በጥሩም ሆነ በመጥፎ ጊዜ በአምላክ አገልግሎት አንድ መሆን
ሚሸልና ባቤት ሙለር እንደተናገሩት
“አንድ አሳዛኝ ዜና ልነግራችሁ ነው” አለ ዶክተሩ። “ወደ አፍሪካ ተመልሰን የሚስዮናዊነት ሥራችንን እንቀጥላለን የሚለውን ሐሳብ እርሱት።” ባለቤቴን ባቤትን ትኩር ብሎ እየተመለከተ “የጡት ካንሰር ይዞሻል” አላት።
ሁለታችንም ክው ብለን ቀረን። በአእምሯችን ውስጥ ብዙ ነገሮች ተመላለሱ። ወደ ዶክተሩ የሄድነው ይህ የመጨረሻ ምርመራ ይሆናል ብለን አስበን ነበር። በምዕራብ አፍሪካ ወደምትገኘው ወደ ቤኒን ለመሄድ የአውሮፕላን ትኬት ቆርጠን ነበር። በአንድ ሳምንት ውስጥ ወደዚያ እንመለሳለን ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። በ23 ዓመት የጋብቻ ሕይወታችን ጥሩም ሆኑ መጥፎ ጊዜያትን አብረን አሳልፈናል። ግራ መጋባትና ፍርሃት ቢያድርብንም ካንሰርን ለመዋጋት ራሳችንን አዘጋጀን።
እስቲ ከመጀመሪያው እንነሣ። ሚሸል የተወለደው በመስከረም 1947 ሲሆን ባቤት ደግሞ በነሐሴ 1945 ነው። ያደግነው ፈረንሳይ ውስጥ ሲሆን በ1967 ደግሞ ተጋባን። ፓሪስ ውስጥ እንኖር ነበር። በ1968 የመጀመሪያዎቹ ወራት አንድ ጠዋት ባቤት ሥራ ሳትሄድ ረፈደባት። አንዲት ሴት ወደ ቤት መጣችና አንድ ሃይማኖታዊ ብሮሹር እንድትወስድ ጋበዘቻት፤ እርሷም ብሮሹሩን ተቀበለቻት። ከዚያም ሴትየዋ “ከአንቺና ከባለቤትሽ ጋር ለመነጋገር ከባለቤቴ ጋር ተመልሼ ልምጣ?” ስትል በትሕትና ጠየቀቻት።
ባቤት ስለ ሥራዋ በማሰብ ላይ ነበረች። ሴትዮዋ ቶሎ እንድትሄድላት ስለፈለገች “እሺ፣ እሺ!” አለቻት።
ሚሸል ከዚያ በኋላ ስለተፈጸመው ሁኔታ እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ስለ ሃይማኖት ምንም ፍላጎት ባይኖረኝም ብሮሹሩ ትኩረቴን ስለሳበው አነበብኩት። ከጥቂት ቀናት በኋላ ጆስሊን ሊሞን የተባለችው ሴት ክሎድ ከተባለው ባልዋ ጋር ተመልሳ መጣች። ክሎድ በመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀሙ የተካነ ሰው ነበር። ጥያቄዎቼን ሁሉ መለሰልኝ። በጣም ገረመኝ።
“ባቤት አጥባቂ ካቶሊክ የነበረች ብትሆንም መጽሐፍ ቅዱስ አልነበራትም፤ ይህ በካቶሊኮች ዘንድ የተለመደ ነው። የአምላክን ቃል በማግኘቷና በማንበቧ በጣም ተደሰተች። ከዚህ ቀደም የተማርናቸው አብዛኞቹ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ሐሰት መሆናቸውን ከጥናታችን ተገነዘብን። ስለምንማራቸው ነገሮች ለዘመዶቻችንና ለጓደኞቻችን መናገር ጀመርን። በጥር 1969 የተጠመቅን የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዘጠኝ ዘመዶቻችንና ጓደኞቻችን ተጠመቁ።”
ሰባኪዎች በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል
