የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 2/1 ገጽ 21-26
  • በይሖዋና በቃሉ ታመኑ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በይሖዋና በቃሉ ታመኑ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በዓለማዊ ጥበብ አትታመኑ
  • የጥርጣሬን አዝማሚያ ተዋጉ
  • በጋብቻ ውስጥ የይሖዋን መመሪያ መከተል
  • ወጣቶች፣ የአምላክን ቃል አዳምጡ
  • ወጣቶች ሆይ፤ ምን ነገር እየተከታተላችሁ ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • እውነትን የራስህ አድርገኸዋልን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ጥርጣሬ እምነትህን እንዲያጠፋ አትፍቀድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • የላቀ የጥበብ ምንጭ
    መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው?
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 2/1 ገጽ 21-26

በይሖዋና በቃሉ ታመኑ

“ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ።”—መዝሙር 9:10

1. በዚህ ዘመናዊ ዓለም ውስጥም ቢሆን በይሖዋና በቃሉ መታመን የምንችለው ለምንድን ነው?

በዚህ ዘመናዊ ዓለም ውስጥ በአምላክና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ታመኑ የሚል ግብዣ ማቅረብ የማይመስልና ምክንያታዊነት የጎደለው ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ሆኖም ባለፉት ብዙ ዘመናት የአምላክ ጥበብ እውነተኛና ጠቃሚ እንደ ሆነ ተረጋግጧል። ወንድንና ሴትን የፈጠረው አምላክ የጋብቻና የቤተሰብ መሥራች ከመሆኑም በተጨማሪ ከማንኛውም ሰው የበለጠ ፍላጎታችንን ያውቃል። የሰው መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዳልተለወጡ ሁሉ እነዚህን ፍላጎቶች ማሟላት የሚቻሉባቸው ዋነኛ መንገዶች አልተለወጡም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ጥበብ የተሞላበት ምክር ምንም እንኳ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የተጻፈ ቢሆንም የተሳካ ሕይወት ለመምራትና ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ መመሪያ ይሰጣል። በዚህ በጣም በተራቀቀ ሳይንሳዊ ዓለም ውስጥ እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተል ከፍተኛ ደስታ ያስገኛል!

2. (ሀ) የይሖዋ ሕዝቦች የአምላክን ትእዛዝ ማክበራቸው በሕይወታቸው ውስጥ ምን መልካም ፍሬ አስገኝቶላቸዋል? (ለ) ይሖዋ ለእርሱና ለቃሉ ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች ምን ተጨማሪ ነገሮች እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸዋል?

2 በይሖዋ መታመንና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል ምን ጊዜም ቢሆን ተግባራዊ ጥቅሞችን ያስገኛል። በመላው ዓለም የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወት ለዚህ ማረጋገጫ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ጽኑ እምነትና ድፍረት አላቸው። በፈጣሪና በቃሉ መታመናቸው ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቶላቸዋል። (መዝሙር 9:9, 10) የአምላክን ትእዛዛት ማክበራቸው በንጽሕና፣ በሐቀኝነት፣ በታታሪነት፣ ለሕይወትና ለሌሎች ሰዎች ንብረት አክብሮት በማሳየት እንዲሁም በምግብና በመጠጥ ልከኛ በመሆን ረገድ ከሌሎች ሰዎች የተሻሉ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በቤተሰባቸው ውስጥ ተገቢውን ፍቅርና ሥልጠና እንዲሰጡ ገፋፍቷቸዋል። እንግዳ ተቀባዮች፣ ታጋሾች፣ መሐሪዎችና ይቅር ባዮች እንዲሆኑና ሌሎች በርካታ መልካም ባሕርያትን እንዲያሳዩ ረድቷቸዋል። ቁጣ፣ ጥላቻ፣ የነፍስ ግድያ፣ ምቀኝነት፣ ፍርሃት፣ ስንፍና፣ ኩራት፣ ውሸት፣ ስም አጥፊነት፣ ልክስክስነትና የጾታ ብልግና ከሚያስከትሏቸው መጥፎ ውጤቶች ተጠብቀዋል። (መዝሙር 32:10) ሆኖም አምላክ ሕግጋቱን የሚጠብቁ ሰዎች መልካም ነገሮችን እንደሚያገኙ ቃል በመግባት ብቻ አልተወሰነም። ኢየሱስ የክርስትናን መንገድ የሚከተሉ ሰዎችን በተመለከተ ሲናገር “አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር . . . እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም” ብሏል።—ማርቆስ 10:29, 30

