መቶ ዓመት ቢሆነኝም አቅሜ አልደከመም
ራልፍ ሚቼል እንደተናገረው
መካከለኛ ቁመት የነበረው አባቴ የሜቶዲስት ሰባኪ ነበር። በየሁለት ወይም ሦስት ዓመቱከአንዱ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌላ ይዛወር ነበር። ብዙውን ጊዜ የሚዛወረው ወደ ትንንሽከተሞች ሲሆን ከእነዚህ መካከል በየካቲት 1895 የተወለድኩባት ዩ ኤስ ኤ ውስጥኖርዝ ካሮላይና የምትገኘው አሽቪል ከተማ ትገኝበታለች። በዚህም የተነሳ የሕዝበ ክርስትናሃይማኖት ምን እንደሚመስል ከልጅነቴ ጀምሮ በሚገባ አውቃለሁ።
ልጅ ሳለሁ ስሜታዊነት በከፍተኛ ሁኔታ በሚታይባቸው ስብሰባዎች ላይ በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት፣ እነርሱ እንደሚሉት “ጽድቅ ለማግኘት” ፊት በሚገኙት የመናዘዣ ወንበሮች ላይ ያስቀምጡኝ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ኃጢአቴን እንድናዘዝ፣ አሥርቱን ትእዛዛት እንድጠብቅና ጥሩ ሰው እንድሆን ይነገረኝ ነበር። እንዲህ ካደረግሁ ስሞት ወደ ሰማይ እሄዳለሁ ማለት ነው። ‘ወደ ሰማይ ለመሄድ የሚያስችል ብቃት ስለማይኖረኝ ወደ ሲኦል መሄዴ አይቀርም’ ብዬ አሰብኩ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች የሚያሟሉት ትልልቅ ሰዎች ብቻ በተለይም ሰባኪዎች ናቸው ብዬ አስብ ነበር።
ነገር ግን ገና ወደ አሥራዎቹ ዓመታት ዕድሜ ሳልደርስ በሃይማኖት ውስጥ ያለውን ግብዝነት ማስተዋል ጀመርኩ። ለምሳሌ አባቴ ከጳጳሱ ጋር በሚያደርጉት ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ለጳጳሱ ብዙ ገንዘብ ለመስጠት ሲል የቤተሰቡን ቁሳዊ ፍላጎቶች መሥዋዕት ያደርግ ነበር። እንዲህ የሚያደርገው በአንድ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ላይ እንደሚሾሙት ተስፋ በማድረግ ነበር። ጥጥ አምራች ገበሬ የነበረ አንድ የአካባቢው ሰባኪ ትዝ ይለኛል። ሥልጣን የማግኘት ጉጉት ስለነበረው አንድ መቶ እስር ጥጥ ሸጠና ብዙ ገንዘብ ይዞ ወደ ስብሰባው ሄደ። አብዛኞቹ ሰባኪዎች የሆኑት ተሰብሳቢዎች የቻሉትን ያህል አዋጥተው ሲጨርሱ ይህ ጥጥ አምራች ሰባኪ ከመቀመጫው ተነሳና ድምፁን ከፍ አድርጎ “ለጳጳሳችሁ የምትሰጡት ይህንን ብቻ ነው? እኔ ሁላችሁ ያዋጣችሁትን እጥፍ እሰጣለሁ!” አለ። በጠቅላላ ከአንድ ሺህ ዶላር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ጳጳሱ ሰውዬውን የአባቴ የበላይ ሆኖ እንዲያገለግል ሾመው። እንዲህ ያለው ሹመት ከአምላክ የመጣ ነው ብዬ ማመን አቃተኝ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ማንኛውንም ነገር መጠራጠር ጀመርኩ።
ዩናይትድ ስቴትስ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ውስጥ ስትገባ ለወታደራዊ አገልግሎት ተመዝግቤ ነበር። ከሠራዊቱ ጋር የዘመቱ ቀሳውስት ለአገራችን በታማኝነት እንድንዋጋ ሲሰብኩን በደንብ አስታውሳለሁ፤ ይህ ራሱ ለሃይማኖት ያለኝን ጥላቻ አሳድጎት ነበር። ግቤ በሕይወት መትረፍ፣ ትምህርቴን መጨረስና ትዳር መመሥረት ነበር። ለወደፊቱ ባወጣሁት እቅድ ውስጥ ሃይማኖት ምንም ቦታ አልነበረውም።
የአቋም ለውጥ