ከተጠመቅን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ‘ልጅ የለንም። ለምን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት አንጀምርም?’ በማለት አሰብን። ስለዚህ በ1970 ሥራችንን ትተን የዘወትር አቅኚነት አገልግሎት ጀመርንና በነቬኽ አቅራቢያ በማዕከላዊው ፈረንሳይ ወደምትገኘው ማኚ ሎኽም ወደምትባለው አነስተኛ የገጠር ከተማ ተዛወርን።
አስቸጋሪ ምድብ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚፈልጉ ሰዎች ማግኘት ቀላል አልነበረም። ሰብዓዊ ሥራ ማግኘት ስላልቻልን በቂ ገንዘብ አልነበረንም። አንዳንድ ጊዜ የምንበላው ድንች ብቻ ነበር። በክረምት ወቅት ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች ይወርድ ነበር። በዚያ ስፍራ ያሳለፍነውን ጊዜ የሰባቱ ከሲታ ላሞች ዘመን በማለት እንጠራው ነበር።—ዘፍጥረት 41:3
ይሁን እንጂ ይሖዋ ረድቶናል። አንድ ቀን ምግብ ሊያልቅብን ሲል ፖስተኛው በትልቅ ዕቃ ከባቤት እህት የተላከልንን ቺዝ አመጣልን። በሌላ ቀን ከአገልግሎት ወደ ቤት ስንመለስ በመኪና 500 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ወደ እኛ የመጡ ጥቂት ወንድሞችን አገኘን። እነዚህ ወንድሞች ያሉትን ችግሮች ስለ ሰሙ ሁለት መኪና ሙሉ ምግብ ይዘውልን መጥተው ነበር።
ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ማኅበሩ ልዩ አቅኚዎች አድርጎ ሾመን። ቀጣዮቹን አራት ዓመታት በወቅቱ ትኻይ ትባል በነበረችው በነቬኽ፣ በመጨረሻም በሞንቲኚ ሌሜትዝ ውስጥ አገለገልን። በ1976 ሚሸል በደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ ውስጥ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እንዲያገለግል ተሾመ።
ከሁለት ዓመታት በኋላ ለወረዳ የበላይ ተመልካቾች ትምህርት በሚሰጥበት ወቅት ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በውጭ አገር ሚስዮናውያን ሆነን እንድናገለግል እንደተጋበዝን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰን፤ ደብዳቤው ከቻድና ከቡርኪና ፋሶ (በዚያን ጊዜ አፐር ቮልታ ትባል ነበር) አንዱን መምረጥ እንደምንችል ይገልጽ ነበር። ቻድን መረጥን። ወዲያው በታሂቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር እንድንሠራ እንደተመደብን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰን። ትልቅ አህጉር በሆነችው በአፍሪካ ውስጥ ለማገልገል ጠይቀን ነበር፤ ሆኖም በአንዲት ትንሽ ደሴት ውስጥ ተመደብን!