በዓለማዊ ጥበብ አትታመኑ

3. ክርስቲያኖች በይሖዋና በቃሉ መታመናቸውን በሚቀጥሉበት ወቅት አንዳንድ ጊዜ ምን ችግሮች ያጋጥሟቸዋል?

3 ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች አንዱ ችግር አምላክ የሚፈልግባቸውን ነገር አቅልለው መመልከታቸው ወይም መርሳታቸው ነው። ከእሱ የበለጠ እንደሚያውቁ ወይም የዚህ የተራቀቀ ዓለም ጥበብ ከአምላክ ጥበብ የላቀና ይበልጥ ዘመናዊ እንደሆነ ማሰብ ይጀምራሉ። የአምላክ አገልጋዮችም በዚህ ዓለም ውስጥ ስለሚኖሩ ይህ ዝንባሌ ሊያድርባቸው ይችላል። ይህም በመሆኑ ሰማያዊ አባታችን ምክሩን እንድንሰማ የሚከተለውን ፍቅራዊ ግብዣ ሲያቀርብልን ተገቢ ማስጠንቀቂያ ጭምር ሰጥቶናል፦ “ልጄ ሆይ፣ ሕጌን አትርሳ፣ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨመሩልሃልና። በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ከክፋትም ራቅ።”—ምሳሌ 3:1, 2, 5-7

4. “የዚች ዓለም ጥበብ” ምን ያህል ተስፋፍቷል? ይህ ጥበብ “በእግዚአብሔር ዘንድ ሞኝነት” የሆነው ለምንድን ነው?

4 ከልዩ ልዩ ምንጮች የዚህ ዓለም ጥበብ በብዛት ይገኛል። አያሌ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ከመሆናቸውም በተጨማሪ “ብዙ መጻሕፍትን ማድረግ ፍጻሜ የለውም።” (መክብብ 12:12) በአሁኑ ጊዜ ኢንፎርሜሽን ሱፐርሃይዌይ ተብሎ የሚጠራው በኮምፒዩተር ተጠቃሚዎች መካከል የሚደረገው የመረጃ ልውውጥ በማንኛውም ርዕስ ላይ እጅግ ሰፊ የሆነ እውቀት እንደሚያቀርብ ተስፋ ይሰጣል። ሆኖም ዓለም ይህን ሁሉ እውቀት ማግኘቱ ከበፊቱ የበለጠ ጥበበኛ እንዲሆን ወይም ችግሮቹን እንዲያስወግድ አላስቻለውም። ከዚህ ይልቅ የዓለም ሁኔታ በየቀኑ በይበልጥ እየተበላሸ በመሄድ ላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የዚች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞኝነት ነው” በማለት የሚናገረው አለ ምክንያት አይደለም።—1 ቆሮንቶስ 3:19, 20

5. መጽሐፍ ቅዱስ ‘የዚህን ዓለም ጥበብ’ በተመለከተ ምን ማስጠንቀቂያዎች ይሰጣል?