በ1922 ልዊዝ ከተባለች ወጣት ጋር ፍቅር ያዘኝ። በኋላም አጥባቂ ካቶሊክ እንደሆነች አወቅሁ፤ ለመጋባት ስንወስን በካቶሊክ የጋብቻ ሥርዓት እንድንጋባ ፈልጋ ነበር። ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት አንዲካሄድ ስላልፈለግሁ ኒው ዮርክ ሲቲ በሚገኘው የማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ውስጥ ለመጋባት ተስማማን።
መጀመሪያ ላይ በመካከላችን ሃይማኖታዊ ግጭት አልነበረም። በሃይማኖት ላይ እምነት እንደሌለኝና ስለ ሃይማኖት እስካላነሳን ድረስ ተስማምተን እንደምንኖር ግልጽ አደረኩላት። ከ1924 እስከ 1937 ባሉት ዓመታት በላይ በላይ አምስት ወንዶችና አምስት ሴቶች ልጆች ወለድን! ልዊዝ ልጆቻችን ካቶሊክ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ፈልጋ ነበር። ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥልጠና እንዲሰጣቸው ስላልፈለግሁ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨቃጭቀናል።
በ1939 መግቢያ ላይ ስለ ሃይማኖት ያለኝን አመለካከት ሙሉ በሙሉ የለወጠ አንድ ነገር ተከሰተ። ሄንሪ ዌበር እና ሃሪ ፒያት የተባሉ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ኒው ጀርሲ ውስጥ ሮዜል ከተማ ወደሚገኘው ቤቴ መጡ። የማልወደውን ርዕሰ ጉዳይ ሃይማኖትን አንስተው ሊያነጋግሩኝ እንደፈለጉ ወዲያውኑ ገባኝ። ከሠራዊቱ ጋር አብረው የዘመቱ ቀሳውስት ‘ለአገራችሁ ተዋጉ’ እያሉ ሲያበረታቱ እዚያው አገር ቤት የቀሩት የሃይማኖት መሪዎች ደግሞ ‘አትግደሉ’ እያሉ ማስተማራቸው በሃይማኖት ላይ ጥላቻ አሳድሮብኛል። እንዴት ያለ ግብዝነት ነው! እነዚህን ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ከስህተታቸው ለማረም አሰብኩ። “አንድ ነገር ልንገራችሁ” አልኳቸው። “የእናንተ ሃይማኖት እውነት ከሆነ ሌሎቹ ሁሉ ውሸት ናቸው። ከሌሎቹ መካከል አንዱ እንኳ እውነት ከሆነ የእናንተን ጨምሮ የተቀሩት በሙሉ ውሸት ናቸው። ሊኖር የሚችለው እውነተኛ ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው።” የሚያስገርመው ግን እነርሱም በዚህ ሐሳብ ተስማሙ!
ከዚያም መጽሐፍ ቅዱሴን እንዳመጣና 1 ቆሮንቶስ 1:10ን እንዳነብ ጠየቁኝ። እዚያም ላይ “ወንድሞች ሆይ፣ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ” ይላል። ይህ ጥቅስ ስሜቴን ነካው። ያም ሆኖ ግን እነዚህ ሁለት ሰዎች መናፍቅ ሊያደርጉኝ ጥረት እያደረጉ ይሆን ብዬ ፈራሁ። ይሁንና ቢያንስ በክርስቲያኖች መካከል መለያየት መኖር እንደሌለበት ተምሬ ነበር። በአእምሮዬ ውስጥ ሌሎች ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ። ከእነዚህም መካከል ሰው ሲሞት ነፍሱ ምን ትሆናለች? የሚለው ይገኝበታል። ይህን ጥያቄ በተመለከተ ከእነርሱ ጋር መወያየት በጣም ፈልጌ ነበር! ቢሆንም ይህ ሁኔታ እቤት ውስጥ ከፍተኛ የሃይማኖት ውዝግብ ይፈጥራል ብዬ አሰብኩ።