በደቡብ ፓስፊክ ውስጥ ማገልገል
ታሂቲ በሐሩር ክልል በደቡብ ፓስፊክ ውስጥ የምትገኝ ውብ ደሴት ናት። እዚያ ስንደርስ መቶ የሚሆኑ ወንድሞች እኛን ለመቀበል አውሮፕላን ማረፊያው ድረስ መጥተው ነበር። እቅፍ አበባ ይዘው ተቀበሉን። ከፈረንሳይ ተነሥተን ረጅም ጉዞ በማድረጋችን ምክንያት ደክሞን የነበረ ቢሆንም በጣም ተደሰትን።
ታሂቲ ከደረስን ከአራት ወራት በኋላ ከበስተጀርባዋ ደረቅ ኮከነት በጫነች አንድ አነስተኛ በነፋስ የምትንቀሳቀስ ጀልባ ላይ ተሳፈርን። ከአምስት ቀናት በኋላ በማርኪዩሳስ ደሴቶች ውስጥ ወደምትገኘው አዲስ የሥራ ምድባችን ማለትም ወደ ኑኩ ሂቫ ደሴት ደረስን። በደሴቲቱ ውስጥ 1,500 የሚያህሉ ሰዎች ቢኖሩም ወንድሞች አልነበሩም። እኛ ብቻ ነበርን።
በዚያን ጊዜ እንደ አሁኑ ቴክኖሎጂ አልተስፋፋም ነበር። ከኮንክሪትና ከቀርክሃ በተሠራ ትንሽ ቤት ውስጥ እንኖር ነበር። መብራት አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ የሚሠራ ቧንቧ ቢኖረንም ውኃው ንጹሕ አልነበረም። አብዛኛውን ጊዜ በውኃ ማጠራቀሚያ ውስጥ በተከማቸ የዝናብ ውኃ እንጠቀም ነበር። ከአቧራማ የእግር መንገዶች በስተቀር የመኪና መንገዶች አልነበሩም።
በደሴቱ ውስጥ ራቅ ወዳለ ስፍራ ለመሄድ ከፈለግን ፈረሶች መከራየት ነበረብን። ኮርቻዎቹ ከእንጨት የተሠሩ በመሆናቸው በተለይ ፈረስ ጋልባ ለማታውቀው ለባቤት አይመቹም ነበር። መንገድ የሚዘጉብንን ቀርከሃዎች ለመቁረጥ ቆንጨራ ይዘን እንሄድ ነበር። በፈረንሳይ ውስጥ ካሳለፍነው ሕይወት ጋር ሲተያይ ከፍተኛ ልዩነት ነበረው።
ምንም እንኳ ሁለታችን ብቻ የምንገኝ ብንሆንም እሑድ እሑድ ስብሰባ እናደርግ ነበር። የምንሰበሰበው ሁለታችን ብቻ ስለሆንን ሌሎቹን ስብሰባዎች አናደርግም ነበር። ከዚህ ይልቅ በስብሰባ ላይ የሚወሰደውን ትምህርት አንድ ላይ ሆነን እናነብብ ነበር።
ከጥቂት ወራት በኋላ ግን በዚህ መንገድ መቀጠል ጥሩ እንዳልሆነ ወሰንን። ሚሸል ስለዚህ ሁኔታ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ባቤትን ‘ሥርዓታማ በሆነ መንገድ መልበስ ይኖርብናል። አንቺ እዚያ ትቀመጪያለሽ፤ እኔ እዚህ እቀመጣለሁ። እኔ በጸሎት ከከፈትኩ በኋላ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና የአገልግሎት ስብሰባ እናደርጋለን። ክፍሉ ውስጥ ያለሽው አንቺ ብቻ ብትሆኝም እንኳ እኔ ጥያቄዎችን ስጠይቅ አንቺ ትመልሻለሽ’ አልኳት። ጉባኤ ከሌለ በቀላሉ በመንፈሳዊ መድከም ስለሚመጣ እንደዚህ ማድረጋችን ጠቅሞናል።”
