራዊ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመ ድርጅት ዘወትር ወደ ስብሰባም ሆነ ወደ ቤት ስሄድና ከዚያ ስመለስ ትራንስፖርት እንዳገኝ ዝግጅት አድርጎልኛል። አፍቃሪ ቤተሰቦቼ፣ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞች እና የጤንነት ችግር ላለባቸው ሰዎች እንክብካቤ የሚያደርገው ድርጅት ሠራተኞች አስደናቂ በሆነ መንገድ ይንከባከቡኛል።

የምችለውን ማድረግ

ራሴን ምንም የማልጠቅም እንደ ሆንኩ አድርጌ አልመለከትም። ቤተሰቤም ሆነ ክርስቲያን ወንድሞቼ በዚህ መንገድ አይመለከቱኝም። ፍቅራዊ እንክብካቤ ስለ ተደረገልኝ ውጤታማ በሆነ መንገድ በሽማግሌነት ማገልገሌን ለመቀጠል ችያለሁ። በየሳምንቱ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ከመምራቴም በተጨማሪ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የሚካሄደውን ሳምንታዊ የጉባኤ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እመራለሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾችን ማገላበጥ ስለሚያስቸግረኝ በስብሰባዎች ላይ አንድ ሰው ጥቅስ በማንበብ እንዲረዳኝ ይመደብልኛል። በተሽከርካሪ ወንበሬ ላይ ሆኜ ስብሰባዎችን ከመምራቴም በላይ ንግግሮች አቀርባለሁ።

በዚህ መንገድ የእረኝነት ጉብኝትን ጨምሮ ከዚህ በፊት ስሠራቸው የሚያስደስቱኝን ሌሎች ብዙ ነገሮችን አሁንም ቢሆን መሥራት እችላለሁ። (1 ጴጥሮስ 5:2) እረኝነት የማደርገው ወንድሞችና እህቶች እርዳታ ወይም ምክር ለማግኘት ወደ እኔ በሚመጡበት ወቅት ነው። በተጨማሪም ራሴም ብሆን ስልክ በመደወል እረኝነት አደርጋለሁ። በዚህ ምክንያት እርስ በርሳችን እንበረታታለን። (ሮሜ 1:11, 12) በቅርቡ አንድ ወንድም “ልክ በተከዝኩበት ወቅት ስለምትደውልልኝ የስልክ ጥሪህ በጣም ያስደስተኛል” ብሎኛል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ጥረቶቼን እንደሚባርክልኝ በማወቄ እኔም ማበረታቻ አገኛለሁ።

ከስብሰባዎች በፊትና በኋላ በጉባኤው ውስጥ ካሉ ልጆች ጋር ጥሩ ቅርርብ አደርጋለሁ። በተሽከርካሪ ወንበሬ ላይ ስለምቀመጥ ዓይን ለዓይን እየተያየን እንነጋገራለን። ቅንነታቸውንና ግልጽነታቸውን አደንቃለሁ። በአንድ ወቅት አንድ ልጅ “አንተ ልዩ የሆንክ ደስ የምትል አካለ ስንኩል ነህ!” ብሎኛል።

ላደርገው የማልችለውን ነገር እያሰብኩ ከመጨነቅ ይልቅ ላደርገው በምችለው ነገር ላይ በማተኮር ይሖዋን ከማገልገል ደስታ እያገኘሁ ነው። በሕይወቴ ካጋጠመኝ ነገር ብዙ ተምሬአለሁ። በፈተናዎች ውስጥ ስናልፍ ሥልጠና እና ጥንካሬ እንደምናገኝ ተገንዝቤአለሁ።—1 ጴጥሮስ 5:10

ብዙ ጤነኛ ሰዎች የሰማያዊ አባታችንን አምልኮ ሁልጊዜ በቁም ነገር መያዝ ያለብን መሆኑን መገንዘብ እንደሚሳናቸው ተረድቻለሁ። ይህን ካላደረግን የጥናት ፕሮግራማችን፣ ስብሰባዎች እና የመስክ አገልግሎት እንዲሁ በዘልማድ የምናደርጋቸው ነገሮች ይሆኑብናል። ከዚህ ዓለም ፍጻሜ በሕይወት ተርፎ አምላክ ቃል ወደ ገባልን ምድራዊት ገነት ለመግባት እነዚህን ዝግጅቶች በጣም አስፈላጊ እንደሆኑ አድርጌ እመለከታቸዋለሁ።—መዝሙር 37:9–11, 29፤ 1 ዮሐንስ 2:17

ሁልጊዜ በመጪው የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖርን ተስፋ በልባችን ውስጥ ማሳደር ይኖርብናል። (1 ተሰሎንቄ 5:8) በተጨማሪም ማናቸውንም ዓይነት የተስፋ መቁረጥ አዝማሚያ በመዋጋት ረገድ እጅ መስጠት እንደሌለብኝ ተምሬአለሁ። ይሖዋን እንደ አባቴ ድርጅቱን ደግሞ እንደ እናቴ አድርጌ መመልከትን ተምሬአለሁ። ጥረት ካደረግን ይሖዋ ማናችንንም ውጤታማ አገልጋዮቹ አድርጎ ሊጠቀምብን እንደሚችል ተገንዝቤአለሁ።

አንዳንድ ጊዜ እንደ ‘ተጣልኩ’ ያህል ቢሰማኝም ‘አልጠፋሁም።’ ይሖዋ እና ድርጅቱ እንዲሁም ቤተሰቤና ክርስቲያን ወንድሞቼ በጭራሽ አልተዉኝም። መጽሐፍ ቅዱስን አንሥቼ ማንበብ በመጀመሬ እንደገና መንፈሳዊ ጥንካሬ አገኘሁ። እኛ ከተማመንበት “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” የሚሰጠንን ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።—2 ቆሮንቶስ 4:7 አዓት

በልበ ሙሉነትና በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ በመተማመን የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቅሁ ነው። ይሖዋ አምላክ እዚሁ ምድር ላይ ስለምትመለሰዋ ገነት እና በእርሷ ውስጥ ስለሚያመጣቸው አስደሳች በረከቶች የገባውን ቃል በቅርቡ እንደሚፈጽም አንዳች አልጠራጠርም።—ራእይ 21:3, 4

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