ከዚያም አንደኛው “በሚቀጥለው ሳምንት መጥተን እንደገና ብንነጋገር ደስ ይለናል” አለ። በዘዴ እንዳይመጡ ለማድረግ ጥረት ባደርግም ሚስቴ ጮክ ብላ “ራልፍ፣ መቼ ተመልሰው መምጣት እንደሚችሉ ለማወቅ ይፈልጋሉ” አለች። አጥባቂ ካቶሊክ ስለነበረች እንዲህ ማለቷ አስገረመኝ! ‘በአንዳንድ ሃይማኖታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ልንስማማ አንችል ይሆናል’ ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ ሄንሪ ዌበር እና ሃሪ ፒያት የሚቀጥለው ዐርብ ተመልሰው እንዲመጡ ተስማማሁ።
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመርኩት በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ኒው ዮርክ ውስጥ በማድሰን ስኩዌር ጋርደን በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ተጋበዝኩ። ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ሰኔ 25, 1939 “መንግሥትና ሰላም” በሚል ርዕስ የሰጠውን ንግግር በደንብ አስታውሳለሁ። በስብሰባው ላይ ከተገኙት 18,000 ሰዎች አንዱ ነበርኩ። በዓለም አቀፍ ደረጃ በሬዲዮ ሞገድ አማካኝነት ያዳምጡ የነበሩትን ስትደምሩ ንግግሩን ይከታተሉ የነበሩ ሰዎች ቁጥር 75,000 ይደ ርሳል።
ቢሆንም ስብሰባው እክል አጋጥሞት ነበር። ቻርልስ ካግለን የተባለ የካቶሊክ ቄስ ተከታዮች የሆኑ ሰዎች ስብሰባውን ለማስቆም ጥረት አድርገው ነበር። የወንድም ራዘርፎርድ ንግግር እንደተጋመሰ በመቶ የሚቆጠሩ የተናደዱ ሰዎች በጩኸት መቃወምና “ሄይል ሂትለር!” እንዲሁም “ቪቫ ፍራንኮ!” የሚሉ መፈክሮችን ማሰማት ጀመሩ። ጩኸቱ በሬዲዮ ሞገዶች አልፎ እስኪሰማ ድረስ ከፍተኛ ረብሻ ተፈጥሮ ነበር! አስተናጋጆች ረብሻውን ለማስቆም 15 ደቂቃ ያህል ወስዶባቸዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ወንድም ራዘርፎርድ ያላንዳች ማመንታት ንግግሩን የቀጠለ ሲሆን አድማጮቹ በተደጋጋሚ የሚያሰሙት ጭብጨባ ድጋፍ ሰጥቶት ነበር።
በዚህ ጊዜ ከፍተኛ የማወቅ ጉጉት አደረብኝ። አንድ የካቶሊክ ቄስ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከፍተኛ ጥላቻ የሚያነሳሳው ለምንድን ነው? ቄሱ እንደ እኔ ያሉ ሰዎች እንዲሰሙ የማይፈልጉት አንድ ነገር በራዘርፎርድ ስብከት ውስጥ መኖር አለበት ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን ቀጠልኩና እድገት አደረግሁ። በመጨረሻም ጥቅምት 1939 በውኃ በመጠመቅ ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን አሳየሁ። በሚቀጥለው ዓመት ከልጆቼ መካከል አንዳንዶቹ የተጠመቁ ሲሆን ሚስቴ ልዊዝ በ1941 ተጠመቀች።
ፈተናዎችን ተቋቁሞ ማለፍ
እውነትን ከሰማሁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እናቴ አረፈች፤ በቀብሩ ላይ ለመገኘት ወደ ኖርዝ ካሮላይና መሄድ ነበረብኝ። በሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚከናወነው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘቱ ሕሊናዬን ሊያቆሽሽብኝ እንደሚችል ሆኖ ተሰማኝ። ስለዚህ ከመሄዴ በፊት ለአባቴ ደወልኩለትና አስከሬኑን በሬሳ ማቆያ ቤት እንዲያቆየው ጠየቅሁት። በሐሳቤ ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም አብሮን መሄዱ አይቀርም ብለው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ጉዟቸውን ቀጥለው ነበር።