ሰዎች ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን መምጣት የጀመሩት ከብዙ ጊዜ በኋላ ነው። የመጀመሪያዎቹን ስምንት ወራት ሁለታችን ብቻ ሆነን ተሰብስበናል። ከዚያ በኋላ አንድ፣ ሁለት አንዳንዴ ደግሞ ሦስት ሰዎች ከእኛ ጋር ይሰበሰቡ ነበር። አንድ ዓመት የጌታ እራት በዓል ሁለታችን ብቻ ሆነን ማክበር ጀመርን። ከአሥር ደቂቃ በኋላ ግን ጥቂት ሰዎች ስለመጡ ንግግሩን አቁሜ እንደገና ጀመርኩ።
ዛሬ በማርኪዩሳስ ደሴቶች ውስጥ 42 አስፋፊዎችና 3 ጉባኤዎች ይገኛሉ። ሆኖም አብዛኛውን ሥራ የሠሩት እኛን የተኩት ወንድሞች ናቸው፤ በአሁኑ ወቅት በዚያን ጊዜ ካነጋገርናቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የተጠመቁ ናቸው።
ወንድሞቻችን ውድ ናቸው
በኑኩ ሂቫ ሳለን ትዕግሥትን ተምረናል። በጣም መሠረታዊ ከሆኑ ፍላጎቶቻችን በስተቀር ሌላ ማንኛውንም ነገር ለማግኘት የግድ መጠበቅ ነበረብን። ለምሳሌ ያህል አንድ መጽሐፍ ለማግኘት ከፈለጋችሁ ደብዳቤ ከጻፋችሁ በኋላ መጽሐፉ እስኪመጣ ድረስ ሁለት ወይም ሦስት ወራት ለመጠበቅ ትገደዳላችሁ።
ሌላው የተማርነው ትልቁ ነገር ወንድሞቻችን ውድ መሆናቸውን ነበር። ወደ ታሂቲ ሄደን ስብሰባ ላይ በምንገኝበት ወቅት ወንድሞች ሲዘምሩ ስንመለከት እናለቅስ ነበር። እርግጥ ከአንዳንድ ወንድሞች ጋር መግባባት ሊያስቸግር ይችል ይሆናል፤ ብቻችሁን ስትሆኑ ግን ከወንድሞች ጋር መሆን ምን ያህል እንደሚያስደስት ትገነዘባላችሁ። በ1980 ማኅበሩ ወደ ታሂቲ ተመልሰን በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እንድናገለግል ወሰነ። እዚያም በወንድሞች ሞቅ ያለ የእንግዳ ተቀባይነት ስሜትና ለስብከቱ ሥራ ባላቸው ፍቅር እጅግ ተበረታታን። በታሂቲ ውስጥ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ለሦስት ዓመታት አገለገልን።
ከደሴት ወደ ደሴት
ከዚያም በፓስፊክ ውስጥ በምትገኝ ራይቲያ በምትባል ሌላ ደሴት ውስጥ ወደሚገኝ አንድ የሚስዮናውያን መኖሪያ ተዛወርን። እዚያም ለሁለት ዓመታት ቆየን። ከራይቲያ ቀጥሎ ደግሞ በቱዋሞቱ ደሴቶች ውስጥ በወረዳ ሥራ እንድናገለግል ተመደብን። ከ80 የቱዋሞቱ ደሴቶች ውስጥ 25ቱን በጀልባ እየሄድን ጎብኝተናቸዋል። ይህ ለባቤት አስቸጋሪ ነበር። ባቤት በጀልባ በሄደች ቁጥር ትታመም ነበር።
ባቤት እንዲህ በማለት ስለሁኔታው ተናግራለች፦ “በጣም አስቸጋሪ ነበር! በጀልባ ውስጥ በምናሳልፋቸው ጊዜያት ሁሉ እታመማለሁ። በባሕር ላይ አምስት ቀናት ካሳለፍን አምስቱንም ቀናት እታመማለሁ። ምንም ዓይነት መድኃኒት አያሽለኝም። ሆኖም ቢያመኝም እንኳ ባሕር በጣም አስደሳች እንደሆነ አምናለሁ። በባሕር ውስጥ እጅግ አስደናቂ ነገሮች ልታዩ ትችላላችሁ። ዶልፊኖች ከጀልባው ጋር ይሽቀዳደማሉ። እጃችሁን ካጨበጨባችሁ ብዙውን ጊዜ ከውኃው ወደ ውጭ ይዘላሉ!”
በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ለአምስት ዓመታት ካገለገልን በኋላ እንደገና በታሂቲ ውስጥ ለሁለት ዓመታት እንድናገለግል ተመደብንና በስብከቱ ሥራ አስደሳች ጊዜ አሳለፍን። በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ጉባኤያችን ከ35 ወደ 70 አስፋፊዎች አደገ። መጽሐፍ ቅዱስ ከእኛ ጋር ያጠኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል አሥራ ሁለቱ ከታሂቲ ከመልቀቃችን ጥቂት ቀደም ብለው ተጠመቁ። በአሁኑ ጊዜ ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ የጉባኤ ሽማግሌዎች ሆነዋል።
በጠቅላላው በደቡብ ፓስፊክ ውስጥ 12 ዓመታት አሳልፈናል። ከዚያ በኋላ ጉባኤዎች ስለበረቱ በደሴቶቹ ውስጥ ሚስዮናውያን እንደማያስፈልጉ የሚገልጽ ደብዳቤ ከማኅበሩ ደረሰን። ወደ ታሂቲ በገባንበት ወቅት 450 አስፋፊዎች የነበሩ ሲሆን ከዚያ ስንወጣ ከ1,000 በላይ ሆነው ነበር።
በመጨረሻ አፍሪካ!
ወደ ፈረንሳይ ተመለስን፤ ከአንድ ወር ተኩል በኋላ ማኅበሩ በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው በቤኒን ውስጥ አዲስ የሥራ መስክ ሰጠን። ከ13 ዓመት በፊት ወደ አፍሪካ ለመሄድ ጓጉተን ስለነበር በጣም ተደሰትን።
ኀዳር 3, 1990 ቤኒን ደረስን። ለ14 ዓመታት የቆየው የመንግሥቱ ስብከት እገዳ ከተነሣ በኋላ ቤኒን ውስጥ ከገቡት የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን መካከል ነበርን። ይህ በጣም የሚያስደስት ነገር ነበር። ኑሮ ከፓስፊክ ደሴቶች ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ራሳችንን ከሁኔታዎቹ ጋር የማለማመድ ችግር አላጋጠመንም። ሕዝቡ የወዳጅነት መንፈስ ያለውና እንግዳ ተቀባይ ነው። በመንገድ ላይ ያገኛችሁትን ሰው ሁሉ አስቁማችሁ ማነጋገር ትችላላችሁ።
ቤኒን ከደረስን ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ባቤት በጡቷ ላይ አንድ ያበጠ ነገር ተመለከተች። ስለዚህ አዲስ በተቋቋመው ቅርንጫፍ ቢሮ አቅራቢያ ወደሚገኝ አንድ አነስተኛ ክሊኒክ ሄድን። ዶክተሩ ምርመራ ካደረገላት በኋላ በአስቸኳይ ቀዶ ሕክምና ማድረግ አለባት አለ። በሚቀጥለው ቀን ወደ ሌላ ክሊኒክ ስንሄድ አንዲት አውሮፓዊት ዶክተር አገኘን። ዶክተሯ ከፈረንሳይ የመጣች ጋይናኮሎጂስት ነበረች። እርሷም በፍጥነት ወደ ፈረንሳይ ሄደን ባቤት ቀዶ ሕክምና ማድረግ እንዳለባት ገለጸችልን። ከሁለት ቀናት በኋላ በአውሮፕላን ወደ ፈረንሳይ ሄድን።
ከቤኒን በመውጣታችን በጣም አዘንን። በአገሪቱ ውስጥ አዲስ በተገኘው ነፃነት ምክንያት ወንድሞች አዲስ ሚስዮናውያን በማግኘታቸው በጣም ተደስተው ነበር። እኛም እዚያ በመሆናችን ደስ ብሎን ነበር። ስለዚህ በአገሪቱ ውስጥ ለጥቂት ሳምንታት ከቆየን በኋላ በመውጣታችን ተረበሽን።