5 በዚህ የመጨረሻ ቀን የመደምደሚያ ጊዜያት ቀንደኛ አታላይ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛነት ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው ለማድረግ የውሸት እሩምታዎችን ማዥጎድጎዱ የሚጠበቅ ነገር ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ጽሑፎች የሚያጠኑ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነትና ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ለቁጥር የሚታክቱ ግምታዊ ሐሳቦችን የያዙ መጻሕፍት አሳትመዋል። ጳውሎስ ክርስቲያን ጓደኛውን ሲያስጠነቅቀው “ጢሞቴዎስ ሆይ፣ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፣ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤ ይህ እውቀት አለን ብለው፣ አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና” ብሎታል። (1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21) መጽሐፍ ቅዱስ ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ” ይላል።—ቆላስይስ 2:8

የጥርጣሬን አዝማሚያ ተዋጉ

6. ጥርጣሬዎች በልባችን ውስጥ ሥር እንዳይሰዱ ለመከላከል ንቁ መሆን የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

6 ሰይጣን የሚጠቀምበት ሌላው የተንኮል ዘዴ በአእምሮ ውስጥ ጥርጣሬዎችን መዝራት ነው። በእምነታችን ደከም ያልንበትን ጎን ለማየትና በዚህ ድክመት ለመጠቀም ምን ጊዜም ንቁ ነው። ጥርጣሬ ያደረበት ማንኛውም ግለሰብ ከእንደዚህ ዓይነቶቹ ጥርጣሬዎች በስተጀርባ ያለው ለሔዋን “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን?” በማለት ጥያቄ ያቀረበላት ፍጡር መሆኑን ማስታወስ ይኖርበታል። ፈታኙ በአእምሮዋ ውስጥ ጥርጣሬ ካሳደረባት በኋላ አንድ ውሸት ነገራት፤ እርሷም አመነችው። (ዘፍጥረት 3:1, 4, 5) እንደ ሔዋን እምነታችን በጥርጣሬ እንዳይጠፋ ንቁዎች መሆን ያስፈልገናል። ይሖዋን፣ ቃሉን ወይም ድርጅቱን በተመለከተ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ በልብህ ውስጥ መጉላላት ከጀመረ እምነትህን ወደሚያጠፋበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት ጥርጣሬውን ለማስወገድ ፈጣን እርምጃ ውሰድ።—ከ1 ቆሮንቶስ 10:12 ጋር አወዳድር።

7. ጥርጣሬዎችን ለማስወገድ ምን ማድረግ ይቻላል?

7 ጥርጣሬውን ለማስወገድ ምን ማድረግ ይቻላል? አሁንም ለዚህ መፍትሔ የሚሆነው በይሖዋና በቃሉ መታመን ነው። “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፣ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና።” (ያዕቆብ 1:5, 6፤ 2 ጴጥሮስ 3:17, 18) ስለዚህ ከልብ ወደ ይሖዋ መጸለይ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። (መዝሙር 62:8) ከዚያም በጉባኤው የሚገኙ አፍቃሪ የበላይ ተመልካቾችን እርዳታ ለመጠየቅ አታመንታ። (ሥራ 20:28፤ ያዕቆብ 5:14, 15፤ ይሁዳ 22) እነርሱም ጥርጣሬ እንዲያድርብህ ያደረጉትን ምክንያቶች እንድትገነዘብ ይረዱሃል። ጥርጣሬ ያደረብህ በኩራት ወይም በአንድ የተሳሳተ አስተሳሰብ ሳቢያ ሊሆን ይችላል።

8. ብዙውን ጊዜ የክህደት አስተሳሰብ የሚጀምረው እንዴት ነው? ለዚህ መፍትሔው ምንድን ነው?

8 መርዛማ ጥርጣሬዎችን ያሳደረብህ የከሃዲዎችን ሐሳብ ማንበብህ ወይም ማዳመጥህ ነው ወይስ የዓለም ፍልስፍና? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ጥበብ የተሞላበት ምክር ይሰጠናል፦ “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ። ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፣ ኃጢአተኝነታቸውን ከፊት ይልቅ ይጨምራሉና፣ ቃላቸውም እንደ ጭንቁር [“ጋንግሪን” አዓት] ይባላል [“እየሰፋ ይሄዳል” አዓት]።” (2 ጢሞቴዎስ 2:15-17) ብዙዎቹ ከሃዲዎች ወደ መጥፎ አቅጣጫ ማምራት የጀመሩት በይሖዋ ድርጅት ውስጥ በሚደረግላቸው አያያዝ እንዳልተደሰቱ በመግለጽ እንደሆነ ማወቅ ትኩረት የሚስብ ነው። (ይሁዳ 16) በእምነቱ ላይ ስሕተት መፈላለግ የሚመጣው በኋላ ነው። አንድ ኦፕራሲዮን አድራጊ ሐኪም በጋንግሪን የተያዘውን የአካል ክፍል በቶሎ ቆርጦ እንደሚያስወግድ ሁሉ ማናቸውንም የቅሬታ መንፈስና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ነገሮች የሚከናወኑበትን መንገድ በተመለከተ የሚሰማህን የማጉረምረም ዝንባሌ በፍጥነት ከአእምሮህ ነቅለህ ማውጣት ይኖርብሃል። (ቆላስይስ 3:13, 14) እንደዚህ ያሉትን ጥርጣሬ የሚያመጡ ማናቸውንም ነገሮች አስወግድ።—ማርቆስ 9:43