እኔ ግን አልሄድኩም። ይህም ቤተሰቦቼን በጣም አስቆጣቸው። ኤድና ከተባለችው እህቴ ጋር በጣም እንቀራረብ የነበረ ቢሆንም ከእናቴ ቀብር በኋላ አላናገረችኝም። ደብዳቤ ብጽፍላትም መልስ ነሳችኝ። ኤድና በኒው ዮርክ ሲቲ ኮሌጅ በሚደረገው የአስተማሪዎች ኮርስ ለመካፈል በየዓመቱ ክረምት ስትመጣ ላገኛት እሞክር ነበር። እርሷ ግን ሥራ እንደሚበዛባት በመናገር ትሸሸኝ ነበር። እርሷን ከማሰልቸት በቀር የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ስለተሰማኝ በመጨረሻ ተውኩት። ከእርሷ ጋር ሳንገናኝ ብዙ ዓመታት አለፉ።
ስድስቱ ልጆቼ ለባንዲራ ሰላምታ አንሰጥም በማለታቸው በአሜሪካና በካናዳ ይኖሩ እንደነበሩት ሌሎች ብዙ ልጆች እነርሱም በ1941 ከትምህርት ቤት ተባረሩ። ልጆች ሕጉ የሚጠይቅባቸውን የትምህርት ብቃት እንዲያሟሉ ለማድረግ ምሥክሮቹ የመንግሥቱ ትምህርት ቤቶች የሚባሉ የራሳቸው ትምህርት ቤቶች አቋቋሙ። ልጆቼ የተማሩት ኒው ጀርሲ ውስጥ ሌክውድ ከተማ የሚገኝ ቀድሞ ሆቴል የነበረ ቤት ውስጥ ነበር። አንድ የመንግሥት አዳራሽ ከትምህርት ቤቱ የመማሪያ ክፍሎች፣ ከማዕድ ቤቱና ከመመገቢያው ክፍል ጋር አብሮ የመጀመሪያው ፎቅ ላይ ይገኝ ነበረ። የሴቶቹ ልጆች መኝታ ቤት ሁለተኛው ፎቅ ላይ የነበረ ሲሆን የወንዶቹ ደግሞ ሦስተኛው ፎቅ ላይ ነበር። ግሩም የሆነ ትምህርት ቤት ነበር። እዚያው የሚያድሩት አብዛኞቹ ተማሪዎች ቤታቸው የሚሄዱት በሳምንቱ የመጨረሻ ቀኖች ብቻ ነበር። ቤታቸው ሩቅ የሆኑት ደግሞ በየሁለት ሳምንቱ ወደ ቤታቸው ይሄዱ ነበር።
እውነትን ከሰማሁባቸው ዓመታት ጀምሮ አቅኚ ተብለው እንደሚጠሩት የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ለመሆን በጣም እመኝ ነበር። በ1941 ሴንት ልዊዝ ሚዙሪ ውስጥ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ አንድ ወንድም 12 ልጆች እያሳደገ እንዴት አቅኚ መሆን እንደቻለ ተናገረ። ‘እርሱ 12 ልጆች እያሉት አቅኚ መሆን ከቻለ እኔ 10 ልጆች ይዤ አቅኚ የማልሆንበት ምክንያት የለም’ ብዬ አሰብኩ። ቢሆንም ያለሁበት ሁኔታ ስላልፈቀደልኝ አቅኚ ሳልሆን 19 ዓመታት አለፉ። በመጨረሻም ጥቅምት 1, 1960 በዘወትር አቅኚነት ይሖዋን ማገልገል ጀመርኩ።
ያልተጠበቀ እንግዳ
በ1975 እህቴ ኤድና ስልክ ደወለችልኝ። በዚህን ጊዜ ዕድሜዬ 80 የሞላ ሲሆን ላለፉት 20 ዓመታት አይቼያትም ሆነ ድምጿን ሰምቼ አላውቅም ነበር። የደወለችው ከአውሮፕላን ማረፊያ ሲሆን መጥቼ እርሷንና ባለቤቷን እንድወስዳቸው ጠየቀችኝ። ኤድናን እንደገና ማየቱ አስደሳች ቢሆንም ከዚህ ይበልጥ የሚያስገርም አንድ ነገር ተከስቶ ነበር። ወደ ቤት እየሄድን ሳለ ባለቤቷ “አንድ የተለወጠ ሰው አግኝተሃል” አለ። ምን ማለቱ እንደሆነ አልገባኝም ነበር። እቤት ስንደርስም “አንድ የተለወጠ ሰው አግኝታችኋል” ብሎ እንደገና ተናገረ። በዚህ ጊዜ ባለቤቴ ምን ማለቱ እንደሆነ ገባት። ወደ እህቴ ዞር ብላ “ኤድና የይሖዋ ምሥክር ነሽ?” ብላ ጠየቀቻት። “አዎ ነኝ” በማለት ኤድና መለሰች።