ፈረንሳይ ስንደርስ ቀዶ ሕክምና የሚያደርገው ዶክተር ባቤትን ከመረመራት በኋላ ቀዶ ሕክምና ማድረግ እንደሚያስፈልጋት አረጋገጠልን። ዶክተሮች ወዲያውኑ አነስተኛ ቀዶ ሕክምና ካደረጉላት በኋላ ባቤት በሚቀጥለው ቀን ከሆስፒታል እንድትወጣ ፈቀዱ። ጉዳዩ በዚህ ያልቃል ብለን አስበን ነበር።
ከስምንት ቀናት በኋላ ቀዶ ሕክምና ወዳደረገላት ዶክተር ሄድን። ዶክተሩ ባቤት የጡት ካንሰር እንደያዛት መርዶ ያረዳን በዚህ ጊዜ ነበር።
ባቤት በዚያን ጊዜ የተሰማትን ስሜት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “በመጀመሪያ የሚሸልን ያህል አልተረበሽኩም ነበር። ይህን መርዶ በሰማሁ ማግስት ግን በድን ሆንኩ። ማልቀስ አልቻልኩም። ፈገግ ማለት አልቻልኩም። እሞታለሁ ብዬ አሰብኩ። ለእኔ ካንሰር ማለት ሞት ማለት ያህል ነው። ማድረግ የሚገባንን ሁሉ አድርገን በሽታውን መዋጋት ይኖርብናል የሚል አመለካከት ነበረኝ።”
ካንሰርን መዋጋት
አርብ ይህን መርዶ ሰምተን ማክሰኞ ባቤት ቀዶ ሕክምና እንዲደረግላት ተወሰነ። በዚህ ወቅት ያረፍነው ባቤት እህት ጋር ነበር፤ ሆኖም እሷም ጭምር ስለታመመች በአነስተኛ ክፍሏ ውስጥ ለመቆየት አልቻልንም።
ወደ የት እንደምንሄድ ግራ ገባን። ከዚያም ቀደም ሲል እቤታቸው አርፈን የነበርንባቸው ኢቭ እና ብሪጂት ሜርዳ የተባሉ ባልና ሚስት ትዝ አሉን። እነዚህ ባልና ሚስት ጥሩ መስተንግዶ አድርገውልን ነበር። ስለዚህ ለኢቭ ስልክ ደወልንለትና ባቤት ቀዶ ሕክምና ስለሚደረግላት የምናርፍበት ቦታ እንዳላገኘን ነገርነው። በተጨማሪም ሚሸል ሥራ እንደሚፈልግ ገለጽንለት።
ኢቭ በቤቱ አካባቢ የሚሠራውን ሥራ ለሚሸል ሰጠው። ወንድሞች በአሳቢነት ለእኛ ብዙ እርዳታ ከማድረጋቸውም በላይ አበረታተውናል። በተጨማሪም የገንዘብ ድጋፍ አድርገውልናል። ማኅበሩ የባቤትን የሕክምና ወጪዎች ሸፍኗል።
ከባድ ቀዶ ሕክምና ነበር። ዶክተሮቹ ጡቷን መቁረጥና በጡቷ አካባቢ የሚገኙትን እጢዎች ማስወገድ ነበረባቸው። ወዲያውኑ በመድኃኒት ሕክምና ጀመሩላት። ከአንድ ሳምንት በኋላ ባቤት ከሆስፒታል ለመውጣት ብትችልም በየሦስት ሳምንቱ ለቀጣይ ሕክምና መመላለስ ነበረባት።
ባቤት በሕክምና ላይ በነበረችበት ወቅት በጉባኤው ውስጥ የነበሩ ወንድሞች ትልቅ እርዳታ አድርገውልናል። የጡት ካንሰር የነበረባት አንዲት እህት እጅግ አበረታታናለች። ባቤት ምን መጠበቅ እንዳለባት ከነገረቻት በኋላ በጣም አጽናናቻት።
ሆኖም ወደፊት እንዴት እንደምንኖር በማሰብ በጣም እንጨነቅ ነበር። ሚሸልና ዣኔት ሴለሪዬ ስለዚህ ሁኔታ በመረዳታቸው ወደ አንድ ሬስቶራንት ወስደው ጋበዙን።