9. ጥሩ ቲኦክራሲያዊ ፕሮግራም ማውጣት በእምነት ጤናሞች ሆነን ለመቀጠል የሚረዳን እንዴት ነው?

9 ከይሖዋና ከድርጅቱ ጋር ተጣበቅ። “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” በማለት ያለ ምንም ማወላወል የተናገረውን ጴጥሮስን በታማኝነት ምሰለው። (ዮሐንስ 6:52, 60, 66-68) እንደ ትልቅ ጋሻ የሆነ ጠንካራ እምነት እንዲኖርህ የይሖዋን ቃል ለማጥናት ጥሩ ፕሮግራም ይኑርህ፤ ይህም ‘የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች በሙሉ እንድታጠፋ’ ያስችልሃል። (ኤፌሶን 6:16) ለሌሎች ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት በፍቅር በማካፈል በክርስቲያናዊ አገልግሎት በንቃት ተሳተፍ። በየቀኑ ይሖዋ እንዴት እንደባረከህ በአድናቆት አሰላስል። እውነትን በማወቅህ አመስጋኝ ሁን። ጥሩ ክርስቲያናዊ ፕሮግራም አውጥተህ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ማከናወንህ ደስተኛ እንድትሆን፣ እንድትጸና እና ከጥርጣሬዎች ነፃ እንድትሆን ይረዳሃል።—መዝሙር 40:4፤ ፊልጵስዩስ 3:15, 16፤ ዕብራውያን 6:10-12

በጋብቻ ውስጥ የይሖዋን መመሪያ መከተል

10. በተለይ በክርስቲያናዊ ጋብቻ ረገድ መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ መመልከት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ይሖዋ ወንድና ሴት ባልና ሚስት ሆነው አንድ ላይ እንዲኖሩ ዝግጅት ያደረገው ምድር በቀላሉ በሰዎች እንድትሞላ ብቻ ሳይሆን የእነሱም ደስታ እንዲጨምር አስቦ ነበር። ሆኖም ኃጢአትና አለፍጽምና በጋብቻ ዝምድና ላይ ከባድ ችግሮችን አስከትለዋል። ክርስቲያኖች ፍጹማን ስላልሆኑና ዘመናዊው ኑሮ የሚያሳድራቸው ተጽዕኖዎች ስለሚገጥሟቸው ከእነዚህ ችግሮች ነፃ አይደሉም። ሆኖም ክርስቲያኖች በይሖዋና በቃሉ እስከታመኑ ድረስ ጋብቻቸው ሊሳካላቸውና ልጆቻቸውን በጥሩ ሁኔታ ሊያሳድጉ ይችላሉ። በክርስቲያናዊ ጋብቻ ውስጥ ለዓለማዊ ልማዶችና ባሕሪዎች ማስተናገጂያ ቦታ የለም። የአምላክ ቃል “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር፣ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” ይላል።—ዕብራውያን 13:4

11. የጋብቻ ችግሮችን ለማስወገድ ሁለቱም የትዳር ጋደኛሞች ምን መገንዘብ ይኖርባቸዋል?

