የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ፊልጶስ አንድ ኢትዮጵያዊ ባለ ሥልጣን አጠመቀ
አንድ ኢትዮጵያዊ በሰረገላው እየተጓዘ ሳለ ጊዜውን በጥበብ እየተጠቀመበት ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሰዎች በሚጓዙበት ወቅት ብዙውን ጊዜ እንደሚያደርጉት ድምፁን ከፍ አድርጎ ያነብብ ነበር። ይህ ሰው “ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት” ባለ ሥልጣን ነበር።a ‘በገንዘብዋም ሁሉ ላይ አዛዥ’ ስለነበረ የገንዘብ ሚንስትር ነበር ለማለት ይቻላል። ይህ ባለ ሥልጣን ከአምላክ ቃል እውቀት ለመቅሰም ያነብብ ነበር።—ሥራ 8:27, 28
በአቅራቢያው ወንጌላዊው ፊልጶስ ነበር። ወደዚህ ቦታ የመራው አንድ መልአክ ሲሆን አሁን ደግሞ “ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ” ተባለ። (ሥራ 8:26, 29) ፊልጶስ ‘ይህ ሰው ማን ነው? የሚያነብበው ምንድን ነው? ወደ እርሱ የተላክሁት ለምንድን ነው?’ በማለት ራሱን ጠይቆ ነበር ብለን መገመት እንችላለን።
ፊልጶስ ከሰረገላው ጎን ሲሮጥ ኢትዮጵያዊው የሚከተሉትን ቃላት ሲያነብ ሰማው፦ “እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፣ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፣ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል?”—ሥራ 8:32, 33
ፊልጶስ ወዲያውኑ ጥቅሱን አወቀው። የሚያነብበው ከኢሳይያስ መጽሐፍ ነበር። (ኢሳይያስ 53:7, 8) ኢትዮጵያዊው በሚያነበው ነገር ግራ ተጋብቶ ነበር። ፊልጶስ “በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” ብሎ በመጠየቅ ውይይት ጀመረ። ኢትዮጵያዊውም “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” በማለት መለሰ። ከዚያም ሰረገላው ላይ እንዲወጣ ፊልጶስን ለመነው።—ሥራ 8:30, 31
“እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው?”
ኢትዮጵያዊው ፊልጶስን “እባክህ፣ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ?” አለው። (ሥራ 8:34) በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሱት “በግ” ወይም ‘ባሪያ’ የሚሉት መለያዎች ለረጅም ጊዜ ምሥጢር ስለነበሩ ኢትዮጵያዊው ግራ መጋባቱ አያስደንቅም። (ኢሳይያስ 53:11) ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው “ስለ ኢየሱስ ወንጌል” ሲሰብክለት ትንቢቱ ግልጽ ሆኖለት መሆን አለበት! ትንሽ እንደተጓዙ ኢትዮጵያዊው “እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው?” አለ። ፊልጶስ ወዲያውኑ አጠመቀው።—ሥራ 8:35-38
ይህ የችኮላ እርምጃ ነበርን? በፍጹም! ኢትዮጵያዊው ወደ አይሁድ እምነት የተለወጠ ሰው ነበር።b ስለዚህ ኢትዮጵያዊው ስለ መሲሑ የተነገሩትን ትንቢቶች ጨምሮ የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት የነበረው ቀድሞውኑ ይሖዋን የሚያመልክ ሰው ነበር። ሆኖም የተሟላ እውቀት አልነበረውም። ኢትዮጵያዊው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚጫወተው ሚና ይህን የመሰለ ጠቃሚ ትምህርት ሲያገኝ አምላክ ከእርሱ ምን እንደሚፈልግ ተገንዝቦና የሚፈለግበትን ለመፈጸም ዝግጁ ሆኖ ነበር። መጠመቁ ተገቢ ነበር።—ማቴዎስ 28:18-20፤ 1 ጴጥሮስ 3:21
ከዚያም “የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው።” ሌላ ሥራ ለማከናወን ሄደ። ኢትዮጵያዊውም ‘ደስ እያለው ጉዞውን ቀጠለ።’—ሥራ 8:39, 40
ከዚህ የምናገኘው ትምህርት
የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ልበ ቅን ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውነት እንዲያውቁ የመርዳት ኃላፊነት አለብን። ብዙዎች በጉዞ ላይ ወይም በሌሎች መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች ምሥራቹን ለሌሎች በማካፈል በኩል ተሳክቶላቸዋል። በመንግሥቱ ስብከት አማካኝነት በየዓመቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ መወሰናቸውን በጥምቀት ያሳያሉ።
እርግጥ ነው፣ አዲሶች ለጥምቀት ከመጠን በላይ መቻኮል የለባቸውም። መጀመሪያ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት አለባቸው። (ዮሐንስ 17:3) ከዚያም ንስሐ መግባትና መጥፎ ጠባያቸውን አስተካክለው የአምላክን የአቋም ደረጃዎች ማሟላት አለባቸው። (ሥራ 3:19) በተለይ መጥፎ አስተሳሰብ ወይም ጠባይ ሥር ሰድዶ ከነበረ እንዲህ ማድረጉ ጊዜ ይወስዳል። አዳዲሶች ክርስቲያን ደቀ መዝሙር መሆን የሚጠይቅባቸውን መሥዋዕትነት ማስላት አለባቸው፤ ሆኖም ራስን ለይሖዋ አምላክ ወስኖ ከእርሱ ጋር ዝምድና መፍጠር ከፍተኛ በረከት እንደሚያስገኝ መጠበቅ ይችላሉ። (ከሉቃስ 9:23፤ 14:25-33 ጋር አወዳድር።) የይሖዋ ምሥክሮች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እንደነዚህ ያሉትን አዳዲስ ሰዎች አምላክ ፈቃዱን ለመፈጸም እየተጠቀመበት ወዳለው ድርጅት እየመሯቸው ነው። (ማቴዎስ 24:45-47) እነዚህ ሰዎች አምላክ የሚፈልግባቸውን ሲያውቁና ሲፈጽሙ እንደ ኢትዮጵያዊው ይደሰታሉ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ህንደኬ” ስም ሳይሆን በኢትዮጵያ ለሚነግሡ ንግሥቶች የሚሰጥ ማዕረግ (እንደ “ፈርዖን” እና “ቄሣር”) ነው።
b ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ የሚባሉት በሙሴ ሕግ ለመመራት የሚፈልጉ እስራኤላዊ ያልሆኑ ሰዎች ናቸው።—ዘሌዋውያን 24:22
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ጃንደረባ የተባለው ለምንድን ነው?
ሥራ ምዕራፍ 8 ላይ በሚገኘው ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያዊው ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ “ጃንደረባ” ተብሏል። ነገር ግን የሙሴ ሕግ አንድ ብልቱ የተቀጠቀጠ ሰው ወደ ጉባኤ እንዲገባ ስለማይፈቅድ ይህ ሰው ቃል በቃል ጃንደረባ አልነበረም። (ዘዳግም 23:1) “ጃንደረባ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ከፍተኛ ሥልጣን ያለውን ሰው ሊያመለክት ይችላል። ስለዚህ ኢትዮጵያዊው ሰው የኢትዮጵያ ንግሥት ባለ ሥልጣን ነበር።