የሚስዮናዊነት አገልግሎትን ለማቆም እንደተገደድንና ወደ አፍሪካ ፈጽሞ ለመመለስ እንደማንችል ነገርናቸው። ሆኖም ወንድም ሴለሪዬ “ምን አልክ? አቁሙ ያላችሁ ማነው? የአስተዳደር አካል ወይስ በፈረንሳይ የሚገኙ ወንድሞች?” የሚል ጥያቄ አቀረበልን።
“ማንም አላለንም። እኔ ራሴ ነኝ” ስል መለስኩለት።
“የለም! ተመልሳችሁ ትሄዳላችሁ!” አለ ወንድም ሴለሪዬ።
ባቤት በመድኃኒት የሚደረግላትን ሕክምና ከጨረሰች በኋላ የጨረር ሕክምና ተሰጣትና በነሐሴ 1991 ሕክምናው አጠናቀቀች። ዶክተሮች ባቤት በተለያዩ ጊዜያት ቋሚ ምርመራ ለማድረግ ወደ ፈረንሳይ መምጣት ከቻለች ወደ አፍሪካ ተመልሰን መሄድ እንደምንችል ገለጹልን።
ወደ ቤኒን መመለስ
ስለዚህ ወደ ሚስዮናዊነት አገልግሎት እንድንመለስ ፈቃድ ለመጠየቅ በብሩክሊን ወደሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ጻፍን። የሚሰጡንን መልስ ለመስማት ጓጉተን ነበር። ቀኑ አልሄድ አለን። በመጨረሻ ሚሸል ብዙ መታገሥ ስላልቻለ ወደ ብሩክሊን ስልክ ደውሎ ደብዳቤያችን ደርሷቸው እንደሆነ ጠየቃቸው። ጉዳዩን እንዳሰቡበትና ወደ ቤኒን መመለስ እንደምንችል ነገሩን! ይሖዋን በጣም አመሰገንነው!
የሜርዳ ቤተሰብ ትልቅ የደስ ደስ ግብዣ አዘጋጀ። በኅዳር 1991 ወደ ቤኒን ስንመለስ ወንድሞች ትልቅ ድግስ አድርገው ተቀበሉን።
ባቤት አሁን የተሻላት ትመስላለች። አልፎ አልፎ የተሟላ ምርመራ ለማድረግ ወደ ፈረንሳይ ስንሄድ ዶክተሮች የካንሰር ምልክት አላገኙባትም። ወደ ሚስዮናዊነት ሥራችን በመመለሳችን በጣም ተደስተናል። በቤኒን ውስጥ እንደምናስፈልግ ይሰማናል። ይሖዋም ሥራችንን ባርኮልናል። እዚህ ከተመለስን በኋላ 14 ሰዎች እንዲጠመቁ ረድተናል። በአሁኑ ጊዜ ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ የዘወትር አቅኚዎች ሲሆኑ አንዱ ዲያቆን ሆኖ ተሹሟል። በተጨማሪም ትንሽ የነበረው ጉባኤያችን አድጎ ሁለት ጉባኤ ሆኖ ሲከፈል ተመልክተናል።
ባለፉት ዓመታት ባልና ሚስት ሆነን ይሖዋን አገልግለናል። ብዙ በረከቶችን ከማግኘታችንም በተጨማሪ በርካታ አስደናቂ ሕዝቦችን አውቀናል። ሆኖም ይሖዋ በችግር ጊዜ እንድንጸና አሠልጥኖናል እንዲሁም ኃይል ሰጥቶናል። ብዙውን ጊዜ እንደ ኢዮብ አንዳንድ ነገሮች ለምን እንደደረሱብን ባናውቅም እንኳ ምን ጊዜም ቢሆን ይሖዋ ከጎናችን እንደሆነ ተገንዝበናል። ይህም የአምላክ ቃል “የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፣ ጆሮውም ከመስማት አልደነቆረችም” እንደሚለው ነው።—ኢሳይያስ 59:1
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሚሸልና ባቤት ሙለር በቤኒን ውስጥ የአገር ልብስ ለብሰው
[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች
በሐሩር ክልል በምትገኘው በታሂቲ ውስጥ ባሉት ፖሊኔዣውያን መካከል የሚስዮናዊነት ሥራ ሲካሄድ