11 በትዳር ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ፍቅር ይሰፍናል፣ የትዳር ጓደኛሞቹ ግዴታቸውን የሚወጡ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በቤቱ ውስጥ የመተማመን መንፈስ ይኖራል። ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው ይግባባሉ። ሁለቱም የራስነት ሥርዓትን ያከብራሉ። ብዙውን ጊዜ ችግሮች የሚፈጠሩት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ችላ ሲባል ነው። አንድን ለረዥም ጊዜ የቆየ ችግር ለማስወገድ ባልና ሚስቱ በሐቀኝነት በችግሩ ላይ ትኩረት በማድረግ ስሕተቱን የሚያጎሉትን ነገሮች ከመመልከት ይልቅ መንስኤዎቹን ለማወቅ መጣራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ባልና ሚስቱ በወቅቱ ያደረጓቸው ውይይቶች ስምምነት ካላስገኙ አንድ አፍቃሪ የበላይ ተመልካች አድልዎ የሌለበት እርዳታ እንዲያደርግላቸው ሊጠይቁ ይችላሉ።

12. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ በጋብቻ ውስጥ ስለሚያጋጥሙት ስለ የትኞቹ የተለመዱ ችግሮች ምክር ይሰጣል? (ለ) ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ነገሮችን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ መሥራት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

12 ችግሩ የሐሳብ ግንኙነትን፣ አንዱ ለሌላው ስሜት ያለውን አክብሮት፣ ለራስነት ሥርዓት አክብሮት ማሳየትን ወይም ውሳኔዎች የሚሰጡበትን መንገድ የሚመለከት ነውን? ልጆችን ከማሳደግ ወይም በጾታ ፍላጎት ረገድ ሚዛናዊ ከመሆን ጋር ግንኙነት አለውን? ወይስ የቤተሰቡ ባጀት፣ መዝናኛ፣ ቅርርብ፣ ሚስት ሥራ መያዟ አለመያዟ ወይም የምትኖሩበት ቦታ ነውን? ችግሩ ምንም ይሁን ምን መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ በሕጎች አማካኝነት አለበለዚያም በተዘዋዋሪ መንገድ በመሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ምክር ይሰጣል። (ማቴዎስ 19:4, 5, 9፤ 1 ቆሮንቶስ 7:1-40፤ ኤፌሶን 5:21-23, 28-33፤ 6:1-4፤ ቆላስይስ 3:18-21፤ ቲቶ 2:4, 5፤ 1 ጴጥሮስ 3:1-7) ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች የራሳቸው ፍላጎት ብቻ እንዲሟላላቸው ከመጠየቅ ከተቆጠቡና በትዳራቸው ውስጥ ፍቅር በተሟላ መልኩ እንዲገለጽ ካደረጉ ከፍተኛ ደስታ ያገኛሉ። ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች አስፈላጊ ለውጦችን ለማድረግና ነገሮችን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት ይኖራቸዋል። “የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ ብትከታተል፣ ሁሉ ነገር ይሳካልሃል፤ በእግዚአብሔርም ብትታመን ደስተኛ ትሆናለህ።”—ምሳሌ 16:20 የ1980 ትርጉም

ወጣቶች፣ የአምላክን ቃል አዳምጡ

13. ክርስቲያን ወጣቶች በይሖዋና በቃሉ ላይ ጠንካራ እምነት ይዘው ማደግ ቀላል የማይሆንላቸው ለምንድን ነው?