ኤድና እውነትን እንዴት ልትቀበል ቻለች? የተበላሸውን ግንኙነታችንን ለማስተካከል በ1972 በስጦታ መልክ የመጠበቂያ ግንብ ኮንትራት ገብቼላት ነበር። አንድ ዓመት ያህል እንዳለፈ ኤድና ታመመችና እቤት መዋል ጀመረች። መጽሔቶቹ እንደታሸጉ ጠረጴዛዋ ላይ ተቀምጠው ነበር። ኤድና እስቲ ልየው ብላ አንዱን መጽሔት አንስታ ማንበብ ጀመረች። መጽሔቱን አንብባ ስትጨርስ በልቧ ‘እውነት ይህ ነው!’ ስትል አሰበች። የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቷ በመጡበት ወቅት በእጅዋ ያሉትን መጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች በሙሉ አንብባቸው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረችና በመጨረሻ የይሖዋ ምሥክር ሆነች።
የደረሰብኝን ኃዘን መቋቋም
ባለቤቴ ልዊዝ የስኳር በሽታ ያዛትና ሕመሙ እየተባባሰባት ሄዶ በ1979 በ82 ዓመቷ አረፈች። ልዊዝ ስትሞት የአካሌን ክፋይ አጣሁ። ሰማይና ምድሩ ተጋጠመብኝ። ምን እንደማደርግ ግራ ገባኝ። ሁሉ ነገር ስለጨለመብኝ ከፍተኛ ማጽናኛ አስፈልጎኝ ነበር። ተጓዥ የበላይ ተመልካች የሆነው ሪቻርድ ስሚዝ በአቅኚነት እንድቀጥል አበረታታኝ። ከፍተኛ ማጽናኛ ያገኘሁት የሚወዱት ሰው የሞተባቸውን ሌሎች ሰዎች በማጽናናት ነበር።
በ1979 የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር እስራኤልን ለመጎብኘት ዝግጅት አድርጎ ስለነበር እኔም ተመዘገብኩ። ይህ ጉዞ ከፍተኛ ማነቃቂያ ሆኖልኝ የነበረ ሲሆን እንደተመለስኩ የአቅኚነት አገልግሎቴን ጀመርኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙት ለየትኛውም ጉባኤ ባልተመደቡ ወይም ብዙም ባልተሠራባቸው ክልሎች እየሄድኩ አገለግላለሁ። ዕድሜዬ ቢገፋም እንኳ በዚህ መብት በማገልገል ላይ እገኛለሁ።
ባለፉት ዓመታት 50 የሚያክሉ ሰዎች በሕይወት መንገድ ላይ እንዲመላለሱ በመርዳት ደስታ አግኝቻለሁ። አብዛኞቹ ልጆቼ በእውነት ውስጥ ናቸው። ሁለቱ ሴቶች ልጆቼ በዘወትር አቅኚነት ያገለግላሉ። ልዊዝ ብላንተን የተባለችው ሌላኛዋ ሴት ልጄ ጆርጅ ከተባለው ባሏ ጋር በመሆን ብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋናው ጽሕፈት ቤት ውስጥ ታገለግላለች። አንዱ ወንድ ልጄ ደግሞ ለብዙ ዓመታት ሽማግሌ ሆኖ አገልግሏል።
ከመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ወላጆቻችን በወረስነው አለፍጽምና የተነሳ ሁላችንም የበሽታና የሞት ተገዢዎች ነን። (ሮሜ 5:12) በመሆኑም ከሕመምና ከሥቃይ እፎይ ያልኩበት ጊዜ የለም። በአሁኑ ጊዜ የግራ እግሬን የሚያመኝ አርትራይትስ የተባለው በሽታ ያሠቃየኛል። አልፎ አልፎ በጣም ቢያመኝም ወዲያ ወዲህ ከማለት አላገደኝም። ወደፊትም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱ ችግር እንዳይደርስብኝ እጸልያለሁ። ሥራዬን ለማቆም አልፈልግም። ትልቁ ምኞቴ የይሖዋን ስምና ዓላማ ለማሳወቅ የቻልኩትን ሁሉ እያደረግሁ እስከመጨረሻው ድረስ በአቅኚነት አገልግሎት መቀጠል ነው።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሪታ ከምትባለው ሴት ልጄ ጋር