13 ዙሪያቸውን በከበባቸው በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ በእምነት መጠንከር ለወጣት ክርስቲያኖች ቀላል አይደለም። ለዚህ አንዱ ምክንያት የሚሆነው “ዓለም በሞላው በክፉው” ማለትም በሰይጣን ዲያብሎስ መያዙ ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) ወጣቶች መጥፎውን ጥሩ ማስመሰል በሚችለው በዚህ አደገኛ ጠላት ዒላማ ሥር ናቸው። ለእኔ ብቻ የማለት ዝንባሌ፣ የራስ ወዳድነት ምኞቶች፣ ሥነ ምግባር የጎደለውንና ጭካኔ የተሞላበትን ነገር ለማድረግ ከፍተኛ ጉጉት ማሳደር እንዲሁም ተገቢ ባልሆነ መንገድ ተድላን ማሳደድ የመጡት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን የሚሠራው መንፈስ’ ተብሎ ከተገለጸው በየትኛውም ቦታ ተንሰራፍቶ ከሚገኘው አስተሳሰብ ነው። (ኤፌሶን 2:1-3) ሰይጣን በተንኮል በትምህርት ቤት መማርያ መጻሕፍት፣ በአብዛኞቹ ሙዚቃዎች፣ በስፖርትና በሌሎች የመዝናኛ ዓይነቶች ውስጥ ይህን “መንፈስ” እንዲስፋፋ አድርጓል። ወላጆች ልጆቻቸው በይሖዋና በቃሉ ላይ እምነት ኖሯቸው እንዲያድጉ በመርዳት እንደዚህ ያሉትን ተጽዕኖዎች ለመቋቋም ንቁዎች መሆን ይኖርባቸዋል።

14. ወጣቶች “ከጎልማሳነት ምኞት” መሸሽ የሚችሉት እንዴት ነው?

14 ጳውሎስ ወጣት የሥራ ባልደረባው ለነበረው ለጢሞቴዎስ አባታዊ ምክር ሲሰጠው “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፣ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል” ብሎታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:22) ምንም እንኳ ሁሉም ዓይነት “የጎልማሳነት ምኞት” መጥፎ ነው ባይባልም ወጣቶች ለአምላካዊ ተግባራት ጊዜ እስኪያጡ ድረስ በዚህ ነገር እንዳይጠመዱ ከእርሱ ‘መሸሽ’ ይኖርባቸዋል። የአካል ማጎልመሻ እንቅስቃሴ፣ ስፖርት፣ ሙዚቃ፣ መዝናኛ፣ በትርፍ ጊዜ የሚሠሩ አስደሳች ነገሮችና ጉዞ መጥፎ ባይሆኑም በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሰጠናቸው ወጥመድ ሊሆኑብን ይችላሉ። ፍሬ ፈርስኪ የሆነ ወሬ በማውራት ጊዜ ከማባከን፣ ያለ ምንም ሥራ በየቦታው ከመኮልኮል፣ ለጾታ ተገቢ ያልሆነ ስሜት ከማሳደር፣ ከስንፍናና ከስልቹነት እንዲሁም ወላጆቼ አስተሳሰቤንና ስሜቴን አይረዱልኝም ብሎ ከማማረር ሙሉ በሙሉ ሽሹ።

15. ወጣቶች ብቻቸውን በቤታቸው በሚሆኑበት ጊዜ ሁለት ዓይነት ኑሮ እንዲኖሩ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉት የትኞቹ ነገሮች ናቸው?

15 ወጣቶች ብቻቸውን ቤት በሚሆኑበት ጊዜም ሳያውቁት አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል። የጾታ ብልግናን ወይም ዓመፅን የሚያሳዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችንና ቪዲዮዎችን የሚመለከቱ ከሆነ መጥፎ ነገሮችን የመሥራት ምኞት በልባቸው ውስጥ ሊሰርጽ ይችላል። (ያዕቆብ 1:14, 15) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን የምትወድዱ፣ ክፋትን ጥሉ” የሚል ምክር ይሰጣል። (መዝሙር 97:10፤ 115:11) አንድ ሰው ሁለት ዓይነት ኑሮ ለመኖር እየተፈተነ ከሆነ ይሖዋ ነገሩን ያውቀዋል። (ምሳሌ 15:3) ክርስቲያን ወጣቶች መኝታ ቤታችሁን ዙሪያውን ተመልከቱት። በግድግዳ ላይ የሚታዩት በስፖርቱ ወይም በሙዚቃው ዓለም በጣም ታዋቂ የሆኑ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ሰዎች ፎቶዎች ናቸው ወይስ መልካም ነገሮችን የሚያስታውሱ ነገሮች? (መዝሙር 101:3) በቁም ሣጥኖችህ ውስጥ ያሉት ልብሶች ልከኛ ናቸው ወይስ ከልብሶችህ ውስጥ አንዳንዶቹ የዓለምን ቅጥ ያጡ ፋሽኖች ያንጸባርቃሉ? መጥፎ የሆነውን ነገር ሞክረህ ለማየት የምትፈተን ከሆነ ዲያብሎስ በረቀቁ ዘዴዎች ተጠቅሞ ሊያጠምድህ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጠን ኑሩ ንቁም፣ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና” በማለት ጥበብ የተሞላበት ምክር ይሰጠናል።—1 ጴጥሮስ 5:8

16. የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አንድ ወጣት ይሖዋን፣ ወላጆቹንና ወንድሞችን የሚያኮራ እንዲሆን ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው?

16 መጽሐፍ ቅዱስ በጓደኛ ምርጫችሁ ረገድ ጥንቃቄ እንድታደርጉ ያሳስባችኋል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ጓደኞቻችሁ ይሖዋን የሚፈሩ መሆን ይኖርባቸዋል። ለእኩዮች ተጽዕኖ አትንበርከኩ። (መዝሙር 56:11፤ ምሳሌ 29:25) ፈሪሃ አምላክ ላላቸው ወላጆቻችሁ ታዘዙ። (ምሳሌ 6:20-22፤ ኤፌሶን 6:1-3) ከሽማግሌዎች መመሪያና ማበረታቻ ለማግኘት ጣሩ። (ኢሳይያስ 32:1, 2) አእምሮአችሁንና ልባችሁን በመንፈሳዊ ቁም ነገሮችና ግቦች ላይ አድርጉ። መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የምትችሉባቸውንና በጉባኤ ሥራዎች የምትካፈሉባቸውን አጋጣሚዎች ፈልጉ። አንዳንድ ነገሮችን መሥራት ተማሩ። በእምነት ጤናሞችና ጠንካሮች ሆናችሁ እደጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ በይሖዋ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር የምትበቁ ዓይነት ሰዎች መሆናችሁን ታስመሰክራላችሁ! ሰማያዊው አባታችን ይኮራባችኋል። ምድራዊ ወላጆቻችሁ ይደሰቱባችኋል። ለክርስቲያን ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ደግሞ የብርታት ምንጭ ትሆኑላቸዋላችሁ። ይህ ከሁሉ የተሻለ ነገር ነው!—ምሳሌ 4:1, 2, 7, 8

17. በይሖዋና በቃሉ የሚታመኑ ሰዎች ምን በረከቶችን ያገኛሉ?

17 መዝሙራዊው በመንፈስ አነሣሽት እንዲህ የሚል ግጥም ጽፏል፦ “እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም። የሠራዊት አምላክ ሆይ፣ በአንተ የታመነ ሰው ምስጉን [“ደስተኛ” አዓት] ነው።” (መዝሙር 84:11, 12) አዎን፣ በይሖዋና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚታመኑ ሰዎች ሁሉ ደስታና የተሳካ ሕይወት ያገኛሉ። ከሐዘንና አስከፊ ከሆነ ውድቀት ይድናሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:14, 16, 17

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ክርስቲያኖች “በዚች ዓለም ጥበብ” መታመን የሌለባቸው ለምንድን ነው?

◻ አንድ ግለሰብ ጥርጣሬ ካደረበት ምን ማድረግ ይኖርበታል?

◻ ነገሮችን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ መሥራት በጋብቻ ውስጥ የተሳካ ሕይወትና ደስታ የሚያስገኘው ለምንድን ነው?

◻ መጽሐፍ ቅዱስ “ከጎልማሳነት ምኞት” እንዲሸሹ ወጣቶችን የሚረዳቸው እንዴት ነው?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች ‘የዚህን ዓለም ጥበብ’ እንደ ሞኝነት የሚመለከቱት ከመሆናቸውም በተጨማሪ መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋና ወደ ቃሉ ይመለከታሉ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋና በቃሉ የሚታመኑ ቤተሰቦች የተሳካ ሕይወትና ደስታ አግኝተዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